Sunday, 19 January 2014 00:00

የአውራምባ የጉዞ ማስታወሻ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ዙምራ እና እኔ (የመጨረሻው ክፍል)

ከትንሿ የኤግዚቢሽን አዳራሽ ተቀምጨ ዙምራን ስጠብቅ ብዙ ጥያቄዎች በህሊናዬ ተመላልሰዋል፡፡ ዕውን በህጻንነቴ የአዋቂ አብራሄ - ህሊና /Enlightenment/ ነበረኝ ያለው ልጅ ከወሎ ጐጃም ጐንደር ሄዶ ማስተማር የፈለገው? ፈጣሪ አስመልክቶት ነውን ወይስ የአእምሮው ፍጥረት ነው አስተሳሰቡን የሰረፀበት? የሚለው ጥያቄ በአዕምሮዬ ግዘፍ - ነስቷል፡፡ ከአምስት አስተሳሰቦች /አስተምሮት/ በላይ እንዲሰፋ ይፈልጋል ወይስ አይፈልግም? መማር ለምን አልፈለገም? 6 ሚስቶች መፍታት ለምን አስፈለገው? የአካባቢው ህዝብ በጥላቻ ዓይን እንደሚያያቸው ካወቁ ለምን ግንኙነታቸውን ለማሻሻል አልፈለጉም? ከ8 በላይ ኮምፒዩተሮች አንድ ኤን ጂ ኦ የተሰጣቸው ካሉ፣ ከዓለም ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊሰፋ መሆኑ ነው፡፡

ይህን እንዴት ያዩታል? … ወዘተ እያልኩ ከራሴ ጋር እጠያየቃለሁ… በመጨረሻ ዙምራ መጣ፡፡ ከገመትኩት በታች አጭር ነው፡፡ ቆፍጠን ያለ ነው፡፡ በልቤ በተለያየ አጋጣሚ ያወቅኋቸውን አዋቂዎችና ፈላስፋዎች፤ የሀይማኖት ፈጣሪዎች፣ በፈረንጂኛ Great Avatars የሚባሉትን ለምሳሌ:- እየሱስ ክርስቶስን፣ ቡድሃን፣ ዘሮስተርን እና ክሪሽናን ወዘተ ሌላው ቀርቶ፤ የአርሲ ፈረቀሳ መሪ የሆኑትን እሥር ቤት አግኝቻቸው የነበሩትን ቀኛዝማች ታየ መሸሻን ሳይቀር፤ ሃሣቤ ውስጥ አስገብቼ አውጠነጥናለሁ፡፡ አሁን የማየው የዙምራ ቁመት ከሁሉም ያጥራል፡፡ “እስቲ ስለልጅነትህ ንገረኝ?” አልኩት ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፡፡ በ64 ነው የጀመርኩት፡፡ በ4 ዓመት ዕድሜዬ ስለ ሰው ልጅ ማህበራዊ ኑሮ እንዳነሳሁ ከእኔ ቀድመው ያወቁት ይነግሩኛል፡፡ እናቴ ናት ዋናዋ፡፡ በልጅነቴ ያን ሁሉ ነገር ሳደርግ ለእኔ አትገልጥልኝም፡፡ “ሃሣቡ ከሰው ተለይቶ፣ ታሞ ነው” ትላለች፡፡ በየመድሀኒት ቤቱ ስትወስደኝ ነው የማውቀው፡፡ ግን አልዳንኩላትም፡፡

ከዚህ በ64 ዓ.ም እነሱን ሳገኝ ነው የረጋሁት፡፡ በ6 ወሩ ቆሞ ይሄድ ነበር ነው የምትለው፡፡ እኔ ቆሜ መሄዴን አውቃለሁ? አላውቅም፡፡ “ወደዚያ ሄደህ ያው የታወቁ ትላልቅ ሰዎች ማግኘትህን መቼም ታስታውሰዋለህ ብዬ ነው?” ሙሉውን ነው እማውቀው ሙሉውን! ተህጻንነቴ ጀምሮ ሃሣቡን ይዤው የምሄድ ስለሆነ አሁን የሚመራኝ ያው ሃሣብ ነው!፡፡ ተሃይማኖት አባቶች ቦታ እሄዳለሁ፡፡ ቤተክርስቲያንም መስኪድም … ሰው በተሰበሰበበት አደባባይ እሄዳለሁ … ሄጄ ግን ሁለት ሶስት አራት ጥያቄዎችን ነው የማነሳው፡፡ መቼም ተማያቸው እየተነሳሁ ነው ሰዎች ከሚሠሩዋቸው፣ ከሚናገሯቸው ….. ስላልተማርኩም ነው፤ ያስተማረኝ ባካባቢ የሚሠራው ህዝብ ነው፡፡ መጀመሪያ 4 ሀሣቦችን ነበር አንስቼ የነበረው፡፡ ኋላ ላይ ወደ 5 ሄደዋል። ይሄ በዙረት ነው፤ በ13 ዓመቴ፡፡ ውጪ በወጣሁ ጊዜ ግን አንድ ቦታ ላይ አንተ አንቺ ሲሉ አያለሁ። ሌላ ቦታ ላይ እርስዎ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ አንቱታና አንተታ፤ አንድ ቦታ አንዱን ሽማግሌ ሰውዬ አንተ ሲሉ እሰማለሁ፤ እድሜ የማይመለከተውን ሰው ደግሞ አንቱ ሲሉ እሰማለሁ፡፡ አንቱታ ሥራው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ አመጣሁ፡፡ ለክብር ነው ይሉኛል፤ ለክብርማ አይደለም፡፡ የላይና የታች ሰው መምረጥ የለበትም፡፡

ለክብር ቢሆን የመጀመሪያውን እድል እናትና አባት ይወስዱት ነበር፡፡ ከዚያም ቀጥሎ ዘመድ ይጋራው ነበር፡፡ ይሄ ከመነሻው ላይ ራሳችን በሰው ልጅ ላይ ልዩነት የፈጠርንበት ነው፡፡ ተሰባት ትውልድ በኋላ ባዕድ፣ ተሰባት ትውልድ በፊት ዘመድ፤ ብለን የፈጠርን ጊዜ፤ ለክብር ከሆነ ዘመድ ለምን ክብር አጣ? ነው ጥያቄዬ፡፡ “የራቀውን ባዕድ ሄደን አንተ ብንል ቀድሞ የጣልከኝን አሁን የት ታውቀኛለህ? የሚል ቁጣ ነው የሚያስነሳው፡፡ ዘመድ ዘንድ መጥተህ ደግሞ፤ አንቱ ብትል ያዝናል፡፡ እኔ ወንድምህ አደለሁ ወይ እንዴት አንተ ትለኛለህ ይልሃል፡፡” “እነዚያ ታላላቅ የተባሉት ሰዎች ካንተ ጋር ስለሃሳብህ ሲወያዩ የጨመሩት የለም፣ የቀነሱት የለም? የተለዩበት የለም?” “እነሱ ባይሰጡኝም እኔ እመልስላቸዋለሁ፡፡ የትኛው ነው ልኩ እላቸዋለሁ፡፡ ይህ ልክ ነው፤ “ግን ሰው አልሄደበትም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡኝ፡፡ አብሮ መሄድ አይቻልም፡፡ አንተ ግን ትክክክል ነህ” ነው እሚሉኝ፡፡ ስለዚህ ሁኔታውን ያዙት ብያቸው እሄዳለሁ … በ13 ዓመቴ ነው የሄድኩት … ዕብድ ነው ታሟል ተብሎ ነበር እሚባል በእናቴ በኩል፡፡ ከ4-13 ዓመት ተቤተሰቤ፣ ተዚያም ከህ/ሰቡ ጋር ነበርኩ፡፡” “በ13 ዓመቱ ኬት አመጣው ?ብለው ነዋ የማይሰሙት” አልኩ ለማስረገጥ፡፡ “ዕብድን ማን ያደምጣል? እሃይማኖት አባቶች ጋ ሄጃለሁ፡፡

ግን ብዙ ነገር አለ፤ መግለፅ የማልችለው እዚህ ውስጥ .. /በእስልምና በኩል ትንሽ ቅር የሚለኝ አለ/ በኦርቶዶክስ በኩል ግን በ13 ዓመቴ ነው እሚሉት እስከ 15 ዓመት ድረስ፡፡ ሁሉን ነገር ጨርሼ ተስፋ ቆርጨ፣ ጠይቄ አብቅቻለሁ፤ እሆነውን ሆኛለሁ። በኦርቶዶክስ በኩል ያገኘኋቸው ሊቅ አዋቂዎች ማን ይሄኮ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ነው የሚሉት እንዴት አመጣሽው? ከምን አገኘሽው አዕምሮው ባልፈቀደው ልጅ እንዴት መጣ? እና ሲያዩኝ ምግብ የለም፤ ምን የለም ዝም ብዬ ነው እምሄደው፡፡ ከሣምንት ከአሥራምስት ቀን ምግብ ባገኝ ነው ዝም ብዬ ነው እምሄደው፡፡ አሁንም እኔ የፈጣሪ ስዕል ነው ብዬ ነው እምሄደው … የእኔ ስዕል አይደለም። ያን ኩሉ ተቋቁሜ መሄድ አልችልም ነበር የእሱ ስዕል ባይሆን! ባንድ በኩል አሳዝናቸዋለሁ፡፡ ባንድ በኩል ደግሞ “እንዴት እቺ ልጅ በፈጣሪ ሥራ እንዴት ገብታ ትቸገራለች” ይላሉ፡፡ በእዝነት ነው እሚያዩት፡፡ በክብር ነው እሚያዩት! በጣም ይገርማቸዋል! በሙስሊሙ በኩል ግን ከነቢዩ መሃመድ ጋር ነው እሚያይዙትም፤ ብዙም አይደለም ፍላጐታቸው አንዳንዶች ኦርቶዶክሶች እንዲያውም “በሕዝብ ያላወረድነውን የመጽሃፍ ቃል ነውኮ እምትናገረው” ይላሉ /አንቺ ነው የሚሉኝ/ … እሷ ይዛ ያለችው፡፡ “የእናትህ ማ/ሰብ ግን በሽተኛ ነው ነው የሚልህ?” “ስሙንም ያወጡልኝ እነሱ ናቸው፡፡...እና…” “ደህና ቤ/ሰብ ነበር ግን ቤተሰብህ? ሀብት ነበረው?” “እናቴ ካባቴ ጋር ሳለv ሀብት ነበራት፡፡ በጊዜው ጥሩ ሰዎች ነበሩ፡፡አባቴ በህጻንነቴ በ4 ዓመቴ ነው የሞተ፡፡

እስከ 13 ዓመቴ ድረስ እናቴ ጋ ነው የቆየሁ፡፡ ለእናቴ እኔ አራተኛ ልጅ ነኝ፡፡ ከበታችም ከበላዬም አሉ… ብቻዋን ነበረች እሷ ሀብት ቢኖርም!” “ወንድም እህት አለህ?” “እህት የለኝም ወንድሞች አሉ፡፡ እናቴ ሴት ልጅ አልወለደችም፡፡” “እነሱስ ስላንተ ምን ይላሉ?” “ታሁን በፊት ታሟል ይሉ የነበሩ፣ “ለካ አንተ አልታመምክም፤ የታመምነው እኛ ነን” የታመምን እኛ ነው! ሚሉ፡፡” “ወደ አውራምባ ታዲያ እንዴት መጣህ? ከዚህ እስቴ አደል የተመለስክ?” “እስቴ ላይ ተመለስኩ፡፡ እስቴ ሆኜ ወደ ትዳር ዓለም ገባሁ፡፡ በትዳር ዓለም እያለሁ እርሻ አርሼ፤ በጋ በጋ ላይ-ብቻዬን መኖር ስለማልችል፤ ሰው ፍለጋ እዞራለሁ፡፡ ለብዙ ዓመታት ከዞርኩ በኋላ እዚህ አካባቢ ሃሣቤን የሚያደምጥ ሰው ሳገኝ፣ በተደጋጋሚ መጥቼ ካስረዳሁ በኋላ እዚሁ መጥቼ ብቀመጥስ አልኩኝ፡፡” የተሻለ ህይወትም አገኛለሁ አልኩ” “ሚስትህንስ እንዴት አገባሀት ታዲያ!? አስተሳሰብህን ተቀብላህ ነው፤ ወይስ እንዲሁ መፈቃቀድ ነው?” “መጀመሪያ ገበሬ ስሆን አጋቡኝ፡፡ ባመቱ ምርቱ የደረሰ ጊዜ እኔ ያገኘሁትን ምርት በአካባቢ ላሉ ችግርተኞች ማካፈል፡፡ የእኔ ደስታዬ እሱ ነው፡፡ እሱን በማደርግ ጊዜ ሚስቴ መስጠቴን የማትፈልግ ሆነች፡፡ “አዬ ዕብድ ነው እያሉኝ ገብቼ! ዕብደቱ የእኔ ነው እያወኩ የገባሁት፤ ራሴ ነኝ እያለች እምቢ አለች፡፡ እሷን ተውሁና እኔ ወደዚህ ማህበረሰብ መምጣት ፈልግሁ፡፡ አሁን እዚሁ አድጋ የተወለደች ልጅ አገኘሁ፡፡

እያሉ ጥለውኝ ሄዱ፤ እነዚያ በዕብደቴ ጥለውኝ ሄዱ፡፡ እነሱ ሀብት ማካበት የሚፈልጉ ይመስለኛል። ምርት እስከሚመጣማ ደህና ነኝ፡፡ ምርቱን የምሰጥበት ጊዜ ነው እምንጣላ! እኔ ደግሞ ማካበት እምፈልገው ሰውን ነው፡፡ ለዕለት የምትለብሰውን ካገኘህ ሌላው ትርፍ ነው፡፡ እሚፈለገው ለጥቂቱ ነው፡፡” “ምን ይሉ ይሆን እነዚህ የፈታሃቸው ሴቶች?” “ዛሬ ላይ ነው?” “አዎ፡፡” “እንግዲህ አላገኘኋቸውም” “እኔ ባገኛቸው ጥሩ ነበር እጠይቃቸው ነበር?” “እኔም አላገኘኋቸው” “ለየት ያለ ባህሪ ነው እንግዲህ አኗኗራችሁ ነገሩ ማ/ሰቡ ባህሉ ለየት ያለ እንዲሆን አድርጐታል ይመስለኛል፡፡” “አዎ፡፡ እኔኮ በሰዎቹ አልፈርድም፡፡ እነሱ’ኮ አደሉም የገቡብኝ፡፡ እኔ ነኝ የተውኳቸው። እየተውኳቸው እሄዳለሁ፡፡ ተመልሼ መጥቼ ይሄ መሆን ነበረበት እላለሁ የምትለው፤ መሆን ያለበትማ አንተ እምትለው ነው፡፡ ግን እንዴት ይቻላል ነው” እሚሉኝ:: “ታዲያ ለምን ለማስፋፋት አልሞከርክም? ይሄ ነገር ከአውራምባ ለምን አልወጣም?” “ዕብድ ነው ተብያለሁ፡፡ ከ93 ወዲህኮ ነው መስፋፋት የጀመርነው፡፡ ተሰደን እኮ ነበር፡፡ የማህበሩ አባል በቁጥር የማይገኝ ነው፡፡ የማ/ሰቡ አባል የማህበሩ አባል ነው፡፡

እየበዛ ነው፡፡ የሃሣቡ ተካፋይ ነው ማ/ሰቡ፡፡” “ከአራቱ ሃሣቦች አምስተኛ ስድስተኛ ሰባተኛ እያልክ ለምን አልቀጠልክም ነው? አልመጣልህም?” “ሃሣቦቼ እንደሱ ሆኖ የተፈቀደልኝ ነው፤ እነሱኮ ብዙ ናቸው?” “ ሲመነዘሩ?” “አንደኛው የሴቶች እኩልነት ነው፡፡ ሴት በሴትነቷ እናት ናት፤ ወንድ በወንድነቱ አባት ነው፡፡ እኩል ናቸው፡፡ እሱ በቤቱ ገዢ ሆኖ አዛዥ ቢፈልግ እሚረግማት፣ ቢፈልግ እሚሰድባት፣ ቢፈልግ እሚደበድባት፣ ሲፈልግ ውጪልኝ ከቤቴ ብሎ አስወጥቷት እሚቀመጥ ለምን? ነው ጥያቄው፡፡ እናት በሌለችበት አባት የለም፡፡ አባት በሌለበት እናት የለችም፡፡ እኩል ናቸው ግን እሷን እንደሞግዚት ያደረግነው ለምንድነው?! በጉልበት ነው? አይደለም፡፡ አፈጣጠሩ እኩል ነው፡፡ ሌላው ህጻናቶችን በሚመለከት ነው ሥራ ሲሰጣቸው አያለሁ ያ ሥራ ሲጠፋባቸው ለምን አጠፋህ ለምን አበላሸህ? አርጩሜ ይከተላል፡፡ ለምን ይሆናል? ነው፡፡” “ከመግረፍ ይልቅ ታዲያ በምን መለወጥ ይቻላል? በነሱ አቅም ምን ይደረጋል?” “በአቅማቸው የሚሆን ነገር መስጠት፡፡ ከዚያም ምክር መስጠት ነው፡፡ እኛ ያልቻልነውን እነሱ አይችሉም፡፡ ተማርን ያልነው ዱላ ስናነሳ ምን ይዘው ያድጋሉ? እሱን ይዘው ነው ሚያድጉት፡፡ እና ለምን? ምን ዘርተን ምን ልናመርት እንፈልጋለን? ምርታችንን ከፍ እያደረግን ነው ከእኛ ይበልጥ እነሱ ይሸከማሉ ለምን ነው?” 3ኛው/ ባካባቢው የወደቁ አረጋውያን አሉ በእርጅና ጠንካራው ደካሞቹን እንዲያስተዳድራቸው፣ በልተው ጠጥተው አርፈው እንዲኖሩ ነው፡፡ እንደኛው ሰው ናቸው እኛ ትተናቸው ከሄድን ማን አላቸው፡፡

ለሰው ደራሹ ሰው ነው፡፡ እኛም አንድ ቀን እንወድቃለን፡፡ የሚረዳን የሚያስጠጋን እንፈልጋለን? እኛ እንደምንፈልገው ሁሉ እነሱም ያስፈልጋቸዋል፡፡ 4ኛው/ ሰውን ሰው ሲዋሸው፣ ሲሰርቀው፣ ሲዘርፈው፣ ሲደበድበው ይታያል፡፡ ለምን? ለራሳችን ሊደረግብን የማይገባ ነገር ለምን በሰው ልጆች ላይ እናደርጋለን ነው፡፡ ከሌሎች እንስሳት የተለየ ከሌለን ለሰውነታችን ምን መኖር አተረፍን? እሄን ባልኩ ሰው እንደሚያስበው አታስብም ይሉኛል የማይወጣ ጥጃ ከማሠሪያው ይታወቃል። ዕውነት አይደለም ወይ? “ዕውነትማ ዕውነታ ነው፤ ግን መሸከም አይቻልም” ይላሉ፡፡ 5ኛ/ ሌላው ቅድም ያልኩህ ነው የአንቱታና ያንተታ ጉዳይ፡፡ ትልቁ ሀብት ሰው መሆን አለበት ሌላው ሁለተኛ ነው፡፡ ሌላው ጠብ እስከናካቴው ተምድረ-ገጽ መወገድ አለበት፡፡ ሰላምን መስርተን ገነትን ፈጥረን መሄድ አለብን፡፡ ጠብ እንዴት ይኖራል? ትላለህ ነው ጥያቄው፡፡ ጠብን የምንሠራው እኛ ነን ከዚያ ይልቅ ፍቅርን ብንሠራ!” “ግን ተገንብቷል? ማህበረሰቦች የተገነባ ሥርዓት አላቸው በዚያ ውስጥ ጠብም ተገንብቷል፡፡ አሁን ጠብ አይኑር ብትለው ማንም እሺ አይል ፡፡ውስጡ ተገንብቷልና ልጆች ግን እንደ አዲስ ማስተማር ከያዝክ ቀላል ነው እሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ልጆች ናቸው ጠብ እንደማይኖርና እንዳይኖር አድርገው ያድጋሉ፡፡

ጥሩ አርገህ ከተንከባከብካቸው ያን ይዘው ያድጋሉ፡፡ ህ/ሰቡ አንዴ የያዘውን ይዞ ታንጿል፡፡ ስለዚህ ለመለወጥ ሳይከብድ አይቀርም። አሁን ለምሳሌ አንተ ሄደህ ከፈላስፎች ጋር አትነጋገርም፡፡ የነሱ ሃሣብ ላንተ ያንተም ለነሱ ሆኖ ምናልባት ልትለውጣቸውም ከቻልክ ለምን አትለውጣቸውም? እዚህ አውራአምባ ውስጥ ብቻ በመኖር ተከልሎ መቆየቱ፣ ብዙ እድሜ እዚሁ እንዲቀር አያረገውም ወይ? አላስፋፋኸውም ማለቴ ነው፡፡ ወደ ህ/ሰቡ ማስተማር ለማደግ…” እያልኩ አቋረጠኝና ትንሽ ቆጣ ብሎ “የተማርነውን ይዘን ከዚህ ብንገባስ የአገኘነውን ይዘን ብንገባስ? እኔ ብቻ ሳልሆን ከኔ ብቻ ሳትጠብቁ የአገኘነውን ይዘን ብንሄድ ቤታችን ብንገባስ?” “እኔኮ እዚህ ድረስ መጥቼ ነው ያገኘሁህ? አንተ ወደህብረተሰባችን አልመጣህም!” “የእኔ እግር ተጠብቆ ነው ታዲያ?! ዓለም እምትድነው የእኔ እግር ተጠብቆ አይደለም፡፡ በአንድ አካባቢ በአንድ ሰው አንድ ሃሣብ ሲመነጭ የግለሰቡ ድካም ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ያገሪቱ ንብረት ነው መሆን ያለበት! ያገሪቱ ንብረት ይሁን ታልን ደሞ ምሁሮች ናችሁ መረከብ ያለባችሁ፡፡ “ምሁሮች እንዲረከቡ መማር አለባቸዋ ፍልስፍናህን?” አዎ ምሁሮች ናቸው መረከብ ያለባቸው ምሁሮች ቁጣው እየጋለ ነው፡፡ “አዎ ምሁሮች ናቸው፣ ወደዱም ጠሉም መረከብ ያለባቸው፡፡ እነማናቸው? የሃይማኖት አባቶችም ይሁኑ፣ የቀለም ምሁሮች መረከብ አለባቸው! ተረክበው ወደ ሀገሪቱ እንዲሰርጥ ማድረግ የምሁሮች ፋንታ ነው! እንደመነጨህ አገሪቱን እየሄድክ አልብስ እሚሉት ፈሊጥ ነው ችግሩ! ከተገኘ አባይን አሁን በአገሪቱ እንውሰደው ብንል ማንም መውሰድ አይችልም፡፡ በራሱ መሄድ አይችልም፡፡ ቅብብሎሽ ካረግነው ግን ይቻላል፡፡ ምሁሮቹ ደሞ ጥሪውን አግኝተው ወደ ህዝብ የማያሰርጡ ከሆነ ያገኙትን ዕውቀት ያገራቸው ሀብት ለራሳቸው ብቻ ለምን ይሆናል ነው፡፡

ሀብት ጥሪት ሳይያዝ ምሁርነታቸው ምንድነው ነው? ተጠያቂ ናቸው! አይደለም በሉኝ አስረዱኝ ምሁርነታቸው ምንድነው? ስተት ነው በሉኝ ተምኑ ላይ? እኔም መማር አለብኝ፡፡ ነው ካልነ ለማን እንተወው ?መቼ ላደርሰው ነው ለህ/ሰቡ ማለት አለባቸው… አሁን ደርሷል በቴሌቪዥን፣ በራዲዮ፣ በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በኢንተርኔት… ዓለምንም ሞልቷል፡፡ ንብረታችን ነው እንውሰደው። አለበለዚያ አንተ እየሄድክ እየተንቆረቆርክ አድርስ ከሆነ እምትሉ እኔ ቀጠልኩ፤ ስንፈት ወይም ቂመት ወይም ቅጥፈት ወይም ሽንፈት ነው ብዬ ነው እማስበው ሽንፈት ነው!!” በጣም ተቆጣ አሁን፡፡ “አሁን ሰዎች ተቀበሉት በኢንተርኔት እንበል። የራሳቸውን ጨመሩበት እንበል አንተ እሥሩ ከሌለህ፤ ኦርጅናሌው ሰው ከሌለህ፣ ነገ እየተዛባ ቢሄድ ማንም ሊከላከለው አይችልም፡፡ ስለዚህ፤ ወይ አንተ የማሳወቂያ መንገድ መፍጠር አለብህ ማለት ነው፡፡ እኔ ሳስበው ግን አንተ መጣጣር አለብህ። ሁልጊዜ እምለው፤ ለምን አይሰፋም? ለምን አዲስ ሃሣብ አልመጣለትም? ለምን አልጨመረም ዙምራ? እላለሁ፡፡ ከሰማሁ ቆይቻለሁ፤ እንደው ዕድሉን ባገኝና ባገኘው ይሄን እለዋለሁ ስል ነበር።” “እንዳንተው ለመፈለግ ያልፈለገ ሁኖ ነው። እንዳንተው፡፡ ከሰማህ ጀምረህ አልመጣህል፡፡” “ያለሁበት አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ፈቃደኛ ሳልሆን ቀርቼ ሳይሆን ሁኔታው አልፈቀደልኝም ነው የምለው፡፡” ዙምራ እየተቆጣኝ እየገነፈለብኝ ነው አሁን፡፡ “ማነው ተጠያቂ እሺ?” “ካልመጣሁ አዎ ተጠያቂ ራሴ ነኝ፡፡ አንተ አትሆንም… ግን ፈቃደኛ ስላልሆንኩ አይደለም… አሁን ለምሣሌ አንተ አውሮፖ ሂድ ብልህ አቅም ላይኖርህ ይችላል.. ግን አውሮጳ አንድ ፈላስፋ ይኖራል ያንተ አይነት አስተሳሰብ ያለው፡፡

ይህን ሰውዬ ባገኝ ጥሩ ነበር የማለት ሃሣብ ካለህ ብቻ ነው በጐ ፈቃደኛ የምትባለው፡፡ ግን… እሱም ለራሱ ነው እኔም የራሴ ነኝ ከሆነ መደጋገፋችን ቀርቷል፡፡ አንዱን ዓላማ ስተነዋል ማለት ነው፡፡ እኔ እምለው አንተ የምታውቀውን ካላካፈልክ ይጐዳል ሰው ላገርህ ነውና ጥቅሙ፡፡ ስለዚህ ወዳንተ መምጣት የሚችለው ይምጣ፡፡ አንተም ደግሞ የምትችለውን መንገድ ፍጠር! ያንተ አስተሳሰብ ቢሰፋ ማ/ሰቡ ይጠቀማል እንጂ አይጐዳም፡፡ ጥሩ አስተሳሰብ አለበትና፡፡ ዋናው ግን ማድረግ መሞከር አለብህ ነው ምልህ!” “በእኔነቴ ስዞር ስዞር ብዙ ቆይቻለሁ፡፡ ወይም እሚሰማኝ ባገኝ ብዬ ወይ የሚጠይቀኝ ብዬ … “ልክ ነው” “አሁን አይደለም፡፡ ኢትÄጵያ አፍሪካ ብናንኳኳ አውቃለሁ የሚል ብቻ ነው ያለው! ‘አውቆ የተደበቀ ቢጠሩት ወይ አይልም’ ነው፡፡ “ልክ ነው” “ተሰማ በኋላ ግን ይህ ነገር ንብረት ነው ብለን ለንብረት መቆርቆር ያለብን ሁላችንም ነን፡፡ ተቆርቁሮ ያልበረረ ሰው ነገር ብትግተው አይዋጠውም፡፡ ዛሬ ብዙ ቀጣፊ አሳማኞች ያሉበት ጊዜ ነው! በየደጃፉ እየቆረቆርክ ይሄ ምንድን ነው ብትለው፤ ሊሰማህ አይሻም፡፡ ምነው ብትል አውቆ…. “አውቆ የተኛ ነው!” “ሊክ! ‘አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት አይነቃ’ ነው፡፡ የሆኑ ፈረንጆች ገቡ፡፡ ሰላም አልኳቸው፡፡ “አሁን አውራምባ ታውቋል፡፡ እነዚህ ሁሉ እሚመጡት ኢንተርኔት አስተዋወቀን እያሉ ነው…” “እኔም ስሄድ ላስተዋውቅ እሞክራለሁ” “እየጣፍክ በየሼልፉ ብታስቀምጥም ገልጠህ ዕቃውን ካሳየህ ዋጋ የለውም… መውሰድ አለብህ። ወስደህለት ካልወሰደ አይወሰድም … ይሄ ዕንቁ ነው ሀብታችን ነው ካልነው ግን ወደፈለቀበት ወደ ምንጩ ይመጣል፡፡ ወደቦታው ስንመጣ ነው እውነት የሚሆነው፡፡ ኑሮ እኖራለሁ ብዬ ባሰብኩ ኑሮዬን በሰው ልጆች ላይ ባደረኩ ነበር፡፡ የለም። አይሆንም፡፡ እና የእኔ ሃሣብ ይሄ ነው፡፡ ሌላው በኢንተርኔት እየታወቀ ነው፡፡ ገለጻዬን መስጠት ነው፡፡

አንድ አውቶቢስ ሰው እዚህ ቢመጣ አሁን፤ ብዙ ገንዘብ ይቀበላቸዋል፡፡ ያን ከማድረግ ይልቅ፤ እኔን ወደዚያ ወስደውኝ ሃሣቤን ብሰጥ መልካም ይሆን ነበር!” “ትክክል ነው አሁን ተግባባን!” “እሱ ነው መሆን ያለበት፡፡ ምንጩ እስከሚታወቅ ድረስ የለፋሁትን ልፋት ብታስብ፣ ይሄ ደጅ እንዴት ይታለፋል ሲሉ፣ አልፌ ሄጃለሁ፡፡ የእኔ ስዕል ሳይሆን የፈጣሪ ስዕል ነው፡፡ እዚያ ድረስ ሄጃለሁ፡፡ አሁን ላይ ግን ተጣቧል፡፡ ከጠበበ በኋላ ዝም ብለን እምናይ ከሆነ ተኝተናል፡፡ ምሁሮች ራሳችንን እያታለልን ነው የምንኖረው፡፡ ባናታልል ጥሩ ነበር፡፡ እኔ አንድ ነገር የማስበው አለኝ፡፡ እኔ ገበሬ ነኝ፡፡ ያንድ ገበሬ ሃሣብ ነው፡፡ በታሪክ ስናይ እየሱስ ክርስቶስንም እንውሰድ ነብዩ መሃመድንም እንውሰድ፤ ብዙ መማርና ትምህርት መውሰድ የነበረባቸው ሰዎች ጥላቻቸውን ተከናንበው ተኝተው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ በነበራቸው ሰዓት ጠይቀው ተረድተው ቢኖር ኖሮ ይሄ ሁሉ መከፋፈል ባልነበረ! ከራሳቸው ከባለቤቶቹ አንደበት ሰምተው ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ መከፋፈል ባልነበረ እነሱን አርቀን አርቀን ከገፋናቸው በኋላ፤ ጊዜያቸውን ሳይጠቀሙበት ካለፉ በኋላ መጽሐፍ ተጽፎ በስማ በለው አይሆንም፡፡ ….ነገር ሁሉ እሚበላሸው እንደዚህ እየሆነ ነው፡፡ …. እንዲያው ከሰማሁት ታሪኩን ልንገርህ ብዬ ነው፡፡ እኔ በየኢትÄጵያ ይሄን ምንጭ ይዘን ቁጭ እንበል፣ እንኑር ከሆነ ራስን መተቸት ነው…” “ግን የመማር ዕድል አልነበረህም? ለምን አልተማርክም?” “እስካሁን የተማርኩትስ “ፊደል ቆጠራውን ማለቴ ነው… “እውነት ካልከኝማ አለመማሬ ይቆጨኛል አንዳንዴ! አንደዜ ደግሞ አይቆጨኝም፡፡ “አንደዜ እሚቆጨኝ ምንድነው? መጣፍ ማሠራጨት ጥሩ ነበር…” “ልክ ነው” “ለራሴ መጣፍ አልችልም፡፡

ማንበብ አልችልም። ስላልተማርኩ ማለት ነው፡፡ እንግሊዝኛ ሲናገሩ እኔ ደንቆር ነኝ፡፡ አውቅላቸው ነበር እሚፈልጉትን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አይቆጨኝም። ለምን? አገራችን ምሁር አላጣችም፡፡ የት ነው የደረስነው ብዬ ሳስብ የትም አልደረስንም! አድቀናታል፡፡ ትልቅ ዳቦ ያማራቸው ሰዎች ሠርተው ያሳደጓት አገር ናት ኢትÄጵያ፡፡ እኔም ብማር ኖሮ አገሬን አደቃት ነበር እላለሁ፡፡” “ሌላ ጥያቄ አለህ?” “ጨርሻለሁ?” እኔ እምለው ነገር ነው እምለው ነው፡፡ ካልክ ምሁር ነህ ውሰደው፡፡ አይደለም ካልክ እምኑጋ እኔም ልማር!” “አመሰግናለሁ!” በልቤ አውራምባ ደግሜ መምጣት አለብኝ - አልኩ፡፡ የቀረኝ ነገር አለ፡፡ “ሰዎች ከሚሠሩት እያየሁ ነው የተማርኩት፤ በ4 ዓመቴ ነው አስተሳሰቡን የጀመርኩት፤ በላቸው አለ ዙምራ ለአስተርጓሚው፤ ለፈረንጆች እንዲነገርለት፡፡ ዕውነትም እንግሊዝኛ አለማወቁ፣ መቆጨቱ ልክ ነው እያልኩ በሆዴ፤ ወጣሁ፡፡ * * * እነሆ ለብዙ ሣምንታት፣ ከእየሩሣሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢህማልድ - JECCDO) ጋር ከአመሠራረታቸው ጀምሮ ልማታዊ ትሥሥር ያላቸውን ማህበረሰብ ተኮና ድርጅቶች (CBOs) (ማህበራትና እድሮች) ስጐበኝ ቆይቻለሁ፡፡ በዚህ ጉዞ ከደብረ ዘይት ጀምሬ፣ በናዝሬት አድርጌ፣ በአዋሳ አቋርጬ፣ ደብረ ብርሃንን አካልዬ በመካያው ባህርዳር ከትሜ፣ የአውራምባን ማህበረሰብ አይቼ አበቃሁ፡፡ የሀገር ልማትና ጥንካሬ በማህበረሰቦች ድርጅታዊና ማህበራዊ አቅም ላይ መመሥረቱን፣ ህዝብን መሠረት አድርጐ የሚጓዝ ልማታዊ እንቅስቃሴ ምንጊዜም ዘላቂነት አንዳለው፣ አስተውያለሁ፡፡

የከተማ ግብርና የህፃናት ትምህርት፣ የአረጋውያን እንክብካቤ፣ የጽዳትና የጤና አጠባበቅ ስልቶች፣ የሴቶች ልባዊ ተሳትፎ የአምራቾች የኅብረት ሥራ ቅስቃሴ በማህበረሰብ ቁጥጥር የሚመራ የገቢ ምንጭ ሀብቶች ጥራት በማህበረሰቡ በራሱ ይዞታዬ፣ ጉዳዬ ተብሎ ሲያዝ ምን ያህል ዘላቂና ለሀገር ልማት ልዩ ፍኖት ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቤአለሁ፡፡ ይህን መሰል እንቅስቃ እንደአስፈላጊነቱና እንደአግባቡ ከመንግሥት ጋር እንዴት ተደጋግፎ ለመሥራት እንደሚቻልም ልብ ብያለሁ፡፡ እንደእየሩሳሌመ ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅትና ሌሎች መሰል ድርጅቶች ህብረተሰብን በማስተባበር፣ በማገዝና ራሱን እንዲችለና እንዲበቃ ከማቴሪያል ጀምሮ እስከ ከፋይናንስና ሥልጠና ድጋፍ በመስጠት፤ ማህበረሰቡ በሁለት እግሩ ሲቆምና ራሱን በራሱ ለማዝለቅ ሲችል፤ ጉዳያቸውን ጨርሰው በመውጣት (Phase – out በማድረግ) ዕድገትን ለማጠናከር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ያየሁበትን ጉዞ አብቅቻለሁ፡፡ ምናልባት በቦታና በጊዜ ጥበት ምክንያት የተውኳቸውን አያሌ አስገራማ ዝርዝር ሰዋዊ አሻራዎች፤ ሌላ ጊዜ በሌላ መልክ እጽፍላችሁ ይሆናል፡፡

Read 4347 times