Print this page
Monday, 23 December 2013 09:43

“የማርያም ብቅል እፈጫለሁ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ከረማችሁሳ!
“ሄሎ!”
“ሄሎ ማን እንበል?”
“አታላይ በፍረዱ፡፡”
“አቶ አታላይ ከየት ነው የሚደውሉት?”
“ከወይራ ሰፈር፡፡”
“እሺ በተነሳው ጉዳይ ላይ ሀሳብዎን ይግለጹ፡፡”
ሀሳብ አለን…በሞሪንሆና ቬንገር መካከል ስላለው ‘እንካ ስላንትያ’ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ጉዳዮችም… “በተነሳው ጉዳይ ላይ ሀሳብዎን ይግለጹ…” የሚለን እንፈልጋለን፡፡ ሁሉም ተልጦ፣ ተከትፎ፣ ተዘልዝሎ ድስቱ ከተጣደ በኋላ…  “የዚህ ሰፈር ነዋሪ እንዲህ፣ እንዲህ አድርግ ተብለሀል!” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ…ብዙ ነገር… አለ አይደል… መከተፉንና መላጡን ሹክ የሚለን እየጠፋ ‘ድስቱ ከተጣደ’ በኋላ እያየነው ተቸግረናል፡፡
ለነገሩ ምን መሰላችሁ… ሀሳብ ለመስጠትም እኮ ችግር አለ፡፡ አሀ…ዘንድሮ ሀሳብን በጥሬው መውሰድ ቀርቷል፡ ልጄ…ከአፍ የወጣ ቃል እንደተፈለገው ቋንጣ ይሆንላችኋል! ኳስም አወራችሁ፣ ‘ባቡር’ም አወራችሁ… ‘ቦተሊካ ተች’ ይሰጠውና የቡድንና የቡድን አባቶች ሳትሉ አንደኛው ቡድን ውስጥ ትደለደላላችሁ፡፡
ልክ ነዋ… “የሳይንስ ትምህርት ለአገር ዕድገት ወሳኝነት እንዳለው አቶ አምታታው በዘዴ ለስብሰባው አስገነዘቡ…” የሚለው ወሬ ‘ሰበር ዜና’ በሚሆንባት አገር ነገርዬው “ወይ ከእኛ ጋር ነህ፣ ወይ ከእነሱ ጋር ነህ፣” ሆኗል፡፡
ስሙኝማ…ኤፍ.ኤም ላይ አድማጮች ሰጡ የተባለውን ‘ሀሳብ’ ስትሰሙ…ግራ ይገባችኋል፡፡ “አሁን ይሄ ጊዜውን ሰውቶ ጆሮውን ለፕሮግራሙ ለሰጠው ሰው ምን ይጠቅመዋል…” ያሰኛችኋል፡፡ ልክ ነዋ… አሰሱንም ገሰሱንም መድገሙ የአየር ሰዓት መሙያ ያስመስላላ!
እናላችሁ…ስለ ፊልም ጽሁፍ የሚያትቱ መጽሀፎች ምን ይሉ መሰላችሁ…ታሪክን ማጦዝ ያቃተው የፊልም ጽሁፍ ጸሀፊ በመኪና ማሳደድና በተኩስ ይሞላዋል ይላሉ፡፡ እኛ ደግሞ…የፕሮግራሙን ሦስት አምስተኛ  “በፕሮግራማችሁ ተመችቶኛል…” እና “ብርድ ስለሆነ ሞቅ ያለ ዘፈን ጋብዙን…” በሚል ሲሞላ በቃ…“ሰዎቹ የአየር ሰዓት መሙያ አጥተው መሆን አለበት…” እንላለን፡፡
  “እሺ፣ እኔ መናገር የምፈልገው አንዳንድ የመንግሥት ባለስልጣናት ባለጉዳይ…”
 “ይቅርታ አድማጫችን፣ አሁን የምንነጋገረው ስለ ባለስልጣናት ሳይሆን ስለመሥሪያ ቤቶች አሠራር ነው…”
የ‘ዋርካዎችን ስም’ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ጠርቶ ማን ይጠጣል! “እስኪጣራ ድረስ ማን ይጉላላል…” እንዳለችው እንሰሳ ልጄ… ‘እስኪጣራ ድረስ’ ብልጥ መሆን ነው፡፡ (“የሚጣራው ምንድነው?” የሚለው ጥያቄ እንደሚያሳስባችሁ ሁሉ እኔንም ያሳስበኛል፡ ቂ…ቂ…ቂ…)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… “አድማጫችን ማን እንበል?” ሲባል…ሰዎች ስማቸውን ሲናገሩ አንዳንዴ የ‘ቁጩ’ ስም እንደሆነ ከቃናቸው ትጠረጥራላችሁ፡፡ ምን ይደረግ…ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ዘንድሮ ስምም የግለሰብ መጠሪያነት ብቻ መሆኑ ቀርቶ በአንዱ ወይም በሌላ የ‘ቦተሊካ’ ቡድን የሚያስደለድልበት ዘመን ሆኗል፡፡
“ግን፣ እሱ ሰውዬ ስሙ ማነው?”
“እንትና እንተና ይባላል፡፡”
“ነው እንዴ! እኔም’ኮ አንዳንዴ ከአነጋገሩ እጠረጥር ነበር፡፡”
“ማለት…”
“ማለትማ የእንትና ደጋፊ ነው፡፡”
“በምን አወቅህ?”
“ይሄ ደግሞ፣ ከስሙ በላይ ምን ማረጋጋጫ ትፈልጋለህ!”
እናላችሁ…እዚህ ደረጃ ልንደርስ ምንም አልቀረን፡፡ በፊት ስልጣኔ ተብሎ… አለ አይደል…እነ ብሪቱ… ብሪትኒ፣ እነ በሪሁን…ብራድ ሲባሉ “ጉድ ነሽ የአንኮበር ቅጠል…” እንል ነበር፡፡ እንደ ዘንድሮ ነገረ ሥራችን ግን “ብሪቱ” ተብሎ ‘አንድ ቡድን’ ውስጥ ከመደልደል “ብሪትኒ” ተብሎ “አልቀረብሽም…” መባሉ ሳይሻል አይቀርም፡፡ አለ አይደል… ብሪትኒ “የኔኦ ሊበራሊስቶች ናፋቂ ነች…” ምናምን ካልተባለ! ቂ…ቂ…ቂ… አሀ…በዚች በሚወጣው ደረጃ ሁሉ አጃቢ ሆና የቀረችው አገራችን ውስጥ የማይሆን ነገር የለማ!
እናላችሁ… “ሆቺ ሚን እበላለሁ…” ብትሉ በቃ ቶሎ ተብሎ “ይሄማ ቅልጥ ያለው ኮሚኒስት ነው…” ምናምን ልትባሉ ትችላላችሁ፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የስም ነገር ካነሳን አይቀር እዚቹ የእኛዋ የዓለም ክፍል እየተበላሹ ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ታዲያላችሁ…ሰዎች በስማቸው የተነሳ የአገልገሎት ቅድሚያ የሚያገኙበት፣ ወይንም ጭርሱን “ከሁለት ሳምንት በኋላ ተመለስ…” የሚባሉበት ነገር በየቦታው አለ ይባላል፡፡
የምር እኮ… አንዳንዴ ችሎታና ብቃቱ ኖሮ እንኳን በስም የተነሳ የሥራ ዕድል ሊያመልጥ ይችላል፡፡ አንድ ሰሞን በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች አገልግሎት ለማግኘት እስከ አያት ድረስ ስም ይጠየቅ ነበር፡፡ “በአባት ቢሸውደን በአያት ያዝነው”… አይነት ነገር ነዋ!
 የስም ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…አንድ ቀን ጠዋት ሰውየው ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ያነባል፡፡ ድንገት ሳያስበው ሚስቱ ከኋላ ትመጣና በሆነ ነገር አናቱን ትለዋለች፡፡ እሱም ይደነግጥና “ሴትዮ ያምሻል እንዴ! ምን መሆንሽ ነው?” ይላል፡፡
እሷም ብጣሽ ወረቀት ታወጣላችሁና… “ይሄን ወረቀት ከኪስህ ውስጥ ነው ያገኘሁት” ትለዋለች፡፡
“እና ምን ይጠበስ!”
“ላዩ ላይ ሜሪ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ሜሪ ማናት?”  
ይሄኔ እሱ ሆዬ ምን ይላል… “ለዚህ ነው እንዴ! ከሁለት ሳምንት በፊት ለፈረስ ውድድር መሄዴ ትዝ አይልሽም!”
“እናስ…!”
“ሜሪ እኮ እኔ የተወራረድኩባት ፈረስ ነች፡፡” ነገርዬው በዚህ ያልቃል፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ እንዲሁ ቁጭ ብሎ ጋዜጣ ሲያነብ ሚስት ከኋላ አድብታ ትመጣና በመጥበሻ አናቱን ትለዋለች፡፡ እሱም “አሁን ደግሞ ምን ሆንሽ?” አላት፡፡
እሷዬዋ ምን ብትለው ጥሩ ነው… “ፈረሷ ሜሪ ስልክ ላይ ትፈልግሀለች፡፡”  
የምር ይሄ የማይረባ ነው…ካልጠፋ ማመሳከሪያ በፈረስ ይወክላታል! እንደፈለገው…. አርባ አምስተኛ ታቦት ነሽ… ሊል ምንም የማይቀረው ሰውዬ መፋጠጥ ሲመጣ  “የተወረራደኩባት ፈረስ ነች…” ሲል አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ… የምር እንጋገር ከተባለ ‘ባህላዊ’ የምንላቸው ስሞች መጀመሪያ ስንሰማቸው የሚሰጠን ትርጉም አላቸው፡፡ ለምሳሌ ለሴቶች ከበቡሽ፣ የዓይኔ አበባ፣ ሁሉአገርሽ የሚባሉ ስሞች አሉላችሁ፡፡ (በሌሎች ቋንቋዎች ያሉትን ስለማላውቅ እንዳልዘባርቅ ብዬ ነው፣) ለወንዶች ደግሞ ባንትይርጉ፣ በአምላኩ፣ ደፋባቸው የሚሉ ስሞች አሉላችሁ፣ እነኚህ ስሞች በ‘አንበሳ ጎፈር’ አይነት የሚወጡ ሳይሆን በውስጣቸው የየራሳቸው ታሪኮች አሏቸው፡፡ እናማ…በአገራችን ስሞች ከመጽሔት ሽፋንና ከ‘ቦክስ ኦፊስ’ ዝርዝር የሚወጡ ሳይሆን የየራሳቸው ጥራዝ የሚወጣ ታሪከ ያላቸው ናቸው፡፡
እናማ…ይሄ ሁሉ ተረስቶ ስሞች የ‘ቦተሊካ ቡድን መደልደያ’ እንዲሁም የአገልግሎት ማግኛና መነፈጊያ ሲሆኑ በጣም ያሳዝናል፡፡ እናማ…መታወቂያ ምናምን ካልተባለ በስተቀር…አለ አይደል…ስምን ‘ለጠያቂው እንዲያመች’ አድርጎ መንገር የአገልግሎት ማግኛ ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእንደዚህ አይነት ዝቅጠት ይሰውረንማ!
ታዲያላችሁ…ስምም ሆነ ነገሮች ሁሉ ‘ለጠያቂው እንዲያመች’ ሆነው እንዲቀርቡ ማድረግ ልናስበው ከምንችለው በላይ እየተለመደ ያለ ነገር ነው፡፡ ምን ይደረግ…አለበላዛ ጦም ማደር ሊመጣ ነዋ!
ነገሮችን ‘ለጠያቂው እንዲያመች’ ስለማድረግ ካነሳን አይቀር ይቺን ስሙኝማ በሶቪየት በኮሚኒዝም ዘመን የሆነ ነው አሉ፡፡ እናማ… የዶሮ እርባታዎች ተቆጣጣሪ የሆነ የመንግሥት ሰው እየዞረ የእርባታ ስፍራዎችን ይጎበኛል፡፡ ለእያንዳንዱ የዶሮ አርቢ አርሶ አደር አሥራ አምስት ሩብል ተሰጥቶት ነበር፡፡
ታዲያላችሁ… አንዱ አርሶ አደር ገንዘቡን እንዴት እንደተጠቀመበት ሲጠየቅ… “አምስቱን ሩብል የዶሮ … ገዛሁበት” አለ፡፡ ተቆጣጣሪውም አርሶ አደሩ ቀሪውን አሥር ሩብል ለራሱ አስቀርቷል በሚል እንዲታሰር ያደርገዋል፡፡
ይህንን የሰማ ሌላኛው ከእርሱ አጠገብ የነበረ አርሶ አደር ሲጠየቅ፣ አሥራ አምስቱንም ሩብል ለዶሮዎቹ ቀለብ ማዋሉን ተናገረ፡፡ ተቆጣጣሪውም “ይህ በጀትን ያለ ዕቅድ ማባከን ነው…” ይልና እንዲታሰር አደረገው፡፡
ሦስተኛው አርሶ አደር ሆዬ፤ እነኚህን ዜናዎች ሰምቶ ተቆጣጣሪውን ተዘጋጅቶ ይጠብቀዋል፡፡
“ከአሥራ አምስቱ ሩብል ለዶሮዎቹ ቀለብ ያዋልከው ምን ያህሉን ነው?” ሲል ተቆጣጣሪው ጠየቀ፡፡ አርሶ አደሩ ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ… “እኔ አሥራ አምስቱን ሩብል ለዶሮዎቹ ነው የምሰጣቸው፡ እነሱ ናቸው የፈለጉትን የሚያደርጉበት፡፡” አሪፍ አይደል!
እናማ…ስማችን ‘ላም ባልዋለችበት ኩበት የምንለቅም’ የሚያስመስለን ከሆነ በምንጠራበት ጊዜ… “የማርያም ብቅል እፈጫለሁ…” የማንልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ አሀ…ከስም ጥሪው ጀርባ ‘የቦተሊካ ጋኔን’ ሊኖር ይችላላ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3819 times