Sunday, 05 January 2014 00:00

“ከሀብታም ቤት ጥብስ፣ ከድሀ ቤት ጥቅስ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(28 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለብርሀነ ልደቱ ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁማ!
እንግዲህ የበዓል ሰሞን አይደል… ያው ያለው “ፏ!” ይላል የሌለው “ዷ!” ይላል፡፡ ቂ…ቂ…ቂ
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… ይቺን ስሙኝማ…እሷዬዋ የዓመት ፈቃድ ነገር ወጣችና ሰው ሳያያት ከረምረም ብላ ትመጣለች፡፡ እናላችሁ… ስትመጣ ‘የቅቤ ቅል’ መስላ፣ ተመችቷት ነበር፡፡
ታዲያላችሁ… ወዳጆቿ “እንዴት ነው ነገሩ እንዲህ ያማረብሽ፣ ምን ተገኘ?” ምናምን ይሏታል፡፡ እሷም ከሀብታም ዘመዶቿ ዘንድ እንደ ከረመች ትነግራቸውና…ልጄ፣ “ከሀብታም መጠጋት ነው የሚያዋጣው…” ትላለች፡፡ እነሱም “ሀብታም ምን ያደርግልሻል፣ ይልቅ ከቢጤዎችሽ ከእኛ ጋር መሆኑ ነው የሚያዋጣው…” ምናምን አይነት ‘የክብር ማስጠበቂያ’ ክርክር ያመጣሉ፡፡
እሷም እነሱ ቤት የምታገኘውንና ሀብታም ቤት የምታገኘውን ልዩነት ስትነግራቸው ምን ብትል ጥሩ ነው… “ከሀብታም ቤት ጥብስ፣ ከድሀ ቤት ጥቅስ አይጠፋም፡፡”
የእውነት እኮ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ጥቅስን የመሰለ ‘ቀን አሳላፊ’ አለ እንዴ! ልክ ነዋ…ኪሳችን ተራግፎ ውስጡን ብል ሲበላው፣ “እንዴት አደራችሁ” ለማለት ሂሳብ የምንጠየቅ እየመሰለን ስንሳቀቅ፣ ዕድሜ ለጥቅስና ለተረት…ምን እንል መሰላችሁ…“ያጣም ያገኝና ያገኘም ያጣና፣  ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!” አለቀ፡፡ በተረት መልክ የመጣ ‘ፓራሲታሞል’ በሉት! የዚችኛዋ ተረት ኮሚክነቷ ምን መሰላችሁ…ይኸው “…ያስተዛዝበናል ይሄ ቀን ያልፍና!”  ስንል ስንት ዘመናችን ሆኖ…አለ አይደል…. የምንታዘበው እስኪመጣ ገና እየጠበቅን ነው!
ልጄ እንደ ዘንድሮ ከሆነ…አይደለም ቁልቁል መውረድ፣ ላይ የወጣው ሁሉ “ባትጋሩኝ!” እያለ ‘ገዢ መሬቱን’ እያጠናከረ ‘በእኛ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት’… ከተረታችን ጋር ረስተውናል፡፡ ስሙኝማ…እግረ መንገዴን አንድ የምትገርመኝ ተረት አለች…“ሀብታም ለሰጠ የድሀ እንትን አበጠ” ምናምን የምትል፡፡ አሁን…ጭንቅላት፣ ትከሻ፣ አንገት የመሳሰሉ የሰውነት ክፍሎች እያሉ…አለ አይደል… እዛ ድረስ ‘ቁልቁል’ መውረድ ለምን አስፈለገ! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…“ያጣም ያገኝና…” የሚለውን ለመሞከር ችግሩ ምን መሰላችሁ…መሰላሉ የለማ! ‘ብልጦቹ’ መሰላሉን ከወጡበት በኋለ  ገፍተው ከመሬት ያጋድሙታል መሰለኝ፣ መሰላል አጥቶ የሚንከራተት መአት ነው፡፡ በእርግጥ ሲወረድ በምን እንደሚወረድ ራሱን የቻለ ጥያቄ ቢሆንም ገና ለገና ስለ‘መውረድ’ አይወራም፣ እዚህ አገር እኮ ያለውም የሌለውም ኑሮን በኪሎ ሜትር ማስላት ትቶ በሚሊ ሜትር እየደመረና እየቀነሰ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እንዳወራነው አንዳንዴ ሰዉን ስታዩት “ነገ” የሚባል ነገር የሌለ ነው የሚመስለው፡፡
“መሰላሉን ያላችሁ፣ እስቲ እንያችሁ…” ምናምን የሚል ዘፈን ይቀናበርልንና በየኤፍ.ኤሙ. ኮምፐልሰሪ ምናምን ነገር ይሁንልን፡፡ (ልክ ነዋ… ኤፍ.ኤሞችን ስናዳምጥ አንዳንድ ጊዜ ዘፈኖች ብቻ ሳይሆኑ ዘፋኞቹም ‘ቢያንስ አንዴ’ እንዲሰሙ ሰርኩላር ነገር ያለ እየመሰለን ቸግሮናላ!)
እናማ…እኛ ግን ጥቅስ መጥቀሳችንን፣ ተረት መተረታችንን እንቀጥላለን፡፡ ልክ ነዋ…ያለመሳቀቅ ልንጠቀምባቸው ከምንችልባቸው ነገሮች መሀል ዋናዎቹ ጥቅሶችና ተረቶች ናቸዋ! ለዛውም ቢሆን ‘ኤዲት’ የተደረጉትን!
እና እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ…የሆነ ዝም ያለ ነገር አልበዛባችሁም! ልክ ነዋ…የሚጮህ ነገር ቢኖር፣ ወይ አዲስ የመዝሙር አልበም ሲያስተዋውቁ፣ ወይ “ሎተሪ ግዙ” ስንባል፣ ወይ “ለአቶ እከሌ መታከሚያ የአቅማችሁን አዋጡ…” ምናምን ሲባል ነው፡፡ መአት የምንነጋርባቸው ከእለት ኑሯችን ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን … ነገርዬው ማን ማንን አምኖ ይናገራል ነው ነገሩ፡፡ እንደ ድንገት አምልጦን ሹክ ያልነው ነገር፣ ዙሪያውን ተሽከርክሮ በመጨረሻ ለእኛው ሲነገረን… አለ አይደል…
“ተናግሮ አናገረኝ ይወደኝ ይመስል፣
ሄዶ ተናገረ የላኩት ይመስል”
ብለን እንተርታለን፡፡ አሁን ‘መተረት’ ባንወድ ኖሮ ይቺን ማደንዘዣ ከየት እናገኛት ነበር! እንኳንስ ቤታችን ጥቅስ አልጠፋ!
ያቺ የለመድናት…
“ከእንግዲህ ነገሬን ከከንፈሬ አልለቅም
የሰው ዶሮ አለና ከአፍ፣ ከአፍ የሚለቅም”
ብለን ተርተን ‘ጭጭ’ ነው፡፡ ምን ይደረግ…‘ሄዶ ተናጋሪ’ ሲበዛ ከቤታችን ‘የማይጠፋውን ጥቅስ’ ለቀም አድርገን ማስታገሻ እናደርገዋለን፡፡
“ዝምታ ለበግም አልበጃት
አሥራ ሁለት ሆነና አንድ ነብር ፈጃት”
የምትለው ተረት…አለ አይደል…የሆነ እርፍና ነገር ቢኖራትም ያለችው ግድግዳችን ላይ ሳትሆን እንጨት ሳጥናችን ውስጥ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…አለ አይደል… “የዛሬውን አያድርገውና…” እያልን በሉካንዳ በኩል ባለፍን ቁጥር በናፍቆት ‘ሽንጥና፣ ታናሽ’ ላይ ዓይኖቻችንን እንተክላለን፡፡ አሀ… መቶ ብር ሦስት ኪሎውን ‘ሻሽ የመሰለ’ ሥጋ ከፋሽኮ ቪኖ ጋር ገዝተን ለቡና ይተርፈን የነበረበት ጊዜ ትዝ ይለናላ! አሁንስ?…አሁንማ ፓሪስ የሚታየው የፒካሶ የስዕል ዓውደ ርዕይና ዶሮ ማነቂያ የሚታየው የሥጋ ‘ዓውደ ርዕይ’ አንድ ሆኖብናላ! ብናጉረመርም ምን ይፈረድብናል! ይሄኔ ነው ተረት የማስታገሻ ሚናዋን የምትወጣው…
“ቁርበት ምን ያንጓጓሃል ቢሉት ባያድለኝ ነው እንጂ የነጋሪት ወንድም ነበርኩ አለ”
የምንንጓጓ ቁርበት መሆናችንን ብቻ አትዩብና! የእውነት ግን እኮ ብዙዎቻችን የምር ቁርበቷን መስለናል! እነ እንትና…ምነው ደብዘዝ አላችሁብኝሳ! ችግር አለ እንዴ!
እናላችሁ… እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ…መቼም ሁልጊዜ እንደምንለው ዘንድሮ እርስ በእርስ መተማመን ቀንሶ የለ! እናላችሁ…አይደለም የማናወቀው ሰው ሲያደናቅፈው “እኔን ድፍት ያድርገኝ…” ምናምን ሊባል የቅርባችን ሰው እንኳን አደናቅፎት ሲንገዳገድ “አንተ ሰውዬ ጭራሽ ደንባራ ሆነህ ቀረኸው…” ምናምን መባባል እየለመደብን ነው፡፡ እናላችሁ…“እባክህ አንድ ችግር ገጥሞኝ…” ለሚለው ሰው እኔ ወንድምህ እያለሁ ምናምን ከማለት ይልቅ…ችግሩ ይጋባብን ይመስል እንሸሻለን፡፡ እናማ ዕድሜ ለ‘ተረት ወዳጅነታችን’… ተረት አናጣለትም…
“ውሀ ለሚወስደው ሰው በትርህን እንጂ እጅህን አትስጠው”
እንልና…በትርም ስሌለን “እንደ ፍጥርጥርህ…” ብለን እንተወዋለን፡፡
ስሙኝማ… የጥቅስ ነገር ካነሳን ሚኒባስ ታክሲ ውስጥ በብዛት እናያለን፡፡ በእርግጥ መልካም ያልሆኑ በተለይ ሴቶች ላይ የሚጠነክሩ ጥቅሶች አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሪፎች አሉ፡፡ አንድ ወዳጄ ያያት ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ…“የከፋው ሲሞት፣ የደላው መች ቀረ፡፡” ይቺ ዝም ብላ የምትመስል ጥቅስ ውስጧ መአት ነገር አላት፡፡ ዘመናችንን የምታሳይ አይመስላችሁም! ‘ስለደላቸው’ ብቻ ሰማይን ለመርገጥ የሚቃጣቸው በበዙበት ዘመን…አሪፍ ጥቅስ ነች፡፡
እኔ የምለው…‘አንደርግራውንድ’ መነጣጠቅ እንዲህ ለየለት ማለት ነው! የምንሰማው እኮ አንዳንዴ…“እነ ስቴፈን ስፒልበርግ ስንት ታሪኮች አምልጧቸዋል…” ያሰኛል። ታዲያ…እንደው ተገኘ ተብሎ…አለ አይደል…ጨዋታው የፊፋንም፣ የካፍንም ሆነ የማንንም ህጎች የማያከብር ይሆንና ‘አራቱን ወር’ ሲደፍን ቁልጭ ነዋ! ይሄኔ ዕድሜ ለተረቶች ወዳጅነታችን…ህመም ማስታገሻ አናጣም…
“ለፍቅር ብተኛት ለጠብ አረገዘች”
እንላለን፡፡ ከዛ ጠብ ይመጣል፡፡ ሁለቱም “የመውደድ መድሃኒት…” ምናምን ሲሉ የቆዩትን “አንተ ነህ…” “አንቺ ነሽ…” ነገር ይመጣል፡፡ ይሄኔ ለተረትና ጥቅስ ምስጋና ይግባውና ምን ይላል መሰላችሁ…
“ያንቺን አትበይ ገንዘብ የለሽ
የሰው አትበይ ምግባር የለሽ”
እናላችሁ… እየጠቀስንም፣ እየተረትንም ጊዜን እንገፋለን፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ እግረ መንገዴን ይቺን ስሙኝማ…የሆነች እንትናዬን ‘ኪሶሎጂ ለማጦፍ’ ስትፈልጉ እንዲህ ትሏታላችሁ…“ሕይወት ምንድነች? ሕይወት ፍቅር ነች፡፡ ፍቅር ምንድነው? ፍቅር መሳሳም ነው፡፡ መሳሳም ምንድው? ጠጋ በዪኝና ምን እንደሆነ ላሳይሽ፡፡” አሪፍ አይደል! እኔም በ‘ፌስቡክ’ ያገኘሁትን ‘ሼር’ ላድርግ ብዬ ነው!
ሌላ ‘ሼር’ እንዳላደርጋችሁ ደግሞ አንድ ተረት ትዝ አለችኝ…
“ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡”
አለቀ፡፡
እናላችሁ…እንኳንም በእኛ ቤት ‘ጥቅስ’ አልጠፋ። የ‘ጥብሱ’ ያለመኖር ‘ወና ያደረገውን’ ባይሞላውም… ማስታገሻ ይሆነናላ!
መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንላችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 17699 times