Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:11

ሕይወት በሕንድ ጐስቋላ መንደሮች - ሴቶች ይናገራሉ “ልጃገረዶችን በማዳን አገሪቷን እናድን”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሴቶች ተፈጥሮ በለገሰቻቸው ብልሃት ከተጨባጩ ነባራዊ ዓለም በሚቀስሙት እውቀትና ልምድ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ እውነታ ዘወትር በየቤታችን፣ በየጐረቤታችን፣ በየአካባቢው፣ … የሚታይ ስለሆነ እማኝ ፍለጋ መባዘን ያለብን አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ነው፣ “ከእያንዳንዱ ስኬት ወይም ከስኬታማ ወንድ ጀርባ ብልህ ሴት አለች” የሚባለው፡፡ “የሴት ብልሃት ይስጥህ” የሚለውም አባባል ይህን እውነታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡


ምን ያደርጋል ታዲያ፣ ያለመታደል ሆኖ፣ መንግሥታት፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የምርምር ድርጅቶች፤ የድሃ ሴቶችን እውቀት፣ ለዕቅዶቻቸው በግብአትነት አይጠቀሙም፡፡ በዚህም የተነሳ በ7 ቢሊዮን ሕዝቦችም ዓለም ሴቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በግንባር ቀደምትነት እንደ ሬት የመረረ የኑሮ ገፈት እየተጐነጩ ነው፡፡ በመልማት ላይ ባሉ አገሮች ሴቶች፣ ለራሳቸው ቀርቶ ለልጆቻቸው እንኳ ተስፋና ዋስትና የማይታይበት አደገኛ ሕይወት እየመሩ ነው፡፡
እጅግ በደኸዩና በቆረቆዙ መንደሮች (Slum) የሚኖሩ ሴቶች በያዝነው ምዕተ ዓመት ወደ ዓለማችን የሚመጡ ሕፃናት እናቶች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ስለዚህ፣ ሴቶችን ማስተማር ኅብረተሰቡን ማስተማር ነው እንደሚባለው ሁሉ ሴቶች ትንሽ ትምህርት ቢያገኙ ወይም ከመሃይምነት ቢላቀቁ እንኳ ልምዳቸውን ሐሳባቸውንና ምክራቸውን ለመለገስ ዝግጁ ናቸው ይላል በቅርቡ የወጣው የ2011 የዓለም ሕዝቦች ሪፖርት፡፡
ሙምባይ፣ 20ሚ. ሕዝብ የሚኖሩባት የሕንድ ሀብታሞች የንግድና የመዝናኛ ማዕከል ናት፡፡ ታሃን ደግሞ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች የሚኖሩባትና በሙምባይ ተፅዕኖ ስር ያለች ጥገኛ ከተማ ናት፡፡ ከታሃን ሕዝብ ከመቶ ሰዎች 30ዎቹ ያህል በፍጥነት እያደጉ ባሉ አካባቢዎች እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ታሃን፣ ሁለት መልክ ያላቸው ጐረቤቶች አሏት፡፡ መካከለኛ ገቢ ያላቸው የሚኖሩባትና ሕይወት መርገምት ሆኖባቸው በችግር አረንቋ የሚላቁጡ በርካታ ሰዎች የሚኖሩባት ሲዖል!
ብሂም ናጋር የሲኦሏ መንደር ናት፡፡ ነዋሪዎቿ ሁሉም ያጡ የነጡ ድሆችና ምስኪኖች፣ መንደራቸውም ብዙ ጊዜ ግጭት የማያጣው ቢሆንም፣ የጐረቤታቸው የተሻለ አኗኗር ሕይወትን ጠልተው ራሳቸውን እንዲያጠፉ አልገፋፋቸውም፡፡ ይልቁንም ሕይወትን እንዲወዱና ችግር ተቋቁመው ለመፍታት ጉልበትና ብርታት ሆናቸው እንጂ፡፡ ለምን መሰላችሁ? በአስገራሚ ሁኔታ በርካታ ቤተሰቦችን አንድ ላይ አቅፈው የሚያስተዳድሩ በጣም ጠንካራና ጐበዝ ሠራተኛ ሴቶች ከስር-ከመሠረቱ ስላሉ ነው፡፡
በቅርቡ አንድ የሕንድ ዘጋቢ፣ ከብሂም ናጋር መንደር ሴቶች ጋር በነበረው ቆይታ፤ ያየውንና የተገነዘበውን ቁም ነገር ላጫውታችሁ፡፡ ከሰዓት በኋላ ነው፤ ትንሽ በርከት ያሉ የመንደሩ ሴቶች አብዛኞቹ መስኮት በሌላቸው ትናንሽ ቤቶች ፊት-ለፊት መሬት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ እነዚያ የብሂም ናጋር ያልተማሩ ሴቶች፣ በዚያ ስፍራ እንዲገኙ ስላደረጋቸው ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሲናገሩ በውስጣቸው ጥሩ ስሜት እንዳለ መገንዘብ ችሏል፡፡
ሴቶቹ የሚናገሩት፣ ስለራሳቸው የዕለት-ተዕለት ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ስለ ምግብ ዋጋ ንረት፣ ደረጃውን ስለጠበቀ የትምህርት ዕድል፣ በመንደሮቻቸው ስላለው የጤና አጠባበቅ ክፍተት ስለ ልጅነት ጋብቻ፤ በሴቶች ላይ ስለሚፈፀሙ በደሎች፣ ያለውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እንዳይጠቀሙ ስለሚከለክሉት ትምክህተኛ ወንዶች ድንቁርና፣ … የመሳሰሉ በርካታ በመልማት ላይ ያሉ አገር ሴቶችን ችግሮችና ተስፋዎች አንስተው ተናግረዋል፡፡ ልጆች ደግሞ በመገረም አፍጥጠው ያዩዋቸውና ያዳምጧቸው ነበር፡፡
ሁሉም ባይሆኑ አብዛኞቹ ሴቶች ማለት ይቻላል፤ ሙምባይ ከምትገኝበት የማሃራሻትራ ግዛት ከባሎቻቸው ጋር ተሰደው የመጡና ቤት አከራዮቻቸው በፈለጉት ጊዜ ሊያስወጧቸው በሚችሏቸው መደዴ፣ ቆሻሻና ጨለማ ቤቶች የተጠለሉ ናቸው፡፡ ሁሉም ሴቶች በታዳጊነት ዕድሜ የተዳሩ ናቸው፡፡ በ1978 የወጣው የሕንድ ሕግ፤ የሴት ልጅ የጋብቻ ዕድሜ 18 ዓመት መሆኑን ቢደነግግም፣ ሕጉ በመላው ዓለም በተለይም በገጠር አካባቢዎች አይሠራበትም፡፡ አንዷ ሴት፣ በእሷና በባሏ ቤተሰቦች መካከል በተደረገ ስምምነት ለባል ሲሰጧት መዳሯን እንኳ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡ ምንም አማራጭ አልነበራትም፤ አግብታ ይኸው የብዙ ልጆች እናት ሆናለች፡፡
የብሂም ናጋር ሴቶች፣ በቤት ሠራተኛነት ወይም አንዳንድ ጊዜ ከገንዳ ውስጥ እየቃረሙ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ብዙ ጊዜ የቤተሰባቸው መተዳደሪያ፣ ሴቶቹ በዚህ ሁኔታ የሚያገኙት ገቢ ብቻ ነው፡፡ ባሎቻቸው የቀን ሠራተኞች ናቸው፡፡ “አንዳንድ ጊዜ የቀን ሥራ ያገኛሉ፡፡ ምንም ሳይሠሩ የሚውሉበት ጊዜም ሞልቷል” ይላሉ፡፡ ከ50 ዶላር ጥቂት ከሚዘለው የወር ገቢያቸው፣ ለእነዚያ ተወታትፈው ለተሠሩ መስኮት አልባ ጨለማ ቤቶች ኪራይ 38 ዶላር ይከፍላሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች፤ ከሁለት እስከ ሰባት ልጆች ያላቸው ናቸው፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ፤ ከቤት ኪራይ በተረፈች በዚያች ኢምንት ገቢ፣ ቤተሰቡ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚመሩበት መገመት አያቅትም፡፡
ስካርና ጥቃት፣ የብዙ ቤተሰቦች ችግር ነው፡፡ አንዷ ሴት ባሏ የሚያደርስባትን ጥቃት ስታስረዳ “ቀኑን ሙሉ ስሠራ ውዬ ቤት መጥቼ ደግሞ ለቤተሰቡ ምግብ አዘጋጃለሁ፡፡ አሳዛኙ ነገር ደግሞ ያን ያዘጋጀሁትን ምግብ ከመብላቴ በፊት ባሌ ይደበድበኛል፡፡ የመደብደቤ ምክንያት ደግሞ “ምግቡ ቀዝቅዟል፣ ወይም አይጣፍጥም ወይም ጨው በዝቶበታል” የሚል ነው በማለት በአስተርጓሚ ገልፃለች፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ሌላ አሳዛኝ ነገር አለ፡፡ ባሎቻቸው በሚፈፅሙባቸው ጥቃት አካላቸው ቢቆስልና ቢጐዳ፣ ቁስሉ እስኪጠግ ወይም ሕመሙ እስኪሻላቸው ድረስ ከቤት ፅዳቱ ወይም ከምግብ ማብሰል ሥራው ፈቃድ አይጠይቁም፤ እያመማቸው ይሠራሉ፡፡ ለምን መሰላችሁ? ፈቃድ ቢጠይቁ ስለሚከለከሉ አይደለም፡፡ ፈቃድ ወስደው ቢቀሩ በእግራቸው ለመተካት አሰፍስፈው የሚጠባበቁ በርካታ ሥራ አጦች ስላሉ፣ “ሥራዬን እንዳልነጠቅ” በሚል ስጋት ነው፡፡ ምን ያድርጉ፤ ቤተሰቡ ምንም ዓይነት ማኅበራዊ ዋስትና ወይም ጡረታ (ድጐማ) ወይም ኢንሹራንስ የለውም፡፡ የቤተሰቡ መሠረት (ምሰሶ) ስለሆኑ፣ አንድ ቀን ቢተኙ፣ ቤተሰቡ፣ ለበለጠ ከፍተኛ ችግር እንደሚዳረግ ስለሚያውቁ፣ እያመማቸው፣ ጥርሳቸውን ነክሰው ይሠራሉ፡፡
እነዚህ ሴቶች እያንዳንዳቸው ከአራት እስከ ሰባት ልጆች መውለዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ስለ ቤተሰብ ምጣኔና መከላከያውንም ከየት ማግኘት እንደሚችሉ ያውቃሉ፡፡ እዚህ ላይ፣ ስለቤተሰብ ምጣኔ እያወቁ፣ እነሱና ልጆቻቸው በችግር አረንቋ እየላቆጡ፣ ለምንድነው ሌላ ሕይወት ለችግርና ለስቃይ ወደዚች ዓለም የሚያመጡት? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ፈልገው አይደለም - በወንድ ትምክህተኝነት በታወሩ መሃይም ባሎቻቸው እየተገደዱ ነው የሚወልዱት፡፡ ባሎቻቸው የወሊድ መከላከያ እንዲጠቀሙ አይፈቅዱላቸውም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ዋናው ምክንያት ድንቁርና ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አባት፣ ልጆች የማሳደግ (የማብላት፣ የማልበስ፣ የማስተማር፣ የማሳከም፣ …) ግዴታና ኃላፊነት የለበትም፡፡ ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነትና ግዴታ የሴቷ ስለሆነ ምንም አይሰማውም፡፡ አርግዛ በሆዷ ተሸክማ እየሠራች ከቆየች በኋላ ወልዳ፣ ሕፃኑንና ቤተሰቡን የምታስተዳድረው ሴቷ ብትሆንም መውለድ ያለባትን ልጆች መጠን የመወሰን መብት የላትም፡፡ ወንዱ እንደ አባቱ፣ አያቱ፣ ቅድመ አያቱ … “ልጅ ይወለድ፣ በዕድሉ ያድጋል …” በሚል ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ታውሮ፣ ልጆች ላይ በላይ እንድትወልድ ያስገድዳታል፡፡
ስለዚህ ጉዳይ አንዷ ሴት ስትናገር፣ “ወንዶች እያስገደዱን ነው ብዙ ልጆች የምንወልደው፡፡ እነሱ በቃ ወንዶች ልጆች እንዲወለዱ ነው የሚፈልጉት፡፡ ከዚህ በላይ መውለድ የለብንም፤ ይብቃን” ብንልም አይሰሙንም፡፡ ጉልበትና ማኅበረሰቡ ያሸከማቸው የበላይነት ስላላቸው በጉልበት እንድንወልድ ያስገድዱናል” ስትል፣ ጐረቤቶቹ በሀሳቧ መስማማታቸውን ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ ገለፁ፡፡ አንድ ቤተሰብ፣ ስንት ልጆች ቢኖሩት ነው ጥሩ የሚሆነው? ለሚለው ጥያቄም “ሁለት ልጆች” ስትል ገልጻለች፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ፣ የዚያን አካባቢ የሕንድ ሕዝብ ቁጥር እንዳይጨምር፣ በመውለድ ዕድሜ ያለች ሴት በአማካይ 2.1 ልጆች ብቻ መወለድ አለባት ከሚለው ስሌት ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡
በብሂር ናጋር መንደር የንፁህ ውሃ አቅርቦት፣ ንፅህና አጠባበቅ፣ የግልና የአካባቢ ሃይጅን፣ የሽንት ቤት ንፅህና፣ ቤትን በንፅህና መያዝ፣ … የሚባሉ ነገሮች ትርጉም የላቸውም፡፡ በሺህ ለሚቆጠሩ የመንደሩ ነዋሪዎች 10 ሽንት ቤቶች ብቻ ናቸው ያሉት አምስቱን ሴቶች፣ የተቀሩትን ደግሞ ወንዶች በጋራ የሚጠቀሙባቸው እንደሆኑ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፡፡ በዚያ ሰፈር የሚያልፍ ወራጅ ውሃ የለም፡፡ ስለዚህ፣ የሴቶቹ ሽንት ቤቶች አልፎ-አልፎ ብቻ ይፀዳሉ፡፡ ወንዶቹ በርካታ ነዋሪ ባላቸው አንዳንድ የመርካቶ መንደሮች እንደሚደረገው ስፒሊት እየሠሩ ነው የሚጠቀሙት ማለት ይቻላል፡፡ ቤት አከራዮቹ ነዋሪዎች ባላቸው የቤት ዕቃዎች ውሃ እንዲቀዱ ፣ በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ለጥቂት ሰዓታት ለሚከፍቱት ውሃ 100 ሩፒ (የሕንድ ገንዘብ) ወይም 2.50 ዶላር ያስከፍላሉ፡፡ ኤሌክትሪክም በእያንዳንዱ ምድጃ ወይም አምፑል በየወሩ 100ሩፒ ስለሚከፍሉ፣ አብዛኞቹ ቤቶች ጭለማ ወይም ከውስጥ ጭል ጭል የሚል ደብዛዛ ብርሃን የሚታይባቸው ናቸው ፡፡
ሴቶቹን ሁልጊዜ የሚያስጨንቃቸው ነገር ለቤተሰቦቻቸው በቂ ምግብ ያለማግኘት ነው፡፡ ይህ ችግር ለበርካታ የአዕምሮ ጭንቀት ሕመም እንደዳረጋቸው ይናገራሉ፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የዘወትር ምግቦችና ነጭ ጋዝ በዝቅተኛ ዋጋ ለሕዝብ በሚቀርበው ፕሮግራም፣ እነሱም መደገፍ እንደነበረባቸው በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ እህሉም ሆነ ነጭ ጋዙ፣ ለሚገባቸው ሰዎች ሳይከፋፈልና እነሱ ጋ ሳይደርስ አቅጣጫውን ቀይሮ አየር በአየር ለሕገወጥ ነጋዴዎች ይሸጣል፡፡ ራሽን ካርድ ያላቸው እንኳ በገበያ ዋጋ እንዲገዙ ስለሚገደዱ ዋጋ የለውም ይላሉ፡፡
እነዚህ ሴቶች ምንም እንኳ ስፍር ቁጥር በሌላቸው በርካታ ችግሮች ቢተበተቡም ሞራላቸው ከፍተኛ ነው - ለችግር የሚበገሩና ተስፋ የሚቆርጡ አይደሉም፡፡ አንድ ቀን የልጆቻቸውን ሕይወት ይለውጥ ይሆናል በሚል ተስፋ ብዙ ሴቶች ልጆቻቸውን መደበኛ ወዳልሆነ (የጥቃቅን ሙያ ሥልጠና) ወይም በአካባቢው ወዳለ ት/ቤት ልከው እያስተማሩ ነው፡፡ ከእነዚያ ልጆች መካከልም ጥቂቱ፣ ወደ ቴክኒክና ሙያ ወይም ወደ ከፍተኛ ት/ቤት ገብተዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ሕይወት ለሴት ልጆች የበለጠ ከባድ እንደሆነባቸው ነው፡፡ አንዳንዶቹ በአቅራቢያቸው ባለ ሰፈር በቤት ሠራተኛነት እየሠሩ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ቤተሰባቸው የእነሱን ድጋፍ ሲፈልግ፣ ከት/ቤት አስቀርቶ የእናታቸውን ሕይወት እንዲደግሙ ቤት ያውላቸዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ ያለ ዕድሜአቸው በልጅነት ይዳራሉ፡፡ በዚያን ዕለት እንኳ አንዲት የ14 ዓመት ታዳጊ ለመዳር ሽማግሌ ተልኮ ነበር፡፡ ያቺ ልጅ ጊዜ ባለፈበት ባህላዊ ጭቆና ለሌላ ተጨማሪ ትውልድ እንድትሰቃይ ተፈርዶባታል ማለት ይቻላል፡፡
ለብሂም ናጋር ቅርብ በሆኑና በአካባቢው ባሉ ጥቂት ሰፈሮች፣ ሴቶች ምክርና ድጋፍ የሚጠይቁበት ቦታ አለ፡፡ ከተባበሩት መንግሥታት ፖፑሌሽን ፈንድ ድጋፍ ማግኘት የጀመረው የባዛርቲያ ማህላ ፌዴሬሽን፤ በአካባቢው ትንሽ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከፍቷል፡፡ ጽ/ቤቱ ሴቶች የምክር አገልግሎት ወይም ጥቂት የሕግ ድጋፍ ሲፈልጉ የሚጠይቁበት ወይም ችግሩ በጣም አደገኛ ከሆነ መጠለያ እንዲያገኙ (ሕፃናትን ይንከባከባል፣ በአዳሪ ቤትነት ያገለግላል) የሚያደርግ ነው፡ መምህራን፣ የማኅበራዊ አገልግሎት ሠራተኞችና ፕሮፌሽናል የሥነ-አዕምሮ ባለሙያ የበጐ ፈቃደኞች ቡድን አባላት ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገው በታሃን ግዛት ለተቋቋመው ለዚህ ጽ/ቤት ማዕከል ሙያዊ እገዛ እየሰጡ ነው፡፡ ለማኅበረሰቡ መልዕክት በማስተላለፍ ለውጥ እንዲመጣ የሚያደርግ የጎዳና ላይ ቴአትርም ተሠርቷል፡፡ የዚህ ትርዒት አባላት “ልጃገረዶችን በማዳን አገሪቷን እናድን (ሴቭ ዘ ገርልስ፣ ሴቭ ዘ ካንትሪ)“ በሚል መሪ ሐሳብ ከ 2,500 በላይ ትርዒቶች በማቅረብ ትልቅ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ ፕራብዛ ራቶር፣ በ14 ዓመቷ ተገድዳ ከገባችበት በግጭት የተሞላ ትዳር ማዕከሉ ነፃ እንዳወጣት ትናገራለች፡፡ ራቶር፣ ባሏ ንቆ ስለተዋት ለዓመታት በጭንቀት ትኖር የነበረች ወጣት መሆኗን ገልፃለች፡ ነገር ግን ማዕከሉ ባደረገላት ድጋፍ፣ ሙምባይ አካባቢ ተወዳጅ የሆነውን የሕንዶች ምሳ እያዘጋጀች መሸጥ ከጀመረች ወዲህ፣ በራሷ የምትተማመን አዋቂ ሴት እንደሆነች ትናገራለች፡፡ ራቶና፣ ከራሷና ከልጆቿ አልፋ የተጣሉ፣ ወይም በምግብ እጥረት እጅግ የተጐዱ ሕፃናትን በሕይወት እንዲቆዩ እየረዳች ነው፡፡ ራቶን አሁን ፈታኝ የሆነ ችግር ገጥሟታል፡፡ በዚያ የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት የችግር መ
ንደር፤ እንደሷ ያለች ራሷን የቻለች ታታሪ ሴት የሚፈልግ ወንድ ብዙ ስለሆነ የጋብቻ ጥያቄ ቀርቦላታል፡፡ እሷም ታዲያ - ጥያቄውን አልጠላችውም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ችግር ሆኖባታል፡፡ የቀድም ባሏ ሁለቱን ወንዶች ልጆቿን ካልሰጠችው በስተቀር እንደማይፈታት ነግሯታል፡፡ ያላት አማራጭ ሁለት ነው፤ ልጆቹን ለባሏ ሰጥታ መፋታት ወይም የጋብቻ ጥያቄውን መሰረዝ፡፡ ሁለቱም ምርጫ ከባድ ቢሆንባትም፣ በወጣትነት ዕድሜ ለብቻ መኖር ስለሰለቻት፣ ልጆቿን ለችግረኛ ባሏ ሰጥታ መፋታትና አዲስ ባል ለማግባት ወስናለች፡፡ “አሁን ሁለት ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ባልም ያለኝ ሴት ነኝ” ብላለች - ከልጆቿ በመለየቷ ቅር እያላት፡፡

 

Read 3547 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:16