Saturday, 18 January 2014 11:44

የሦስት ፎቅ ሰማይ

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(7 votes)

           “ሳምሶን ወደ ጥንቅሹ እንዴት ተቀየረ?” ሳምሶንን ድሮ ለሚያውቁት ሁሉ አስገራሚ ጥያቄ ነው፡፡ እንደ ሳምሶን አይነት ከይሲ …. ቂጡን በእግሩ የጠረገ ዱርዬ …. አንገቱን የሰበረውን፣ ሰው ቀና ብሎ የማያየውን … ከቤቱ የማይወጣውን ጥንቅሹን እንዴት በቅጽበት ሆነ? መልሱ ሳይሆን ጥያቄው ነው አስገራሚ፡፡ መልሱማ፤ ግልጽ ነው፡፡ ጌታን አገኘ ወይንም ጌታ አገኘው፡፡ ፀጉሩን ላጭቶ እማኝ አደረገው፡፡ ልቡን እና ትዕቢቱን ሰበረለት፡፡ ጌታ ጥንቅሹን፣ፍልስጤማዊያኑ ሳምሶንን በእጃቸው ያስገቡበት መንገድ አንድ ነው፡፡ መንገዱ ሴት ናት፡፡ ደሊላ፡፡

ጥንቅሹን ግን ለጌታ አሳልፋ የሰጠችው የኤሮናዛ ፋርማሲ ባለቤት ናት፡፡ ወደ ፋርማሲው የሄደው ኮንዶም ለመግዛት ነበር፡፡ ፋርማሲስቷን ሲያይ ሌላ በሽታ ያዘው፡፡ መድሐኒት ሻጯን እንደ መድሐኒት መዋጥ ፈለገ፡፡ ከእነ ሁሉ ነገሯ፤ ከእነ ወጣትነቷ፣ ከእነ መድሐኒት መደብሯ፣ መድሐኒት መደብሩ ደጃፍ ከነአቆመችው መኪና…እሷን ከነሁሉ ነገሯ ቢውጥ ህይወቱን የመታው የእጦት ደዌ እንደሚፈወስ አመነ፡፡ እሷን ለመዋጥ ግን መጀመሪያ በእሷ መዋጥ እንዳለበት አውቋል። ግን የሚዋጥ ነገር የለውም፡፡ ከይሲ ነው፣ ቂጡን በእግሩ የጠረገ ዱርዬ፡፡

ኮንዶም መግዛቱን ትቶ የባጥ የቆጡን አወራላት፡፡ መጥበሱ ነው በሱ ቤት፡፡ ያወራላት ነገር ለእሥረኛ የሚበቃ በመሆኑ መረቧን ጣለችበት፡፡ ወደ ቤተክርስቲያኗ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰማ ጋበዘችው፡፡ ግብዣዋን ተቀብሎ ሊወጣ ሲል በህክምና ሳሙና በታጠበ እጇ ጨበጠችው፡፡ ወደ ተጋበዘበት ጉባኤው ሲገባ ጀምሮ ሳምሶንነቱ አጠረው፡፡ እውነተኛ ስሙን ለመናገር አፈረ፡፡ ስሙን ስትጠይቀው “ጥንቅሹ” አላት። እውነተኛ ስሙን በደንብ ከተግባቡ በኋላ ሲገልጽላትም መጀመሪያ የተነገራትን ይዛ ቀረች፡፡ ጥሪዋን አልለውጥ አለች፡፡ የዋጠችው በፍጥነት ነው፡፡ ከተዋወቁበት እለት ወደ ቤተክርስቲያኗ እስክትጋብዘው በመሃል ተለያይተው ከቆዩበት ጥቂት ቀናት በስተቀር ግንኙነታችሁ በየእለቱ እንዲሆን አደረገች፡፡ ወደ ሳምሶንነት የሚመለስባቸውን መንገዶች ነፈገችው፡፡ በሦስተኛው ወር አጋማሽ ላይ ከአባቷ ጋር አስተዋወቀችው፡፡ ወደ ወላጆቹዋ ቤት ወስዳ ከአባትና ከእናቷ ፊት ፈትታ ለቀቀችው፡፡ አባት እና እናትየው በዛ እለት የተዋወቁት ጥንቅሹን ብቻ ሳይሆን የታናሽዋይቱን ልጃቸውንም እጮኛ (እስረኛ) ነው፡፡ ታላቂቱ ጥንቅሹን፣ ታናሽቱ ለምቦጫሙን አጥምደው ወላጆቻቸው ፊት ፈትተው ለቀቁዋቸው፡፡ አባትየው ተይዘው የመጡትን ሁለት ወንድ በጐች ወገባቸውን ጨበጥ ጨበጥ እንደማድረግ በተለያዩ የአይን እና የንግግር መመዘኛዎች ለኳቸው፡፡ ጥርስ መሽረፍ እና አለመሽረፋቸውን አረጋገጡ፡፡ እኛም ወደናል ይሁን አሉ፡፡

የጥንቅሹ እጮኛ ወላጆች የሚኖሩት ፎቅ ቤት ሰርተው ነው፡፡ የቤቱ ሶስተኛው ፎቅ ላይ አባትና እናት፣ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ኤልሻዳይ/የጥንቅሹ እጮኛ/፣ አንደኛው ፎቅ ላይ ህይወት (የመጨረሻ ልጃቸው) ይኖራሉ፡፡ ከትውውቁ በኋላ ጥንቅሹ ሁለተኛው ፎቅ ላይ ከኤልሻዳይ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ በዘመቻ ፍጥነት ህይወትም ለምቦጫሙን አስገብታ መኖር ጀምራለች፡፡ ለምቦጫሙ የክርስቲያን ግንባር ነው ያለው፡፡ ስሙ ግንባሩን አይመስልም፡፡ “አቡ” ብለው የእጮኛው ወላጆች ጠሩት። የሴቶቹ ወላጆች ወንዶቹን የሚጠሩት በመጥሪያ ነው፡፡ ሶስተኛ ፎቅ ሞቅ ካለው ሳሎን ቤት ውስጥ ያለውን የመጥሪያ ደወል ለአንደኛው ወይም ሁለተኛ ፎቅ አነጣጥረው ይደውላሉ፡፡ በተነጣጠረው ደወል የተመታ ምላሽ ለመስጠት ወደ ሶስተኛ ፎቅ ይሮጣል፡፡ የፎቁ ምድር ቤት ለአገልግሎት ሰጪ ሠራተኞች የተዘጋጀ ነው፡፡ ሦስተኛ ፎቅ ሁለተኛ እና አንደኛ ፎቅን ያዝዛል፡፡ ሁለት እና አንድ ደግሞ ምድር ቤትን ያዛሉ፡፡ ምድር ቤቱ ውስጥ ብዙ አይነት አገልግሎት ሰጪዎች አንድ አንድ ክፍል ተሰጥቷቸው ይኖራሉ፡፡ ምግብ የሚቀቅሉ፣ የሚያፀዱ፣ ጥበቃ የሚሰሩ፣ አትክልት የሚቆፍሩ …ወዘተ፡፡

የሰራተኞቹ ብዛት እንደሁኔታው በአምስት እና አሥር መሃል ከፍ ዝቅ ይላል፡፡ የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ የታቀደው በወላጆቹ ነው። ከሦስተኛ ፎቅ እቅዱ ወደ ተግባር የተቀየረው በሁለቱ ሴት ልጆች፡፡ ሴቶቹ ልጆች ለራሳቸው ሰርግ ሚዜ ነበሩ፡፡ ወንዶቹ፤ ጥንቅሹ እና አቡበከር ለኩ የተባሉትን ሱፍ መለካት…ቁሙ በተባሉበት ቦታ መቆም ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡ አድርጉ የተባሉትን እስካደረጉ ድረስ፣ የሚስቶቻቸው ወላጆች በእነሱ ደስተኛ ይሆናሉ፡፡ ወላጆች ህግ አውጪ ናቸው፣ ሚስቶች ህግ አስፈጻሚ ናቸው …ባሎች ህግ ተወጪ፡፡ ጥንቅሹ ለሰርጉ ዕለት የሚጠራቸውን ዘመዶቹን በጥንቃቄ በማጥናት የይለፍ ካርድ የሰጡት አባትየው ናቸው፡፡ ከሶስተኛ ፎቅ ሆነው በየዕለቱ ማታ ማታ፤ ልጆች የወላጆችን እግር የማጠብ ሥነ ሥርዓት ያከናውናሉ፡፡ ክርስቶስ የደቀ መዛሙርቱን እግር ያጠበበትን ሥነ ሥርዓት ለማስታወስ፡፡ ወንዶቹ ልጆች የሴቶቹን ወላጆች እግር ያጥባሉ፡፡ አንዱ የአባትን፣ ሌላው የእናትን፡፡ ጥንቅሹ የአባትን እግር የማጠብ ተራ ሲደርሰው ደረቱን የሚያፍን ስሜት ይሰማዋል፡፡ አስም ስለጀመረው መድሐኒት እንድትፈልግለት ለሚስቱ ኤልሻዳይ ነግሮአት ነበር፡፡ አፈናው በመድሃኒት እንደማይቆም ግን ቀልቡ ነግሮታል፡፡ ሴቶቹ ልጆች ደግሞ በተዋረድ የባሎቻቸውን እግር በወላጆቻቸው ፊት ያጥባሉ፡፡

በየምሽቱ ተሰናብተው ወደ ራሳቸው መኖሪያ እንደ ደረጃቸው ሲወርዱ እና በፎቅ ፎቃቸው ሲከተቱ፣ ባሎች የሚስቶቻቸውን ጀርባ ያሻሉ፡፡ የሰርጉ እለት ጥንቅሹ ቀኑን ሙሉ ፈዞ ከዋለበት ድንገት ነቅቶ መለፍለፍ ማብዛቱ፣ በእስክስታ በጉባኤ መሃል የመግባቱ ሚስጥር የታወቀው ምንጣፉ ላይ ከማስመለሱ ጥቂት ቀደም ብሎ ነበር፡፡ መጠጥ ከየት እንዳገኘ ማንም ማስረዳት አልቻለም፡፡ ኤልሻዳይ የክርስቶስን ስም እየጠራች ስጋ ለባሽ ስድቦች ስትሰድበው ማንም አፏን ለማስጣል አልሞከረም፡፡ የሰርጉ ቀን አለፈ፡፡ ጥንቅሹም ተኝቶ ስካሩን አሳለፈ። ሲሰክር ሳምሶምነት ይጠናወተዋል፡፡ በሰርጉ እለት አባትየው ለሙሽሮች ለማበርከት ያቀዱትን ስጦታ ለጥንቅሹ እና ለ “አቡ” የሰጠዋቸው ቆየት ብለው ነው፡፡ ግምገማ እና ተግሳፅ መቅደም ስለበረበት፡፡ የሰርጉ ቀን ካለፈ ሁለት ሳምንት በኋላ የእግር ማጠብ ሥነ ሥርዓቱም በአዲስ መልክ ተጀመረ፡፡ ወላጆች ለሁለት ሳምንት ልጆቻቸውን እና ባሎቻቸውን አጣምረው አኮረፉ፡፡ ከሶስተኛ ፎቅ ላይ ሆነው፡፡ ስጦታው ለሙሽሮች በሚበረከትበት ቀን፤ ከማለዳ እስከ ቀትር የምክር እና የፀሎት ፕሮግራም በቅድሚያ ተካሂዷል፡፡ እጅ በጥንቅሹ ላይ ተጭኖ ተፀለየለት፡፡

ሳምሶም በኢየሱስ ስም እንዲባረር ሆነ፡፡ የአባትየውን እግር ሲያጥብ ብቻ ሳይሆን የአባትየው እጅ ሲጫንበትም ጥንቅሹን ያፍነዋል፡፡ የአባትየው ትንፋሽ ያለበት ቦታ የአስሙ ምክንያት እንደሆነ መቀበል ግን አልደፈረም፡፡ አስሙ ለቀቅ እያደረገው የመጣው ስጦታው ይፋ ሲሆን ነው፡፡ የጠበቀው ስጦታ ቤት ቢሆንም መኪናም ግን የሚያስከፋ አይደለም፡፡ ቢያንስ አስሙ ሲነሳበት ሞተር አስነስቶ ወደ ሶደሬ፣ ላንጋኖ ሊሄድ ይችላል፡፡ ከኤልሻዳይ ጠባብ ሱሪ እያፈነገጠ እንደ ጡት ብቅ የሚለው መቀመጫዋ ሲያቅለሸልሸው… የተስተካከለ የሰውነት ገበያ ወዳለባቸው ክለቦች በመኪና ሊደርስ ይችላል፡፡ መኪና ራሱ የሚንቀሳቀስ ቤት ነው፡፡ ወጣት ልጃገረዶች ሊፍት ሰጥቶ ዛፍ ጥላ ስር ሆኖ መጨዋወት አያቅተውም፡፡ ስጦታውን ሲያይ ያፈነው አስም ከደረቱ ወጥቶ እንደ ጉም በነነ፣ ንጹህ ትንፋሽ ሳንባው ያገኝ ጀመረ፡፡ ጥሩ ትንፋሽ ሳንባ ሲያገኝ፣ ጥሩ ደም ልቡን ነዘረው…. እንደ ጥንቱ ጥሩ ጥሩ ሃሣብ አእምሮው ውስጥ ተፍታታ፡፡ ሶምሶንነቱ ከተላጨው ጸጉር ውስጥ እንደ አዲስ ሽፍ ብሎ ሲበቅል ተሰማው፡፡ የሰርጉን ስጦታ ለማየት ባይችልም ዘመናዊ እና አዲስ መኪና መሆኑን አምኖ፣ በልበ ሙሉነት ወደ አልጋው ሄደ፡፡ የሚስቱን ኤልሻዳይን ጀርባ ሲያሽ… እንደ ቀድሞው በትህትና አልነበረም፡፡

በአፉ ጥንቅሹን ሆኖ ቢያወራም… በአስተሳሰቡ እና አኳኋኑ ግን ሳምሶምን ሆኗል፡፡ ኤልሻዳይ እየሰባበረ ከሚያሻት የባሏ መዳፍ ጋር ድምጿ እየተሰባበረ፣ የተገዛለት መኪና ምን አይነት እንደሆነች ነገረችው። ቀለሟንም በአፉዋ ቢጫ አድርጋ ቀባቻት፡፡ ማፈኑ እንዳይጀምረው ቢፈራም ለአስም እጁን አልሰጠም። አቶዝ የሴት መኪና ብትመስልም መኪና ናት፣ ቤንዚን መስጫውን እንደ ወንድ አድርጐ ከረገጠው ልታርቀው ትችላለች፡፡ ቀለሟ ቢጫ ቢሆንም እሱ ከውስጡ ሆኖ እስከ ነዳት ድረስ ውጪው አይታየውም፡፡ ከውጭ ሆነው የሚያዩዋት ሴቶች ስለሆኑ እንዲያውም ትስባቸዋለች፣ ብሎ ተጽናና፡፡ የሳምሶን ጸጉር በውስጡ አያደገ ሲመጣ ተሰማው፤ መጠጥ አማረው፡፡ ግን መኪናው እጁ እስክትገባ መታገስ አለበት፡፡ አቡ የተሰጠው መኪናም ከእሱ ጋር ተመሳሳይ አንደሆነ ኤልሻዳይ ታሽታ ከመጨረሷ በፊት ለባሏ አጫወተችው፡፡ በቀለምም ሆነ በብራንድ የእሱ እና የሚስቱ እህት ባል መኪኖች አንድ ናቸው፡፡ የታርጋ ቁጥር ነው የሚለያቸው፡፡ ከስም ታርጋ ልዩነት በስተቀር ተመሳሳይ እህቶች… አንዳገቡት፡፡ ተመሳሳይ መኪና ለባሎቻቸውም አባትየው ገዝተውላቸዋል፡፡

አባትየው ወንዶቹን ባሎች ከሴት ልጆቻቸው ሚስትነት አስበልጠውም ሆነ ለይተው ማየት አይፈልጉም፡፡ በእግዜር ፊት ሁሉም እኩል እንደሆነ፣ አባትየው ፊትም ልጆቻቸው እና ባሎቻቸው እኩል ናቸው፡፡ አባትየው ራሳቸውን የባለ ሦስት ፎቅ እግዜር አድርገው መቁጠራቸው ተገልጾላቸው የሚያውቅ አይመስልም፡፡ ጥንቅሹ በጠዋት ተነስቶ የመኪናውን ቁልፍ ሲፈልግ ኤልሻዳይ ወደ ፋርማሲዋ ለመሄድ እየተሰናዳች ነበር፡፡ ቁልፉ በአባቷ እጅ እንዳለ ነግራው ወጣች፡፡ በደወል ሳይጠራ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሶስተኛ ፎቅ ሮጠ፡፡ የእየሱስን ስም በእየ አረፍተ ነገሩ መሀል እየቀቡ ዳቦአቸውን በማርማላት ሲነክሩ ደረሰባቸው፡፡ አባትየው የበኩር ልጃቸውን ባል ግንባሩን ከሳሙት በኋላ፣ አብሮአቸው ቁርስ ለማድረግ ተቀመጠ፡፡ በብዙ ማባበል ቁልፉን እና መኪናዋ የት እንደሚገኙ ጠየቃቸው፡፡ መኪናዋ ግቢ ውስጥ መሆንዋን፤ ቁልፉ ግን የሚሰጠው ለምን ጉዳይ እንደሚሄድ፣ ምን ያህል ርቀት እንደሚሄድ እና መቼ እንደሚመለስ አስመዝግቦ መሆኑን አንደተራ ነገር ገለፁለት፡፡ ለዚሁ አገልግሎት ያዘጋጁትን ዶሴ መሰል ነገር አወጡ፡፡ በተዘረዘረው ተራ ቁጥር መሰረት መሄድ የፈለገበትን እንዲሞላ ጠየቁት፡፡ የተጠየቀውን ሞላ፡፡ አንድ አልባሌ ቦታ፡፡ ከእሱ ፍላጐት በጣመ የራቀ፣ ወደ አባትየው ፍላጐት በጣም የቀረበ ቦታ፡፡ ሱፐር ማርኬት፡፡ የሱፐር ማርኬቱን ስም ጠይቀው አሁንም አስሞሉት። ከባለሶስቱ ፎቅ እስከ ሱፐር ማርኬቱ ያለውን የደርሶ መልስ ርቀት አስልተው የቤንዚን ብር ወደሱ ዘረጉ። እያስጨበጡት አንድ ተጨማሪ ህግ ነገሩት፡፡

ከእንግዲህ የወላጅነት ድርሻን መወጣት ላይ ስለሆነክ የገንዘብ አወጣጥህ ላይ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤ ስለዚህ ኤልሻዳይ ፋርማሲ ሸጣ ከምታመጣው ትርፍ የምትሰጥህን ገንዘብ እኔ እየተቀበልኩ ልቆጥብልህ ወስኛለሁ፡፡ ገንዘብ ስትፈልግ እኔን ትጠይቀኛለህ፣ እኔም ጥያቄህን መርምሬ፣ ተገቢ ሆኖ ካገኘሁት፤ የጠየቅኸኝን አሟላለሁ፤ ህይወት በኘሮግራም መመራት አለበት፤ ትላንት ሳልሰጥህ የረሳሁት ነገር አለ፤ ብለው፤ ከጠረዼዛው ላይ ትራስ የሚያህል በላስቲክ የተቋጠረ ነገር አንስተው አቀበሉት፡፡ ለክተህ አሳየኝ አሉት፡፡ ደረጃውን እየወረደ ፌስታሉን ፈትቶ ተመለከተው፡፡ ብርቱካን አይነት ቲሸርት አና አረንጓዴ ቦላሌ የመሰለ ቁምጣ ከፌስታሉ ውስጥ ተከታትለው ተመዘዙ፡፡ ከቲሸርቱ እና ቁምጣው ስር ቢጫ የኤርጌንዶ ነጠላ ጫማ አለ፡፡ እንደ አዲስ ጐማ ይከረክራል፡፡ ወደ ሁለተኛ ፎቁ ገብቶ ልብሱን አውልቆ፣ ከአባትየው የተሰጠውን አጠለቀው፡፡ አያጐጠጐጠ ያለ ሳምሶምነቱ በቅጽበት ከለበሰው ቲሸርት፣ ቦላሌ እና ኤርገንዶ ጋር ረገፈ፡፡ ሲረግፍ ሁለተኛ እንደማይበቅል ሆኖ ነው፡፡ ከልብሱ ጋር የማይወልቅ ማንነቱ ጥንቅሽነቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አረጋገጠና ጸና፡፡ ከዚህ ቀደም የሚስቱን እህት ህይወትን እና ባሏን በልቡ ይጠላቸው ነበር፡፡ ኤርገንዶውን ሲጫማ ድንገት ወደዳቸው፡፡ የሚስቱን ባል “አቡ”ን በአዲስ መልክ ለመተዋወቅ፣ ሰላም ለማለት ወደ አንደኛ ፎቅ ቁልቁል ተንደረደረ፡፡ አቡም፤ ወደ ላይ ወደ አባትየው እየተንደረደረ መሀል መንገድ ተገናኙ፡፡ በግጭቱ ውስጥ ተቃቀፉ፡፡ አቡም ብርቱካን አይነት ቲሸርት በአረንጓዴ ቦላሌ አጥልቋል፡፡ ቢጫ ኤርገንዶውን ገርግዷል፡፡ ጫማው ትንሽ ሰፍቶታል፡፡ የአባትየውን ፈቃድ መሙላት ስላለበት ግን ቢሰፋውም ራሱን አሳድጐ የሰፋውን ጫማ ይሞላል፡፡ አቡ አመጹን ካስወገደ ቆይቷል፡፡ ወደ ሶስተኛው ፎቅ አብረው ከጥንቅሹ ጋር ተንደረደሩ፡፡

አባትየው የገዙላቸውን ልብስ ለማስመረቅ፡፡ እደጉ ለመባል፡፡ ጥንቅሹ እና አቡ በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከተመሳሳይ ሚስቶቻቸው ተመሳሳይ ሴት ልጆች ወለዱ፡፡ በተመሳሳይ ቀን፣ከሦስተኛው ፎቅ በተሰጣቸው ትዕዛዝ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ክርስትና አስነሱ፡፡ ሴት ልጆቻቸው ሲያድጉ፣ አባትየው በፎቅ ቤቱ ላይ ሁለት ደረጃ ለመጨመር ይገደዳሉ፡፡ የልጅ ልጆቻቸው ባል ይዘው ለመምጣት ሲደርሱ የሚገቡበትን ስፍራ ለማመቻቸት፣ እሳቸው ወደ አምስተኛ ደረጃ ወጥተው አራቱን ከላይ ሆነው ያስተዳድራሉ፡፡ የፎቅ ቤቱን ደረጃ ከፍ ከማድረግ በተረፈ ሁለት ተጨማሪ ፋርማሲዎች ይከፍታሉ፡፡ ለሴቶቹ ልጅ ልጆቻቸው፡፡ ፋርማሲ ውስጥ እንደ ሸረሪት ድር ሰርተው የታመሙ ሰዎችን ያክማሉ… ከታመሙት መሀል አንድ አጥምደው ወደ አያቶቻቸው ዘንድ ወስደው ያስተዋውቃሉ፡፡ ፈቃድ ሲያገኙ ያገባሉ። የልጅ ልጆቻቸውን ህይወትም ለማስተዳደር የሚበቃ እድሜ አና አቅም በውስጣቸው አንዳለ ሰውየው እርግጠኛ ናቸው፡፡ በፊት ባል የነበሩት፣ በኋላ አባት፣ ቀጥለው አያት የሆኑት የሶስተኛ ፎቁ አምላክ፣ እርግጠኛ ናቸው፡፡ በአያትየው አይን ሁሉም የቤተሰቡ አባል እኩል ነው፡፡ ሁሉም ሴት ልጆቻቸው ናቸው፡፡

Read 3720 times