Saturday, 30 November 2013 11:29

“የፍልሰት ጉዳይ መፍትሔ ካልተሰጠው የአፍሪካንና የአረቡን አለም ግንኙነት እስከማቋረጥ ሊደርስ ይችላል” - የኩዌት ፖለቲካ ተንታኝ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በመካከለኛው ምስራቅ በፐርሺያን ገልፍ ሰሜን ምእራብ ጫፍ የምትገኝ በረሀማ ነገርግን ስትራቴጂካዊ እና በነዳጅ ሀብት የበለፀገች አገር ናት። ለዜጎቿም ሆነ ለሌሎች አገሮች ዜጎች በነፃ ህክምና ትሰጣለች፡፡ የአገሪቱ ዜጎች ከመንግስታቸው ሌሎች የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ያገኛሉ፡፡ የኩዌት ዲናር አቅም ካላቸው ገንዘቦች በቀዳሚነት የሚመደብ ሲሆን አንዱ ዲናር ሶስት ብር ከሀምሳ የአሜሪካን ዶላር ይመነዘራል፡፡ ኩዌት በህገመንግስታዊ የንጉስ ስርአት የምትመራ አገር ናት፡፡
ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀችው ሶስተኛው የአፍሪካ አረብ ጉባኤ 34 የአገር መሪዎችን፤ 7 ምክትል ፕሬዚደንቶች፣ 71 አገሮች እና ድርጅቶች ተሳትፈዋል። የጉባኤው ዋና አጀንዳ በአፍሪካ እና በአረብ መካካል ያለውን ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ማጠናከር ነበር። ጉባኤውን በንግግር የከፈቱት የኩዌት አሚር ሼክ ሰባህ አሀመድ አል ሰባህ የሁለቱ አካባቢ ህዝቦች ቆየት ያለ ታሪካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እንዳላቸው በመግለፅ በዝቅተኛ የወለድ መጠን የሚከፈል  በአፍሪካ አህጉር ለተለያዩ ኢንቨስትመንት የሚውል አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በቀጣዩ አምስት አመት እንደሚሰጥና ለተለያዩ የምርምር ስራዎች የሚውል  አንድ ሚሊዮን ዶላር ከኩዌት ለአፍሪካ እንደሚለግስ ቃል ገብተዋል፡፡ በሁለቱም አካባቢ ህዝቦች የምግብ ዋስትና  እና የፀጥታ እና የደህንነት ጉዳዮች  ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች  ሊሆነ እንደሚገባ በአፅንኦት የተናገሩት አሚሩ፣ ነገር ግን አንዱ ወገን እርዳታ እየሰጠ ሌላው ወገን ምንም አስተዋፅኦ የማያደርግበት አካሄድ መስተካከል እንዳለበት በንግግራቸው አስምረውበታል፡፡ የጉባኤው ትኩረት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ቢሆንም አሚሩ የሶሪያን ጉዳይ በተመለከተ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበው እስራኤል የምትወስዳቸው እርምጃዎች እንደሚያሳስቧቸው ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛው አፍሮ አረብ ጉባኤ በሊቢያዋ ስርት ከሶስት አመት በፊት ሲካሄድ ከ2001 እስከ 2016 ይተገበራሉ የተባሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው የነበረ ቢሆንም ቱኒዚያን፣ ሊቢያን፣ ግብፅን እና የመንን ያናወጠው ህዝባዊ አመፅ እና የመሪዎች ከስልጣን መውረድ  እንዲሁም እስከ አሁን የቀጠለው የሶሪያ ቀውስ ፕሮጀክቶቹ ብዙም እንዳይራመዱ ቀስፈው የያዙ ምክንያች ናቸው፡፡
ጉባኤውን በሊቀመንበርነት የመሩት የኢትዮጲያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ለቀመንበር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፣ የስደተሦች ጉዳይ የጉባኤው አጀንዳ መሆኑ ተገቢ እና ወቅታዊ እንደሆነ በመግለፅ ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ  መፍትሄ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው አስቀምጠዋል፡፡ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ካለ ችግሩን መፍታት ይቻላል ያሉት አቶ ሀይለማርያም ጉዳዩ እንደ ከዚህ ቀደም ዝም ብሎ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡ የጉባኤውን ዋና አጀንዳ አስመልክቶም በአረብ በኩል ያለው አቅም እና በአፍሪካ በኩል ያሉ የተለያዩ  እምቅ ሀብቶች ሁለቱን አካባቢዎች እንደሚያስተሳስሯቸው ተናግረዋል። ከመሪዎቹ ስብሰባ ቀደም ብሎ በተካሄደው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ የስደተኞችን በሚመለከት ይቋቋማል የተባለው የአፍሮ አረብ የተቀናጀ ኮሚቴ ጥሩ ውጤት ያመጣል በለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
ከጉባኤው ጎን ለጎንም ከሰላሳ በላይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ከግጭቶች እና ከኢንቨስትመንት ጋር የተያያዙ አጀንዳዎች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ።  የኢትዮጲያ እና የግብፅ መሪዎች መሀመድ ሙርሲ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ተገናኝተው  ኢትዮጲያ  እየገነባች ስላለው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተወያይተዋል፡፡ የግድቡን ግንባታ አስመልክቶ በግብፅ በኩል የቀረበው ግንባታው ላይ የመሳተፍ ጥያቄ በኢትዮጲያ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ ሲሆን ግድቡን አስመልክቶ በያዝነው ወር ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ካርቱም ላይ ተገናኝተው ውይይት ያደረጉ ሲሆን ቀጣዩ ስብሰባም  በታህሳስ ወር ካርቱም ይደረጋል፡፡
ጉባኤው ባወጣው የአቋም መግለጫ በአፍሪካ እና በአረብ አገሮች መንግስታት እና ህዝቦች መሀል የቀረበ ትስስር መፍጠር፣ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአረ ሊግ የአፍሮ አረብ የድርጊት መርሀ ግብሮች እና ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ የሚያግዝ ግብረ ሀይል እንዲያቋቁሙ፣ የአፍሪካ እና የአረብ አገሮ የገንዘብ ተቋሞች የግሉን ዘርፍ እና  የሲቪል ማህበራትን በማጠናከር የሁለቱን አካባቢዎች የንግድ ትስስር እንዲያፋጥኑ ማስቻል፣ የአፍሪካ እና የአረብ የንግድ ምክር ቤቶች እና የኢንዱስትሪው ዘርፍ እነዲሁም ሌሎች የግል ተቋሞች ተከታታይ የሆነ የምክክር መድረኮችን በመፍጠር የሁለቱን አካባቢዎች ትስስር ለማፋጠን እገዘ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በሁለቱም አካባቢዎች ያሉ መንግስታት፣ የግሉ ዘርፍ እና የሲቪል ማህበራት የግብርናውን ዘርፍ እንዲያሳድጉ ማበረታታት፣ የገጠርልማት፣ የግብርና እና የምግብ ዋስትና ላይ የሚሰሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአረብ ሊግ ይህ የአቋም መግለጫውም ሆነ የአፍሮ አረብ የአጋርነት ስትራቴጂ ተግባራዊ እንዲሆኑ በገንዘብም ሆነ በቴክኒክ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል። ፍልሰትን በተመለከተም የተቋቋመው የአፍሮ አረብ የቴክኒክ እና የቅንጅት ኮሚቴንም ሆነ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ስትራቴጂዎች ሁለቱ አካባቢዎች በቅንጅት እንዲሰሩ፣ ለፈለሱ ሰዎች የደህንነትና ማህበራዊ ጥበቃ ማድረግ፣ ስደተኞችን፣ ተፈናቃዮቸችን  እንዲሁም የፈለሱ ሰዎችን ለሚቀበሉ አገሮች በተለይም ለቡርኪናፋሶ እና የመን እገዛ ማድረግ እንደሚገባና ህገወጥ ፈላሾችን ለመለየት የአፍሮ አረብ የመረጃ ልውውጥ ማእከል እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን መግለጫው ያሳያል፡፡
የባህር ላይ ውንብድና እና የካሳ ጥያቄ፣ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዝ እፅ ዝውውር  እና የህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ላይ በጋራ ለመሥራትም ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
አንድ የኩዌት ከፍተኛ ባለስልጣን የፍልሰት ጉዳይ አሳሳቢ ችግር ነው ያሉ ሲሆን በጉባኤው ላይ ያነጋገርኳቸው ተንታኝም፣ የፍልሰት ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት ካልተሰራበት እና መፍትሄ ካልተሰጠው የአፍሪካን እና የአረቡን አለም ግንኙነት እስከማቋረጥ ሊደርስ እንደሚችል አስቀምጠዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት ከአምስትመቶ ሺህ በላይ አፍሪካውያን ወደ አረብ አገሮች ፈልሰዋል።
ሁለቱ አካባቢዎች በፀጥታ እና አሸባሪነትን በጋራ ለመከላከል ለዚህመም መረጃ ለመለዋወጥ  የተስማሙ ሲሆን በሁለቱ አካባቢዎች ለሚገኙ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ለዜጎች አመቺ ሁኔታን በሚፈጥሩና ለደህንነታቸው ትኩረት በሰጠ መልኩ እልባት እንዲያገኝ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡  
የኩዌቱ አሚር ሼክ ሰባህ በጉባኤው መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር ከፊታችን ረጅም እና አስቸጋሪ መንገድ ይጠብቀናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት በሁለቱም አካባቢዎች ያለው ያለመረጋጋት ነው። ስለዚህ ያቀድናቸውን ለማሳካት ብዙ ጥረት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ርካሽ የሰው ጉልበት፣ ለእርሻ የሚውል ሰፊ የሚታረስ መሬት፣ አፋጣኝ የመሰረተ ልማት ፍላጎት  ይገኛል፡፡ ይህን እድል ሁለቱም አካባቢዎች ሚዛኑን በጠበቀ የዜጎቻቸውን ፍላጎት በተከተለ መንገድ እንዴት ሊወጡት ይችላሉ የሚለው ጥያቄ ምላሽ ለግንኙነቱ ምላሽ ይሰጣል ያሉት የጉባኤው ተሳታፊ፣ በተለይ በአፍሪካ በኩል ጥንቃቄ የተሞላበት እርምጃ ግድ ይላል ይላሉ፡፡
ቀጣዩ የአፍሮ አረብ ጉባኤ በአፍሪካ እንዲዘጋጅ የተወሰነ ሲሆን ሰባተኛውን የአፍሮ አረብ ንግድ ትርኢትም  ሞሮኮ በቀጣዩ አመት እንድታስተናግድ ተወስኗል፡፡

Read 4801 times