Sunday, 05 January 2014 00:00

የአውራምባ የጉዞ ማስታወሻ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(5 votes)

(ከተወካይ አሊያም የዙምራ ወራሽ፤ ነው ብዬ ካሰብኩት ከኑሩ ጋር ስለዙምራ የምናደርገው ውይይት ላይ ነበር ያለፈው የጉዞ ማስታወሻዬ የተቋረጠው ከዛው ልቀጥል)
“ስለ ዙምራ እስቲ ንገረኝ?”
“ዙምራ፤ ገና በልጅነቱ … ‘እያንዳንዱን ነገር እኔ እማየው ከተፈጥሮ ሥዕል ነው፡፡ ከዛ ተነስቼ ነው ሚዛኑን የማየው፡፡ አብዛኛውን ከወላጆቼ እወስዳለሁ፡፡ ይሄ የወንድ ሥራ ነው፣ ይሄ የሴት ሥራ ነው፣ ይሄ ወገን ነው፣ ይሄ ባዕድ ነው፣ የሚባለውን ነገር ከዚያው አያለሁ፡፡ ይሄ ነገር ምንጩ ምንድነው? ብዬ ከቤት ስወጣም የማየው የምሰማውም ያው ነው፡፡ ለምን የሚለው ጥያቄ በውስጤ እያደገ ነው የመጣው” ይላል፡፡ ይሄንን ነገር ለማጥናት እስከ 13 ዓመታት ፈጅቶበታል፡፡ ትላልቅ የሃይማኖት አባቶችን፣ ኦርቶዶክሶችን፣ ሙስሊሞችን ያነጋግር ነበር፡፡ ስለአመሠራረቱ አንተ ራስህ በአካል ከአንደበቱ ብተሰማው በጣም ጥሩ ነበር…” አለኝ ኑሩ፡፡
“እናትዬዋ ምን ዓይነት ሰው ነበሩ፤ አንተ ስትደርስባቸው?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“በዕድሜ በሰል ብላ ነው ያገኘሁዋት፡፡ በእርግጥ በአስተሳሰቡዋም ታላቅ ሰው ናት፡፡ ለሁሉም ሰው አክብሮት አላት፡፡ ትንሽ ትልቅ አትልም ትመክራለች፡፡ የእሱን የህይወት ታሪክ ስንጠይቃት፤ ለመግለጥ ትቸገራለች፡፡ ‘ከባድ ነው! ከወለድኳቸው ልጆች ሁሉ ከእርግዝና ጀምሮ ልዩ ነው፡፡ በእጅጉ ልዩ ነው! አወላለዱም ልዩ ነው’ አለች፡፡ የቤት ሥራዋን ሰርታ ወደ ጉልጓሎ ልትሄድ ነሐሴ 16 ቀን አካባቢ ነው፤ 64 ወይ 65 ዓ.ም ይመስለኛል፤ (ሌላ ሰው እንጠይቃለን መረጃውን ቆይ) የምታስጐበኘዋን ልጅ ጠርቼ ታብራራልሃለች አለ፡፡  
“መጀመሪያ የኅብረት ሥራ ማህበራቱን (ኮኦፕሬቲቮቹን) እንጨርስ” አልኩት፡፡
“ኮኦፐሬቲቮቹ እንዴት ተቋቋሙ? አየህ፤ ባህሉ እዚህጋ አለ፡፡ ኮኦፕሬቲቮቹ የሁሉም ናቸው፡፡ ገበሬ ማህበሩ፣ የአውራምባ ማህበረሰብ ከዛ የተውጣጣ ማህበር አለ… እናንተ የራሳችሁ ኮኦፕሬቲቭ አላችሁ ማለት ነው?” አልኩት፡፡
“አዎ” ይሄ አንድ አለ፡፡ ያካባቢው ቀበሌ የኅ/ሥ/ማህበር አለ በመመሪያ ደረጃ የሚፈቀደው ከአንድ ቀበሌ ላይ አንድ ኮኦፕሬቲቭ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን መመሪያ ነው በሚል የማህበረሰቡን እሴት መረበሽ የለብንም ከሚል፤ ታሰበበትና ከህጉ ወጣ ብለንም ቢሆን እንደዚህ ያለውን አስተሳሰብ ማጐልበት አለብን በሚል፤ ኮኦፕሬቲቩ ራሱን ችሎ ተቋቋመ። 2000 ዓ.ም ነው ዕውቅና ያገኘው፡፡ በክልሉ ፍትሕ ቢሮ፡፡ ከዚያ ኮኦፕሬቲቩ ተጠናከረ”
“ምን ይሠራል?”
“የዕደ ጥበባት ሥራዎች ይሠራል፡፡ ግብርናውንም ይሠራል፡፡ ወፍጮ፣ ሱቅ ላይም ይሠራል፡፡ ሻይ ቤት ምግብ ቤት፣ እንግዳ ማረፊያ ነገሮች አሉት፡፡ ምናልባትም ወደፊት የዘይት ሞተርም ይኖረዋል፡፡ ቦታው፣ አዳራሹ ተዘጋጅቷል፡፡ ሞተሩ ተገዝቷል፡፡”  
“ፈንዱን ከየት ታገኙታላችሁ”
“ለምሣሌ የዘይት ሞተሩን የገዛንበትን፣ ከህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት፤ ነው ያገኘነው፡፡ 50% የእኛን ጨምረን ማለት ነው፡፡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ የእኛው ነው፡፡ ሞተሩም የእኛ ብዙ ድርሻ አለበት፡፡ የእንግዳ መቀበያው በእኛው ነው የተገነባው” (ይህ guest room በቀን 100 ብር የሚያስከፍል ዘመናዊ ሽንት ቤትና መታጠቢያ ያለው ነው፡፡ እዚያ ውስጥ ያረፈ 5ኛ ቀኑን የያዘ ፈረንጅ አለ፡፡) ማህበረሰቡ ከሚያመርተው፣ ከሚገበየው፣ ከሚሸጠው ነው፡፡”
“አሁን የምጐበኛቸው የሚፈተሉት፣ የሚሸመኑት ሁሉ ወደ ሽያጭ ይሄዳሉ ማለት ነው?”
“ይህ ዶኩሜንት የሂሳቡን ውጣ ውረድ ያሳይሃል፡፡ ኮሚቴ አለው። ማህበረሰቡ ለብቻ አለው፡፡ ግዢ አለው፡፡ ሽያጭ አለው፡፡ በየመልኩ በሂሳብ የተሠራ ነው፡፡ ወደ ክፍፍል ስንመጣ፤ ልናንቀሳቅሰው የምንችለው ምን ያህል ነው? የሚለው በኮኦፕሬቲቭ ህጉ መሠረት አለው፡፡ ያ ይወሰናል።”  
“ስሙ ማን ይባላል?”
“የአውራምባ ማህበረሰብ የገበሬዎችና ዕዳ ጥበብ ሁለገብ ህብረት ሥራ ማህበር”
“ከጄክዶ ጋር እንዴት ነው መጀመሪያ ግንኙነታችሁ?”
“ስንገናኝ አቶ ተስፋዬ፤ አቶ ሙሉጌታ (ኃላፊዎቹ) የማህበረሰቡን ሁኔታ በሚዲያም ሰምተው መጥተው ይጐበኙት ነበርና አንዳንድ ነገሮችን አብረን ብንሠራ፤ እኛ እምንሠራው አብዛኛው ነገር ከእናንተ ሥራ ይመሳሰላል የሚል ሃሳብ ነበር፡፡ በተለይ ወላጅ ያጡ ህፃናትን ከመደገፍ አኳያ ብንሠራ የሚል ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ተቆፍሮ አገልግሎት መስጠት ያልቻለም የጉድጓድ ውሃ አለ ስለሱም ተወያየን፡፡ ሁለት ሶስቴ ለጉብኝት ይመጡ ነበረ፡፡ በዚያው አጋጣሚ ግንኙነቱ ተጀመረ፡፡ ለጐበዝ ተማሪዎች የሚያስፈልጉ ድጋፎች ላይም ሃሳብ ቀረበ፡፡ የአንድ ዓመት ፕሮጄክት በዛ ሠራን፡፡ በደንብ አቀድን ተፈራረምን፡፡ ተጠናቀቀ በ2001 ዓ.ም. -በ2002 ገደማ!! በጠቅላላው በህፃናት፣ ከአረጋውያን ላይ በጣም አተኮርን፡፡ በመሠረቱ ከመረዳት፤ መርዳት ብንችል ነው ጥሩ እሚሆነው! … ስለዚህ ሠርተን እምንመልሰው ፈንድ ቢሆን በሚል የመጀመሪያው የ170,000 ብር ፕሮጀክት ሆነ፡፡ በሚቀጥለው የ300 መቶ ሺህ ብር፡፡ በዓመቱ ሠርተን መለስን፡፡ ከሞዴልም አኳያ ከአስተሳሰብም አኳያ በጣም የተመቸ ነበር-ለሁሉም፡፡ ለእነሱ በጣም ደስ አላቸው … ወለድም አላሰቡብንም፡፡ ሁለት ዙር ተሠራ፡፡ የዘይት ሞተሩ 3ኛ ዙር ነው፡፡
“እንዴት ዘላቂ ይሆናል የኮኦፕሬቲቩ አካሄድ ያሳድገዋል? ወይስ የማ/ሰቡ ባህላዊ አካሄድ?” ብዬ ጠየኩት፡፡
“ዘላቂ ሊያደርገው የሚችለው የማ/ሰቡ አስተሳሰብ፤ ባህልና ዕድገት ነው ብዬ አስባለሁ … ኮኦፕሬቲቭ በህግ እሚመራ ነው፡፡ ህግ ሲለወጥ ይለወጣል፡፡ በእርግጥ እሱን መከተል ይቻላል ከተቻለ፡፡ መሠረተ ጉዳዩ ግን የማ/ሰቡ ጥንካሬ ነው፡፡ ይህን ያልኩበት ምክንያት በደርግ ሥርዓት የተቋቋመ የህብረት ሥራ ማህበር ደርግ ሲበተን፤ አንድም የለም፡፡ ይህ ማ/ሰብ ግን በራሱ ፀንቶ ቀጥሏል-ተሸጋግሯል፡፡ ስለዚህም ማ/ሰቡ የራሱ ባህል፣ አኗኗር፣ ዕድገት፣ ለውጥ … ነው ያስቀጥለዋል ብዬ እማምነው፡፡
“ከኢየሩሣሌም ጋራስ ምን ያህል ትዘልቃላችሁ? ፈንዱ ሲያልቅ ያልቃል?”
“ያው እንግዲህ፣ በመሠረቱ በፈንድ ብቻ አይደለም፡፡ ያለን ትሥሥር ሂሳብ አሠራር፣ አያያዝ፣ ሪፖርት አጠቃቀም… የፕሮጀክት አነዳደፍ፣ ሪፖርት አደራረግ … ሰፊ ሥልጠና ነው የሰጡን በያመቱ! አክብረው ነው የሚጠሩን! … ከብዙ ሰዎች አገናኝተውናል፣ ብዙ አካባቢዎች ሄደን የልምድ ልውውጥ እንድናገኝ አድርገውናል … እስከ ድሬ ድረስ ተንቀሳቅሰናል … ናዝሬት፣ ቢሾፍቱ፣ ጐጃም ወዘተ … ልምዱ ውስጣችን ይቀጥላል፡፡ … ማ/ሰቡን ያከብራሉ … ሥርዓታችንን እንኳ ወደ ሌላ ለማስተላለፍ የእኛን ይሁንታ ነው የጠየቁት! … ትልቅ ድርጅት ነው እየሩሣሌም!...”
ወደ ወ/ሮ ጥሩ ሰው (አስጐብኚዬ ዞርኩኝና) “እስቲ ደግሞ አንቺ እምትይኝን በይኝ?” አልኳት፡፡ “ማነሽ? ምንድነሽ? የት ትደርሻለሽ? ጥሩ ሰው እስቲ አንድ በይኝ”
ሳቂታ ናት፡፡ ጠይም ናት፡፡ ጠይም ሳቅ ሳቀች፡፡
“ጥሩ ሰው ፈንቴ እባላለሁ፡፡ የሥራ ድርሻዬ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብዬ፣ ለምን ዓላማ እንደመጡ ጠይቄ ጉብኝት ካሉ ማስጐብኘት፣ የማ/ሰቡን ባህል ማስተዋወቅ፣ ከዶ/ር ዙምራም ጋር አገናኚኝ ካሉኝ ማገናኘት ነው፡፡”
“የማህ/ሰቡ በሩ ነሽ ማለት ነዋ!! …
ጥሩ ሰው የሳቅ ሰው ናት … የጠይም ቆንጆ ሳቋን ስቃ ነው ጥያቄዬን መመለስ የጀመረችው፡፡ አንደበተ-ስል ናት!
 “አባትሽ አቶ ፈንቴ አሉ? ምን ይሠራሉ?”
“አቶ ፈንቴን አላቃቸውም … የ19 ዓመት ልጅ ሆነሽ ነው አባትሽ የሞተ ትለኛለች እናቴ…
እናቴ እዚሁ ናት… ከነዙምራ ጋር መስራች ሆና ቆይታ እኔን እዚህ አሳደገችኝ”
“አንቺ አ.አ. መጥተሽ መኖር አትፈልጊም?” ሳቋን ለቀቀችው፡፡ “እዚሁ አዲሳባን መፍጠር ነው እምፈልገው! ጠንክረው ከሠሩ ዓለም የደረሰበት ቦታ ማ/ሰብን ማድረስ ይቻላል! … ቦታ ቢቀይሩ፣ የትም ቢደርሱ፤ ሰው የአስተሳሰብ ለውጥ ካላመጣ ባለበት ጠንክሮ መሥራት በታማኝነት! የትም ቦታ አዲሳባን መፍጠር ይቻላል!”
“የማ/ሰቡ ህግጋት ምንድናቸው?”
“ዋናውና ትልቁ ለሰው ልጆች ክብር መስጠት!! ከገንዘብ ይልቅ ትልቁ ሀብት፤ ሰው ነው፡፡ ገንዘብ ሁለተኛና ሰውን የሚደግፍ የሚገነባ ነው ሚሆነው! ሌላው የሰውን ልጆች በልዩነታቸው ሳይሆን ባንድነታቸው ነው ምናምነው! ነጭም እንሁን ጥቁር ያንድ ሐረግ ፍሬዎች ነን! እንጂ ያዳም ዘር አልተቀየረም ብሎ ሚያምን ማ/ሰብ ነው! በሥነ - ምግባሮች በኩልም መጥፎዎቹን አስወግደን፣ ጐጂና ጠቃሚ ብለን ጐጂዎቹን ላንመለስባቸው አስወግደን፣ ጠቃሚዎቹን በተግባር እየሠራን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ነው! ዙምራ የኛን ወላጆች ካገኘና ከመሠረተ ጀምሮ፤ ይህን አስተሳሰብ ተግባራዊ አድርገው እየቀጠሉት ነው የቆዩት፡፡ እኛም ያንኑ ይዘን ተመችቶን እያስፋፋነው ነው፡፡ ዓለም እንዲያውቀው፣ ሁሉን ባለበት እንዲኖረው ነው እምንፈልገው!”
“እንዴት ይሰፋል?”
“ሊሰፋ እሚችለው ስንወስደው ነው! ዙምራ ከኛ ወላጆች ጋር ሲመሠርት እሱ ከህፃንነቱ ጀምሮ ቢሆንም፤ ዓላማ የተማሩ ሰዎች እንዲያገኙት ነው የተነሳው፡፡ የተማሩ ሰዎች እነማናቸው፤ የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ የቀለም ምሁሮች ናቸው፡፡ እነሱ ካገኙት ህዝባቸው የሚነሳው በነሱ ነው! በነሱ ጉያ ነው! …ሁሉም ወስዶ ሲያስፋፋው ዓለም አንድ ይሆናል ብለን እናስባለን!”
“እየዞረ ያስተምራል ዙምራ?”  
“ከህፃንነቱ ጀምሮ እየዞረ የሀሳቡ ተካፋይ ለማግኘት ይሞክር ነበረ! እናቱ እምትገልፅልን የ4 ዓመት ህፃን ሆኖ ጀምሮ በዚህ መሠረተ - ሀሳብ እንደተነሳ ነው! በ2 ዓመቱ እንዳዋቂ ይጠይቅ ነበር፡፡ በ4 ዓመቱ ስለ ሰው ልጅ መሠረታዊ ኑሮ ይጠይቅ ነበር፤ ነው እናቱ ምትለው! በ4 ዓመቱ ከተነሳባቸው ሀሳቦች 1ኛው የሴቶች እኩልነት ነው! አባቱ በናቱ ላይ በሚያሳድረው ጫና ተነስቶ ነው!
ሴት እናት ነች፤ ወንድ አባት ነው፤ አለቀ፡፡ እናቴና አባቴ እኩል መብት የማይኖራቸው ለምንድን ነው? የዱር ሥራ ላይ ገበሬዎች ናቸው … አብረው ሲሠሩ ውለው ማታ ላይ ሲመለሱ ያባት ሥራ ዱር ይቀራል፤ የእናት ሥራ ግን ቤት እንጀራ ትጋግራለች… ወጥ ትሠራለች፣ … ያ መቅረት አለበት፡፡ ወንዱም መሥራት አለበት!
ድንጋይና ድንጋይ ተፈጭቶ ቤት ተሰርቶ ቤተሰብ ታስተዳድራለች እናቲቱ፡፡ እሱ ቢፈልግ ይተኛል፣ ቢፈልግ ይቀመጣል፡፡ ሥራው ለምን የሷ ብቻ ይሆናል? ይላል ዙምራ! የቤቱ ሥራ ለእናቴ ብቻ የሆነበት ለምን ነው? ስለዚህ መጀመሪያ የሚያስፈልገው የሴቶች እኩልነት ነው” አለ፡፡
(2ኛው) የህፃናት መብት ነው! ህፃናት እግረ-ተከል ከሆኑ ጀምሮ አላቅማቸው ሥራ ይሰጣቸዋል፡፡ አቅማቸው አልችል ካለ ለምን አጠፋህ ለምን አበላሸህ? የስሜት ማውጫው ዱላ ነው! ለምን? ህፃናት ህይወት አደሉም ወይ? ያላቅማቸው ብትሩ ኬት መጣ? ነው! 3ኛው) በጤናም ሆነ በእርጅና የደከሙ ሰዎችን ሁሉም እያለፋቸው ይሄዳል፡፡ … ሌላው በልቶ፣ ጠጥቶ ሲሄድ ደካሞች ይወድቃሉ፡፡ ለሰው ደራሹ ሰው ነው፡፡ እኛም አንድ ቀን ያው ነን-ደጋፊ ያስፈልገናል፡፡ ደካሞችን ያንን ዕድል ለምን እናሳጣቸዋለን?
4ኛው) ሰውን ሰው ሲዋሸው፣ ሲቀጥፈው፣ ሲደበድበው፣ ሲገለው፣ አያለሁ እሰማለሁ … በጥቅሉ በራሳችን ላይ ሊሆን የማንፈልገውን በወገኖቻችን ላይ የምንፈፅመው ለምንድነው? ይህን ከሠራንስ ከእንስሶቹ በምን ተሻልን? ይህን አስተሳሰብ የአራት ዓመት ህፃን ሆኖ እንዳነሳው፤ እናቱ ለእኛ ታወራልን ነበር፡፡ እሱ ግን አላስታውስም ነው ሚለው። እስከ 88 ዓ.ም የዙምራ እናት ከእኛጋ ነበረች፡፡ አባቱ በህፃንነቱ ነው የሞቱት፡፡ የአካባቢው ሰው የ4 ዓመት ህፃን ሆኖ ይሄን ካሰበ ታሟል፣ አብዷል አለው፡፡ “የማይወጣ ጥጃ ከማሠሪያው ይታወቃል” እንዲሉ፤ ይህን አስተሳሰብ ካራመደ ነገ ምን እንደሚሠራ አናውቅም፤ እየተባለ ታሟል ይሉት ገቡ፡፡ እስከ 13 ዓመቱ እቤተሰቡ ጋር ይቆያል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ያለንበት ፎገራ ወረዳ ነው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኝ ወረዳ እስቴ ነው፡፡ ዙምራ እስቴ ነው አገሩ፡፡ በ13 ዓመቱ የሀሳቡ ተካፋይ ለማግኘት ከአገር አገር መዞር ነው ያሰበው፡፡ የመጀመሪያው ጉዞዬ ከእስቴ ተነስቼ ወደ ጐጃም ለ5 ዓመታት ተጓዝኩ፡፡ ሰዎች በተሰበሰቡበት የማገኘውን አጋጣሚ 4ቱን መሠረተ - ሀሳብ አካፍላለሁ፡፡ ይህን ሳካፍላቸው እንደቤተሰቦቼ ዕብድ ነህ ጅል ነህ አላሉኝም፤ ይላል፡፡ ሀሳቤን በግርምት ይመለከቱታል፡፡ “እምትናገሪው ነገር መልካም ነው፤ ግን ማን ይወስደዋል ከማለት ውጪ የሚከተለኝ አላገኘሁም ይላል፡፡ የ13 ዓመት ልጅ በመሆኑ “አንቺ” ብለው ነው የሚጠሩት! … የሚቀበለኝ አላገኘሁም፡፡ ስለዚህ ወደ ቤተሰብ ተመልሼ፣ እርሻ እያረስኩ፣ ባመቱ የማገኘውን ምርት፣ ለአካባቢው ደካሞች ባከፋፍል፣ አንድ የህሊና እረፍት አገኛለሁ ብዬ በማሰብ ወደ እስቴ ተመለስኩ፡፡ ፊት 13፣ በስደት 5 ዓመት፤ 18 ዓመት ሆኖታል፡፡ ቤተሰቡን ሄዶ ትዳር ልይዝ ነው፣ ሴት ፈልጉልኝ ሲላቸው፤ “በሽታው ለቆት ነው ትዳር ታሰበ” … “በሽታው ባይለቀው ኖሮ ትዳር አያስብም ነበር” -ይሉት ነበር፡፡ ሴቷን ፈልገው ትዳር ይመሰርታል … ትዳር መሥርቶ፣ ያርሳል ያመርታል … ምርቱን ግን ባካባቢው ለወደቁ ደካሞች ማከፋፈል ነው ያሰበው! የኔ ደስታዬ እሱ ነው፤ እሚለው ዙምራ! እሱን በማደርግ ጊዜ ቤተሰቦቼ “አይደለም እንዲያውም በሽታ ጨምሮ ነው የመጣው … አልበላም፣ አልጠጣም፣ አልታደለም … ‘የሱን ገንዘብ ዘመድ እንኳን አላገኘውም ለባዒድ ነው እሚሰጠው’ አሉኝ፤ አለ፡፡ እዚህ ላይ 5ኛ) ጥያቄ ያነሳው ዙምራ ‘ከሰው ልጆች ላይ ባዕድ የምትሉት የትኛውን ነው? ዘመድስ የምትሉት የትኛውን ነው? ብሎ ጠይቋል ቤተሰቡን፡፡ ከ7 ትውልድ በኋላ ያለው ባዕድ፣ ከዚያ በታች ወገን/ዘመድ ነው ብለውታል፡፡ ከ7 ትውልድ በኋላ ያለው ባዕድ ይሆናል ያለው ማነው? ንገሩኝ አላቸው፡፡ በእኔ በኩል ነጭ ጥቁር ማረግ የፈጣሪ አሠራር ነው፡፡ ሰዎች ብቻ ሳይሆን እንስሳትንም፣ መሬትንም … ብንወስድ አንድ ቦታ ነጭ አንድ ቦታ ጥቁር፤ እሱን ለፈጣሪ እንተወውና ሰዎቹ ሁሉ ያንድ ፍሬ ሐረግ ፍሬዎች ነን! የእኔ ገንዘብ ለባዕድ ሳይሆን ለዘመዶች ነው እሚሄደው ይልና ይረዳና፤ ለሀሳብ ብቸኛ ነው-ብቻውን መኖር አይችልም-ከአገር አገር እንዲሁ በጋ በጋ ላይ ሲዘዋወር፤ ከዕለታት አንድ ቀን ከእስቴ ተነስቶ እዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎችን ያገኛል፡፡ ይህን ሀሳብ ሲያካፍላቸው፣ ስለተቀበሉት፡፡ እዚህ ቦታ ብመላለስ እቅዴ ይሳካል ሲል ለብዙ ዓመታት በተከታታይ በጋ በጋ ላይ እየተመላላሰ፤ በትክክል ሀሳቡን መቀበላቸውን ሲያረጋግጥ ነው በ64 ዓ.ም. መጥቶ እዚህ ከእኛ ወላጆች ጋ ሊኖር የቻለው፡፡ ሲመሠርቱም 4ቱን መርሆች ይዘው ነው፡፡ ሴት በሴትነቷ እናት ነች፣ ወንድ በወንድነቱ አባት ነው፡፡ የሥራን አጋርነት ፈጥረን መሄድ መቻል አለብን፡፡ ሴት የወንዱን ሥራ ብትሠራ ያባቷ ሥራ ነው፡፡ ወንድ የሴቷን ሥራ ቢሠራ የእናቱ ሥራ ነው። ችግሩ ምኑ ላይ ነው፡፡ በጋራ ስንኖር የጠብ ምንጭን ማስወገድ አለብን። የጠብ ምንጭን አስወግደን፣ ሰላምን ዘርግተን፣ ገነትን ፈጥረን መሄድ መቻል አለብን! ነው ያላቸው፡፡ በጋራ ማህበራዊ ኑሮ  ስንገባ መጀመሪያ መወገድ ያለበት ይሄ ነው! ጠብ እንዴት ይቀራል ብለህ አሰብክ? ተብሎ ሲጠየቅ፤ ለጠብ የሚያነሳሱ ሁለት ነገሮች ናቸው (1) መጥፎ አነጋገር (2) መጥፎ አሠራር፡፡ እነሱን ካስወገድናቸው ጠብ የለም፡፡ ስሙም የለም፡፡ ሥርም አይኖረውም፡፡ ለጠብ የሚያነሳሳን በሀሳብም፣ በአሠራርም ራስ ወዳድነት ሲበዛ ነው! መብት ለመብት ተከባብረን ከሄድን ጠብ የለም። ስምም አይኖረውም! እሺ ምድራዊ ገነትንስ እንዴት ነው መፍጠር የምንችለው? ብለውታል፡፡ ምድራዊ ገነትን እኛ የምንችለው ነው፡፡ ማንም ሰው መጥቶ እንዲፈጥርልን አንጠብቅም፡፡ ምድራዊ ገነት የሚፈጠረው አንድ ሰው ችግር ሲደርስበት ዝም ብለን መመልከት ሳይሆን፤ ሁላችንም እጃችንን አውጥተን የዛን ሰው ችግር መርዳት ማስወገድ ነው! (የጉዞዬ ማስታወሻ የመጨረሻውና ከዙምራ ጋር ያደረግሁት ውይይት ይቀጥላል)  

Read 3186 times