Saturday, 08 March 2014 12:08

“አገር ስትለማ ቀስ በቀስ ሀብታም መሆን ይቻላል፡፡ አገር ስትጠፋ ግን በአንድ አፍታ በመልፀግ ይቻላል”

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ሬት በትለር (ነገም ሌላ ቀን ነው)

አንድ የፖለቲካ ምርጫ ተሳታፊ፤ ሁሌ የቆሸሸና አልባሌ ልብስ ይለብሱ ነበረ ይባላል፡፡ አደባባይ ከሚገኝ አልባሌ መሸታ ቤት እየገቡ ነበር የሚዝናኑት፡፡ ይሰክራሉ፤ የፖለቲካ ክርክር ያበዛሉ፡፡ ይሟዘዛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ጨዋና ደግ ነው የሚባለው መራጭ ህብረተሰብ በተመራጩ ቅሬታ ይሰማዋል፡፡ ደጋፊዎቹም በጣም ይቀየሙዋቸዋል፡፡ የህዝቡን ብሶት የሰማ፤ የተመራጩን ተራ መሆን ና ወረዳ መሆን አስመልክቶ ሊያጋልጣቸው የፈለገ አንድ የተቃዋሚ ጋዜጣ አዘጋጅ ሪፖርተሩን ይጠራና፤
“ስማ እኒህን ተመራጭ በተቻለ መጠን ተከታትለህ፤ እንዴት እንደሚደነፉ፣ የሚያገኟቸውን ሰዎች እንዴት እንደሚከራከሩ፣ የሚሳደቧቸውን ስድቦች፣ ከሚያሽኮረምሟቸው ሴቶች ጋር ምን እንደሚባባሉ፤ በደምብ አዳምጠህ ስታበቃ በመጨረሻ ቃለ-መጠይቅ ታደርግላቸዋለህ፡፡ በጥንቃቄ እንድትዘግብ” ይለዋል፡፡
ጋዜጠኛው ተመራጩ ወደሚዝናኑበት መሸታ ቤት ይሄድና እንደተባለው  አግኝቶ ሲከታተላቸው ይቆያል፡፡ በመጨረሻም፤
“ጌታዬ ኢንተርቪው ላደርግዎ ነበር?” ሲል በትህትና ይጠይቃል፡፡
“ስለ ምንድነው … ቃለ …መጠይቅ … እንድሰጥህ የፈለከው?” አሉ ተመራጩ፡፡ ድምፃቸው ክፉኛ ይንተባተባል፡፡
“በአጠቃላይ ስለ ምርጫው”
“መ..ል..ካም” አሉ በተንጀባረረ ቃና፡፡
ጋዜጠኛው ቴፑን ደግኖ ቃለ-መጠይቁን አደረገና አበቃ፡፡ የቀደመውን መልሶ አዳመጠው፡፡ ወደ ፅሁፍ ለወጠው፡፡ በጣም ደነገጠ፡፡ መንተባተብ በመንተባተብ ሆኗል፡፡ ንግግሩ ቁርጥርጥ ያለና ጭራና ቀንዱ የማይያዝ ነው፡፡ በዚያ ላይ የመጨረሻው አረፍተ ነገር አስደንጋጭ ነው፡፡
“ያልመረጥሺኝ ወዮልሽ! ዋጋሽን ታገኛለሽ!” ነበር ያሉትሰ፡፡ ጋዜጠኛው ኢንተርቪውን አርትዖት እንዲያደርግለት ለአለቃው አሳየው፡፡ አለቃውም እንደዚያው ደነገጠና፤
“በል ጠዋት ወደ ቢሮዋቸው ሄደህ የሚያስተካክሉት ነገር ካለ ይዩት በላቸው” አለው፡፡
እንደታዘዘው ጋዜጠኛው ወደተመራጩ ቢሮ ሄዶ “ጌታዬ የሚያስተካክሉት ነገር ካለ አንዴ ያንብቡት?” አላቸው፡፡ ተመራጩ በዞረ-ድምር እየተጨናበሱ፤ አነበቡት፡፡ ውልግድግዱ የወጣ ፅሁፍ ሆኖ አገኙት፡፡  ለጋዜጠኛው መልሰው ወረቀቱን ሲሰጡትሱ፤ “ስማ አንተ ጋዜጠኛ! አንድ ምክር ልስጥህ! ወደፊት በምንም ዓይነት፤ ሰክረህ ቃለ-መጠይቅ አትሥራ! ካሁን በኋላ እንዲህ እያወለጋገድህ ትፅፍና ከጐንህ ታገኛታለህ!! እኛንኮ ነው የምታሳጣን!!”
*   *   *
የዛሬውን የሀገራችንን ሁኔታ ስናየው ልማት እየተካሄደ ያለበት፤ አያሌ ሹም ሽሮች፣ የተካሄዱበት… እንደ ቴሌ፣ መብራት ኃይልና ውሃ ልማት ያሉ ድርጅቶች ተዳክመውና ድክመታቸውን ለማረም ሁነኛ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ የማይታዩበት፣ የህዝባችን የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚ እየደቀቀ የመጣበት … ህይወት በየአቅጣጫው ዛሬም አሳሳቢ የሆነበት፤ ባለሥልጣን ትላንት ያለውን ዛሬ የሚክድበት፣ አሊያም ትላንት የካደውን ዛሬ የሚያምንበት፤… ወደድንም ጠላንም ግን ዛሬም ኤጭ አይባል የአገር ጉዳይ የምንልበት ነው! ሁላችንንም ያገባናል! ሚዲያዎች ይህንን ሁኔታ በደከመም ሆነ በከረረ መልኩ ሁሌም ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡ መረጃ ያላገኘ-ህዝብ (uninformed public) በደመ-ነብስ የሚኖር ህዝብ ይሆናልና፡፡ ሀቅን መቀበል የዲሞክራሲ የበኩር ልጅ ነው፡፡
የሀገራችንን ድክመትና ጥንካሬ የሚመለከታቸው አካላት ሊያሳውቁን ይገባል፡፡ ግልፅነት አንዱ መርሀችን ነው ብለናልና የፓርቲና የፓርቲ ግጭት፣ የፓርቲና የመንግሥት አካላት አለመጣጣም፤ የበላይ መኰንንና የበላይ መኰንን አለመግባባት፤ የአለቃና የምንዝር ፍጥጫ፤ የበዝባዥና የተበዝባዥ ህዝብ መካረር፣ የኮንትራባንዲስቶች ሻጥር፣ አሻጥርና የተከላካይ አካላት ግፍጫ፣ ሹም ሽርና የመተካካት ለውጥ፤ የአይነኬ ባለሥልጣናትና የአውቆ ዝሞች ማቀርቀር፤  … ወዘተ ሳይገለፁና ሳይታሰብባቸው ውጥረትን የሚፈጥሩ፣ ችግርን የሚያባብሱ፣ ምሬትና ብሶትን የሚያቁሩ፤ ፍሬ-ጉዳዮች ናቸው፡፡ በጥንቃቄ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ናቸው! የእኔን ከተወጣሁ ሌላው እንደ ፍጥርጥሩ ማለት፤ አገርን ከዝብርቅርቅ ቀለምና ከተበጫጨቀ ጨርቅ ተገጣጥማ የተሰፋች ያስመስላታል፡፡
የሀገራችን ሌላው አሳሳቢ ችግር የሥራ-መቀዛቀዝ መንፈስ ነው፡፡ ዛሬም ለምን መባል አለበት፡፡ ጥቅሙ ለማን እንደሆነ የማይታወቅ ሥራ-ቀልባሽ ሂደት ነው፡፡ ያም ሆኖ የብዙ ውስጥ-ውስጡን የበሰሉና ያረሩ ምሬቶች ጥርቅም ይመስላል፡፡ የሰው-ጤፉነትና የበላይነት ስሜት (Superiority complex)ም ሆነ፣ የበታችነትና ራስን ዝቅ-አድርጐ የመመልከት አስተሳሰብ (Infiriority complex) ስሜት፤ የዴሞክራሲያዊ አመለካከት አካላት አይደሉም፡፡ የትምክህተኝነትም (Chauvenism) ሆነ፣ የጠባብ አመለካከት (Narrow Nationalist) ፈርጆች፤ የዲሞክራሲያዊ አመለካከት አካላት አይደሉም፡፡ ያለመቻቻል (Tolerance)፣ ወገንተኛነትና ተዓብዮ የዲሞክራሲያዊ አመለካከት አካላት አይደሉም፡፡ እነዚህን ሁሉ መርምሮ “ዴሞክራሲያዊ ነኝ ወይ?” ብሎ ሁሉም ራሱን በጊዜ መፈተሹ የቀኑ ጥያቄ ነው፡፡
ከቶውኑም የውጪ ባላንጣን (external enemy) አሸንፈናል ብሎ መኩራራት፤ የውስጥ ባላንጣ (internal enemy) መፈልፈያውን ጊዜ (incubation time) እንደሚወልድ በቅጡ ማስተዋል ይገባል፡፡ የማንኛውም ሥርዓት የለውጥ ዕድገት ወይ ዝገት እንደሁኔታው የሚያጐነቁላቸው አያሌ እንግዳ-ብቃዮች ይኖራሉ፡፡ በታሪክ የታየ፣ ያለ፣ የነበረ ነው፡፡
ጉልሁንና ዋናውን ስዕል (the bigger picture) በቅጥ በቅጡ ማየቱ አግባብ የመሆኑን ያህል፤ ጥቃቅኖቹንና አንጓ ካንጓ ማያያዣዎቹን (Political ligaments) አበክሮ ማስተዋል ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ የተጀመረው ልማት ይህን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡
Even lies mature ይባላል (ውሸትም እንኳን ይበስላል እንደማለት ነው፡፡) ስልክ ስንተክል፣ ኔትዎርክ ስናሰራጭ፤ መብራት ስንዘረጋ፣ ውሃ ስናስገባ፣ አጥንተንና አቅማችንን ለክተን መሆን አለበት፡፡ የልማት ስትራቴጂ ስንቀይስም አጥንተንና አቅማችንን ለክተን መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ!” የሚለው ግጥም ይመጣል፡፡ በመሠረቱ ልማትን በጐ በጐውን ማየትና መኩራራት ብቻ ሳይሆን ውስጡ ያለውስ ምሥጥና ግንደ-ቆርቁር ምን ይመስላል? ብሎ፣ ይሆነኝ ብሎ ዐይንን ገልጦ ማየት የአባት ነው፡፡ እሸት እሸቱን እያየን ነቀዙን ካላስተዋልን፣ ምርቱን አይተን የግርዱን ብዛት ካላመዛዘንን፤ ሁሌ “ጉሮ-ወሸባዬ” እያልን፤ ውስጥ-ውስጡን መሽመድመዳችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ ነገ ስለ ምርጫ ስናወራም ለህዝቡ ዕውነተኛ ገፅታችንን ማሳየት አለብን፡፡ ከልማቱ ተጠቃሚው፤ ህዝብ መሆን አለበት፤ እንጂ ከላይ ከላዩ ቦጥቧጩ መሆን የለበትም፡፡ ማርጋሬት ሚሼል “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚባለው መፅሀፏ ውስጥ የገለፀችው፣ ሬት በትለር የተባለው በጦርነቱ ጥቅም ያጋብስ የነበረ ነጋዴ፤ “አገር ስትለማ ቀስ በቀስ ሀብታም መሆን ይቻላል፡፡ አገር ስትጠፋ ግን በአንድ አፍታ መበልፀግ ይቻላል” የሚለን ለዚህ ነው!!

Read 5365 times