Print this page
Monday, 23 December 2013 10:24

ብቻ አንድ ጊዜ ፈገግ በል!

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(1 Vote)

ብቻ አንድ ጊዜ ፈገግ በል!
ነ.መ

ሙት - ዓመት በቃል አይገባም፡፡
ቢሆንም አሴ ቢሆንም፤
     በመንፈስ ፅናት ውስጥ‘ኮ
     በመንፈስ ጽዳት ውስጥ‘ኮ
        ጊዜም ቦታም ተነው ቢያልቁ፣ ድምፅ አለ ሩቅ እሚያግባባ!
     የሚናገር ልሣን አለ፣ ያገርን ፈገግታና ዕንባ!
       ነብስ - አጥንት ድረስ ዘልቆ፣ ዕውነቱ ሲያስቡት
     ቢያምም
     ባገር ነገር ሆድ - አይቆርጥም፣
     ተራቁታ ብናያት እንኳ፣ እርቃኗም የእኛ ነው
     ዛሬም!
አሴ!
አልበራ ባለው መብራትም፣ እኛ ተስፋችን
ይበራል
አላናግር ባለው ስልክም፣ እኛ ድምፃችን
ይሰማል
ባላደገ የዕድገት ቀንም፣ እኛ ቀናችን ይነጋል
ለተቀጨ ምኞት ሳይቀር፣ ራዕይ ወጌሻ ሆነናል
ተሰደው በተመለሱ፣ ብዙሃን ግፉዓን ዕድል
ሄደው ተሰደው በቀሩም፤ ብዙሃን መንገደኞች
ውል
ስለአገር መጮህ አይቀርም፣ በዕልቆ - መሣፍር
ምሬት ቃል
ስለዚህ ካለህበቱ፣ አሴ ዛሬም ፈገግ በል!
የልብን መሙላት ነው የሰው - ድል፣ አሴ ሰላም
እንባባል!!
በሳቅህ ቁጥር ነው ሀሳብህ፣ እንደ ኤርታሌ
እሚያቃጥል
በሳቅህ ቁጥር ነው ህልምህ፣ እንደተራራ
እሚሰቀል
በሳቅህ ቁጥር ነው ዓላማህ፣ እንደ ሊማሊሞ
እሚገዝፍ
በሳቅህ ቁጥር ነው አድማስ፣ እሚዳረስ ከፅንፍ
ፅንፍ
ብቻ አንድ ጊዜ ፈገግ በል!...
ፈገግ በል አሴ፤ ፈገግ በል……

(ለአሰፋ ጐሣዬ 9ኛ ሙት ዓመት) ከመላው ቤተሰብና ከወዳጆቹ ታህሣሥ 11/ 2006 ዓ.ም

Read 2915 times