Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 10 December 2011 09:01

ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ሜርኩሪ የተባለውን አምላክ ምስል ሰርቶ ገበያ አውጥቶ መሸጥ ይፈልጋል፡፡
ገበያ ወጥቶም፤
“የሚሸጥ ምስል!! የሚሸጥ ድንቅ ምስል! እንዳያመልጣችሁ አሁኑኑ ግዙ!” ይላል
ሆኖም ገዢ አጣ፡፡
ከዚያም ምናልባት ጥቅሙን ባለማወቃቸው ይሆናል ብሎ፤
“ድንቅ የአምላክ ምስል ይሄውላችሁ! ታላቅ ጥቅም ያለው ምስል ይሄውላችሁ፡፡ እድልን ያጐናፅፋችኋል፡፡ እድለኛ ያደርጋችኋል፡፡ ባለፀጋ ያደርጋችኋል፡፡ ባለሀብት ያደርጋችኋል!” አለ፡፡


በመካከል ከገበያተኛው መካከል አንድ ሰው ጠጋ ብሎ፤
“እንደምን ውለሃል ወዳጄ?” ይለዋል፡፡
“ደህና እንደምን ውለሃል” ብሎ አፀፋውን ይመልሳል፡፡
“አንድ ጥያቄ ነበረኝ፡፡ ፈቃድህ ከሆነ መልስልኝ”
“ስለምንድን ነው ጥያቄህ?”
“ስለዚህ ይሸጣል ስላልከው ሜርኩሪ ስለተባለው የአምላክ ምስል”
“መልካም ነው አስረዳሃለሁ፡፡ ጠይቀኝ” አለው፡፡
“ወዳጄ ሆይ ይህ ምስል እውነት አንተ እንዳልከው፤ እድልን የሚያጐናፅፍ ከሆነ፤ እድለኛ የሚያደርግ ከሆነ፣ ባለፀጋ የሚያደርግ ከሆነ፤ ባለሀብት የሚያደርግ ከሆነ፤ አንተ እዚህ ገበያ አውጥተህ እንድትሸጠው ምን አስፈለገህ? ለምን እራስህ አትጠቀምበትም?”
ነጋዴውም፤
“ወዳጄ ሆይ! በእርግጥ ተገቢ ጥያቄ ነው የጠየቅኸኝ፡፡ ይህ ምስል ሀብት እንድታፈራ እንደሚያደርግህ አትጠራጠር፡፡ ነገር ገን ያንን እስኪሰጥህ የራሱን ጊዜ ይወስናል፡፡ እኔ ደሞ ቶሎ መበልፀግ ነው የምፈልገው፡፡ ስለዚህ ባንድ ጊዜ ሸጨው ሀብት ለማፍራት ብዬ ነው” ሲል መለሰ፡፡
***

በአስቸኳይ የመበልፀግ፤ በአስቸኳይ ድልን የመቀዳጀት፡፡ በአስቸኳይ የመለምለም እቅድ በአቋራጭ ህይወትን ለመለወጥ መሯሯጥን እንጂ እውነተኛ ፍሬ የማስገኘት ውጤትን መስጠቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ መንገዶች ሁሉ ውጣ ውረድ አላቸው፡፡ በእርግብ ላባ በወርቅ አልጋ ላይ ለመተኛተ አስቀድሞ ድካምና አመርቂ ትግል ማካሄድን ይጠይቃል፡፡ ፈጣን ነው ያልነው ሁሉ ላይፈጥን ይችላል፡፡ ያቀድነው ሁሉ ወደተግባር ላይለወጥ ይችላል፡፡ ያሰብነው ሁሉ አንጀታችንን ላያርስ ይችላል፡፡ አቋራጮች ሁሉ ዋናው ጐዳና ጋ ላያደርሱን ይችላሉ፡፡
ከሰይጣን ዱቄት የሚበደር ሳይበላው ይሞታል እንደሚባለው በቀናው መንገድ ያልሄድንበት ጉዞ ማረፊያችንን ላያሳምረው እንደሚችል ማስተዋል መልካም ነው፡፡ ጊዜውም ነው፡፡ እኛ የምንሄድበት መንገድ ብቻ ቅዱስ፤ ሌሎች የሚሄዱበት ሁሉ እርኩስ እያልን አንዘልቀውም፡፡ የእኛ መንገድ ብቻ ዲሞክራሲያዊ ሌሎች የሚሄዱበት ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው እያልን ብዙ ወንዝ አንሻገርም፡፡
አበሻ “ምቀኛ አታሳጣኝ” የሚለው፤ ተፎካካሪ የለኝም ብለን አንዘናጋ፣ አንኩራራ ሊል ፈልጐ ነው እንጂ ምቀኛ ፈልጐ ወይም እንደ ንጉሥ ልብነድንግል የጦርነት ያለህ ለማለት አይደለም፡፡ የምንናገረውን በቁጥብነት፤ በጨዋነት፤ ምራቅን በዋጠ ሰው ልሳነ ማቅረብ ይኖርብናል፡፡
The more you say, the more likely you are to say something foolish. powerful people impress by saying less. ብዙ በተናገርክ ቁጥር ጅላጅል ነገር ልትናገር ትችላለህ፡፡ ሃያል ሰዎች ከአንደበታቸው በመቆጠብ ሌሎችን ይማርካሉ፤ እንደማለት ነው፡፡
በሀገራችን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሶሻል ተራምደንባቸዋል ያልናቸው እሴቶች፤ ያሉ እየመሰሉ የሌሉ፣ የሌሉ እየመሰሉም ያሉ በርካታ ናቸው፡፡ ፈተነዋል ያልነው ችግር በሎሚ እንደተፃፈ ፅሁፍ ቆይቶ ብቅ የሚለው በብስለትና በሀቅ ሳይሆን፤ በአቋራጭና በለብ ለብ ከአንገት በላይ ስለምናደርገው ነው፡፡ የቅርብ የቅርቡን ብቻ እያየን ስለሩቁ ባለማሰባችን ውሎ አድሮ የሚያጋጥመን ነገር ይበረክታል፡፡ ማስተዋል ያንሰናል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ካርዲናል ደ ሬዝ እንደፃፈው፤
“የሰዎች ትልቁ የስህተት ምንጭ ስለቅርቡ አደጋ ሲያወሩና ሲፈሩ፤ የሩቁን አደጋ ስለሚዘነጉ ነው” ይላል፡፡
የኑሮ ውድነት አደጋ በዕለት ዕለት ድጐማ የምንቋቋመው ችግር አይደለም፡፡ ብዙ በሶትን የተሸከመ በመሆኑ ማህበራዊ ምስቅልቅልን እንዳያስከትል አበክሮ መከታተልን ይጠይቃል፡፡ ፅናትን ይጠይቃል፡፡ እኔ ጠግቤ ካደርኩ ስለሌሎቹ ምን አገባኝ አለማለትን ይጠይቃል፡፡ Apre moi le deluge እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለማለትን ይጠይቃል፡፡ ገንዘብ መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ለግብር ከፋዩ ምን አደረኩለት ማለትን ይጠይቃል፡፡ ሁሉን መንገድ በአቋራጭ እንዝለቀው ማለት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ችግርን ለመፍታት የቆራጥ መሪዎች ፈጣንነት ብቻ ሳይሆን የህዝብ ተሳትፎን ይፈልጋል፡፡ የአሳታፊነት መርህ ለአገር የሚበጁ ወገኖችን አሰተዋፅኦ ያጐለብታል፡፡ ብቻችንን በመጓዝ መንገዱን ሁሉ አንገፋውም፡፡ ሁሉን በራሳችን ዙሪያ ብቻ ስናጠነጥን አንደኛ የወጣን ሊመስለን ይችላልና መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ብቻውን የሮጠ የሚቀድመው የለ፤ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ የሚባለው ምፀቱ ይሄው ነው!

Read 4011 times