Saturday, 14 December 2013 13:28

“...ምንም እናት ሞታ አታውቅም...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ በተለያዩ መስተዳድሮች አዲስ አበባን ጨምሮ ከተወሰኑ የግል የህክምና ተቋማት ጋር ይሰራል፡፡ ከመስተዳድር አካላቱም በአማራው ክልል የደብረማርቆስን እና ባህርዳርን እንቅስቃሴ በመመልከት ከፊሉን ከአንድ ሳምንት በፊት በወጣው እትም ያስ ነበብን ሲሆን ዛሬ በባህርዳር ያለውን እንቅስቃሴ እናስነብባችሁዋለን፡፡ ቀደም ሲል በወ ጣው ዘገባ በአማራው ክልል ከESOG ጋር ከሚሰሩ የህክምና ተቋማት መካከል በጸጋ ሆስፒታል ይገኝበታል ተብሎ የተገለጸውም አለም ሳጋ ሆስፒታል በሚል እንዲ ታረም ልን እንጠይቃለን፡፡   
ዶ/ር መኮንን አይችሉህም የጋምቢ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅና ከመስራቾች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ ስለሆሰፒታሉ ሲገልጹ...
“...የጋምቢ ሆስፒታል አመሰራረት ረጅም ነው። በቅድሚያ ስራ የጀመረውም በአነስተኛ ክሊኒክ ሲሆን አመሰራረቱም  አብረን የተማርን ጉዋደኛሞች ስለሕክምና አገልግሎት በተለያየ አጋጣሚ በምናደርገው ውይይት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ይህን ሆስፒታል እንዲመሰረት ያበቃነው ስድስት የሙያ ባልደረቦች በተለያየ ቦታ በጤናው ዘርፍ በኃላፊነት ስንሰራ የነበርን ስንሆን በመስኩ ያለውን አገልግሎት በሚመለከት የምናው ቃቸውን ችግሮች እኛ ስራውን ብንጀምር ምን ያህል ህብረተሰቡን ለማርካት እንችላለን ከሚል በመነሳት ከብዙ ውጣ ውረድ በሁዋላ እነሆ ሆስፒታሉን እውን አድርገናል፡፡”
በጋምቢ ቲቺንግ ሆስፒታል ያገኘናቸው የጽንስና ማህጸን  ሕክምና ባለሙያ ዶ/ር አየነው በላይ ይባላሉ። እሳቸው እንደሚገልጹት የእናቶች ሕክምና በተሟላ መልኩ የሚ ሰጥ ሲሆን በኦፕራሲዮን ወይንም በተፈጥሮአዊ መንገድ የሚወልዱት እናቶች በወር በአማካይ ወደ 25/ይደርሳል፡፡ በእርግጥ ቀደም ሲል ይህ ቁጥር ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን መንግስት የእናቶችን ሕክምና በነጻ እና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሰራ ስላመቻቸ አብዛኛዎቹ እናቶች የእርግዝና ክትትላቸውን ከጨረሱ በሁዋላ ሪፈራል ተጽፎላቸው ወደ መንግስት ሆስፒታል  እየሄዱ መሆኑ ታውቆአል፡፡ ይህ ደግሞ እጅግ የሚያበረታታ ሲሆን በጋምቢ ሆስፒታል ለመውለድም ሆነ ለመታከም የሚመጡትም ምንም ቅሬታ በሌለው ሁኔታ መስተንግዶ እያገኙ ነው ብለዋል፡፡
በሆስፒታሉ ያገኘናት እርጉዝ ሴት የእርግዝና ክትትልዋን ለማድረግ የመጣች ናት፡፡ ስሙዋ ደጅይጥኑሽ ሳህሌ ይባላል፡፡
“...እኔ የመጣሁት ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በእርግጥ ከአሁን ቀደም ወደቤተሰብ መምሪያ ሄጄ ነበር፡፡ ነገር ግን ምርመራውን በሚገባ ለማከናወን ከዚህ መምጣትን ልቤ ስለፈቀደ ከባለቤ.. ጋር ተመካክረን መጥቻለሁ፡፡ አሁን ስድስት ወር ቢሞላኝም እንደአዲስ ምርራውን እያደረጉልኝ ነው፡፡ ስለዚህም የኢችአይቪ ቫይረስ በደሜ ውስጥ መኖር አለመኖሩ ገና ውጤ..ን አልሰማሁም፡፡ ቫይረሱ ከደሜ ውስጣ ባይኖር ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አለ ከተባለም ከባለቤ.. ጋር ተመካክረን ሐኪሞች በሚነግሩን መሰረት ክትትል ማድረግ እንጂ አሻፈረኝ ማለት አይገባም፡፡ ቅድሙኑም መጠንቀቅ ነበር እንጂ ከሆነ በሁዋላማ የሚበጀውን ከማድረግ በቀር ከራስ ጋር ሙግት ምን ያረጋል?”
ይህች እናት ከላይ ያነበባችሁትን መልስ ስትሰጥ በፊትዋ ላይ ምንም የቅሬታ ምልክት አይታይባትም ነበር። ሐኪሞቹም ጥሩ ጎን ብለው የሚገልጡት በኤችአይቪ ቫይረስ ላለመያዝ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ሲሆን ከሆነ በሁዋላ ግን በሕክምናው ዘርፍ ሊደረግ ለሚገባው ክትትል ሙሉ ተባባሪ መሆን ይገባል፡፡
ዶ/ር አየነው በላይ እንደሚሉት “...በህብረተሰቡ ዘንድ ሙሉ  በሙሉም ባይሆን በከፍተኛ ደረጃ የግንዛቤ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበሩት አመታት አንዲት ሴት ለእርግዝና ክትትል መጥታ ቫይረሱ በደምዋ ውስጥ ሲገኝ ለማ ስረዳት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር የሚታወስ ነው። ውጤቱ በሚነገ ራቸው ሰአት ይታይ የነበረው ፍርሀት እና እራስን መደበቅ እንዲሁም ከህክምናው እስከመራቅ ድረስ የመድረስ ሁኔታ ይታይ ነበር፡፡ አሁን ግን እንደዚህ ያሉ ሁኔታዎች ቀርተዋል፡፡ ብዙዎች ምርምራውን በሚያደርጉበት ሰአት የምክር አገልግሎት ሲሰጣቸው የሚያሳዩት ምላሽ ለሕክምናው አገልግሎት ምቹ ይሆ ናል፡፡ ምክንያቱም በትክክል ከሐኪሙ የሚነገራቸውን በተግባር ላይ ስለሚያ ውሉ የራሳቸውን ጤና ከመጠበቅ ባሻገር ከቫይረሱ ነጻ የሆነ ልጅን ለማፍራት ይችላሉ፡፡ ዶ/ር አየነው እንደሚገልጹት በጋምቢ ሆስፒታል ለክትትል ከመጡት እናቶች ውስጥ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩት ከ2%  አይበልጡም፡፡ ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ በመንግስት የወጣውን መመሪያ በመከተል አስፈላጊውን ክትትል ስለሚደረግላቸውም እስከአሁን ድረስ ባለኝ መረጃ መሰረት በቫይረሱ የተያዘ ወይንም ከቫይረሱ ጋር የተወለደ ሕጻን በሆስፒታላችን የለም ማለት ይቻላል፡፡ እንደ ዶ/ር አየነው ምስክርነት በጋምቢ ሆስፒታል የእናት ሞት አጋጥሞ አያውቅም፡፡
ዶ/ር ቴዎድሮስ ማለደ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የPMICT ፕሮጀክት የአንድ ቡድን አስተባባሪ ሲሆኑ በአማራው ክልል በተካሄደው የስራ ጉብኝት ወቅት የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡
“...በቅርብ ጊዜ መንግስት ይፋ ያደረገው (Option B+) ኦፕሸን ቢ ፕላስ የመድሀኒት አጠቃቀም ከተጀመረ ወዲህ ጥሩ እመርታ እየታየ ነው፡፡፡ አንዲት እናት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ከሆነች ለእራስዋም ጤንነት እና ልጅዋንም ከቫይረሱ ነጻ ሆኖ እንዲወለድ ለማስቻል ወዲያውኑ ወደህክምናው እንድትገባ ይደረጋል፡፡ ከዚህ በፊት ግን ሲዲ ፎርን የማየት ወይንም እናትየው እስኪብስባት ክሊኒካል እስ..ጅ እስከሚባለው የመጠበቅ አካሄድ እንዲቀር ተወስኖአል፡፡ ይህ አሰራር እናቶችን ከተወሳሰበ የህክምናው አሰራር ግልጽ ወደሆነው እንዲመጡ በማድረጉ ችግሩን ቀርፎታል፡፡ በአማራው ክልል ከኢሶግ ጋር የሚሰሩ የግል የህክምና ተቋማትን አሰራር እንዳየነው ከሆነ የእናቶችን ታሪክ ምስጢራዊነት በጠበቀ መልኩ አስፈላጊውን የምክር አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ተገቢውን ሕክምና በማድረግ አብዛኛዎቹ እናቶች በመረጡት መንገድ እየተስተናገዱ የሚገኙበትን አሰራር ተመልክተናል፡፡ ቀደም ሲል ከነበረው በተሻለ መንገድ ብዙ እናቶች ወደሕክምናው እየገቡ መሆኑንም ለመመልከት ተችሎአል፡፡” ብለዋል፡፡
ወደጋምቢ ሆስፒታል አሰራር ስንመለስ ዶ/ር መኮንን አይችሉህም የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
“...ጋምቢ ሆስፒታል ስራ የጀመረው ከሁለት አመት በፊት ነው፡፡ ሆስፒታሉ ቲቺንግ ሆስፒታል በመሆኑ የህክምና ተማሪዎችን በማስተማር ያስመርቃል፡፡ በሆስፒታሉ በራሱ ቅጥር ደረጃውን የጠበቀ መድሀኒት ቤት ያለው ሲሆን በሁሉም ዲፓርትመንቶችም የተሟላ ነው፡፡ ነገር ግን ጋምቢ ሆስፒታልን ከሌሎች ሆስፒታሎች የሚለዩት ነገሮች አሉ፡፡
አልጋ የያዙ Central oxygen supply ያለው በመሆኑ አየር ቢያ ስፈልጋቸው የሚመጣላቸው በበርሜል እየተገፋ  ሳይሆን ከራስጌያቸው በሚገኝ አፍ ላይ በሚደረግ መሳቢያ በሲስተም ከአንድ ማእከል አልጋቸው ድረስ ይታደላል፡፡
ሴንትራል ሳክሽን Central suction ያለው በመሆኑ ሕመምተኞች የሚያስወግ ዱዋቸው ቆሻሻዎች ማለትም እንደ አክታ የመሳሰሉትም በተመሳሳይ ሁኔታ ተቀብሎ ወደ አንድ ሴንተር የሚልክ መሳሪያ በየአልጋው አጠገብ ስለተገጠመ በአንድ ላይ ተሰብስቦ እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡
ከጋምቢ ሆስፒታል መስራቾች መካከል የሆኑት ዶ/ር መኮንን እንደሚሉት ሆስፒታሉ ሁሉ ንም የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን በተለይ ለእናቶች ግን የተሻሉ አሰራሮችን ለመቀየስ በሂ ደት ላይ ናቸው፡፡ እናቶች በእርግዝና ወቅት ከተለያዩ እሩቅ ቦታዎች የሚመጡ ሲሆን የመ ውለጃ ጊዜያቸው ሲደርስ በተለያዩ ችግሮች ወደ ሆስፒታል ሳይመጡ እንዳይቀሩ የሚያስችል የእናቶች መቆያ ለመስራት በእቅድ ላይ ነው፡፡ ነገር ግን ይህንና ሌሎች ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት እንዲቻል የተፈቀደላቸውን ተጨማሪ አምስት ሺህ ሜትር ካሬ ሜትር ቦታ ከመ ንግስት መረከብ ግድ ይሆናል፡፡
በስተመጨረሻው ዶ/ር መኮንን እንደገለጹት የእናቶች የጤና ችግር በርካታ ሲሆን በተለይ በአካባቢው የሚታየው የማህጸን ወደውጭ መውጣት ጊዜ የማይሰጠው መፍትሔን የሚሻ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ ለምሳሌም በአንድ አመት ውስጥ ከ 70/ በላይ እናቶች የማህጸን መውጣት ችግር አጋጥሞአቸው የመጡ ሲሆን ኦፕራሲዮን የተደረጉት ግን ሶስት ብቻ ነበሩ፡፡ የተቀሩት ችግሩን እንደያዙ በየቤታቸው እንዲቀሩ ያደረጋቸው የአቅም ውስንነት መሆኑን መጠራጠር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ከሆስፒታሉ አጋር አካላትን በማፈላለግ ጭምር በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን በነጻ እየሰጠ ይገኛል። አጋር ድርጅቶች የሰዎቹን ትራንስፖርት እና ለኦፕራሲዮን የሚያስፈልገውን ነገር የሚረዱ ሲሆን ሆስፒታሉ ደግሞ አልጋውን እና ባለሙያውን በነጻ በማቅረብ በትብብር መፍ ትሔ ለእናቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከፈለገ ሕይወት ሆስፒታል ጋር በመነጋገር ሕመምተ ኞቹን ወደጋምቢ ሆስፒታል እንዲልካቸው በማድረግ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ወደ ሁለት ወር የሚሆነው ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ከ12-15/ የሚደርሱ የማህጸን መውጣት የገጠማቸው እናቶች መፍትሔ አግኝተዋል፡፡

Read 2212 times