Saturday, 14 December 2013 12:21

የባህር ዳር የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(9 votes)

“ለካ በራሳችን ራሳችንን መርዳት፣ ማሻሻል፣ መለወጥ እንችላለን አልን” አቶ አበበ ብርሌ

          በአውሮፕላን ባህር ዳር ከተማ ገብቼ ወደ ማረፊያዬ ሆቴል ሄድኩኝ፡፡ ባህር ዳር እንደወትሮው ሞቅ ደመቅ እንዳለች ናት፡፡ ከእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ድርጅት ተጠሪ ጋር ሆነን በመጀመሪያ እንድጐበኝ በተዘጋጀው ፕሮግራም መሠረት፤ ጐህ ለሁሉም ማህበረሰብ ልማት ማህበርን ለማየት ወደዚያው አመራሁ፡፡ ግሼ አባይ ቀበሌ ማህበር ካረፍኩበት ሆቴል ቅርብ ነው። የማህበሩን የሂሳብ ሹም አገኘሁ፡፡ ወደ ጽ/ቤታቸው እየሄድን የሠሯቸውን አንዳንድ ሥራዎች ለመቃኘት እየተዘዋወርን ነው። “ገቢ ማስገኛ ምን አላችሁ?” አልኩት፡፡ “ባጃጅና ለስላሳ ማከፋፈያ አለን” አለኝ፡፡

“ያቻትልህ ባጃጇ፡፡ ካፌም ልንከፍት ነው፡፡ አሁን ድሆች ሠራተኞችን ምልመላ ላይ ነን፡፡ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ልጆች ላይ ነው የምናተኩረው፡፡ ይሄ የምታየው የት/ቤት ቅፅር ግቢ ከ1-6 ድረስ ትምህርት ማጠናከሪያ ነው፡፡ እናስተምራለን፡፡ መምህራኑ በዲግሪና በዲፕሎም የተመረቁ ናቸው፡፡ የተወሰነ የኪስ ክፍያ እንከፍላቸዋለን፡፡ ይሄኛው መጋዘናችን ነው፡፡ ቢራ፣ ለስላሳ፣ ወይን ጠጅ የምናከማችበት ነው፡፡ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ናቸው ሠራተኞቹ፡፡ ተቀጥረው ለኛ ትንሽ ገቢ እየሰጡ ራሳቸውን እንዲችሉ የምናደርግበት ነው፡፡ ያችኛዋ የፎቶ ኮፒና የህትመት ሥራ የሚሠሩባት ያከራየናት ክፍል ናት፡፡

ዛሬ እሁድ ስለሆነ የሉም እንጂ በደምብ ይሠሩባታል፡፡ እቺም የገቢ ማስገኛ ናት!” “የተቋማቋማችሁት መቼ ነው?” አልኩት፡፡ በ1995 መጨረሻ አካባቢ ነው፡፡ ጥር ጀምሮ ራሳችንን ችለናል - 2005፡፡ ሠርቶ ሠርቶ እየሩሳሌም ወጣ በቃ! አስረክበውናል!” ወደሌላ ቢሮ እያሳየኝ፤“እቺኛዋ ባህር ዳር ከተማ ውስጥ ያሉ አቻ ማህበራት ጥምረት ፈጥረን የምንሠራባት የጥምረት ቢሮ ናት፡፡ የጋራ ችግሮችን እንፈታባታለን፡፡” “አንተ ወደ “ጐህ ለሁሉም” እንዴት ገባህ?” “ያኔ ያካባቢውን ችግር ለመፍታት እየሩሳሌም ይንቀሳቀስ ነበረ፡፡ ማህበረሰቡንና ቀበሌውን ሰብስቦ ሲያወያይ፤ በኤችአይቪ ዙሪያ ተተኩሮ፣ እናት አባታቸውን ያጡ ህፃናትን ለመርዳት ምን እናድርግ ሲባል፤ ሰው ይመረጥ - ፍቃደኛ የሆኑ ተባለ፡፡ ተመረጥን፡፡ እኛ ገባን፡፡ ፋብሪካ ነበር ፊት የምሠራው! አሁን የማህበሩ የሂሳብ ሹም ሆኜ ነው ይሄን የህል ዓመት የምሠራ!” “የጐጃም ሰው ነህ?” “አዎ፤ ይቺኛዋ ደግሞ የልማት አመቻቾች ቢሮ ናት” አለኝ ወደሌላ ቢሮ እየጠቆመኝ፡፡ ጽ/ቤቱ ቢሮ ገባን፡፡ የሂሳብ ሹሙ ሰብሳቢውን ሊጠራ ፈጥኖ ሄደ፡፡ ሰብሳቢው መጡና መጨዋወት ጀመርን፡፡ * * * የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ አበበ ብርሌ ዝግ ብለውና አስረግጠው ከመናገራቸው ባሻገር መንፈሰ ምሉዕነትና ቅንነት ይታይባቸዋል፡፡ “እስቲ ስለ ሁሉ ነገራችሁ እናውራ - ያጫውቱኝ” አልኩ፡፡ “አበበ ብርሌ እባላለሁ - የጐህ ለሁሉም ማህበረሰብ ልማት ማህበር ሰብሳቢ ነኝ፡፡

መጀመሪያ ማህበራችን ሲመሰረት በዚሁ በግሼ አባይ ቀበሌ ሶስት ቀበሌዎች ነበሩ፡፡ ራሳቸውን የቻሉ ልማት ማህበሮች ተመሰረቱ፤ በ95 መጨረሻ፡፡” “እንዴት?” “በተለይ ይህ ቀበሌ ቀደምት ነው - የባህር ዳር ከተማ ሲመሠረትና ሲጀመር ገበያው ሳይቀር የነበረ ነው፡፡ ገበያውን ተከትሎ ህዝቦች የሠፈሩበት ሲሆን አሁን ግድ ባህርዳር እየተለወጠችና እየተሻሻለች በመጣችበት ሁኔታ ላይ፤ አዲስ ቀበሌዎች የራሳቸውን ግንባታ እየገነቡ ሲወጡ፣ እዚህ ያለው ምንም አማራጭ የሌለውና በቀበሌ ቤት የሚኖር እጅግ ደሀ የሆነ ሰው ብቻ ስለቀረ፣ ከዚህም ውስጥ በኤች አይ ቪ ፣እናት አባት ያጡ ህፃናት ነበሩና ምን ይሁኑ ሲባል፤ ቁጥራቸውም ከፍ እያለ በመሄዱ፤ ይህንን ሁኔታ ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ ችግሩን ለመፍታት፣ ሊቋቋም ችሏል፡፡” “እየሩሣሌም ድርጅትስ ያኔ እዚህ ነበር እንዴ?” “እየሩሳሌም ድርጅት መጀመሪያ በእኛ ውስጥ አልነበረም። የነበረው ቀበሌ 12 ላይ ነው፡፡ የቀበሌውን አቅም እየገነባ ህዝቡ እየተረባረበ ነበር፡፡ ያንን ስናይ ለካ በራሳችን ራሳችንን መርዳት፣ ማሻሻል መለወጥ እንችላለን አልን፡፡ የራሳችንን ችግር በራሳችን ለመፍታት ይቻላል፤ አልን፡፡ አመንን፡፡ ያለምንም ደጋፊ አካል መቋቋም ጀመርን። የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (እህማልድ) ወደኛ መምጣት ጀመረ፡፡

ታሪካዊ አመጣጡ ማህበረሰቡ ቀበሌ 12 ዕድገት እያሳየ ነበረና መንፈሳዊ ቅናት ፈጠረ፡፡ እኛም‘ኮ የበለጠ ለመንቀሳቀስ እንችላለን ተባባልንና ስብሰባ ተጠራ አለቀ፤ ተመረጥን፡፡ ለበጐ አድራጐት ተመረጥን። 7 ሥራ አስፈፃማዎች መጣን፡፡ ተመሠረተ፡፡ ትኩረታችን ወላጅ ባጡ ህፃናት ላይ ነው፡፡ አንድ አመት ቆየን መዋጮ ለማዋጣት እየሞከርን፡፡ በተለይ ልጆቻቸው ሞተው የተቀመጡ ሰዎች አሉ። የልጅ ልጅ ይዘው የቀሩ አሳዛኝ ሰዎች አሉ፡፡ የልጅ ልጅ ይዘው ራሳቸውን እንኳ ማስተዳደር የማይችሉ ምስኪን አያቶች አሉ። ከአያትና ከጐረቤት ጋር የሚኖሩ 23 ልጆች መርጠን ተነሳን። የአመራረጣችን መስፈርት ምንድን ነው? ሁለቱንም ያጡ፣ አንደኛውን ያጡ፣ እያልን ነው፡፡ ከዛ እየሩሳሌም መጣ 4 ፕሮግራሞችን ይዞ!” “ምን ምን?” “ወላጅ ላጡ ህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ፣ ከዛ በትምርት ዘርፍ፣ ቀጥሎ የጤና፣ ከዛ የከተማ ግብርናና የኑሮ ማሻሻል!! ያን ይዘን ፕሮግራሙን ማስኬድ ጀመርን፡፡ ፕሮግራሙን ማስኬድ ማለት እንዴት ነው? ከ1-6 የሚማሩትን ከመንግሥት ት/ቤት ብቻ መርጠን ማጠናከሪያ እንዲያገኙ አደረግን፡፡” “ለምን ከመንግሥት ት/ቤት ብቻ?” አልኳቸው፡፡ “ምክንያቱም በመንግሥት ትምህርት ቤት በነፃ የሚማሩት አብዛኞቹ ገንዘብ የመክፈል አቅም የሌላቸው ስለሆኑ፤ የእኛ ዓላማና ትኩረት ደግሞ፤ የተቸገሩትን ለይቶ መርዳት ስለሆነ፤ እነሱን ብቻ አጥርተን ወስደን ነው ማጠናከሪያ ትምህርት እንዲያገኙ ያደረግነው፡፡

መጠናከሪያ ት/ቤቶችን፣ በየቦታው በቀርክሃ የተሠሩ ሼዶችን፣ የጥላ ከለላ ት/ቤቶችን ሠራን፡፡ የተማሪዎች በተለያየ ቦታ መቀመጥ የመቆጣጠር ችግር ስለፈጠረብን ወደ አንድ ትልቅ ሼድ ባንድ አካባቢ ባንድ ጥላ ጠቅላላ ሥር አደረግናቸው፡፡ ቀበሌውና መስተዳድሩ አንድ ቦታ ሰጠን፡፡ እየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ደግሞ ክፍሎቹን ሠራልን፡፡ ከ1ኛ -6ኛ ክፍል የዲግሪና የዲፕሎማ ደረጃ ባላቸው መምህራን የትምህርት ማጠናከሪያ ያገኛሉ ማለት ነው፡፡ በሚያርፉበት ፈረቃ ነው መጠናከሪያው የሚሰጣቸው፡፡” ቅንጅቱ ገረመኝ፡፡ መንግሥት፣ እየሩሳሌምና ማህበረሰቡ! “ጤናም አለ፡፡ ያካባቢ ንጽህና ኮሚቴ አቋቁመን በቡና ጠጡ ፕሮግራም ከእየሩሣሌም በሚደረግንል ድጋፍ በሣምንት አንድ ቀን፤ በየሠፈሩ፣ በየተራ ይጠራሉ፡፡ እዛ ላይ ስለ ኤች አይ ቪ፣ ስለተላላፊ በሽታዎች፣ ስለ አካባቢ ንጽህና፤ ትምህርት ይሰጣል፡፡ በራሪ ጽሑፎች ይነበባሉ፡፡ ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ ቤቶች ውስጥ ላሉ አቅመ ደካማ አረጋውያን ፤ ሊፈርሱ የደረሱ ቤቶች እንዲታደሱላቸው ይደረጋል፡፡ በክረምት የሚያፈሱ፣ በበጋ ፀሐይ የማይከልሉ ቤቶች ከቀበሌው ጋር ዞረን መርጠን ነው። እስካሁን ወደ 17 ቤቶችን ጠግነናል፡፡ ባለ 8 ክፍል ሻወር ቤት ሠርተናል። ለጤና ጠቃሚ ነው፣ ገቢም አለው፡፡ ባካባቢው ካሉት ዝቅ ባለ ዋጋ ለችግረኛው ማህበረሰብ ሲባል፤ ያገለግላሉ፡፡ መፀዳጃ ቤትም ገንብተናል፡፡ በተለይ የኛ ማህበረሰብ የገነባውን ሽንት ቤት ልዩ የሚያደርገው፤ አካል ጉዳተኞችንም ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ነው! ለምሳሌ በዊል ቼር በቀጥታ ሊገቡ የሚችሉበትና መቀመጪያውም ለነሱ በሚያመች ተጠንቶ የተሠራ መሆኑ ነው። ህብረተሰቡ ተራ በተራ እያፀዳ ንጽህናውን ይጠብቃል፡፡ የኑሮ ማሻሻያና የከተማ ግብርናም እንደዚሁ፡፡

“የኑሮ ማሻሻያ ማለት ምን ማለት ነው” አልኳቸው፡፡ “ለምሳሌ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑትን ሴቶች በማነቃቃት ብድር በመስጠት በተዘዋዋሪ ፈንድ መደገፍ ነው፡፡ የኑሮ ማሻሻያ ይሄው ነው፤ ሌላ ትርጉም ነገር የለውም፡፡” አሉኝ ፍርጥም ብለው፡፡ “ደሞ ኑሯቸው በእርግጥ ተሻሽሏል እልሃለሁ!” በከተማ ግብርናም በኩል፤ ባለቻቸው ቦታ ላይ ዶሮ፣ በግ እንዲያረቡ ሆነዋል፡፡ በእየሩሣሌም በኩል ይሰለጥናሉ። እኛ መልምለን እንልካለን፡፡ በእርግጥ በመሥፈርት ነው፡፡ ትኩረታችን ሴቶች ላይ ነው፡፡ ከዚያ የዶሮ ቤት እንዲሠሩ እገዛ ይደረግላቸዋል። ሚስቶቻቸው የሞቱ ልጆች ይዘው ቀርተው ያሉ ወንዶችም አሉ፡፡ እነሱንም፣ ሚስቶቻቸውንም እንደግፋለን። በእርግጥ በዚህ በኩል ጥሩ ሁኔታም ይታያል፡፡ ደካማ ጐንም ይታያል፡፡ ለስላሳ፣ ቢራ፣ አምቦውሃ እናከፋፍላለን፡፡ አሁንም በዝቅተኛ ዋጋ ለዝቅተኛ አከፋፋዮች፡፡ እነሱም እኛም እንጠቀማለን፡፡ አንዲት የሻይ ክበብ ሠርተናል፡፡ ዓላማችንን አንስትም አየህ፡፡ 3 ወጣቶች ሴቶች ሥራ የሌላቸው መልምለን ሥራ ማስያዝ ነው፡፡ ራሳቸውም ፈጠራ ጨምረው ከኛ ተረክበው እየሸጡ ራሳቸውን መቻል ነው ትልቁ ነገር!! ሌላው ጄክዶ - ሲዳ የገዛልን ባጃጅ ናት። እሷ አሁን በቀን 100 ብር ታስገባለች፡፡ የህዝቡ መዋጮም አለ፡፡ ገና ስንነሳ ያለን አላማ!!” “ትዘልቁ ይመስላችኋል?” “እርግጥ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ በጣም ሰፊ ነው። እንደውም ያኔ እየሩሳሌም ከጐናችን ባይቆም ኖሮ እምንዘልቀው አይሆንም ነበር፡፡

ሁለተኛ፤ የበጐ ፈቃደኝነት ስሜት ደሞ በጣም ያጥራል፡፡ ምርጫ ስናደርግ “እኛ በቃን ስንል፤ “እንዴ እናንተ ከለቀቃችሁማ ማህርበረሰቡና ገንዘቡ የትም ይውደቁ ማለታችሁ ነው ወይ” ይላሉ፡፡ ይሄ ግን በእኛ ስንረዳው ሁለት መልዕክት አለው (1) ምናልባት ከልብ የምንሠራውን ሥራ ተቀብለውት አምነውበት ሊሆን ይችላል (2) ሌላ ትንሽ የማይባለው ቁጥር፤ ምናልባት ቆንጆ ብቃትና ችሎታ ያለው ሆኖ ወደዚህ ሃላፊነት ግባ እንዳይባል ሌላውን እየገፋፋ እኛን እዚሁ ቆዩ እንዲለን ያደርግ ይሆናል፤ የሚል ግምት አለኝ! በፍቅርና በእኛ ሥራ በማመን ብቻ ነው ያቆዩን የሚል ዕምነት የለንም! ሌሎችን ደሞ እንሞክር መባል አለበት፡፡ ዕውነት እንንገርህ ምንም ዓይነት የታክሲ የምን የምን የሚሰጥ ነገር የለም፡፡ ፈንድ ሲገኝ ለስልክና ለአንዳንድ ወጪዎች ማካካሻ ተብላ የምትሰጥ ሣንቲም አለች፡፡ ያ ከሌለ ያለምንም እንሠራለን፡፡ ጊዜው ሲረዝም ግን እየቀዘቀዙ መሄድ አለ፡፡ አመቻቾች ብዙ ሥራ ይሠራሉ፡፡ ተዘዋዋሪ ብድር እንሰጣለን፡፡ ሆኖም እናጣራለን፡፡ ከሌላ አካባቢ ወስደው ቢሆን ገንዘቡ ወጥቶ መቅረት የለበትማ!” “የማኅበራት ጥምረት አላችሁ?” “10 ማኅበራት አሉ፡፡ ጐህ ለሁሉ ፀሐፊ ነው” “Experience Sharing (የልምድ ልውውጥ) እንዴት ነው?” “አዎ፡፡ አዳማ፣ ደብረዘይት፣ ድሬዳዋ፣ ወረታ፣ ሐሙሲት፣ እንድብር፣ ወልቂጤ… መዓት ነው የሄድንበት፡፡ የእየሩሳሌም ባህርዳር ፕሮግራም ጽ/ቤት፤ ቀበሌዎች፤ አቻ ማህበረሰብ፣ አንድ ላይ አቀላቅሎ ለልምድ ልውውጥ ይዞን ይሄዳል። የዕድሮችን ህብረት ቅንጅት ልዩ ልዩ ዘርፎችን እንቅስቃሴ በማየታችን እኛም ተጠቅመናል፣ እነሱም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ “ግን በብዛት ጐጃም ሄደን ልምድ አግኝተናል ብለውኛል። ይሄ ልዩ ምክንያት ይኖረው ይሆን?” “እንደ ፕሮግራም ጽ/ቤቱ ጥናት ነው፡፡

አንዱ ጋ የጐለበተ ልምድ፣ ሌላ ጋ ደካማ ሊሆን በመቻሉ በፕሮግራም ተጠንቶ የሚኬድበት ነው፡፡” “ጄክዶ ብቻ ነው እናንተም መክራችሁ ትንቀሳቀሳላችሁ?” “እኛም አጥንተን ፕሮግራም ይዘን ፕሮጀክት እንቀርፃለን። አንዳንዴም ፕሮግራም ጽ/ቤቱ ራሱ ያዘጋጃል፡፡ የእኛን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ብዙ ድርጅቶች አሉን፡፡ ጄክዶ Phase out ካረገ በኋላ እኛ ነን የምንከታተላቸው ገንዘብም ምደባ ላይ እንሠራለን። ካፒታል አላቸው፡፡ ሂሳቡን የእኛ ማህበር ይሠራላቸዋል፡፡ ከራሳቸው መልምለው የሚሰጡንን መንግሥት እንዲያውቅ ይደረጋል። ወጣቶችን በሙያ እናሳድጋለን፡፡ ለምሳሌ አራት ወጣቶች በሹፌርነት አሰልጥነናል፡፡ የፀጉር ሥራ፣ የኤሌክትሪክ ጥገና፣ የምግብ ዝግጅት ሥልጠና እንዲያገኙ እንጥራለን፡፡ (ይቀጥላል)

Read 4909 times