Monday, 23 December 2013 10:23

የሎተሪው እጣ

Written by  ደራሲ - አንቶን ቼኾቭ ትርጉም - ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(12 votes)

ኢቫን ዲሚትሪች፤ እራቱን በልቶ እንዳበቃ ሶፋው ላይ ተቀምጦ የዕለቱን ጋዜጣ ማንበብ ጀመረ፡፡ በዓመት 1200 ሩብል ደሞዝ የሚያገኘው ዲሚትሪች፤ከቤተሰቡ ጋር መካከለኛ ኑሮ የሚመራ ደስተኛ  አባወራ ነው፡፡
 “ዛሬ እርስት አድርጌው ጋዜጣውን አልተመለከትኩም” አለችው ሚስቱ፤እራት የበሉበትን ጠረጴዛ እያፀዳዳች “እስቲ የሎተሪ ዕጣ ዝርዝር ወጥቶ እንደሆነ ተመልከትልኝ”
“አዎ ወጥቷል” ከመቅፅበት መለሰላት፤ ኢቫን ዲሚትሪች “ግን ያንቺ ሎተሪ ጊዜው አላለፈበትም እንዴ?”
“በፍፁም፤ ማክሰኞ እኮ አይቼው ነበር”
“ቁጥሩ ስንት ነው?”
“የኮድ ቁጥሩ 9‚499፣ የእጣው ቁጥር ደግሞ 26”
“ደህና እንግዲህ፤ የኮዱንም የእጣውንም ቁጥር እናየዋለን”
ኢቫን ዲሚትሪች፤ በሎተሪ እድል የሚያምን ሰው አይደለም፡፡ ሎተሪም ገዝቶ፣ አሸናፊ የእጣ ቁጥሮችንም ተመልክቶ አያውቅም፡፡ አሁን ግን ሌላ የሚሰራው ነገር ስለሌለውና ጋዜጣውም ዓይኑ ስር ስለሆነ፣ ጣቱን አሸናፊ የእጣ ቁጥሮች ወደተደረደሩበት የጋዜጣው ረድፍ በመላክ መመልከት ጀመረ፡፡ የሎተሪ ዕድል ላይ ያለውን ጥርጣሬ የሚፈታተን በሚመስል መልኩ፣ ገና አንደኛውን  መስመር እንዳለፈ፣ 9‚499 የሚል ቁጥር ተመለከተ፡፡ ዓይኑን ፈጽሞ ማመን አቃተው። ጥርጣሬውን ለማጥራት ዳግም ጋዜጣው ላይ አፈጠጠ፡፡ የተለወጠ ነገር ግን የለም፡፡ 9‚499 - ይላል በሁለተኛ መስመር ላይ የሰፈረው  የኮድ ቁጥር፡፡ ከመቅፅበት ጋዜጣውን ጉልበቱ ላይ ቁጭ አደረገው፡፡ የተለያዩ ስሜቶች ተፈራረቁበት - ድንጋጤ፣ መገረም፣ መደነቅ፣ እና ደስታ፡፡ የፊቱ ገፅታ ላይ ጎልተው የሚታዩት ግን የግርምትና የድንጋጤ ስሜቶች ናቸው፡፡
 “ማሻ፤ ቁጥሩ ጋዜጣው ላይ ወጥቷል --- 9‚499 የሚለው” አለ፤ ኦና በሚመስል የተዋጠ ድምጽ፡፡  
ሚስቱ ግርምትና ድንጋጤ የወረሰውን ፊቱን ባትመለከት ኖሮ እየቀለደ መስሏት ነበር፡፡
“9‚499?” ጠየቀችው፤ በድንጋጤ ተውጣና የተጣጠፈውን የጠረጴዛ ልብስ ጠረጴዛው ላይ እየጣለች፡፡
“አዎ…አዎ….የምሬን ነው --- ጋዜጣው ላይ ወጥቷል!”
“የእጣው ቁጥርስ?”
“አዎ-- እሱም አለ…ግን ቆይ… ማለቴ ---ለማንኛውም የኮዱ ቁጥር አለ! ገባሽ--”
ኢቫን ዲሚትሪች፤ ለሚስቱ ምክንያት አልባ ፈገግታ ለገሳት - ልክ ህፃን ልጅ  አንፀባራቂ እቃ ሲያሳዩት እንደሚሆነው፡፡ እሷም አፀፋዋን በፈገግታ መለሰችለት፡፡ የኮዱን ቁጥር እንጂ የእጣውን ቁጥር አለመመልከቱ እምብዛም የቆረቆራት አትመስልም፡፡ ለነገሩ ራስን ባልተረጋገጠ የአዱኛ ተስፋ ማጓጓትና ማሰቃየት ሲጣፍጥ ለጉድ ነው ፤ በጣም ደስ ይላል!
ከረዥም ዝምታ በኋላ “የኮድ ቁጥሩ እኮ  የእኛ ነው--- ማንም የማይወስድብን” አለ ኢቫን ዲሚትሪች፤ “ስለዚህ ዕጣውን የምናሸንፍበት ዕድል አለን … ኮዱን ግን ወሰድነው!”
“በል አሁን --- የዕጣውን ቁጥር ተመልከት!”
“ትንሽ ቆዪ --- ለመበሳጨት የምን መጣደፍ ነው፡፡ የእኛ ቁጥር ከመጀመርያው ሁለተኛ መስመር ላይ ነው ያለው፡፡ እናም  ሽልማቱ 75ሺ ሩብል ነው፡፡ ይሄ ገንዘብ አይደለም ፡፡ ተዓምር ነው። የሃብት ተራራ! በደቂቃ ውስጥ ደግሞ ዝርዝሩን እንደገና እመለከተዋለሁ … 26 ነው አይደል? ግን የምር ቢደርሰንስ?”
ባልና ሚስቱ ሲሳሳቁ ቆዩና እርስ በእርስ መተያየት ጀመሩ - በዝምታ ተውጠው፡፡ የሎተሪ ዕድሉን እናሸንፋለን የሚለው ሃሳብ አቅላቸውን አስቷቸዋል፡፡ 75ሺ ሩብሉ ቢደርሳቸው--- ምን እንደሚሰሩበት፣ ምን እንደሚገዙበት፣ የት እንደሚጓዙበት… አላሰቡም፤ አላለሙም፡፡ እነሱ ማሰብና ማለም የቻሉት  9‚499 የሚለውን የኮድ ቁጥርና 75.000 ሩብሉን ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ሎተሪውን ማሸነፍ ስለሚያጐናጽፋቸው ደስታ ትዝ አላላቸውም፡፡
ኢቫን ዲሚትሪች፤ ጋዜጣውን በእጁ እንደያዘ ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላኛው ጥግ ብዙ ተመላለሰ። ከመጀመሪያው የድንጋጤ ስሜት ሲወጣ ነው ስለሎተሪው ገንዘብ ትንሽ ማሰብና ማለም የጀመረው፡፡
“ሎተሪውን ካሸነፍን…” አለ ለሚስቱ “በቃ…አዲስ ህይወት ነው የምንጀምረው፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ የሎተሪ ትኬቱ ያንቺ ነው፤ የእኔ ቢሆን ኖሮ ግን መጀመሪያ 25ሺውን ለሪል እስቴት አውለዋለሁ፡፡ 10ሺውን ደግሞ ለአስቸኳይ ወጪዎች… ለአዳዲስ የቤት ቁሳቁሶች… ለጉዞ… ለዕዳ መሸፈኛና ለመሳሰሉት፡፡ የቀረውን 40ሺ በቀጥታ ባንክ እከተውና ወለዱን መብላት!”
“አዎ፤ ሪል እስቴት ግሩም ሃሳብ ነው!” አለች ሚስቱ፤ ሶፋው ላይ እየተቀመጠችና እጆቿን ጭኖቿ ላይ እያሳረፈች፡፡ “ከቱላ ወይም ከኦርዮል ግዛቶች አንዱ ጋ ሊሆን ይችላል…በመጀመሪያ ደረጃ ግን እኛ የበጋ ቪላ አያስፈልገንም…እናም ቤቱ ሁሌም የገቢ ምንጭ ይሆናል ማለት ነው” ስትል ሚስቱ ማብራርያ ሰጠች፡፡
አሁን አዕምሮውን የሚያጨናነቁ ምናባዊ ምስሎች እየተግተለተሉ ይመጡበት ጀመር-ኢቫን ዲሚትሪች፡፡
እያንዳንዱ ምስል ደግሞ ከመጨረሻው የበለጠ የሞቀና የደመቀ፣ ቅንጡ ህይወትን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ በምናባዊ ምስሎቹ ሁሉ ራሱን በቅጡ ተመጋቢ፣ ጤናማና፣ የሰከነ አድርጐ ነው የሳለው። የወደፊቱን በአዱኛ የተሞላ ህይወት ሲያስብ ሞቅ አለው፤ ተኮሰም ሳያደርገው አልቀረም፡፡ በዚህ ህይወቱ …እንደ በረዶ የቀዘቀዘ  የበጋ ሾርባውን ካጣጣመ በኋላ፣ ከምንጩ አጠገብ እሚያቃጥለው አሸዋ ላይ ወይም እመናፈሻው ካለው የሎሚ ዛፉ ስር በጀርባው ይንጋለላል፡፡ አቤት ሲሞቅ! አቤት ሲያቃጥል! ... ትናንሽ ልጆቹ አጠገቡ እየዳሁ፣ አሸዋውን በጣታቸው ይቆፍራሉ፤ አሊያም ከሳሩ ላይ ቢራቢሮ እየያዙ  ይጫወታሉ፡፡ ትንሽ ደከም ሲለው--- ያለአንዳች ሃሳብ ጣፋጭ እንቅልፉን ይለጥጣል፡፡ ዛሬ ቢሮ መሄድ ላያሰኘው ይችላል…ነገም ከነገወዲያም እንዲሁ ካላሰኘው ይቀራል፡፡ ዝም ብሎ መጋደምና መንጋለል ከሰለቸው ደግሞ የእንጉዳይ ማሳ ወዳለበት ጫካ ይሄዳል ወይም ገበሬዎች አሳ ሲያጠምዱ ቆሞ ይመለከታል፡፡ ፀሐይዋ መጥለቅ ስትጀምር፣ ፎጣና ሳሙናውን ይይዝና ወደ ገላ መታጠቢያው ያመራል፡፡ ዘና ብሎ ልብሱን ያወላልቅና እርቃን ደረቱን በእጁ ፈተግ ፈተግ ያደርጋል፤ ከዚያም ውሃው ውስጥ ይገባል። ገላውን ታጥቦ ሲያበቃ ደግሞ ሻይ በክሬም ይጠብቀዋል፡፡ መሸትሸት ሲል የእግር ጉዞ ያደርጋል ወይም ከጐረቤቶቹ ጋር ወግ ይጠርቃል …
ከሰጠመበት ምናባዊ ዓለም ድንገት ያነቃው የሚስቱ ንግግር ነበር፡፡
“አዎ፤ ሪል እስቴት መግዛት ግሩም ነው!” አለች፤ እንደሱ የሞቀና የደመቀ፣ ቅንጡ ህይወት ስታልም ቆይታ፡፡ በህልሞቿ እንደተደሰተች የፊቷ ገጽታ ይመሰክራል፡፡
ኢቫን ዲሚትሪች፤ የመከርን ዝናባማ ወቅትና ቀዝቃዛ ምሽቶች በምናቡ ይስል ገባ፡፡ በዚህ ወቅት በአትክልት መናፈሻውና በወንዙ ዳር ረዥም ጉዞ ያደርጋል፤ በደንብ እንዲቀዘቅዘው፡፡ ከዚያ ሲመለስ በትልቅ ብርጭቆ ቮድካ ይጐነጫል። ጨው የበዛበት እንጉዳይ ወይም ኩከምበር ይበላል፡፡ ከዚያ እንደገና ሌላ ቮድካ ይቀዳል… ልጆቹ ከጓሮ ካሮት ነቅለው አፈር አፈር እየሸተቱ ሲሮጡ ይመጣሉ፡፡ ወደ ኋላ ላይ ደግሞ ሶፋው ላይ በረዥሙ ተንፈላሶ በተንደላቀቀ ስሜት፣ በምስሎች የተሞላ መጽሔት ያገላብጣል፤ አሊያም ፊቱን ይሸፍንበታል፡፡ የካፖርቱን ቁልፎች ፈታቶም ራሱን ለእንቅልፍ ያዘጋጃል…
በመከር መገባደጃ ላይ የሚመጣውን የበጋ ወቅት ተከትሎ፣ ደመናማና ጭጋጋማ አየር ከተፍ ይላል፡፡ ቀንና ሌሊት ሲዘንብ ውሎ ሲዘንብ ያድራል፡፡ እርቃናቸውን የቆሙት ዛፎች፤ ከሰማይ የተቀበሉትን ዝናብ እንደ እንባ ያፈሱታል፡፡ ለቅሶ በሚመስል ዜማ፡፡ አየሩ ውርጭና ቅዝቃዜ የሞላው ነው፡፡ ውሾቹ፣ ፈረሶቹ፣ ዶሮዎቹ…ሁሉም በስብሰዋል፡፡ ሁሉም ገፅታቸው ጨፍግጓል። ሁሉም የፈዘዙ የደነገዙ ናቸው፡፡ የትም መሄጃ ሥፍራ የለም፡፡ ለቀናት ያህል ማንም ሰው ከቤቱ ንቅንቅ አይልም፡፡ እዚያው መንጐራደድ ብቻ! በመስኮት የጨፈገገውን አየር በደነዘዘ ስሜት እየተመለከቱ፡፡ አቤት ሲቀፍ!  
ኢቫን ዲሚትሪች፤ ቆም አለና ሚስቱን  ተመለከተ፤ “ማሻ፤ ውጭ አገር መሄድ አለብኝ …” በመከር  መገባደጃ ላይ ወደ አንዱ ውጭ አገር … ወይ ደቡብ ፈረንሳይ … ወይ ጣልያን አሊያም ህንድ መጓዝ… ምንኛ ግሩም እንደሆነ ማሰብ፤ ማሰላሰል ያዘ፡፡
“እኔም ራሴ  መሄድ አለብኝ!” አለች፤ ሚስቱ “ግን መጀመርያ የእጣውን ቁጥር ተመልከት!”
“ቆይ! … ቆይ! … ”
ወዲያው በክፍሉ ውስጥ እየተንጐራደደ ማሰብ ማሰላሰሉን ቀጠለ፡፡ ግን ሚስቱ ከምር አብራው ውጭ አገር ብትሄድስ? ይሄን ሀሳብ ጨርሶ አልወደደውም፡፡ መጓዝስ ለብቻ ነው- ሲል አስቧል፡፡ ወይ ደግሞ ከሰለጠነችና ጭንቀት ከማያቃት ዘመናዊት ሴት ጋር! ሚስቱ በጉዟቸው ስለ ልጆቻቸው እያሰበችና  እየለፈለፈች … በእያንዳንዷ ሰባራ ሳንቲም እየነተረከች እንደምታሰቃየው አልጠፋውም፡፡ ይሄ ደግሞ ሰላምና ነፃነትን ይነፍጋል፡፡ ሚስቱ ባቡር ውስጥ በበርካታ እሽግ ካርቶኖች፣ ቅርጫቶች፣ ቦርሳዎች … ተከብባ  ስትጓዝ በሃሳቡ ሳላት፡፡ በሆነ ባልሆነው ስትቃትት … ባቡሩ ራሴን አሳመመኝ እያለች ስትነዘንዘው … ብዙ ገንዘብ አጠፋሁ ብላ ስታማርር … ይሄ ሁሉ ታሰበውና ዘገነነው፡፡ በየጣቢያው የፈላ ውሃ እንዲሁም ዳቦና ቅቤ እያለቀበት ሲሰቃይ ---- እሷ ደግሞ እራት ውድ ነው ብላ ፆሟን ስታድር …
“ለምትከፍላት እያንዳንዷ ድምቡሎ ልትነዘንዘኝ እኮ ነው!” ሲል አሰበና፤ ሚስቱን ለአፍታ ቃኘት አደረጋት፡፡ “በእርግጥ የሎተሪ ትኬቱ ባለቤት እሷ እንጂ እኔ አይደለሁም፡፡ ግን የሷ ውጭ አገር መሄድ ፋይዳው ምንድነው? እዚያ ምን ጉዳይ አላት? ራሷን ሆቴል ውስጥ ከርችማ እኮ ነው የምትከርመው!  እኔን ደግሞ ከአጠገቧ ውልፊት እንደማታደርገኝ አውቃለሁ!”
በህይወቱ ለመጀመርያ ጊዜ ስለሚስቱ ማርጀትና መገርጣት፣ እንዲሁም ስለራሱ ጐረምሳነት፣ ጤናማነትና ሌላ ሚስት ሊያገባ እንደሚችል በማሰብ ተጠመደ፡፡  
“ይሄ እንኳን ዝም ብሎ የጅል ሃሳብ ነው ...” አለ፤ ሌላ ሚስት የማግባቱን ጉዳይ፡፡ “ግን እሷ ለምንድነው ውጭ አገር መሄድ ያስፈለጋት? ቆይ እዛ መሄዷ ምን ይፈይድላታል? ብትሄድም እኮ ሁሉም አገር ለሷ አንድ ነው … የእኔን ሰላማዊ ጉዞ ከማስተጓጐል በቀር ምንም የምትሰራው የለም። በቃ እኔን የእሷ ጥገኛ ለማድረግ ነው! አዎ እንደማንኛዋም ተራ ተርታ ሴት፣ የሎተሪውን ገንዘብ በእጇ ካስገባች በኋላ ሳጥን ውስጥ ትከረችመዋለች፡፡ ከዚያስ? እኔን ለእያንዳንዷ ድምቡሎ እየነዘነዘች፣ ዘመዶቿን ትጠቅምበታለች!”
ኢቫን ዲሚትሪች፤ ወዲያው ስለ ዘመድ አዝማዶቿ ማሰላሰል ያዘ፡፡ እነዚያ መናጢ ወንድሞቿና እህቶቿ፤ እነዚያ ድሆች አክስቶቿና አጐቶቿ … ሎተሪ እንደደረሳት ሲሰሙ፣ እየተጓተቱ ይመጡና እንደ ለማኝ ማላዘናቸውን ይጀምራሉ፤ አንዳንዴም ራሳቸውን በይስሙላ ፈገግታ ሞልተው፣ የውሸት ውዳሴ ያወርዳሉ። እነዚህ  መናጢዎች! … በሃዘኔታ የሆነ ነገር ጣል ሲያደርጉላቸው! ሌላ ጨምሩ፤ ሌላ አምጡ ብለው ችክክ ይላሉ፡፡ አይሆንም ሲባሉ ደግሞ ስድብና እርግማናቸው አይጣል ነው፡፡
የራሱንም ዘመድ አዝማዶች አልዘነጋቸውም- ያውም ከእነ ፊት ገፅታቸው፡፡ በፊት ሁሉንም በቅን ልቦና ነበር የሚመለከታቸው፡፡ አሁን ግን በጣም አስጠሉት፤ ሲበዛ ቀፈፉት፡፡
“ቀበሮ ሁላ!” ሲል በጅምላ ወረፋቸው፡፡
የሚስቱም ገፅታ እንዲሁ ቀፋፊና አስጠሊታ ሆኖ ታየው፡፡ ድንገተኛ ቁጣ በልቡ ውስጥ ገነፈለ፤ በሚስቱ ላይ ያነጣጠረ! በክፋት ተሞልቶም እንዲህ ሲል አሰበ፤ “እሷ እኮ ስለ ገንዘብ አንዲት ነገር አታውቅም፡፡ ስለዚህ ቋጣሪ ናት፤ ስግብግብ! ሎተሪው ከደረሳት እኮ … 100 ሩብል ትወረውርልኝና አታስደርሰኝም … የቀረውን ትከረችመዋለች፡፡”
በዚህ መሃል ሚስቱን ቀና ብሎ ተመለከታት። አሁን ግን የይስሙላ ፈገግታ እንኳን ፊቱ ላይ አይታይበትም፡፡ ጥላቻ እንጂ፡፡ እሷም አየት አደረገችው - እንደሱው በጥላቻና በቁጣ እየገነፈለች፡፡ እሷም እንደ ባሏ በራሷ ምኞቶች፣ በራሷ ዕቅዶች፣ በራሷ ሃሳቦች… ስትብሰለሰል ነው የቆየችው፡፡ የባሏን ሃሳብና ምኞት ጠንቅቃ ተረድታለች፡፡ ሎተሪው ቢደርሳት መጀመርያ ሊነጥቃት የሚሞክረው ማን እንደሆነ አሳምራ ታውቃለች፡፡
“በሌሎች ሰዎች መስዋዕትነት የራስን የቅንጦት ህልም ማለም ግሩም ነገር ነው!” የሚል  መልዕክት ነው ዓይኗ ላይ የሚነበበው፡፡ “በፍፁም! … አታደርገውም! ቆሜ ነው ሞቼ!” አለች - ለራሷ፤ ባሏን እየተመለከተች፡፡ ኢቫን ዲሚትሪች ገፅታዋን በቅጡ አንብቦታል፡፡ ለዚህ ነው ደረቱ ሥር የጥላቻ ስሜት ዳግም መንፈራገጥ የጀመረው፡፡
ሚስቱን ለማብሸቅና ስሜቷን ለመጉዳት ክፉኛ ተጣደፈ፡፡ ከመቅፅበት የጋዜጣውን አራተኛ ገፅ ገለጠና በድል አድራጊነት ስሜት ጮክ ብሎ ማንበብ ጀመረ:-   
“ኮዱ 9,499 ነው፤ አሸናፊው የእጣ ቁጥር ግን 46 ነው! 26 አይደለም!”
ጥላቻና ተስፋ ከመቅፅበት ድራሻቸው ጠፋ፡፡ ለኢቫን ዲሚትሪችና ባለቤቱ፤ ቤታቸው ጠባብ፣ ጨለማ የወረሰውና ጣራው ዝቅ ያለ መሰላቸው። የበሉት እራትም የተስማማቸው አይመስልም፤ ሆዳቸው ውስጥ ተቀምጦ የከበዳቸው እንጂ! ምሽቱም የማይገፋና አሰልቺ ሆነባቸው፡፡
“አሁን ይሄ ምን ማለት ነው?” አለ ኢቫን ዲሚትሪች፤ በቁጣ ገንፍሎ፡፡ “የትም ቦታ አንድ እርምጃ ሲራመዱ ቁርጥራጭ ወረቀት፣ ትርፍራፊ ምግብ፣ የፍራፍሬ ልጣጭ ነው የሚገኘው፡፡ ክፍሉ ጨርሶ መጥረጊያ ነክቶት አያውቅም፡፡ ውጡ ውጡ እንጂ ተቀመጡ አያሰኝም፡፡ በቃ ነፍሴ ወደ መቀመቅ ትወርዳለች፡፡ ቀጥ ብዬ ሄጄ ራሴን የመጀመርያው ዛፍ ላይ እሰቅላለሁ!”   

Read 3784 times