Saturday, 10 December 2011 09:25

ሞረሽ! የስጋትና የትንበያ ስሞች! ወግ

Written by  በእምሻው ገ/ዮሐንስ
Rate this item
(0 votes)

የዛሬ ወጋችን እንግዲህ “ስምን መላዕክ ያወጣዋል” በሚል ተረት የተበጀለትን የስም አወጣጥ የሚያነሳሳ ነው፡፡ ስለስምና አሰያየም ጉዳይ ከተነሳ መቼስ “ውድነሽ በጣሙ”ን ይሁን “ቦጋለ መብራቱን አሊያም” “ይሁን በፈቃዱ” እና “አንተነህ ተስፋዬ”…የሚሉ ስሞችን ለማስታወስ የግድ የ”ሐዲስ አለማየሁ”ን “ፍቅር እስከመቃብር” መጥቀስ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡

ከርዕሰ - ጉዳያችን ጋራ የሚስማማ ዘፈን ለመምረጥ ሳስብ አንዱ ላይ ለመወሰን ድፍረት አጣሁና የጂጂ (እጅጋየሁ ሽባባውን) “ስም የለኝም፣ ስም የለኝም በቤቴ”፤ የሒሩት በቀለን “እንቅፋት ሲመታኝ ስሄድ በጐዳና፤ ድረስልኝ ብዬ በስምህ ልጣራ…” የሚለውንና የ”መሠንቆው ዳኛ” አርቲስት ኤልያስ ተባበል “የሀገሬ ሴቶች” በሚል አዝማች የኢትዮጵያውያን እንስት ስሞችን በዜማ በመደርደር፣ በአንድ ዘፈን ከድምፃዊነት ወደ “ሆምሩም ቲቸር”ነት ያደገበትን ዘፈን ጋባዥም፣ ተጋባዥም ሆነን በቀጥታ ወደ ወጋችን እንሻገር፡፡  
ስም ከመጠሪያ አልፎ ለመተንበያነት እንደሚያገለግል በዚሁ በዘመናችን ለማረጋገጥ “ይገደብ” የሚለውን የአቶ “አባይ”ን ልጅ ስም ማየቱ በቂ ይመስላል፡፡ “ስም ይቀድሞ ለገቢር” እንዲል መጽሐፍ፡፡
ስም አንዳንዴ የትውልድና የዘመን ማስታወሻ እንደሚሆን ለማሳየት ደግሞ “ነፃነት”፣ “ተፈሪ”፣ “ጠቅሌ”፣ “መኮንን”፣ “አብዮት”፣ “ደርጉ” የሚሉ ጥቂት ስሞችን ለአብነት ያህል መጥቀስ ይቻላል (እዚህች ላይ ማነሽ ወይዘሮ አብዮት ባለፈው ቀን “የተወለድሁት በ1974 ነው” ያልሽን ጉዳይ ሳስበው እንዲያው ቁጥሩ ባያጣላንም የአቆጣጠሩ ጉዳይ በሀገርኛ ነው በፈረንጅኛ የሚለውን እባክሽ ለይተሽ አስረጂኝ)
ከአባታቸው ስም ጋር ሲነበቡ በሚሰጡት ትርጓሜ፣ ወቅት አልፎ ወቅት ሲተካ፣ ከመጠሪያነታቸው ይልቅ ስጋትነታቸው የሚያይል ስሞችም አሉ፡፡ ለምሳሌ በአለፈው ስርአት አቶ በለጠ ለወለዷቸው ልጆች ያወጡላቸው “ደርጉ”፣ “አብዮት”፣ “መንግስቱ”ና “ደህንነት” የሚባሉ ስሞች በመንግስት ለውጥ ጊዜ እራሳቸው ለራሳቸው በፈጠሩት ስጋት ምክንያት አባት የአራቱን ልጆቻቸውን ስሞች በጋዜጣ አሳውጀው ለማስለወጥ አስበው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ በኋላ ላይ ግን ሌላ ብልሀት ዘየዱ፡፡ በልጆቻቸው አራት ስሞች ፈንታ የእሳቸውን አንድ ስም አሳውጀው አስለወጡ አሉ፡፡ “በለጠ”ን ወደ “ቀለጠ”፡፡ እናም ከዕዳም ከስጋትም ተገላገሉ፡፡ ከዚያም “ደርጉ ቀለጠ”፣ “አብዮት ቀለጠ”፣ “መንግስቱ ቀለጠ”፣ “ደህንነት ቀለጠ” እንዲሉ፡፡
ደግሞም ስም አንዳንዴ “ከመጠሪያነት ይልቅ ለመጠርጠሪያነት እንደሚሆንም የአንድ አብሮ አደጌ እውነተኛ ገጠመኝ በቂ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ልንገርህ የተባለው ይሄ አብሮ አደጌ፤ በአንድ ወቅት ወደ አንድ አገልግሎት መስጫ ተቋም ይሄድና ለስም መዝጋቢው ስሙን ለማስመዝገብ ይቀርባል፡፡
መዝጋቢው፡- “ስምህን ንገረኝ”
ወዳጄ፡- “ልንገርህ”
መዝጋቢው፡- “እሺ ንገረኝ”
ወዳጄ፡- “ልንገርህ አልኩህ”
መዝጋቢው፡- “እኔምኮ ንገረኝና ልመዝግብህ ነው ያልኩህ” ይሄኔ ብዙ፤ ብዙ ነገር መጠርጠር ይጀምራል፡፡ የወዳጄን አመሉንም ጤናውንም፡፡
“ልንገርህ”
“ንገረኝ”…በመጨረሻም አጠገባቸው ሆኖ ጉዳዩን ይከታተል የነበረና ነገሩን በተረዳ የሦስተኛ ሰው አስረጅነት ነገሩ ተብራርቶ ጓደኛዬ “ልንገርህ” የሚባለውን ስሙን ነግሮለት ተመዘገበ፡፡
አንዳንድ ስሞች ደግሞ አሉ “ለማቆላመጥ” ሲሞከሩ “የሚቆላመሙ”፡፡ “በአክብሮት ጥሪ” ጊዜም “አክሮባት” የሚሠሩ፡፡ ይኸንን ለመረዳት እንዲያው እስኪ ለምሳሌ “በድሉ” የሚለውን ስም አንዴ ብቻ አቆላምጣችሁ ለመጥራት ሞክሩ፡፡ እርግጠኛ ባልሆንም አትደግሙትም፡፡
ስም ትርጉሙ ከሚታወቅበት መደበኛ ቋንቋው ሲወጣ ለሰሚው ወይም ለጠሪው የሚፈጥርበትን ስሜት ለመጋራት “አባዲት” የሚለውን የትግርኛ ስም የአማርኛ አነባበብና ትርጉም እንዲሁም “ውዱ” የሚለውን የአማርኛ “ሸጋ” ስም “ሁዱ” ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ጋር ያለውን የድምጽ አንድነትና የኦሮምኛውን ትርጉም ማየቱ በቂ ነው፡፡ በአነሳነው ምሳሌ መሠረትም ለ”አቶ ውዱ” በአማርኛ ስሙ ሲሆን በኦሮምኛ ደግሞ “ስድቡ” ይሆናል ማለት ነው፡፡ (እዚህች ላይ ማነህ ውዱ የኔ ጌታ ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል እንጅ እኔ አንተን እንደስምህ ውድድ ነው እማረግህ!)
አንዳንድ ዕውቅ ሰዎቻችን ደግሞ በአባት ስም ዝምድና እየፈጠሩ መምጣታቸውን አስተውያለሁ፡፡ ከሙዚቃ ሰዎቻችን ለምሳሌ ነፃነት፣ ዳዊትና አበበ የአቶ መለሰ ልጆች ናቸው፡፡ አበበ እና ተመስገን ደግሞ የእናታቸውን እንጃ እንጂ በአባታቸው ግን ወንድማማች ናቸው - የአቶ ተካ ልጆች፡፡ እነ ፍቅርአዲስና ጌራወርቅ ደግሞ ከደግአረገ ጋር የአቶ ነቅአጥበብ ልጆች ይሆናሉ፡፡ በዚህ ታናሽና ታላቅ በማይለይበት የማዛመድ ሕግ… (ጐበዝ ማነህ! እዚህች ላይ ሁልጊዜ “ታላቅና ታናሽ” ሲባል አብሮ “ባይን ባይንህ” የሚሄደው “ሽንጥ” ከእንግዲህ እሴት ልጅ ወገብ ላይ ካልሆነ በአይንህም እምታየው አይመስለኝምና በጊዜ “ቨጂቴሪያን” ብትሆን ይመረጣል፡፡)
በአንድ አባት ልጅነት ጉዳይ ከሰዎች አልፈን ሀገሮችንም ብናይ የአቶ “ያ”ን ልጆች የሚያህል የለም፡፡ ከሀገሮች መሀከል ለምሳሌ ከእኛው ለመጀመር ኢትዮጵ ያ፣ ቀጥሎ ኬን ያ፣ ታንዛኒ ያ፣ ማሌዠ ያ፣ ራሽ ያ፣ አውስትራሊ ያ፣ ቡልጋሪ ያ፣ ላይቤሪ ያ (ማነህ ጐበዝ “ወርልደ ማፕ”ን ጠጥቼዋለሁ ስትለኝ የነበርከውን እስኪ ጥቂት የአቶ ያ ተጨማሪ ሀገሮችን ተንፍስብኝ፡፡ ለነገሩ እኔ እንኳን አጣጥመህ የጠጣኸውና ከትንፋሽህ ዘወትር የምቆጥርልህ የአለም ካርታ ሀገሮችን ሳይሆን የግብጦ፣ የነጭ ሽንኩርት፣ የኮሶ፣ የማር፣ የጤናዳም፣ የጥይት..አረቄ ሁሉ እንዳልተረፈህ ነው)
ከሀገራችን ከተሞችም ቢሆን የአቶ “ሌ”ን ልጆች የሚያህል አይኖርም፡፡ እህትማማቾቹ እነ ባ “ሌ”፣ መቀ “ሌ”፣ ሠገ”ሌ”፣ ነገ”ሌ”፣ ሠላ”ሌ”፣ ሞላ”ሌ” (ጐበዝ ማነህ በቀደምለት ሰዎች በባሌም በቦሌም ሲሉ ሰምተህ በባሌም በመቀሌም ብዬ ውጭ እወጣለሁ ስትለኝ የነበረው በባሌ እንኳን እኔንጃ የመቀሌው ግን ምናልባት አዲግራትና ዛላንበሳ ውጭ ሀገር ናቸው ትል እንደሆነ እንጃ! አንተው ታውቃለህ)
አንዳንዴ ደግሞ ስም እንደ ክፉ አድራጊ በክፉ ሊያሰጋ እሚችል መሆኑን ለማየትም “አሸባሪነት”ን ለማጥፋትና ደምስሶ ለማደር ስንትና ስንት ስልቶች ሲቀየሱበትና ሲዘየዱበት የሚውሉበት “አዳራሽ” ውስጥ፣ ያውም አሸባሪነትን የማጥፋት ስልት ቅየሳው አካል ሆኖ መልሶ ራሱ “አሸብር” የሚል ስም ይዞ መገኘት እንዴት ላይከብድ ይችላል? (ጐበዝ ማነህ አንተ አብሮ አደጌ” ፀጉር ቆራጩ” አሸብር፤ ለማንኛውም ይሄ በአለም ላይ አሸባሪነትን ለማጥፋት የሚቆፈረው ጉድጓድ ካልሞላ ቀጥሎ ለማሟያ እንዲሆን “አሸብር” የሚባሉ ስሞች ይግቡበት ሊባል እንደሚችል፣ ከጥንቸል ብዙ የምትማረው ያለ ይመስለኛል፡፡) ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ዝሆኖች ይታደኑ ሲባልና ዱሩ ሲሸበር ሰምታ ወ/ሪት ጥንቸል እግሬ አውጭኝ ትላለች፡፡ “አንቺ ደግሞ ምን ሆነሽ ነው ዝሆኖች ለሚታደኑት እንዲህ ልብሽ እስኪፈርስ እምትሮጭው” ቢሏት “እስኪጣራ ማን ይጉላላል” አለች አሉ፡፡
ስምና ማዕረግ እንዴት እንደሚጋጩ ለማየት ደግሞ ሦስት ጠጠር የተሰጠውና ቤተሰቦቹ በልጅነቱ “ሻምበል” ብለው ስም ያወጡለት ወታደር፤ ስሙን ከነማዕረጉ ለመጥራት ሂሳባዊ ስሌት መጠቀም የግድ ይላል፡፡ “ሻምበል2” ወይም “ሻምበል ስኩዌር” እንደማለት፡፡
እንደ እውነቱ ለልጆቻችን ስም ስናወጣ አፋችን እንዳመጣ ባይሆን ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ “ቡጢ”፣ “ጡጢ”፣ “ዙጢ” እያሉ ልጅን መጥራት ምን ማለት ነው? “አቶ ቡጢ” እና “ወ/ሮ ዙጢ” ለባለስሞቹ እስከሚገባኝ ድረስ “መጠሪያቸው” ሳይሆን “ማጠሪያቸው” ነው፡፡ (ማነህ ጐበዝ እንዲህ በየግሮሰሪው ሠርክ ለምትቀመቅመው ጠርሙስ ቢራ የምትመዠርጠው ቀያይ ባውንድ ሳይከብድህ፣ ለልጅህ ስም ግን ያውም በነፃ ከባዶ ጠርሙስ ያነሰ ስም ታወጣለህ!)
የአንዳንድ ክልሎችና ከተሞችን ስሞች ትርጉም ካጤንን ደግሞ ስም ለማስጠንቀቂያነት ወይም ለማስመዝገቢያነት እንደሚውል እናያለን፡፡ “ዳንግላ” በአገውኛ “ሌባ የለም”፤ “ቡታጅራ” በኦሮምኛ “ሽፍታ አለ” እና አሁንም “ወልቂጤ” “የርቀቱ አጋማሽ” ማለት ናቸው፡፡ (እዚህ ላይ ማነህ ጐበዝ ኑሮ መሮኛልና መሸፈቴ ነው እያልክ ታስወራ ነበር አሉ ወንድሜ እኔ በፍላጐትህ ጣልቃ መግባት አልፈልግም፤ ነገር ግን ለአሰብከው አላማ ምናልባት “ቡታጅራ”ን ከመረጥክ አንተን ጠቁሞ ለማስያዝ አገሩ ብቻውን በቂ መሆኑን ጠቆም ላደርግህ እወዳለሁ)፡፡
ትልልቅ ሀገሮችና ፓርቲዎች ሳይቀር ችግራቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተው በሚፈቱበት ዘመን እስኪ ለልጅ “በላቸው” እና “ድፋባቸው” የሚባሉ ስሞችን ማውጣት ለማን “ሀርድ” ለመስጠት ነው? (ጐበዝ ማናችሁ ወንድሞቼ፤ እነበላቸውስ ለእኔ እንደገባኝ ይሔ የስማችሁ ትርጉም እያደር “መፈሪያችሁ” ሳይሆን “ማፈሪያችሁ” እየሆነ ነውና እባካችሁ ከ”ሃፍረት” ለመውጣት በጊዜ መላ ምቱ፡፡ አንተ ደም መላሽስ ብትሆን ደግሞ የመቼው የሳይንስ ሰው ሆነህ ነው በ”ፕሎሞናሪ ቬን” ተሰይመህ መማሪያ የሆንከው? “ደሜ” ለማንኛውም ለአንተ ብዬ ነው እንጅ እምቢ ካልክ “ባየሎጂ”ን በአማርኛ ብዬሀለሁና አርፈህ ደምህን አመላልስ፡፡)
በአንዳንድ አካባቢ የተለያዩ ስሞች በቅጽል መጠሪያነት ሲውሉ የሚያመጡትን የትርጉም መፋለስ በጥቂቱ ለማየት ደግሞ አዲስ አበባ ወይም ሌላ ቦታ አንድ ወጣት በከባድ ሚዛን ስድብነት የሚያውቀውን “ውሻ”ን ወደ ባሌ ሮቤ እና ጐባ ብቅ ብሎ “አንተ የኔ ውሻ” የፍቅር መግለጫ መሆኑን ሲሰማ ነገሩ እስኪገባው ድረስ ቢያንስ በቅሬታ ፊቱ ቅጭም ማለቱ አይቀርም (ውድ ባሌዎች በዚህች አጋጣሚ የሰው ልጅ ባለውለታ የሆነውን እንስሳ የፍቅር መግለጫ በማድረጋችሁ ወድጃችኋለሁ! እናም ሁላችሁንም ቅቤ ካሳበደው ጭኮ እና ቡና በወተታችሁ ጋር “ይሕንንም ሚስተር” ኮፊ አናን ሳይሰሙ ሠላም ብያችኋለሁ፡፡ የዲንሾን ቆሎ ሳልዘነጋ ማለት ነው)፡፡
የሚገርማችሁ የሀገራችን የስም አወጣጥ የዋጋ ግሽበትንና የገንዘብ የመግዛት አቅምን ከግምት ውስጥ የሚያስገባም ጭምር ነበር፡፡ በልጅነታችን ለምሳሌ እነ “ሺብሬ”ና “ሚሊዬን” የሚባሉ ብዙ አብሮ አደጐች ነበሩን፡፡ አሁን አሁን በርግጥ እንዲህ የሚባሉ ስሞች ከ”ቦክስ ኦፊስ” እየወጡ ነው፡፡ ግን ለምንድነው የኑሮ ውድነቱን እና የብር ቅለቱን ተከትሎ ለልጆቻቸው “ቢሊዬን” እና “ትሪሊዬን” የሚባሉ መጠሪያዎችን የሰየሙ ወላጆች ያላጋጠሙኝ? (በዚህ አጋጣሚ አብሮአደጐቼ “ሺ ብሬ”ና “ሚሊዮን” እባካችሁ ተገናኝታችሁ ተደራጁና “አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዬን ብር” ሁኑ)፡፡
እንግዲህ ለተረፈው ቀጠሮ ይዘን ለዛሬ ከመሰነባበታችን በፊት የሁላችሁንም ስም ተዋውቄ ለመጥራት እንደ “ኤልያስ ተባበል” ትዕግስቱም፣ ጉልበቱም የለኝምና የሚወዱትን ሰው፣ የሚስጥር ወዳጅንና ሁነኛ ዘመድን በሽፍንፍን ለመጥራት እንደ ጐጃሞች እኔም “ሞረሽ” ብዬ ልሰናበታችሁ፡፡

 

Read 4854 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 09:32