Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:09

ታውቃለህ ቢሉት ባንድ እግሩ ዘመተ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሌባ ወደ አንድ ሰው ግቢ ይገባና ምን የመሰለ ሠንጋ-ፈረስ ይሰርቃል፡፡ በዚያን ሰሞን ያን ሠንጋ-ፈረስ እያጠበ፣ የክት ልብሱን እየለበሰ አደባባይ ብቅ ሲል ዐይን ይገባል፡፡ ሰው ሁሉ እንዴት አማረበት ይለዋል፡፡ እሱም በኩራት ካባ ደርቦ ቼ-በለው ሲል ይታያል፡፡
አንድ ቀን አንድ የታወቀና የተከበረ ጠጅ ቤት ይመጣና ሠንጋ-ፈረሱን ደጅ አሥሮ እየጠጣ ሳለ ለካ ሌባ ደጅ ያቆመውን ሠንጋ-ፈረስ ሰርቆታል፡፡ ሲመጣ ሠንጋ-ፈረሱ የለም፡፡
ከዚያን ቀን ጀምሮ በእግሩ ሲሄድ ይታያል፡፡ ይሄን ያየ አንድ ወዳጁ፤
“አቶ እከሌ እንዴት ነህ?”
“ደህና” ይላል
“ሰሞኑን በሠንጋ-ፈረስ ሆነህ መጭ ስትል፤ አለፈለት፣ ሀብት በሀብት ሆነ ስንል ነበር፡፡ ሥራ እንዴት ነው?”
“እንደምታውቀው የእኛ ሥራ ውጣ-ውረድ ይበዛዋል እንጂ መልካም ነው”


“እንዴት?”
“ላብህን ሳታንጠፈጥፍ በቀላሉ አታገኘውም ማለቴ ነው!”
“ያ ፈረስህ የት ሄደ ታዲያ? ሰሞኑን በእግርህ ነው የማይህ”
“ሸጥኩት”
“በምን ያህል ሸጥከው?”
“በዚያው ባመጣሁት ዋጋ!”
***
ከመስረቅ ይሰውረን፡፡
ባመጣንበት ዋጋ ከመሸጥም ይሰውረን፡፡
“ሌባን ሌባ ቢሰርቀው
ምን ይደንቀው” ነው ነገሩ፡፡
“ወትሮውንም ባልሰረቅሽ፣ ከሰረቅሽም ባላፈርሽ፡፡” ማለትም ያባት ነው፡፡ ከፍ ሲል ተቋማዊ ዘረፋ,ኧ ዝቅ ሲል ግለ-ሰባዊ ሌብነት እንዳይደርስ የሁላችንም ጥረት መኖሩ ተገቢ ነው፡፡ ዕዳው በቀጥታ የራሳችን፤ በተዘዋዋሪ የልጆቻችን መሆኑን አለመዘንጋት ነው!
“ከህመም ሁሉ የበረታብን የአድር-ባይነት በሽታ ነው” ይላል አንድ የጥንት ሩሲያዊ ፀሀፊ፡፡ ከአድር-ባይነት ይሰውረን-ለሚታደርበትም፣ ለአድር-ባዩም አይበጅምና!
አድር ባይነት በየዘመን መለወጫው እንደልክፍት ብቅ ይላል፡፡ “ሌኒን The Pendulum of Opportunism never stops oscillating” ይላል፡፡ (የአድር-ባይነት ፔንዱለም መወዛወዙን መቼም አያቆምም እንደማለት ነው) አብዛኞቹ አድር-ባዮች ሰብዕናን ባወጣው ዋጋ የሚሸጡ ናቸው፡፡ በዚህ ሽቀላና ደጅ-ጥናት ላይ የተሰማሩ ሁሉ፤ አቋም ለበስመ-አብ-ወልዱም ስለሌላቸው፤ አቋም ያለው አይጥማቸውም ወይም ከናካቴው ይጠላሉ፡፡ እንዲህ ካሉ ይሰውረን፡፡
ጫን ላለው ኮርቻ
ለምን ላለው ስልቻ
አይነሳውም ይባላል፡፡
ሁለቱንም የነሳቸው ይሳፈሩበትም ይለምኑበትም የላቸውምና ለገዢም ለሻጭም አትራፊ አይደሉም፡፡ ቀን ለሰጠው መልካም መደላድል ለመሆኑ ዝግጁ ናቸው፡፡ ታዛቢ ዐይን ጠያቂ ታሪክ እንዳለ ይዘነጋሉ፡፡ የዓላማ ፅናት ስለሌላቸው ፅኑዎችን ይረግማሉ፡፡ ልብ ካልን፤ “ከትላንት ተርፈናል፡፡ ከዛሬም እንተርፋለን፡፡ ያለ ጥርጥር ነገም ይኖረናል” ይለናል ንጉጊ፡ፅናትና ዘላቂነት ከዕቅዳችን ጋር ይተሳሰሩ ዘንድ አለመዋዠቅ ሾውሸዌ አለመሆን ዋና ነገር ነው፡፡
አንድ ወቅት በአንድ ክፍለ ሀገር ግብር አንከፍልም ያሉ ገበሬዎች ምነው? ቢባሉ “የሸዋ መንግሥት መች ጠና? ገና ጊዜያዊ ነኝ እያለ አይደል?!”፡፡ አሉ፤ አሉ፡፡
“ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ” ከመሆን ይሰውረን! ዛሬ አውጀን ነገ ከመሻር ያድነን፡፡ ላንዱ የሚሠራ ላንዱ የማይሠራ መመሪያ አውጥተን የማታ ማታ “እስቲ ቆዩ ልናፈርሰው እንችላለን” ከማለት ይገላግለን!
መቼም በእኛ አገር፤ ዕውነተኛ ያልሆነው ነገር ዕውነተኛ ታሪክ ይበዛል
(a real story of unreality እንደሚሉት ፈረንጆች)
ትውልድ ተስፋ እንዳይቆርጥ ተስፋ እናሳየው እንጅ በጥቅም አናማልለው፡፡ ለምርጫ ዕድል እንስጠው፡፡ ወላዋይ ትውልድ እንዳንፈጥር እንጠንቀቅ፡፡
“ጎጆ ውስጥ ያለችው ወፍ መቼ በርሬ ስትል፣ ሰማይ ላይ ያለችው ደግም መቼ አርፌ ጎጆ ገብቼ” ትላለች ይላሉ፡፡ ውስጥና ውጪ ያለው ኢትዮጵያዊ እንዲህ በምኞት የተሳከረ እንዳይሆንብን ከልብ እናስብ! የመዋዠቅንና የአድር-ባይነትን ባህል ካላስወገድን ሁነኛ ህብረተሰብ ለመፍጠር ያስቸግረናል፡፡ በተሳሳተ መንገድ የተሳሳተ አቅጣጫ ይዞ የሚሄድ ማህበረሰብ እንዳንፈጥር ከልብ እንጣር፡፡ አድር-ባይነትን እናስወግድ፡፡ “ታውቃለህ ቢሉት ባንድ እግሩ ዘመተ” የሚለው የጉራጊኛ ተረት ውስጥ-ነገሩ ይሄው ነው፡፡

Read 4340 times