Saturday, 15 February 2014 13:27

ሳንሱረኞቹ

Written by  ድርሰት - ሉይዛ ቫሌንዙዬላ - /ቦነስ አይረስ - አርጀንቲና/ ትርጉም - ፈለቀ የማርውሃ አበበ /filmethiopia@yahoo.com/
Rate this item
(4 votes)

         ምስኪን ጁዋን! አንድ ቀን በራሱ ጠባቂ እግር ስር አንበረከኩት፡፡ እያጣደፈ ወደ ላይኛው እርካብ ያወጣው የዕድሉ መሰላል ቁልቁል ተሽቀንጥሮ የሚፈጠፈጥበት የውድቀት ዕጣ ፈንታው ወጥመድ እንደነበር ከቶም አልጠረጠረም፡፡ ይህን መሰሉ ውድቀት፤ ነገሮችን ችላ ባልንበት ቅፅበት የሚከሰት ነው፡፡ ችላ የማለት አመል በተጠናወተው ሰው ላይ ደግሞ ይብሳል፡፡ በተለይ፤ ያልተጠበቀ ገጠመኝ የሚፈጥረው በደስታ የማነሁለል አባዜ፤ አንድን ያልተጨበጠ ጉዳይ ፍፁም የሆነ ያህል እንድናምን የማድረግ ሀይል አለው፡፡
ለዚህም ነበር ጁዋን፤ ማሪያና ፓሪስ ውስጥ እንዳለችና እሱንም እንዳልረሳችው ሹክ ብሎት፤ አድራሻውን የሰጠውን ሰው አምኖ፤ ለማገናዘብ ፋታ ሳይወስድ እንኳ፤ በሀሴት ሰክሮ ደብዳቤውን መፃፍ የጀመረው፡፡
የዚያ ደብዳቤ ስጋት ግን፤ ቀን ስራውን ባግባቡ እንዳያከናውን፤ ሌትም እንቅልፉን እንዲያጣ አደረገው፡፡ ስለምን ጉዳይ ነበር ወረቀት ሙሉ የቸከቸከው? ለማሪያና ገጥግጦ ፅፎ በላከው ደብዳቤ ላይ ምን ነበር የዘበዘበው?
ጁዋን፤ በደብዳቤው ላይ የፃፈው ጉዳይ ሁሉ፣ አንድም ለትችት የሚያጋልጥ ወይም ጉዳት የሚያመጣ ይዘት እንደሌለው ያውቃል፡፡ ግን “በሌላውስ አይን ሲታይ?” ነው ጥያቄው፡፡ ሰዎቹ እንደሁ፤ የማንኛውንም ሰው ደብዳቤ ገንግነው፣ አሽትተው፤ የእያንዳንዷን መስመር ዐረፍተ ነገሮች፣ ሀረጋት፣ ያልተለመደ አይነት የቃላት አገባብ፣ የስርዓተ ነጥብ አጠቃቀም ሁሉ ብጥርጥር ብትንትን አድርገው እንደሚያነብቡና ሌላው ቀርቶ በድንገት፣ የወረቀቶች ገጽ ላይ ጠብ ያለ ነገር ቢያጋጥማቸው፤ ለዚሁ በተዘጋጀው ማሽን እገዛ በጥንቃቄ አነፍንፈው፣ በተጠና የቅብብሎሽ አሰራር፣ ከአንዱ መርማሪ ወደ ሌላው እያስተላለፉ በትጋት እንደሚመረምሩ ይታወቃል፡፡ ከየትም፤ ወዴትም የተላኩ ፖስታዎች ሁሉ፤ በጥንቃቄ የሚበረበሩበትን የግዙፉን ሳንሱር ጣቢያ ቅጥልጥል የምርመራ ሰንሰለት ማጣሪያ አልፈው፤ ከየትየለሌ ደብዳቤዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ተቀባዮቻቸው ዘንድ ለመድረስ ጉዞአቸውን የሚቀጥሉት፡፡ ይሄ ሂደትም ባብዛኛው በወራት የሚቆጠሩ ጊዜያትን ሊወስድ ይችላል፤ ካስፈለገም ለአመታት፡፡ ይህም ማለት፤ የደብዳቤው ችግር አልባነት እስኪረጋገጥ ድረስ ባሉት የምርመራ ጊዜያት የላኪም ሆነ የተቀባይ የነፃነትና የህልውና ጉዳይ በስጋት መክረሙ ነው ማለት ነው፤ እስኪጣራ! ለዚህም ነው ጁዋን በጭንቅ የተያዘው፡፡ እሱ በላከው ደብዳቤ ጦስ ማሪያናን አጉል እንዳያረጋት ክፉኛ ሰግቶ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ማሪያና፤ እንደምትመኘው፤መኖር ትፈልግበት በነበረው አሁን ባለችበት ስፍራ በአስተማማኝ ደህንነት ውስጥ መቆየት አለባት፡፡ ሆኖም ግን፤ የሳንሱረኞቹ ምስጢራዊ እዝ፤ በየትኛውም የአለም ክፍል ተንፈራጥጦ የተንሰራፋ ነው፡፡ አባላቱም፤ በቁጥጥር ስር ሊያውሉት የሚፈልጉትን ማንኛውንም ሰው የገባበት ገብተው፣ ጆሮውን ይዘው በማምጣት ሊቀፈድዱት ይችላሉ፡፡ ታዲያ በአንዲት ፓሪስ ውስጥ በምትገኝ መኖሪያ መንደር ውስጥ በተሸሸገችው ማሪያና አንገት፣ ሸምቀቆ ከማስገባትስ ማን ሊያስቆማቸው ይቻለዋል? የሰዎቹ ዋንኛ የመኖር ተልዕኳቸውስ ይኸው አይደል? በመንግስት ባለስልጣናቱ አይን ሞገስ የሚያገኙበትን፣ የሹማምንቱ አምሮት ይረካ ዘንድ የሚወነጨፉለትን፣ የሌላውን ጎጆ ሰላም የማራቆት ዒላማቸውን አሳክተው ወደ ሞቀ እልፍኛቸው ከተፍ! ከተፎዎች፡፡
እናም፤ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ አይበጅም፡፡ የሆነ ነገር መደረግ አለበት! የሰዎቹን እኩይ ተግባር ለማደነቃቀፍ የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ! ማንም ሳያውቅ አፈርና ጠጠር ውስጡ ሞጅሮ መመርመሪያ ማሽኑን ማስተጓጎል፡፡ አዎ!ጭራሽ እንዳይላወስ ሆኖ እንዲቆም መሽከርከሪያ ጥርሶቹን ማርገፍ! ብቻ፤ የሚመጣውን አደጋ ለማስቆም ማንኛውንም አቅም የሚፈቅደውን እርምጃ ሁሉ መውሰድ!
ጁዋን፤ ይህን ረቂቅ ሴራውን በውስጡ እያውጠነጠነ ነበር፤ ከሌሎች ለሳንሱረኝነት ክፍት የስራ ቦታ ከሚያመለክቱ ሰዎች ጋር ተሰልፎ የተመዘገበው፡፡ ለሞያው ብቁ የሚያደርግ ክህሎትም ሆነ ስራውን የመፈለግ ዝንባሌ ኖሮት አይደለም፤ ራሱ ጽፎ የላከውን ደብዳቤ መልሶ እጁ ለማስገባት ብቻ እንጂ፡፡ ምንም እንኳ እቅዱ፤ ለመተግበር ቀርቶ ለማሰብም የሚከብድ ያልተለመደ አይነት ውጥን ቢሆንም፡፡ ወዲያውኑ ተቀጠረ፡፡ ሰዎቹ በየቀኑ አዳዲስ የሳንሱር ሰራተኞችን ይቀጥራሉ፡፡ በአዲስ ገቢዎቹ ተቀጣሪዎች ላይም ያን ያህል ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርጉባቸው አይታዩም፡፡ ከሰራተኞቹ መካከል ድብቅ ፍላጎቱን የሚጎነጉን ቢገኝ ግን የሳንሱር ክፍሉ ምህረት የለውም፡፡ እናም እንዲህ ቸል ማለታቸው፤ ‹አንድ ምስኪን አዲስ ቅጥር ሳንሱረኛ፤ የሚፈልገውን ደብዳቤ ለማግኘት ቢሞክር ምን ያክል እንደሚቸገርና የፈለገውን ቢያገኝም ን‘ኳ፤ አይኑ ስር ተዝረክርከው በተከመሩት እልፍ አዕላፍ ደብዳቤዎች እድል ላይ መወሰን የሚችል ሆኖ ሳለ፤ በአንድ ወይም በሁለት ደብዳቤዎች ላይ ትኩረት ቢያደርግ ምን ሊያመጣ ይቻለዋል?› ብለው ስለሚያስቡ ይሆናል፤ አለ ጁዋን ለራሱ፡፡ ቀድሞውኑም ቢሆን እኒህን መሰል ግምቶቹን ተማምኖ ነበር፤ በሳንሱር ጣቢያው የፖስታ ቅድመ ምርመራ ቅርንጫፍ ክፍል ውስጥ ሰርጎ ለመግባት የተነሳው-በስውር ሊያከናውነው የነደፈውን ሴራ ለብቻው እያብሰለሰለ፡፡
የግዙፉ ሳንሱር ጣቢያ የውጪ ገፅታ ማራኪነት፣ በሆዱ ውስጥ ሌት ተቀን የሚከናወነውን ከፍተኛ የስራ ውጥረት የሚጠቁም ምንም ፍንጭ አይሰጥም። ጁዋን፤ ውሎ ሲያድር በጀመረው የሳንሱረኝነት ሞያ ይበልጥ እየተመሰጠ . . . ሄደ፡፡ በየእለቱ በሚያከናውነው ተግባር ምቾት እየተሰማው መጣ፡፡
አቅሙ በፈቀደው መጠን እየተፍጨረጨረ፣ ለማሪያና የላከውን ደብዳቤ እጁ ለማስገባት የሚያደርገውን ጥረት ያላንዳች መሳቀቅ በሰላማዊ ሁኔታ ገፋበት፡፡ በተቀጠረ በወሩ የፍንዳታ አደጋ የሚያስከትሉ ነገሮችን ይዘዋል ተብለው የሚታሰቡ እሽጎች በረቀቀ መንገድ ወደሚመረመሩበት ‹ኬ ክፍል› ባጋጣሚ ተመድቦ ሲሄድ እንኳ፤ ምንም ታህል ፍርሀትና መጨነቅ ሳይነበብበት ተረጋግቶ ነበር የታዘዘውን ሁሉ ያቀለጣጠፈው፡፡
በርግጥ፤ እሱ ‹ኬ ክፍል› በተመደበ ገና በሦስተኛው ቀን ላይ፣ በምርመራ ላይ ከነበረ የታሸገ ፖስታ በተከሰተ ፍንዳታ፤አንድ እሱን መሰል አዲስ ቅጥር ሳንሱረኛ ተቃጥሎ፣ ቀኝ እጁ እርር ብሎ ተንጨርጭሮ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ ምንም እንኳ የ ‹ኬ ክፍል› የሳንሱር ምርመራ ኃላፊው፤ አደጋው የተፈጠረው በሰራተኛው ገደብ የለሽ ንዝህላልነት መሆኑን ማረጋገጫ ቢሰጡም፡፡ አደጋውን ተከትሎ ጁዋንና ሌሎቹ ሰራተኞች ለዚህ መሰሉ ጉዳት የመጋለጥ ስጋት  ወደሌለበት ክፍል እንዲዛወሩ ተፈቀደላቸው፡፡ የእለቱ ስራ ሰአት ከመጠናቀቁ በፊት ታዲያ፤ከሰራተኞቹ መሀል አንዱ፤በእንዲህ ያለ ክፉ አደጋ ባንዣበበበት የስራ ቦታ ለሚያከናውኑት ተግባር ተጨማሪ የደመወዝ ክፍያ ሊደረግላቸው እንደሚገባ አሰሪዎቻቸውን የሚያፋጥጥ ሀሳብ ጠንስሶ፣ ሰራተኞቹን በህቡእ ለአመፅ አስተባበረ። ጁዋን ግን በአመፁ እንቅስቃሴ አልተባበረም። ይልቅስ ጉዳዩን ደጋግሞ ካሰበበት በኋላ፣ ወደ ላይ አለቆቹ ሄዶ፣ የአመፁን ቆስቋሽ ሰው ማንነት በምስጢር ሪፖርት አደረገ፡፡ ለዚህም መሰሉን አሳልፎ የመስጠት የአጋላጭነት ‹ምስጉን› ተግባሩ ውዳሴና እድገት ተቸረው፡፡ የአለቃውን ቢሮ በር ከፍቶ እየወጣ ሳለም፤… ‹መቸም፤ገና ለገና እርሜን፤ ዛሬ ብቻ፤ ይኼን የማጋለጥ ነገር ስለፈፀምኩ፤ የአቃጣሪነት ባህሪ አይጠናወተኝም› ብሎ ራሱን በከንቱ አጽናና፡፡ ከዚህ ምስጋናን ካተረፈለት ድርጊቱ በኋላም የደብዳቤዎች መርዛምነት ወደሚመረመርበት ‹ጄ ክፍል› ሲዛወር፣ ከናወነው መልካም ተግባሩ የዕድገት መሰላል በመወጣጣት ላይ መሆኑ ጠልቆ ተሰማው፡፡
ጠንክሮ በመስራትም በፍጥነት ወደ ሌላኛው ረቀቅ ያለ የምርመራ ተግባር ወደሚከናወንበት፣ የእያንዳንዱን ደብዳቤ ይዘት አጣርቶ ማንበብ ወደሚችልበት ‹ኢ ክፍል› ተዛወረ፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥም ራሱ ጽፎ የላከውን ደብዳቤ እንደሚያገኘው እርግጠኛ ሆነ፡፡ ‹ይኼ ጊዜ ደርሶ እዚህ ለመገኘት ስል ነበር እስከዛሬ ፍዳ የበላሁባቸውን ክፍሎች ሁሉ ማለፍ የነበረብኝ› አለ፡፡
ያም ሆኖ ግን፤ ፋታ በማይሰጠው ሳንሱረኝነቱ ተጠምዶ፤ ዋናውን ሊያሳካው ያለመውን እቅዱን እስኪዘነጋ ደረሰ፡፡ ቀን በቀን እየታፈሱ የሚቀርቡለትን ደብዳቤዎች፤ ከጧት እስከ ማታ ወንበሩ ላይ ተሰፍቶ፤ አይኖቹን በያንዳንዱ መስመሮች ላይ አጨንቁሮ እያነበበ፤አንቀፆቻቸውን በቀይ እስኪርቢቶ ሲያሰምር መዋልና ወደ ሳንሱር ቅርጫቱ ማጎር የእለት ተዕለት ኑሮው ሆነ፡፡ በእነዚያ አሰቃቂ ቀናት ውስጥም፤ቅርጫቱን ካጨቀባቸው የደብዳቤ ልውውጦች፤የሰዎችን ምስጢራዊ የቋንቋ አጠቃቀም የመረዳትና የመታዘብ እድል አግኝቷል። እንደ ‹‹አየሩ ከብዷል›› ወይም ‹‹የትራፊኩ መጨናነቅ አያፈናፍንም››  አይነት ቀላል የሚመስሉ በደብዳቤ ጽሁፎች ውስጥ የተመሰጉ ወሽመጥ ሀረጋት ፤መንግስትን ለመገልበጥ የሚሰነዘሩ ‹‹ሽብር ቀስቃሽ!›› መልዕክቶች ስለመሆናቸው በሳንሱረኝነት ለሰላ ንቁ አእምሮው ፍንትው ብሎ ይገለጥለት ነበር።
በቃ! በልጓም አልባ ጉጉቱ የጦዘ ታታሪነት ውሎ አዳሩ፣ በአናት ባናቱ ሹመት ይደራርብለት ጀመር። እንግዲህ ይኼ ሁሉ ሲሆን እሱን ምን ይሰማው እንደነበር ለማወቅ አለመቻላችን ይቆጫል። እናም በዚህ ከነፋስ የፈጠነ በረራው፤ የተወሰኑ ደብዳቤዎችን ብቻ ተረክቦ ወደሚመረምርበት ‹ቢ ክፍል› ደረሰ። ሌሎቹን የምርመራ ሂደቶች አልፈው ከእጁ የደረሱትን አንድ እፍኝ ያህል ጥቂት ደብዳቤዎች እጅግ በጥንቃቄ፤ ከሙሉ የመልዕክታቸው ይዘት ትርጉም ጀምሮ በየአንቀፆቻቸውና ዐረፍተ ነገራቱ፣ ሀረጋቱ፣ ቃላቱና ፊደላቱ መካከል እየተመላለሰ ደግሞ ደጋግሞ ማንበቡን ቀጠለ። አጉሊ መነፅሩንም ባግባቡ መጠቀም ነበረበት። በአይን የማይታዩ የማይክሮ ፕሪንት ረቂቅ ምልክቶችን አጣርቶ ለማሳለፍ የሚያስችል ኤሌክትሮኒክ ማይክሮስኮፕም በጠረጴዛው ላይ ቀርቦለታል፡፡ ጠረናቸውንም ጭምር  በጥንቃቄ ሲያነፈንፍ ውሎ ራስ ምታት እየጠለዘው ነበር ቤቱ የሚደርሰው። እጁን በሙቅ ውኃና ሳሙና ሙልጭ አድርጎ ከታጠበ በኋላ፣ አልጋው ላይ ጋደም ብሎ ፍራፍሬዎችን እየገመጠ፣ ቀኑን ሙሉ ባከናወነው የላቀ ተግባሩ እርካታን ተመልቶ በዚያው ያሸልባል። እናቱ ብቻ ነች በእሱ ነገር በጭንቀት ተወጥራ የምትብሰለሰለው፡፡
እሷም ብትሆን ግን ከገባበት ማጥ ጎትታ የማውጣት አቅም የላትም፡፡ እውነቷን ይሁን  ባይታወቅም፤ ሁልጊዜ ከስራ ሲገባ፤ ‹‹ሎላ ደውላ ነበር፤ ከጓደኞቿ ጋ መናፈሻው ስፍራ ናት፤ ይመጣል ብለው እየጠበቁህ ነው…›› ትለዋለች። ወይም ደግሞ ቀይ ወይን ጠጅ ገዝታ ከራት ማዕዱ ጋ ጠረጴዛ ላይ ታቀርብለታለች፡፡
ጁዋን ግን ንክች አያደርጋትም፡፡ አንዲትም የግዴለሽነት ድርጊት ብትሆን ከጥንቃቄ ጉድለት ለሚመጣ ውድቀት ትዳርጋለቻ! ከዚያም በላይ ደግሞ አንድ ሳንሱረኛ ማንንም ቢሆን ማመን አይጠበቅበትም፡፡ እናቱስ ብትሆን፡፡ የቀረበለትን ግብዣ ዝም ብሎ መቀበል የለበትም። የተቀነባበረ ሴራ ቢሆንስ፡፡ ህ! ዙሪያ ገባውን ተጠራጣሪ፤ጥላውንም የማያምን መሆን ይገባዋል፡፡ የተሰማራበት የሞያ መስክ ራስን የመካድ ያህል መስዋዕትነት የሚጠይቅ፤ ግን ደግሞ በእድገት የሚመነጥቅ መሆኑን አሳምሮ ያውቀዋል፡፡
ተመርምረው በወደቁ ደብዳቤዎች ጢም ብሎ የሞላው የጁዋን ቢሮ የሳንሱር ቅርጫት፤በመላ የሳንሱር መስሪያ ቤቱ ካሉት ቅርጫቶች ሁሉ የተጨበጨበለት ሆኖ ነበር፡፡ ራሱን በራሱ ‹‹አንተ ታላቅ ሰው እንኳን ደስ አለህ!›› ለማለት የቃጣው ግን፤ በመጨረሻ እሱ ራሱ ጽፎ የላከው ደብዳቤ እጁ ሲገባ ነው፡፡ እናም ልክ ሌሎቹን ደብዳቤዎች ሲመረምር እንደሰነበተው፤ በእሱው በራሱው ጽሑፍ ላይም፤ ያለ ምንም አድልዎና ርህራሄ፤ ያንኑ ጥንቃቄ የተመላበትን አይነት ምርመራ አለማድረግ አልቻለም፡፡ ቀጣሪዎቹም እንዲሁ፤ በማግስቱ፤ ልክ እንደ ሌሎቹ እልፍ አእላፍ ደብዳቤዎች ሁሉ፤ በእሱ ደብዳቤ ላይም፤ ያለ ምንም አድልዎና ርህራሄ፤ ያንኑ በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባራቸውን አለማድረግ አልቻሉም፡፡ እነሆ በተሰማራበት የሳንሱረኝነት ሞያው ፍቅር የወደቀ ምርኮኛም ሆነ፡፡ ቅርጫት ሙሉ…
(‘’The Censors’’ combines the real and the fantastic, a Latin American style called ‘’magical realism.’’)

Read 2682 times