Monday, 10 February 2014 07:08

የውሸት ደዌ በምን ይድናል?

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(1 Vote)

ውሸት በቀላሉ ሲተረጐም ከእውነት ጋር የሚቃረን፤ ያልሆነውን ሆነ፣ ያልታየውን ታየ፣ ያልተሰማውን ተደመጠ ብሎ ማውራት ወይም ማስወራት ነው ብሎ መግለጽ ይቻላል፡፡ ውሸት በቤተሰብ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በማህበራዊ ግንኙነቶች፣ በእምነት ቦታዎች፣ በጤና ተቋማት፣ በግለሰቦች፣ ወዘተ የሚስተዋል ጣጣ ነው፤ አንዳንዴ እንዲያውም በዋሾ ሰዎች ጦስ የሞቀ ትዳር ሊፈርስ፣ የንጹሃን ደም በከንቱ ሊፈስስ ይችላል፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም በውሸት በሽታ ከመለከፋቸው የተነሳ ራሳቸውን ጭምር ሲዋሹ ይስተዋላሉ፤ ለምሳሌ እናቱ በየቤቶቱ እየዞረች እንጀራ በመጋገር፣ ልብስ በማጠብ፣ ወይም ቤት በመጥረግ ያሳደገችው ምስኪን፤ “እናቴ ነፍሳቸውን ይማረውና ሞልቶ የተረፋቸው ሃብታም ነበሩ፤ ምን ዋጋ አለው፤ ደርግ ያንን ሁሉ ሐብት ወርሶ ሜዳ ላይ ጣላቸው፤ በዚሁ ምክንያት ቀሪ ዘመናቸውን በብስጭት አሳልፈው በደም ግፊት ሞቱ፡፡” ብሎ ይዋሸናል፡፡ አድማጮችም የተናገረው እውነት ቢመስለን አይፈረድብንም፤ እንባው እየተናነቀው ነዋ የሚያወራን፡፡
ችግሩ ግን ምን አልባት የዋሾውን ሥረ- መሠረት የሚያውቅ ሰው ከአድማጮች መሃል የተገኘ እንደሆነ ነው፤ እሱም ቢሆን ሊፈጠር የሚችለው ትዝብት ብቻ ሊሆን ወይም “ለምን ትዋሻለህ? እናትህን እኮ አውቃለታለሁ” ብሎ ዋሾውን የሚጠይቅ ካለም “ተመሳስላብህ እንጂ እንኳን እናቴን እኔንም አታውቀኝም” የማይልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የተጠናወተው የውሸት በሽታ ጓደኛውን ሳይሆን ራሱን እንኳ እንዲዋሽ ያስገድደዋልና፡፡
ያጣ የነጣ ኪስ ይዞ በምሳ ሰዓት መንገድ ለመንገድ ሲንከራተት ቆይቶ፤ ወደ ሥራ ቦታው ሲመለስ “አቤት ምሣ! እንዲህ ያለ ሥጋ በህይወቴ በልቼ አላውቅም!” እያለ ራሱን የሚዋሽ ከንቱም ያጋጥማል፡፡ ይህን ሁሉ የሚለፈልፈው ደግሞ ተጠይቆ አይደለም፤ በውስጡ ያለውን የበታችነት ስሜት በውሸት ያካካሰው እየመሰለው ነው፡፡ የውሸት በሽታ ለከት የለውማ! የደፈረሰ ውሃ በሰፈሩ ከጠፋ ሳምንትና ከዚያ በላይ የሆነው ዋሾም “ገላዬን የምታጠበው በጠጅ ነው” ብሎ ለማውራት አይገደውም፡፡ ምክንያቱም የተጠናወተው የውሸት በሽታ ነው፡፡
“እኔ አባታችሁ ምቀኛ በዝቶብኝ፣ አለቃዬ ጠምዶ ይዞኝ፣ የእንትን ብሔር አባል በመሆኔ ወደ ታች እየቀበሩኝ እንጂ እውቀቴኮ ከማንም በላይ ነበር፤ ምን ዋጋ አለው? ደሞዜ ለዘመናት እንደ ካሮት ቁልቁል ሲወርድ የሚኖረው፣ እናንተንም በአግባቡ የማላሳድጋችሁ ለዚህ ነው” የሚለው የውሸት አቁማዳም ብዙ ነው፤ በብሔር ምክንያት ጭቆና የሚደርስበት የለም ብሎ መከራከር ባይቻልም ለግለሰቡ ድህነት ሰበቡ ግን ሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድም በደሞዙ ይጠጣበታል፤ ወይም ደባል ሱሱን ያስታግስበታል፡፡
“ማጨስ ለሳንባም ሆነ ለአጠቃላይ ጤና ጠንቅ ስለሆነ ከዚህ ድርጊት መታቀብ አለባችሁ” ብሎ ከአንድ ሆስፒታል ግቢ ይመክር የነበረ አንድ የጤና ባለሙያ፤ እዚያው አደባባይ ሳለ መሀረብ ሲያወጣ ሁለት ሲጋራዎች ከኪሱ ድንገት ወድቀውበት ምን ያህል እንደተሳቀቀ አስታውሳለሁ፡፡ ከዚህ በላይ ያሳፈረውና እኛንም (በቦታው የነበርነውን ታዳሚዎች) ያስገረመን ግን ድርጊቱን ለማስተባበል የፈጠረው ከንቱ መወላፈት ነው፤ “ይቅርታ ከእግሬ ስር ሲጋራ የጣላችሁ ሰዎች አንሱና ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት ውስጥ ጨምሩት” ሲል ሳቃችንን መቆጣጠር አቅቶን መበተናችን መቸም አይረሳኝም፡፡
በየመዝናኛ ቦታዎች፣ በሥራ ተቋማትና በመሳሰሉት አጋጣሚዎች ከሚያገኛቸው ሴቶች ጋር ሲቀብጥ እየዋለ፣ እያመሸና እያደረ ከሰው ፊት “ባለቤቴኮ ሁለመናዬ ናት፤ እናቴ፣ ትዳሬ፣ ህይወቴ ማለት እሷው ናት፤ እሷ ባትኖር ኖሮ ህይወቴ ምን ያህል ለአደጋ የተጋለጠ ይሆን እንደነበር እግዜር ነው የሚያውቀው” የሚል የውሸት አጋሰስም እጅግ ብዙ ነው፡፡ ከሰው ፊት ሲሆን ስለሚስቱ መቀባጠር ይቀናዋል፤ ዘወር ስትል ግን ምላሱን ያወጣባታል፡፡ ከሰው ፊት ያወደሳት እውነት ስለሚመስላትም የውሸት አቁማዳውን ለመሙላት ምቹ ሁኔታ ይፈጠርለታል፤ የትም የሚልከሰከሰው “ትዳሩን ለማቃናት፣ የሚስቱን ህይወት ለማሻሻል ደፋ ቀና እያለ…” ይመስላታል፡፡
ተንቀሳቃሽ ስልክ ከመጣ በኋላማ  የውሸታሞች ቁጥር በአያሌው ተበራክቷል፡፡ መገናኛ ሆኖ “ቃሊቲ ነኝ” የሚል፤ ከውሽማው ጋር አልቤርጐ ውስጥ እየቀበጠ፣ ድንገት ሚስቱ ስትደውል “ሥራ ቦታ ነኝ፣ ስብሰባ ነኝ፣ ወዘተ…” የሚለውን ቀልማዳ ቤቱ ይቁጠረው፡፡
ከሁሉ የሚገርመኝ ግን የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና የእምነት ሰዎች ውሸት ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ የሃይማኖት ሰዎች ብዙ ተከታዮች አሏቸው፤ ያሉትን ነገር ሁሉ የፈጣሪ ቃል አድርገው የሚያምኑ ብዙ የኔቢጤዎች አሉ፡፡ ኑሮ ከመርግ በላይ ከብዶን መከራችንን እያሳየን እያለ የመንግሥታችን መሪዎች ሞቅ ባላቸው ቀን በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ይሉና “የኢኮኖሚ ግሽበቱን በ20 በመቶ ቀንሰነዋል፤ ዕድገታችንም ባለ ሁለት አኃዝ ደረጃውን እንደጠበቀ በፍጥነት ወደፊት እየገሰገሰ ነው” ሲሉ ያጃጅሉናል፤ ውሸት መሆኑ የሚታወቀው ግን ዓለም አቀፍ ገለልተኛ ድርጅቶች  የዕድገታችንን ልኩን ሲነግሩን ነው፡፡
ሌላው ባለስልጣንም “የሕግ የበላይነት ሰፍኗል፤ የመጻፍ፣ የመናገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግና የእምነት ነፃነት ተከብሯል” ሲል በሬዲዮና ቴሌቪዥን መግለጫ  ይነግረናል፡፡ አባባሉ ምን ያህል ከእውነት ጋር እንደሚጋጭ የምናውቀው ግን እኛው የፈረደብን ዜጐች ነን “ኧረ እባክህ እየዋሸኸን ነው፤ እዚህ ቦታ ያለ ፍርድ የታሰሩ፣ በፀጥታ ኃይል አባላት የተደበደቡ ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ዜጐች አሉ” ሲባልም የሚሰጠው መልስ “ይሄ የፀረ - ልማት ኃይሎች ወሬ ነው” ይለናል፡፡
መንግስትም ሆነ ገዢው ፓርቲ “ዜጐቼን የሚገርፉ፣ የሚዘርፉ፣ የሚገድሉና የሚያንገላቱ ባለሥልጣናት ወዮላቸው” የሚል ጨዋ መሳይ አስተያየት የሚያሰማው በምርጫ ዋዜማ ላይ ነው፤ ከምርጫ በኋላ ለህዝብ ታዛዥ መስሎ የመቅረቡና የውሸት ትህትናው ሁሉ እንደ ጉም በንኖ ይጠፋና “ማን አባቱ ተናግሮኝ” የሚል ጉልቤነቱን ይቀጥልበታል፡፡ የመንግሥት ባለስልጣናትን ውሸት ለመቀነስ ሲባል ምን አለበት “ምርጫ” በየሶስት ወሩ ቢኖር!
አንዳንድ የእምነት ቦታዎች አካባቢ የሚስተዋለው የውሸት ናዳም በእጅጉ ይገርመኛል፤ አንድ ሰባኪ በየአገኘው አጋጣሚ “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌላው ይስጥ፤ ገንዘቤ የኔ ብቻ ነው አትበል” እያለ ሲያስተምር ሚስቱ ሁልጊዜ ታዳምጥ ነበርና ራሷን መጠየቅ ትጀምራለች “ሁለት ልብስ ያለው አንዱን ለሌለው መስጠት አለበት የሚለው የአምላክ ቃል ነው?” ስትልም ባሏን ጠይቃ ታረጋግጣለች፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሰባኪው ባሏ ስብከት ነበረበትና ልብስ መቀየር ፈለገ፤ ግን የፈለገውን ልብስ አጣ፡፡ ባለቤቱን ሲጠይቃት “ትምህርትህን ሰምቼ፤ የጌታ ቃል መሆኑን ተረድቼ ምንም ለሌለው ድሃ ሰጠሁት” አለችው፡፡ ባሏ ምን አለ መሰላችሁ? “እኔ ሌሎች እንዲሰጡ ነው እንጂ የእኔን ስጭ አልኩሽ?” ብሎ አናቷን አላትና ሞተች ይባላል፡፡
ይሄን ትልቅ  ጣጣ ያመጣውም ውሸት ነው፤ ውሸቱ ከመጽሐፉ አይደለም፡፡ ሰባኪው የተጠቀመበት መንገድ እንጂ “የምእመናን ሃብት ሲሆን ለድሃ ይሰጥ፤ ሰባክያን ግን ሃብት ያጋብሱ” የሚል አስተምህሮ የለማ፡፡ የሃይማኖት መጻሕፍት ሁሉ፣ የሚደነግጉት ሃይማኖታዊ ሕግ ሁሉ ለአማንያኑ በጠቅላላ እንጂ ለምእመናን ብቻ አለመሆኑ ግልጽ ይመስለኛል፡፡ አለዚያ እንደ ዓለማዊው ሕግ ሆነ ማለት ነው፣ የፈለጉትን ወንጀል ሰርተው “ያለ መከሰስ መብት አለን” እንደሚሉት ዘመነኞች፡፡
እዚህ ላይ ከአስር ዓመት በፊት በነበርሁበት አካባቢ የተከሰተ አንድ አጋጣሚ መጥቀስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንዲት ክርስቲያን እና አንድ ሙስሊም ተጋብተው ይኖሩ ነበር፤ ልጆች ወልደው ሃብት አፍርተው በፍቅር ሲኖሩ ድንገት አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ተከሰተ፡፡ የሙስሊሙ  ሚስት ክርስቲያኗ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡ መሞቷ አይደለም ችግሩ፤ ይልቁንም “የት ትቀበር?” የሚለው ጉዳይ ነበር በርካታ ሰዎችን ያነጋገረው። ድሮውንም የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችን ጋብቻ ይቃወሙ ለነበሩ ወግ አጥባቂዎች፣ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸውም በመቃብር ምክንያት ነው። ሁለቱም ወገኖች የመቃብር “ዕድል” ነፈጓትና ክርስቲያንም ሆነ ሙስሊም ከማይቀበሩበት ሜዳ ላይ ተቀበረች፡፡
የቀብሯ ሥርዓት ከተፈፀመ  ከተወሰኑ ቀናት በኋላ አንድ አስገራሚ ነገር ከተማዋን ያምሳት ጀመር፤ እሱም “ዕገሊት ስትጮህ ተሰማች፤ በዚህ ቀንም እንደምትነሳ ተናገረች” የሚል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የከተማዋ ነዋሪ ሥራውን እየፈታ ወደ ሟቿ መቃብር መጉረፉን ተያያዘው፤ ይህን የሰማው ፖሊስም ህዝቡን ለመግታት ሲሞክር የባሰ ችግር ተፈጠረ፡፡ የነበረው አማራጭ “ሄጄ አያለሁ፤ አትሄድም፣ የተፈጠረ አዲስ ነገርም የለም” ከማለት ይልቅ አይቶ እንደሚያምን በነፃነት መተው ሆኖ ተገኘ፡፡
በተለይ “በአርባኛው ቀኗ እንደምትነሳ ነግራናለች” የሚሉ ሰዎች ጉዳይ ትልቅ ትኩረት አግኝቶ ነበርና በሞተች በአርባኛው ቀን ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የከተማዋ መንገዶች እጅግ በሚያስደንቅ መልኩ ተጨናነቁ፤ እንኳን ፖሊስ ሌላ ኃይል ቢመጣም የሰውን ማዕበል ሊገታው የሚችል አልነበረም፤ እኔም ከታዳሚው አንዱ ስለነበርሁ በዚያ የህዝብ ማዕበል እየተገፋሁ ከአንድ ሰዓት የትርምስ፣ የግፊያና ወከባ ጉዞ በኋላ ከቦታው ደረስሁ፤ ግን ያን ያህል ከተማዋን እንደ ገብስ ያመሳት ወሬ ውሸት ነበር፡፡
በነበረው ትርምስም የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፡፡ በዚህ የተነሳ እኔ ብቻ ሳልሆን በቦታው የነበረው ህዝብ ሁሉ መጀመሪያ “ስትጮህ ሰማኋት” ያለውን ሰው በቦታው ቢያገኘው፣ እርግጠኛ ነኝ የዘለዓለም ቤቱን ከሟቿ መቃብር ጋር ያደርገው ነበር፡፡
የውሸት ደዌ በጠበል፣ በህክምና፣ በአባይ ጠንቋይ፤ ወይም በቃልቻ የሚድን አይደለም፡፡ በማህበረሰቡ ንቃት፣ ድፍረትና ውሸታሙን “እረፍ፣ ከዚህ ድርጊትህ ታረም!” ባይነት እንጂ፡፡ የውሸት ደዌ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከማህበረሰባች ውስጥ እንዲጠፋ ከፈለግን ለእውነት ዋጋ መስጠት መጀመር አለብን፡፡

Read 3134 times