Tuesday, 04 March 2014 11:42

የድምፅ መቅረጫው ማሽን

Written by  ደራሲ፡- ጆን ስታንቤክ ተርጓሚ፡- አሸናፊ አሰፋ
Rate this item
(1 Vote)

(ጆን ስታንቤክ አሜሪካዊ ደራሲ ነው፡፡ አሜሪካ ካፈራቻቸው ምርጥ ደራሲያን አንዱ ነው፡፡ በ1902 ካሊፎርኒያ ውስጥ ተወለደ፤ በ1962 ኖቤል ተሸለመ፤ በ1968 ሞተ፡፡ በህይወት እያሉ አለም አቀፍ እውቅና ካገኙ ጥቂት ደራሲያን አንዱ ነው)
ለሥራ ተቀይሬ ሎማ ወደ ምትባል ከተማ ሄድኩ፤ ወይም መጣሁ፡፡ ሎማ በጣም ትንሽ ከተማ ናት፡፡ ቢበዛ ሁለት መቶ ሰዎች ቢኖሩባት ነው፤ ከመኖሪያ ቤቶቹ ሌላ ከተማዋ ውስጥ ያሉት አንድ ቤተክርስቲያን፣ ሁለት ሱቆች፣ አንድ የስብሰባ አዳራሽ፣ አንድ የህንፃ መሳሪያዎች መደብር እና ቡፋሎ የሚባል አንድ የመጠጥ ግሮሰሪ ብቻ ናቸው፤ በቃ፡፡
ሲመሽ፣ ከስራ መልስ፣ የትም መሄጃ የለም፡፡ መሄጃ ወይም ሌላ ምንም መዝናኛ ስለሌለ ሁሉም ቡፋሎ ግሮሰሪ ይታደማል፡፡ በእያንዳንዱ ምሽት፣ እያንዳንዱ መለኪያ መጨበጥ የሚችል የሎማ ነዋሪ፣ ቡፋሎ ግሮሰሪ ጎራ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ወደ ቡፋሎ ግሮሰሪ ጎራ ስትሉ ካርል ዘረጦ በተሰላቸ፣ ደባሪ ፈገግታ ይቀበላችኋል፡፡ ካርል ዘረጦ የቡፋሎ ግሮሰሪ ብቸኛ ባለቤት እና ብቸኛ አስተናጋጅ ነው፡፡
እንደ እኔ ግሮሰሪ እና መጠጥ ለሚወድ እና ለሚያዘወትር ሰው እንኳ ቡፋሎ ግሮሰሪ ደባሪ ቦታ ነው፤ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ከተማዋ ሎማ ናታ! የት ትሄዳለህ?! አንደኛ፡- ደንበኞቹ የታወቁ ናቸው፤ ሁለተኛ፡- አስተናጋጁ ካርል ዘረጦ ነው፤ ሶስተኛ፡- መጠጡ አንድ አይነት ቀሽም ውስኪ ነው፤ አራተኛ፡- ዋጋው ርካሽ አይደለም። በቃ ሲመሽ ቀስ እያልክ፣ እየደበረህ ወደ ቡፋሎ ግሮሰሪ ታመራለህ፡፡ ልክ በሩን ስትከፍት ካርል ዘረጦ በተለመደው ፈገግታው ይቀበልሃል፤ ሰዎች መጠጥ ይዘው ሲንሾካሾኩ፣ ሲንጫጩ ትደርሳለህ፤ ያኔ በትንሹም ቢሆን ድብርትህ ይለቅሃል፡፡
አንድ በጣም የሚገርመኝ የካርል ዘረጦ ባህሪ አለ፤ ግሮሰሪው ውስጥ የሚሸጠው ውስኪ ብቻ ነው፣ ለዚያውም አንድ አይነት ውስኪ ብቻ፣ እንዲያም ሆኖ አዲስም ይሁን ነባር ደንበኛ በመጣ ቁጥር ካርል ዘረጦ፡- “ምን ልታዘዝ?!” ይላል፤ ለዚያውም በአጽንኦት፡፡ ይኼ የካርል ዘረጦ ባህሪ ሁሌ ይገርመኛል፡፡
ሎማ እንደመጣሁ ሰሞን ሜ ሮሜሮ የምትባል ልጅ ተዋወቅሁ፡፡ ግማሿ ሚክሲኳዊት የሆነች ቆንጅዬ ነገር ናት፡፡ ከሥራ ስወጣ ተያይዘን ወደ ከተማዋ ጭር ያለ አካባቢ የእግር ጉዞ እናደርጋለን … ከዚያ እሷን ወደ እቤቷ ሸኝቻት እንደፈረደብኝ ወደ ቡፋሎ ግሮሰሪ እሄዳለሁ፡፡
ዛሬም እንደተለመደው ሜ ሮሜሮን ወደ እቤቷ ሸኝቻት ወደ ቡፋሎ ግሮሰሪ አመራሁ፡፡ አሌክስ ሀትርኔል አጠገብ ያልተያዘ ወንበር ነበር፤ እዚያ ተቀመጥኩ፡፡ አሌክስ ሀርትኔል እዚሁ ግሮሰሪ ውስጥ የተዋወቅሁት የሎማ ነዋሪ ነው፤ ታዋቂ ገበሬ ነው፤ ምርጥ ሰው ነው፡፡
ካልር ዘረጦ ውስኪ እየቀዳልኝ፡- “ምን ልታዘዝ?” አለኝ፡፡ ፈገግ አልኩ፣ የንዴት ፈገግታ። እኔና አሌክስ ውስኪያችንን እየጠጣን ይሄንንም ያንንም እየቀባጠርን ሳለ የቡፋሎ ግሮሰሪ በር በቀስታ ተከፈተ እና የሆነ ሰው ገባ፡፡ ግሮሰሪዋ ውስጥ የሚገርም ጸጥታ ሰፈነ፡፡
አሌክስ በክንዱ ጎሸም አድርጎኝ፡-
“ጆኒ ድቡ ነው፡፡” አለኝ፡፡
ሰውየውን አየሁት፡፡ ቅጽል ስሙ በደንብ ይገልጸዋል፤ ቁርጥ ድብ ነው የሚመስለው፤ ግዙፍ፣ ሳቂታ እና ጅል ድብ ይመስላል፡፡ ጥቁር ፀጉር የተከመረበት ትልቅ አናቱ ወደፊት ዘንበል ብሏል፤ እጆቹ ወደጎኖቹ ተንከርፍፈዋል፤ ሁሌ በአራት እግሮቹ የሚራመድ አሁን ግን የሰርከስ ትርኢት ለማሳየት፣ እኛን ለማሳቅ በሁለት እግሮቹ የቆመ ይመስላል፡፡ ቅልጥሞቹ አጭር እና ሽብርክ ያሉ ናቸው፡፡ የእግሮቹ ተፈጥሮ የተለመደ አይደለም፤ እግሮቹ አራት መዐዘን ናቸው፤ እርዝመቱም ወርዱም እኩል የሆነ አራት መዐዘን፤ ስኩዌር፡፡ ጫማ አለበሰም፡፡ የነተበ ጥቁር ሱፍ ለብሷል፡፡
በጣም ትንንሽ ጆሮዎች አሉት፡፡ እንዲህ አይነት ቅርፅ እና መጠን ያላቸው ጆሮዎች አይቼ አላውቅም።
ጆኒ ድቡ ልክ ዘገምተኞች እንደሚያደርጉት የተንከረፈፉ እጆቹን እያወዛወዘ ቆመ፡፡ ዘገምተኞች ፊት ላይ ሁሌ የሚታየው ደስ የሚል ፈገግታ ፊቱ ላይ አለ፡፡ ወደ ግሮሰሪው መሀል ተራመደ፡፡ ግዝፈቱን እና አኳኋኑን ላየ የሚራመድ ሰው ሳይሆን የሚሳብ እንስሳ ነው የሚመስለው፡፡ ግሮሰሪው መሀል ሲደርስ ቆመ፡፡ በትንንሽ፣ ብሩህ አይኖቹ ጠጪዎቹን ቃኘ፡፡ አስተያየቱ የልምምጥ፣ የቅልውጥና ነው፡፡ እባካችሁ ጋብዙኝ አይነት፡፡ በመጨረሻም እንዲህ አለ፡-
“ጋብዙኝ፤ ውስኪ ጋብዙኝ”
የሎማ ነዋሪዎች ደጎች አይደሉም፡፡ አንዱ አንዱን የሚጋብዘው እንደሚጋብዘው እርግጠኛ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ይግረምህ ሲለኝ ነው መሰለኝ አንዱ ጠጪ ለጆኒ ድቡ የአንድ መለኪያ ከፈለለት። ካርል ዘርጦ፡- “ምን ልታዘዝ?” እያለ ቀዳለት፡፡ አስገራሚው ፍጡር የተቀዳለትን ውስኪ በአንድ ትንፋሽ ጨለጠው፡፡
“ምን አይነቱ ፍጡር ነው?!” የሚል ነገር አመለጠኝ፡፡ አሌክስ እንደ መጀመሪያው ጎሸም አድርጎኝ “ቆይ ዝም በል” አለኝ፡፡
“ምን ሊያሰማን ይሆን? ምን ሊያሰማን ይሆን? ምን ሊያሰማን ይሆን? …” እያሉ ጠጪዎቹ ሲንሾካሾኩ ሰማሁ፡፡
ጆኒ ድቡ እየተሳበ ሄዶ ጥግ መሬት ላይ ተቀመጠ። ከዚያ ማውራት ጀመረ፤ በተለያዩ ቅላፄዎች ነው የሚያወራው፤ በወንድ እና በሴት ቅላፄ፤ ድምጾቹን በደንብ አውቃቸዋለሁ፡፡
“እዚህ ደባሪ ከተማ ውስጥ አንቺ ባትኖሪልኝ ኖሮ ምን እሆን ነበር?”
“አትደልለኝ”
“የምሬን ነው፡፡”
“ወደኸኛል?!”
“ግጥም አድርጌ ነዋ፡፡”
“አምራለሁ እንዴ?!”
“ለዚህ ከተማ ያለሽው ጌጥ አንቺ ብቻ ነሽ፡፡”
በጣም እርግጠኛ ነኝ ለደቂቃዎች እራሴን ስቼያለሁ፡፡ ጆሮዎቼ ጋሉ፤ ፊቴ ቀላ፡፡ ከጆኒ ድቡ ይፈልቅ የነበረው ድምጽ የእኔ እና የሜ ሮሜሮ ነበር። የራሴ ቃላት፣ የራሴ ቅላፄ፤ የሜ ሮሜሮ ቃላት፣ የሜ ሮሜሮ ቅላፄ፤ አንድም ሳይዛነፍ፡፡ ዛሬ ማታ ወደ ቤቷ ስሸኛት ያወራነውን ነው መልሼ የሰማሁት፡፡
ይህን ዝተት ሰው እያየሁት ባይሆን ኖሮ፣ የሜ ሮሜሮን ድምጽ ስሰማ ልመልስላት ዳድቶኝ ሁሉ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡-
“ግን ወደኸኛል?” ስትል፡-
“ግጥም አድርጌ ነዋ” ልል ነበር፤ አጠገቤ ያለች መስሎኝ፡፡
ጆኒ ድቡ ወሬውን ቀጠለ፡፡ ምን ጆኒ ድቡ ወሬውን ቀጠለ እላለሁ? እኔ እና ሜ ሮሜሮ ማውራት ቀጠልን ልበል እንጂ፡፡ እራሴ እንዳላልኳቸው ነገር ያልኳቸውን ነገር ከጆኒ ድቡ ስሰማ አፈርኩ፣ ተሸማቀቅሁ፣ ደበረኝ፡፡ ስንሳሳም ያወጣነውን ድምጽ እና አተነፋፈሳችንን ሳይቀር አለው፡፡
ቀጠለ ጆኒ ድቡ፤ ላስቆመው አልችልም፤ ሁሉም በጉጉት እየሰሙት ነው፣ ላስቆመው  ብሞክር እርግጠኛ ነኝ አንዳቸው ወይ ሁላቸውም ይጣሉኛል፤ ኧረ እንዲያውም ይደበድቡኛል፤ አኳኋናቸው እንዲያ ነበር፡፡
ከጆኒ ድቡ የሰማሁት የራሴ ድምጽ (እሱ ይበለው እንጂ የራሴ ድምጽ ነው) ድለላ፣ ውሸት፣ ማስመሰል አለበት፤ ደሞ ፈታ ብዬ አልነበረም የማወራው፡፡
ተመስገን፡፡ የማያልቅ ነገር የለም፤ ጆኒ ድቡ አውርቶ ጨረሰ፡፡ ምን ጆኒ ድቡ አውርቶ ጨረሰ እላለሁ? እኔ እና ሜ ሮሜሮ አውርተን ጨረስን ልበል እንጂ፡፡ ሜ ሮሜሮ ወይ ቤተሰቦቿ ይህን ጉድ ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? ይህን የሰው ድብ ቀጥቅጠው ይገሉታል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ይገሉታል፡፡ እኔ ራሴ ብገለው ደስታዬ ነው፡፡
ጆኒ ድቡ አውርቶ እንደጨረሰ እሱ ላይ ተተክለው የነበሩት አይኖች አንድ ላይ ወደ እኔ ተሻገሩ፤ እንደአፈሩልኝ ያስታውቅባቸዋል። በሀፍረት ፊቴ ላይ ችፍ ያለውን ላብ ሲያዩ አይኖቻቸውን ነቀሉልኝ። የእኔን እና የሜሮ ሮሜሮን ትኩስ ምስጢር በማወቃቸው እንደተደሰቱ ያስታውቅባቸዋል፡፡ ይህንን ያስተዋለው ጆኒ ደቡ ከተቀመጠበት ተነሳ፤ ወደ ግሮሰሪው መሀል ተራመደ፤ እዚያው እንደቆመ።
“ውስኪ ጋብዙኝ፡፡” አለ
እንዳያቸው ያልፈለጉ ግን ያየኋቸው ጠጪዎች ጋበዙት፡፡ የተጋበዘውን በሙሉ በአንድ ትንፋሽ ከጨለጠ በኋላ ወጥቶ የግሮሰሪው በረንዳ ላይ እንደውሻ ተጠቅልሎ ተኛ፡፡ ወዲያው ማንኮራፋት ጀመረ፤ ማንኮራፋቱ ከበረንዳው እኔ እስካለሁበት ቦታ ይሰማል፡፡
አሌክስ በሚያሳዝን አይን እያየኝ፡-
“ዛሬ ገና ነው የሰማኸው አይደል? ጆኒ ድቡን አታውቀውም አይደል?” አለኝ፡፡
“ፈጽሞ አላውቀውም፡፡ ምን ይሉት ፍጥረት ነው?” አሌክስ ጥያቄዬን ችላ ብሎ እንዲህ አለኝ፡-
“ስለ ሜ ሮሜሮ አትጨነቅ፤ ተጨንቀሀል አይደል? ከዚህ በፊትም ከሌሎች ወዳጆቿ ጋር ያወራችውን ሰምቶ እዚህ መጥቶ አሰምቶናል። እሷም ማውራቱን ሰምታለች፤ ስለዚህ የዛሬውን እንዳወራ ብትሰማም አይገርማትም፤ አይዞህ ስለ እሷ አትጨነቅ፡፡”
“ግን እንዴት ሊሰማን ቻለ? ብቻችንን ነበርን፤ ማንም አልነበረም፡፡”
“እዚህ ቤት እራሱ ሲራመድ አላየኸውም እንዴ? ካስተዋልከው አይራመድም እሱ፤ ይሳባል እንጂ፤ እኔ እና አንተ እንደምንራመደው አይደለም እሱ የሚራመደው፤ ይሳባል፤ ማንም ጆኒ ድቡን ሲመጣ ወይም ሲሄድ አይሰማውም፡፡”
“ግን እንዴት የሰውን ድምጽ እንዲህ መቅዳት ይቻላል? እንዴት ቻለ? ምን ይሉት ፍጥረት ነው?”
አሌክስ አግራሞቴን ተጋራኝ፡-
“አዎ ልዩ ፍጡር ነው፡፡ እኛም በመጀመሪያ ይህን ችሎታውን ያወቅን ጊዜ ጉድ ብለን ነበር፡፡ ማን እንደሆነ አላስታውስም፣ ለሆነ ዩኒቨርስቲ ስለ ጆኒ ድቡ ችሎታ ጠቅሶ ደብዳቤ ጻፈላቸው፡፡ እነሱም አንድ ጉዳዩ የሚመለከተው ሳይንቲስት ላኩ፤ መጥቶ አየው፤ እሱም እንደኛው ተደነቀ፣ እና ስለ እውሩ ቶም ነገረን፡፡ መቼም ስለ እውሩ ቶም ሳትሰማ አልቀረህም?”
“ኔግሮው ፒያኖ ተጫዋች አይደል?”
“አውቀኸዋል፤ እሱ ነው፡፡ በቃ እውሩ ቶም እና ጆኒ ድቡ አንድ ናቸው፡፡ የሚገርመው ሁለቱም ዘገምተኞች ናቸው፤ ሁለቱም ደግሞ ልዩ ችሎታ አላቸው፡፡ ቶም ብዙ አያወራም፣ ኧረ ከጥቂት ቃላቶች በቀር አያውቅም፡፡ ምንም አይነት ሙዚቃ አንዴ ብቻ በፒያኖ ተጫወትለት፣ ያለ አንዳች ማዛነፍ ደግሞ ይጫወተዋል፡፡ ደግመው ደጋግመው ፈተኑት፤ የየትኛውንም ታላቅ ቀማሪ የፒያኖ ጨዋታ ሲያሰሙት ደግሞ ይጫወተዋል፣ ረዣዥም ሰዓታትን የሚፈጁትን ቅማሬዎች ሁሉ አንዴ ብቻ ሰምቶ ይደግማቸዋል፡፡ የሚገርምህ ሁለት ፒያኒስቶች የአንድ ታዋቂ አንድ ቅማሬ እየተጫወቱ ቢሰማ፣ የሁለቱንም ልዩነት ቁልጭ አድርጎ ነው የሚጫወተው፡፡ የሁሉንም ሙዚቀኞች ጨዋታ ተለማምዶት ይሆን እንዴ? ብለው ሊያሳስቱት የተወሰነች ቦታ ላይ ስህተት ቢጫወቱ ከነስህተቱ ነው ደግሞ የሚጫወተው፣ እያንዳንዷን ቅንጣት ነው የሚሸመድዳት፡፡ ጆኒ ድቡም እንደ እውሩ ቶም ነው፡፡ ልዩነቱ ያ የሰማውን የፒያኖ ጨዋታ በፒያኖ ደግሞ ይጫወታል፣ ጆኒ ድቡ ደግሞ የሰው ቃላት እና ድምጽ ሰምቶ ይደግመዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የመጣው ሰውዬ ለጆኒ ድቡ ረዥም በግሪክኛ የተፃፈ መጽሐፍ አነበበለት፤ ጆኒ ድቡ ቃል በቃል ደገመለት፡፡ አስበው ጆኒ ድቡ ግሪክኛ አይችልም፡፡ በማንኛውም ቋንቋ ምንም አይነት ድምጽ ይስማ ደግሞ ይለዋል። የሰማውን ነው የሚደግመው፤ አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ቆይ ቅድም አንተ እና ሜ ሮሜሮ ካወራችሁት የጨመረው ወይ የቀነሰው ነገር ነበር?”  
“ምንም፣ አንዲትም ነገር፡፡”
“አየህ ቅድም ሰዎች ሁሉ አሰፍስፈው ጆኒ ድቡን ሲሰሙት የነበረው ለዚያ ነው፡፡ ጆኒ ድቡ ሲያወራ ልክ ሰዎች በቦታው የተገኙ ያህል ነው፡፡ ምንም አያመልጣቸውም፡፡ ሁሉን ይሰማሉ፤ ለዚያውም በሰዎቹ ቅላፄ፡፡ የከተማችን ሴቶች ከፍቅረኞቻቸው ጋር ሲዝናኑ ምን እንደሚያደርጉ ታውቃለህ? ውሾቻቸውን አስከትለው ይወጣሉ፤ ውሾቹ ጆኒ ድቡን አይወዱትም ወይም ይፈሩታል፣ ስለዚህ ጠረኑ ከሩቅ ሲደርሳቸው ይጮሀሉ…”
ኤሌክስን አቋረጥኩት፡፡
“ጆኒ ድቡ ዘገምተኛ ነው ብለኸኛል፡፡ ሰዎች የሚሉትን ሰምቶ ይደግማል እንጂ ምን እንዳሉ እንኳ አያውቅም ብለኸኛል፤ እና ለምን ይሰማል? ምን ያደርግለታል? የማይረዳው ነገር ለምን ተደብቆ፣ ያውም በጨለማ ለምን ይሰማል? ምን ያደርግለታል?”
አሌክስ ሲጋራ ለኮሰ፡፡
“የሰው ልጆችን ከቅናት እና ከጥላቻ ቀጥሎ የሚነዳቸው ነገር ጉጉት ነው፣ የማወቅ ጉጉት፤ ስለ ሌሎች ሰዎች የማወቅ ጉጉት፤ ሰዎች ስለ ሌሎች ሰዎች ገመና ማወቅ ይፈልጋሉ፡፡ አሁን እዚህ ቤት ያሉ ሰዎች ሁሉ ያወሩትን ነገር ሁሉ ጆኒ ድቡ ቢሰማ ያለ አንዳች ማዛነፍ ይደግመዋል፡፡ ይህ ግን ዋጋ ቢስ ይሆናል፤ ሌሎች እየሰሙ በአደባባይ የተወራውን ነገር መድገሙ ዋጋ የለውም፤ ሁሉም ሰምቶታላ፤ ምስጢር አይደለም፤ ስለዚህ ማንንም አይስብም፤ ግን ደግሞ በድብቅ፣ በጨለማ፣ በግል፣ ምስጢር ነው ተብሎ የተወራን ነገር፣ ለዚያውም ልክ እንደተወራው ሆኖ ለመስማት የማይጓጓ የለም፡፡ ሰዎች የሌሎችን ገመና ማወቅ ይወዳሉ፤ ጆኒ ድቡ ደግሞ ውስኪ ይወዳል፡፡ በየውድቅቱ፣ በየቤቱ የተወራውን በየመስኮቱ፣ በየበሩ እየተለጠፈ ይሰማል፤ እንደተወራው አድርጎ እዚህ መጥቶ ያወራል፤ የሰሙ ሰዎች ውስኪ ይገዙለታል፤ ይጋብዙታል፡፡ ያ ነው ምስጢሩ፡፡”
“እስከአሁን ግን በሰዎች አለመገደሉ ይገርማል፡፡ እንዴት አንዳቸው ሳይገድሉት ቀሩ?!” የምር በጣም ነው የገረመኝ፡፡
“ጆኒ ድቡ በራቸው ወይ መስኮታቸው ላይ ተለጥፎ ሲሰማቸው እዚያው ሊደፉት ብዙዎቹ ሞክረዋል፡፡ አንዳቸውም አልተሳካላቸውም፡፡ ችግሩ ምን መሰለህ? ጆኒ ድቡን ለመያዝ እያደባህ ከሆነ እያወራህ አይደለም፤ እያደባህ ነው፡፡ እያወራህ ከሆነ ደግሞ እያወራህ ነው፤ እያደባህ አይደለም፤ እሱን እየጠበከው አይደለም፡፡ እሱ ደግሞ ወሬህን ፈልጎ ነው ወደ አለህበት የሚመጣው፤ ስለዚህ መስኮትህን ጥርቅም አድርገህ በሹክሹክታ ያወራሃትን ነው የሚሰማህ፤ ያኔ በቃ አለቀልህ፡፡ በዚያም ላይ ጆኒ ድቡን ሲመጣም ሆነ ሲሄድ አትሰማውም፡፡ የመስማት ችሎታው ደግሞ የተለየ ነው፡፡” እኔ እና አሌክስ መጠጥ አላስቀዳም ነበር፤ ልናስቀዳ ወደ ባንኮኒው ሄድን፡፡
“ምን ልታዘዝ?” አለን ካርል ዘረጦ፤ ሁለት ብርጭቆዎች ላይ ውስኪ እየቀዳ፡፡ አንዳችንም አልመለስንለትም፡፡
ካርል ዘረጦ ጠቀሰኝ፡፡
“ሰራልህ አይደል?” አለኝ በሹፈት፡፡
“ሌላ ቀን ከሴት ጋር ስሆን ውሻ ይዤ እሄዳለሁ።” አልኩት እኔም በሹፈት፡፡
ብርጭቆዎቻችንን ይዘን ወደ ወንበሮቻችን አመራን፡፡ በረንዳው ላይ ተጠቅልሎ ወደተኛው ድብ ተመለከትኩ፤ ተኝቶም የጅል ሳቁ ፊቱ ላይ አለ፤ ከእንቅልፉ ነቃ፤ ከዋሻው ለመውጣት ሲል ስለላ እንደሚያደርግ አውሬ ወደ እኛ አማተረ፤ ተነስቶ ወደ አለንበት መራመድ ጀመረ፤ ይህ ሰው ልዩ ፍጡር ነው፤ እንቅስቃሴው ለየት ያለ ነው፤ እንዲያው ሲያዩት ቅርጽ አልባ የስጋ ክምር ነው የሚመስለው፤ ሲራመድ ግን ያለ አንዳች ጥረት ነው፡፡ እንደለመደው ግሮሰሪው መሀል ሲደርስ ቆመ፡፡
“ጋብዙኝ፤ ውስኪ ጋብዙኝ፡፡”
የሰማው ሰው አልነበረም፤ ማለት ሰምተው ችላ አሉት፡፡ ከዚያ የተለመደው ቦታ፣ ጥግ ሄዶ መሬት ላይ ተቀመጠ፤ ቀኝ እጁን ቀኝ ጆሮው ላይ ለጠፈ፤ ፊቱ ላይ አትኩሮት አለ፡፡
“ምን እያደረገ ነው?” ብዬ አሌክስን ጠየኩት፡፡
“ዝም በል፡፡” አለኝ አሌክስ፡፡ ከዚያ ወደእኔ በጣም ቀረብ ብሎ፡-
“እጁን ጆሮው ላይ መለጠፉ በቅርቡ የሆነ በር ላይ ወይ መስኮት ላይ ተለጥፎ የሰማው ነገር እንዳለ እየጠቆመን ነው፡፡ የሆነ ነገር ሊያወራልን ነው፤ ዝም በል ቆይ፡፡”
አሌክስ ይህን እንዳለኝ የሴት ድምጽ ተሰማ። ረጋ ያለ፣ ቀዝቃዛ የሴት ድምጽ፤ የድምጿ እርጋታ እና ቅዝቃዜ ከዚህ በፊት ሰምቼው የማላውቅ አይነት እርግጠኛነት አለው፡፡ የድምጿ እርጋታ፣ ቅዝቃዜ እና እርግጠኛነት አንድ ላይ ተሰናስሎ አድማጭ ላይ ፍርሃትን ይፈጥራል፡፡ ቃላቶቿ እየተቆጠሩ ነው ከአፍዋ የሚለቀቁት፡፡
“እንዴት እንዲያ ታደርጊያለሽ? እኔ እራሴ በአይኔ በብረቱ ባላይሽ፣ እንዲያ አይነት እንስሳ ፍጥረት መሆንሽን ማንም ቢነግረኝ አላምንም ነበረ፡፡”
ቀጥሎ የተሰማኝ የሚንሾካሾክ፣ በስቃይ እና በመከራ የተጨማለቀ ድምፅ ነበር፡፡
“እንዳልሺው እንስሳ ሳልሆን አልቀርም፡፡”
“እንዲያ አትበይኝ አንቺ እንስሳ፡፡” አለች ረጋ፣ ቅዝቅዝ፣ ርግጥ ያለ ድምፅ ያላት፡፡
“በቃ ምንም ማድረግ አልችልም፤ እንደ አንቺ እራሴን መግዛት አልችልም፡፡” አለች ሌላኛይቱ፡፡
“እኔ ብሆን ኖሮ ግን ምንም ማድረግ አልችልም፤ በቃ እያልኩ አልዘላብድም፤ አንቺ ያደረግሽውን ከማደርግ ቢያንስ አንድ ነገር ማድረግ እመርጣለሁ፤ እራሴን ማጥፋት፡፡ አንቺን ብሆን ኖሮ እራሴን አጠፋ ነበር፡፡”
ከዚያ ለቅሶ ተሰማ፡፡ በህይወቴ እንዲህ አይነት ልብ የሚሰብር ለቅሶ ሰምቼ አላውቅም፡፡ በህይወቴ እንዲህ አይነት ተስፋ ቢስ ድምፅ ሰምቼ አላውቅም።
አጠገቤ የተቀመጠውን አሌክስ በጥያቄ አየሁት። ዝም አለኝ፡፡ ጥያቄዬን ወደ ድምፅ ልለውጠው ስል አሌክስ ዝም እንድል በምልክት አሳየኝ፡፡ አሌክስ እጁን አጣምሮ፣ ቀጥ ብሎ ነው ቁጭ ያለው። አይኖቹ በአግራሞት ፈጠዋል፤ አይርገበገቡም። እነዚያ ምልልሶች ከጆኒ ድቡ መሰማት ከጀመሩ ጀምሮ እንዲያ ሆኖ ነው የተቀመጠው፡፡ ሌሎቹንም ግሮሰሪ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ቃኘሁዋቸው፤ ሁሉም እንደ አሌክስ ሆነው እያዳመጡ ነው፡፡
ለቅሶው ተቋረጠ፡፡
“ኤማሊን አንቺን አንድም ቀን እንዲያ አይነት ስሜት ተሰምቶሽ አያውቅም?” ስታለቅስ የነበረችው ሴት የጠየቀችው ጥያቄ ነው፡፡ አቤት ድምጿ ውስጥ ያለው ልምምጥ!
“በፍፁም፤ በጭራሽ፡፡” አቤት እርጋታ፣ አቤት ቅዝቃዜ፣ አቤት እርግጠኝነት፡፡
“አንድም ቀን እንኳ? አንድም ምሽት እንኳ? እንዲያው በህይወትሽ ለአንዲት ደቂቃ እንኳ?” አለች ምስኪኗ ሴት፡፡
“ቅዱስ መፅሃፍ እንደሚለው ነው፡፡ አንድ የሰውነትህ ክፍልህ ቢያስትህ ቆርጠህ ጣለው ነው የሚለው፡፡ እኔም አንቺ እንዳደረግሽው ከማደርግ ያሳተኝን የሰውነት ክፍሌን ቆርጬ እጥለው ነበር። አሁን አትነፋረቂብኝ፡፡ ጤነኛ አትመስይኝም፡፡ ዶክተሩ ቢያይሽ ጥሩ ነው፡፡ አትነፋረቂ ብያለሁ፡፡ አሁን የፀሎት ሰአት ደርሷል፡፡ ወደ ክፍልሽ ሂጂ እና አምላክሽ እንዲረዳሽ ፀልዪ፡፡ አሳፋሪ፡፡ ባለጌ!”
ወሬው አለቀ፡፡ ጆኒ ድቡ ሳቀ፤ ሁላችንንም አየን።
“ጋብዙኝ፤ ውስኪ ጋብዙኝ፡፡”
አምስት ሰዎች የአንድ አንድ መለኪያ ጠረጴዛቸው ላይ አስቀመጡለት፡፡ ጆኒ ድቡ አንድ በአንድ፣ በአንድ ትንፋሽ ጨለጣቸው፡፡
ቤቱ ውስጥ አስፈሪ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ ማንም ማንንም አያዳምጥም፤ እያንዳንዱ ሰው በሃሳቡ ከሆነ አስፈሪ ነገር ጋር እየታገለ ነው፡፡ ቀስ በቀስ ሁሉም ሰው ሂሳቡን እየከፈለ መሰስ እያለ ወጣ፡፡ በመጨረሻም አሌክስ ተከተለ፤ ተከተልኩት፡፡
ቀፋፊ ምሽት ነው፡፡
አሌክስ በሚገርም ፍጥነት ነው የሚራመደው፤ እሱ ላይ ለመድረስ መሮጥ ነበረብኝ፡፡
“ምንድነው ነገሩ? ምንድነው የሰማችሁት? ምንድነው ሁላችሁንም እንዲህ ሊያደርጋችሁ የቻለው? ጆኒ ድቡ ምንድነው ያወራው?”
አሌክስ መቼም የሚያወራኝ አይመስልም ነበር፤ ድንገት ግን በከፍተኛ ድምፅ እንዲህ አለኝ፡-
“አቦ ምን አይነት አስጠሊታ ቀን ነው! ወዳጄ እያንዳንዱ ከተማ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ያስፈልጉታል፤ ደግሞም አሉት፡፡ ከምንም ነገር የፀዱ፣ በምንም ነገር በተምሳሌትነት የሚጠቀሱ ሰዎች ያስፈልጋሉ፣ ለእያንዳንዱ ከተማ፡፡ ኤማሊን እና ኤሚ የኛ ከተማ የምርጥ ሰው ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ አንድም እንከን የማታወጣላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ አባታቸው የኮንግረስ አባል ነበር፡፡ ዛሬ የተከሰተው በጣም ቀፋፊ ነገር ነው፡፡ ጆኒ ድቡ ያንን ቤት መሰለል አልነበረበትም! ደግሞም እኮ ከርሱን የሚሞሉለት እነሱ ናቸው! ደሞ ሰዎቹ እንዴት አባታቸው ውስኪ ይጋብዙታል! በቃ ከዛሬ ወዲህ ከዚያ ቤት በር እና መስኮት ስር አይጠፋም፡፡ እንደዛሬ ብዙ ውስኪ ተጋብዞ አያውቅም፡፡” አሌክስ በጣም ተናዷል፡፡
“ቆይ አንተ እንዲህ ምን አንጨረጨረህ? ሰዎቹ ዘመዶችህ ናቸው እንዴ?” አልኩት፡፡
“ምን እንደተከሰተ፣ ምን እየነገርኩህ እንዳለ ምንም አልገባህም፡፡ ሰዎቹ ዘመዶቼ አይደሉም። ምን ይሆናል መሰለህ? የዚህ ከተማ ቤተሰቦች ለልጆቻችን ምርጥ ሰው ምን አይነት እንደሆነ ለማስረዳት ስንፈልግ የምንጠቅስላቸው ኤሚሊን እና ኤሚን ነው፡፡ አሁን ገባህ?” አለኝ አሌክስ፡፡
“ዛሬ ጆኒ ድቡ ካወራው ምንም ሊያነውራቸው የሚችል ነገር አልሰማሁም፡፡ የትኛው ነው ሊያነውራቸው የሚችል?” መንገብገቡ ገርሞኛል፡፡
“አላውቅም፡፡ አላውቅም፡፡ አውቃለሁ ግን አላውቅም፡፡ አቦ አሁን ተወኝ፡፡” ብሎ አለሁበት ጥሎኝ ሄደ፡፡
ወደ ቤቴ ሄድኩኝ፡፡ እንቅልፍ እስኪወስደኝ ስለ ኤማሊን እና ስለ ኤሚ ሳስብ ነበር፡፡ በሰማሁት ድምፃቸውን መልካቸውን ልቀርፅ ሞከርኩ፡፡
በነጋታው ስራ ውዬ እራት ልበላ ስሄድ አሌክስን መንገድ ላይ አገኘሁት፡፡
“ወደ መስሪያ ቤትህ እየመጣሁ ነበር፤ አንተን ፍለጋ፡፡” አለኝ አሌክስ፡፡
“ለምን?”
“ጠዋት ከቤት ስወጣ ሁለት ዶሮዎች ገድዬ ነበር፤ እና አሁን ብቻዬን መሄድ ፈራሁ፡፡ ለምን አብረን ሄደን መጨረሻቸውን አናይም?” አለኝ እየሳቀ፡፡
ግብዣውን በደስታ ተቀበልኩ፡፡
ከአሌክስ ጋር ወደ ቤቱ እየሄድን መንገድ ላይ፡-
“ያ ቤት ይታይሃል?” አለኝ በጣም ትልቅ ግቢ እያሳየኝ፣ ከአጥሩ እርዝመት የተነሳ የቤቱ ጣሪያ ብቻ ነው የሚታየው፡፡
“አዎና፡፡ ምነው?”
“የእነ ኤማሊን ቤት ነው፡፡” አለኝ፡፡
“ያ ቀጥሎ ያለው ትንሹ ቤትስ የማን ነው?” ጠየኩት አሌክስን፡፡
“የቻይናዎቹ ነው፡፡”
“የምን ቻይናዎች?”
“አማሊን እና ኢማ እርሻቸውን የሚያርስላቸው ሰው የላቸውም፡፡ እነዚህን ቻይናዎች ቀጥረው ነው የሚያሳርሱት፤ ያርሱላቸዋል፤ በፈርቅ ይካፈላሉ። ቻይናዎቹ አሪፍ ሰራተኞች ናቸው፤ እኔ እራሱ እንደነሱ አይነት ሰራተኛ ባገኝ ቀጥሬ አሳርስ ነበር፡፡”
ወደ እኛ ይመጣ የነበረ ሰው፡-
“ታዲያስ አሌክስ፡፡” አለ
“እንደምነህ ዶክተር?”
“ደህና ነኝ”
አሌክስ ወደ እኔ ዞሮ፡- “ተዋወቁ ዶክተር ሆልመስ ይባላል፡፡” አለኝ፤ ተዋወቅሁት፡፡
“ከየት ነው ዶክተር?” አለ አሌክስ፤ ዶክተሩ ወደ እነ ኤማሊን ቤት ጠቆመ፡፡
ተሰነባብተን ተለያየን፡፡
ልክ የእነ ኤማሊን ቤት ጋ ልንደርስ ስንል ግዙፍ የግቢያቸው በር ተከፈተ እና ከተንጣለለው ግቢ አንድ ሠረገላ ወጣ፡፡ ይኼን ጊዜ አሌክስ፡-
“ተመልከት፣ ተመልከት እነሱ ናቸው፣ ኤማሊን እና ኤሚ ናቸው፤ ወደ ቤተክርስቲያን እየሄዱ ነው።” አለኝ፡፡
አጠገባችን ሲደርሱ ሁለታችንም ኮፍያችንን አውልቀን እጅ ነሳን፤ በእርጋታ አፀፋውን መለሱልን።
በደንብ አየኋቸው፡፡
እንዲህ እንደዛሬ ደግንጬ አላውቅም፡፡ ኤማሊን እና ኤሚ ድምፃቸውን ሰምቼ ምን እንደሚመልሱ እንደገመትኳቸው ናቸው፤ ቁርጥ እንደገመትኳቸው! የጆኒ ድቡ ብቃት አሁን ትንፋሽ አሳጠረኝ፡፡ የሰዎችን ድምፃቸውን ብቻ አይደለም የሚሰማው። ድምፃቸው ውስጥ መልካቸውንም ይቀርፃል፤ ይህ ልዩ ብቃት ነው፡፡
አሌክስን ኢማሊን የቷ ናት? ኤሚስ የቷ ናት? ማለት አላስፈለገኝም፡፡ ንፁህ እና አትኳሪ አይኖች፣ የተሞረደ እና የሚቋረጥ አገጭ፣ በአልማዝ መቁረጫ የተሞረደ የሚመስል አፍ፣ ቀጥ ያለ እና እንደ እምነበረድ የተቀረፀ የሚመስል የሰውነት ጠርዝ ያላት ማን እንደሆነች መገመት አላስፈለገኝም፤ ኤማሊን ናት፡፡ ኤሚ እህቷን በጣም ትመስላታለች፤ ግን ደግሞ ፈፅሞ አትመስላትም፡፡ መልካቸው አንድ አይነት ነው፤ ግን ይለያያሉ፡፡ የኤሚ የሁሉም ሰውነት ክፍሎቿ ጠርዞች እንደ ደመና የሳሱ ናቸው። አይኖቿ ቋማጭ ናቸው፣ አፏ ደግሞ ያቋምጣል፣ ጡቶቿ ያኮበኮቡ ነገር ናቸው፡፡ ኤማሊን ንቁ ስትሆን ኤሚ ግን ንቁ ለመሆን የምትጥር ናት፡፡ ኤማሊን እድሜዋ ሃምሳ ወይም ሃምሳ አምስት ቢሆን ነው፤ በእርግጠኝነት ኤሚ የአስር አመት ታናሿ ናት። እህትማማቾቹን ለቅፅበት ነው ያየኋቸው፤ ከዚያ ቀን በኋላም አይቻቸው አላውቅም፤ ግን እምላለሁ እስከዛሬ በህይወቴ ከማውቃቸው ሰዎች ሁሉ ይልቅ ኤማሊን እና ኤሚን ጠንቅቄ አውቃቸዋለሁ፡፡ ድምፃቸውን ከጆኒ ድቡ የሰማሁት እና ለቅፅበት ብቻ ያየኋቸውን እህትማማቾች እስከዛሬ ከማውቃቸው ሰዎች በላይ እንደማውቃቸው ሲታወቀኝ ደነገጥኩ። ድንጋጤዬን ያስተዋለው አሌክስ፡-
“ስለ ኤማሊን እና ኤሚ የነገርኩህ አሁን ገና ገባህ አይደል?” አለኝ፡፡
“ይገርማል፣ በጣም ይገርማል፡፡” አልኩት፡፡
አሌክስ የነገረኝ ግልፅ ነበር፡፡ በቃ ማንኛውም ማህበረሰብ ኤማሊን እና ኤሚን መሳይ አባላት ያስፈልጉታል፡፡ እንዲህ አይነት አባላት ያሉት ማህበረሰብ ይፅናናል፤ ምን መፅናናት ብቻ ይበረታል፡፡
ምርጥ እራት በላን፣ እንዲህ የሚጥም ዶሮ በልቼ አላውቅም፡፡ ከእራት በኋላ ደግሞ አሌክስ ውስኪ ቀዳልኝ፣ ምርጥ ውስኪ ነበር፡፡
“እቤትህ ውስጥ እንዲህ አይነት ውስኪ እያለ ቡፋሎ ግሮሰሪ ምን ልታደርግ ነው የምትመጣው?” አልኩት አሌክስን በመገረም፤ ውስኪዬን እያጣጣምኩ፡፡
“ብዙዎቻችን የሎማ ነዋሪዎች ለመጠጡ አይደለም ቡፋሎ ግሮሰሪ የምንሄደው፤ ቡፋሎ ግሮሰሪ ግሮሰሪያችን ብቻ አይደለም፣ ቡፋሎ ግሮሰሪ ለኛ መዝናኛችን፣ መገናኛ ብዙኃናችን፣ ቴአትር ቤታችን፣ የምሽት ክለባችን ነው፡፡”
አሌክስ ስለ ቡፋሎ ግሮሰሪ የነገረኝ በሙሉ እውነት ነው፡፡ ወደ ቤቴ በፎርድ መኪናው ሊሸኝ ስንወጣ ቡፋሎ ግሮሰሪ ጎራ እንደምንል ሁለታችንም እርግጠኞች ነበርን፡፡ ቡፋሎ ግሮሰሪ ገባን፡፡
ካርል ዘረጦ ወደ እኛ መጣ፡፡ “ምን ልታዘዝ?” ሳይለን በፊት “ውስኪ” ብለን ሁለታችንም ጮህን፡፡
እየጠጣን እያለ ጆኒ ድቡ መጣ፡፡ ዛሬም ቤቱ ውስጥ ፀጥታ ሰፈነ፡፡ የጅል ፈገግታው አሁንም ፊቱ ላይ አለ “ውስኪ ጋብዙኝ፣ አንድ ውስኪ ለጆኒ!” አለ። ሰዎቹ ሁሉ ላይ የማወቅ ጉጉት አለ፤ ጉጉታቸው እንዲያ የፈጠጠ በመሆኑ ሁሉም አፍረዋል፣ ግን ሁሉም ስለ ኤማሊን እና ኤሚ ለማወቅ ጓጉተዋል። የሚያሳፍር ጉጉት ነው፣ ግን መስማት ፈልገዋል፡፡ የሚገርመው ማንም ሳይጋብዘው በፊት ካርል ዘረጦ እራሱ ቀዳለት፤ የተለመደው ጥግ ጋ ተቀመጠ፡፡
“ኤማሊን እህትሽ የት ነው ያለችው? ሰሞኑን በተደጋጋሚ እያመማት በተደጋጋሚ እየጠራሽኝ ነው፡፡ እዚህ ቤት ውስጥ ምን እየተካሄደ እንደሆነ አላውቅም፤ አንቺም እሷም ምንም ነገር አትነግሩኝም። እኔ የወላጆቻችሁ ሰሃኪም ነበርኩ፤ ነገሮችን ለምን እንደምትደብቁኝ አላውቅም፡፡ አሁን እህትሽ የት ናት ያለችው? ድምፁን ወዲያው ነው ያወቅሁት፤ የዶክተር ሆልመስ ድምፅ ነበር፤ ዶክተር ሆልመስ ድምፅ ውስጥ ንዴት ነበር፡፡
“መኝታ ቤቷ ውስጥ ነች፡፡” እንዲህ አይነት ከሞት የቀዘቀዘ ድምፅ ሰምቼ አላውቅም፣ ግን ቅዝቃዜውም ውስጥ ሃዘን አለ፡፡
“ጉድ ይላሉ ይሄ ነው! እራሷን ሰቅላለች?! ለዚያውም ተሰቅላ ቆይታለች፤ ስንት ሰዓት ይሆናል ከታነቀች፡፡” አለ ዶክተር ሆልመስ፡፡
“አላውቅም ዶክተር፡፡” የኤማሊን ድምፅ ነው፡፡
“ለምን እራሷን የሰቀለች ይመስልሻል?”
“አላውቅም ዶክተር፡፡”
“እርጉዝ እንደነበረች ታውቂ ነበር፡፡”
“አውቃለሁ ዶክተር፡፡”
“በጣም ልትንከባከቢያት ይገባ ነበር!”
“ዶክተር የምርመራህ ወረቀት ላይ እርጉዝ መሆኗን ባትጠቅስ መልካም ነው፤ ያንን ማድረግ ትችላለህ?”
“እችላለሁ”
“አመሰግናለሁ ዶክተር”
“ኤማሊን፤ አንቺ እራሱ የህመም ማስታገሻ ያስፈልግሻል፡፡”
“እሺ ዶክተር”
ንግግሩ አበቃ፡፡
“ጋብዙኝ፣ ውስኪ ጋብዙኝ፡፡”
ተቀዳለት፤ ብዙ ተቀዳለት፤ ብዙ ጠጣ፡፡ ሁላችንም ተጨማሪ ነገር እየጠበቅን ነበር፡፡
ጆኒ ድቡብ ውስኪዎቹን ተራ በተራ ጨልጦ፣ ጥጉ ላይ ተቀመጠ፡፡
“አንተ ሰውዬ ከአሁን በኋላ አንድ ነገር ትናገር እና ውርድ ከራሴ፤ ወራዳ ነገር ነህ፤ እንዴት እንዲህ ገመናቸውን አደባባይ ታወጣለህ?” ብሎ ጮኸ አሌክስ፣ የሰማው አንድም ሰው አልነበረም፤ ሁሉም አሰፍስፎ ጆኒ ድቡን እየጠበቀ ነው፡፡
አሁን የቻይናዊ ድምፅ ተሰማ፣ ወሲብ ጣሪያ ላይ ያለ የቻይናዊ ድምፅ ነው፤ ቀጥሎ የሴት ድምፅ ተሰማ፤ እሷም የወሲብ ጣሪያ ላይ ናት፤ ቻይናዊው የሚለውን ነገር ነው በስሜት የምትደግመው፡፡
ጆኒ ድቡ ተነስቶ፡- “ጋብዙኝ፤ ውስኪ ጋብዙን።” አለ፡፡ ይኼኔ አሌክስ ተንደርድሮ ሀይለኛ ቦክስ ጋበዘው፡፡
የጆኒ ድቡ ከንፈር ተሰነጠቀ፤ አፉ ደም በደም ሆነ፤ አሁንም ግን ያ የጅል ፈገግታው ፊቱ ላይ አለ፡፡ ጆኒ ድቡ ግጥም አድርጎ አሌክስን አቀፈው። ሁላችንም አሌክስን ለማስለቀቅ የጆኒ ድቡ እጆች ላይ ተረባረብን፡፡ አልቻልንም፡፡ ካርል ዘረጦ በዱላ እራሱን እስኪስት አናቱን ከቀጠቀጠው በኋላ ነው የለቀቀው፡፡
“አጥንቶቼን ሳይሰብራቸው አይቀርም፡፡” አለ አሌክስ እንደተለቀቀ፡፡
አሌክስን በራሱ መኪና ወደ ቤቱ እየሸኘሁት፡-
“ለምን መታኸው?” አልኩት
“ቻይናዊው የሚለውን የምትደግመዋን ሴት ድምፅ አውቀሃል?”
“አላወቅሁም፡፡”
“ኤሚ ናት!”


Read 3503 times