Saturday, 14 December 2013 13:10

የማንዴላ ሌላኛው ገፅታ!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(4 votes)

በአይሁዶች ሚሽናህ ውስጥ “በእድሜ ዘመኑ የሰዎችን ልብ ደስ ለሚያሰኝ መልካም ስራ የተጋ፣ እነሆ የሌሎችን ቀንበር የተሸከመ፣ ከእርሱም ታላላቆችና ታናናሾች ለሆኑ ለወንዶችም ለሴቶችም ጠዋት በሆነ ጊዜ እንደሚገኝ ብርሃን የሆነ፣ እርሱ በሞቱም እንኳ ቢሆን በአምላክና በሰዎች ዘንድ እጅግ ይከብራል፣ ወደ ላይም ከፍ ከፍ ይላል፡፡” የሚል ቃል ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ይህ ቅዱስ ቃል በኔልሰን ማንዴላ ተፈጽሞ እነሆ በዘመናችን ለማየት በቅተናል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ መላ ደቡብ አፍሪካውያን ከፍ ባለ አክብሮትና ፍቅር “ማዲባ” እያሉ የሚጠሯቸው ኔልሰን ማንዴላ፤ በረጅሙ የትግል ህይወታቸው የፈፀሙት ስራ በመላእክት እንጂ በስጋ ለባሽ ሰው የሚፈፀም አይመስልም። የዘር መድልዎና የጭቆና አገዛዝ ቀንበር ተሸክመው፣ ወደር የሌለው ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉበት ያ ረጅሙና እጅግ አስቸጋሪው ጉዞአቸው ለዘመናት ሲገፋ ለኖረው ሰፊው ህዝባቸው፤ ከማለዳ ጀንበር በብዙ እጥፍ የደመቀ የነፃነትና የእኩልነት ብርሃን አብርቶላቸዋል፡፡
“የማይናወጥ ጽኑ እምነት ያለው ተራሮችን ማንቀሳቀስ ይችላል” ተብሎ በቅዱስ መጽሐፍ እንደተጠቀሰው፣ ለእኩልነትና ለአንድነት የነበራቸው መቼም የማይናወጥ ጽኑ እምነት፣ ቀናቶች ሁሉ እስኪያልቁ ድረስ ይገረሰስ የማይመስለው የአፓርታይድ የዘር መድልዎና የጭቆና አገዛዝ፣ እግራቸው ስር አይሆኑ ሆኖ እንዲፈረካከስ አድርጐታል፡፡
ከመላእክት እንጂ ከሰው ልጆች መቸም ቢሆን እንዲህ እንደዋዛ በማይገኘው እፁብ ድንቅ ርህራሄአቸውና ፍፁም ይቅር ባይነታቸው፣ ከዚህ በፊት የትም ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ፣ የህዝባቸውን የደቡብ አፍሪካውያንን ብቻ ሳይሆን ድፍን የአለማችንን ህዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ በከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት መማረክ ችሏል፡፡ እነሆ በሞታቸውም ጊዜ ቢሆን በአምላካቸው ፊት በእጅጉ ተከብረው፣ በሰው ልጆች ዘንድም  አቻ በሌለው ከፍተኛ ፍቅርና ክብር እንደ ንስር ወደ ላይ፣ ወደ ሰማይ ከፍ፣ እጅግ ከፍ ብለዋል፡፡ ለዘጠና አምስት አመታት ያህል የዘለቀው የኔልሰን ማንዴላ ረጅም የትግል ህይወት፤ በችግርና በፈተና፣ በጽናትና በአይበገሬነት፣ በውድቀትና በድል ታሪኮች የተሞላ ነው ብሎ በቀላሉ መናገር ምናልባት የአንባቢን ንቃተ ህሊና አሳንሶ እንደመገመት ሊቆጠር ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእሳቸው የህይወት ታሪክ እንደነዚህ ባሉ ታሪኮች የተሞላ መሆኑን ድፍን አለሙ በሚገባ ያውቀዋልና፡፡  
ኔልሰን ማንዴላ፤ በአፓርታይድ አገዛዝ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸው ሮቢን ደሴት በሚገኘው ጥብቅ ወህኒ ቤት ውስጥ ለሀያ ሰባት አመታት በእስር የማቀቁት የቀለም ትምህርት አሊያም የሙያ ክህሎት ስልጠና በመውሰድ ሳይሆን የኖራ ማዕድን በመቆፈር ነበር፡፡ ይህም ለተለያዩ የእፎይታና የመተንፈሻ አካላት በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ አጋልጧቸዋል፡፡ ከሀያ ሰባት አመታት አስከፊ የእስር ቅጣት በሁዋላ ተፈተው፣ የሮቢን ደሴት ወህኒ ቤትን ለቀው ሲወጡ፣ ሳምባቸው በኖራ ብናኝ ክፉኛ ተጎድቶ በከፍተኛ የመተንፈስ ችግር እየተሰቃዩ ነበር፡፡ ይህም ብቻ አልነበረም፡፡ እስር ቤት ከገቡ ከአስራ አራተኛው አመት ጀምሮ ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ የእንባ አመንጪ እጢያቸው በኖራና በአስቤስቶስ ብናኝ ሙሉ በሙሉ በመጎዳቱ፣  ስሜታቸውን እንባ አውጥተው በማልቀስ መግለጽ አይችሉም ነበር፡፡
የቀድሞው የኬጂቢ ኮሎኔል፣ የዛሬው የራሺያ ቆፍጣና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ ስለ ራግቢ ጨዋታ የፈለገውን ያህል ቢያወሯቸው ጨርሶ አይሞቃቸውም አይበርዳቸውም። የጂዶ ጨዋታን ነገር ካነሱላቸው ግን መላ ስሜታቸው የሚነቃውና ሰውነታቸውን የሚነዝራቸው ከመቅጽበት ነው።
የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜም የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ነፍሳቸው ነው፡፡ አደባባይ ወጥተው ሲጫወቱ አይታዩ እንጂ የእረፍት ጊዜአቸውን በአብዛኛው የሚያሳልፉት ከመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ ከልጃቸው ጋር ነጭ ላብ እስኪያልባቸው  ድረስ የቅርጫት ኳስ በማልፋት ነው፡፡ እርግጥ ነው ማዲባ እንደ ቭላድሚር ፑቲን ጂዶ ሲታገሉ ወይንም እንደ ፖል ካጋሜ በመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ ከልጆቻቸውና ከልጅ ልጆቻቸው ጋር የቅርጫት ኳስ ሲጫወቱ ታይተው አያውቁም፡፡ ልጫወት ቢሉም የማያወላዳው ጤናቸው፣ ከተጫጫናቸው እርጅና ጋር ተዳምሮ ይህን መሰሉን እድል እንዳልሰጣቸው ይታወቃል። ይሁን እንጂ ሀገራቸው የአፍሪካና የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ እንዲሁም የራግቢ የአለም ዋንጫ ውድድሮችን እንድታዘጋጅ ያደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ፣ አዘጋጅ ከሆነች በኋላም የሀገራቸውን ብሔራዊ የእግር ኳስና የራግቢ ቡድን ማሊያ ለብሰው ውድድሩ በሚካሄድበት ስታዲየም በመገኘት የሰጡት የሞቀ ድጋፍ፣ ብዙዎች ማንዴላ የእግር ኳስና የራግቢ ስፖርት ቅልጥ ያለ ደጋፊ ናቸው ብለው እንዲገምቷቸው አድርጓል፡፡
እውነቱ ግን ይህ አይደለም፡፡ ኔልሰን ማንዴላ የእግር ኳስም ሆነ የራግቢ ጨዋታ አድናቂ አልነበሩም፡፡ እርሳቸው የሚወዱትና የሚያደንቁት የስፖርት አይነት ቦክስና የረዥም ርቀት የሩጫ ውድድሮችን ብቻ ነበር፡፡ ሀያ ሠባት አመታትን ባሳለፉበት የሮቢን ደሴት ወህኒ ቤት ውስጥ ኖራና አስቤስቶስ ለመቆፈር ዶማና አካፋቸውን ይዘው ከመውጣታቸው በፊት ዘወትር ጧት ጧት የቦክስ ልምምድ ያደርጉ ነበር፡፡
“ረዥሙ የነፃነት ጉዞ” በሚል ርዕስ ባሳተሙትና የህይወት ታሪካቸውን በተረኩበት መጽሀፍ ውስጥ የቦክስ ስፖርትን ሲገልፁ “የቦክስ ስፖርት ሳይንሱ እንጂ ድብድቡ አዝናንቶኝ አያውቅም፡፡ አንዱ ራሱን ለመከላከል እንዴት ሰውነቱን እንደሚያንቀሳቅስ፣ ሌላው ደግሞ ለማጥቃትና ለመከላከል እንዴት ያለ ስትራተጂ እንደሚጠቀም፣ አንዱ ሌላኛውን እንዴት እንደሚቀድመው ሳይ ግን በጣም እገረም ነበር” በማለት ጽፈዋል፡፡
ለኔልሰን ማንዴላ የቦክስ ስፖርት ከዚህ ያለፈ ሌላ ትርጉምም ነበረው፡፡ ይህንንም በመጽሃፋቸው እንዲህ በማለት ገልፀውታል:- “የቦክስ ስፖርት ነፃና ዲሞክራሲያዊ ነው፡፡ በቦክስ ሪንግ ውስጥ ማዕረግ፣ እድሜ፣ ቀለምና ሀብት ምንም ቦታ የላቸውም፡፡ ፖለቲከኛ ከሆንኩ በኋላ የምሬን ተቧቅሼ አላውቅም፡፡ ዋናው ፍላጐቴ ልምምዱ ላይ ብቻ ነበር፡፡ አድካሚው ልምምድ ጭንቀትና ውጥረትን ማስተንፈሻ ድንቅ መሳሪያ ሆኖልኝ ነበር፡፡ ከባድ የቦክስ ልምምድ ካደረግሁ በኋላ አዕምሮዬንም ሆነ አካሌን ቅልል ይለው ነበር”
ኔልሰን ማንዴላ ለቦክስ ስፖርት የነበራቸውን ስሜት በመጽሀፋቸው ላይ በይፋ ከመግለፃቸው በፊት ዋልተር ሲሲሉስን ከመሳሰሉት የቅርብ የትግልና የእስር ቤት ጓዶቻቸው በቀር የሚያውቅ ሰው እምብዛም አልነበረም። የአለም የቦክስ ሻምፒዮን የነበረው አሜሪካዊው ሹገር ሬይ ሊዎናርድ፣ የአለም ሻምፒዮንነት ክብር የተቀዳጀበትን ቀበቶ በስጦታ ያበረከተላቸውም ይህንን ታሪካቸውን ጨርሶ ሳያውቅ ነው፡፡ ሹገር ሬይ ሊዎናርድ ያበረከተላቸው ይሄው የሻምፒዮንነት ቀበቶ፣ ሶዌቶ በሚገኘው የኔልሰን ማንዴላ ቤተሰብ ሙዚየም ውስጥ ተቀምጦ በጐብኝዎች እየታየ ይገኛል፡፡  ዛሬ ኔልሰን ማንዴላ የሚለው ስም በአለማችን አራቱም ማዕዘናት እንደ ጉድ የናኘና በቢሊዮን በሚቆጠሩ የአለማችን ህዝቦች ዘንድ በሚገባ የታወቀ መሆኑን አሌ ብሎ መከራከር ጨርሶ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ከ1926 ዓ.ም በፊት ግን የማንዴላ ወላጆች ሮሊህላህላ ማንዴላ እንጂ ኔልሰን ማንዴላ የሚል ስም ያወጡለት ወይም በዚህ ስም የተመዘገበ ልጅ አልነበራቸውም፡፡ ለሁሉም ተማሪዎች የክርስቲያን ስም ማውጣት ይገባል በሚል ኔልሰን የሚለውን ስም ያወጣላቸው፣ የዘጠኝ አመት ብላቴናና የሜቶዲስት ቤተክርስቲያን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሆነው ያስተምራቸው የነበረ መምህራቸው ነበር፡፡
ኔልሰን ማንዴላ ሲገረዙ የወጣላቸው ስም ዳሊ ቡንጋ የሚል ሲሆን ትርጉሙም የባህላዊው የቡንጋ አመራር አካል መስራች ማለት ነው፡፡ በአብዛኛው ደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ በአክብሮት የሚጠሩበት “ማዲባ” ደግሞ የሚለው የጐሳ መጠሪያ ስማቸው ነው፡፡
ለኔልሰን ማንዴላ በተዘጋጀው የመታሰቢያ ስነ ስርአት ላይ ንግግር ካደረጉት መሪዎች አንዱ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ናቸው፡፡ እሳቸውም ኔልሰን ማንዴላ ለነፃነት ሲሉ የከፈሉትን መስዋዕትነት በማውሳት፣ አለም ከእሳቸው ህይወት ጠቃሚ ልምድ ሊቀስም ይገባል ብለዋል፡፡  እንደ እውነቱ ከሆነ እንደ ግለሰብ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ያደረጉት ንግግር እንከን የለሽ ነው፤ እንደ ሀገር ከታሰበ ግን በጣም ኮሚክ ነው። ለምን ቢባል የአፓይታይድን ስርአት ሲያራምድ ከነበረው የደቡብ አፍሪካ የነጮች መንግስት በበለጠ የኔልሰን ማንዴላን የነፃነት ትግል የተቃወመች፣ በመጨረሻም ኔልሰን ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ የተሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና ጨርሰው ሀገራቸው እንደገቡ እግር በእግር ተከታትላ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ፣ ከዚያም የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖባቸው ለሀያ ሠባት አመታት በወህኒ ቤት እንዲማቅቁ ያስደረገችው አሜሪካ ስለነበረች ነው፡፡ ይህም አልበቃ ብሏት እስከ 2008 ዓ.ም ደረስ ኔልሰን ማንዴላንና ይመሩት የነበረውን የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ በአሸባሪና በአሸባሪ ድርጅትነት መዝግባ ይዛቸው ነበር፡፡  
ኔልሰን ማንዴላ፤ ኮልፌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ለስድስት ወር የተሰጣቸውን ወታደራዊ ስልጠና አጠናቀው ሲመረቁ፣ ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሽልማትም፣ ማስታወሻም የሚሆን አንድ ሽጉጥ ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ ይህንን ሽጉጥ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት አንድ ሰዋራ ቦታ ላይ ቀብረውት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከቀበሩበት ፈልገው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ሽጉጡን ፈልጐ ማግኘት ከቻለ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ ቢሉም ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ አገኘሁ ያለ የለም፡፡ 

Read 7885 times