Monday, 10 February 2014 07:48

የቫለንታይን ቀን

Written by  ደራሲ Cecelia Ahern ውርስ ትርጉም - ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(10 votes)

        ሉሲ ጭንቅላቷን መስተዋቱ መስኮት ላይ አስደግፋ ያሸለበች ትመስላለች፡፡ ባቡሩ በተንገራገጨ ቁጥር   ከመስኮቱ ጋር ትላጋለች። በተደጋጋሚ ከተላጋች በኋላ ዓይኗን ገልጣ ዙሪያዋን መቃኘት ያዘች፡፡ ባቡሩን የሞሉት ጥንዶች ናቸው፤ፍቅረኛሞች፡፡ ዓይኗን መልሳ ጨፈነች- ጥንዶቹን  ላለማየት፡፡
በየመሃሉ ባቡሩ ያቃስታል፡፡ የድካም ድምጽ፣ የመታከት እንጉርጉሮ ያስተጋባል፡፡ የእሷና የባቡሩ ህይወት በሆነ መንገድ የሚመሳሰል ሆኖ ተሰማት፡፡ ባቡሩ ቀኑን ሙሉ በአንድ መስመር ሲጓዝ ይውላል። በአንድ አቅጣጫ ሲመላለስ፡፡ በራሱ ፍጥነት የመጓዝ ነፃነቱን ተነፍጓል፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ይከንፍና በርዶ ይቆማል፡፡ እንደገና ደግሞ ይነሳል፡፡ ጉዞ ይጀምራል፡፡ መቆም … መነሳት፡፡ የሚፈቀድለት ይሄ ብቻ ነው፡፡
  ባቡሩ ሲንገራገጭ ሉሲ ዓይኗን ገለጠች፡፡ አንድ ወንድና ሴት ከባቡሩ ለመውረድ ከመቀመጫቸው ሲነሱ ተመለከተች፡፡ እጅ ለእጅ ተያይዘዋል። ወንድየው ክንዶቹን ፍቅረኛው ትከሻ ላይ አድርጐ ግንባሯን ሳማት፡፡ እሷም እጇን ወገቡ ላይ ጠምጥማ፣ ጣቷን የጂንስ ሱሪው የኋላ ኪስ ውስጥ እየከተተች  ጭንቅላቷን ትከሻው ላይ አሳረፈች፡፡ በርቀት ሲታዩ በአንድ ላይ የተሰፉ ይመስላሉ፡፡ ለእነሱ ብቻ ጊዜ መቁጠሩን አቁሟል፡፡
 ከእነሱ አጠገብ አንድ ዘናጭ ወጣት ቆሟል - በእጁ ቀይ አበቦች የያዘ፡፡ እየተቁነጠነጠ አስሬ ሰዓቱን ይመለከታል፡፡ ይሄኔ አንዲት ወጣት  ቆማ እየጠበቀችው እንደሆነ ሉሲ አሰበች፡፡ እሷም እንደሱ አስሬ ሰዓቷን እያየች፡፡
“ሂድ” አለችው፤ ባቡሩን - ጮክ ብላ፣ ግን ድምፅ ሳይሰማ፡፡ ሉሲ ተጨማሪ የፍቅር ትዕይንቶችን ማሰብም ሆነ ማየት አልፈለገችም፡፡
ባቡሩ ሃሣቧን የተረዳ ይመስል በሩ በቀስታ ተንሻትቶ ተዘጋና መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ቢያንስ ለጥቂት ደቂቃዎች እንደማይቆም አውቆ በደስታ ይከንፍ ጀመር፡፡ ሉሲ የውጭውን ትዕይንት ስትመለከት በፈገግታ ተሞላች፡፡ አረንጔዴው፣ አመድማው፣ ገብስማው----- ሁሉም ትዕይንት ከባቡሩ ፍጥነት ጋር ብዥ እያለ ያልፋል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ባቡሩ እንጉርጉሮ አሰማ፡፡ ማልቀሱ ነበር - ለምን በረድኩ፣ ለምን ተገታሁ ብሎ፡፡ እየቆሙ መነሳቱ የታከተው ይመስላል፡፡ በሩ በዝግታ፣ በድካም ስሜት ተንሻትቶ ተከፈተ፡፡ ሌሎች ጥንዶች ደሞ ተሳፈሩ፡፡
ሰውየው ከሉሲ አጠገብ፣ ሴቲቱ ፊት ለፊቱ  ተቀመጠች፡፡ በዕድሜ የሉሲ እኩያ ትሆናለች። ከፍቅረኛዋ በቀር ሌላ ነገር አታይም፡፡ ዓይኗቿ እንደክዋክብት ያበራሉ፡፡ ፍቅረኛዋ ጠጋ ብሎ ከንፈሯ ላይ ሳማትና ጠቀስ አደረጋት፡፡ ይሄኔ ፊቷ የበለጠ ፈካ፡፡ በስር በኩል ጉልበታቸው ተነካክቷል። በላይ እየተሳሳቁ ይደባበሳሉ፡፡ ሉሲ ዓይኗን ጨፍና  ሃሳቧ ውስጥ ተጠቀለለች፡፡
ድንገት አይኗን ስትገልጥ መውረጃዋ ደርሷል። ገና ባቡሩ ፍጥነቱን ሳያበርድ ከመቀመጫዋ ዘላ ተነሳች። “አመሰግናለሁ፤ የነገ ሰው ይበለን” አለች ለባቡሩ - በለሆሳስ፡፡ ከየካቲቱ የሚጋረፍ ቀዝቃዛ አየር ራሷን ለመከላከል ካፖርቷን እስከላይ ድረስ እየቆለፈች ከባቡሩ ወረደች፡፡ እንደ ጩቤ የሚዋጋው ብርድ ነበር የተቀበላት፡፡ ሁለት እጆቿን ካፖርት ኪሶቿ ውስጥ ከትታ  መገስገሷን  ቀጠለች - ወደ ሥራዋ። ሉሲ ዱብሊን ከተማ እምብርት ላይ በሚገኝ አንድ የፈረንሳይ ሬስቶራንት ውስጥ አስተናጋጅ ናት።  
ቀኑ ፌብሯሪ 14 ነው፤ ቫለንታይንስ ዴይ!
በዚህ ምሽት የእነሉሲ ሬስቶራንት ገበያው እንደ ጉድ ይደራል፡፡ እንግዶች ጠረጴዛ “ሪሰርቭ” የሚያደርጉት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ አስተናጋጆች “የፍቅረኞች ቀን” በመጣ ቁጥር ማታ የሚመደበው ማነው በሚለው ጉዳይ መጨቃጨቃቸው የማይቀር ነው፡፡ ሁሉም ምሽቱን ከፍቅረኛው ጋር ማሳለፍ ይፈልጋል፡፡ እዚህ ውስጥ የሌለችበት ሉሲ ብቻ ናት፡፡ ቫለንታይንስ ዴይ እሷን አይመለከታትም። ለዓመላቸው ያህል ይጨቃጨቃሉ እንጂ በቫለንታይን ምሽት ሥራውን የሚሸፍነው ማን እንደሆነ አሳምረው ያውቃሉ፡፡ ለነገሩ ሉሲ ሁሌም የማታ ምድብ ናት፡፡ በተለይ የፍቅረኞች ቀን የሚከበርበት ምሽት ሲሆን ዋና ባለዕዳ እሷ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ ግን ወድዳና ፈቅዳ ነው፡፡
ሉሲ በሚቀጥለው ወር 31ኛ ዓመቷን ትይዛለች። ሆኖም ፍቅረኛ ኖሯት አያውቅም፡፡ እንደዚያች ባቡሩ ውስጥ እንዳየቻት ሴት ግንባሯ ላይ የሚስማት ሰው የለም፡፡ የአበባ ስጦታ ተበርክቶላት አያውቅም። ከንፈሯን ለመሳምም አልታደለችም፡፡ ቀጠሮ እንዳያረፍድባት የሚጨነቅላት ወንድ አላገኘችም። ዓይኑን ትክ ብላ ስታየው ቆይታ፣ለዘላለም ከእሱ ጋር ለመኖርና የእሱ ብቻ ለመሆን የተመኘችው ሰው የለም፡፡ የወደፊት ልጇን ስም እንድታስብ ያደረጋት ወንድ አልገጠማትም፡፡ ሉሲ አፍቅራም ተፈቅራም አታውቅም፡፡
ስለ ፍቅር አታውቅም ማለት ግን አይደለም። አሳምራ ታውቃለች፡፡ የፍቅረኞችን ታሪክ በመጽሃፍት አንብባለች፡፡ በባቡር ስትመላለስ ብዙ ፍቅረኞችን አይታለች፡፡ ጓደኞቿ ስለፍቅረኞቻቸው ሲያወሩም ሰምታለች፡፡ ከሚፋቀሩ ወላጆች ጋር ነው ያደገችው፡፡ በፊት በፊት በፍቅር ላይ ያላት እምነት ፅኑ ነበር፡፡ ዕድሜዋ ሲሄድና እያንዳንዱ ዓመት ለእሷ የተጣፈላትን የነፍስ ጓደኛ ሲነፍጋት እምነቷ ተሸረሸረ፡፡ ፍቅር ለሁሉም የተሰጠ ጸጋ ሳይሆን ዕድለኞች ብቻ የሚያጣጥሙት ነው ብላ ተፈጠመች፡፡ ብቸኝነትን ጓደኛዋ አደረገች፡፡
የፖስት ካርድ መሸጫ መደብሮች በወንዶችና በሴቶች ተጨናንቀዋል፡፡ ሁሉም ለፍቅረኛው ስጦታ እየሸመተ ወደቀጠሮው ሥፍራ ለመድረስ ይጣደፋል፡፡ ይሄ ሁሉ ግርግር ግን ለሉሲ ምኗም አይደለም፡፡   በየሱቆቹ መስኮቶች ላይ የተሰቀሉት ቀያይ የልብ ቅርጾች /ምስሎች/ የመንገደኛን ቀልብ ይስባሉ፡፡ ሉሲን ግን አልሳቧትም ፤ ሆድ አስባሷት እንጂ፡፡ እግሯን እየጎተተች ነው ሥራ ቦታዋ የደረሰችው፡፡
ሬስቶራንቱ በር ላይ የቫላንታይን ቀን ልዩ ሜኑ (የምግብ ዝርዝር) ተሰቅሏል፡፡ የምግብ ቤቱ ዙሪያ ገባ  በትላልቅ  ቀያይ የፍቅር  “ልቦች” አሸብርቋል፡፡
12፡30 ላይ የመጀመርያዎቹ የምሽቱ ጥንዶች የሬስቶራንቱን በር ከፍተው ገቡ፡፡ ሉሲ ክፍሉን ብሩህ በሚያደርግ ፈገግታ ተቀበለቻቸው፡፡
“ጤና ይስጥልን፤ እንኳን ደህና መጣችሁ” አለች ደስተኛ ለመምሰል እየሞከረች፡፡
“እናመሰግናለን፤ ለሁለት ሰው ቦታ ትሰጭናለሽ?” ሰውየው ኦናውን ሬስቶራንት እየቃኘ በትህትና ጠየቃት፡፡
“ቀድማችሁ አሲዛችኋል?” ፈገግታ ሳይለያት ጠየቀች፡፡
“አዎ፤ ማክ ግላድዌል በሚል ለ 12፡30 አሲዘን ነበር---”
ሉሲ የእንግዶችን ስም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ እየገለጠች ካየች በኋላ     “ትክክል ነው ተይዞላችኋል፤ ካፖርታችሁን ልቀበል----?”
ካፖርታቸውን ተቀብላ ፊት ፊት እየመራች ወደተያዘላቸው ጠረጴዛ ወስዳ አስቀመጠቻቸው። ከዚያም የምግብ መዘርዝሩን (ሜኑ) ለሁለቱም ሰጠቻቸው፡፡ ሁልጊዜም እንዲህ ናት፡፡ ሰዎች በፍቅር እንዲደላቸው ታስተናግዳለች፡፡ እሷ ግን የፍቅር አካል ሆና አታውቅም፡፡  
አሁንም የሬስቶራንቱ በር ተከፈተና ተዘጋ። ሌሎች ጥንዶች ናቸው፡፡ ሁለተኛው የምሽቱ እንግዶች፡፡  
“ጤና ይስጥልኝ፤ እንኳን ደህና መጣችሁ” አለች በተለመደው የይመስል ፈገግታዋ ታጅባ፡፡
“እናመሰግናለን፤ ለሁለት ሰው ቦታ ይኖርሻል?” አለ ሰውየው፤በእንግዶች ያልተያዙትን በርካታ ጠረጴዛዎች እየቃኘ፡፡
“ቀድማችሁ ቦታ ይዛችኋል ጌታዬ?” ስትል ጠየቀች፤ ጥርሷን ነክሳ ፈገግ እያለች፡፡
“አዎ ይዘናል፤ ዴቪድ ሳንድ  በሚል ስም” አለ - የደንበኞች ስም ዝርዝር የያዘውን መዝገብ ቃኘት እያደረገ፡፡ ሉሲ ዝርዝሩን አይታ የሰውየው ስም ላይ ምልክት ካደረገች በኋላ፤ የተለመደውን ጥያቄ አቀረበች፡፡
“ካፖርታችሁን ልቀበላችሁ?”
ካፖርታቸውን ተቀብላ ፊት ፊት እየመራች ወደተያዘላቸው መቀመጫ ወሰደቻቸው፡፡ ከዚያም  የምግብ መዘርዝሩን (ሜኑ) አቀበለቻቸው፡፡ ቀኑን ሙሉ ተመሳሳይ ስራ! ሁልቀን አታካች ድግግሞሽ፡፡
እንደገና የሬስቶራንቱ በር ተከፍቶ ተዘጋ፡፡
“ጤና ይስጥልኝ” አለች ሉሲ- በፈገግታ!
መቆም-- ከዚያ መነሳት፡፡ እንደገና መቆም--- እንደገና መነሳት፡፡ በራሷ ፍጥነት እንድትጓዝ ወይም መስመሯን እንድትቀይር ጨርሶ አይፈቅድላትም፡፡ ባቡሩ ትዝ አላት፡፡
“እባክሽ ለሁለት ሰው ቦታ” አለች ሴቲቷ፡፡ ሉሲ ጉሮሮዋን ያነቃት መሰለች፡፡
የስም ዝርዝሩን መዝገብ ስትገልጥ ጣቶቿ ይንቀጠቀጡ ነበር፡፡
“ለሁለት ሰው ቦታ--” የሚሉትን ቃላትን አትወዳቸውም፤ ሁሌም ያሳምሟታል፡፡
“ቦታ ይዛችኋል?” ጠየቀቻቸው፤ እንደምንም ፈገግ ለማለት እየሞከረች፡፡
ሴቲቱ ቀድመው መያዛቸውን ነገረቻት። መዝገቡ ላይ ስማቸው መኖሩን አረጋገጠች፡፡ ካፖርታቸውን ተቀብላ መቀመጫቸውን ካሳየቻቸው በኋላ ሜኑውን  አቀበለቻቸው፡፡
እንግዳ መቀበያው ዴስክ ላይ ቆማ በሃሳብ ተውጣለች - ሉሲ፡፡ ከሚያፈቅሩት ጋ የቫለንታይን ቀን ምሽትን ማሳለፍ ምን  ስሜት ይፈጥር ይሆን? ከፍቅረኛ ጋር እንዲህ እራት መብላትስ? ማውራት--መሳቅና መላፋትስ? ---- ሉሲ እኒህን ሁሉ ስሜቶች አታውቃቸውም፡፡
ዴስኩ ላይ እንደቆመች ሬስቶራንቱ ቃኘት አደረገች፡፡ ከአንድ ጠረጴዛ በቀር ሁሉም በጥንዶች ተይዟል፡፡ ከ16 እስከ 60 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ፍቅረኞች ቤቱን ሞልተውታል፡፡ ብዙ ዓይነት ጥንዶች ያሉትን ያህል ብዙ ዓይነት ፍቅርም ይታያል -  አዲስ ፍቅር፣ ያረጀ ፍቅር፣ የከረመ ፍቅር፣ የስርቆሽ ፍቅር፣ የጥድፊያ ፍቅር፣ የይምሰል ፍቅር ወዘተ-- አንዳንዶቹ ጥንዶች በዝምታ ተውጠዋል፡፡ ሌሎች ሳይነካኩ መቀመጥ የሚችሉ አይመስሉም። አንዳንዶች ኮስተር ያለ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ ከጣራ በላይ የሚያስካኩም አሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ይላቀሳሉ፡፡ ጠብ ያማራቸውም አልጠፉም፡፡
  ይሄ ሁሉ ፍቅር በሞላበት ክፍል ውስጥ ሉሲ ግን ተደብታለች፡፡ በእዚሁ ሁሉ ሰው መሃል ሆና ብቻዋን ናት፡፡ በዚያ ላይ ሥራው አድክሟታል። እግሯና ወገቧ ደቋል፡፡ ዓይኗ ሊከደን ምንም አልቀረውም፡፡ ከዚህ በኋላ “ለሁለት ሰው ቦታ ይኖርሻል?” የሚል ጥያቄ ባትሰማ ደስታዋ ነው፡፡ ጥንዶች ማየት አንገሽግሿታል፡፡ በሩ ሲከፈት ሰምታ ቀና አለች፡፡ አብሯት ያመሸው የስራ ባልደረባዋ ዘሎ ወጣና፤
“ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ፤ እንኳን ደህና መጡ” በማለት ተቀበለ፡፡
“ጤና ይስጥልኝ፤ ለአንድ ሰው ቦታ ይኖራችኋል?”
ይሄን ነበር ሉሲ ምሽቱን ሙሉ ለመስማት የናፈቀችው፡፡ ከድቅድቅ ብቸኝነት መንጥቆ የሚያወጣትን ይሄን እንግዳ ድምፅ፡፡ አሁን ከአንገቷ ቀና አለች፡፡ ዓይኖቿ በደስታ እንባ ተሞሉ፡፡ በ30ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ ያለ ሰው እንደሆነ ገምታለች፡፡
 እንግዳው በጨረፍታ አየት አደረጋትና ቁራሽ ፈገግታ ወረወረላት፡፡ የእጆቹን መዳፎች እርስ በእርስ እያፋጨ ሬስቶራንቱን ቃኘ፡፡ የሉሲ ልብ በደስታ ጮቤ ረገጠ፡፡ ወጣት ነው፡፡ ጣቱ ላይ ቀለበት አላሰረም፡፡ በቫለንታይን ምሽት ፍቅረኛ ሳይዝ  መምጣቱ ያሳፈረው አይመስልም፡፡
“ለአንድ ሰው ቦታ ይኖራችኋል?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ ደግማ ብትሰማው ተመኘች፡፡
“አዝናለሁ ጌታዬ፤ ቀድመው ካላስያዙ ልናስተናግድዎት አንችልም” የስራ ባልደረባዋ ምላሽ ነበር፡፡
“ምን?” ሉሲ ከቆመችበት ዴስክ ዘላ ወጥታ ባልደረባዋ ላይ አፈጠጠችበት፡፡
በልቧ ውስጥ ስትደንስበት የነበረው የሙዚቃ ሲዲ ተጫጭሮ የቆመ  መሰላት፡፡
“ሉሲ--” አላት ባልደረባዋ - ከእንግዳው ዞር ለማለት እየሞከረ፡፡  
“ምን እያልሽ ነው?” ጠየቃት ግራ በተጋባ ስሜት፡፡
“አንድ ያልተያዘ ጠረጴዛ አለ እኮ” አለችው መስኮቱ አጠገብ ወዳለው ቦታ እያመለከተችው፡፡
 “እሱ እኮ የሁለት ሰው መቀመጫ ነው፤ እንዴት አንድ ሰው ይቀመጥበታል?” አለ በቁጣ
“እስቲ የማይቀመጥበትን ምክንያት ንገረኝ? እንግዳ አይደለም እንዴ!” ሉሲ ሽንጧን ገትራ መከራከር ያዘች፡፡  
“የበለጠ ገንዘብ የምናገኘው እኮ ጥንዶች ሲቀመጡበት ነው” ባልደረባዋ በቁጣ እንደማይሆን ገብቶታል፡፡
“ገንዘብ? ገንዘብ ነው ያልከው?” ተሳለቀችበት፡፡
  ባልደረባዋ አፍሮ ዝም አለ፡፡ ወዲያው የሬስቶራንቱ በር ተከፈተና የረፈደባቸው ጥንዶች እየተሳሳቁ ገቡ፡፡ የሉሲ ባልደረባ ሁለመናው ጥንዶቹ ላይ አነጣጠረ፡፡ ሆኖም ሉሲ ቀደመችው፡፡
“ጤና ይስጥልን---እንኳን ደህና መጣችሁ” አለች ቀልጠፍ ብላ፡፡
“እባክሽ ለሁለት ሰው ቦታ ፈልጊልን?”
ሲያሰለቻት ያመሸውንና ትክት ያላትን  ነገር ነው የሰማችው፡፡
“አዝናለሁ---ለጥቂት ተያዘ” አለቻቸው በትህትና፡፡ ዞር ብላ ባልደረባዋን ተመለከተች። ድፍረት አጣ እንጂ የሆነ ነገር መናገር እንደፈለገ ያስታውቃል፡፡ ጥንዶቹ  ሬስቶራንቱን ለመጨረሻ ጊዜ ከቃኙ በኋላ ተያይዘው ወጡ - እየተሳሳቁ፡፡ ሉሲ በድል አድራጊነት ስሜት ተሞልታ ብቸኛውን እንግዳ እያየች
 “ካፖርትህን ልቀበልህ?” አለችው፤ ልብ የሚያሞቅ ፈገግታ እየፈነጠቀች፡፡
ከካፖርቱ በፊት ብርድ ያቀዘቀዘውን እጁን እያቀበላት “አመሰግንሻለሁ!” አላት፡፡
ልቧ በደስታ ሞቀ፡፡ ካፖርቱን ተቀብላ በሬስቶራንቱ ውስጥ ወደ ቀረው ብቸኛ ጠረጴዛ እየመራች ወስዳ በክብር አስቀመጠችው፡፡
 ወጣቱ እንግዳ ብቻውን ገብቶ ሁለት ሆኖ ወጣ።
ሉሲም  በቫለንታይን ቀን ከብቸኝነት ጋር ተፋታች፡፡  

Read 4478 times