Saturday, 11 January 2014 11:02

ወንዝ ለወንዝ መማማል…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(7 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንኳን ለመውሊድ በዓል በሠላም አደረሳችሁ፡፡ በዛ ሰሞን አንድ ወዳጃችን አንድ ዝግጅት ላይ የሆነች ሴት ትጠራዋለች፡፡ ሴትዮ ስላላወቃት ለጊዜው ግራ ይገባዋል፡፡ ከዛ ትዝ ሲለው በደንብ የሚያውቃት ሴት ነች፡፡ አራት አምስት ዓመታት ገደማ አይቷት አያውቅም። “ወደ ፎርቲው እየተንደረደረች ነበር፡፡ አሁን ግን ሃያ መጀመሪያ ሆናለች!” ወዳጃችን ግራ የገባው ወጣት መሆኗ ሳይሆን ገጽታዋ ላይ ያየባት ለውጥ ነው፡፡ “አፍንጫዋና ጡቶቿ የእሷ እንዳልሆኑ እወራረዳለሁ!” ነው ያለው፡፡ ስሙኝማ…መቼም ከፈረደባቸው ‘ፈረንጆች የማንኮርጀው’ ነገር የለም አይደል…የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና እየተለመደ ነው ይባላል፡፡ (የኩረጃ ነገር ከተነሳ ‘ታንክስ ጊቪንግ’ እንኳን ሲኮረጅ!) እናላችሁ…ሰዎች ራሳቸውን ለመለወጥ መከራቸውን እያዩ ነው፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…የ54 ዓመቷ ሴት የልብ ድካም ይገጥማትና ሆስፒታል ትገባላችኋለች፡፡ እናላችሁ… ገና በቀዶ ጥገናው ጠረዼዛ ላይ እያለች እግዚአብሔር ያናገራት ይመስላታል፡፡

እሷም… “እግዚአብሔርዬ፣ አበቃልኝ ማለት ነው?” ስትል ትጠይቃለች፡፡ እግዚአብሔርም… “አይዞሽ፣ አላበቃም፣” ይላታል። “ገና ሌላ 43 ዓመት ከሁለት ወር ከስምንት ቀን ትኖሪያለሽ፡፡” ሴትየዋም ደስ ይላትና ተሽሏት ስትወጣላችሁ… “ይሄ ሁሉ ዓመት ከቀረኝማ…” ትልና ራሷን ወጣት ለማድረግ ትወስናለች፡፡ ፊቷ በቀዶ ጥገና ተለወጠ፣ አፍንጫዋ ሰልካካ ሆነ፣ ጡቶቿ ከጉች፣ ጉችነትም አልፈው ለመወንጨፍ የተዘጋጁ የአሜሪካ ‘ፓትሪዮት’ ሚሳይሎችን መሰሉ። “ዋ! አንድ ነገር ካላደረግሽ ተወርውሬ መሬቱ ላይ ለሽ ልል ነው!” የሚል ይመስል የነበረው ቦርጯ ድራሹ ጠፋ። የጸጉሯ ቀለምና ዞማነት ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ተለወጠና እነኚህ የሻምፑ ማስታወቂያዎች ላይ የምናያቸውን ሴቶች ‘ጸጉር’ መሰለ፡፡ ብቻ…ምን አለፋችሁ “ፏ!” አለችላችሁ፡፡ ታዲያችሁ…አንድ ቀን የመጨረሻውን የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና አካሂዳ ከሆስፒታል እየወጣች ነበር፡፡ እናማ… ከየት መጣ የማይባል አምቡላንስ መኪና ይገጫትና በዛው ይቺን ዓለም ትሰናበታለች፡፡

እግዚአብሔር ፊትም ስትደርስ እየተንዘፈዘፈች… “ገና 43 ዓመት አለሽ ብለኸኝ አልነበረም እንዴ! ታዲያ መኪና ሲገጨኝ ለምንድነው ያላዳንከኝ!” ትላለች፡፡ እግዚአብሔርም ትኩር ብሎ ካያት በኋላ ምን አላት መሰላችሁ… “ጉድ! ጉድ! አንቺው ነሽ እንዴ! እኔ ታዲያ ምን ላድርግ፣ ሌላ ሰው መሰልሽኛ!” ዘንድሮ እኛ ዘንድ መልክን መለወጥ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር ሌላ ሰው የመምሰል ፉክክር ‘ብሔራዊ ስፖርት’ ነገር ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ እና የብዙዎቻችንን እውነተኛ ባህሪይ ለማወቅ ‘መፋቅ’ አማራጭ ሳይሆን ግዴታ ሆኗል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ብዙ ቃለ መጠይቆችን ነገሬ ብላችሁልኛል…ተጠያቂዎቹ ሌላ ሰው ለመምስል የሚያደርጉት ሙከራ…ምን አለፋችሁ…“ሰዉ ሁሉ ምን ነካው!” ያሰኛል፡፡ ከየሁለትና ከየሦስት ቃሉ በኋላ “እ…” እያሉ መጎተት የአዋቂነት ‘ግሪን ካርድ’ የሚመስለን መአት ነን፡፡ በነገራችን ላይ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… “እ…” እየረዘመችና እየበዛች በሄደች ቁጥር ችግሩ የሽለላ ሳይሆን የሆድ ቁርጠት ሊሆን ይችላል! ቂ…ቂ…ቂ…. ልክ ነዋ! ስንት መሸለያ መንገድ እያለ፣ እዚቹ ከተማችን ውስጥ ስንት ‘ፈልሰው የመጡ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ስንት የሽለላ አይነቶች እያሉ አታሳቁና! እናማ…“እ…” ማለት የምታበዙ ሰዎች… አለ አይደል… “አድናቂው ነኝ!” ከማለት ይልቅ… “ሰውየው ምን ያምጥብናል! መጸዳጃ ቤት እንኳን ቢያጣ የሆነ ሰንሰል ምናምን ጀርባ አይሄድም እንዴ!” እንደምንል ይጻፍልን፡፡ እናማ…በምኑም በምናምኑም ሌላ ሰው ለመሆን የምንሞክር…አለ አይደል… በኋላ “እኔ ምን ላድርግ፣ ሌላ ሰው መሰልሽ/ከኛ!” ነገር እንዳይመጣብንማ! ችግሩ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ሰዉ ሁሉ አትኩሮቱ እኛ ላይ ያለ ይመስለናል፡፡ በመንገድ ስንሄድ፣ በሬስቱራንት ስንመገብ፣ ‘በግሮሰሪ’ ስንጨልጥ፣ ሲኒማ ቤት ስንገባ፣ ሚኒባስ ስንሳፈር…ምን አለፋችሁ… ሰዉ ሀያ አራት ሰዓት ሙሉ ስለእኛ የሚያስብ ይመስለናል፡፡ አንዱ ያለውን ስሙኝማ… “በሀያዎቹ ዕድሜያችን ዓለም ስለእኛ ምንም ያስብ ምን ጉዳያችን አይደለም፡፡ በሠላሳዎቹ ዕድሜያችን “ሰዎች ምን ይሉን ይሆን!”” ብለን መከራ እንበላለን፡፡ በአርባዎቹ ዕድሜያችን ግን ማንም ሰው ስለእኛ ይቺን ታክል ጉዳዩ እንዳይደለ ይገባናል፡፡

እናላችሁ…ብዙዎቻችን ሰዉ ስለ እኛ ብቻ የሚጨነቅ እየመሰለን የሆነ ዓለም ፈጥረናል፡፡ በእርግጥ መፋጠጥ በጣም በዝቷል፡፡ በየቦታው ዓይኑን ተክሎ ሰው ላይ የሚያፈጥ መአት ነው፡፡ ግን ምን መሰላችሁ… እንደዛ አይነት ሰዎች የሚያፈጡት ሁሉም ‘ጸጉረ’ ልውጥ ላይ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… አሀ፣ እሱ የማያውቀው ሰው ሁሉ ለእሱ ‘ጸጉረ ልውጥ’ ነዋ! እናላችሁ…በሚዲያ ቀርቦ ልክ የዓለም የገንዘብ ድርጅት እየተጣሉበት ያለ የምጣኔ ሀብት ጠቢብ ይመስል…ቦሶቻችንን መስሎ “የህዝቡ ኑሮ በጣም ተሻሽሏል…” ምናምን ነገር ሲል… የለየለት ቅሽምና ነው። ልከ ነዋ… “እንዴት ነው የሰዉ ኑሮ የተሻሸለው?” ብትሉት… አለ አይደል… ምን የሚል መሰላችሁ… “የቦሌን መንገድ እንዴት እንደሚያምር አላየኸውም!” ይላችኋል፡፡ የምር ግን…ቆዳችንን ገፈን የ‘ቦሶቻችንን ቆዳ’ ካላጠለቅን የሚሉ፣ በእከሌ ፓርቲ ጠበል ለመጠቀም ‘ሰልፍ የሚይዙ’…ምን አለፋችሁ፣ የባህሪይ ‘ፕላስቲክ ሰርጀሪ’ ራሳችን ላይ የምናካሂድ ሰዎች በዝተናል፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… የሂሳብ ሊቅ፣ አካውንታንትና ኤኮኖሚስት ለአንድ ክፍት የሥራ ቦታ ይወዳደራሉ፡፡

ቃለ መጠይቅ አድራጊው የሂሳብ ሊቁን ይጠራውና እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡፡ “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” “አራት፣” ይላል የሂሳብ ሊቁ፡፡ ጠያቂውም ““በትክክል አራት!” ሲል ደግሞ ይጠይቀዋል፡፡ “አዎን፣ በትክክል አራት፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ጠያቂው አካውንታንቱን ይጠራና ያንኑ ጥያቄ ይጠይቀዋል፡፡ “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” “በጥቅሉ አራት ነው፡፡ አሥር ከመቶ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል፡፡ ግን በጥቅሉ አራት ነው፡፡” ጠያቂው ኤኮኖሚስቱን ያስገባና “ሁለትና ሁለት ስንት ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ኤኮኖሚስቱ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ?” እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኛ ዘንድ የቁጥርና የመቶኛ መአት እየተደረደ…አለ አይደል… “አላወቃችሁ ሆናችሁ ነው እንጂ፣ ዲታ ሆናችኋል…” አይነት ነገር የምንባለው “ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ?” በሚለው ስሌት ነው እንዴ! ስሙኝማ…ልክ እኮ ጓደኛ “ስንት ልስጥህ?” እንደሚለው ቁጥርን “ስንት እንዲሆንልህ ትፈልጋለህ?” አይነት ኮሚክ ነገር ነው፡፡ መቼም ቁጥሮች እንዲሀ አገር መከራቸውን ያዩበት ቦታ ያለ አይመስለኝም— “ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ…” ከሚለው ጀምሮ፡፡ እና…በተለይ ተቋሟት ሁሉ ነገራቸው የቁጥር ጨዋታ ሆኗል፡፡ ችግሩ… “ስንት እንዲሆንላችሁ ትፈልጋላችሁ?” የሚለን መጥፋቱ ነው፡ ያኔ እቅጯን እንልና…ምን አለፋችሁ የየድርጅቱ የፋይናንስ መምሪያዎች ያሉ ሁሉ ‘ላይ ቤታቸው’ ያለ ቡሎን ሁሉ አንድ በአንድ ወልቆ ያልቅ ነበር! ይቺን ስሙኝማ…የአእምሮ በሽተኞች ሆስፒታል ነው፡፡

አንድ ቀን…አንዱ በሽተኛ “እኔ ናፖሊኦን ነኝ! እኔ ናፖሊኦን ነኝ!” እያለ ይጮሀል፡፡ ሌላኛው በሽተኛም… “ናፖሊኦን መሆንህን በምን አወቅህ?” ይለዋል፡፡ ያኛውም “እግዚአብሔር ነግሮኝ ነው፣” ሲል ይመልሳል፡፡ ይሄኔ ጎን ካለው ክፍል ምን የሚል ድምጽ ተሰማ መሰላችሁ… “ውሸቱን ነው፣ እኔ አልነገርኩትም!” እናላችሁ…መልክን በመለወጥም ሆነ፣ እውነተኛ መረጃዎችን በመለወጥ ነገሮችን…ሌላ ለማስመሰል መሞከር ቀሺም ነው፡፡ ‘መፋቅ’ የማያስፈልገው እውነተኛ ባህሪይ፣ ለማረጋገጥ እንደ ዘይት ጉድጓድ ጥልቅ ቁፋሮ የማያስፈልገው እውነተኛ መረጃ…እየናፈቁን ነው። መፋፋቅ ሲበዛ ያለመተማመን በዛ ማለት ነው፡፡ ያለመተማመን ደግሞ ወንዝ ለወንዝ መማማል ይሆናል፡፡ ወንዝ ለወንዝ ከማማል ይሰውረንማ! ድፍን አገር ‘ወንዝ ለወንዝ መማማል’ ደረጃ ሲደርስ አሪፍ አይደለም፡፡ ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2987 times