Sunday, 05 January 2014 00:00

ማህበራዊ የጤና መድህን - አዲሱ የቤት ስራችን

Written by  አንተነህ ይግዛው
Rate this item
(7 votes)

ማማሟቂያ
አየለ ሞተ!... በድፍን ደብረ ማርቆስ ዝናው የናኘው ቀልደኛው፣ ተረበኛው፣ የቀን ሰራተኛው አየለ፤  ቋጠሮ ተሸክሞ ሲመላለስበት ከኖረው የከተማዋ ጎዳና ዳር ተፈጽሞ ተገኘ፡፡ ትናንት ቀልዱን ሰምተው ተንከትክተው የሳቁ፣ ዛሬ ጧት ሞቱን ሰምተው ተንሰቅስቀው አለቀሱ፡፡
ከጓደኞቹ ጋር መጠጥ ቢጤ እየቀማመሱ ሲጨዋወቱ አምሽተው፣  “በሉ ደህና እደሩ!” ተባብለው ተሰነባብተው ነበር፣ ሁሉም ወደ ማደሪያቸው ጉዞ የጀመሩት፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል፣ አየለ ደህና አላደረም፡፡ በእግሩ ላይ የነበረበት አካል ጉዳት ከስካሩ ጋር ተዳምሮ፣ ድንገት መዝነብ ከጀመረው ዶፍ ማምለጥ አላስቻለውም፡፡ ውሽንፍሩና ዶፉ ተባብረው ከመንገድ ዳር ካለ የጎርፍ መፍሰሻ ቱቦ ስር ጣሉት። ታግሎ የሚያመልጥበት እንጥፍጣፊ አቅም ያልነበረው አየለ ተሸነፈ።  ጨለማ ውስጥ እንደወደቀ ዶፍ ቀጠቀጠው፣ ጎርፍ አሰመጠው፡፡ ጧት ላይ አስከሬኑ ቱቦ ስር ደለል ሰርቶበት ተገኘ፡፡
የአየለ ሞት በመላ ደብረ ማርቆስ ተሰማ፡፡ ሁሉም ስለ አየለ አዘነ… እና ደሞ ተጨነቀ፡፡ ሃዘኑ ስለሞቱ፣ ጭንቀቱ ስለ ቀብሩ ነበር፡፡ በወግ በወግ አድርጎ የሚቀብረው የስጋ ዘመድ አልነበረውም፡፡ ዘመዱ ህዝቡ ነበር፡፡ በሸክም የሚያገኘው የማያወላዳ ገቢም የእድር አባል የሚያደርገው አልነበረም። በቅርብ የሚያውቁት ግለሰቦች አስከሬኑን አንስተው እንደሚሆን አድርገው ለመቅበር ወዲያ ወዲህ ማለት ጀመሩ። በዚህ ጊዜ ነው፣ የአየለን ሞት የሰሙ በከተማዋ የሚታወቁ ባለሃብቶች፣ ሟች በህይወት ሳለ የሰጣቸውን አደራ ይዘው ከያሉበት ብቅ ብቅ ያሉት፡፡
“እኔ ጋ 500 ብር አለው”፤“ይሄው… 350 ብር”፤“ለእኔ 150 ብር ነው የሰጠኝ… ይሄውላችሁ!” የሚለው የባለሃብቶች ያልተጠበቀ ንግግር ተደመጠ፡፡ አየለ ግን፣ አንድ ቀን ይህ እንደሚሆን ይጠብቅ ነበር፡፡ አንድ ቀን መታመሙ ወይም መሞቱ እንደማይቀር ያውቅ ነበር፡፡ “ቢያመኝ ጎረቤትን፣ ብሞትም መንግስትን ማስቸግር አልፈልግም!… ይህቺን ለክፉ ቀን አስቀምጡልኝ!” እያለ፣ ቋጠሮ ተሸክሞ የሚያገኘውን ገንዘብ በአደራ ያስቀምጥ ነበር፡፡ ይህን የሚያደርገው፣ ገንዘብ ይዞ መገኘትን የሚጠይቅ አንዳች አስቸገሪ ሁኔታ የሚከሰትበት ወሳኝ ወቅት ሊመጣ እንደሚችል ስለሚያውቅ ነው፡፡ የአየለ ጥንቃቄና አርቆ አሳቢነት በወቅቱ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ የግርምቱ ሰበብ ሁለት ነው፡፡ አንድም እታመማለሁ ብሎ በማሰብ መታከሚያ ገንዘብ ማጠራቀሙ፣ ሁለትም ከእለት ወጪው ቆጥቦ ለክፉ ቀን የሚቀመጥ ገንዘብ ማግኘቱ፡፡
እንዲህ እንደ አየለ ቀድመው ያልተዘጋጁ ወይንም ለመዘጋጀት አቅም የሌላቸው ብዙዎች ግን፣ ለሚያጋጥማቸው ድንገተኛ የጤና እክል መታከሚያ የሚሆን ገንዘብ በማጣት ለከፋ ስቃይና ለሞት መዳረግ ዕጣቸው ነው፡፡ ከፍለው ይታከሙበት በቂ ገንዘብ አጥተው፣ ከጤና ተቋማት ደጃፍ ሳይደርሱ በህመም ሲሰቃዩ ቆይተው ለሞት የሚዳረጉ በርካቶች ናቸው፡፡
ከዕለት ተዕለት ኑሮ ተርፎ ድንገት ለሚከሰት የጤና እክል መታከሚያ ተብሎ የሚቀመጥ በቂ ገንዘብ የሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል እምብዛም ነው፡፡ በህክምና ወጪ እጦት ተገቢውን ህክምና ማግኘት ተስኗቸው ለስቃይና ለሞት ከሚዳረጉ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል፣ በወርሃዊ ደመወዝ የሚተዳደሩ ተቀጣሪዎችና ጡረተኞች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡
በመንግስትም ሆነ በግል ተቋማት ለሚሰሩ ሰራተኞች ህክምና የሚውል የእርዳታ ገንዘብ ማሰባሰቢያ ቅጽ በየቢሮው ሲዞር መመልከት የተለመደ ክስተት ነው፡፡ ደመወዛቸው ቤተሰብ ከሚያስተዳድሩበት የወር ወጪ ተርፎ ለህክምና ክፍያ አልበቃ ብሏቸው፣ የመስሪያ ቤት ባልደረቦቻቸውን የገንዘብ ድጋፍ ለመጠየቅ የሚገደዱ ታማሚ ሰራተኞች ብዙዎች ናቸው። ችግሩ ግን በዚህ መልኩ አስር አምስት ተብሎ የሚሰበሰበው ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑና ለህክምና በቂ አለመሆኑ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ህመም እንደ ደመወዝ ወር ጠብቆ አይደለም የሚመጣው። ገንዘቡ የሚሰባሰበው ሰራተኛው ደመወዝ በሚቀበልበት ወቅት በመሆኑ፣ በተፈለገው ወቅት ደርሶ ታማሚውን የመታደግ ዕድሉ እምብዛም ነው፡፡
ድንገተኛ የጤና እክሎች ሲከሰቱ የሚፈጠረውን የህክምና ወጪ እጥረት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው፣ በችሮታ ላይ በተመሰረቱና አስተማማኝነት በሌላቸው መደበኛ ያልሆኑ መሰል የገንዘብ ድጋፍ ማፈላለጊያ መንገዶች አይደለም፡፡
የማህበረሰቡ የመረዳዳት ባህል የሚገለጽባቸው እንደ እድር ያሉ ተቋማት ቢኖሩም፣ አብዛኞቹ ከሞት በኋላ እንጂ በህይወት እያሉ ድጋፍ ለማድረግ ትኩረት የሚሰጡ አይደሉም። ብዙዎቹ የማህበረሰብ ዕድሮች ዕድርተኞች በህይወት እያሉ ከሚገጥማቸው የጤና ችግር ለሚላቀቁበት የህክምና ወጪ ሳይሆን፣ ከሞቱ በኋላ ለሚመጣው ቀብራቸውና ለንፍሮ ግዢ ገንዘብ የሚያወጡ ናቸው፡፡
እርግጥ በአንዳንድ አገራት ዕድሮችን የመሳሰሉ የማህበረሰብ ተቋማትን የበለጠ በማደራጀት እንደ አማራጭ የጤና ፋይናንስ ምንጭ አድርጎ ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡ እድሮችን እንደ አማራጭ ከመጠቀም ጋር ተያይዞ፣ በአፍሪካ ደረጃ የተሰራ ጥናት እንደሚያሳየው ጋናን በመሳሰሉ ጥቂት አገራት አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም በአብዛኞቹ አገራት ይህ ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም፡፡ ጥናቱ እንደሚለው በእድሮች አማካይነት በተበጣጠሰ ሁኔታ የሚሰሩ መሰል የጤና መድህን ስራዎች ዘላቂነታቸው አጠያያቂ ነው፡፡ አሰራሩ ከአባላት ቁጥርና ከመዋጮው ማነስ ጋር ተያይዞ በቂ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስችል ካለመሆኑም በላይ፣ ዕድሮች በተለያዩ ምክነያቶች የመፍረስ እድላቸው ከፍተኛ በመሆኑ የአማራጩን ዘላቂነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል፡፡
በአገራችንም ዕድሮችን እንደ አማራጭ መጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እ.ኤ.አ 2007 ዓ.ም በየካቲት ወር ዕድሮችን መሰረት ያደረገ የጤና መድህን አገልግሎት ለመዘርጋት ታስቦ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በጅማ ከተማ የተመረጡ 4 ቀበሌዎች ዙሪያ የተሰራው የናሙና ጥናት ከእነዚህ አንዱ ነው፡፡ የከተማዋን ማህበረሰብ ፍላጎትና የዕቅዱን አዋጪነት ለመገምገም ታስቦ የተሰራውና፣  ‘የጅማ ከተማ ዕድሮችን በአማራጭ የጤና ክብካቤ አገልግሎት የፋይናንስ ምንጭነት መጠቀም’ የሚለው የዚህ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው፣ ማህበረሰቡ በእድሮች አማካይነት የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን ፍላጎቱን አሳይቷል፡፡ በዚህ የናሙና ጥናት ጥያቄ ከቀረበላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች 76.5 በመቶው  ፈቃደኝነታቸውን ገልጸዋል። ቀደም ብሎ በአገር አቀፍ ደረጃ የተሰራ ጥናትም በአገሪቱ የእድር አባል ከሆነው ቤተሰብ 94.7 በመቶ ያህሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት አለው፡፡
ችግሩ ግን፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ባልተደራጀ ሁኔታ የሚከናወነው ይህን መሰሉ አሰራር፣ ረጅም ርቀት የሚያስኬድና የህግ ማዕቀፍ ተበጅቶለት ዜጎችን በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ የሚያደርግ አለመሆኑ ነው፡፡ ይልቁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ለሚታየው የጤና መድህን አገልግሎት ተጠቃሚነት ፍላጎት በተደራጀ፣ መንግስታዊ እውቅና ባለው፣ የአገሪቱን የጤና ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ባማከለና ዜጎችን የበለጠ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ምላሽ መስጠት ተመራጭ ይሆናል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት ይህን መሰሉ ያልተደራጀና አስተማማኝ ያልሆነ አካሄድ ለዜጎች የጤና ወጪ ጥያቄ ሁነኛ ምላሽ የማይሰጥ መሆኑን በመገንዘብ ነው፣ አስተማማኝ የሆነና በአግባቡ የተደራጀ የጤና መድህን ዋስትና ስርዓትን ለመዘርጋት ከረጅም ዘመናት በፊት ጥረት ማድረግ የጀመሩት።
የማህበራዊ የጤና መድህን፣ ጅማሮና ተሞክሮ
 አውሮፓዊቷ ጀርመን የአለማችን ዘመናዊና አሃዳዊ ማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት መነሻ ናት፡፡ ጊዜው ደግሞ እ.ኤ.አ በ1883 ዓ.ም፡፡ ከዚያ በፊት በአገሪቱ የነበሩትን የተበታተኑና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረቱ የመድህን ማህበራት ወደተቀናጀ፣ በማዕከላዊ መንግስት ወደሚደጎምና ወደሚመራ እንዲሁም ግዴታን መሰረት ወዳደረገ ስርዓት እንዲለወጥ ያደረገው፣ የአገሪቱ ቻንስለር የነበረው ኦቶቫን ቢስማርክ በወቅቱ ያወጣው ህግ ነበር፡፡
ጀርመንም ሆነ ሌሎች አገራት የጤና መድህን ስርዓቶቻቸውን አደረጃጀት በሂደት የማስተካከል እርምጃ ወስደዋል፡፡ ከተበታተኑና በፈቃደኝነት ላይ ከተመሰረቱ የማህበረሰብ መረዳጃ ማህበራትነት፣ ወደ አገር አቀፍና በማዕከላዊ መንግስት ህግ የተደገፉ ተቋማትነት በማሸጋገር ዜጎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል፡፡ የዚህን አሰራር ጠቀሜታ የተረዱት የተለያዩ የአፍሪካ አገራትም፣ ባለፉት 25 አመታት የተለያየ አደረጃጀት ያለው የጤና መድህን ዋስትና ለመዘርጋት ጥረት አድርገዋል፡፡
‘የማህበራዊ የጤና መድህን ስኬት፣ ውድቀትና መልካም ተሞክሮዎች በሰብ ሰሃራ የአፍሪካ አገራት’ በሚል ርዕስ ኤ.ኤም ስፒወርስና ግሪት ጃን ዲናት ለንባብ ያበቁት ጽሁፍ እንደሚያሳየው፣ በአፍሪካ አገራት በጤና ፋይናንስ ምንጭነት ከሚውሉት አማራጮች ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ከታካሚዎች የሚገኝ ክፍያ ነው፡፡ መረጃው እንደሚያሳየው፣ በሁሉም የአፍሪካ አገራት እ.ኤ.አ በ2007 ከወጣው የጤና ወጪ 50 በመቶው ከግል ምንጮች የተገኘ ሲሆን፣ ከዚህ ወጪ 71 በመቶው የተገኘውም ታካሚዎች ከከፈሉት የህክምና ወጪ ነው፡፡ ይህም በታካሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫና የሚፈጥር መሆኑን ጸሃፊዎቹ ይናገራሉ፡፡
ጋና፣ ሱዳን፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች በርካታ የአፍሪካ አገራትም በዜጎቻቸው ላይ የሚደርሰውን የህክምና ወጪ ጫና ለማቃለልና የጤና አገልግታቸውን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ፣ ማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት ዘርግተው መተግበር ከጀመሩ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ አገራቱ ስርዓቱን በመዘርጋታቸው፣ ዜጎቻቸው በተለይም ደግሞ ድሆች በከፍተኛ የህክምና ክፍያ ሳቢያ የተለየ የኑሮ ጫና እንዳያድርባቸው በማድረግ የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ከማዳረስ ባለፈ፣ የፋይናንስ አቅማቸውን በማሳደግ የጤና አገልግሎታቸውን ለማስፋፋት ችለዋል፡፡
አገራቱ የማህበራዊ የጤና መድህንን ተግባራዊ ለማድረግ ትኩረት የሰጡት፣ አሰራሩ ዜጎች ድንገት ከሚከሰቱ በሽታዎች ለመዳን ጥሪታቸውን አሟጠው በሚያፈሱት ያልታሰበ የህክምና ወጪ ሳቢያ ለከፋ የኑሮ ቀውስና ለድህነት እንዳይዳረጉ የሚያስችል መሆኑን በመገንዘብ ነው፡፡
በህክምና ወጪ ለድህነት መዳረግ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የአለም አገራት ችግር ነው፡፡ ጥሪታቸውን አሟጠው ለህክምና ወጪ በማዋል ለኑሮ ቀውስና ለከፋ ድህነት የሚዳረጉ የተለያዩ የአለም አገራት ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ የአለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው፣ እ.ኤ.አ በ2012 ብቻ ለራሳቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው ህክምና ከፍተኛ ወጪ በማውጣታቸው ሳቢያ ለከፋ ድህነት የተዳረጉ የተለያዩ አለም አገራት ዜጎች ቁጥር ከ150 ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ አገራት ይህን ችግር በመቅረፍ ረገድ ሁነኛ መላ ያሉት የጤና መድህን ስርዓት መዘርጋትን ነው፡፡
ማህበራዊ የጤና መድህን ለምን?
ማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት፣ ተጠቃሚው በጤና ተቋማት አገልግሎት በሚሻበት ወቅት አብዛኛውን ከኪስ የሚከፈል ወጪ በመቀነስ ጥራት ያለውና ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያገኝ የማድረግ አላማ ያለውና፣ በመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማሩ ዜጎችን የሚያቅፍ ትርፍን መሰረት ያላደረገ የመድህን ስርአት ነው፡፡
የማህበራዊ ጤና መድህን ስርአትን መዘርጋት፣ የአገራትን አጠቃላይ የጤና ዘርፍ ልማት በማፋጠንና የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የስርአቱ ተጠቃሚ የሆኑ አገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡ የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች፣ የጤና አገልግሎት ክፍያ የሚከፍሉት አገልግሎት በሚፈልጉበት ወቅት ሳይሆን ቀደም ብሎ በተተመነ ሂሳብ መሰረት በየጊዜው በመሆኑ የክፍያ ጫና አይኖርባቸውም፡፡ ክፍያው ለህመም ተጋላጭነትን ሳይሆን ገቢን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ሀብታሙ ድሃውን፣ ጤነኛው በአንጻራዊ ደረጃ ታማሚውን እንዲደግፈው በማስቻል የጤና ወጪን ጫና በመቀነስ ረገድም ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ የመክፈል አቅምን መሰረት ሳያደርግ ሁሉም ተጠቃሚ እንደየ ፍላጎቱ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆንም ያስችላል፡፡
መደጋገፍን፣ፍትሃዊነትና አሳታፊነት አመላካች መርሆዎቹ ያደረገው ይህ የጤና መድህን አይነት፣ በአባላት መካከል አንድነትንና መተባበርን በመፍጠር፤ ያለው የሌለውን፣ ጤነኛው ታማሚውን የሚደጉምበትና፤ ሁሉም የመድህን ስርአቱ አባል እንደ ገቢው መጠን ከፍሎ፣ እንደ መዋጮው ሳይሆን እንደ ህመሙ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው፡፡ ግለሰቦች ወይም ቤተሰቦች አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ ወይም ክፍያ አማካይነት የጤና መታወክ በሚድረስባቸው ጊዜ ከሚያጋጥማቸው ያልታሰበ ከፍተኛ የህክምና ወጪ የሚድኑበት ከመሆኑም በላይ፣ አባላት ገንዘባቸውን የሚያዋጡ በመሆናቸው የመድህኑን አሰራር በባለቤትነት እንዲመሩና እንዲከታተሉ ዕድል የሚፈጥር ስልት ነው፡፡
አሰራሩ የጤና አገልግሎት ገዢውንና አገልግሎት ሰጪውን (የጤና ተቋማትን) በመለያየት ከአገልግሎት ሰጪዎች ጋር በመደራደር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና የተሸለ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለማግኘት ያስችላል፣ ተጠያቂነትንም ያጎለብታል፡፡ የማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት ለጤና አገልግሎት የሚውለውን ፋይናንስ በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም መረጃዎች ያመለክታሉ። ህብረተሰቡ በታክስ መልክ ከሚጠየቅ ይልቅ በጤና መድህን ስርዓት ለአገልግሎቱ እንዲከፍል መጠየቁ፣ የባለቤትነት መንፈስ በመፍጠር ገንዘቡን ለማዋጣት የበለጠ ፈቃደኛ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አሰራሩ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታክስን የመሰብሰብ ውሱን አቅም ላላቸው አገራት ተመራጭ ነው፡፡
 እኛስ የት ጋ ነን?
በአገሪችን የጤና ዘርፍ ልማትና የጤና አገልግሎት አጠቃቀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ የተለያዩ ተግዳሮቶች አንዱ መሆኑ ይነገራል - የጤና ፋይናንስ ስልት ውስንነት፡፡ በኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር የፖሊሲ፣ ፕላንና ፋይናንስ ጄኔራል ዳይሬክቶሬት ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ለአገሪቱ የጤና ዘርፍ የሚያስፈልገው ፋይናንስ ከመንግስት (31 በመቶ)፣ በአገልግሎት ወቅት በቀጥታ ከተጠቃሚዎች ከሚሰበሰብ  ክፍያ (30 በመቶ)፣ ከልማት አጋሮች (37 በመቶ)ና ከመድህንና ከሌሎች የግል ምንጮች (2 በመቶ) የሚሸፈን ነው፡፡
ይህም ለጤናው ዘርፍ የሚውለው ወጪ አነስተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ፣  በአገልግሎት ወቅት ከተጠቃሚዎች ከሚገኘው ክፍያ የሚሸፈነው ወጪ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ፣ በተጠቃሚዎች በተለይም በድሆች ላይ የተለየ ጫና ስለሚያሳድር የጤና አገልግሎትን በፍትሃዊነት ለማዳረስ አስቸጋሪ መሆኑን ያመላክታል፡፡ በጤና ፋይናንስ ላይ በሚታየው ውስንነትና በሌሎች ምክነያቶች በአገሪቱ ያለው የጤና አገልግሎት አጠቃቀም ዝቅተኛ መሆኑ፣ በህብረተሰቡ የጤንነት ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ማድረጉና በአገሪቱ ጤና ነክ የልማት ግቦች አፈጻጸም ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም፡፡
ከአገሪቱ ጠቅላላ የጤና ወጪ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ተጠቃሚዎች በአገልግሎት ወቅት በሚከፍሉት ክፍያ የሚሸፈን መሆኑ፣ የአከፋፈል ስርዓቱ ከፍትሃዊነት አንጻር የራሱ የሆነ ችግር ያለበት መሆኑን ያሳያል፡፡ ሃብታሙም ሆነ ድሃው ለጤና የሚከፍሉት ክፍያ የገቢ መጠናቸውን ያገናዘበ ሳይሆን እኩል ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም። ተጠቃሚዎች ለጤና አገልግሎት ክፍያ የሚፈጽሙት አገልግሎቱን በሚያገኙበት ጊዜ መሆኑ፣ በተጠቃሚዎች ላይ ጫና የሚያሳድርና አገልግሎቱን ለማግኘት የሚያዳግት፣ በተለይ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን ደግሞ ገንዘባቸውን በማሟጠጥ ወደ ከፋ ድህነት እንዲገቡ የሚያደርግ ነው። ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችም የየራሳቸው ችግሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡  ለዚህ ነው፣ መንግስት አገሪቱ የጤና ግቦቿን ለማሳካት የጤና ፋይናንስ ስልቷን ህብረተሰቡ የጤና አገልግሎትን ለመጠቀም በሚገፋፋና በሚያስችል መልኩ መቃኘት እንደሚኖርባት ድምዳሜ ላይ የደረሰው፡፡ የጤና መድህንን እንደ አንድ የፋይናንስ ምንጭ በመጠቀምና በአገሪቱ የጤና ዘርፍ  የሚስተዋለውን የገንዘብ ጉድለት በመሙላት የጤና አገልግሎቱን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግም ትኩረት የሰጠው፡፡
መንግስት በአገሪቱ የጤና መድህንን በመዘርጋትና የጤና ፋይናንስ አከፋፈልን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና መተሳሰብን የሚያጎለብት እንዲሆን፣ የጤና አገልግሎት ሽፋንን እንዲስፋፋና ተጠቃሚነትም እንዲጨምር በማድረግ የአገሪቱን ዜጎች የጤንነት ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አስፈላጊ ህጋዊ ማዕቀፎችንና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ፈጥሯል። የጤና አገልግሎት ሽፋን መስፋፋት ለአገሪቱ የተቀላጠፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን በመገንዘብ፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ የጤና ሽፋንን ለማረጋገጥ በመንግስትና በተጠቃሚው ህብረተሰብ መካከል ወጪን መጋራት ወሳኝ ሆኖ በመገኘቱ፣የማህበራዊ ጤና መድህን በአባላት መካከል መደጋገፍን በመፍጠር ፍትሃዊና የተሸለ የጤና አገልግሎትን ለማጎልበት የሚረዳ ቀጣይነት ያለው የጤና ፋይናንስ ማሰባሰቢያ ስልት በመሆኑ፣  የማህበራዊ ጤና መድህን በአዋጅ ቁጥር 690/2002 በነሃሴ 2002 በተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ ውሏል፡፡
የጤና መድህን ስርዓቱን በአግባቡ የሚያስፈጽም ተቋም መገንባት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም፣ የሚንስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 191/2003 ባወጣው የማቋቋሚያ ደንብ  የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲን ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። የጤና መድህን ስርዓቱን የማስፈጸም አላማ ይዞ የተነሳው ኤጀንሲው፣  ተጠሪነቱን ለሚንስትሩ በማድረግ ከተቋቋመ ጀምሮ ባሉትአመታት ተቋማዊ አቅሙን የማደራጀትና ስርአቱን በአግባቡ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኤጀንሲው በአገሪቱ ሊዘረጉ ከታቀዱት የጤና መድህን ስርዓቶች አንዱ የሆነውን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን በ13 ወረዳዎች የሙከራ ትግበራ አስጀምሯል። ከመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ ውጭ ያሉትንና ቋሚ ገቢ የሌላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በቤተሰብ መዋጮና ከክፍያ ነጻ በሆነ አሰራር የጤና መድህን ስርዓቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ ህብረተሰቡ በጉዳዩ ዙሪያ በቂ መረጃ እንዲኖረውና ጠቀሜታውን በመገንዘብ ለእቅዱ ተፈጻሚነት የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት በመስራት ላይ የሚገኘው ኤጀንሲው፣ መገናኛ ብዙሃን ስለ ጤና መድህን ተገቢውን መረጃ ለህብረተሰቡ በተገቢው መንገድ ማሰራጨት የሚችሉት፣ ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ሲኖራቸው ነው በሚል እሳቤም ለጋዜጠኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ኤጀንሲው በቅርቡ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአገሪቱ የማህበራዊ የጤና መድህን ስርዓት አባላት የሚሆኑት፣ 3 ወርና ከዚያ በላይ የአገልግሎት ዘመን ያላቸው ሁሉም የመንግስት ሰራተኞች፣ 10ና ከዚያ በላይ የሰራተኞች ቁጥር ባላቸው የግል ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች፣ ሁሉም መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች እና የጡረታ ባለመብቶች ናቸው፡፡
በማህበራዊ የጤና መድህን አዋጅ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ማንኛውም አሰሪ ሰራተኞቹን፣ የማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ደግሞ ሁሉንም የጡረታ ባለመብቶችን ለማህበራዊ የጤና መድህን በኤጀንሲው ዘንድ ማስመዝገብ ይኖርበታል፡፡ ኤጀንሲው በበኩሉ የአባላትን አመዘጋገብ በተመለከተ በሚያወጣቸው የራሱ መመሪያዎችን ተፈጻሚ ያደርጋል፡፡
ስርአቱ የአባላት መዋጮን፣ የአሰሪዎች መዋጮን፣ ከኢንቨስትመንት የሚገኝ ገቢን እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ምንጮችን የፋይናንስ ምንጩ በማድረግ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ የስርአቱ ተጠቃሚዎች አባላትና ቤተሰቦቻቸው ሲሆኑ፣ ይህም ከ18 አመታት በታች የሆኑ ልጆች፣ ቤተሰብ፣ ባል ወይም ሚስትን ያጠቃልላል፡፡
 የማህበራዊ ጤና መድህን አባላት በየወሩ ከሚያገኙት ደመወዝ ወይም የጡረታ አበል በመቶኛ ተሰልቶ የሚከፍሉት መዋጮ  የአረቦን ክፍያ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ አሰሪዎችም አባል በሆኑ ሰራተኞቻቸው ስም ከደመወዝ በመቶኛ የሚሰላ ገንዘብ ለመድህኑ ያዋጣሉ፡፡ የመዋጮው መጠን ከአገር አገር የሚለያይ ሲሆን፣ በአገራችንም ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባና ተመጣጣኝ የሆነ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት፣ ሰራተኞች ከደመወዛቸው 3 በመቶ ሲከፍሉ፣ አሰሪዎች ደግሞ ለሰራተኞቻቸው 3 በመቶ ያዋጣሉ። ጡረተኞች በበኩላቸው የጡረታ አበላቸውን 1 በመቶ ሲያዋጡ፣ መንግስትም ለጡረተኞች 1 በመቶ የሚከፍል ይሆናል፡፡
በአገሪቱ የማህበራዊ የጤና መድህን የሚሸፈኑ አገልግሎቶች ዋነኛ በሚባሉ የህብረተሰቡ የጤና ችግሮች ላይ ትኩረት ያደረጉና አባላቱ የሚፈልጓቸው እንዲሆኑ ለማስቻል ትኩረት ተሰጥቷል፡፡
በየደረጃው ከሚገኙት የጤና ተቋማት ጋር በተጣጣመ መንገድ በጤና መድህኑ ሊሸፈኑ የሚገባቸው አገልግሎቶች የጥቅም ፓኬጅ በጥናት ላይ ተመስርቶ ተዘጋጅቷል፡፡ የጥቅም ማዕቀፉ በመሰረታዊ የጤና አገልግሎት ማዕቀፍ (basic health service package) የተካተቱትን የፈውስ ህክምናዎችና ለህይወት አስጊ የሆኑ ህመሞችንና ጉዳቶችን ለማከም በየደረጃው ባሉ የጤና ተቋማት የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችን ያካትታል።  
ማንኛውም የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት ተጠቃሚ የተመላላሽ ህክምና፣ የተኝቶ ህክምና፣ የወሊድ አገልግሎት፣ የቀዶ ህክምናና በህክምና ባለሙያዎች የታዘዙ የምርመራ አገልግሎቶችና በኤጀንሲው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱትን መድሃኒቶች ማግኘት ይችላል። በማዕቀፉ ውስጥ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ተብለው የተካተቱት የጤና ችግሮች ያሉ ሲሆን፣ እነሱም ተላላፊና ተላላፊ በሽታዎች፣ የደም ግፊት፣ የልብ ችግር፣ የስኳር በሽታ፣ የካንሰር፣ የአእምሮ በሽታና የድንገተኛ በሽታ ህክምናዎች ናቸው፡፡
የማህበራዊ ጤና መድህን ስርዓት ማስፈጸሚያ ደንብ፣ በማዕቀፉ የማይካተቱ ብሎ ካስቀመጣቸው አገልግሎቶች መካከል፣ ከአገር ውጭ የሚደረግ ማንኛውም ህክምና፣ በተፈጥሮ አደጋዎች፣ በማህበራዊ ብጥብጥ፣ በወረርሽኝና ከፍተኛ አደጋ ባላቸው ስፖርታዊ ውድድሮች ለሚደርሱ አደጋዎች የሚደረጉ ህክምናዎችና አደገኛ እጾችን በመውሰድ ለተከሰተ ጉዳት ወይም ለሱስ ተገዢነት የሚደረግ ህክምና ይጠቀሳሉ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፣ በየጊዜው የሚደረጉ ከህመም ጋር ያልተያያዙ የጤንነት ሁኔታ ምርመራዎች፣ የስራ ላይ ጉዳቶች፣ የትራፊክ አደጋዎችና በሌላ የህግ ሽፋን የተሰጣቸው ሌሎች አደጋዎች፣ ለውበት ሲባል የሚደረጉ ቀዶ ጥገናዎች፣ የአካል ቀዶ ማዛወር፣ ድንገተኛ የኩላሊት ስራ ማቆምን ለመታደግ ከሚሰጥ ህክምና ውጭ የሚደረግ የዲያሊሲስ ህክምናዎችም በአገልግሎቱ አይካተቱም፡፡
የአይን መነጽርና ኮንታክት ሌንስ፣ በሰው ሰራሽ ዘዴ ከአካል ውጭ ለማስጸነስ የሚደረግ ህክምና፣ ሰውሰራሽ አካል መተካት፣ ሰውሰራሽ ጥርስ ማስተካከልና በኢንፌክሽን ምክነያት የሚደረግ የሩት ካናል ህክምናን ሳይጨምር ሌላ ማናቸውም የሩት ካናል ህክምና፣ የመስማት ሃይልን የሚያግዙ መሳሪያዎች ወዘተ… የመድህን አባሉ የማያገኛቸው አገልግሎቶች ናቸው። በሌሎች ህጎች የተሸፈኑ እንዲሁም ያለክፍያ ለሁሉም ዜጎች እኩል የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶችም በማዕቀፉ አይካተቱም፡፡
የኢትዮጵያ የጤና መድህን ኤጀንሲ በመጪው ጥር ወር የማህበራዊ ጤና መድህንና የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግና፣ አባላቱ በመላ በአገሪቱ በሚገኙ 123 የመንግስት ሆስፒታሎች አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ዕቅድ ይዞ ሲሰራ ቢቆይም፣ ሁሉም ክልሎች እኩል ወደስራ መግባት ባለመቻላቸው፣  ለተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል፡፡  
እርግጥም ይሄን አገራዊ ተልዕኮ ማስጀመር ቅንጅትን የሚሻ ትልቅ የቤትስራ ነውና፣ ተጨማሪ ጊዜ ወስዶ በወጉ ለመዘጋጀትና ወደ ስራ ለመግባት ትኩረት መሰጠቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

Read 6236 times