Saturday, 08 March 2014 12:56

“…ብርዱስ መቼ አስረስቶኝ!...”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(9 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…‘ቢዙ’ ሁሉ ቀዘቀዘ የሚባለው ነገር እንዴት ነው! አቤቱታ በዛማ!
ይሄንን የኑሮ በረዶ ዘመን ያሳጥርልንማ!
ይቺን አሪፍ ነገር ስሙኝማ…ቄሱን ጋቢያቸውን አንዱ ይሞጨልፋቸዋል፡፡ እናም እሳቸው ማንነቱን አውቀው “መቼስ ምን ይደረጋል!” ብለው ዝም ይላሉ፡፡
ታዲያላችሁ…አንድ ቀን መንገድ ሲሄዱ አጅሬው ያገኛቸዋል፡፡ ተንሰፍስፎም ሰላም ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም አጸፋውን ይመልሱለታል፡፡ ከዛም “አባቴ ይፍቱኝ…” ምናምን ሲላቸው “ፈትቼሀለሁ…” ብለው መንገዳቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ርቀው ሳይሄዱም እሱ ሆዬ ጮክ ብሎ ምን ይላል…“አባቴ እባክዎ በጸሎትዎ አይርሱኝ…” ይላል። ይሄኔ ቄሱ ምን ቢሉ ጥሩ ነው…“አልረሳህም ልጄ፡፡ ብርዱስ መቼ አስረስቶኝ!”
አንጀት ማራስ ይሏችኋል እንዲህ ነው፡፡
ዘንድሮ ብልጥነት እየበዛ ሄደና…አለ አይደል…የልቡን ሰርቶ “በጸሎትህ አትርሳኝ…” ባይ በዝቷል፡፡
እና ብዙ ነገር የረሳን ለሚመስላቸው የምንለው አለን…ብርዱ መቼ አስረስቶን፡፡
ስሙኝማ…የዚህ አገር ስልጣን ሁልጊዜ አይገረማችሁም! ልክ ነዋ፣ ወንበሩ ሲሰጥ አብሮ የሆነ ‘የስልጣን ወንበር ከትባት’ ተብሎ የሚሰጥ አለ እንዴ! ግራ ይገባናላ! “ምን የመሰለ ደግ፣ ሰው አክባሪ መሰላችሁ…” የሚባል ሰው ወንበሯ ላይ ሲቀመጥ በአንድ ጊዜ ቀንድና ጭራውን ደብቆ የመጣ ‘ሉሲፈር’ ምናምን ነገር ይመስላል፡፡
እንዴት መሰላችሁ…‘ወንበሯ’ እንደተያዘች አንበሳ ይኮንና “ባለፍኩበት መንገድ ማን ዝር ብሎ…” “የቤቴን ግንብ አጠር ማን ተጠግቶ…” አይነት ደረት መንፋት ይጀመርላችኋል፡፡ ምን አለፋችሁ… ለሰላምታ እንኳን መጠየፍ አይነት ነገር ይደርሳል። ከዛ ደግሞ መቼስ መውረድ ሲመጣ…ኧረ የሰው ያለህ፣ መደበቂያ ጉድጓድ አሳዩኝ…” ነገር ይመጣል፡፡
በተዘዋዋሪ “በጸሎትህ አትርሳኝ…” አይነት ነገር ነው፡፡ እኛም…“ብርዱስ መቼ አስረስቶኝ!” እንላለን፡፡
እንዴት ያለው ሩቅ ጭንቅ ያለው መንገድ፣
አሻቅቦ ወጥቶ ወደ ታች መውረድ፡፡
የሚሏትን ማስታወስ አሪፍ ነው፡፡
ስሙኝማ…መቼም ዘንድሮ በአንድ ጊዜ ‘ብር፣ በብር’ የሚሆን ሰው ይገጥማችኋል፡፡ እናላችሁ…የሆነ ሰው ገንዘብ ያገኛል፡፡ መቼስ ‘ወዳጅ ለመቼ ነው’ ይሉና በችግር ጊዜ ወደ እሱ ብቅ ይላሉ፡፡
“እባክህ ሚስቴ ታማብኝ እጄ ላይ ገንዘብ አጣሁ፣ ደሞዝ ላይ የምመልስህ…” ምናምን ይላሉ፡፡
እሱም “ገንዘብ ከዛፍ ላይ እንደ ቅጠል ይበጠስ መሰለህ እንዴ!” ብሎ የሞራላችሁን ሚዛን ከ75 ኪሎ ወደ 26 ኪሎ ያንደረድረዋል፡፡
እናንተም እንደሚሆን፣ እንደሚሆን ጊዜውን ታልፉታላችሁ፡፡ ታዲያላችሁ…አያልፍ የመሰለ ቀን ጋደል ይልና ሰውየው በአንድ ጊዜ ሁሉንም ነገር ያጣል። ከዛ ሲያገኛችሁ ምን ይላል…በጣም አጣዳፊ ችግር ገጥሞኝ ነው፡፡ እቁብ አትሰበስቡልኝም!” አይነት ነገር ይላል፡፡ በተዘዋዋሪ “በጸሎትህ አትርሳኝ…” አይነት ነገር ነው፡፡ እናንተም “አልረሳህም፣ ብርዱስ መቼ አስረስቶኝ!” ትሉታላችሁ፡፡
ወጥቼ ወጥቼ ሲያልቅልኝ ዳገቱ፣
ተመልሼ ወረድኩ ከነበርኩበቱ፡፡
የሚባል ነገር ይመጣልና ጋቢያችንን ወስዶ “በጸሎትህ አትርሳኝ…” አይነት ነገር ቀሺም ነው፡፡
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል…አንድ የምናውቀው ሰው ሞባይል ስልኩ ይደወልለትና ያነሳል፡፡ “ሀሎ!” ይላል፡፡ እዛኛው ጫፍ ያለው ሰው ሰላምታ ሳያቀርብ፣ ማንነቱን ሳይናገር…ምን አለፋችሁ…“አሁን አንተም ሰው ሆነህ እኔን ማታለልህ ነው…” ምናምን ብሎት መጻፍ የማይቻሉ የስድብ አይነቶች ያወርድበታል፡፡ ከዛ ስልክ መሳሳቱን ይነግረዋል፡፡ ይሄኔ ያኛው ሰው ምን ቢያደርግ ጥሩ ነው…“ነው እንዴ!” አለና ስልኩን ጠረቀመው፡፡
ምን አይነት ጊዜ ላይ እንደደረስን እሱ አንድዬ ይወቀው፡፡  
ስሙኝማ…የስልክ ነገር ካነሳን አይቀር…የሆነ ስልክ ይደወልላችኋል፡፡ “ሃሎ!” ትላላችሁ፡፡ በወዲያኛው ወገን ያለው ሰው… “ይሄ ቁጥር ስንት ነው?” ይላል፡፡ እኔ የምለው… እንዴት ነው ነገርዬው! …የደወለው ራሱ! ስንት ብሎ ነው የደወለው! እናላችሁ…ከስልክ መቋረጥ እኩል የስልክ ስነ ምግባር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡
የሚገርማችሁ…በእናንተ ስልክ ሌላ ሰው ሲጠይቃችሁ…“ተሳስተዋል…” ምናምን ስትሉ አብዛኛው ሰው… “ይቅርታ” የምትለዋን ቃል ወይ ረስቷታል፣ ወይ ቃሏን ከተናገራት የምታንቀው ይመስላል! እናላችሁ…ጆሯችሁ ላይ ጥርቅም ያደርገዋል፡፡
የምር ግን…ይሄ የስልክ ነገር…“አሁንስ አቤቱታ ማቅረቡም ሰለቸን…” የሚባል ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ ለሦስት ደቂቃ ንግግር አምስት ጊዜ እየተቋረጠ!
እኔ የምለው…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን ስሙልኝማ፡፡ ሰውየው ሌላ ከተማ ያለ ጓደኛው ዘንድ በኦፕሬተር በኩል ይደውልና…“እባክህ ለአስቸኳይ ጉዳይ አሁኑኑ አንድ ሺህ ብር በባንክ በኩል ላክልኝ…” ይላል፡፡
“መስመሩ ተበላሽቷል መሰለኝ፡፡ የምትለው አይሰማኝም፡፡”
“ያልኩህማ ገንዘብ ስለቸገረኝ አንድ ሺህ ብር ላክልኝ፡፡”
“ዛሬ መስመሩ ልክ አይደለም፡፡ የምትለው አንዲቷም ቃል አትሰማኝም፡፡”
ይሄን ጊዜ ኦፕሬተሯ ጣልቃ ትገባና.. “ሃሎ ኦፕሬተሯ ነኝ፡፡ መስመሩ ችግር የለበትም፡፡ የሚለው ሁሉ ለእኔ በደንብ ይሰማኛል…” ትላለች፡፡ ይሄኔ ገንዘብ የተጠየቀው ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው… “እንግዲያው አንቺ አንድ ሺህ ብሩን ላኪለት፡፡”
ስሙኝማ… እንግዲህ እውነት እንነጋገር ከተባለ…የሚባለውን እየሰማን ስልኩ ይቆራረጣል እንል የለ! ለምን ይዋሻል… የማንፈልገው ሰው ከሆነ፣ መስማት የማንፈልገው ነገር ከሆነ (ዕድሜ ለኔትወርክ መቆራራጥ!) “ኧረ ስልኩ ይቆራረጣል፣ ምንም አይሰማኝም፣” ብለን ጥርቅም ነው፡፡
ስሙኝማ…ቢሮ ውስጥ ስልክ ይደወላል… ሰውየው ያነሳና ካዳመጠ በኋላ ለሥራ ባልደረባው… “ለአንተ ነው መሰለኝ…” ይለዋል፡፡ ያኛውም ሰው፣
“መሰለኝ ብሎ ነገር ምንድነው… ወይ የአንተ ነው ወይ አይደለም ይባላል እንጂ…” ነገር ይላል፡፡ ስልኩን ያነሳው ምን አለ መሰላችሁ፤
“አይ ልክ ሀሎ ስለው የደወለው ሰው ‘አንተ ደደብ፣ አሁን በህይወት አለህ!” አለኝ፡፡
ከዚህ ይሰውራችሁ፡፡    
ስሙኝማ…ቴክኖሎጂው እየተራቀቀ ይሄ የስልክ ነገር አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ‘ፕራይቬሲ’ ምናምን የሚሏቸው ነገሮች ለመብት ተሟጋች ድርጅቶች ብቻ እየቀሩ ይመስላል፡፡ ልጄ… እነ አንጄላ ሜርኬል እንኳን ‘ከተጠለፉ’ በኋላ እኮ በስልክ… “ስማ፣ የሆነ ምስጢር ልነግርህ ፈልጌ ነው…” ምናምን መባባል እየከበደ ነው፡፡ ‘ሀከር’ ምናምን የሚሏቸው ነገሮች በበዙበት ዘመን፣ መንግሥታት ሁሉ ጓዳ ጎድጓዷውን በሚሰልሉበት ዘመን… “በእኔና በአንተ ብቻ ይቅር…” ብሎ ነገር ለ‘ሮማንቲክ ኮሜዲ’ ታሪኮች ብቻ ሊሆኑ ምንም አልቀራቸው።  
የምር ግን… ስልካችሁ ላይ የማይሆኑ እንግዳ ነገሮች አይገጥሟችሁም! አንድ ጽሁፍ ላይ ያነበብኳትን ስሙኝማ…እያወራችሁ እያለ ሞባይል ስልካችሁ ውስጥ ‘ቀጭ፣ ቀጭ’ ምናምን የሚሉ ድምጾች ካሉ፣ ሞባይላችሁ በቀላሉ አልዘጋ ብሎ ሲያስቸግር፣ ደግሞም…ሳትነኩት ለረጅም ጊዜ እንደ በራ ከቆየ… ነገር አለ ማለት ነው ይላል። ብዙዎቻችን እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲገጥሙን “ድሮስ ርካሽ ሞባይል…” ምናምን ብለን እናልፈዋለን፡፡ እነኚህ የፔንታጎን ጓዳ የሚያምሱት ‘ሀከሮች’ ዓይን ውስጥ ገባን እንዴ!
ይቺን ስሙኝማ…
ትንሽ ቤት ሠራሁ እንዳቅመኛ፣
ሁለት ሦስት ሰው የሚያስተኛ፣
አላስገባ አለች ያቺው ጠባ፣
ሰው በሰው ላይ እየገባ፡፡
የሚሏት የቆየች ነገር አለች፡፡ እናላችሁ…ዘንድሮ ‘ሰው በሰው ላይ እየገባ’… አለ አይደል… መፈነጋገል በጣም የተለመደ ሆኗል፡፡ እናላችሁ… በየመሀል በቆረጣ እየተገባ ዕድላቸውን የሚነጠቁ ሰዎች መአት ናቸው፡፡ እነኛው ‘በሰው ላይ እየገቡ’ የሰው ዕድል የሚነጥቁት… ቀን ዘወር ሲልባቸው ምን ይመጣል…በተዘዋዋሪ “በጸሎትህ አትርሳኝ…” አይነት ይመጣል፡፡
እኛም…“ብርዱስ መቼ አስረስቶኝ!” እንላለን።
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4349 times