Print this page
Monday, 25 November 2013 11:32

መልስ አልባ ጥያቄ መልስ እንዳለው ያውቃል

Written by 
Rate this item
(10 votes)

መልስ አልባ ጥያቄ መልስ እንዳለው ያውቃል
ምልእቲ ኪሮስ
ምስልሽን ለመሳል መች አልወጠርኩ ሸራ
ዓይንሽን ለማየት መች አጣኝ መከራ
የዓይንሽን ብሌን ቅንድብሽን አስታውሶ
የስዕልን ብሩሽ በፍቅር ቃል ለውሶ፤ ቀለም ማንጠባጠብ
በመውደድሽ ምትሀት በፍቅርሽ መተብተብ
ከዚያም ቀለም ማፍሰስ …….
ማፍሰስ … ማፍሰስ … ማፍሰስ …
በማፍቀር መ ኮ ፈ ስ!!
ከጠጉሮችሽ መሀል ገብቶ መንፈላሰስ
ድንገት ያምረኝና … ድንገት ያምረኝና
ከበድን ሸራዬ ጠጉር እስልና
ዕልመት እስልና
ከብርሀን ግንባርሽ፣ ከዕድሜ ቀጣይ ዓይንሽ፣ ድንገት እደርስና
ከጠጉርሽ ጥቁር ፅልማት ቀላቅዬ ብሌንሽን ቀባለሁ … ደሞ ፀልያለሁ
ጥቁርሽን ‘ሚያሳዬኝ ዓይኔን አጥፋ እላለሁ
ብሌንሽ ተቀባ ዳር ዳሩ ተኳለ
የእግዚሀር መልኩ ጠፋ
ከኔ ምስልሽ አለ ፊቴ ካለው ፊትሽ
ምስልሽ ሸራዬ ላይ ቡሩሼ ላይ ወዝሽ
ድምፅሽ ላይ ትዝታ … ድምጼ ላይ ስቅታ
ስቅታዬ ደስታሽ ሳጌ ደማቅ ሳቅሽ
ታዲያ እንዲ አይደል ስዕል?
ካንቺ እየተያዩ ቀለም መቀላቀል
ሰማያዊ ህብር ከቀዩ መቀየጥ
ከጥቁሩ ነክሮ ነጩ ላይ መገልበጥ
ከስዕል ሸራ ላይ ዓይንን ተክሎ ማደር
ኋላም መጮህ ማበድ በቀለማት መስከር
ማይታወቅ ቀለም እስኪመጣ ድረስ
አንዱን ካንዱ መድፋት እላዩ ላይ ማፍሰስ
በእጅ እያፈሱ ወደ ሰማይ መርጨት
ምስልሽን ሽቶ ከአምላክ መጋጨት
ጠያቂን መጠየቅ … ጥያቄን … ማስጨነቅ
የቆዳዋን አይነት ቀለም ደባልቄ
ይሄው ከትቤያለሁ ልቤ ውስጥ አርቅቄ
እንድትፈርድ እያት
የአንገቷን ጠረን በምን ልሳላት?
የማይተው ሆኖ ክፉ ዝቋን መግለጥ
እስኪ በል ንገረኝ ምን ከምን ልቀይጥ?
ከሸራዬ ሸራ የሷን ድምፅ መስማት
ምን ይሉት መቀደስ እንዴት ያለ ምትሀት
የዕድሜ ልክ እርግማን ሴት የመሳል ምክንያት!!!
መልስ አልባ ጥያቄ
ሀዘንተኛ ሳቄ
ያውም በኮሳሳ በደሳሳ ጎጆ
ከየዋህ አፍቃሪ ብርታቱን ኮርጆ
ሽንቁሩ በበዛ በተሰበረ በር
ከነብሴ ሚነጣ ውብ ሸራ መወጠር
ከደሜ ቀይ ቀለም ከላቤ ወዝ መንከር
ከድሜ እየቀነሱ እሷ ላይ መከመር
በነገረ ነብሷ ጠልቆ መመራመር
በቃል ኪዳን አስሮ ቀለማት ማጋባት
እ…ሰይ…!! ብዙ ብሎ ንግስናን መቀባት
ከዚያ … …
ከቆሙበት ብሩሾችን ማንሳት
እልባት እስኪገኝ ላመታት መረሳት
ከሸራው ምስልሽን ከምስልሽ ላይ አንቺን እያነቡ … መቅደድ
ወደ ማይታወቅ ወደ ሩቅ መስደድ
ቀለማት አርግዘው ቀለም እስኪወለድ
ምስልሽን ሚተካ፣ ዓይን ሚሞላ ውበት፣ በጣት የሚነካ፣ ህብር ቅኔ እስኪገኝ
ምስልሽና ነብስሽ ከሸራ እስኪገናኝ
ውበትሽን ሸርፌ አላጓድልሽም
እስከጊዜው ድረስ ተይኝ አልስልሽም!!!
…….//……

Read 5201 times
Administrator

Latest from Administrator