Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 03 December 2011 08:14

Catherine the Great: ታሪክ፣ አፈታሪክና ውሸት! “ከዚህች እንስት ጋር ልደርና በነጋታው ቱርክ ይግደለኝ” - ጓድ ሌኒን

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የተከበራችሁ አንባብያን:- 
ዛሬ ከጽሑፋችን ዋና ገፀባህሪ ጋር ወደ ጓድ ሌኒን አገር እንዘምታለን፡፡ በታሪካዊ መረጃ እንጀምር፡፡ የጀርመንንና የራሽያን መልካም ጉርብትና ለማጠናከር ሲባል የጀርመንዋ ልእልት (Catherine) ለራሽያው አልጋ ወራሽ ተዳረች፡፡ ብዙም ሳይቆዩ ባልና ሚስት ነገሱ፡፡ ንጉሱ (1729-96) በአስራ ዘጠኝ አመትዋ አገር ለማስተዳደር ሲሞክርና እንደማይችልበት ሲያስመሰክር ሁለት አመት ካስተዋለችው በኋላ፣ የወንድ ወኔ እንኳ እንደሌለው አይታ ናቀችው፡፡ (ከጥቂት ምርጥ ኮሌኔሎች ጋር ተመሳጥራ) አስገደለችውና በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ ስልጣን ጨበጠች፡፡

በራሽያ ታሪክ “The Great” የሚል ማእረግ ያላቸው ነገስት ሁለት ብቻ ናቸው፡፡ መጀመሪያው Peter the Great፤ ከፊል እስያዊት ከፊል ኤውሮፓዊት የነበረችውን ራሽያ፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ ቢቃወሙትም አስገድዶ እሺ አሰኝቷቸው “ኤውሮፓዊት” አደረጋት፡፡ 
ሁለተኛ Catherine The Great Russia ከጥንት ጀምሮ ልትቆጣጠረው ስትጥር የነበረውን፣ ወደ አትላንቲክ ውቅያኖስ የሚያስገባትን ወደብ በጦር ሀይል ከቱርክ ማረከች፡፡ ቋንቋውን የምትናገረው በጠራ ጀርመናዊ ቅላፄ ነበር፡፡ እና ይህን ከፍተኛ አክብሮትና አድናቆት ያተረፈችው ሴትዮ “ለህዝቡ ባዳ ለባህሉ ባይተዋር” ነበረች፡፡ 
ታሪካችን ሲቀጥል ካተሪንን ደጋግመን እናገኛታለን…
…በአንድ የጀርመን ክፍለ አገር ውስጥ አንድ Museum ነበረ፡፡ ጥንታዊ ስለሆነ ብዙ ታሪካዊና ባህላዊ እሴት ያላቸው ቅርሳ ቅርስ የሆኑ ንብረቶች በዘመናቱ ብዛት ተጠራቅመውበታል፡፡
አዲስ አስተዳዳሪ ተቀጠረ፡፡ ሙዝየሙ እጅግ ዝርክርክ መሆኑን አይቶ፣ እቃዎቹ ሁሉ በየአይነታቸውና በጽዳት ለጐብኚዎች በጣም እንዲመቹ አደረገ፡፡ አገረ ገዢው ሲበዛ ተደስተው ለአስተዳዳሪው የሙዝየሙን በጀት አሳደጉለት፡፡ ታታሪው አስተዳዳሪ ታማኝ ባለሙያ መስሎ፣ እቃዎችን ለመግዛት ወደ ሌሎች አገሮች ይዘዋወር ነበር፡፡
ግን ጮሌ ሞላጫ ሌባ ስለነበረ፣ ሳይታወቅበት የሙዝየሙን ውድ እቃዎች እየቸበቸበ ብዙ ገንዘብ አጠራቀመ፡፡
ይህን ሁሉ ሲሰራ እሁድ እሁድ የሚውለው Baron Munkhausen መኖሪያ ቤት ውስጥ ነበር፡ታሪካችን ሲቀጥል ይሄ ሌባ የሚያጫውተን ደሳስ የሚሉ የባረን ሙንክሀውዘን ታሪኮች አሉ…
Baron ማለት ከአባት ወደ በህር ወንድ ልጅ የሚተላለፍ የመኳንንት ማእረግ ነው፡፡ በጦር ሜዳ አሰላለፍ ቢሆን ባረን ያገራችንን ቀኛዝማች ወይም ደጃዝማች ቦታ ይይዛል፡፡ ከዚህ ጋር ደግሞ እጅግ ባለፀጋ ነው፡፡ መኖሪያ ቤቱ መለስተኛ ቤተ መንግስት ይመስላል፡፡ የባረን ሙንክሀውዘን ቤቶች ለብዙ ትውልድ በመላው ጀርመን የተደነቁ የጦር ሜዳ ጀግኖች ነበሩ፡፡
ባረን ሙንክሀውዘን ያባቶቻቸውን ጦረኛ መንፈስ ስለወረሱ፣ ለውጊያ ሁልጊዜ እንደተጠሙ እንደተራቡ ነበር፡፡ ዳሩ ምን ይሆናል፣ አገሩ ሰላም ሆነ፡፡ ከፈረንሳይ ወይም ከእንግሊዝ ጋር እንዳይዋጉ እነዚያ ሁለቱ ወይ ፍጥጫ ላይ ናቸው ወይ የሆነ ነገር እየዶለቱ ነው፡፡ ለማንኛውም ከነሱ ጦርነት አይጠብቅም፡፡ ከራሽያ ጋር እንዳይዋጉ ያገር ልጅ ካተሪን ከቱርክ ጋር ስትፋጠጥ ቆይታ አሁን ወደ “ግጭት” እየተሸጋገረች ነው፡፡ በረን ሙንክሀውዘን ሲያስቡበት ጊዜ፣ እዚህ ተጐልተው ከሚደበሩ ወደ ራሽያ ተጉዘው ለንግስት ካተሪን ቢዋጉላት ይመረጣል፡፡
ሄዱ፣ ዘመቱ፣ ባባቶቻቸው ወኔ ተዋጉ፡፡ ካተሪን ድል አድርጋ ተመልሳ ባረን ሙንክሀውዘንን አመስግና፣ ለአንፀባራቂ ጀግንነታቸው ተገቢውን ኒሻን ሸልማ፣ በግል ባለውለታዋ በመሆናቸው ደግሞ ሁለመናው አንፀባራቂ ወርቅ የሆነ ሽጉጥ “ያገር ልጅ፣ አትርሳኝ አስታውሰኝ” ብላ እንዳበረከተችላቸው ይናገራሉ፡፡
…ታሪክ የመስራት ጊዜ አለፈ፡፡ ተመልሶ ሰላም ሰፈነ፡፡ በምትኩ ታሪክ የማውራት ጊዜ መጣ፣ (ዳግም ተመልሶ ጦርነት የሚያስገመግምበትን ወቅት እየናፈቁ)
ሰንበት ሰንበት የባረን ሙንክሀውዘን መኖሪያ ቤት ለወዳጆቻቸው ክፍት ነው፡፡ ከጧት ቁርስ እስከ ማታ እራት (እና ከዚያም በኋላ) ብሉልኝ ጠጡልኝ ነው፡፡ ዘንካታው ባረን ግርማ ሞገሳቸውን ተላብሰው እየተጐማለሉ እንደ ስላሴው አብርሃም ሲያስተናግዱ ይውላሉ፡፡
ማታ ወደ ሁለት ሰአት ላይ ወደ መኝታ ቤት ሄደው ወርቅ ሽጉጣቸውን ይዘው ተመልሰው ሲቀመጡ፣ ገድል ስለሚተራመስበት የህይወት ታሪካቸው ቁርጥራጩን ማውራት ሊጀምሩ ነው ማለት ነው፡፡
አብዛኛዎቹ እንግዶች እየተደሰቱ ቢውልም፣ በተለይ የመጡት ለዚች ሰአት ነው፡፡ ከነዚህም አንዱ ያ ሌባ የሙዝየም አስተዳዳሪ ነበረ፡፡ እሱ ብልህ ሰውዬ ከሙዝየሙ የዘረፈውን ገንዘብ ለንደን ሄዶ ጨፈረበት “አለሙን ቀጨበት!”
ባዶ ኪሱን ሲቀር ጊዜ፣ አሰበበትና The Adventures of Baron Munkhausen የሚል መጽሐፍ አሳትሞ እንደገና ለአጭር ጊዜ በጣም ሀብታም ሆነ፡፡ ባረንየው ራሳቸው ናቸው ታሪካቸውን የሚናገሩት…
ሲያወሩ ከአድማጮች ሙሉ ፀጥታ ይጠበቃል፡እርብ በርስ እንኳን መነጋገር ቀርቶ መንሾካሾክ አይፈቀድም፡፡ ኧረ መጠቃቀስ ወይም ፈገግታ መለዋወጥ ክልክል ነው ማዳመጥ ብቻ! አለዚያ ወርቅ ሽጉጣቸውን እያየናቸው አጉርሰውት ቀኝ እጃቸው አጠገብ ተጋድሟል፡፡ የፀጥታ ትእዛዛቸውን የጣሰ ደሙ “ደመ ከልብ” ነው (ብዙ ምስክር አይቷል)
አሀዱ - ለማንም መሪ ቢሆን እዘምት ነበር፡ (አሉ ባረንነታቸው) ላገሬ ልጅ ለንግስት ካተሪን ተሰልፌ ቱርክን ያህል ሃያል ጠላት መጋተር ሲሆን ጊዜ ክንፍ እንዲኖረኝ ተመኘሁ፡፡ በዘራችን ምንም ብንቸኩል መጣደፍ የለም፡፡ ስለዚህ ወዳጆች አማከርኩ፡፡ “ኤውሮፓ አገር የትም ቢሆን መቸም ቢሆን መጓዝ ይቻላል” አሉኝ፡፡ “የራሽያ ጐዳናዎች ግን ጥንት ከተነጠፉ አንስቶ ተጠግነው ስለማያውቁ፣ በየአምስት ስድስት እርምጃ ርቀት ጉድጓድ በጉድጓድ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ያለህ አማራጭ አንድ ብቻ ነው፡፡ በክረምት የሆነ እንደሆነ በየእለቱ የሚወርደው በረዶ ጉድጓዶቹን ይደፍናቸዋል፡፡ ስለዚህ አንድ የክረምት ተንሸራታች በፈረስ የሚጐተት ጀልባ መሳይ ሰረገላ አስሰርተህ መጋለብ ነው፡፡”
ጉዞዬ አስገራሚ መሆን የጀመረው ፖላንድ ከደረስኩ በኋላ ነበር፡፡ በረዶው ለሳምንት ያህል ሌትም ቀንም ሲወርድ ሰንብቷል፡፡ መንገድ ሁሉ ተሸፍኖ፣ ዛፎችና ቤቶች አልፎ አልፎ ብቻ ጫፋቸው ይታያል፡፡ አቅጣጫ የሚመረጠው በግምትና በነሲብ ነው፡፡
ሊጨልም ሆነ፡፡ ፈረሴን የማስርበት ስፈላልግ አንድ ጉቶ መሳይ ነገር አየሁ፡፡ እሱ ላይ አሰርኩትና፣ በረዶው ውስጥ ጉድጓድ ነገር ቆፍሬ እውስጡ ተጋደምኩ፡፡
ጧት ስነቃ ጫጫታ ሰማሁ፡፡ ዙሪያውን ብመለከት ሰፊ አደባባይ ውስጥ ነን፡፡ ዳሩ ላይ ከቆመው ትልቅ ቤተክርስትያን ጉልላት ላይ፣ ፈረሴ ማታ ጉቶ መስሎኝ እንዳሰርኩት ተንጠልጥሎ፣ ሰዎች ተጋግዘው ሊያወርዱት እየተጯጯሁ ነው፡፡ ቤተክርስትያኑን ሳይቀር ሸፍኖት የነበረው በረዶ ቀስስስ እያለ ሙዋሙቶ ነው በእንቅልፌ በዝግታ መሬቱ ላይ የተወኝ፡፡
በብዙ ገመድ፣ በብዙ ብልሀትና በብዙ ትብብር ፈረሴን አወረዱልኝ…
ክልኤቱ - የፖላንድን ድንበር ላልፍ ትንሽ ሲቀረኝ ፊኛዬን ለማቃለል ቆም አልኩ፡፡ ከመንገዱ ወጣ ለማለት ጥቂት እንደተራመድኩ ከኋላዬ ሀይለኛ የአውሬ ጩኸት ሰምቼ ዘወር ብል፣ ተኩላ እየጋለበ ወደኔ ይመጣል፡ አለቀልኝ ብዬ ሳስብና፣ ያባቶቼ ወኔ ሲያንቀሳቅሰኝ እኩል! አፉን ከፍቶ ወደ ጉሮሮዬ ሲዘል፣ በመብረቅ ፍጥነት እጄን ወደ አፉ ውስጥ ወረወርኩት፡፡ ጭራውን ጨበጥኩና ሳብኩት፡፡ ተኩላው እንደሚያወልቁት ካልሲ የውስጡ ወደ ውጪ ተገለበጠና፣ በመጣበት ፍጥነት እየጋለበ ወደ ጫካው ገባ፡፡
ያባቶቼን አምላክ እያመሰገንኩ ወደ ሰረገላዬ ተመለስኩ፡፡ (ፖላንድን አልፌ ወደ ሞስኮ) መንገዴን ስቀጥል ምንም ያህል ጊዜ ሳያልፍ የተኩላ ጩኸት ሰማሁ፡፡ በደመነብሳዊ ፍጥነት ጐንበስ አልኩ፡፡
ተኩላው ስቶኝ ፈረሱ ዳሌ ላይ አፉን ተከለ፡፡ ፈረሴ በረገገ፣ በእግሬ አውጪኝ ፍጥነት ሲጋልብ፣ ተኩላው በክረምት ጠኔ ሲበላው፣ እኔ በፍርሃትና በንዴት ተኩላውን ስገርፍ፣ ተኩላው እየበላ እየበላ የፈረሱን ግማሽ ጨርሶት፤ ግማሽ ፈረስ ግማሽ ተኩላ ሆነው ሲጋልቡ ሲጋልቡ፣ ተኩላው ፈረሱን በልቶ ጨርሶት፣ በሱ ተተክቶ እየነዳሁት ሞስኮ ደረስን፡፡
ሰለስቱ - የተቀበሉኝ መስኮባውያን ከድካሜና ከፍርሃቴ እንዳገግም ያህል ብቻ ሶስት ሰአት ያህል እንድተኛ ፈቀዱልኝ፡፡ ከዚያ እኔም በሰረገላዬ ላይ ቆሜ፣ እነሱም በፈረስና በእግር እየተራመዱ ቤተመንግስት ደረስን፡፡
ንግስት ካተሪን ገና ብቅ ሲሉ ግርማ ሞገሳቸው፣ ቀረብ ሲሉ ውበታቸው ይማርካል፡፡ እንደዚች የምታምር ሴት እኔም አይቼ አላውቅ፣ እግዚአብሔርም ፈጥሮ አያውቅ፡፡ እድሜ ልኬን እንደማፈቅራት ታወቀኝ፣ ከሷ ሌላ ሴት ዘወር ብዬ እንደማላይም እርግጠኛ ሆንኩ፡ ጀግኖች አባቶቼ ይቅር ይበሉኝ እንጂ፣ ከጦርነትም አስበልጬ እወዳታለሁ (ለሞስኮ አድባር እሳላለሁ፡፡ ከዚች እንስት ጋር ልደርና በነጋታው ቱርክ ይግደለኝ አሜን!)
ካተሪንና ባለሟሉችዋ ከነሚስቶቻቸው እና አንድ አምስት የሚሆኑ ከፍተኛ መኮንኖች በተገኙበት የእንኳን ደህና መጣህ እራት ተጋበዝኩ፡፡ ድንቅ ምሽት ነበር፡፡ (ካተሪን በቮድካ ሞቅ እያላት ሲሄድ “ያገር ልጅ” አለችኝ “እንደናንተ አይነት ጀግኖች ከጐናችን ከተሰለፋችሁማ፣ ቱርክን ባጭር ጊዜ ድባቅ ባንመታውማ እኔ ካተሪን አይደለሁማ” አይኖችዋ በተለይ ለኔ የሚያበሩ መሰለኝ፤ የሞስኮ አድባር ፀሎቴን ሰምታ!
ንግስቲቱ የመደቡልኝ ባልደረባ ከሶስት ሳምንት በኋላ የልደት በአላቸውን እንደሚያከብሩ ነገረኝ፡፡ ማንም ሊያስበው የማይችለውን የልደት ስጦታ ላበረክትላት አቅጄ፣ በየቀኑ ተኩላዬን አንድ ትርኢት ሳለማምደው ሰነበትኩ፡፡ ዝርያው የውሻ ዘመድ ስለሆነ ማሰልጠኑ ምንም ያህል አስቸጋሪ አልነበረም፡፡
ግን ደሞ እውነት መናገር ይሻላል፣ ይሄ የጀብዱ ጓዴ ላዩን ተኩላ ይሁን እንጂ ውስጡን ደሞ ፈረስ፣ አንድም ሁለትም፣ ከኔ ጋር አንድም ሁለትም ሶስትም ናቸው ነን፡፡ ለዚህ የተዘጋጀንለት ቀን ደረሰ፡፡ ንግስቲቱ በቁርስ ሰአት ከተከፈተላቸው ሻምፓኝ መጠጣት የጀመሩ፣ በመሀሉ በመጠኑ እየተበላ ሲጠጡ ውለው ዋናው የእራት ሰአት ሲደርስ በሞቅታ፣ እንዲሁም ከኔና ከአንድ ሁለት ኮሎኔሎች ጋር በብርሃን ፈገግታዋ የመፈላለግ መልእክት በመለዋወጥ የተነሳ የቅንዝር እሽክርክሪት መሀሉ ሆናለች፡ለእራት ፊት ለፊትዋ አስቀመጠችኝ፡፡ በቀኝዋ ጠቅላይ ሚኒስትር Potemkin ተቀምጦ ዙሪያውን ሲቃኝ፣ ፊቱ ላይ አስተዋይነትና የቀበሮ ብልጠት ይታየኛል፡፡
በሶስት ረድፍ በአራት ማእዘን የተቀመጡት ጠረጴዛዎች እያንዳንዳቸው አንድ ደርዘን ተጋባዥ ተቀምጦባቸዋል፡፡
ሾርባ ተጠጥቶ ሰሀን ማንኪያዎቹ ከተነሱ በኋላ አሳላፊዎቹ በየሰሀናችን ቢስቴካ ሊያስቀምጡልን ሲጀምሩ፣ ካተሪንን
“ንግስት ሆይ” አልኳት “ይህን የመሰለ እራት ከተኩላው ጓዴ ጋር ብጋራው ነብሴም እንደ ስጋዬ ትጠግባለች”
“ይጋበዝልኝ እንጂ”
ተነስቼ ወጥቼ እየመራሁ አመጣሁት፣ ከተደረደሩት ጠረጴዛዎች በአንዱ ጫፍ ጀመርን (ከካተሪን ርቆ በተሰራው)
ጠረጴዛው ላይ ወጥቶ በኋላ እግሮቹ ቆመ፡፡ እኔ አሳላፊ በሚቆምበት ቦታ ቆምኩ፡፡ ከመጀመሪያው ተመጋቢ ሰሀን ቢስቴካውን በሹካ አንስቼ አጐረስኩት፡፡ ወደሚቀጥለው ሰሀን ተራመደ፣ አንስቼ አጐረስኩት፡፡ እንዲህ ሲራመድ ሳጐርሰው፣ አርባ ቢስቴካ ጐረሰ (ሀያ ለተኩላነቱ ሀያ ለፈረስነቱ)
ሲጠግብ እጅ ነሳና በአራት እግሩ ቆመ፡፡
“ብራቮ!” ብላ ጮኸች ንግስት እያጨበጨበች፡፡ ቤቱ ሙሉ ተቀበላት እንደ ጭፈራ፡፡
ወደ ማደርያው መልሼው ስመለስ እንደገና ተጨበጨበልኝ፡፡ እጅ ነስቼ ስቀመጥ ካተሪን “የተከበራችሁ እንግዶቼ፣ ለኮሎኔል ሙንክሀውዘን ፅዋችንን እናንሳ!”
ቆሜ ሰገድኩላት፣ ለጤናዬ ተጠጣልኝ …
… ታሪካዊ መረጃ (information) ንግስት ካተሪን ለውበትዋ ወደር አይገኝላትም ተብሎላታል፡፡ ከዚህም ጋር ወንድ መሄድ እጅግ ማዘውተርዋ “ያደባባይ ምስጢር” ነበር፡፡ ምርጫዋ አብዛኛውን ጊዜ ረጃጅም መልከ ቀና ኮሌኔሎች ነበሩ፡፡ አንዱን ለጥቂት ወራት (እድለኛ ካልሆነም ለጥቂት ሳምንታት ብቻ) እቅፍዋ ገነት ውስጥ ከሰነበተ በኋላ ይሰለቻታል፡፡ ጧት ጩቤ የተሰካበት ሬሳው ወንዝ ውስጥ ተንሳፍፎ ይገኛል፡፡
ሳምንት ያህል ከፆመች በኋላ ሌላ ዘንካታ ኮሎኔል ትመርጣለች፡፡ ወታደር መቸም ሞትን አይፈራም፡፡ ለሀገር አገልግሎት ብቻ ጦር ሜዳ ላይ ከመሞት ለንግስቲቱ አገልግሎት ከአልጋ ወድቆ መሞት! ጊዜያዊ ፍቅረኞችዋ ሁሉም እጣ ላልደረሳቸው ጓዶቻቸው እንደሚያወሩት አንድ ሌሊት ብቻ አብረዋት አድረው እቺን አንዲት ህይወት መክፈል ፀጋ ነው፡፡
የብዙ ሴት ወሲባዊ energy ተሰጥቷታል ከውበቷ የሚስተካከል፡፡ እንዲሁም ራሽያን ያህል ሰፊ አገር (ከአለም ሁለተኛ!) ለማስተዳደር የቻለ አእምሮ፡፡ ቱርክን በጦር ድል ለማድረግ የሚያስችል ወኔ!
ገና አስራ ዘጠኝ አመት ሳይሞላት (ማለት እትውልድ አገርዋ ስትኖር) best selling ልቦለድ ደራሲ ነበረች (ስራዎችዋ ለመጪ ትውልዶች ለመዝለቅ ብቃት እንደሌላቸው አሳምራ ታውቅ ነበር)
በታላቅዋ ካተሪን ዘመን ራሽያ የኢኮኖሚ እድገት አሳይታለች፡፡ ለህዝብዋ ከዚያ የላቀ እድገት ያበረከተችው ለትምህርት ከሌላው ሁሉ ጉዳይ የበለጠ ትኩረት በመስጠት ነበር፡፡ ለወደፊት እድገት ዋናው መሰረት መሆኑን በመገንዘብዋ! በማስገደድ አይደለም፡ በለስላሳው፣ በማግባባት፣ ጥቅሙን በማስረዳት ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ከባድ ጉዳይ እየፈፀመች፣ ከዚያ የተረፋትን energy ነበር ከኮሎኔሎችዋ ጋር ለመደሰት ያዋለችው፡ አለዚያ ምናልባት እንደ ጓድ ሊቀመንበር Peptic Ulcer ያሰቃያት ነበር፡፡ ያችን የመሰለች እንቁዬ የሄዋን ልጅ!] …
… ኮሎኔል ሆኜ ምሽቱ እየቀጠለ ሄዶ፣ በመጨረሻ ተሰናብቼ መኝታ ቤቴ ገባሁ፡፡ አልጋ ውስጥ ገብቼ ከናፍቆትዋ ጋር ምንም ያህል ሳልቆይ፣ እሷ ራሷ መጣች፣ ስስ የውስጥ ቀሚስዋ የገላዋን ድምቀት ስስ ደመና ፀሀይን እንደሚያሳይ እያሳየኝ፣ ሆን ብሎ ለኔ የፈጠራት እየመሰለችኝ፡፡
አልጋውን ገለጥኩላት፣ ተቃቀፍን፡፡ ይህ የተባረከ አልጋ ሌሊት ሌሊት ሶስት ወር ሙሉ አስተናገደን፡ የሀገር ጉዳይ፣ በተለይ ከቱርክ ጋር የመጨፋጨፉ ዜና በባልደረባዬ በኩል ይደርሰኛል፡፡ ከሷ ጋር የግል ህይወታችንን ነው የምንጨዋወተው፡፡
ይህን ስርአት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የሻርነው፡ ከመሬት ተነስታ “ወስኛለሁ በቃ!” ስትለኝ ነበር “ፍቅራችን’ኮ ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የዛሬ ወር Christmas ሲመጣ ይፋ እናወጣውና አንተ ንጉስ እኔ ንግስት እንሆናለን፡፡”
“ንጉሱም ንግስቲቱም ጀርመን ሲሆኑ ሩስኪዎቹ አይቀየሙም?”
“ምን እንዳያመጡ? ስታቅፈኝ ጊዜ ንግስት ካተሪን መሆኔን ረሳህ’ንዴ?”
ዝም አልኩ፡፡ “ተናገር እንጂ” አለችኝ
“ተራ የራሽያ ንግስት ብትሆኚ ኖሮ መልካም ነበር፡፡ አይደለሽማ! ታላቅዋ አንድዬዋ ካተሪን ነሽ፡፡ አጠገብሽ እንኳን ባል የባል ጥላ ሊቆም አይገባውም፡፡ ፍቅራችንን ለፍቅር አምላክ እንተወውና እንደምወድሽ ውደጂኝ”
“ይበልጥ ነው’ምወድህ እኔስ፡፡ ባረን ሙንክሀውዘን ሆንክና ነው እንጂ፣ ማንም ሌላ ወንድ ቢሆን ቂጡ እየሳቀ ይነግስ ነበር”
“ባገሬ ቋንቋ ፍቅር መስራት ሲናፍቀኝ ሲናፍቀኝ -አንተ ከተፍ!” ያለችኝን አስታወስኩ “ካንተ ጋር ስሆን ብቻ ነው ሙሉ ሴት መሆኔ የሚታወቀኝና የሚያበራኝ” …
… እዚህ ላይ ስንደርስ documentation (መፃህፍት፣ ደብዳቤዎች፣ የአይን ምስክሮች) ይጐድለናል፡፡ ሊቃውንት የባረን ሙንክሀውዘንን የግል ማስታወሻ ሲመረምሩ፣ ከመሀሉ አንድ ሉክ (ሁለት ገፅ) ተቦጭቆ ጠፍቶ፣ የሚከተለው እንዲህ ይነበባል፡-
“እኔ’ኮ እነዚያ ኮሎኔሎች ካንቺ ጋር ሰንብተው በጩቤ ተገድለው ይገኛሉ ሲሉ አላምንም ነበር”
“እመን እውነት ስለሆነ”
“አስረጂኝ”
“ይሰለቹኛል፡፡ በህይወት ቢኖሩ፣ ለሚያምኑት ሰው መንገራቸው አይቀርም፡፡ እሱም ለሚያምነው እያቀበለ፣ ካተሪን ንግስትን “ባዳ ጀርመን! አገርሽ ግቢ!” ብለው ያባርሩኝ ነበር፡፡ ደሞ መርጠው ነው ‘ሚገቡበት፣ ማጥፊያቸው መሆኔን እያወቁ”
ወደ ንጉስነት ጓዳ ማየት አሁን ለአፍታ ብቻ ብቻ ያስደመመኝ፣ ሌላውን ሁሉ ባውቅ ማበዴ ይቀራል ወይ? ባረን ሙንክህውዘን ካተሪን እንደፎከረችው መንገስ ሳይሆን፣ ለክሪስመስ ወደ ጦር ሜዳ መጓዝ ነበር የሚጠብቃቸው፡፡
እንደዚያን ቀን ምድርን winter በነጭ የብርድ ከፈን ጠቅልሏት አያውቅም [ይሉናል ባረንነታቸው] ስነስርአት ነውና፣ ተኙ ሲባል ተረኛው ወታደር ጥሩንባውን ነፋ፡፡ አንዳችም ድምፅ አይደመጥም፣ ግን ስርአት ነውና እስከ ዜማው ማለቅያ ቀጠለ፡፡
በነጋታው ፀሀይ ስትወጣ፣ ምንም ደካማ ሙትቻ ብትሆን ፀሀይ ናትና፣ ምድሪቱን ትንሽ አሞቀቻት፡፡ እና ትላትን ማታ የብርዱ ብዛት አድርቆዋቸው ያልተሰሙን ድምፆች አሁን ሞቃቸውና በደምብ ተደመጡ … እያለ ይቀጥላል የባረን ሙንክሀውዘን ገድል፡፡
እኛ ስንሰናበታቸው ካተሪን በተኩላ-ፈረሳቸው ከተደነቀችው የበለጠ እንድትደመም አቀዱ፡፡ ወደ ሰሜን ዋልታ ተጉዘው ሲያበቁ፣ በብርድና በቀዝቃዛይቱ ጨረቃ መካከል ያለውን ስበት በመጠቀም ወደ ጨረቃ ተጓዙ፡፡
ተመልሰው ከተረኩልን እናቀብላችኋለን፡፡
እስከዚያው ቸር ይግጠመን አሜን፡፡

 

Read 3766 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 12:59