Monday, 25 November 2013 11:14

“...ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት እትም ለንባብ ያልነው ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው የሚሰጠውን የህግ፣ የማህበራዊና ስነልቡና እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ አንድ ወጥ በሆነ አወቃቀር እና መመሪያ እንዲሰጥ የሚያስችል መመሪያ ረቂቅ ላይ ውይይት መደረጉን ለንባብ ማለታችን ይታወሳል፡፡ በዚህም ስብሰባ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሰረት ጾታዊ ጥቃት GBV (gender based violence). ሲባል የቤት ውስጥ ድብደባን ስድብን እና የመሳሰሉትን ብዙ አይነት ድርጊቶችን የሚያካትት ሲሆን  ይህ መመሪያ የሚመለከተው ግን በወሲብ ምክንያት ጥቃት የሚደርስባቸውን ብቻ በመሆኑ ወደ ወሲባዊ ጥቃት SV (Sexual violence) የደረሰባቸው በሚል እንዲለወጥ ሆኖአል፡፡
ይህንን ረቂቅ ያሰናዱት በኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የበላይነት የፌደራል ፖሊስ፣ የሴቶች ወጣቶችና ሕጻናት ጉዳይ ሚኒስ..ር፣ የሳይኮሶሻል ድግፍ ሰጪዎችና የሕግ ተቋሙ ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በጋራ ሆነው ነው፡፡ በዚህ ረቂቅ መመሪያ ላይ የወጣ ውን የተለያየ የስራ ድርሻ ሁሉም እንደየተቋማቸው አግባብ አገልግሎት መስጫውን በአንድ ቦታ በመመስረት ለተጠቃሚዎች ምቹ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ አጠቃላይ መመሪያ ተብሎ ለሁሉም አገልግሎት ሰጪ አካላት የተቀመጠው ነጥብ የሚገልጸውም፡-
በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ፣በአገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን  መሰረት ማድረግ፣
የህጻናትን በተለይም የሴት ልጆችን ማንኛውንም ደህንነት በማስጠበቅ፣
የህብረተሰቡን አቅም ለማጎልበት እና ለሚፈጠሩ ችግሮች ያገባኛል ባይነትን ለመፍጠር የሚያስችል የተቀናጀ አሰራር መፍጠር፣
ተቋማት በጋራ በትብብር እና በተማከለ አሰራር መረጃን መሰረት ያደረጉ፣ እውቀትና ችሎታን በሚያጋራና ተጠያቂነትን ሳይዘነጉ የየድርሻቸውን እንዲወጡ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል የሚል ስሜት የያዘ ነው፡፡  
ይህ ረቂቅ በህግ ፣በስነልቡናና በሕክምናው አገልግሎት ረገድ የያዛቸው መሰረተ ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡  
በህግ አገልግሎት፡-
የህግ ባለሙያዋ ማህሌት ገ/የሱስ እንደገለጹት.....አንዲት ሴት ወይንም ወንድ ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ወደአገልግሎት መስጫው ደርሰው እስኪመለሱ ያለውን ሁኔታ መመሪያው ይገልጻል፡፡ ጉዳቱ የደረሰባት ሴት ከቤተሰብ ጀምሮ በአካባቢዋ ለሚገኝ ሰው ሁሉ ችግሩዋን ልትገልጽ የምትችል ሲሆን ለእርዳታ የምትሄድባቸው ቦታዎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ የመጀመሪያው ሁሉም አይነት አገልግሎቶች በተቀናጀ መልኩ በአንድ ቦታ የሚሰጠበት ሲሆን ሌላው ደግሞ በዚህ መልክ ባልተደራጀበት በተናጠል በሚሰራበት ቦታ ይሆናል፡፡ ጉዳቱ የደረሰባት ልጅ አገልግሎቱ በአንድ ቦታ ወደሚሰጥበት ተቋም ከደረሰች የህግ ተወካዩ ወይንም ፖሊስ በሚያነጋግራት ጊዜ ምናልባት የተረጋጋ መንፈስ ከሌላት በዚያው ወደሚገኘው የስነልቡና አገልግሎት ሰጪ ለሆነው ባለሙያ ወይንም በቀጥታ ሕክምና ወደሚሰጣት ዶክተር ትላካለች፡፡ ነገር ግን በሕግ ባለሙያው ለሚቀር ብላት ጥያቄ እስዋ ትክክለኛውን አቅጣጫ የሚያመላክት ምላሽ ልትሰጥ የምትቸ ልበት ወይንም አብሮአት ያለው ሰው ሁኔታውን በግልጽ የሚያስረዳበት አግባብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ልጅቷ የመፍራትና ያለመረጋጋት ሁኔታ ከታየባት ወደማበህራዊ ሰራተኛው ትላካ ለች፡፡ በሕግ በኩል ለተጎጂዎች የሚቀርቡት ጥያቄዎች ጊዜን የማይፈጁ አጫጭር እንዲ ሆኑና ተጠያቂዎችን የማያስጨንቅ እና የማያስቆጣ መሆን እንዳለበት መመሪያው ይጠቅ ሳል፡፡ የህግ ተወካዮች ተጎጂዎችን በሚያነጋግሩዋቸው ጊዜም ግልጽና አጠር አጠር ያሉ ጥያቄዎ ችን ማቅረብ ፣በተቻለ መጠን ተጠያቂዎቹን የሚያስፈራ ነገር በአቅራቢያ እንዳይ ኖርና ማድረግ፣ ለብቻቸው ቢሆኑም እንደሚመረጥ ረቂቅ ሰነዱ ይገልጻል።  በተለይም ጉዳት የደረሰባት ልጅ ሕጻን ከሆነች ከጠያቂው ማግባባትን ማጫወትን የመሳሰሉትን የማነጋገር ዘዴዎች በንግግር ወይንም በአን እንቅስቃሴ፣ በምልክት በማሳየት ቢሆን የተሻለ መልስ ለማግኘት እንደሚረዳ ይጠቁማል፡፡  
በጤናው ረገድ...
በጤናው ዘርፍ ሊኖር ስለሚገባው አሰራር ማብራሪያውን የሰጡት ዶ/ር መንግስቱ ኃ/ማርያም የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ፡-
.....አንዲት ሴት የወሲብ ጥቃት ደርሶባት ወደመንግስትም ይሁን ወደግል ህክምና ተቋም ስትመጣ ተቋማቱ ሊከተሉት የሚገባ አሰራር መኖር አለበት፡፡ የህክምና ተቋማቱ የማህጸ ንና ጽንስ እንዲ ሁም ጠቅላላ ሐኪም ሊኖራቸው ይገባል፡፡የጤና መኮንን፣ አዋላጅ ነርስ ወይንም ልዩ ስልጠና የወሰዱ የህክምና ባለሙ ያዎች ሊኖሩዋቸው ይገባል፡፡ የወሲብ ጥቃት የደረሰበት ወንድ ከሆነ እና ወደህክምና ተቋሙ ለሕክምና ከመጣ የጽንስና ማህጸን ሐኪሙ ከሌላ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ጋር ሕምናውን ሊሰጥ እንደሚችል መመሪያው ያካትታል፡፡ ይህ የሚሆንበት ምክንያትም የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች የማያዩዋቸው ... ነገር ግን ስልጠናውም ሙያውም ያላቸው ሌሎች ሐኪሞች ተገቢውን እርዳታ እንዲሰጡ ሲባል     ነው፡፡ በተጨማሪም የወሲብ ጥቃቱ የደረሰው በህጻናት ላይ ከሆነ የህጻናት ሐኪ ሞች ሊያዩዋቸው እንደሚገባ እና በተለይም ሕጻናቱ ሴቶች ከሆኑ የጽንስና ማህጸን ሐኪ ሞች አብረው እንዲያዩዋቸው መመሪያው ይገልጻል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተጎጂዎቹ የአእምሮ ችግር የገጠማቸው ከሆኑም በዚህ ዘርፍ አስፈላጊውን እውቀት የያዙ ባለሙ ያዎች ቀርበው ስራቸውን በጋራ እንዲያከናውኑ ያስፈልጋል። ይህ የህክምና አገልግሎት ከአሁን ቀደም በሆስፒታሎች ብቻ የሚሰጥ ሲሆን አሁን ግን ህብረተሰቡ ዘንድ ካሉ የጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኞች ከሚሰሩበት ጤና ኬላዎች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው የህክምና ተቋም ድረስ እንዲሰጥ ይጠበቃል ፡፡ ሁሉም የጤና መዋቅሮች አገልግሎቱን የሚሰጡትም እንደየደረጃቸው በተቀመጠላቸው የስራ ድርሻ ይሆናል፡፡
በሕክምናው ዘርፍ የወሲባዊ ጥቃትን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡
ዶ/ር መንግስቱ ኃ/ማርያም አክለው እንደገለጹትም የጤናው ዘርፍ ወሲባዊ ጥቃትን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ አሰራሮች አሉት፡፡ በተለይም ከቅርብ አመታት ወዲህ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከህብረተሰቡ ጋር በጤና ኤክስ..ንሽን ሰራተኞች እና የጤና ልማት ሰራዊቱ አማካኝነት ያላቸው ቅርርብ እየጨመረ ስለሆነ ህብረተሰቡን በጉዳዩ ላይ አስቀድሞ ማስተማር የሚቻልበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ይሆናል፡፡ የጤና ኤክስ.. ንሽን ፕሮግራሙ 16/አይነት አገልግሎት ያለው ሲሆን ከዚህም ሁለቱ በቀጥታ ከጾታዊ ጥቃት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ስለዚህም የጤና ትምህርት በሚለው ፕሮግራም በአብዛኛው በሴቶች ጤና ላይ የተመረኮዙ ጥሩ ነገሮችን ለህብረተሰቡ ማስተ ማርን የሚያካትት ስለሆነ ወንዶች ስለሴቶች ጤንነት እንዲያስቡ ያበረታታል፡፡ ይህንን ፕሮራም በመጠቀም ህብረተሰቡን ትምህርት በሚያስተምሩበት ጊዜ ወንዶች የተሳሳተ አስተሳሰብ ይዘው ሴቶችን በወሲብም ይሁን በማንኛውም መንገድ ጥቃት እንዳያደርሱ በማስተማር ወሲባዊ ጥቃትን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡
Psychosocial support:-  የማህበራዊና ስነልቡናዊ ድጋፍ፡-
የማህበራዊና ስነልቡናዊ ባለሙያው አቶ መኰንን በለጠ ሊደረግ የሚችለውን ድጋፍን በተመለከተ በረቂቁ መመሪያ ላይ ከሰፈረው መካከል የሚከተሉትን ገልጸዋል።
..... ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ወይንም ወንዶች ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ ሊሰጣቸው የሚገባው የማህበራዊና ስነልቡናዊ  ድጋፍ በሶስት ይከፈላል፡፡
በጥቃቱ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ሴቶች ወይንም ወንዶች የሚገባቸውን የስነልቡና ድጋፍ መስጠት፣
አገልግሎቱ በአንድ ተቋም በተማከለ መንገድ ወይንም በተለያየ ቦታ የሚሰጥ ከሆነ ቦታውን  ለተጠቃሚዎች ማመላከት፣
የስሜት ጉዳት የደረሰባቸው ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ ናቸው፡፡  
አቶ መኮንን እንደገለጹት ...የዚህ መመሪያ መግቢያ እንደሚያመላክተው ማንኛውም ይህንን አገልግሎት የሚሰጥ ባለሙያ ርህራሄና ፍቅር በተሞላበት መልኩ ጉዳቱ ካደረሰባቸው የስነልቡና ቀውስ እንዲያገግሙ አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ ማድረግ ይገባል፡፡ ከዚህም ጉዳት አንዱ የስሜት ጉዳት ሲሆን ይህ ችግር የደረሰባቸው ሰዎች ከሚደርስባቸው የስሜት ጉዳት አገግመው  በተቻለ መጠን ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ማድረግ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት ቤተሰብንም በማካተት ቀጣይነት ባለው መንገድ የምክር አገልግሎት መስጠትን ይጨምራል። ከዚህም በተጨማሪ ከአሁን ቀደም ችግሩ ደርሶባቸው ነገር ግን ባገኙት አገልግሎት ሳቢያ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ሰዎችን በምክር አገልግሎቱ ወቅት መጠቀም ብዙ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ደሴ እንግዳየሁ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እንደገለጹት ይህ ረቂቅ መመሪያ ተሰርቶ እንዳለቀ በብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚ..ው የበላይ አካላት ተፈርሞ እስከ ዲሴምበር /ድረስ በአዲስ አበባና በመላው የአገሪቱ መስተ ዳድር አካላት ለሚያስፈልገበት ቦታ ሁሉ እንዲሰራጩ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ እንደመመሪያ ሁሉም ሴክተሮች ተግባብተው በአንድነት የሚሰሩበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡     

Read 1532 times