Saturday, 22 February 2014 13:00

የቀልድ - ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ትንሽ     ስለ ቀልድ

ቀልድ መቼና እንዴት መጠቀም አለብን ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡ ቀልድ በመደበኛም ሆነ በኢመደበኛ ንግግር ውስጥ መሠረታዊ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ቀልድ ቅመም ነው፡፡ ወጥ በቅመም እንደሚጣፍጥ ሁሉ በጥንቃቄ መመረጥ፣ መመጠንና በትክክለኛው ሰዓት መጨመር ይኖርበታል፡፡ ቀልድ በትክክል ከተመጠነና ከተጨመረ በብርቱ ጥንቃቄ በበቃ ባለሙያ የተነገረውን ዲስኩር እንኳ የበለጠ አመርቂና ለታዳሚው እጅግ የሚጥም ያደርገዋል፡፡
ጆርጅ ጄሰል የተባለ ፀሐፊ፣ “ጥሩ ንግግር ልክ እንደጥሩ ካልሢ፣ ካልሢው በተሰራበት ጨርቅ ዓይነት ይወሰናል” ይላል፡፡ (የቻይናን አቃጣይ ካልሲዎች ልብ ይሏል) የቀልድ ጥግ የሚለው የአምድ-ሩብ፤ ታላላቅ ሰዎች፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች፣ የጥበብ ሰዎች፤ በንግግር፣ በውይይት፣ በስብሰባ መግቢያና ሌሎች የዕለት ተዕለት የንግግር እንቅስቃሴዎቻቸው ውስጥ፤ ትኩስ የቀልድ ምንጭ እንዲሆን የታሰበና የተዘጋጀ ነው። ቀልዶቹ በዘርፍ የተከፋፈሉ ስለሆነ በአጫጭር ጭውውቶች፣ ገጠመኞች፣ ተረቦች፣ ውጋውጎች /witticisms/፣ የነገር አዋቂዎች አባባሎች፣ ተረቶችና የአንዳንድ ሀሳቦች ትርጓሜዎች ወዘተ እየተመረጠ የሚቀርብበት ነው፡፡
በመሰረቱ ቀልድ መጠቀም ያለብን አንድን መልዕክት ፅኑ ነጥብ ለማጠንከር ስንሻ ወይም የተደበረና የተኮሳተረን ታዳሚ ላላ ለማድረግ ስናስብ፤ አሊያም የከረረና የመረረ ስሜቱን በተለየ አቅጣጫ ለመቃኘት ስንፈልግ ነው፡፡
ቀልድ ሌላውን ሰው ወይም ታዳሚ ለማጥቃት የምንጠቀምበት መሆን የለበትም፡፡ ስለዚህ ከመጠቀማችን በፊት የታዳሚው ምላሽ ምን ይሆናል? ታዳሚው  ምን ይሰማዋል? ብሎ ማሰብ መልካም ነው፡፡ ለማረጋገጥ በራሳችን የቅርብ ሰው ላይ ሞክረን የሚያስከፋው መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡
ቀልድ ለዛ የሚኖረው በቦታው ሲቀርብ፣ በሰዓቱ ስንገለገልበት ነው፡፡ ቀልድ በኮስታራ ንግግር ውስጥ ጣልቃ አስገብተን ከምንጠቀምበት ሰዎች ጀምሮ፤ ለመዝናኛ እንደማሺንገን የሚተኩሱ፣ እንደተልባ የሚንጣጡ ኮሜዲያኖች እስከሚጠቀሙበት ድረስ፤ የተለያየ የመገልገያ መንገድ አለው፡፡ ሆኖም ብዙዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የተመራመሩ ፀሐፍት ቀልዶች አንድ ላይ እንደጥይት ዝናር ከሚደረደሩ ከቁምነገር ንግግሮች መካከል ጣልቃ ቢገቡ እንደለዘዘ ቆሎ ጥርስ ከማስቸገር ይድናሉ ይላሉ፡፡
እኛም ይህንን መንፈስ በማጠንከር የተወሰኑ ቀልዶችን ብቻ በየጊዜው እናቀርብላችኋለን፡፡
የቀልዶቹ ዘርፎች ለምሳሌ አንድ ሳምንት በሰካራሞችና በአካል ዙሪያ፣ በሌላ ሳምንት በዶክተሮችና በሕክምና ዙሪያ፣ ቀጥሎ በባንክና በባንከሮች ዙሪያ፣ ከዚያ በነጋዴዎችና በንግድ ዙሪያ እንቀጥላለን፡፡ እናንተም ያጋጠማችሁን የሰማችኋቸውን ብትልኩልን ደስ ይለናል፡፡ ሣምንት እንጀምርላችኋለን፡፡

Read 7137 times