Saturday, 08 March 2014 13:40

መረጃን መሰረት ያደረገ የእናቶችና የህጻናት ጤና የESOG 22ኛ አመታዊ ጉባኤ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(1 Vote)

         የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 22ኛውን አመታዊ ጉባኤውን እንደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር February 24-25 በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል አካሂዶአል፡፡ ጉባኤው በተካሄደበት ወቅት የማህበሩ አባላት እና ተባባሪ አባላት የተገኙ ሲሆን የተለያዩ ድርጅቶች ተወካዮችም ተሳትፈዋል፡፡ ኮንፍረንሱን የከፈቱት ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚኒስትር ደኤታው ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው፡፡  
የማህበሩ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ማህበሩን ወክለው ባቀረቡት የመግቢያ ንግግር
“ ...ለ22ኛው አመታዊ ኮንፍረንስ እንኩዋን ደህና መጣችሁ እያልኩ በመቀጠል ያለኝን የልብ ሀዘን ለመግለጽ እድሉን ልጠቀም እወዳለሁ፡፡ ዶ/ር አየለ ኃይሉ በምስራቁ የአገራችን ክፍል የነበረንን ቅርንጫፍ ቢሮ ይመሩ የነበሩ ...በአካባቢው ላሉ እናቶችና ህጻናት የተሟላ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን በድንገትና በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወታቸው በማለፍዋ ሐዘናችን ከልብ የመነጨ ነበር፡፡ ከመካከላችን በሞት የተለዩንን የማህበራችን አባል የሆኑትን ዶ/ር አየለ ኃይሉን ለአንድ ደቂቃ በህሊናችን እናስባቸው ዘንድ የኮንፍረንሱን ተሳታፊዎች እጠይቃለሁ...” በማለት የህሊና ጸሎት ተደርጎአል፡፡
በመቀጠልም ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት ባቀረቡት የመግቢያ ንግግር እንደገለጹት ባለፈው አመት ESOG ከተለያዩ አጋዥ ድርጅቶች እና አብረው ከሚሰሩ አካላት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የእናቶችን ጤና ለማሻሻል በርካታ ጥረቶችን አድርጎአል፡፡ ከሚጠቀሱት መካከልም በወሊድ ጊዜ የሚከሰት የደም መፍሰስ እና በእርግዝና ጊዜ የሚከሰትን የደም ግፊት ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ የበኩሉን ጥረት አድርጎአል፡፡ እነዚህን በተለይም ሴቶችን በእርግአዝና እና በወሊድ ጊዜ ለአደጋ የሚያጋልጡ ሕመሞችን በሚመለከት ለባለሙያዎች በመከላከል ላይ ያተኮረ አውደጥናት በተከታታይ ተሰጥቶአል፡፡ በዚህም ተሳታፊዎች ችግሩን እንዴት ማቃለል እንደሚገባ አምነው ለመከላከሉ የራሳቸውን እርምጃ እንደሚወስዱ ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኤችአይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ 52/ ከሚሆኑ የግል የህክምና ተቋማት ጋር በተለያዩ መስተዳድር አካላት ጋር ...አዲስ አበባን ጨምሮ ይሰራል፡፡ በዚህም ፕሮግራም ከ/100,000/ በላይ እናቶች የእርግዝና ክትትል ያደረጉ ሲሆን ከ/2207/ በላይ የሚሆኑ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ እናቶች እና ልጆቻቸው ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህንን ፕሮግራም ከኢሶግ ጋር በመሆን የሚሰሩ የግል የህክምና ተቋማት በአሁኑ ወቅትም Option B+  የተባለውን ፕሮግራም ...ማለትም እርጉዝ ሴቶች በምርመራ ወቅት ቫይረሱ በደማቸው ከተገኘ ወዲያውን የህክምና እርዳታውን እንዲያገኙ የሚለውን አሰራር በመከተል አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት በኦክቶበር 2013/ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የመጀመሪያውን የAFOG&FIGOን ስብሰባ በኢትዮጵያ /አዲስ አበባ/ ማካሄዱን ገልጸው በዚህም ስብሰባ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ወደ /807/ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ ኮንፍረንሱ ከተለያዩ ሐገራት የመጡ ባለሙያዎች አስተሳሰባቸውን የተጋሩበት እና በተለይም በምእተ አመቱ የልማት ግብ ከሚጠበቁት ውጤቶች አንጻር ሁኔታዎች የሚሻሻሉበትን መንገድ መወያየት የተቻለበት ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ወደ /300/ የሚደርሱ ሳይንሳዊ ወረቀቶች እና ፖስተሮች ቀርበው እንደነበር የማይዘነጋ ነው ብለዋል፡፡
22ኛው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ኮንፍረንስ ለዚህ አመት መነጋገሪያ እና የትኩረት ወይም የስራ አቅጣጫ ያደረገው መረጃን መሰረት ያደረገ የእናቶች እና የህጻናት ጤን ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምእተ አመቱን የልማት ግብ ቁጥር 4/ን አሳክታለች፡፡ የእናቶችን ጤንነት ማሻሻል እና ሞትን መቀነስን በሚመለከትም ስራዎች ለመሰራታቸው አመላካች ነገሮች ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ችግሮች እንዲቃለሉ የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ማህበሩ እና አባላቱ በተለመደው መንገድ ጥረታቸውን ይቀጥላሉ እንደ ዶ/ር ይርጉ ንግግር፡፡
አመታዊው እና የማህበሩ የትኩረት አቅጣጫ መረጃ ላይ የተመሰረተ የእናቶችና የህጻናት ጤና ሲሆን በዚህ ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች ቀርበዋል፡፡
በስብሰባው ላይ ከቀረቡት ጥናታዊ ስራዎች መካከል ከእናቶች ወደህጻናት የኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይተላለፍ በመቀነስ ዙሪያ ፕሮግራሙን እና ሳይንሳዊውን አተያይ የተመለከተ ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ ጨቅላ ሕጻናትን፣ የእናቶች ሞትን ምክንያት ማወቅን፣ በአማራ ሁለት ወረዳዎች ላይ ያተኮረ የእናቶች እና የህጻናት ጤና ክትትል የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በደቡብ አካባቢ በቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እና ተያይዞም በኤችአይቪ ኤይድስ ዙሪያ የሚደረገውን የጤና ክትትል እንዲሁም እናቶች ከእርግዝና ጋር በተያያዘ በተለይም በመውለጃ ሰአት ሊደርስባቸው የሚችለውን የጤና ጉዳት አስቀድ መው ሊያውቁ እንደሚገባ የሚጠቁም ጥናት ከሐራማያ ቀርቦአል፡፡ ከላይ የተገለጹት በኮንፍረንሱ ላይ ከቀረቡት ጥናቶች በመጠኑ የተወሰዱ ናቸው፡፡
ስብሰባውን የከፈቱት ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ...
“... በእናቶች እና ሕጻናት ጤና ላይ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ ብዙ ለውጦችንም እያታዩ ነው፡፡ በተለይም ነብሰጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት ክትትል እንዲያደርጉ እና በጤና ተቋም እንዲወልዱ የሚያስችላቸው አሰራር በስፋት ተዘርግቶ በዚህም አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሆስፒታል እና ጤና ጣቢያ እናቶች ለመውለድ ሲመጡ አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ እየተደረገ ነው፡፡ ይህንንም ለማሟላት አስፈላጊው ስልጠና እና የህክምና መገልገያ አቅርቦቶች እየተሟሉ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህብረተሰቡን በሚመለከት የጤና የልማት ሰራዊት በየቦታው ተገንብቶአል፡፡ ይህ ሰራዊትም ሁሉም እናቶች በጤና ጣቢያ ሄደው እንዲወልዱ አስፈላጊውን እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ይህንን ፕሮግራም በጥንቃቄ እና በትኩረት እየተከታተሉ ያስፈጽማሉ፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ሰአት በጤና ተቋም የመውለድን ባህርይ አምና በተመሳሳይ ሰአት ከነበረው ሁኔታ ጋር ስናነጻጽረው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ወደ 30% ያህል አድጎአል፡፡ ዶ/ር ታዬ አያይዘው እንደገለጹትም የተያዘው አሰራር በዚህ አካሄድ ከቀጠለ በአመቱ መጨረሻ ላይ 50% ወይንም 60% እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእናቶችን ጤና ከመጠበቅ እና ሞትን ከመቀነስ አንጻር ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ  የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ሲሆን የዚህም አላማው እናቶች በመረጡ ጊዜ ልጆችን እንዲወልዱ ማድረግ ነው፡፡ ይህንን በሚመለከትም ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን የኤክስቴንሽን ሰራተኞች በየቀበሌው በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የጤና የልማት ሰራዊቱም ይህንን እንደ አንድ ትልቅ ተልእኮ ወስዶ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ የዚህ የስራ ውጤት እንደሚያሳየውም ቀደም ባሉት አመታት ወደ 27%  የነበረውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነት ወይንም ተጠቃሚነት ዛሬ ግን ወደ 39% ደርሶአል፡፡ ስለዚህም ጥሩ ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ሌላው የጨቅላ ሕጻናት ጤንነት ጉዳይ ሲሆን አገልግሎቱም እየተስፋፋ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የህጻናት ሞት በመቀነሱ በምእተ አመቱ የልማት ግብ ስኬት ላይ ለመድረስ ተችሎአል፡፡ በአጠቃላም አሁን ያሉት እንቅስቃሴዎች እጅግ የሚያበረታቱ ቢሆንም ወደፊት ደግሞ ከተመዘገበው በላይ ውጤትን ለማምጣት ጠንክረን መስራት እንዳለብን እናምናለን ብለዋል ዶ/ር ታዬ ቶሌራ፡፡
የህክምና ባለሙያዎች በከተሞች ካልሆነ በስተቀር ህብረተሰቡ ዘንድ የመድረሳቸው ሁኔታ እምብዛም አይደለም በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ ዶ/ር ታዬ ቶሌራ ሲመልሱ...
“...በእርግጥ መስራት የሚገባንን ያህል ሰርተናል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን በእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ ሁለት ሁለት አዋላጅ ነርሶችን አሰልጥነን መድበናል፡፡ በሆስፒታሎችም ከአዋላጅ ነርሶች በተጨማሪ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ተመድበው እየሰሩ ነው፡፡ ስለዚህ በእርግጠኝነት በጤና ጣብያዎችም ሆነ በሆስፒታሎች ደረጃ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያ አሉ ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ስለዚህ ማስተላለፍ የምፈልገው መልእክት የጤና ተቋማቱ በባለሙያም ይሁን በአቅርቦት ደረጃ የተሟሉ በመሆናቸው እናቶች በእርግዝና ጊዜ እየሔዱ ክትትል እንዲያደርጉና በጤና ተቋም በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲወልዱ ማድረግ ነው፡፡ የቅብብሎሽ ስርአቱም በጥሩ ሁኔታ የተዘረጋ ስለሆነ ምናልባት በጤና ጣብያ መውለድ የማይችሉ ከሆነ ወደሆስፒታል የሚተላለፉ በመሆኑ በዚህ ረገድ ምንም ስጋት ሊኖራቸው አይገባም ብዋል ዶ/ር ታዬ ቶሌራ፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 22ኛው አመታዊ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ፌብረዋሪ 25/2014 ተጠናቆአል፡፡

Read 2928 times