Saturday, 22 February 2014 12:48

ጐንደርን ለ20 ዓመት ያስጐበኙት የቱሪዝም ከፍተኛ ኤክስፐርት

Written by 
Rate this item
(3 votes)

“ቱሪዝም አሁንም ገና ጨቅላ ነው”
የአገሪቱን ቱሪዝም ምቅር ቤት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው
አስጐብኚ ምንም ነገር አላውቅም ማለት የለበትም
ባለፈው የጥምቀት በዓል ሰሞን በጎንደር ከተከናወኑት ጉዳዮች አንዱ የጎንደር እህት ከተማ በሆነችው የፈረንሳይዋ ቬንሰን ከተማ ሁለገብ እድሳት ተደርጎለት የተጠናቀቀውን የ“ራስ ግንብ”ን ማስመረቅ ነበር፡፡
ግንቡ ራስ ሚካኤል ስሁልን ጨምሮ በርካታ የጎንደር ነገስታት ራሶች መኖርያ ስለነበር ነው፡፡ “ራስ ግንብ” የተባለው፡፡
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ለ20 ዓመታት የፋሲል አብያተ-መንግስትን በማስጎብኘት እውቅናና አድናቆትን ካተረፉት
የቱሪዝም ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ጌትነት ይግዛው ንጉሴ ጋር በጐንደር የቱሪዝም እንቅስቃሴ፣ በታሪካዊ ቅርሶች እድሳት፣
በአስጎብኝነት ህይወታቸው፣ እንዲሁም
በቱሪዝም ኢንዱስትሪና ተያያዥ
ጉዳዮች ዙርያ
ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡  

ወደ ፌደራል ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከመምጣትዎ በፊት የአፄ ፋሲል አብያተ መንግስትን ለ20 ዓመታት እንዳስጎበኙ ሰምቻለሁ፡፡ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ያጫውቱኝ …
ዌል! ይሄ ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ለ 21 ዓመታት የቱሪስት ጋይድ ነበርኩ፤ የጎንደር አካባቢ ሲኒየር ጋይድ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ከዛ በኋላ የጎንደር ዓለም አቀፍ ቅርስ አስተዳደር (የአብያተ መንግስታት አስተዳደር) ማናጀር ሆንኩኝ፡፡ የዩኔስኮም ተጠሪ (ፎካል ፐርሰን) ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ የጎንደር ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ በመሆናቸው፣ አሁን እኔ ስራዬን ወደ ፌደራል ባህልና ቱሪዝም በመቀየር የዛሬ አንድ ዓመት ከአምስት ወር አካባቢ ጀምሮ የቱሪዝም ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኜ እየሰራሁ ነው፡፡
ጎንደርን ለመጎብኘት እጅግ በርካታ ቱሪስቶች ይመጣሉ፤ አንዱ ሲሄድ ሌላው እየተተካ በቀን ለብዙ ጎብኚዎች ገለፃ ማድረግ ይኖርብዎታል፡፡ አድካሚነቱ ምን ያህል ነበር?
የማስጎብኘት ሥራ የዲፕሎማሲ ስራ እንደመሆኑ የአገርን ታሪክ፣ የአገርና ህዝብን ባህል፣ የአገርን ኢኮኖሚና ፖለቲካ እያገናዘቡ፣ ህዝብንና አገርን ማዕከል በማድረግ ገለፃ የሚደረግበት ነው፡፡ እንዳልሽው የተለያየ ዓይነት ቱሪስት ነው የሚመጣው፤ ከአገር ውስጥም ከውጭም ማለቴ ነው፡፡ እጅግ በርካት የሆኑ ሰዎችን አግኝቻለሁ። ለምሳሌ የአገር መሪዎች፣ በርካታ የጥናትና ምርምር ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ ለመዝናናትና አዲስ ተመክሮ ለመቅሰም የሚጓዙና መሰል ሰዎችን አግኝቻለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁለት አስርት ዓመታት ቀላል አይደሉም፡፡ እንደውም ዝም ብዬ ሳስበው የያኔው ስራዬ አሁን ካለሁበት ስራ አንፃር ሲታይ እጅግ ውስብስብ ነበር፡፡ ምክንያቱም በቱሪዝም ህግ መሰረት አንድ አስጎብኚ “አላውቅም” አይልም፡፡ ስለዚህ የምትጠየቂውን ሁሉ መመለስ ይጠበቅብሻል፡፡ ስትመልሺ ታዲያ ታሪክሽን እንዳታዛቢ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ፡፡ ምክንያቱም አሁን በዓለማችን ውስጥ ከፍተኛ የታሪክ ሽሚያ አለ፡፡ ሃይማኖትን፣ ዘርንና ቀለምን ሳታይ ለሁሉም እኩል መስተንግዶ መስጠት ግዴታሽ ነዉ። ከዚህ አንፃር ሳየው በጣም የተወሳሰበና አድካሚ ነበር፤ ሆኖም ኃላፊነቴን በአግባቡ ተወጥቻለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡
የትምህርት ዝግጅትዎ ከቱሪዝም ሙያ ጋር የተያያዘ ነው?
የትምህርት ዝግጅቴ ከቱሪዝምና ከቅርስ አስተዳደር የወጣ አይደለም፡፡ ከሰርተፍኬት ጀምሮ እስከ ማስተርስ ዲግሪ የሰራሁት ከቱሪዝምና ከቅርስ አስተዳደር እስከ ሄሪቴጅ ማኔጅመንት ድረስ ነው። ለምሳሌ ማስተርሴን የሰራሁት በቱሪዝምና ሄሪቴጅ ማኔጅመንት፣ የመጀመሪያ ዲግሪዬ በቱሪዝም ማኔጅመንት፣ ዲፕሎማዬ በእንግሊዝ አገር ከሚገኝ ካምብሪጅ ኮሌጅ በቱሪዝም እና ትራቭል ኤጀንት ማኔጅመንት ሲሆን ሰርተፍኬቴን ያገኘሁት ደግሞ በአገራችን በቱሪዝም ዘርፍ ፈር ቀዳጅ ከሆነው CTTI ቱሪስት ጋይድ በተባለ ዘርፍ ነው፡፡ እንደምታይው ከቱሪዝም አልወጣሁም ማለት ይቻላል፡፡
አንዳንድ ጎብኚዎች በተለይም ከአውሮፓ እና ከሌሎች አህጉራት የሚመጡት የግንቦቹን አሰራር ረቂቅነት ሲመለከቱ እጃችን አለበት በማለት እንደሚሟገቱ ሰምቻለሁ፡፡ እነዚህን ዓይነት ፈታኝ ጥያቄዎች እንዴት ነበር የሚጋፈጧቸው?  
የዓለም ስልጣኔ መጀመሪያ የአፍሪካ አህጉር እንደሆነ በማስረዳት እጀምራለሁ፡፡ ምክንያቱም አገራችን የሰው ዘር መገኛ ሆና በዓለም ከታወቀችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በሌላ ዓለም ቀደምት የሰው ዘር ቅሪት አልተገኘም፡፡ ስልጣኔ የሚነሳው ደግሞ ከሰው ልጅ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰው የኑሮ ጫናዎቹን ለማቃለል ደፋ ቀና ሲልና ለችግሮቹ መፍትሄ ሲፈልግ ነው ስልጣኔ እና ፈጠራ አብሮ የሚመጣው፡፡ የመጀመሪያው መልሴ ከላይ የገለፅኩት ነው፡፡ አውሮፓውያን የስልጣኔ ምንጭ አውሮፓ ናት ካሉ፣ ያ በእነሱ መልክ ነው የሚሆነው። አሜሪካኖችም እንዲያ ሲሉ በእነሱ መልክና እሳቤ ነው፡፡ ለምን ካልሽኝ … የዛሬ 400 ዓመት የተመሰረተች አገር፣ ከሶስት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ካላት አገር ጋር እኩል መሆን አትችልም፡፡ የሰው ልጅ እስካለ የኪነ-ህንፃም ሆነ ሌላም ስልጣኔ ይኖራል፡፡ ይህን ሳስረዳቸው የዚያ ጥበብና ስልጣኔ ባለቤት እንደሆንን ያምናሉ፤ የመንፈስ ቅናት አድሮባቸው ካልካዱ በስተቀር ማለቴ ነው፡፡
ከኪነ-ህንፃ ጋር በተያያዘ በተለይ የውጭ ጎብኚዎች ምን ይላሉ? እንዴት ነው ስሜታቸው? ይገርምሻል! አግራሞታቸው ሰፊ ነው፡፡ ጥቁር ህዝብ ቤተ-መንግስት ውስጥ የሚኖርባት የአፍሪካ አገር መሆኗ ይገርማቸዋል፡፡ በእነሱ እምነት ቤተ-መንግስት ውስጥ የሚኖረው አውሮፓዊ ብቻ ነው፤ የታላቋ ብሪታኒያ ነገስታቶች፣ የፈረንሳይ ነገስታቶች ብቻ ይመስሏቸዋል፡፡ ይታይሽ … ከ16ኛው ክ/ዘመን መጀመሪያ አንስቶ እስከ 17ኛው ክ/ዘመን፣ በጎንደርና አካባቢዋ ከፍተኛ ቤተ-መንግስታት ተሰርተው ነበር፤ ስልጣኔውም ነበር፡፡ እንደሚታየው ግንባታው ከኖራ ጋር ተቀላቅሎ ዝም ብሎ የተሰራ ሳይሆን የኪነ-ህንፃ ልዩነቱን ጠብቆ በጥልቅ ፈጠራ የተገነባ ነው እና የኪነ-ህንፃ ጥበብ ያረፈባቸው፣ ገላጭ የሆኑ ህብረ-ህንፃዎች ናቸው፡፡ ይህን በአግራሞትና በመደመም ነው የሚመለከቱት፡፡ ከዚህ አንፃር የሚያነሱት ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ማባሪያ የላቸውም፡፡
ከ400 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው የፋሲል አብያተ መንግስታት ግንባታዎችን ከአሁኑ ዘመን የኪነ-ጥበብ ህንፃ ጋር ማነፃፀር ይቻላል? እርስዎ ያነፃፅሩ ቢባሉ እንዴት ይገልፁታል?
እንግዲህ ውርስ ሊኖር ይችላል፤ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ውርስ ማለቴ ነው፡፡ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ውርስ ይኖራል ብሎ መናገር ይከብዳል፡፡ የጎንደርን ኪነ-ህንፃዎች አንቺ ቅድም እንደገለፅሽው የውጭ ዜጎች ናቸው የገነቡት ይላሉ፤ እኔ በፍፁም በዚህ አልስማማም፡፡ የኪነ-ህንፃ ጥበብ ልክ እንደ ሙዚቃ የአለም ቋንቋ ነው፡፡ አንዲት አገር የራሷ ወጥ የሆነ የኪነ-ጥበብ ህንፃ የላትም፡፡ በምን ምክንያት ካልሽ … በእኛ በሰዎች ምክንያት፡፡ ሰው የተለያየ የህይወት ውህደት አለው፤ ይዘዋወራል፡፡ ሲዘዋወር አካባቢውን ይመስላል፤ ከአካባቢው የሚወስደውም ጥበብ ይኖራል፡፡
ያ ሰው ከሄደበት አካባቢ የወረሰውን ጥበብ፣ ሌላ ቀን የራሱ አድርጎ ይተረጉመዋል፤ ነገር ግን የነበረበት አካባቢ ተፅዕኖ ያርፍበታል፡፡ በዚህ የተነሳ ኪነ-ህንፃ የዓለም ቋንቋ ነው ይሉታል፡፡ እዚህ አካባቢ የፖርቹጋል፣ የህንድ፣ የአርመንና የሞሪሽየስ ዜጎች ነበሩ፡፡ በእርግጥ ከጎንደር በፊት የተሰሩ የአክሱም፣ የላሊበላና የየሀ ህንፃዎች አሉ፡፡ ሰዎች እስካሉ ድረስ እንኳን ጥበብ ዘርም ይቀያየራሉ፤ ከዚህ አንፃር የጎንደር ኪነ-ህንፃዎች የእነዚህ አገር ሰዎች ተፅዕኖዎች አለበት ይባላል፡፡
ከስድስቱ የፋሲል አብያተ መንግስታት አንዱ፣ በህንዳዊ የኪነ-ህንፃ ባለሙያ እንደተሰራ ይነገራል። እውነት ነው?
እርግጥ አብዱልከሪም የሚባል ህንዳዊ የኪነ-ህንፃ ባለሙያ በአፄ ፋሲለደስ ዘመን ነበር፡፡ እንደሚታወቀው አፄ ፋሲል አባታቸው አፄ ሱስንዮስ የካቶሊክን እምነት ለማስፋፋት ጥረት ያደርጉ ስለነበር በ1622 (ቅድመ ክርስቶስ ልደት) በርካታ ህዝብ አልቋል፡፡ አፄ ፋሲል ይህን አልተቀበሉም ነበር፡፡ የንግስና ዙፋኑን ሲይዙ 7 ሺህ ገደማ የካቶሊክ ሚሽነሪዎችን ከኢትዮጵያ አስወጥተዋል፡፡ የዛን ጊዜ ታዲያ ኢትዮጵያ ቢያንስ ለ200 ዓመት በሯን ለአውሮፓውያን  ዘግታ ነበር፤ ይህ “የጨለማ ዘመን” እያሉ የሚጠሩት ነው፡፡ ስለዚህ አብዱልከሪም የተባለው ህንዳዊ ሰውዬ ምንም እንኳ ሙስሊም ቢሆንም በኪነ-ህንፃ ጥበብ የተካነ ስለነበር፤ ከአባ ገ/እግዚያብሔር ጋር በመሆን የንጉስ አፄ ፋሲልን ቤተ መንግስት እንዲሰራ ተደርጓል፡፡ በዚህ ምክንያት የህንዶች ኪነ-ህንፃ ተፅዕኖ አለበት፡፡
እስቲ ወደ እርስዎ የአስጎብኚነት ጊዜ እንመለስ። ዝነኛ አስጎብኚ እንደነበሩና እንደነ ሲኤንኤን፣ ቢቢሲ እና መሰል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ሲመጡ፣ በሰከንድ 120 ዶላር ለእርሶ እየከፈሉ በሙያዎ ያገለግሏቸው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እውነት ነው? እስቲ ያጫውቱኝ…
ይህ እንግዲህ በፈረንጆቹ 1991 ዓ.ም አካባቢ ነው፡፡ ያኔ “ፍሮም ፖል ቱ ፖል” የተሰኘ ፊልም ተሰርቶ ነበር፡፡ የዛን ጊዜ አብሬ ሰርቻለሁ፤ ክፍያው በሰከንድ ሳይሆን በሰዓት ነበር፡፡ በሰዓት 150 ዶላር! ለእኛ አገር ትልቅ ይመስላል እንጂ ለእነሱ በጣም ዝቅተኛ ክፍያ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ገና ከለንደን ከመነሳታቸው ከአንድ ወር በፊት ነው አፈላልገው ያገኙኝ፡፡ ከዚያም ያንን ፊልም ሰርተናል፡፡ ከቢቢሲ በኋላ ከሌሎችም የፊልም ቡድኖች ጋር ብዙ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ ለምሳሌ ከጀርመንና ከጣሊያን፣ የፊልም ቡድኖች ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ከፍተኛ የህይወት ልምድም አግኝቼበታለሁ፡፡
በጎንደር ከተማ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው መኪና የነበረዎት ብቸኛው ሰው እንደነበሩም ሰምቻለሁ …
(ሳ…ቅ!) በአንዳንድ አጋጣሚ በግልሽ ቢዝነስ ስትሰሪ ገንዘብ ታገኛለሽ፡፡ ስለዚህ መኪና መግዛት ቻልኩ፡፡ የዛን ጊዜ መኪና እንደአሁኑ ውድ አልነበረም፤ እኔ በገዛሁበት ወቅት 50ሺ ነበር ዋጋው። የዛሬ 12 ዓመት አካባቢ ማለት ነው፡፡ እርግጥ ያኔ ብሩ በደንብ ዋጋ ነበረው፡፡ ስለዚህ በዚያን ወቅት መኪና መግዛት ያን ያህል የሚያስደንቅ ነገር አልነበረም፡፡
የበፊቷ መኪና ተቀየረች ወይስ…
አልተቀየረችም ራሷ ናት፤ አዲስ አበባ ነው አሁን ያለችው፡፡
ስለ አገራችን ቱሪዝም ስታስብ የሚቆጭህ ነገር ምንድን ነው?
አሁን የሚቆጨኝ ነገር የለም! እኔ ቱሪዝምን በአስተሳሰብ ደረጃ ተረድቼ ስሰራ በነበረበት ወቅት ብዙ ሰው ገና አልተረዳውም ነበር፡፡ ቱሪዝምን የምቾት፣ የቅንጦትና የመዝናናት አድርገው የሚያዩት ወገኖች ነበሩ፡፡ ቱሪዝም ግን እንደዛ አይደለም፡፡ ቱሪዝም የስራ እድል ፈጣሪ ነው፤ ዳቦ ነው፤ ሰላም ነው፤ ሁሉም ነገር ማለት ነው፡፡ አገርሽ ውስጥ ያለውን የባህልና የታሪክ ቦታዎች የምትሸጭበትና የስራ እድል የሚፈጥር ኢንዱስትሪም ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የዚያን ጊዜ ሰዎች ቱሪዝምን የተረዱበት አስተሳሰብ ትክክል አልነበረም፡፡ እናም ሰው መቼ በትክክል እንደሚገባው፣ ገብቶትም መቼ ወደ ቢዝነስ እንደሚቀይረውና ተጠቃሚ የሚሆንበትን ቀን እናፍቅ ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ሁሉም ሰው ስለቱሪዝም ያወራል፡፡ ስለ ገፅታ ግንባታው፣ ስለ ስራ ፈጣሪነቱና ስለተያያዥ ጉዳዮች ሰው ሲናገር ስሰማ በጣም እደሰታለሁ፤
ምክንያቱም ማንም ሳይረዳሽ ብቻሽን ስለቱሪዝም የምታወሪበት ጊዜ አልፎ አሁን አጋር ስታገኚና ሰው ሲገባው በጣም ያስደስትሻል፡፡
በወሬ ብቻ ነው ወይስ በተግባርም ነው?
አገሪቱ በዚህ ቅኝት ውስጥ እየገባች ነው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ወደ ኢንዱስትሪው እንሸጋገራለን የሚል እቅድ ላይ ነው ያለነው፡፡ ወደ ኢንዱስትሪ ዘመን ሲገባ የበለጠ የሚያይለው የአገልግሎቱ ዘርፍ ነው፡፡ አሁን አገራችን ወደዚያ እየሄደች ነው፡፡ የቱሪስቱ ፍሰት እየጨመረ ነው። የበላይ አመራሮችና ውሳኔ ሰጪ አካላትም ስለቱሪዝም እያቀነቀኑ ነው፡፡ የትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ተቋቁሟል፡፡ ከዚያ ባሻገር የአገሪቱን የቱሪዝም ምክር ቤት የሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ይህን ስታይ አገሪቱ ወደ ቅኝቱ ገብታለች ማለት እችላለሁ፡፡ እና ቁጭት የለኝም፤ እንዲያውም በጣም ደስታ ነኝ፡፡
ጎንደር ባሏት ታሪካዊ መስህቦች የሚገባትን ያህል ተጠቅማለች ይላሉ?
እዚህ ላይ ነው ወሬ የምናቆመው! ከተማዋ ያላትን ሀብት በአግባቡ አልምታ፣ የህብረተሰቡን ግንዛቤ አሁን ካለው የበለጠ አስፍታ፣ ህዝቡን ቀጥተኛ ተጠቃሚ አድርጋ የማስኬድ ስራ ገና ይቀራታል፡፡ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ውስጥ የ30 እና የ40 ዓመት እድሜ ነው ያለው፡፡ ቅርስ አጠባበቅም እንደዚሁ! ምክንያቱም ቱሪዝም ካልሽ የምትሸጪው ቅርስ ስለሆነ፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ከ80 በላይ ብሄር ብሄረሰቦች፣ ከ35ሺህ በላይ ገዳማትና ቤተክርስቲያናት፣ ከ25 በላይ ከፍታቸው ከ4ሺህ ሜ በላይ የሆኑ ተራሮች፣ በምስራቅ አፍሪካ ትልቁ የስምጥ ሸለቆ ስክራች መነሻና ሌሎች አገሮችን የሚያቋርጥ ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም አሁንም በአይን የሚታይና አክቲቭ የሆነ እሳተ ጎመራ ያላት ናት። ይህም ሆኖ ቱሪዝም አሁንም በአገራችን ጨቅላ ነው፡፡ ይህንን ወደ ጥቅም ለመለወጥ እኔም፣ አንቺም ሌላውም በየሞያው የቤት ስራ አለበት፡፡ አለቀ፡፡
አሁን ቆመን የምንነጋገርበት ቦታ በእነ ፋሲለደስ ዘመን ራሶችና ተመሳሳይ ስልጣን የነበራቸው ሰዎች የሚኖሩበት “ራስ ግንብ” ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ቦታ የተገናኘነውም የጎንደር እህት ከተማ በሆነችው የፈረንሳይ ቬንሰን ከተማ እድሳት ተደርጎለት የምርቃት ስነ-ስርዓቱ በመሆኑ ነው፡፡ በእድሳቱ የተነሳ “ራስ ግንብ” ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አብያተ መንግስታት ምንነታቸውን እና የቀድሞ መስህብነታቸውን ያጣሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ ይህ እንዳይሆን ምን ምን ቅድመ ጥንቃቄዎች ይደረጋሉ?
አሪፍ ጥያቄ ነው! አገራችን እንደምታውቂው የገንዘብ እጥረት አለባት፡፡ ይህንን ነገር ለመሸፈን ከተሞች አንዳንድ ሁነቶችን ማዘጋጀት አለባቸው፡፡ የገንዘብ ሁኔታ እንዲጎለብት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመፍጠርና ስምምነቶችን በማድረግ፣ ከእነዚያ የአውሮፓ ከተሞች ተሞክሮዎችን ይወስዳሉ፤ በገንዘብም ይደጎማሉ፡፡ የጎንደር የቬንሰን ታሪክም ይሄ ነው፡፡
ይህን ፕሮጀክት የጀመሩት እርስዎ ነዎት ይባላል?   
ትክክል ነው! ፕሮጀክቱን የጀመርኩት እኔ ነኝ፡፡ ፕሮጀክቱን ቢያንስ ለስድስትና ለሰባት ወር ብቻዬን ነው የሰራሁት፤ ማንም ሰው አያውቅም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ነው በግልፅ ወደ ከንቲባ ጽ/ቤትና ወደ ከተማ አስተዳደሩ ያሸጋገርነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጎንደር የቬንስን እህት ከተማ እንደመሆኗ፣ የእነሱም ከተማ ስለሆነች ይህን ራስ ግንብ ማደስ እንደሚፈልጉና የሙዚየም፣ የሀንድክራፍትና የቱሪዝም ልማነት እንዲሆን ገንዘቡን አቀረቡ፡፡ የግንቡ ፕሮጀክት አራት ምዕራፍ ነው ያለው፡፡
አንዱ ሙዚየም ልማት ነው፡፡ ሁለተኛው የሀንድክራፍት ልማት ሲሆን ሶስተኛው ቱሪዝም ልማት ነው፡፡ አራተኛው ደግሞ ግንቡን መጠገን ነው፡፡ አሁን የተሰራው የፕሮጀክቱ አራተኛ መዕራፍ ነው፡፡ የግንቡ ጥገና አልቆ ዛሬ ሊመረቅ እስፍራው ተገኝተናል፡፡
ይህ ግንብ ሲጠገን፣ የዩኔስኮ ንብረት የዓለም ህዝብ ንብረት በመሆኑ፣ ሶስት ነገሮች መጠበቅ አለባቸው፡፡
አንደኛው ኦተንትሲቲ (የዱሮ ይዞታውን የጠበቀ መሆን አለበት)፣ ይህ ማለት ለእድሳቱ የምንጠቀመው እንጨት፣ ድንጋይና ሌሎች ቁሳቁሶችም ጭምር የዱሮ መሆን አለባቸው ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ድሮ ከነበረው ከባቢ ጋር ቅንጅት (integrity) ያለው መሆን አለበት።
ከኢትዮጵያ ኪነ-ህንፃ ሁኔታ ጋር የተስማማና የተቀናጀ መሆን አለበት፡፡ በሶስተኛ ደረጃ “ሲንክሮናይዜሽን” የሚባል ነገር አለ፡፡ ይሄ ማለት አዲስ እንጨት ለእድሳቱ ካስገባሽ አዲስ ለመሆኑ ምልክት ማስቀመጥ አለብሽ፡፡ እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ጥንቃቄዎች ተሟልተው ሲታደሱ ቅርሱ የቀደመ ምንነቱን አያጣም፡፡ ይህ ራስ ግንብም በዚህ መሰረት ነው የታደሰው፡፡
እርስዎ ሃገርዎን እንደሚያስጎበኙት ውጭ አገራትን የመጎብኘት ዕድል ገጥመዎታል? እስቲ ስለሌሎች አገራት አስጎብኚዎች ይንገሩኝ…
ለጉብኝት የሄድኩባቸው የውጭ አገሮች ብዙ ላይሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በሌላም ስራ የሄድኩባቸው ብዙ ቦታዎች አሉ፡፡ ከአፍሪካ ብንጀምር ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዚምባብዌ… ወደ አውሮፓ ስንመጣ ትምህርቴን አልጨረስኩም እንጂ የመጀመሪያ ስኮላርሺፕ ያገኘሁት ቡልጋሪያ ነበር። ምስራቅ አውሮፓን ብትወስጂ ሀንጋሪ፣ ራሺያ እና ሌሎችንም አውቃለሁ፡፡ ከምዕራብ አውሮፓ ፈረንሳይን አይቻለሁ፡፡ ሁለት ጊዜ የመሄድ እድል ገጥሞኛል፡፡ ህንድ ሄጃለሁ፡፡
እንግሊዝም እንዲሁ። የማስጎብኘት ሁኔታው እንደየአገሩ ይለያያል፡፡ በሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ ጉብኝት አድርጌያለሁ፤ ለቬንሰንም ጉዳይ ፈረንሳይ ሄጃለሁ፣ በአስጎብኚም ጎብኝቻለሁ፡፡ አስጎብኚ ለመሆን የታሪክ ሰው መሆን ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ?
የታሪክ ሰው መሆን ያን ያህል ላያስፈልግ ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ጥሩ ነው፡፡ ዋናው ልብ ልንል የሚገባው አስጎብኚ ሁሉም ነገር ማለት ነው፡፡ ቀደም ሲል እንዳልኩት አስጎብኚ ምንም ነገር “አላውቅም” ማለት የለበትም፡፡
ፖለቲከኛ፣ የባዮሎጂ ሰው፣ የጂኦሎጂ ሰው፣ አርኪዎሎጂስት፣ የታሪክ ሰው፣ …ሁሉንም መሆን አለበት፡፡
ዘርፈ-ብዙ እውቀት ያስፈልገዋል፡፡

Read 4209 times