Saturday, 03 December 2011 08:32

አንጋፋዎቻችን ከወዴት አሉ?

Written by  ይታገሱ ጌትነት
Rate this item
(0 votes)

“ኢትዮጵያ ሃገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ”

ከጥቂት ወራት በፊት እኔ፤ ደራሲ ኃይለመለኮት መዋዕልና፣ ፀሐይ መላኩ በአንድ የመቃብር ስፍራ ተገናኘን፡፡ በዚህ የመቃብር ሥፍራ የምንፈልገው የታላቁን ባለቅኔ ደራሲና ዐርበኛ የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴን ሐውልት ነበር፡፡ የመቃብሩን ሥፍራ ከዓመታት በፊት ተመልክቶ እኛን ሲመራ የነበረው ኃይለመለኮት ነው፡፡ የዮፍታሔ መቃብር ከበርካታ መቃብሮች መኻል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በሥፍራው ላይ ከፈራረሱ የሐውልት ቁልል ድንጋዮችና የቆሻሻ ክምር በቀር አንዳች የለም፡፡ ሥፍራው ለልማት ታስቦ የሙታኑ ዐፅም እንዲፈልስ ተደርጓል፡፡ ዮፍታሔ የት ሄደ? ገረመን፣ ደነገጥን፡፡


ዮፍታሔ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ደራሲ ነው፡፡ ዮፍታሔ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ጀማሪ፤ የትምህርት ቤት ቴአትሮችን ያስፋፋ፣ ምትክ የሌለው ብርቅዬ ሰው ነው፡፡ ዮፍታሔ በድጓ ምልክቶች ሙዚቃዎች ይደርስ የነበረ በዚህም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ብዙ ያበረከተ ሊቅ ነበር፡ እስካሁን ድረስ እንደትውፊት የሚነገሩ ግጥሞች ደራሲ ነበር፡፡ በአርበኝነትና በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሀገሩን ያገለገለ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ላበረከተው በጐ ሥራ፤ ለከፈለው መሥዋዕትነት፤ ለተቀበለው መከራና ስደት ብድራት ይመስል መታሰቢያው እንኳን ለሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ እድል አልተሰጠውም፡፡
ከብዙ ድካም በኋላ ከመቃብር ከተሰበሰቡት ዐጽሞች መኻል የሀገር ተቆርቋሪ ጥቂት ሰዎች የሊስትሮ ሳጥን በምታህል የእንጨት ሳንዱቅ ውስጥ ዐጽሙን አስቀምጠውት አገኘን፡፡ ይሄን በጐ ሥራ ያደረጉትን ሰዎች አመሰገንን፤ በራሳችን ግን አፈርን፡፡
ይሄን ታላቅ ሰው እንዴት ትውልድ እንዲያስበው ማድረግ አልቻልንም ስንል ተጠያየቅን፡፡ ዮፍታሔ ከሚታወቅበት ግጥሙ መኻል
“ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የምትለውን ስንኝ ካሰላሰልን በኋላ ዐጽሙን ተሰናብተን ወጣን፡፡
ከዚህ በኋላም በዚያው የመቃብር ስፍራ ሌላ ደግሞ ገጠመኝ አገኘን፡፡ “ሞረሽ”፣ “ጣጠኛው ተዋናይ”፣ “አባ ነፍሶ” ቲያትሮቹ ሲሆኑ “የቴዎድሮስ ዕንባ”፣ “የዕንባ ደብዳቤዎች” “የታንጉት ምሥጢር፣ “አማኑኤል ደርሶ መልስ” ፣ “ማዕበል የአብዮት ዋዜማ፣ መባቻና ማግስት” በተሰኙት ሥራዎቹ ይታወቃል፡፡ ከዚህም በላይ “የኢትዮጵያ ድምጽ” እና “አዲስ ዘመን” ጋዜጣን በዋና አዘጋጅነት መርቷል፡፡ ይህ ሰው ብርሃኑ ዘሪሁን ነው፡፡ የብርሃኑ የቀብር ሥፍራ ዮፍታሔ ባረፈበት በቅድስት ሥላሴ ሲሆን አሁን ባለው ይዞታ ከዮፍታሔ ይሻላል እንጂ በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ላይ ካለው አስተዋጽኦ አንፃር አሳዛኝ ነው፡፡ ከፈለሱት አጽሞች መሀል አዲስ በተሠራ የብዙሀን መቃብር ውስጥ አንዲት መስኮት ደርሳው ስሙ በድንጋይ ላይ ታትሞ ተቀምጦበታል፡፡
እርግጥ ነው በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ደራስያን አይደለም ሞተው መቃብራቸው ያማረ የከበረ ሊሆን ቀርቶ፣ እየኖሩም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ሕይወታቸውን የሚያሳልፉት፡፡ የአንዳንዶቹም የመጨረሻ የሕይወታቸው ክፍል አሳዛኝ እና አስጨናቂ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ውስጥ ቀለመ ደማቁ የኮሜዲ አባት አብዬ መንግሥቱ ለማ የሳቅ ምንጭ፤ ዋዘኛና ለዘኛ እንደሆኑ ነበር የሚታወቁት፡
በዕረፍታቸው ወቅት ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ ቀብራቸውን ለማስፈፀም ገንዘብ ጠፍቶ መንግሥት እንዲደጉም እስከመለመን ተደርሷል፡፡ አብዬ መንግሥቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረዥም ዓመታት ከማስተማራቸውም በላይ “… ግጥም ጉባኤ” “የአባቶች ጨዋታ”፣ “ጠልፎ በኪሴ”፣ “ያላቻ ጋብቻ”፣ “መጽሐፈ ትዝታ ዘ አለቃ ለማ ኃይሉ” የተሰኙትን መጻሕፍት አሳትመዋል፡፡ ከሥራዎቻቸው መሀል ሁለቱ በሩሲያኛ እና በእንግሊዝኛ ለመተርጐም በቅተዋል፡ በሀገር ውስጥና በአፍሪካ ደረጃ የሽልማት ባለቤት የነበሩት እኒህ ታላቅ ሰው፤ የጐላ መታሰቢያ እንኳን ሳይኖራቸው ካረፉ ይኸው ሩብ ክፍለ ዘመን ሊሆናቸው ነው፡፡
አብዬ መንግሥቱን ሳነሳ ሁሌ የሚታወሰኝ የሥራ ባልደረባቸው የነበረው ደበበ ሰይፉ ነው፡፡ ደቤ በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ዕድገት ላይ በጐ ተጽእኖ አሳድረዋል ከሚባሉ ሰዎች መሀል ተጠቃሽ ነው፡፡ ከማንበብ እስከ መጻፍ፣ ከመጻፍ እስከ ማስተማር፣ ከማስተማር እስከምርምር ያሉትን ዳርቻዎች ሁሉ ደበበ ተወጥቷቸዋል፡፡ “የብርሃን ፍቅር” ቅጽ 1 እና 2 የግጥም ሥራዎቹ ሲሆኑ በተውኔት ዙሪያ የፃፈው መጽሐፍና ሌላ የትርጉም ሥራዎቹም ይጠቀሳሉ፡፡
ይህን ሁሉ ያበረከተላት ሀገሩ የደበበን የመጨረሻ ዓመታት አሳዛኝ አድርጋበታለች፡ አንገቱን ሰብሮ፣ ልሳኑን ዘግቶ ወደ ምድር ሲመለስም ካለምንም ተጨማሪ ክብርና መታሰቢያ በዮሴፍ ጓሮ ወርውራዋለች፡፡ ጳውሎስ ኞኞስ ቢሆን፡፡ ጳውሎስ ስሙን በሥራው ማድመቅ የቻለ ከምንም ተነስቶ በሁሉም ላይ የነገሠ ጋዜጠኛና ደራሲ ነበር፡ ለመጪው ትውልድስ ቢሆን ከጳውሎስ የተሻለ ታላቅ መምህር ከየት ሊመጣ ኖሯል?
“አጤ ምኒልክ”፣ “የኔዎቹ ገረዶች” እና በበርካታ ሌሎች ሥራዎቹ እንዲሁም በጋዜጠኝነት ሙያው በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ደምቆ የበራ ታላቅ ኮከብ ነበር፡፡
ጋሽ ጳውሎስ ኞኞን የሚያስታውሰው ነገር ዛሬ ምን አለ? ከዓመታት በፊት ወጣቶች በስሙ ለመሰብሰብ ደፋ ቀና ይሉ ነበር፤ ምን ተደረገላቸው ዛሬስ የት ናቸው ጥያቄ ብቻ ነው፡፡ መልስ ግን ማግኘት ሩቅ ነው፡፡ ዛሬ ለጳውሎስ የቀረበለት መታሰቢያ ቀራንዮ መድኃኔዓለም ጓሮ ያለው የመቃብሩ ሥፍራ ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ መቃብር አላቸው፡፡ አልተከበረላቸውም እንጂ፤ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ኑሮአቸውን ብቻ ሳይሆን መኖራቸውንም አሳልፈው የሰጡ እንደ በዓሉ ግርማ ያሉ ፀሐፍትም ተከስተዋል፡፡ መቃብር የሌላቸው፤ የትናችሁ የማይባሉ መታሰቢያ የሌላቸው፡ “ደራሲው”፣ “ከአድማስ ባሻገር”፣ “የኅሊና ደወል”፣ “የቀይ ኮከብ ጥሪ” “ሐዲስ” እና ጣጠኛው “ኦሮማይ”ን ከማሳተሙም በተጨማሪ በጋዜጠኝነትና በኃላፊነት ሀገሩን አገልግሏል፡፡ የት እንደወደቀ ባይታወቅ፣ መታሰቢያ እንኳን ሊኖረው አይገባም? በርግጥ በቅርቡ በፋውንዴሽን ደረጃ ሥራዎች ቢጀመሩም የሚታይ ቅርስ እንዲሆን ማስቻል ደግሞ ሌላው መንገድ ይሆናል፡፡
እንዲህ መዘርዘር ከጀመርኩ ማብቂያ ላይኖረኝ ነው፡ ተመስገን ገብሬ፣ አረጋሽ ሰይፉ፣ ፊርማዬ አለሙ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ወዘተ… እያልኩ ብዘረዝር ተመሳሳይ ነጥቦችን ከማንሳት የዘለለ አዲስ ነገር አልልም፡፡ ታላቁ ደራሲ ገብረሕይወት በሥራ ጉዳይ ወደ ድሬዳዋ ሄዶ ሳለ ዐረፈ፡፡ ዐጽሙ ሐረር ጥምቀተ ባሕር ሚካኤል አርፏል፡፡
ጽሑፉን ከማጠናቀቄ በፊት ግን የ”አልወለድም” እና ሌሎች 24 መጻሕፍት ደራሲ አቤ ጉበኛ በትውልድ ሀገሩ ጐጃም ይስማላ ጊዮርጊስ፤ ከመቃብር በላይ በመታሰቢያነት ሐውልት የቆመለት መሆኑን ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪም በቅርቡ በሞት ያጣናቸው የክቡር ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ፣ የክቡር ዶ/ር ከበደ ሚካኤል፣ የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን የመቃብር ሥፍራዎች በቅድስት ሥላሴና ጳውሎስ ቤ/ክርስቲያን ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ በከበደ ሚካኤልና በሀዲስ አለማየሁ ስም ት/ቤት መሰየሙ እንደበጐ ጅምር ሊበረታታ እንደሚገባ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ ምናልባት ይህንን ጽሑፍ የሚያነብ ሰው፤ ለሰው ሀገሩ ምግባሩ ነው፤ ከመቃብር በላይ ያለው ሥራው ይበቃዋል ሊል ይችል ይሆናል፡፡ በሀሳቡ እስማማለሁ፡ የሚከበር ሥራ የሠራ ግን ሊከበር ይገባዋል፡፡ በሚታይ፣ በሚጨበጥና በሚዳሰስ መልኩ ያንን ሰው ማክበር ትውልድን ይቀርጻል፡፡
ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ፤ የመጀመሪያውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ አማርኛ በመተርጐምና “ወዳጄ ልቤ” በሚሰኘው መፅሐፋቸው የሚታወቁት ታላቁ ደራሲ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ በስደት እያሉ ቢሞቱ ከስደት በኋላ ሀገር ቤት አስመጥተው እንዳስቀበሯቸው በታሪክ ሠፍሮ ይገኛል፡፡ ህሩይ ሀብትነታቸው የኢትዮጵያ ነው፤ ክብራቸው የኢትዮጵያ ነው ብለው ስላመኑ ነው ያንን ያደረጉት፡፡
ቀጣዩ ትውልድ የተጻፉትን መጻሕፍት ሲያይ ስለእነዚህ ታላላቅ ሰዎች ያስባል፣ ይጠይቃል፣ ክብራቸውንም አይቶ የተከበረ ሥራ ለመሥራት ይተጋል፡፡ ለዚህም ነው እነዚህን “ታላላቅ ክዋክብት” አክብረን ልናሳየው የሚገባን፡፡
በኢትዮጵያ የኪነጥበብ መስክ አገልግለው ደምቀው ለሚያርፉ የሀገር ባለውለታዎች ደረጃውን የጠበቀ የክብር ማረፊያ ቢዘጋጅ፣ ለጉብኝት የሚሆንና እግረመንገድንም የሚከበሩበት ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል ለደራስያኑ መታሰቢያ ሙዚየም መገንባት ቢቻል መልካም ነው፡፡
የተለያዩ በጐ አድራጊ ተቋማትም በነዚህ ታላላቅ ሰዎች ስም እርዳታ ቢያደርጉ፣ መንግሥትም አንዳንድ ተቋማትን፣ አደባባዮችንና መናፈሻዎችን እንዲሁም መንገዶችን በነዚህ ኢትዮጵያውያን ስም ቢሰይም ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል እላለሁ፡፡
ከአዘጋጁ - (ከዚህ በላይ መጠነኛ አርትኦት ተደርጐበት የቀረበው ፅሁፍ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር የኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን አስመልክቶ ካወጣው “ብሌን” ልዩ ዕትም መፅሄት የተወሰደ ነው)

 

Read 3961 times Last modified on Saturday, 03 December 2011 08:34