Monday, 27 January 2014 08:16

“ፉርሽ ባትሉኝ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(4 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…እምጥ ይግቡ ስምጥ ያላወቅነው፣ በፊት የ‘አደባባይ ፊት’ የሚባሉ አይነት የነበሩ ሰዎች አሉ አይደል…ግዴላችሁም፣ ምን አለ በሉኝ ዘንድሮ ምሰው ከገቡበት ጉድጓድ ምስው ወጥተው ብቅ ሳይሉ አይቀሩም፡፡ ከየትም ይሁን ከየት ብቻ ብቅ ብለው ሳንጠራቸው “እዚህ ነኝ” የሚሉን ይመስለኛል፡፡፡ አሀ…የ“ፉርሽ ባትሉኝ…” ዘመን ነዋ! እናማ…እስከ ከርሞ ‘ኢሌክሽን’ ስንት “ፉርሽ ባትሉኝ…” ይኖራሉ የሚል የሪያሊቲ ቲቪ ሾው ይዘጋጅልንማ!
ስሙኝማ…የዚህ አገር ‘ቦተሊካ’ አንዳንዴ የሆነ አሪፍ ነገር አለው፡፡ “ፉርሽ ባትሉኝ…” ማለት ችግር የለውማ! ልክ ነዋ… “ፉርሽ ባትሉኝ…” እያለ ‘አጥር የዘለለውን’ (‘እየዘለለ ያለውን’ ብሎ ማስተካከልም ይቻላል) እስቲ አስቡት፡፡
እንግዲህ ባለችን ሚጢጢ ግንዛቤ በብዙ ሀገራት እንደምናየው ከ‘ቦተሊካው’ እልፍኝ የወጣ…በቃ “ወጣ” ነው፡፡  
ስሙኝማ… ሆሊዉድ አንድ እኛ “ቴክስ” ብለን የምንጠራቸውን፣ በስድስት ጎራሽ ሽጉጥ… አለ አይደል… መልሰው ጥይት ሳያጎርሱ አሥራ ሦስት ጊዜ ተኩሰው አሥራ አንድ የሚጥሉ አይነት ገጸ ባህሪያት አዘውትሮ የሚጫወት ተዋናይ ነበር፡፡ እናማ…ትንሽ ይቀሽምላችሁና ከትወናው መድረክ ይጠፋል፡፡ ጥቂት ዓመታት ቆይቶ ብቅ ይልና አንዱን ዳይሬክተር የሆነ ፊልም ላይ  አንድ ገጸ ባህሪይ እንዲሰጠው ይጠይቃል፡፡
ዳይሬክተሩም “ካው ቦይ ሆነህ ስትጫወት ፈረስ ብዙ ትጋልባለህ…” ይለዋል፡፡ ተዋናይም “እንዴታ!” ሲል ይመልሳል፡፡ ዳይሬክተሩም ምን አለው መሰላችሁ… “ተመልካቹ የሚፈልገውን ልንገርህ አይደል …ፈረስህ ላይ ተቀምጠህ ዘወር ብለህ ሳታይ እስከ ዘላለምህ እንድትጋልብ ይፈልጋል…” አለውና አረፈላችሁ፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮ “ዘወር ብለህ ሳታይ እስከ ዘላለምህ እንድትጋልብ ይፈልጋል…” የሚባሉ “ፉርሽ ባትሉኝ…” ሰዎች እየበዙብን ነው፡፡
ታድያላችሁ…“አበቃለት፣ በቃው፣ የምናምን ዴሞክራሲ ማኒፌስቶውን ሰቀለ” (ቂ…ቂ…ቂ…) ምናምን የተባለ ‘ቦተሊከኛ’፣ ምናምነኛ… ድንገት ብቅ ይልና…ስንት ዓመት ፖውዝ ላይ የነበረችውን ቁልፍ ትቶ ፕሌይን ይጫናል፡፡ እኛ የፈረደብንም ‘ተቀባይና ሸኚዎችም’ ዜማና ግጥሙ ለ“ፉርሽ ባትሉኝ…” እንደሚመች ሆኖ የተዘጋጀውን ‘ቲሪሪም ታራራም እንሰማለን፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንዳንዴ የሆኑ ዝግጅቶች ላይ ነገሬ ብላችሁ እንደሁ አስተናጋጁ፣ “ብሉልኝ፣ ጠጡልኝ” ባዩ አይበዛባችሁም! የዝግጀቱ ባለጉዳዮች መሆናቸውን የምታውቃቸው ሰዎች እኮ ሌሎች ናቸው! እናላችሁ…ሰዎቹ ዋና አጋፋሪ ሆነው ‘አዳራሹ ይጠባቸዋል’። ዋናው ሥራ ላይ፣ ዝግጅቱን እዛ ደረጃ ለማድረስ የጠየቀው ልፋት ላይ ግን ለደቂቃ ብቅ ብለው አያውቁም፡፡ “እሱ ሰውዬ ምነው ጠፋ፣ ውጭ አገር ሄደ እንዴ!” ምናምን ሲባልላቸው የከረሙ ናቸው። እናላችሁ… ሥራው ሁሉ አልቆ የ‘መታያው’ ጊዜ ሲመጣ ምን አለፋችሁ…ከየት ይሁን የት ዱብ ይሉና መድረኩን ይቆጣጠሩታል፡፡ ነገርዬው  “ፉርሽ ባትሉኝ…” ነዋ!
እናላችሁ… በ“ፉርሽ ባትሉኝ” ስትራቴጂ ‘በጨው ደንደስ በርበሬ ሲወደስ’ ይኖርላችኋል። ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… አሁን፣ አሁን የሚሳካላቸው እንደነኚህ አይነት ሰዎች እየሆኑ መምሰሉ፡፡ አስመሳይ መሆን የሚያሳማው ‘ለአፍ’ ነው እንጂ በተግባር ነገርዬው ሌላ እየሆነ ነው፡፡
አባቶቻችን እኮ “ለጌሾ ወቀጣ ማንም ሰው አልመጣ፣ ለመጠጡ ብቻ ከየጎሬው ወጣ” የሚሉት…“ፉርሽ ባትሉኝ” ባይ ሲበዛባቸው ነው፡፡
ምን መሰላችሁ…አንድ ነገር ሲታሰብ መጀመሪያ ‘ሀይ፣ ሀይ’ ባዮች እነኚሁ “ፉርሽ ባትሉኝ…” ባይ ሰዎች ናቸው፡፡
“ፉርሽ ባትሉኝ…” አለ አይደል በብዙ መልኳ ትመጣለች፡፡ ለምሳሌ በአነጋገር ትመጣለች፡፡ ልክ ነዋ፣ ሥራው ቦታ ላይ “ይሄ ሰውዬ የተቀጠረው ቁጭ ብሎ እንትኑን ሲያሽ ሊውል ነው እንዴ!” የሚባልለት ሰው…አለ አይደል…የሆነ ስብሰባ ምናምን ላይ ምን ይላል መሰላችሁ… “አገራችን በተያያዘችው የልማት ጎዳና ሠራተኛው ደከመኝ ሳይል በንቃት…” ምናምን ብሎ የቦሶችን ቋንቋ ለ“ፉርሽ ባትሉኝ…” ስትራቴጂ ቋንቋ ይጠቀምባታል፡፡
የምር ግን… የሆነ የኃይማኖት ትምህርት የሚሰጣችሁ ሰው… “በተያያዝነው የዴሞክራሲ ጎዳና…” ምናምን ቢል “ይህንን ደግሞ ከየትኛው የኃይማኖት ድርሳን ላይ ነው ያገኘኸው…” ምናምን ማለት አያስፈልግም፡፡ አሀ…“ፉርሽ ባትሉኝ…” ስትራቴጂ ሊሆን ይችላላ! (እግረ መንገዴን…በሰላም በምንጓዝበት ጎዳና ‘የግድ’ ያህል እያስቆሙ “የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ እኛ ዘንድ ነው” አይነት ዕውቀት ሊሰጡን የሚሞክሩ ሰዎች መብታችንን እየታገፉ እንደሆነ ልብ ይባሉልንማ!) ስሙኝማ…መቼም ጨዋታ አይደል…አንዳንድ ጊዜ እኮ ሊሉ የፈለጉትን ነገር ብሎ “በሰላም ያውለን” ብሎ መለያየት አሪፍ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ…አንዳንድ ጊዜ የዕቁብ ጸሀፊ ለመሰየምም፣ “የሹሮ ዕቃዬን አልመልስ አለችኝ፤ ልብ አድርጉኝ…” ለማለትም…አለ አይደል… “ዓለምን እያስቀና ያለው ልማታችን…” አይነት “ፉርሽ ባትሉኝ” ቀሺም ነው፡፡
ከዚህ በፊት ደጋግመን ያወራናት ነገር ነበረች። ያኔ ገና ‘ወንበሩም እንዳሁኑ ሳይሞቅ’፣ ‘ፊትና ኋላው ሳይለይ’… ሁሉም ሰልፍ ላይ የማትጠፋ መፈክር ነበረች... “የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር እንደግፋለን፣” የምትል፡፡ ልክ ፖሊዮ በሽታን ለመከላከል የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ “የእነ እንትና ወገኖች ናቸው” ላለመባል አገልግሎት ላይ የምትውል ‘ክትባት’ በሏት፡፡ (ስኳር ይፈቀድልን ብለው የተሰለፉ ‘የማር ጠጅ’ ነጋዴዎች ሳይቀር ይቺን መፈክር ሳይዟት ቀሩ ብላችሁ ነው! ያኔ “ጠጁን የምንጥለው በማር ነው” እንዳላሉን በአደባባይ “የስኳር ያለህ” ሲሉ ሳቅን፡፡  በኋላ ‘ስኳር መላስ’ እንዲህ የአገር ጉዳይ ሊሆን!)
እናላችሁ…ዘንድሮም “በተያያዝነው ፈጣን የልማት ጎዳና…” ምናምን ማለት “የሽግግር መንግሥቱን ቻርተር እንደግፋለን፣” የ‘ክትባት’ አገልግሎት የምትሰጥ መፈክርን የተካች ትመስላለች። እዚህ አገር እኮ በማስመሰልና በመመሳሰል ‘ቅዝምዝሙን ዝቅ ብሎ ማሳለፍ’ ልዩ ጥበብ እየሆነ ነው፡፡ ደግነቱ ቦሶችንም ቢሆን በ“ፉርሽ ባትሉኝ…” ማስቀየሱ እስከዚህ የአይዛክ ኒውተን ጭንቅላት የሚጠይቅ መምሰሉ፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የቃላት አጠቃቀምን ካነሳን አይቀር ይሄ ለ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተያየት’ የሚያገለግለው ቃልና ሀረግ ውስጥ ሁሉ ነገር  እየገባላችሁ ነው፡፡
ደግሞላችሁ…በአጭሩ ማለቅ የሚችሉ ሀሳቦች እየረዘሙ “”ይህንን ላለመስማት የት አገር ልሰደድ ሊያሰኙ ምንም አይቀራቸውም፡፡
ስሙኝማ… ለምሳሌ…ሚዲያ ላይ ስለ ኳስ ሲወራ… አለ አይደል…“ይሄ ነገር ኳስ ነው ወይስ የሆነ የፖለቲካ ቡድን ማኒፌስቶ…” ምናምን የሚያሰኙ አቀራረቦች ይገጥሟችኋል፡፡ ልክ ነዋ… አሁን ለምሳሌ “የማን ዩናይትድ አሰልጣኝ ዴቪድ ሞይስ በደጋፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እያስተናገዱ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው…” አይነት አቀራረብ አሪፍ ሚስቶ አይደለም፡፡ “ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል…” አይነት እጥር ምጥን ያለ አባባል እያለ፡፡
እናላችሁ… “አሸንፏል” የምትል እጥር ምጥን ያለች አባባል እያለች “ባርሴሎና ሪል ቤቲስን በሜሲ ጎል ማሸነፍ ችሏል” አይነት ነገር ትንፋሽና ወረቀት መጨረስ እንዳይመስልብንማ፡፡
እናላችሁ…በዛ ሰሞን ኳሳችን ትንሽ አንቀሳቅሶን በነበረ ጊዜ…የዚህ አይነት አቀራረቦች በዝተው ነበር። (ስሙኝማ…እግረ መንገዴን ይሄ ኳሳችን አሁን እንግዲህ ያው የደረሰበት ስፍራ ደርሷል፡፡
እናላችሁ…መለስ ብሎ ከጥቂት ወራት በፊት የጭፈራው ሰሞን የነበረው ‘ፓትሪዮቲዝም’ ምናምን ያልተጫነው ውይይት ለማድረጊያ አሪፍ ጊዜ ነው፡፡ እናማ…ስፖርት ጋዜጠኞቻችን እውነት ቡድን ተመስርቶ ነበር ወይስ በአብዛኛው የግለሰብ ተጫዋቾች ችሎታ ነው ምናምን የሚለውን ተንትኑልንማ! በወቅቱ የነበረውን ‘እውነታውንና ህልሙን’ ለዩልን!)
እናላችሁ…እጥር ምጥን ማለትና ግልጽ መሆን እየተቻለ… “በትናንቱ ጨዋታ ቼልሲ በሜዳው ሽንፈት አስተናግዷል…” አይነት ነገር…አለ አይደል… ትንሽ ግራ ይገባል፡፡ “ተሸንፏል” የምትል እጥር ምጥን ያለች ቃል እያለች! ደግሞ ‘ሽንፈትን ማስተናገድ’ ምንም ማለት እንደሆነ እስቲ አጠያይቃለሁ፡፡
እናላችሁ…“ይቺ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው…” ፣ “በተያያዝነው ፈጣን የልማት ጎዳና…” መንግሥት፣ የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ ባለው ከፍተኛ ቁርጠኝነት…” የሚሏቸው ጉደኛ ሀረጎች ለ“ፉርሽ ባትሉኝ” እየተጠቅምንባቸው ነው፡፡
እንትናዬ…ያቺ ‘ሳዮናራ’ ምናምን የተባለባት ቀን ስንት ዓመት ሆናት? ግዴለሽም…እሱን ተዪውና…“ፉርሽ ባትይኝ…”
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4876 times