Saturday, 28 December 2013 10:18

“...በመሰረተ ሀሳቡ... መመለስ የለባትም...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(0 votes)

“...ማንኛዋም እናት አደጋ ውስጥ እንዳለች ማሰብ ያስፈልጋል...” “...ከተወሰኑ አመታት በፊት ነው ...ወሬው በአዲስ አበባ ከተማ የተሰማው፡፡ በጊዜው በመገናኛ ብዙሀንም ተደምጦአል... ሲሉ አንድ ተሳታፊያችን የሚከተለውን መልእክት አድርሰውናል፡፡” “...ሁኔታው ያጋጠመው ምናልባትም የዛሬ 15/ አመት ገደማ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዲት እናት በምጥ ተይዛ በየሆስፒታሉ ስትሄድ ...አልጋ የለንም ...አልጋ የለንም የሚል ምላሽ ታገኛለች፡፡ ከዚያም በስተመጨረሻ በሄደችበት ሆስፒታል አልጋ የለም ተብላ ወደመኪናው ስትመለስ በድንገት የሆነ ነገር ከሰውነቷ ዱብ ይላል፡፡ ለካንስ ልጁዋ ሊወለድ ደርሶ ኖሮአል፡፡ በዚህ ሳቢያም ብዙ ውዝግብ ተነስቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በእርግጥ ዛሬ ...ዛሬ ሁኔታዎች ተሻሽለዋል ቢባልም አልፎ አልፎ ግን ችግር ሊኖር ይችላልና እስኪ አነጋግራችሁ መልስ ስጡን...” ያሉን አቶ ወንድአጥር ማስረሻ ከአዳማ ናቸው። የዚህ አምድ አዘጋጅም በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታልና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመገኘት የእናቶችን የሪፈራል አሰራር በመመልከት ለአንባቢ ብላለች፡፡በጋንዲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጥ/ እናቶች በምጥ ሰአት ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ተቀባይነት የማይኖራቸው ምን ሲጎድል ነው? መ/ በመሰረተ ሀሳቡ አንዲት ሴት ምጥ ይዞአት ለመውለድ ወደ ሆስፒታል ስትመጣ መመ ለስ የለባትም፡፡ አገልግሎቱን ማግኘት ይገባታል፡፡ በእርግጥ የማዋለድ አገልግሎቱ የሚሰ ጥባቸው ጤና ተቋማት ደረጃ ይለያያል፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጥባቸውም ቦታዎች በመጀመሪያ ሆስፒታሎች ከዚያም ጤና ጣብያዎች እንዲሁም ከጤና ጣቢያም በታች እስከ ጤና ኬላ ድረስ ያሉ ተቋማት በተመሳሳይ ደረጃ የማዋለድ ስራውን አይሰሩም፡፡ ነገር ግን የምጡን አመጣጥና የእናትየውን ጤንነት እየተከታተሉ ጤና ኬላዎች ወደ ጤና ጣቢያ ጤና ጣቢያዎች ደግሞ ወደሆስፒታል ሪፈር እንዲያደርጉ አሰራሩ ይፈቅዳል፡፡ አንዲት እናት በጤና ጣቢያ ለመውለድ ከምትቸገርባቸው ምክንያቶች... ምጡ በትክክለኛው መንገድ ካልመጣ፣ የጽንሱ አቀማመጥ ትክክል ካልሆነ፣ ደም በጣም እየፈሰሳት ከሆነ እና ሌሎች የጤና ችግሮች ካሉ እንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች ካጋጠሙ ጤና ጣቢያዎች ወደሆስፒታል ለተሻለ አገልግሎት ሊልኩ ይችላሉ፡፡ ሆስፒታሎች የተላኩላቸውን እናቶች ተቀብለው የማዋለድ አገልግሎቱን መስጠት ይጠበቅ ባቸዋል እንጂ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ከአንዱ ሆስፒታል ወደሌላው ሆስፒታል መላክ የለባቸ ውም፡፡ በሆስፒታል ማንኛውንም እርዳታ ሊሰጥ የሚችል የሰው ኃይል ማለትም ከእስፔሻል ሐኪም ጀምሮ እስከ ሚድዋይፍ ድረስ መኖር አለበት፡፡ በሆስፒታል የደም ባንክ አገልግሎት አለ፡፡ በሆስፒታል የኦፕራሲዮን አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በሆስፒታል በቂ አልጋዎች ወላድ እናቶችን መጠበቅ አለባቸው፡፡ ጥ/ ከመሰረተ ሀሳብነት ደረጃ ባለፈ ተግባራዊነቱ ምን ይመስላል? መ/ በአዲስ አበባ ባሉ ሆስፒታሎች የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ብዙ ጊዜ አልጋዎች እየሞሉ ምጥ የያዛቸው እናቶች ከሆስፒታል ወደ ሆስፒታል የሚላኩበት አሰራር አለ፡፡ ኦፕራሲዮን የሚያደርግ ሐኪም የለም ወይንም ኦፕራሲዮን የሚሰራበት እቃ የለንም በሚል እናቶች ወደሌላ ሆስፒታል የሚላኩበት አጋጣሚም ይስተዋላል። ከዚህም በተጨማሪ ውሀ የለም ወይንም መብራት የለም የሚሉ ምክንያቶችም የሚሰጡ አይጠፉም፡፡ በተለይ በጋንዲ ሆስፒታል አብዛኛው የሪፈራል ምክንያት የአልጋ ጥበት ነው፡፡ በሆስፒታሉ በቀን ከ25-30/ እናቶች የማዋለድ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ከዚህ በላይ ግን በቀን እስከ 40 ወይንም ከዚያ በላይ እናቶች ቢመጡ ለማዋለድ የሚያስችል አቅም ስለማይኖር በየቀኑ ከአምስት እስከ ሰባት የሚሆኑ እናቶች በየቀኑ ወደሌላ ሆስፒታል ሪፈር ሊባሉ ይችላሉ፡፡ ጥ/ ምጥ የያዛትን ሴት ሪፈር ለማለት የምጡ ደረጃ ወይንም የሴትየዋ አቅም የሚለካበት አሰራር አለ? መ/ በጋንዲ ሆስፒታል በጭራሽ ሪፈር የማይባሉ እናቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ... በምጥ ሰአት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ያለባት ከሆነ፣ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ በኦፕራሲዮን የተገላገለች ከሆነች፣ የማህጸን መከፈት ደረጃው ስምንት ሴንቲ ሜትር እና ከዚያ በላይ ከሆነ፣ ልጁ በከፍተኛ ሁኔታ መታፈን ያለበት ከሆነ እና ሕይወቱን ሊያሳጣው ይችላል ተብሎ ከታመነ፣ የጽንሱ አቀማመጥ በአግድም በመሳሰለው ሁኔታ ካለ እናትየው ሪፈር አትደረግም፡፡ ከላይ ከተጠቀሱትና መሰል ምክንያቶች ውጭ ግን ምጡ አሳሳቢ ወይንም አስቸጋሪ ካልሆነና ጊዜ የሚሰጥ ከሆነ አልጋ ከሌለ ሪፈር ይባላሉ፡፡ ማንኛዋም እናት ሪፈር ከመባልዋ በፊት ግን በሐኪም ታይታ እና ተመዝግቦ ነው ውሳኔው የሚሰጠው፡፡ ጥ/ ምጥ የያዛት ሴት ወደሌላ ሆስፒታል ሪፈር ስትባል ልትሄድ የምትችልበት ሆስፒታል ይነገራታል? ወይንስ እራስዋ ፈልጋ እንድትሄድ ነው የሚደረገው? መ/ ይህ አገልግሎት አሁን በተጀመረው አሰራር ውስጥ የተካተተ ነው፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳድር ጤና ጥበቃና አዲስ አበባ ጤና ቢሮ አንድ ላይ በመሆን የአሰራር መረብ ዘርግተዋል፡፡ በዚህ አደረጃጀትም እያንዳንዱ ሆስፒታል በስሩ ከስምንት እስከ አስራ አንድ የሚደርሱ ጤና ተቋማት ተደልድለውለታል፡፡ ለምሳሌም ጋንዲ ሆስፒታል በስሩ አስራ አንድ ጤና ጣቢያዎች አሉ፡፡ እነዚህ አስራ አንድ ጤና ጣብያዎች ምጥ የያዛቸውን ሴቶች ሪፈር የሚያደርጉት በቀጥታ ለጋንዲ ሆስፒታል እንጂ ለሌላ ሆስፒታል አይደለም። በዚሁ መንገድ ሁሉም የጤና ጣብያዎች ሪፈር የሚያደርጉት ለተመደቡበት ሆስፒታል ብቻ ነው። ስለዚህ አሁን በተጀመረው አሰራር ኮማንድ ፖስት፣ ጤና ጣቢ ያዎቹና ሆስፒታሎቹ በመናበብ የሚሰሩበት ነው፡፡ በየሆስፒታሉም ላይዘን ኦፊስ የሚባል ቢሮ ስለተቋቋመ በዚህ የተመደበው ኦፊሰር ከሌላ ሆስፒታል የላይዘን ኦፊሰር ጋራ የስልክ ግንኙነት በማድረግ አልጋ የት እንዳለ በማመቻቸት አገልግሎቱን ወደሚያገኙበት ተቋም እንዲሄዱ ይደረጋል፡፡ የእናቶች ተገቢውን የጤና አገልግሎት የማግኘት አሰራር የመንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ስለሆነ ሆስፒታሎችን እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማትን በአስፈላጊው ደረጃ እያሟሉና የተሻለ አሰራር እየዘረጉ ስለሆነ አሁን የተሻለ አሰራር ይታያል፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የእናቶች ሪፈራል አሰራር በአብዛኛው ከጋዲ መታሰቢያ ሆስፒታል አሰራር ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ዶ/ር አብዱርቃድር መሐመድ ሰይድ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሜዲንል ዳይሬክተር የሚከተለውን ብለዋል፡፡ “...በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስር ስምንት የሚሆኑ ጤና ጣቢያዎች ተመድበዋል፡፡ ከእነዚህ ጤናጣቢያዎች ጋር ሆስፒሉ በቅርብ እየተገናኘ የሚገጥሙዋቸውን ችግሮች በመወያየት የሚፈታበት አሰራር ተዘርግቶአል። በተለይም ምጥ የያዛቸው ሴቶችን በሚመለከት ሂደቱ እንዴት እንደነበርና ያጋጠመውን ችግር በመለየት በጤና ጣብያዎቹ ሊፈታ የማይችል ከሆነ በአገናኝ ባለሙያዎች አማካኝነት በመነጋገር ወደ ጥቁር አንበሳ እንዲመጡ እና አስፈላጊው ሕክምና ተደርጎላቸው እንዲወልዱ ይደረጋል። ማንኛዋም እናት አደጋ ውስጥ እንዳለች ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ምጡ ችግር አለበት የለበትም ወይንም በዚህ ጊዜ ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በድንገት ሊፈጠር የሚችለውን ነገር አስቀድሞ መገመትም የሚያስቸግርበት ሁኔታ አለ፡፡ ስለዚህ እናቶች ምጥ ይዞአቸው ወደሕክምና ተቋም ከደረሱ ጀምሮ ሁሉም ቦታ ትኩረት እንዲያገኙ ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አልጋ የማይኖር ከሆነ እና ችግሩ ብዙም አሳሳቢ ካልሆነ በአገናኝ መኮንኖቹ አማካኝነት በመነጋገር ወደሌላ ሆስፒ ታል የምንልክበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ አጠቃላይ የሪፈራል አሰራሩን በሚመለከት ብዙ የተሻሻለ ነገር ያለ ሲሆን ገና ብዙ መስተካከል ያለበት ነገር እንደሚኖር እናምናለን፡፡

Read 1570 times