Saturday, 15 February 2014 13:04

“ዘርዓ ያዕቆብ አውሮፓዊ ነው” ማን አለ?

Written by  ሰሎሞን አበበ ቸኮል (saache43@yahoo.com)
Rate this item
(2 votes)

           ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነበር ወይ? ብዬ በመጠየቅ ያቀረብሁተን ጽሑፍ ለመቃወም የታሰበበት ጽሑፍ ባለፈው ሳምንት በደረጃ ኅብስቱ ቀርቧል፡፡ ጸሐፊው በእርግጥ በስም ተቅሰው እኔን እንደሚመለከት ባይገልፁልኝም በቅርቡ የጻፍኩት እኔው ብቻ በመሆኔ የአቶ ደረጄም ጽሑፍ ይህንኑ ጽሑፌን እንደሚመለከት ለመገመት አያዳግትም፡፡
ደረጀ ኅብስቱ ፮ ድረስ የተቆጠሩ መከራከሪያ ሐሳቦችን አቅርበዋል… ነገር ግን እንዳሉ ለዚህ ባበቃቸው የእኔ ጽሑፍ ላይ ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ መኖሩን ለመጠየቅ ያበቃኝን ሐሳብ በቀጥታ ያገኟቸው አልመሰለኝም… ስድስቱም ነጥቦቻቸው ዘርዓያዕቆብ አበሻ አይደለም፤ ፈረንጅ (አውሮፓዊ፣ ሮማዊ) እንጂ” ለሚሉ ሰዎች የቀረቡ መሟገቻ ሐሳቦች ናቸው፤ እነዚያውም አቅም የሌላቸው፡፡ እኔ ደግ ይህን አላልኩም እስኪ የደረጄን ፮ ነጥቦች እንያቸው፡፡
፩/ ዘርዓ ያዕቆብ ተብሎ በተጻፈው መጽሐፍ፣ ይኼው ገጸ ባህርይ “ዳዊት ለ፫ ወር፣ ቅኔ ለ፬ ዓመት፣ መጽሐፍ ለ፲ዓመት” ጠቅላላ ለ፲፬ ዓመት በአብነት ትምሕርት ከውሻና ከችግጋር ጋር እየታገለ … መከራውን እየታገሰ የሚማረው ኢትዮጵያዊ ካልሆነ በቀር ሌላ ማንም እንዳልሆነ ታሪካችን ይመሰክራል” ይኼን መከራ ታግሶ መማር የሚችል “አውሮፓዊ ከተገኘ እሰየው ነው፡፡”
፪/ ዘሩን ከካህናት፣ ከደኃ ወገን የሚቆጥር ሮማዊ ይገኛል ወይ? ከደኃ ቤተሰብ መወለዱም ለኢትዮጵያዊ እንጂ ለአውሮፓዊ አይሆንም…
፫/ “የሐሳቡን አደረጃጀትና አቀራረብ ከአውሮፓዊያን በማመሳሰላቸው ነው” ዘርዓ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊ አይደለም የሚሉት፤
፬/ ዘርዓ ያዕቆብ አውሮፓዊ ቢሆን ኖሮ ሸሽቱ ወደ ዋሻ ሳይሆን ወደ ቀይ ባህር በኾነ ነበር፡፡  
፭/ ዳዊቱን አንግቦ መሰደዱ ራሱ ፍጹም ኢትዮጵያዊነቱን ይመሰክራል፡፡
፮/ በመጽሐፉ እንደቀረበው ከሽሽት በኋላ ማለትም የአፄ ሱስንዮስ ዘመነ መንግስት አክትሞ የአፄ ፋሲል ዘመን ላይ የተጻፈ መምሰሉንም በመያዝ፣ በዚህ በአፄ ፋሲል ዘመን ደግም ፈረንጅ ኹሉ ተባርሮ ነበር፡፡ “ዘርዓ ያዕቆብ ፈረንጅ ከሆነ ታዲያ በአፄ ፋሲል ዘመን እንዴት በእንፍራዝ ውስጥ ሊኖር ቻለ?”
እያንዳንዳቸው ዘርዓ ያዕቆብ እንዴትም ሆኖ አውሮፓዊ (ፈረንጅ) ሊኾን አይቻልም፤ አይደለም፣ ኢትዮጵያዊ እንጂ የሚሉ ናቸው፡፡ ማነው ፈረንጅ ያለው? “ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነበረ ወይ?” ብሎ መጠየቅ፣ “ዘርዓ ያዕቆብ ፈረንጅ ነው፣” ማለትን ያመላክታል? በጭራሽ፣ ያልተባለውን በመያዝ ነው ደረጄ የደከሙት፡፡
እኔ ያልኩት፣ “ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል በእውን ዓለም በምድር ላይ የኖረ ሰው አልነበረም” ነው። የዘርዓ ያዕቆብ መጽሐፍም ዘርዓ ያዕቆብ የተባለ ፈላስፋ ገጸ ባሕርይ ተፈጥሮ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በአፄ ሱስንዮስና ፋሲል ዘመን የተነሳ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ተደርጎ የቀረበበት ነው፡፡ ምናልባትም ጸሐፊው ልብ ወለድ ልጻፍ ብሎ የጻፈው መኾን አለመሆኑ ሊጠየቅ ቢችልም፣ ያልተዋጣለት ልብወለድ፣ የልብ ወለድነት መጠንን ያልያዘ ልብወለድ ሠራ ነው። … ይህ ነበር የኔ ሀሳብ፡፡ ስለዚህ ከ ፩ - ፮ ያሉት በሙሉ፣ ምንም እንኳን በዚያም ቢሆን ምንም ያህል ውጤት የማያስገኙላቸው ቢሆኑም፣ ዘርዓ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ እንጂ ፈረንጅ ሊባል አይገባውም ለማለት የቀረቡ ናቸውና ከኔ ጋር የሚገናኙ አይደሉም፡፡ ነገር ግን አሁንም የጸሐሀፊውንና የአንባቢውን ግርታ ለማስወገድ ሲባል ተራ በተራ እያነሳሁ እነዚህኑም ቢኾን እመለከታቸዋለሁ፡፡
አንድ፡- “ዳዊት ለ ፫ ወር፣ ቅኔ ለ፬ ዓመት፣ የመጻሕፍት ትርጉም ለ ፲ ዓመት…” ሊኖር የሚችለውን መከራ ታግሶ ለመማር የሚችል አውሮፓዊ ሊኖር እንደማይችል ያስደመደመው ይህ ዘርዓ ያዕቆብ ራሱ ስለራሱ የገለጸው ቆጠራ ነው፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ የዚህ አገላለጽ ዘይቤ በራሱ ይህ ሰው የአብነት ት/ቤት ደርሶ የማያውቅ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በት/ቤቱ ያለፉ ሁሉ ሊመሰክሩት የሚችሉት ነው፡፡
የ፫ወር የዳዊት ትምህርቱን ከ ፬ ዓመቱ ግዕዝና ከ፲ ዓመቱ መጻሕፍት ጋር በቅደም ተከተል ማሰለፉ ብቻ ሳይሆን በነዚህ መስመር ያለፈ ሰው አገላለጽ እንዳልሆነም ሊታወቅ ይችላል፡፡ ሊባል የተፈለገው በትክክለኛ የቤቱ ቃሎች አልተገለጹም። “ዳዊት ደገምሁ፣ ይህን ያህል ጊዜ ዘለቅሁት ወይም ወጣሁት፣ ነው የሚባለው፡፡ ፀሐፊው በዚያ ቢያልፍ ኖሮ አፉም፣ መጻፊያውም እሺ አይለውም ነበር “ዳዊት ተማርሁ” ለማለት፡፡
ይበልጥ እንበርብር ካልን እኮ ዳዊት የደገሙበት ወሮችንም የመቁጠር ልማድም የለም  ት/ቤቶቹንም ሲጠሩዋቸው ይለያሉ፡፡
“በቅኔ ቤት፣ በመጻሕፍት ቤት …” እያሉ ይናገሯቸው እንደሁ እንጂ እንዲያ “ግእዝ ፣ ቅኔ በመማር” ፣“የመጻሕፍት ትርጓሜ በመማር” ተብሎ መገለጹ ስህተት ነው ባይባልም በነሱ ዘንድ ያልተለመደ፣ በሩቅ ያለ የኛ ብጤው የሚገልጽበት አገላለጥ ነው፡፡ ቅኔም “ተማርኩ” አይባልም፤ “ቆጠርኩ፣ ቀጸልኩ፣ ዘረፍኩ፣ አደላደልኩ፣ አስነገርኩ፣…” ዓይነቶቹን እንጂ፡፡ “ተማርኩ” ቀድሞ ነገር ባፋቸውም አይገባም፡፡
ቅኔውንና መጻሕፍቱን ከመቁጠሩ እስከ ከፍተኛው ደረጃ ወይም እስከምን ድረስ እንደተጓዘበት ባይገልጽልንም ከማን ዘንድ እንደተማራቸው ሳያስቀድም መቅረቱም አጅሬ ለቤቱ ባዕድ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ይህ ለነሱ መማር ዋነኛው አስረጋጩ ነገር ነው፡፡ ባህላቸውና ልማዳቸውም ነው፡፡
የመጻሕፍት መምህርነቱን የሚናገረው ገጸ-ባህርይ ዘርዓ ያዕቆብ በየትኛው ዘርፍ እንደሆነ አይነግረንም፡፡ ዝም ብሎ የመጻሕፍት መምህር አይባልም፡፡ መጋቤ ብሉይ? መጋቤ ሀዲስ? ወይስ የሊቃውንቱና የመነኮሳቱ? ከነዚህም ሌላ ሕግጋት ምናልባትም የቁጥር ትምህርት የሚባሉ አሉ። በየትኛው ነው ያ ሰው ጉባኤ የዘረጋው? በ፬ቱም የተመሰከረለት እኮ “፬ዓይና” ይባላል፡፡ ይህን የመሰለ ማዕረጉን ትቶ ይጽፋል? ከ፬ ዓይና ውጭ ነው ብንል “መጋቤ ብሉይ፣ መጋቤ ሀዲስ” ይባላል፡፡ ይኽ ጸሐፊም የራሱን ጉባኤ የዘረጋ ከሆነ ከነዚህ አንዱን በሆነ ነበር፡፡ ከሆነም ደግሞ በጻፈው ነበር፡፡ ግና ልብወለድ ነውና ይሄ ይሄ ቀዳዳ ሁሉ ይገኝበታል፡፡
ደግሞስ በ፲ ዓመት የተወሰነው የመጻሕግት ተምህርት የትኛው ነው? ሙሉው እኮ በትንሹ ፳ዓመት ነው የሚፈጀው! ቢያንስ ሁለቱን ያህል ይጨርስበት ይሆናል፡፡ ግን ይህን ለማወቅ ስላልቻለ እንዳለ “መጽሐፍ” ብሎ ዘጋው፡፡ ባጠቃላይ ይህ የመጀመሪያው ነጥብ ይበልጥ ዘርዓ ያዕቆብ የተባለው አብነት ት/ቤትን በስማ በለው የሚያውቀው መሆኑን ነው የሚገልጸው፡፡
ሁለት፡- ዘሩን ከካህናት፣ ከደኃ ወገን… ይቆጥራል ይላል ራሱ ስለቆጠረ እንዴት መሟገቻ ሆኖ ይቀርባል? ደግሞስ እንዴት ያለ ማያያዝ ነው፣ “ዘሩን ከካህንና ከደኃ ወገን የሚቆጥር ፈረንጅ ይኖራል ወይ?” ብሎ ጥያቄ? ...
ሦስት፡- ስለ ሀሳቡ አደረጃጀትና አቀራረብ ይነሳል፡፡ ብዙዎች አውሮፓዊ ነው የሚሉት የሐሳቡን አደረጃጀትና አቀራረብ በማየት ነው ይላሉ፡፡ የዘርዓ ያዕቆብን ፍልስፍና ያን ያህል ጥሩ የሚባል እንዳልሆነም ጠቁመው በኢትዮጵያ ከዚህም የበለጡ ፍልስፍናዎች እንዳሉ ገልጸዋል። በዚህስ ከኔም ጋር ይስማማሉ፤ እኔም ይህንኑ ነበር የገለጽሁት፡፡ ነገር ግን የተጠቀሙበት ላይ እንለያያለን፡፡ እርሳቸው ለፈረንጆቹ ጸሐፊዎች የሚሆን መሟገቻ አድርገውታል፡፡ በእርግጥ ይሆናል ግን፣ “ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ነበር፣” ለማለት ግን አያስችልም፡፡
አራት፡- አውሮፓዊ ቢሆን ኖሮ ሽሽቱ ወደ ቀይ ባህር እንጂ ወደ ዋሻ አልነበረም፡፡ ይህም እንደ አንድ መከራከሪያ የቀረበ ነው፡፡ ወደየትም ይሽሽ፣ ቀድሞ ነገር ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ሲኖር አይደለም? ጸሐፊው እኮ ኢትዮጵያዊ ገጸ ባህርይ ነው ያቀረበው፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለበትን አድርጓል። ወደ ውጭ ከማሸሽ እዚሁ ተደብቆ እንዲኖር ዋሻውን ፈጠረለት፡፡ አለቀ፡፡ ኢትዮጵያዊ አድርጎ ነውና ሊያቀርብ የሞከረው፡፡  
አምስት፡- የዳዊቷ ነገር መጣች፡፡ ዳዊት በኢትዮጵያውያን ጸሎት የማትቀር መሆኗ! ይህንንም ነው የዘርዓ ያዕቆብም ጸሐፊ የተመለከተው። ይልቅስ ደረጄ አንድ በቤቱ ያለ ጥሩ ልማድ አንስተዋል። በቃላችን ብናጠናው ከሰስህተትና ከግድፈት ለመዳን በመጽሐፍ እንደግማለን፣” ብለዋል …
ልክ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ በቃል ትምህርት ብቻ ለያዙት እንጂ ለመጻሕፍት ሊቃውንት አይሆንም፡፡ ቀድሞ ነገር ነውር ነው፡፡ ውርደት ነው፡፡ ትምህርቱን ያላደላደሉት መሆኑን ማስመስከሪያ ነው፡፡
ስድስት፡- ወደ ታሪክ የሚገባ ሐሳብ ይቀርባሉ። መጽሐፉ የተጻፈው በፋሲል ዘመን ነው፤ ያን ጊዜ ደግሞ ፈረንጅ ከሀገር ተባርሯል፡፡ እና ከየት የመጣ ፈረንጅ ነው በእንፍራዝ ተቀምጦ የሚገኘው?
ደረጀ ኅብስቱ አሁንም እዚያው ናቸው፡፡ መጽሐፉ በፋሲል ዘመን እንደተጻፈ ስለሚያስገነዝብ የትኛው ፈረንጅ ነው በዚያ ዘመን የነበረው ይሉናል። በፋሲል ዘመን ለመጻፉ ከራሱ ዘርዓ ያዕቆብ ከተባለው ገጸ ባህርይ ቃል ውጭ ምንም ነገር የለንም፡፡ እርሱ ደግሞ ወደኋላ ሄዶ ፬፻ እና ፫፻ ዘመን አይደለም ፬ሺ እና ፫ሺ ዓመት ላይ ሊያስቀምጠው ይችላል፡፡ መጽሐፉ ግን የተጻፈው በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ስለመሆኑ በጊዜው ከነበሩ ሰዎች የተጻፈው ብቻ ይበቃል፡፡ (“ገድለ ያዕቆብ” በሚል ርእስ ስለ ጃኮቢስ ገድል አባ ተክለሃይማኖት በተባሉ የአድዋ ካቶሊካዊ መነኩሴ የተጻፈውን ያንብቡ፡፡ በጊዜው በሕይወት የነበሩና በጊዜው የሆነውን የጻፉ ናቸው፡፡)   
ከዚህ ውጭ በመካከል ክላውድ ሳምነር የዘርዓ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት አልተጠራጠሩም የሚል አስገብተዋል፡፡ “ክላውድ ሳምነር በኢትዮጵያ ፍልስፍና ላይ እድሜያቸውን የፈጁ” መሆናቸውንም በመጥቀስ ነው ደረጄ ይህን ያስገቡት፡፡ እንዲህ ከኾነ ይህን የማይረባ ፍልስፍና ትተው ራሳቸው ደረጄ ረቀቅ-መጠቅ ያሉ መኾናቸውን የገለጿቸውን ለምን መርምረው አላገኟቸውም? ነገሩ ግን ወዲህ ነው ክላውድ ሳሞነር ፊትለፊት የገኟቸውን ብቻ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ብለው፣ ፍልስፍናው ላይ ትኩረት አደረጉ እንጂ ብዙም በዚህ ነገር ላይ አልገቡበትም፡፡
በአጠቃላይ አሁንም ዘርዓ ያዕቆብ የሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ላለመኖሩ ምንም ዓይነት መረጃና ማስረጃ (መጽሐፍ ተብሎ በስሙ ከቀረበለት ውጭ) አናገኝም.. መጽሐፉም ዘርዓ ያዕቆብ ምናባዊ ሰው መሆኑን ነው እያሳየን የሚገኘው፡፡
ደረጄ ጽሑፋቸውን ሲጀምሩ፣ ይኼው ዘርዓ ያዕቆብ እንዳለው ተደርጎ በመጽሐፉ የቀረበውን፣ ወሐሳዊ ብእሲሰ ዘየኅሥሥ ንዋየ አው ክብረ...። የሚለውን በመጥቀስ የቀረበው ዝርዝር ግን እኔን ይመለከት እንደሆነ እንዲሁ በድፍኑ “ያለመተዋወቅ!” ብዬ እተወዋለሁ፡፡


Read 5469 times