Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:07

“የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በጉልበት ሳይሆን በድርድር ነው”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከደበበ እሸቱ ጋር የእግዚአብሔር ሰላምታ እንኳን የለንም …
የአገሪቱ ችግሮች ኢህአዴግ ከሚሸከመው በላይ ናቸው
የድሃው ኑሮ “ቁምራ” ሆኗል - “ቁርስ፣ ምሳና እራት አንዴ መብላት”
በሽብር ወንጀል ተጠርጥርው ከተከሰሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች ጋር በተገናኘ በኢቴቪ የቀረበውን ፕሮግራም መመልከታቸውን የገለፁልን ዶ/ር መራራ ጉዲና፤ አሁን ስላለው የአገሪቱ የፖለቲካ ችግርና መፍትሄው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ሰሞኑን በሽብር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በተመለከተ በኢቴቪ ስለቀረበው ፕሮግራም ምን ይላሉ?

ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን ማየት እፈልጋለሁ፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ሃያ አመታት የአገሪቱ ጉዳዩ ያገባናል ከሚሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር አልደራደርም፤ በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን አልፈታም የሚል አቋሙን ይዞ በመግፋቱ የተለያዩ የፖለቲካ ሀይሎች ከህጋዊ መድረክ ተገፍተው እየወጡ ሌላ ስልት እንከተላለን የሚሉበት ሁኔታ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ለእነሱም ለመንግስትም ለአገርም አይጠቅምም፡፡ ለኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ያንን አቅጣጫ ለሚከተሉ የፖለቲካ ሀይሎች የምመክረው፤ የሀገሪቱን ጉዳዮች በውይይት እንዲፈቱና ችግሮች እንዲቃለሉ ነው፡፡  
የኢትዮጵያ መንግስት ሁልጊዜ በር እየዘጋና ከህጋዊ የትግል ሜዳ ገፍትሮ እያስወጣ ችግር ሲደርስበት መጮኹ አያዋጣውም፡፡ በብዙ ሀገሮች ችግሮች የተፈቱት በመነጋገር እንጂ በጉልበት አይደለም፡፡ እንግሊዞች የሰሜን አየር ላንድን ችግር የፈቱት ከብዙ አመታት መነጋገርና መደራደር በኋላ ነው፡፡ እስራኤሎችም ከፓኪስታን ጋር እንደራደራለን እንነጋገራለን እያሉ ነው፡፡ ፓኪስታንም እንዲሁ፡፡ አፍጋኒስታን እንኳን ታሊባንን ከሚወክሉ ጋር እንድትደራደር አሜሪካ ግፊት እያደረገች ነው፡፡ በ21ኛው ክ/ዘመን ችግሮች በጠመንጃ ሳይሆን በመነጋገር ነው የሚፈቱት፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ቢያስብበት ይመረጣል፡፡ መንግስት በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ህጋዊ የፖለቲካ ሀይሎችን ጨምሮ ጠላቴ የሚላቸውን ሁሉ “ሽብርተኞች” በሚል ከኤርትራና ከአልሸባብ ጋር ማገናኘቱ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ ዋናው ጉዳይ በኢትዮጵያ ያሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ሁሉ በሰላምና በድርድር እስካልተፈቱ ድረስ ችግሮቻችን መፈታት አይችሉም፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ግን በሁሉም ላይ ጦርነት እያወጁና እየከሰሱ፣ ንፁሀን ዜጐቹን ጭምር ያላሰቡትን እያሳሰቡ ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ግን መደራደር ይመረጣል፡፡ መድረክ ብዙ ጊዜ የድርድር ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ኳሷ ያለችው የኢትዮጵያ መንግስት ሜዳ ላይ ነው፡፡ በኢቴቪ የምናየው ቴያትር ምናልባትም ለአንዳንድ ሰዎች ሌላ መልዕክት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይሄን ሁሉ ወንጀል ሰርተናል በሚሉ ወገኖች በተቀነባበረ ቴያትር፣ ንፁሃን ዜጐችን መክሰስ አያዋጣም፡፡ ግን ቲያትሩን በኢቴቪ ካሳዩን በኋላ ሰራን ላሉት ወንጀል ሲቀጡ አናይም፡፡ ተፈተው ይዝናናሉ፡፡ ወንጀል የሠራ ሰው ግን ለሰራው ወንጀል በተገቢው መንገድ መቀጣት አለበት፡፡
እንደዚህ አይነት ሰዎች ንፁሀን በምንላቸው ላይ እየመሰከሩ፣ ከመንግስት ደህንነቶች ጋር ተስማምተው ቲያትር የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠር ብዙ አይጠቅምም፤ ምክንያቱም እኛ የታሠሩ አባሎቻችንን እናውቃቸዋለን፡፡ ምስክሮች እንዴት እንደሚቀርቡና እንደሚመሰክሩ እናውቃለን፡፡ እንዴት እንደሚቀናጁም እናውቃለን፡፡ ይሄ ጨዋታ ቢለወጥ ይሻላል፡፡ ምክንያቱ ቲያትሩ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ቲያትሩ አገሪቷን እያረጋጋ ነው? ወይስ እውነታው ምንድነው? እነዚህ ሰዎች የሚናገሩት እውነት ነው ወይስ ዜጐችንና በመንግስት ኢላማ ስር ያሉ የፖለቲካ ሰዎችን ለማዳከም ነው? ይሄንን ደጋግመው ቢያስቡበት ይሻላል፡፡ ሁላችንም የኢትዮጵያ ዜግነት ያለን ነን፡፡ ሁላችንንም በእኩልነት ሊያስተናግድ የሚችል አገር መፍጠር ነው የሚያዋጣው፡፡ ይሄ እስከሚመጣ ድረስ ህጋዊና ሰላማዊ ትግላችን ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣውን ህገመንግስትን ማክበር አለበት፡፡ ካድሬዎችም ሆኑ የመንግስት መሪዎቹ ህጉን የማክበር እና በሀቅ የመስራት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ ዜጐችን ወንጀለኛ ለማድረግ፤ ዜጐችን ጠልፎ ለመጣል፤ ከሠላማዊ የትግል ሜዳ ለማባረር ሳይሆን ኢህአዴግ በሀቅ የአገሪቱ ችግሮች እንዲፈቱ፤ ሠላማዊ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ፤ ሰው ተረጋግቶ ወደ ልማት እንዲመለስ ቢጥር ይሻላል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ከታሰሩት መካከል የተፈቱ አሉ…
አሸባሪ የሚባሉት እና አድርገናል የሚሉ ሰዎች እንደቀላል ነገር ፈርመው እየወጡ ነው፡፡ ወንጀል ሠርተናል እያሉ የሚለቀቁበትን ሁኔታ ነው ያየነው፡፡ ስለዚህ ሰው ለኢህአዴግ ምስክር ለመሆን እስከፈለገና እስከተመለመለ ድረስ ምንም አይነት ከባድ ወንጀልም ቢሠራ ከተማ ላይ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ ባለስልጣናትን ለመግደል የተሠማሩ፣ በእጃቸው ክላሽ ያለና ሶስት መቶ ቦምብ የተገኘባቸው የተባሉት ሲንሸራሸሩ ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ አሳማኝ ነገር አይፈጥርም፡፡ መንግስትና ህዝብንም የሚያስማማ አይደለም፡፡ ሀቀኛ ተቃዋሚዎች ከመንግስት ጋር ተደራድረው የሚሠሩበት ሁኔታ ሳይሆን ኢህአዴግ የሚጠላቸውን የፖለቲካ ሀይሎች ከትግል ሜዳ ለማስወጣት የሚደረግ ትግል ነው የሚመስለው፡፡
በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩት ውስጥ ጥቂቶቹ የተፈቱት ጥፋታቸውን ስላመኑ ነው ብለው ያስባሉ?
እነሱ ይላሉ፡፡ እያየን ያለነው እኮ ከባድ ወንጀል ሠርቻለሁ እያለ፣ አንድ ወር እና አራት ወር ታስሮ በንፁህ ዜጐች ላይ ጣት እየቀሰረ ያለበትን ሁኔታ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ነገሩን የሚጠራጠሩትም ለዚህ ነው፡፡ እውነት ነው ወይስ ቲያትር እየተሠራ ነው የሚል ጥያቄ ፈጥሯል፡፡ እኛም ጋ የገጠመንም ይሄ ነው፡፡ አንዷ ልጅ ዘጠኝ ሰዎች ላይ ለመመስከር መጥታ ጫካ አብረን ነበርን ብላለች፡፡ መልኩን ለይ ስትባል ደግሞ አሁን ወፍረዋል በማለት መለየት አቅቷታል፡፡
አብራ ጫካ የገባችውን ሰው መለየት ካቃታት ከባድ ነው፡፡ የእኛን ሰዎች እኮ እንዲህ ካላላችሁ እንዲህ ትደረጋላችሁ እያሉ ያስፈራሯቸዋል፡፡ ስለዚህ ሃያ አመት ከምታሰር በሚል በሁለትና ሶስት ሰዎች ላይ ደፍድፈን እንወጣለን ብለው ይመሰክራሉ፡፡ በምስክርነታቸው አፍረው ከአገር ሁሉ የጠፉ ምስክር አሉ፡፡ ድሮ በማውቀው የኢትዮጵያ ህግ አንድ ሰው የራሱን ወንጀል ወደ ሌላ ማስተላለፍ አይችልም፡፡ አሁን ግን ራሳቸው ሠራን የሚሉትን ወንጀል ለሌሎች እያስተላለፉ ነው፡፡ ይሄንን ለመስራት ስንል አብረን ነበርን ብለው ለሌላ አስተላልፈው እራሳቸውን ነፃ ያደርጋሉ፡፡ ፍ/ቤት ሊመሠክር የተቀመጠ ሰው ፀብም ዝምድናም የለኝም ብሎ ነው የሚመሰክረው፡፡ እኛ ላይ ግን የከዱን ሰዎች ሲመሰክሩ አይተናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ስለእኛ ጥሩ ሊመሰክሩ አይችሉም፡፡ በ1997 ዓ.ም ከእኛ የወጡ ግለሰቦች አሁን በተከሰሱት የእኛ አባላት ላይ ሲመሰክሩ ታዝበናል፡፡ አንዱ የእኛ አባል የተከሰሰው በ97 ምርጫ ጊዜ አስረብሸሃል በሚል ነበር፡፡ ይሄንን ለማጣራት ከኢህአዴግም ኮሚቴ ተመርጦ ተመርምሮ ነበር፡፡ ውጤቱን ደጋግመን ብንጠይቅም ኢህአዴግ ሊያሳየን ፍቃደኛ አልሆነም፡፡ አባላችን ግን አሁን በዛው ጉዳይ ተመልሶ ተከሰሰ፡፡ በዛን ወቅት ከኢህአዴግ ኮሚቴ ጋር አብሮ ሲሰራ የነበረ ነው ድርጊቱን ፈጽመሀል የተባለው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ኢህአዴግ በገለፍተኝነት ነው ጥቃቱን ያደረሰብን ብለው መስክረው ነበር፡፡ አሁን ከስድስት አመት በኋላ ግን አዋጁን ጠብቀው ከሰሱት፡፡
ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት አስተያየት መስጠት እና በእርግጠኝነት መናገር የፍርድ ሂደቱ ላይ ጫና አይፈጥርም?
መሠረታዊ የህግ ስርአት ነው የተጣሰው፡፡ አንድ አስፈፃሚ አካል እራሱ በከሰሳቸው ላይ “ወንጀለኞች ናቸው፤ እንዲህ አድርገዋል” ብሎ ካለ ሌላ ምን ያስፈልጋል? እራሱ ጨርሷል ማለት እኮ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው ጥፋተኛ ብሎ የማይፈርድ ዳኛ ከየት ይመጣል፡፡ በተለይ ዳኞች ህግ አስፈፃሚዎችን በጣም በሚፈሩበት አህጉርና አገራችን ውስጥ እንደዛ ማድረግ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ፍ/ቤት ጉዳዩን አጣርቶ እስኪፈርድ ድረስ መናገር ወንጀል ነው፡፡ ፍ/ቤት ወንጀለኛ ካላለው አንድ ሰው ተጠርጣሪ እንጂ ወንጀለኛ ወይም ጥፋተኛ ሊባል አይችልም፡፡ ከፍ/ቤት ውሳኔ በፊት ተጠርጣሪዎችን ወንጀለኛ የሚሉትን ወገኖች መክሰስም ይቻላል፡፡ በርካታ አመት ታስረው ነፃ የወጡ ሰዎች እንዳሉ እኮ እናውቃለን፡፡ አሁንም ከዩኒቨርስቲ ኢህአዴግ ለምን እንዳሰራቸው ሳይታወቅ ታስረው የተፈቱ ተማሪዎች አሉ፡፡
ከፖለቲካው ጋር ተያይዞ በዩኒቨርስቲ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ምንም የማውቀው ነገር የለም፡፡ መናገርም አልፈልግም፡አርቲስት ደበበ እሸቱ ስለ እርስዎና ሌሎች የፓርቲ አመራሮች ጠቅሶ የተናገረውን በቲቪ ተከታትለዋል?
ያለኝን ነገር በትክክል አልሰማሁም፡፡ ያመስግነኝ ይክሰሰኝ አላውቅም፤ ማወቅም አልፈልግም፡፡ ከእኔ ጋር በፖለቲካ አለም ተገናኝቶ አያውቅም፡፡ የእግዚአብሔር ሠላምታም የለኝም፡፡ ኢቴቪ ባስተላለፈው ርዕስ የሌለው ቲያትር ሰውዬው የራሱን የትወና ድርሻ ተወጥቷል፡፡
የአርቲስት ደበበ ንግግርን በኢቴቪ ማስተላለፉ አግባብ ነው ይላሉ?
እኛ እንግዲህ እናደርግልሀለን፤ አንተ ይሄንን ቲያትር ስራልን ብለውት ይሁን ወይም እስር ቤት ተጨንቆ ያንን ይለፍልፍ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ተጨንቆ ለመዳን ብሎ እንደለፈለፈ ግምት አለኝ፡፡ የለበሰው ልብስ ያንን ያሳያል፡፡ ከእስር ለመውጣት ራሱ ያደረገውን ወንጀል በሰው ላይ በመመስከር ሌላውን ለማሳየት ሲል ያደረገው እንጂ ከወህኒ ከወጣ በኋላ ቤቱ ተዝናንቶ የሰጠው አለመሆኑ ያስታውቃል፡፡ ምናልባትም በዚህ ነገርም ሊሆን ይችላል የተለቀቀው፡፡
የአገሪቱ ፖለቲካ ወዴት እየሄደ ነው ይላሉ?
ወዴት እንደሚወስዱን የሚያውቁት ኢህአዴግና አባሎቹ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሳይንሳዊ ትንተናም አስቸጋሪ የሆነ ከባቢ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አስቦና መርምሮ በዚህ አቅጣጫ ይሄዳል ለማለትና ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ አገሪቷ እስከ አንገቷ ድረስ ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ አንዳንዱ እየበለፀገ ቢሆንም፤ ቀላል የማይባል ህዝብ ወደ ድህነት ወለል እያሽቆለቆለ ነው፡፡ አሁንማ “ቁምራ” የሚባል ቃል ተፈጥሯል፡፡ ቁርስ ፣ምሳና እራት አንዴ መብላት መጀመሩን ለመጠቆም ነው፡፡ የደሀው ኑሮ ቁምራ ሆኖ ኢህአዴግ ግን ሁልጊዜ ማደጋችንንና መካከለኛ ገቢ ላይ መድረሳችንን እየተናገረ ነው፡፡ መቼም ፊደል የቆጠሩ ሰዎች መካከለኛ ገቢ አገሮች እዛ ደረጃ እንዴት እንደደረሱ ያውቃሉ፡፡ ቀንቶን ኡጋዴን ላይ ነዳጅ ካልተገኘልን በቀር በዚህ ሁኔታ ለቀጣይ ትውልድ እንኳን መድረስ አንችልም፡፡
ታዲያ ምን ይሻላል? መፍትሔው ምንድነው?
ከድርድር ውጪ ሌላ መፍትሄ አይታየኝም፡፡ ኢህአዴግ ብቻውን ይሄንን አገር ተሸክሞ የትም አይደርስም፡፡ የአገሪቱ ችግሮች ኢህአዴግ ከሚሸከመው በላይ ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንኳንስ ኢትዮጵያ ትቅርና ደህና የሚባሉ አገሮች ራሳቸው ችግር ላይ ወድቀዋል፡፡ ራሱ ኢህአዴግ እንደሚለው የአገሪቱ ችግሮች ተፈተው ኢትዮጵያን ምድረ ገነትም ይሁን መሀከለኛ ገነት ለማድረግ ከድርድር ውጪ ሌላ መፍትሄ የለም፡፡

 

Read 4764 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:11