Monday, 03 February 2014 12:56

“የምዋሸው ዕውነቴን ለመቆጠብ ብዬ ነው” አለ አሉ አያ ዋሾ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂ ነኝ ባይ ሰው ወደገበያ ቦታ ይሄድና “ዕጣ - ፈንታችሁን እነግራችኋለሁና ማወቅ

የምትፈልጉ ተሰብሰቡ” ይላል፡፡
ሰው ባንድ ጊዜ ይሰበሰባል፡፡ ለመጀመሪያው ሰውዬ፤ “ምን እንድረዳህ ትፈልጋለህ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ይህ ሰውዬ

አለባበሱ ለየት ያለ ነው፡፡ በጣም ደማቅ አረንጔዴ ካፖርትና አረንጓዴ ቆብ አድርጓል፡፡ አረንጔዴ ጫማም ተጫምቷል፡፡
ሰውዬውም፤ “እዚህ አገር ያልሞከርኩት ሥራ የለም፡፡ ሆኖም ሊያልፍልኝ አልቻለም፡፡ አሁን ተስፋ ወደመቁረጡ ነኝ፡፡

የመጨረሻ ዕድሌን አንተ በምትሰጠኝ ምክር እሞክራለሁና ምክርህን ለግሰኝ” አለው።
አዋቂውም፤ “ዕጣ ፈንታህ ይታየኛል፡፡ የሚያልፍልህ የተጠራቀመ ሀብት አለና እሱን ካለበት ቦታ ቆፍረህ በማውጣት

ነው፡፡ ያ ሀብት ባለቤቱ በቀላሉ ሳይወጣ ሳይወርድ፣ ሳይደክም ያገኘው በመሆኑ አይጠቀምበትም፡፡ ውድ ውድ የቤት

ዕቃዎች፣ የቅርሳቅርስ ጌጦች፣ አልማዝና ወርቆች እንዲሁም የከበረ ድንጋይ አለው፡፡ አሁን የአንተ አንድ ትልቅ ሥራ

የዚያ ሰው ቤት የት እንዳለ ማወቅ ብቻ ነው፡፡ እንደምንም ቤቱን ካገኘኸው፤ እሱ ብዙ ጊዜውን ውጪ ስለሚያሳልፍ

ልትወስድበት ትችላለህ” አለው፡፡
ሰውዬው ተደስቶ በስንት ጊዜ ካጠራቀመው ገንዘብ አውጥቶ ለአዋቂው ዋጋውን ከፈለው፡፡ አዋቂው በጣም አመስግኖት

“እንግዲህ በደማቅ አረንጔዴ ካፖርትህ፣ በጫማህና በባርሜጣህ አስታውስሃለሁ” አለው፡፡ ባለአረንጓዴ ካፖርቱ ሰው

መንገዱን ቀጠለ፡፡
አዋቂውም ሌሎች ተረኛ ሰዎችን እያነጋገረ፤ ዕጣ ፈንታቸውን መንገሩን ቀጠለ፡፡ አንዷን “ምቀኞች አሉብሽና ሰፈርሽን

ለቀሽ ሌላ ቦታ ኑሪ” ይላታል፡፡ አመስግናው ገንዘብ ከፍላ ትሄዳለች፡፡ አንዱን ደግሞ “አለቃህን ደጅ ካልጠናህ በስተቀር

አይሳካልህም፡፡ ስታየው ላንተ ደግ ይመስልሃል፤ ግን ዕድገትህን ቆልፎ ይዞብሃል” አለው፡፡ አመስግኖና ገንዘብ ከፍሎት

ይሄዳል፡፡ ሌላውን “አዲስ ሸሪክ ያዝ፡፡ እስካሁን አብሮህ ይሠራ የነበረው ሰው ምቀኛህ ነው!” ይለዋል፡፡ ይሄም ገንዘብ

ሰጥቶት አመስግኖት ይሄዳል፡፡ በዚህ ዓይነት ለብዙ ሰዓታት የዕጣ - ፈንታ ትንቢት ሲነግር ይቆያል፡፡
በድንገት አንድ ሰው ወደ አዋቂው እየሮጠ ይመጣል፡፡
“ምነው ምን ሆነህ እንዲህ እያለከለክህ መጣህ?” ሲል አዋቂው ይጠይቃል፡፡
ሲሮጥ የመጣውም ሰውዬ፤
“አዋቂ ሆይ! እኔ የሰፈርህ ሰው ነኝ፡፡ የሰፈራችን ሰዎች ሁሉ ተሰብስበው “ያን አዋቂ ከወዴት እናግኘው?” ሲባባሉ

ሰማሁ፡፡ “ለምን ፈለጋችሁት ብዬ ብጠይቅ፤ “ሌባ ቤቱ ገብቶ ያለ የሌለ ንብረቱን ጥርግርግ አድርጐ ወስዶበት ሄደ”

አሉኝ፡፡ እኔም የሰፈር ሰው ሆኜ ሳልነግርህ ብቀር ጥሩ አይሆንም!” ብዬ ስሮጥ መጣሁ አለው”
አዋቂው እጅግ ተደናግጦ ተነስቶ ወደሠፈሩ በረረ፡፡ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ፡፡
“ምን ዓይነት ሰው ነው የሰረቀኝ? አይታችሁታል ወይ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ሁሉም ዝም ዝም አሉ፡፡ አንድ ትንሽ ልጅ ግን፤
“እኔ አይቸዋለሁ” አለ፡፡
“ምን መሳይ ነው?” ሲል ጠየቀ አዋቂው፡፡
ልጁም፤
“አረንጌዴ ካፖርት፣ አረንጔዴ ባርሜጣ፣ አረንጔዴ ጫማ ያረገ ነው!” አለው፡፡
“አዬ ጉድ! በገዛ ጥይቴ ነዋ የተመታሁት!” ብሎ እያዘነ ወደቤቱ ገባ፡፡
*    *    *
አበሻ “ጠንቋይ ለራሱ አያውቅ!” ይላል፡፡ የሌሎችን እጣ - ፈንታ እየተናገረ የራሱን ዕጣ ፈንታ አያውቅም ለማለት ነው፡፡

አብዛኞች የታዳጊ አገር መንግሥታት የራሳቸው ቤት እየተዘረፈ ስለሌሎች አገሮች ሙስና ሲያወጉ ያመሻሉ፡፡
የብሪቲሽ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጂም ካላግሃን ለፓርላማው ባረጉት ንግግር “ውሸት የዓለምን ግማሽ አዳርሶ ሲጨርስ፤

ዕውነት ገና ቦት - ጫማውን እያጠለቀ ነው!” ያለው ወዶ አደለም፡፡ ቀጣፊው ቢበዛበት ነው፡፡
የምንናገረው የምናወጣው መመሪያ የምንመራበት መራሄ - ፅድቅ፣ የምናቅደው እቅድ፤ የምንነድፈው ስትራቴጂ፤

መሠረታቸው ዕውነት እንጂ ባዶ ተስፋ መሆን የለበትም፡፡ ዕውነት ላይ ስንመረኮዝ አዕምሮአችንም ልቡናችንም ከፍሬ

ጉዳያችን ጋር የተቆራኘ ይሆናል፡፡ የምናፈራው ፍሬ የዚህ ውጤት ነው፡፡
ለመንገዶቻችን ሁሉ አማራጭ እናብጅላቸው፡፡ በህይወት ውስጥ አንድና ቀጥ ያለ መንገድ አይገኝም። በርካታ መንገዶች

ናቸው የመሻሻል አማራጭ የሚሰጡን፡፡
ብልጧን አይጥ ተመልከት፡፡ ኑሮዋን ለአንድ ጉድጓድ ብቻ አትሰጥም” ይላሉ ጣሊያኖች፡፡ አንድም በገዢው ፓርቲ ትይዩ

በተፃራሪ የቆሙ፣ አንድም ወግነው ያሉ ሁለት ቁምነገሮችን ማሰብ አለባቸው፡፡
አሿፊው እረኛ፤ “ተኩላ ተኩላ!” እያለ ሲቀልድ ከርሞ ዕውነተኛው ተኩላ መጥቶ በጐቹን ሲበላ ማን ያግዘው? ዋዛ ፈዛዛ

ልብ አያስገዛ! ሆነ!!”
በአንፃሩ አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤
“እሳት! እሳት” ስትል “ቀጣፊ ነሽ” ሲሏት
ሰፈሩ ነደደ፣ በዐይናቸው እያዩት!”
የሚለውንም አንርሳ፡፡ የሀገር ጉዳይ የዋዛ ፈዛዛ አይደለም፡፡ የሚሉንን እንስማ፡፡ እሳት ከነደደ በኋላ፣ ቤት ፈርሶ ካበቃ

በኋላ አይደለም ህዝባችን አደገ ማለት ያለብን፡፡ ከህዝብ እንመካከር፡፡
ለማሰብ ከሰነፍን፣ መጥፎ ሥራ እንኳ ለመሥራት ከንቱ ከሆን፣ ያንን ለመቀበልም ከፈራን፤ ጥበብና ብስለት የሚባል

በሠፈራችን አይደርስም፡፡
ወጣቶችን በመልካም ስብዕና መቅረፅ የሁሌም ግዴታችን መሆን አለበት፡፡ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ”

ነውና ታሪክን፣ ባህልን፣ ብሔረተኝነትን፣ ጀግንነትን ይዞ ያላደገ ትውልድ የማንነት ድቀት ወይም ቀውስ (Identity

crisis) ውስጥ እንደሚገባ የዓለም ታሪክ በስፋት አሳይቶናል፡፡ የወላጅ የመምህርና የመንግሥት ሦስትዮሽ ድጋፍ

ያስፈልገዋል፡፡
አንድም በግብረ - ገብነት፣ አንድም በትምህርት፣ አንድም በፖለቲካ ስብዕና ብቃት እንዲጠናና እንዲጐለብት ማድረግ

በተለይ ዛሬ ዋና ጉዳይ ነው!
ሽማግሌዎቹ ወጣቶቹን ከእናንተ እንበልጣለን ሲሉ፤ ወጣቶቹ ይሄ ምን ዓይነት የጅል አስተሳሰብ ነው እያሉ

እስከሚመራመሩና እስኪያሰላስሉ፤ ሲያረጁ፤
መላው ቀለጠ፡፡ አገር ከሰረ፡፡
“ሲዋሽ ልክ እንደምሥክር ነው” ይላሉ ሩሲያኖች፡፡ የምንዋሸው ነገር የትውልድ መዳከም ነው፡፡ ዛሬም እናስብበት!
“የምዋሸው ዕውነቴን ለመቆጠብ ብዬ ነው” አለ አሉ አያ ዋሾ፡፡ የረቀቀ ውሸት መዋሸት ካልቻልን በስተቀር ዕውነት

መናገርን መመሪያ ማድረግ ምርጥ ነገር ነው!!

Read 5900 times