Tuesday, 04 March 2014 11:16

ቻልኩበት፣ ዘንድሮስ ቻልኩበት…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(11 votes)

ተሊከኞች’ ቋንቋ ወደዛ እየጎተተን ይመስላል፡፡
እናላችሁ…‘በዛችኛዋ’ ባልፈረሰችው ሩስያ ጊዜ ነው አሉ፡፡ የአንድ አካባቢ የፓርቲ ጸሀፊ ሩስያ ወደፊት ገነት እንደምትሆን እየነገራቸው ነው፡፡
“ጓዶች፣ አሁን የያዝነው የአምስተ ዓመት ዕቅድ ሲጠናቀቅ ሁሉም ሰው የራሱ አፓርትመንት ይኖረዋል፡፡ የሚቀጥለው የአምስት ዓመት ፕላን ሲጠናቀቅ ሁሉም ሰው የየራሱ መኪና ይኖረዋል። ተከታዩ የአምስት ዓመት ፕላን ሲጠናቀቅ ደግሞ ሁሉም ሰው የየራሱ አውሮፕላን ይኖረዋል፣” ይልላችኋል፡፡
ይሄኔ ከሠራተኞቹ መሀል አንዱ “ሌላውስ ይሁን፣ አውሮፕላን ግን ምን ይሠራልናል?” ብሎ ይጠይቃል፡፡
የፓርቲው ጸሀፊ ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“ጓዶች አይታያችሁም እንዴ! ለምሳሌ በእናንተ ከተማ የድንች እጥረት ይፈጠራል፡፡ ምንም ችግር አይኖርም! የየራሳችሁን አውሮፕላን እያበረራችሁ ሞስኮ ሄዳችሁ ድንች ገዝታችሁ ትመለሳለችሁ፡፡ አሁን ገባችሁ!”
አሪፍ አይደል!… እናላችሁ… ዘንድሮ ብዙ ነገሮችን “ለምን እንዲህ ይሆናል?” ብለን ስንጠይቅ መልሱ ‘በግል አውሮፕላን ሄዶ ድንች መግዛት…’ አይነት እየሆነብን ነው፡፡ መሥሪያ ቤቶች የሚነግሩን ከእንዲህ ያህል ወራት በኋላ፣ ከእንዲህ ያህል ዓመታት በኋላ ነገሮች የ‘ምድራዊ ገነት’ አይነት እንደሚሆኑ ነው፡፡ እኛ የቸገረን… የተበላሹት ነገሮች ዛሬና ነገ እንዴት እንደሚስተካከሉ ሆኖ የሚነገረን ደግሞ ከሆነ ጊዜ በኋላ እንዴት ‘የአፍሪካ ቁንጮ’ እንደምንሆን ነው፡፡
ነገርዬውማ…አለ አይደል…
ቻልኩበት፣ ዘንድሮስ ቻልኩበት
የኑሮ አያያዙን፣ እኔም አወቅሁበት
አይነት ነው፡ የያዙት መንበር ላይ ለመቆየት፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በየጊዜው የሚወጡት ዓለም አቀፍ መለኪያዎች የሚያሳዩት፣ አይደለም ወደ አፍሪካ ቁንጮነት ልንጠጋ ቀርቶ፣ በብዙ ነገሮች ከመጫወቻ ሜዳ ልንወጣ እየተንሸራተትን መሆኑን ነው፡፡ ወደ ቁንጮነት ከመውጣታችን በፊት…መጀመሪያ ተንሸራተን “ያሆ በሌ” እያልን ከጨዋታው ሜዳ እንዳንወጣ ቧጠንም ነክሰንም መትረፉ ነው፡፡
ስሙኝማ…አንዳንድ ጊዜ የልጅነት ጨዋታ አይናፍቃችሁም! ያኔ…አለ አይደል… “በዘፈን ህንድ አንደኛ፣ ሱዳን ሁለተኛ፣ ኢትዮዽያ ሦስተኛ…” የሚባልበት ‘የዋህ ዘመን’ አሪፍ ነበር፡፡ “ለምን?” “እንዴት?” “በምን ምክንያት?” ምናምን ብሎ የሚጠይቅ የለማ! ዘንድሮ ግን… “አገራችን በዘፈን ሦስተኛ…” ብለው ‘አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች’ ቢናገሩት እንኳን… ህዝባችን እንዲህ በቀላሉ  መሸወድ ትቷል፡፡ እናማ… “ከዚህ ያህል ዓመት በኋላ አፍሪካ አናት ላይ ቂብ ባንል ምን አሉ በሉን…” አይነት ነገር ቀሺም ነው፡፡
ነገርዬው ግን… አለ አይደል…
ቻልኩበት፣ ዘንድሮስ ቻልኩበት
የኑሮ አያያዙን፣ እኔም አወቅሁበት
ሆኗል፡ ምክንያቱም አደባባይ ላይ ‘እንዲህ እናደርጋለልን…’ ‘እንዲህ እንፈጥራልን…’ ምናምን ማለቱ ብቻ ‘ሲቪ’ የሚያወፍር ይመስላል፡፡
ዘንድሮም…የተያዘውን እንኳን በቅጡ መሥራት እያቀተ “ከአፍሪካ ቁንጮ…”  “ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ…” ምናምን የሚለው ነገር ስልችት እያለን ነው፡፡
ደግሞላችሁ…ይቺን አንድ ሁለቴ ያወራናት ቢሆንም እንድገማትማ፡፡ አንድ ሩሲያዊ፣ አንድ ፈረንሣዊና አንድ እንግሊዛዊ ስለ ዓዳም ዜግነት እየተወያዩ ነው፡፡ ፈረንሣዊው “አዳም ፈረንሣዊ ነው፣ ከሔዋን ጋር እንዴት ቅልጥ ያለ ፍቅር እንደሠራ አላያችሁም!” ይላል፡
እንግሊዛዊው ደግሞ… “በእርግጠኝነት አዳም እንግሊዛዊ ነው፡፡ አንዲት አፕል ብቻ ብትኖረው ጨዋ ከመሆኑ የተነሳ ለሔዋን ሰጣት!” ይላል፡፡
ሩስያዊ ሆዬ በተራው ምን ቢል ጥሩ ነው…“አዳም በእርግጠኝነት ሩስያዊ መሆን አለበት። ከአንዲት አፕል በቀር ምን ሳይኖረውና ራቁቱን ጫካ ውስጥ እየተንገላወደ መንግሥተ ሰማያት ያለ የሚመስለው ሩስያዊ ብቻ ነው፡፡”
ዘንድሮ ራቁታችንን እየተንገላወድንና አንዲት እስር በለጬ ስለያዝን… “መንግሥተ ሰማያት ነው ያላችሁት…” የሚሉን ብዙ አሉ፡፡ የተራገፈ የእህል ጆንያችንን እኛ እያወቅነው… እሪታውን የሚያቀልጠውን ሆዳችንን እኛ እያወቅነው…“መንግሥተ ሰማያት ናችሁ…” የሚሉን ‘አዳሞች’ ሞልተዋል፡፡
ነገርዬውማ…አለ አይደል…
ቻልኩበት፣ ዘንድሮስ ቻልኩበት
የኑሮ አያያዙን፣ እኔም አወቅሁበት
ነው፡፡ እናላችሁ…ከ‘ወደላይ አካባቢ’ የምንሰማቸው ዲስኩሮች…አለ አይደል… “…የኑሮ አያያዙን፣ እኔም አወቅሁበት…” ናቸው፡፡ ወሬው ስለ እኛ ቢመስልም ስለ አኛ አይደለም…ስለ ተናጋሪዎቹ ነው፡፡  
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ይሞትና መንግሥተ ሰማያት ይላካል፡፡ ከጊዜ በኋላ በአበባ የተዋበውና ምንም አይነት ጭንቀት የሌለበት መንግሥተ ሰማያት ስልችት ይለውና እንደ ቱሪስት ገሀነምን ለማየት ፈቃድ ይጠይቃል፡፡ እግዚአብሔርም ይፈቅድለታል፡፡ ገሀነም ሲደርስ ህዝቡ ሆዬ እያውካካ ካርታ ሲጫወት፣ ወይን ጠጅ ሲጠጣ፣ ፍቅር ሲሠራ ይመለከታል፡፡ ያየውን ሁሉ በጣም ስለወደደው መንግሥተ ሰማያት ሲመለስ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ገሀነም ለመዘዋወር ጥያቄ አቅርቦ ይፈቀድለታል፡፡
እናላችሁ…ጓዙን ጠቅልሎ ይመለሳል፡፡ ልክ ገሀነም በር ላይ ሲደርስ ዘቦቹ ይይዙትና በሚንተከተክ ሬንጅ በርሜል ውስጥ ሊከቱት ያንጠለጥሉታል፡፡
እሱም ይጮሀል… “ተሳስታችኋል! እረፉ እንጂ! ባለፈው ስጎበኝ ሰዎች ቮድካ ሲጠጡ፣ ካርታ ሲጫወቱና ፍቅር ሲሠሩ ተመልክቻለሁ፡፡ እዛ ውሰዱኝ…” ይላል፡፡
ዘቦቹ ምን ብለው ቢመልሱለት ጥሩ ነው…“አታምታታዋ! ቀደም ሲል ያየኸው ቦታ ለቱሪስቶች የተዘጋጀ ነው፣ የዜጎች መኖሪያ ይህኛው ነው…” ብለው ‘ለዜጎች የተዘጋጀው በርሜል’ ውስጥ ወረወሩት፡፡
ዘንድሮ…አለ አይደል…እኛም ዘንድ ‘የፈረንጅ’ና የዜጎች የሚል አስተሳሰብ በየቦታው ነው የሚገጥማችሁ፡፡ በአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ለፈረንጅ እጥፍ ዘርጋ የሚሉ፣ እኛን በግልምጫ አንስተው የሚያፈርጡ መአት ናቸው፡፡ እና በተዘዋዋሪ ‘ለዜጎች የተዘጋጀው በርሜል’ ውስጥ ይከቱናል፡፡
ታዲያላችሁ…አንዳንዴ ትላልቅ ስብሰባዎች ሲኖር ከቤት እንኳን ለመውጣት የሚያስጠላን ‘ለዜጎች የተዘጋጀው በርሜል’ አይነት ነገር ስለሚገጥመን ነው፡፡ አንዳንዴ “ከመንገድ ራቅ በሉ…” ስንባል እንኳን ክብራችን ተጠብቆ፣ አገሩ የእኛ መሆኑ ታውቆ ምናምን ሳይሆን ልክ ድንበር ጥሰን፣ ኬላ ሰብረን የእኛ ባልሆነ በሌላ ሰው ይዞታ ውስጥ ልንገባ የሞከርን ያስመስሉናል፡፡
ኮሚክ ነገር እኮ ነው…አብዛኞቹ አገሮች ቅድሚያ የሚያሳስባቸው የዜጎቻቸው ደህንነትና ምቾት ነው። እንግዳ ቢቀበሉም ከዜጋቸው መብት ላይ ይቺን ታክል ሳይቀንሱ ነው፡፡ እኛ ዘንድ ግን…ተቃራኒ ነው። ‘እትብታችን በተቀበረባት’ ምድር እንደ ባይተዋር ነገር ስንታይና ‘ለዜጎች ወደተዘጋጀው በርሜል’ ስንገፋ ምነዋ አይከፋንማ!
እናላችሁ…ብዙዎች ታዲያ ባይተዋርነት እንዲሰማን የሚያደርጉን ጉዳዩ ስለ እኛ ሳይሆን፣ ስለ እነሱ ነው፡፡ ነገርዬው… አለ አይደል…
ቻልኩበት፣ ዘንድሮስ ቻልኩበት
የኑሮ አያያዙን፣ እኔም አወቅሁበት
ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…አንድ ጊዜ ስታሊን የህዝቡን ስሜት ለማወቅ ብሎ እንደ ምንም ተሸፋፍኖ ራሱን ይለውጥና አንድ ሲኒማ ቤት ይገባል፡፡ ፊልሙ ከመጀመሩ በፊት ስክሪኑ ላይ የስታሊን ፎቶ በትልቁ እየታየ ተመልካቹ ተነስቶ የሩስያን የህዝብ መዝሙር ይዘምራል፡፡ ስታሊን ብቻ በተቀመጠበት ይቆያል። ይሄኔ ከኋላው የነበረ ሰው ወደ ጆሮው ጠጋ ብሎ ምን ይለዋል መሰላችሁ… “እኛም እንዳንተ ይሄንን አረመኔ አንወደውም፣ ግን እንዳትበላ ቆመህ ብትዘምር ይሻልሀል፡፡”
እናላችሁ…እዚቹ አገር ላይ “እንዳትበላ ቆመህ ዘምር…” አይነት ነገር በየቦታው የምታዩት ነው። የክብር እንግዳው ሲመጡ አዳራሹን በጭብጨባ ማደባለቅ በአብዛኛው ከአንጀት ሳይሆን… አለ አይደል… “እንዳትበላ ቆመህ ዘምር…” አይነት ነገር ነው፡፡ ‘በከፍተኛው ባለስልጣን’ ሳቅ ሳይሆን ሰቆቃ በሚያስከትል ንግግር ሆድ እስኪቆስል መሳቅ…አለ አይደል… “እንዳትበላ ቆመህ ዘምር…” አይነት ነገር ነው፡፡ (ቦሶች ሆይ…ሆዳችን እስኪቆስል የምንንከተከተው ቀልዳችሁ ኮርኩሮን ሳይሆን… የ“እንዳትበላ ቆመህ ዘምር…” ታክቲክና ስትራቴጂ እንደሆነ ይታወቅልን፡፡
እናላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ነገር…
ቻልኩበት፣ ዘንድሮስ ቻልኩበት
የኑሮ አያያዙን፣ እኔም አወቅሁበት
ሆኖ እህሉን ከገለባ መለየት አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
እንኳን ለአድዋ የድል በዓል አደረሳችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5102 times