Saturday, 07 December 2013 13:20

በሲጋራ ማጨስ ሳቢያ በዓለም 13ሺ ሰዎች በየዕለቱ ይሞታሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ሌሎች ባጨሱት ከ600ሺ በላይ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ
በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን በላይ አጫሾች አሉ
ኢትዮጵያ ሲጋራ ማጨስን በተመለከተ አዲስ አዋጅ ልታፀድቅ ነው

በዓለማችን ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዘ በየዕለቱ 13 ሺህ ሰዎች እንደሚሞቱ አንድ መረጃ ይፋ አደረገ፡፡ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ይፋ ያደረገው ይኸው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በዓለም ላይ 1.3 ቢሊዮን የሚሆኑ ሲጋራ አጫሾች የሚገኙ ሲሆን ይህም ከአጠቃላዩ የዓለም ህዝብ ብዛት 1/5ኛው ማለት ነው፡፡
በመላው ዓለም ላይ በትምባሆ ምክንያት በየዓመቱ 6 ሚሊዮን ሰዎች የሚሞቱ ሲሆን ይህም ማለት በየስድስት ሰከንዱ አንድ ሰው በትምባሆ ሣቢያ ህይወቱን ያጣል ማለት ነው፡፡ ከዚህም ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የሚሞቱት ሲጋራን በቀጥታ በማጨሳቸው ሣቢያ ሲሆን 600ሺ የሚሆኑት ደግሞ ትምባሆን በቀጥታ የማያጨሱ ነገር ግን በሁለተኛ ወገን አጫሽነት (Second hand smoking) ምክንያት የሚሞቱ መሆናቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2010 ዓ.ም የዓለም ጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ባለስልጣን መ/ቤቱ ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ 10 ሚሊዮን የሚሆኑ አጫሾች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ መካከል የሴት አጫሾች ቁጥር ከ1 በመቶ አይበልጥም፡፡
ሰሞኑን በግዮን ሆቴል በተካሄደ አውደ ጥናት ላይ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከበደ ወርቁ እንደተናገሩት፤ ሲጋራ ማጨስ አንድ ሰው በህይወት ከሚቆይበት ጊዜ ከ10 ዓመት የበለጠ ዕድሜ ሊቀንስበት ይችላል፡፡ በዓለማችን ከሚከሰቱ 10 የአዋቂ ሰዎች ሞት መካከል አንዱ ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዙ ችግሮች የሚከሰቱ እንደሆኑ የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአገራችንም ከሲጋራ ማጨስ ጋር በተያያዙ የሚከሰቱ የጤና ችግሮች እየጨመሩ መጥተዋል ብለዋል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት መረጃ፤ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የአጫሽ ቁጥር ያላት አገር መሆኗን አመልክቶ የአጫሽ ዜጐቿ ቁጥር ግን የመጨመር አዝማሚያ ይታይበታል ብሏል፡፡
በዓለማችን እጅግ በርካታ ሰዎች የሚያጨሱባት አገር ቻይና መሆኗን ያመላከተው መረጃው፤ 1.3 ቢሊዮን ከሚሆነው ህዝቧ ወደ 550 ሚሊዮን የሚጠጋው ከሲጋራ ጢስ ጋር ለተያያዙ የጤና ችግሮች ተጋላጭ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
“ያለፈቃዳቸው እንዲያጨሱ” በመገደዳቸው ምክንያት በየዓመቱ ህይወታቸውን ከሚያጡት 600ሺ የዓለም ህዝቦች መካከል አብዛኛዎቹ ህፃናትና ሴቶች ሲሆኑ አጫሾች ሲጋራ በሚያጨሱበት ወቅት ከሣንባቸው የሚወጣውን ወይንም በቀጥታ ከሲጋራው የሚለቀቀውን ጢስ እንዲቀበሉት ወይንም እንዲተነፍሱት ይገደዳሉ፡፡ ይህም በአጫሹ ቤተሰቦች ላይ ጉዳቱ እንዲጐላ ያደርገዋል ይላል-መረጃው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርጐ እንደገለፀው፤ ሲጋራ በሚጨስበት አካባቢ ያሉ ሰዎች ከዋናው አጫሽ በአማካይ ከ15-30% የሚሆነውን ድርሻ ወደ ሣንባቸው ያስገባሉ፡፡
ይህንን በቀላሉ ለማስረዳትም በአካባቢያችን ከተጨሱ 10 ሲጋራዎች መካከል አንድ ተኩል የሚሆነውን ያለፍላጐታችን እንድናጤስ እንገደዳለን ማለት ነው፡፡ ከ85% በላይ የሚሆነው የሲጋራ ጢስ ለዓይን በማይታይና ምንም አይነት ሽታ በሌለው ጋዝ መልክ ወደ ሣንባችን የሚገባ ሲሆን ጢሱ ካርቦንሞኖክሳይድና ሃይድሮጂን ሲያናይድን የመሳሰሉ መርዛማ ጋዞችን ይይዛል፡፡
ሌሎች ሰዎች ያጨሱትን ሲጋራ ወደ ሣንባቸው በማስገባታቸው ሣቢያ ለጉዳት የሚዳረጉ ሁለተኛ ወገን አጫሾች ለሣንባ ካንሰር፣ ለልብ ህመም፣ ለአስም በሽታ፣ ለማስታወስና የመረዳት ችሎታ መቀነስ፣ የፅንስ ማስወረድና ደካማ ለሆነ የደም ዝውውር እንደሚጋለጡም ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።
ሲጋራ ማጨስ በነፍሰጡር እናቶች ላይ የሚያስከትለው የጤና ችግር እጅግ የከፋ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ጢሱ በፅንሱ ላይ እጅግ የከፋ የጤና ችግር ከማስከተሉም በላይ ዝቀተኛ ክብደት እንዲኖረውና ፅንሱ ያለጊዜው እንዲወለድ ሊያደርገውም እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ ለማርገዝ የሚፈልጉ ሴቶች ሲጋራ ማጨሳቸውን ወይንም ለሁለተኛ አጫሽነት የመጋለጥ ዕድላቸውን በእጅጉ ሊቀንሱ ወይንም ሊያስቀሩ ይገባል ያለው ሪፖርቱ፤ የሲጋራው ጢስ የማርገዝ ብቃታቸውን ሊቀንሰው አሊያም ሊያስቀረው ይችላል ብሏል፡፡
በግዮን ሆቴል በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት ዶ/ር አበባየሁ አሰፋ እንደገለፁት፤ በሲጋራ ማጨስ ሣቢያ የሚከሰተውን የጤና ችግርና እየጨመረ የሄደውን የአጫሾች ሞት ቁጥር ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ጥረት አጋዥ የሆነ 38 አንቀፆች ያሉት ስምምነት በ177 አገራት መፈረሙን ዶክተሩ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ ስምምነቱን ካልፈረሙ ስድስት የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ገልፀዋል፡፡ በሲጋራ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሣደግና ለማስተማር የሚያስችሉ አዳዲስ ደንቦችና መመሪያዎች ለማፅደቅ በሂደት ላይ እንደሆነችም ተናግረዋል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ያፀድቀዋል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ መመሪያና ደንብ፤ ህዝብ በተሰበሰበባቸው ሥፍራዎች፣ በሆስፒታሎች፣ በአውቶቡሶችና የህዝብ ማጓጓዣ ትራንስፖርቶች ላይ ሲጋራ ማጨስን የሚከለክል ሲሆን በሆቴሎችና በመዝናኛ ሥፍራዎች ሲጋራ ለማጨስ የሚያስችሉ የተከለሉ ሥፍራዎች የማዘጋጀት ግዴታም የሚጥል እንደሆነ ታውቋል፡፡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ከበደ ወርቁ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን በቅርቡ አፅድቆ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በሲጋራ ማጨስ ሣቢያ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል ዋነኞቹ የልብ ህመም፣ የደም ግፊት መጨመር፣ ካንሰር፣ የአይን ሞራ ግርዶሽ፣ የጥርስ መበስበስ፣ የቆዳ መጨማደድ፣ የጨጓራ ቁስለት፣ የማስታወስ ችሎታ መቀነስ፣ የመሥራት አቅም መዳከም እና የራስ ፀጉር መመለጥ ጥቂቶቹ ሲሆኑ ከሲጋራ አጫሾች ጋር አብረው በመኖር ወይንም ሲጋራ በብዛት በሚጨስባቸው አካባቢዎች ላይ በመሆን የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ደግሞ የመተንፈሻ አካላት ህመም፣ ለደም መርጋት ችግሮች መጋለጥ፣ በሣንባ ካንሰር መያዝ፣ አስም፣ የዓይን የማየት ችሎታ መዳከም የልብ ህመምና የማስታወስ ብቃት መቀነስ ችግሮች ተዘውትረው መታየታቸውን የአለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
በሲጋራ ማጨስ ሣቢያ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ለማስወገድ አገሮች እንደየአገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ህጐችንና መመሪያዎችን እያወጡ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ የዓለም አገራት መካከል ጥቂቶቹን መጥቀስ ቢያስፈልግ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እንግሊዝና ሆላንድ ሰዎች በሚሰበሰቡባቸው ሥፍራዎች፣ በባቡር ጣቢያዎች፣ በአውቶቡስ መጠበቂያ ሥፍራዎች፣ በሲኒማና ቲያትር አዳራሾች፣ በሆስፒታሎችና በሕክምና ተቋማት እንዲሁም የተከለለ የሲጋራ ማጨሻ ሥፍራ በሌለባቸው ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ሲጋራ ማጨስ በህግ እንዲያስቀጣ ደንግገዋል። ይህንን መሰል ህጐች ህዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲጋራ እንዳይጨስ ለማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ቢኖረውም በየመኖሪያ ቤቱና በየመንገዱ ላይ ሲጋራ በማጨስ በሁለተኛ ወገን አጫሽነት የሚቆጠሩ ዜጐችን በሲጋራ ሣቢያ ከሚመጣ ችግር ሊታደጉ አይችሉም የሚሉ ወገኖች ሌላ መፍትሄ ይሰነዝራሉ፡፡ በግዮን ሆቴል በተካሄደው አውደ ጥናት ላይ፤ ይህንን ችግር ለማስወገድ በሲጋራ ላይ የሚጣሉ ታክሶችን ከፍ በማድረግ፣ አጫሾች ሲጋራ የመግዛት አቅማቸውን ማዳከሙ የተሻለ አማራጭ እንደሚሆንና በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት አበክሮ እንዲያስብበት ተጠቁሟል፡፡




Read 5923 times