Saturday, 10 December 2011 09:19

ሰው በብርሃን እንጂ በጨለማ አይተገንም ግብረ ሠዶማዊነት ለአፍሪቃም ሆነ ለኢትዮጵያ አፀያፊ ውርደት ነው

Written by  ከበደ ደበሌ ሮቢ
Rate this item
(1 Vote)

ሞኝ የተከለውን ብልህ አይነቅለውም፤ ይባላል፡፡  
ግብረ ሠዶማዊነት ለአህጉር አፍሪቃም ሆነ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ አፀያፊ ውርደትና አስከፊ ማኅበራዊ ዝቅጠት ነው፡፡ የሰብአዊ ተፈጥሮን ሚዛን ማዛባትና አጉራ ዘለልነት ብቻ ሳይሆን የከበሩ የማኅበራዊ እሴቶች መሠረትን የሚያዋርድ እና የሚንድ አዘቅት ነው፡፡ ሰብአዊ የሰውነት ተፈጥሮን የሚያጐሳቁልና የሚያዛባ መታወክ ብቻ ሳይሆን በማኅበረሰብ ውስጥ አንዴ ከተተከለ በቀላሉ የማይነቀል፣ ኅብረተሰባዊ ህይወትን ወደ ጨለማ እና አዘቅት የሚገፋና የሚነዳ፤ ከኢንዱስትሪያል ቴክኖሎጂ ማደግና ከአጉራ ዘለልነት መስፋፋት ጋር አብሮ የሚመጣ ማኅበራዊ ውርዴና የትውልድ ነቀርሳ ነው፡፡

ልክ “ዩናይትድ ፎር ላይፍ ኢትዮጵያ” የተሰኘው ተቋም ዳይሬክተርና የቀዶ ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ሥዩም አንቶኒዮስ እንዳሉት:-የግብረ ሰዶማውያን የህይወት ዘይቤዎች በሳይንሳዊ ምርምር ለትውልድ ጠር፤ ለአገር እድገትም ዕንቅፋት መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ በአፍሪቃ ደረጃ ግብረ ሰዶማዊነትን እንዴት ማስፋፋት ይቻላል? የሚል ስብሰባ እኛ አገር መደረጉ በጣም አደጋ ነው፤ ግብረ ሰዶማዊነትን በሚመለከት የሚደረግ ስብሰባ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀባይነት እንደሌለው ይታወቃል…  
ግብረ ሠዶማዊነትን ከየትኛውም መመዘኛ አንፃር ብናየው ግለሰባዊና ማኅበራዊ፣ ተፈጥሮአዊ ክብርና ባህሪን እንደ ብል የሚበላ አሳፋሪ ልምምድ ነው፡፡ ከአሥራ ሶስት ዓመታት በፊት “ቴር ዴዝ ሆም” በተሰኘ አውሮጳዊ ግብረ ሠናይ ድርጅት ውስጥ ሲረዱ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ወንድ ህፃናት ላይ በአሣዳሪዎቻቸው በተፈፀመ ግብረ ሠዶም፣ ህፃናቱ ለማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ችግሮች ተዳርገዋል፡፡ በህፃናቱ ላይ ግብረ ሠዶሙን በተደጋጋሚ ሲፈፅሙ ከነበሩት ለአካለ መጠን የደረሱ ወንድ ፈረንጆች በደረሠባቸው ማኅበራዊ ቀውስ የተነሣ ራሳቸውን እስከ መስቀል የደረሡ አሉ፡፡ ጉዳዩ አደባባይ ሲወጣ የአሣፋሪ ልምምዱ መገለጥ ባደረሰበት ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት አገሩ ሄዶ ራሱን የገደለ ፈረንጅ፡፡ ጉዳዩ ፀሐይ ሲሞቅ ከአዲስ አበባ እስከ ወሎ ጃሪ ያለውን የግብረ ሠናይ ድርጅቱን የህፃናት ማሳደጊያና መርጃ መዋቅር በማይረሳ ሀፍረትና ሀዘን አነቃንቋል፡፡
ግብረሠዶማዊ ልምምድ:- ወንዶች ከወንዶች ጋር ሊያደርጉ የማይገባቸውን ነገር ግን እያደረጉ ያሉትን የወሲባዊ ግንኙነት ሂደት (Homosexual) ማሳደግ ወይም መለማመድ ነው፡፡ ይህ ልምምድ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአህጉር አፍሪቃ አገሮችና ህዝቦች አደገኛና አሳፋሪ ነው፡፡ ከተፈጥሮአዊ ባህሪ የወጣና ድንግል ተፈጥሮን የሚያስተጓጉል፤ ድንቁርና እና አጉራዘለልነት ፈረንጆች እንደሚሉት:- Ignorance & Arrogance
በክርስትናም ሆነ በእስልምና፣ በአይሁድም ሆነ በሂንዱ፤ በቡድሃም ሆነ በገዳ፤ በታኦም ሆነ በኮንፊሺየስ፤ በባቢም ሆነ በባሃኢ የአምላክን ክብር እና ባህሪ የሚያሳዝን (የሚያስቆጣም) ድርጊት ነው ግብረ ሰዶም፡፡የአምላክ ክብር ያዝናል እንጂ አይዋረድም፤ ይወቅሳል እንጂ አይከሰስም፡፡ በሳይንስም ሆነ በፍልስፍና በጥበብም ሆነ በየዋህነት የሚነወር፤ የሰብአዊ ተፈጥሮን ክብርና ባህሪ የሚያጓድል ብቻ ሳይሆን የሚያስተጓጉል (Abuse የሚያደርግ)፤ ለሥልጡን እና ጤናማ ኅብረተሰብ ግንባታ ጠንቅ የሆነ ፤በህግና በርትዕም ሆነ በየትኛውም ሥልጡን አስተሳሰብ የማይደገፍ፣ ሊደገፍም የማይገባው የነፃነት መብትና የሥልጣኔ ክፈፎች ያሉት ቆብ አጥልቆ በአፍሪቃ የተስፋ ንጋት ውስጥ ብቅ ያለ አደገኛ አዝማሚያ ግብረ ሠዶም፡፡ በመሠረቱ ግብረ ሠዶም የማኅበራዊ ዝቅጠት መታያና ተፈጥሮን ማጐሳቆል እንጂ የነፃነት መብትም ሆነ የሥልጣኔ ጉዳይ አይደለም፡፡ እንደዚህ ዓይነት የነፃነት መብትም ሆነ ሥልጣኔ የለም፡፡
ይሄ ዛፍ በቅጠሎቹ በኩል አይተከልም፤ በሥሮቹ በኩል እንጂ፤ ቢተከልም አይበቅልም፡፡ ይሄ ሰው በዓይኖቹ አይሰማም፤ በጆሮዎቹ አያይም፡፡ የሰው ልጅ በዓይኖቼ ካልሰማሁ በጆሮዎቼ ካላየሁ ብሎ አላስፈላጊ ልምምድ ውስጥ መዳከር የለበትም፡፡
ግብረ ሠዶምን የሚደግፍ ወይም በህግ የሚያፀና አፍሪቃዊ አገር ካለ አፍሪቃ ለልጆቿ በቀላሉ የማይወጡት ሥልጡን የኅብረተሰብ ግንባታ ፀርና የብሔራዊ አዘቅት የማኅበራዊ ዝቅጠት ውርዴ እየተከለች፤ አሻግሮ ማየት ለተሳነው ትውልድ ልጆቿን አሳልፋ እየሰጠች ነው ሊባል ይቻላል፡፡ ይሄን ማድረግ አሻግሮ ማየት ያለመቻል (Far sighted ያለመሆን) ብቻ ሳይሆን የህሊና መታወርም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች፤ የአፍሪቃ ልጆች ምሁራንና ልሂቃን፣ የሃይማኖት አባቶችና የፖለቲካ ሥልጣናት ይሄንን አጥብቀው በጽኑ መቃወም ብቻ ሳይሆን ማገድና ማስወገድ አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ የመንግሥትና የሃይማኖቶች የጤና ባለሙያዎችና የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት (ግድም) ለመጀመሪያ ጊዜ የሲኒማ ጥበብ በአገራችን ሲታይ አባቶቻችን የአሁኑን አምፊ ቲያትር ሰይጣን ቤት ያሉት ስላልሰለጠኑ እንደሆነ አላውቅም፤ እኛ ግን ግብረ ሰዶም ለአፍሪቃና ለኢትዮጵያ ህዝቦች አደገኛና አፀያፊ ውርደት ነው የምንለው ሥላልሰለጠንን ሳይሆን በሰለጠነ ኅብረተሰብ ግንባታ ውስጥ የትውልድ ጠንቅነቱንና አደጋውን አስቀድመን ማየት ስለቻልን ነው፤ ወይም ደግሞ አሻግረን ስላየን፡፡ አሻግሮ ማየት የመሪዎችና የሊቃውንት ዓይነተኛ ባህሪ ነው፡፡ አምላክ ደግሞ ከቀባቸው መሪዎችና ልዩ ችሎታ ከሰጣቸው ሊቃውንት በላይ አሻግሮ የሚያየው አለው፡፡ ከሰባት ቢሊየን የዓለም ህዝቦች ውስጥ ከአንድ ቢሊየን በላይ የሆኑት ክርስቲያኖች አስተምህሮ (Doctrine) ዋነኛ መፍለቂያ ማህፀን የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያወሳው፤ አምላክን ካሳዘኑትና ካስቆጡት ተግባራት አንዱ ሰዶምና ገሞራ ነው፤ ግብረ ሰዶማዊ አጉራ ዘለልነት፡፡ የየትኛውም ሃይማኖት አስተምህሮ ግብረ ሰዶምን አይቀበልም ብቻ ሳይሆን አይፈቅድም፤ አይፈቅድም ብቻ ሳይሆን በጽኑ ይቃወማል ያወግዛል፡፡ የሃይማኖት አስተሳሰቦች የሰውን ልጅ ከአምላክ ቀጥሎ ከሠሩና ካነፁ ጥቂት የከበሩ አስተሳሰቦች አንዱ ነው፡፡ ይሄንን ልብና አእምሮ እግዚአብሔር ሰጠ፤ ይሄንን ልብና አእምሮ ሃይማኖትና ሳይንስ፣ በአብላጫው ጥበብና ፍልስፍና በተወሰነ መጠን አነፁት፡፡
ግብረ ሰዶም በBiology የጥናት ዘርፍ (በሳይንስ ዓይን ሲታይ) ተገቢ ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ጉዳትም አለው፡ አንድ ገበሬ ዘሩን በአለት ላይ አይዘራም:- ቢዘራም አለቱም አያበቅልም ዘሩም አይበቅልም፤ ዘሩም ይበላሻል አለቱም ባላስፈላጊ ነገር ለመሸፈን ይገደዳል፡፡ የግብረ ሰዶማዊነት አደጋ ከዚህም ያለፈ ማኅበራዊና ትውልዳዊ ውድቀት ጭምር ነው፡፡ አንድ ወንድ በማይገባ አኳኋን ከሌላ ወንድ ጋር ወሲብ ሲፈጽም (ወሲብ ከተባለ) ግብረ ሰዶማዊ ልምምድን በውስጡ ማሰልጠን (obssesed መሆን ብቻ ሳይሆን) ከወንድነቱና ከሰብአዊ ሰውነቱ ውስጥ የሚያጣቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ይሄ መወሳት Biological የሆነውን አደጋ ብቻ የሚያሳይ ነው፡፡ ግብረ ሰዶም ለባለጉዳዮቹ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ቤተሰባዊ ጠንቅም ነው፤ ማኅበራዊ አዘቅትና በቀላሉ የማይነቀል የትውልድ ነቀርሳም ጭምር፡፡
የሰው ልጅ እያንዳንዱ አካሉና መላው ተፈጥሮ የየራሱ ተፈጥሮአዊ ክብር አለው፡፡ ከሰባት መቶ ሚሊየን በላይ ተከታዮች ባሉት የሂንዱ ሃይማኖት አስተምህሮዎች አንዱ አንጓ አሂምሣ (Ahimsa) ነው፤ የአሂምሣ ፍልስፍና ሥረ መሠረት መላውን ተፈጥሮ በማክበር ላይ ተመስርቶ፣ ለመላው ተፈጥሮ የሚሰጠው ክብር ስፋት መጠን የእንስሳት ተዋጽኦዎች በሆኑ ቆዳን በመሳሰሉ መጠቀሚያዎች እስካለመጠቀም ይዘልቃል፡፡ የኢትዮጵያ የልብ ወዳጅ የሆነው ጃማይካዊው ኩዊንተሰብ በምድረ ኢትዮጵያ በባዶ እግሩ የሚሄደው ጫማ በማድረግ ሊገኝ የሚችለውን ምቾት ስለማይፈልግ አይደለም፤ ኢትዮጵያ የተባለችው አገር ቅድስትና የጥቁሮች የነፃነት ብርሃን ተስፋይቱ ምድር ናት ብሎ ስለሚያምንና ለአገራችን ገፀ ምድር (እንኳ) ልዩ ክብር ስለሚሰጥ ነው፡፡ የማይሻረው ንጉሥ የምለው ጥላሁን ገሠሠ ከፍ ብሎ ሲዘፍን ኢትዮጵያን የእግዚአብሔር ቅዱስ (ትሁት) ልጅ ቅድስት ኢትዮጵያ ብሎ ነው የሚገልፃት፡፡ እንኳን ሰው ምድሩ፤ በምድሩ ላይ ያለው የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ድንግል ተፈጥሮ ሳይቀር የተከበረና የከበረ ነው፤ የሰው እያንዳንዱ አካል (ብልት)ም የተከበረ፡፡ ቢሊዮን ህዝቦች ወደ ቤተ መቅደስ ሲገቡ ጫማቸውንና ባርኔጣቸውን ያወልቃሉ፤ ያ ቤተ መቅደስ (ቅድስተ ቅዱሳን) እጅግ የተከበረ ስለሆነ፡፡ የአምላክ ዋነኛው ማደሪያና ቤተ መቅደስ ደግሞ የሰው ልጅ ነው፡፡ ግብረ ሰዶም ለሰው ልጅ ክብር ሳይሆን ውርደት ነው፡፡
ለዚህ ጽሑፍ እዚህና አሁን መፃፍና መነበብ ምክንያት የሆነው፤ ባለፈው ሳምንት የአፍሪቃ ግብረ ሰዶማውያን ስብሰባ በርዕሰ መዲናችን በአዲስ አበባ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስብሰባ ማዕከል መካሄዱ ነው፡፡ የስብሰባው ዓላማና አጠቃላይ ሁናቴ በአጭሩ እና በምጥኑ እንደሚከተለው ያለ ነው፡፡
ተቀማጭነታቸውን በአሥራ ሶስት የአፍሪቃ አገራት ያደረጉ አሥራ አምስት የሚሆኑ ግብረ ሰዶማዊነትን እንደ በጐ ምግባር የሚያንፀባርቁ ድርጅቶች ያዋቀሩት በደቡብ አፍሪቃ የሚገኝ አምሸር (Amsher) The African men for sexual Health & rights ተብሎ የሚጠራ ድርጅት፤ የአፍሪቃ ግብረ ሰዶማውያን የቅድመ ኮንፍረንስ ማነቃቂያ ስብሰባ ማድረጉና 200 ግብረ ሰዶማውያን የሚሳተፉበት ዋነኛ ጉባኤ ማካሄዱ ነው፡፡ ቁልጭ ቅልብጭ፣ እጥር ምጥን ባለ አቀራረብ የጉባኤው ዓላማዎች :-
1 ለአህጉር አፍሪቃ ግብረ ሰዶማውያን አዲስ ትብብር ለመፍጠርና ለማቀናጀት፤
2. ምርጥ ተመክሮዎችን ለማስፋፋትና ለሚቀጥለው ትውልድ ይህንኑ ዘይቤ ለማስተላለፍ፤
በአፍሪቃ የወንድ ለወንድ ግብረ ሰዶማዊ ግንኙነቶችን Men who Have Sex With Men እውን ማድረግ ለኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት አስተዋጽኦ ስለሚያደርግ ትኩረት እንዲያገኝ ማስቻል፤
Claim Scale up & Sustain (የራስ ማድረግ ማሳደግና ቀጣይነት) በሚል መሪ ቃል ከሃያ አምስት የአፍሪቃ አገሮች የተወጣጡ ሁለት መቶ ግብረ ሰዶማውያን በሚሳተፉበት ስብሰባ ግብረ ሰዶማዊነት ህጋዊ እንዲሆን ከማስቻል አኳያ አፍሪቃዊ ምላሽና ነፀብራቅ ማሳየት፤
5.ኤች አይ ቪ ኤድስን ከመከላከልና ከመቆጣጠር አኳያ ግብረ ሰዶማዊነትን ህጋዊ ማድረግ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በመለየት ማሳየት …የሚሉ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የስብሰባው ዓላማዎች ሲታሸሙ በአህጉር አፍሪቃ ግብረ ሰዶምን ማስፋፋት፤ እና ግብረ ሰዶማዊነትን እንደ መብት ህጋዊ ማድረግ (ህጋዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ) ነው፡፡
ይሄ ለአፍሪቃም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝቦችና ትውልዶች ትልቅ አደጋና ሀፍረት አፀያፊ ውርደትና አሳፋሪ ነው፡፡ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለተባለው ሰው በብርሃን እንጂ በጨለማ አይተገንም፤ ግብረ ሰዶማዊነት የማኅበራዊ አዘቅትና የጨለማ በደደረ ድንቁርና የመታወርና የአጉራ ዘለልነት መንገድ እንጂ መድኃኒት ላልተገኘለት ደዌ በጭራሽ ፈውስና መድህን ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲያውም የራሱን ደዌ ለአገርና ለትውልድ እያወራረደ ወደ አዘቅት የሚነጉድ የተነወረ ማኅበራዊ ውርዴ ነው፡፡ ይሄ የተባለው እውነት ቢሆን እንኳ ኤችአይቪ ኤድስን ለመከላከል ለመቆጣጠርና ለማስወገድ ግብረ ሰዶምን በማስፋፋት የሚመጣና የሚገኝ ጊዜያዊም ሆነ ዘለቄታዊ ፈውስና መፍትሔ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፡፡ ተግባራችን ችግሮቻችንን ጨርሶ ማስወገድ እና የሥልጡንና ጠንካራ ኅብረተሰብ መሠረት መጣል እንጂ፤ የችግሮችን ቀለም መቀየር ወይም ችግሩን ከአንዱ ትከሻ ወደ ሌላው ትከሻ ማዛወር በጭራሽ ዓላማችን ሊሆን አይችልም፡፡ ቀንበርን እንሰብራለን እንጂ ቀንበርን የምንቀይር አይደለንም፡
የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የአፍሪቃ ግብረ ሰዶማውያንን ስብሰባ ለማስተናገድ ያለመፍቀዱ በሰብአዊነትም በኢትዮጵያዊነትም የሚያኮራና ትክክለኛ አቋም ነው፡፡ በአዲስ አበባ የጁፒተር ሆቴሎች ምክትል ማርኬቲንግ ማናጀር አቶ ያየህ ይራድ ያሉት፡- በዕለቱ ሌላ ስብሰባ እንጂ የግብረሰዶማውያን ስብሰባ ፈጽሞ አይካሄድም፤ ይህን ማረጋገጥ የፈለገ ሰው በስብሰባው ቀንና ሰዓት ወደ ሆቴላችን መጥቶ ማየት ይችላል…ነው፡፡
አህጉር አፍሪቃም ሆነች ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ግብረሰዶምንና መሰሎቹን ማኅበራዊ ጠንቆች ለማስተናገድም ሆነ ለመሸከም አይፈቅዱም፡፡
ግብረሰዶምን እንኳንስ እንደ በጐ ምግባር እና ደዌ አስወጋጅ አስቦ ማስፋፋት ይቅርና አደጋውን በመገንዘብ በህግም ሆነ በማናቸውም መልኩ ባለበት መግታት የመጀመሪያውና አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው፡፡
ከዚህ ጋር ግብረ ሰዶማውያን የሆኑትን ዜጐች ፈቃደኛ ሆነው እስከተገኙ ድረስ በህክምና በሥነ ልቦና እና በማኅበራዊ ህይወት እንክብካቤ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ወደ ቀድሞውና ትክክለኛ ተፈጥሮአዊ ባህሪያቸው እንዲመለሱ ማድረግ፤ ግብረ ሰዶም መፈፀም ወዳለመፈለግ ነባር ባህሪያቸው መመለስ፤ የኅብረተሰቡን ተፈጥሮአዊና ነባራዊ ባህላዊና ማኅበራዊ… ክቡር እሴቶች መኮትኮትና ማበልፀግ ከነዚህ መወሳቶች ጋር አብሮ መታየትና መፋጠን ያለበት ቁርጥ ቁምጥ ያለ ትክክለኛና እውነተኛ ዘለቄታዊ የመፍትሔ አቅጣጫ ነው፡፡
ሠላምዎ ይብዛ በፍቅር
Soli. Deo. Gloria

 

Read 6733 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:24