Saturday, 15 March 2014 12:05

ሉሲፈር

Written by  ዮናስ ነማርያም
Rate this item
(6 votes)

            ሰሜን ሆቴል እና በዮሐንስ መሀል ላይ-ዳትሰን ሰፈር፡፡ የቀለጠው መንደር። ሰፈራችን በመጠጥ ቤት እጥረት አይታማም፡፡ ሄድ ሲሉ ቡና ቤቶች፣ እጥፍ ሲሉ ግሮሰሪዎች … ወረድ ቢሉ የአረቄ ቤት ድርድር … ጠምዘዝ ቢሉ ጠጅ ቤት፡፡
ጠጅ ቤት ተሰይሜያለሁ፡፡ አራተኛ ብርሌ ወደማገባደዱ ተዳርሻለሁ፡፡ … ሁለት ወጣቶች ገቡ፡፡ ከፊት ለፊቴ ተቀመጡ፡፡ የተቀዳላቸውን ጠጅ በፍጥነት ጭልጥ አደረጉ፡፡ ሌላ ብርሌ - ጭልጥ! ሦስተኛ ላይ ሰከን አሉ፡፡ ባቄላ አሰፍረው በመስገብገብ አሻመዱ፡፡
…አራት! አራት! ቅቅል እንቁላል ዋጥ ስልቅጥ አደረጉ፡፡ ጨዋታ ጀመሩ ልበል-አልዘለቁበትም፡፡ የፔርሙዝ ቡና የምትሸጠው ስትገባ ገቱት፡፡ ሁለት ሁለት ሲኒ ቡና ጠጡ፡፡ አፍታም ሳይቆዩ ሲጋራ ለኩሰው ይለመጥጡ ጀመር፡፡ የሲጋራው ጢስ በዙሪያቸው ተጉተለተለ፡፡ በዚያ የጭስ ጉም ሽንቁር፣ የአንደኛውን ልጅ እይታ ተከትዬ ሳማትር አይኔ ፀዳለ ላይ አረፈ፡፡ ፀዳለ አደገኛ ቀምቃሚ ናት። እግረ መንገዷን ቢዝነስ ትወጣለች። ልጁን ጠቀሰችው። እንደማግኔት ስባ ከጎኗ አስቀመጠችው። ጥቂት ተጨዋወቱ ልበል-ተያይዘው ወጡ፡፡
ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጠጅ-ባቄላ-ቅቅል እንቁላል-ቡና-ሲጋራ-ሴት! አቤት የአምሮት መዓት! ከዚያስ የትኛው አምሮቱ ያገረሽበት ይሆን?
ከቀረው ልጅ ጋር ወግ ጀመርን። ለሦስት ዓመት ወህኒ ወርደው ዛሬ መፈታታቸውን አጫወተኝ፡፡ … ሸምገል ያሉ እንግዳ ብርሌ አጣቢ ላይ አይኔ አረፈ። ግር አለኝ፡፡ ፍቃዱስ? … ጠጅ ቀጂውን ጠርቼ “ብርሌ አጣቢው ፍቃዱስ?”  
“ለመስቀል ሀገር ቤት ገባ፤ ጋሼ… ወጪውን ሁሉንም ነገር ችለው ላኩት።” … ፍቃዱን ቢያንስ ለአምስት ዓመት እዚሁ ጠጅ ቤት አውቀዋለሁ፡፡ ስለ ፍቃዱ ማንም ምንም አያውቅም፡፡ የትውልድ ሀገሬ እዚያ ነው - ከዚህ መጣሁ - ከዚህ ፈለስኩ - ሲል አይደመጥም፡፡ ጉራጌ መሆኑ ግምቴ ነው፡፡ ጥርት ባለ አነጋገሩ፡፡ መስቀል ብሎ ሀገር ቤት ገብቶ አያውቅም፡፡ ብርሌ አጣቢ የነበሩ ወደ ቀጂነት ደረጃ ከፍ ሲሉ፣ ፍቃዱ ከብርሌ አጣቢነት ፈቅ አላለም፡፡ ብርሌዎቹን እንደ መስተዋት ጥርት አድርጎ ማጠብ ከምንም ነገር በላይ ያረካኛል ይላል፡፡ ለብርሌዎቹ ልዩ ፍቅር አለው፡፡ በጠጅ ቤት አንባጓሮ ለምን ሰላሳ ሁለት ጥርስህ አይረግፍም ፍቃዱ ቅንጣት የሀዘኔታ ስሜት አይማውም፡፡ የአንድ ብርሌ መሸረፍ ግን ቱግ! አድርጎት፣ ሽራፊውን አንቄ ካልገደልኩ የሚል ሰው ነው፡፡ የመጨረሻዋን ብርሌ ጠጅ ጨለጥኩ፡፡ አስር ብር ከፍዬ ወጣሁ፡፡
“በዚህ የኑሮ ውድነት ጠጅ ባይኖር ምን እንጠጣ ነበር?”
 “መርዝ!”
መስከረም 17 ቀን 1999 ዓ.ም
መስቀልን አየር ጤና አክስቴ ቤት አሳለፍኩ። ደንገዝገዝ ሲል ወደ ሰፈሬ ለመመለስ ተነሳሁ፡፡ ታክሲ ከመያዜ በፊት አንድ ሁለት ብልስ ብዬ ግሮሰሪ ገባሁ። ደብል አፕሬቲቭ አዘዝኩ፡፡ ከውስጥ አንድ ሰው ወጣ-እንዴ ፍቃዱ! … እሱም ዞር ሲል እኔን በማየቱ ዱብዳ ሆኜበት በግርምት አፈጠጠብኝ፡፡ የምንተፍረቱን “ሰላም ነህ… በዓልስ?” ብሎ ወንበር ስቦ ከጎኔ ተቀመጠ፡፡ “ለመስቀል ገጠር የገባህ መስሎኝ?”  
“ከአመታት በኋላ ለመስቀል ገጠር ገባ የተባለው ብርሌ አጣቢ፣ አየር ጤና ገብቶ ስታገኘው ግር ይላል፡፡ ሁሉንም አጫውትሃለሁ፡፡” አለና ደብል ኡዞ አረቄ አዘዘ፡፡ … አልኮሉን በአንድ ትንፋሽ ጨለጠ። ፊቱን ልብ ብዬ አየሁት፡፡ እርጅና እና መታከት ታትሞበታል፡፡
“… በአስራ ስድስት ዓመቴ ነበር ከገጠር አዲስ አበባ መርካቶ የገባሁት። ሰባት ዓመት ልብስ ሰፊውን አጎቴን እየረዳሁ ሙያውን ተማርኩ፡፡ … አጎቴ በማረፉ የልብስ ስፌት መኪና እና ቤቱን ወረስኩ፡፡ በልብስ ስፌት ከራሴ አልፌ ለቤተሰብ ተረፍኩ…”
ኡዞውን ጨለጠ፡፡ እኔም ጨለጥኩት፡፡
“ዛሬም ቀኑ ትዝ ይለኛል፡፡ ጥር 15 ቀን 1980 ዓ.ም ሦስት ቀዘባ የመሰሉ የመንደሬ ልጃገረዶች ቤተሰብ ሊድራቸው ዳር ዳር ሲል ጠፍተው አዲስ አበባ መጡ። ያረፉት መርካቶ እኔው ዘንድ ነበር … ለገሃር በሚገኝ ገበያው የደራ ምግብ ቤት ዋስ በመሆን አስቀጠርኳቸው … በየወሩ ዕረፍት ሲወጡ በቀጥታ የሚመጡት እኔው ቤት ነበር … አንዷ እቃውን ታጥባለች፤ ሌላዋ ልብሴን… ሦስተኛዋ ምግብ ታዘጋጃለች … እናም ያንን የገጠር ውብ ሕይወት እያነሳን፣ እየበላን እየጠጣን መሳሳቅ ነው። … እንደዘበት አመታት ተቆጠሩ፡፡” አለና አረቄውን ጨለጠ፡፡ እኔም አፕሬቲቬን …
“በሆነ በዓል ከምግብ፣ ከመጠጡም ገደብ አልፈን ስንጯጯህ በመሀል ጤናዬ … “ሌላ ሴት አልያዝክ፤ ወጣት ነህ … እንዴት አንዳችንንም ለፍቅር አልጠየከንም … ይህን ያህል መልከ ጥፉ አይደለን… ወይንስ … ያ ነገር የለህም። ያለ መጠን የጋፈችው ፊልተር ጠላ፤ የሴትነት ይሉኝታዋን አሳጥቶ፣ ሆድ ያማውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ… በንግግሯ ክው አልኩ፡፡ ውዴ እና የሺ፤ በጤናዬ ጋጠ ወጥ ጥያቄ ደንገጥ ቢሉም፣ የእኔን ምላሽ ለመስማት አፈጠጡብኝ፡፡ ምን ብዬ እንደምመልስ ግራ ገባኝ … በርግጥ ወጣት ነኝ፡፡ የ25 ዓመት ጉብል-የቀይ ዳማ ሰልካካ… አይናማ ወጣት…”
የዛሬውን ፍቃዱ ልብ ብዬ አስተዋልኩት። ተጨራምቶ የወየበ ፊቱ ጥንታዊ ብራና ይመስላል ልበል፡፡ “እንደ እህቶቼ እንደማያቸው ቀበጣጠርኩ … ያቺ እርጉም ጤናዬ ‘ድንቄም እህትነት! ባህታዊ አይደለህ! ለዚህም ነው ያ ነገር!” … አላስጨረስኳትም፡፡
“ጋጥ ወጥ አግድም አደግ ባለጌ ነሽ!” ስል ጤናዬ ላይ ደነፋሁ … እየተመናቀረች ወጣች፡፡ የሺ ልትመልሳት ተከተለቻት። ሁለቱም አልተመለሱም።”
“ውስጥ የቀረችው ልጅስ?”
“ውዴ! … ዛሬም እንደ ህልም ያ ትዕይንት ምትሀት ሆኖ ይታየኛል፡፡ ከጎና ተቀመጥኩ - ልጥፍ አለችብኝ፡፡ እርቃን የቀረ ጭኗ ላይ አይኔ ተጣበቀ። ቀና ስል አይኖቿ ተቀበሉኝ፡፡ የብርሃን ፀዳል ይረጫሉ፤ ያ የብርሃን ሞገድ ነዘረኝ፡፡ ጣዝማ መሳይ ማር አካሏ ላይ አጣበቀኝ፤ ንጥር ስሜቷን ያለ ንፍገት ጋበዘችኝ… ድንግል ነበረች” መጠጡን በፍጥነት ጨለጠ፡፡ የታሪኩንም አዙሪት በፈጣን ምላሱ አሾረው…
“በሳምንቱ የሺ ብቻዋን ቤቴ መጣች … ያውም በምሽት - ጉንጯን የምስም መስዬ ከንፈሯን መጠጥኩ - የወይን ዘለላ እንደ መምጠጥ ነበር … አንዳችም ተቃውሞ አላሳየችም - እንዴት በእርቃን እንደቀረን አላስታወስንም … ጡቶቿ መሀል ሟሟሁ - ከሰማይ ሰማያት በላይ በሩካቤ ሰረገላ ተንሳፈፍን - ከዋክብት ከሰሙ፤ እንደ አበባ ረገፉ - ብር አምባር ሰረበልዎ! ላቤ እንደ ጤዛ ኮለል ብሎ ወረደ - እንባዋ ገባር ወንዝ ሆኖ ተመመ”
… ደም፡፡ ላብ፡፡ እንባ፡፡ ፍቅር። የማላውቀው ንዴት ብልጭ አለብኝ። ግንባሩን በብርጭቆ ብበረቅሰው በወደድኩ፡፡ ፍቃዱ ትረካውን ቀጠለ …
“… ውዴና የሺ ድብብቆሽ የያዙ መሰለኝ፡፡ ሁሌም የሚመጡት ለየብቻ ነው፡፡ እንደበፊቱ የወር ፈቃድ ጠይቀው አንድ ላይ እየተንጋጉ መምጣቱን እርግፍ አድርገው ተውት፡፡ ጨዋታው በግል ሆኗል - የአልጋ ላይ ጨዋታ … እንዲህ በማፈራረቅ ለወራት ከሁለቱም ጋር ቀበጥኩ፡፡ … ከዕለታት በአንደኛው ቀን የሺህ “የወር አበባዬ ቀረ” ብላ ተንሰቅስቃ አለቀሰች … ዱብ ዕዳ ሆነብኝ፡፡ በየሺ እርግዝና ለሳምንታት ስጨነቅ ስጠበብ ውዴ አይኖቿ ቀልተው … ፊቷ አባብጦ “ሳልፀንስ አልቀርም-የወር አበባዬ? አለች”
“እንዴት ተደርጎ?”
“ያደረግነውንማ ታውቀዋለህ!”
የምይዝ የምጨብጠውን አጣሁ፡፡ በየተራ እየመጡ መነፋረቅ ሆነ … ቀናት እንደዘበት ነጎዱ … በዕለተ ሰንበት ሁለቱም አብረው መጡ፡፡ ባለማመን አፈጠጥኩባቸው … ሀቁን ተነጋግረው ነበር፡፡ በወሲብ የተለያየ ጓደኝነታቸው፣ እርግዝና አንድ አድርጓቸው … መላቀስ ሆነ፡፡
እኔም ሆድ ብሶኝ ለስንቱ ዘመድ የመጨረሻ መሰናበቻ የሚሆነኝን እንባ እንደ ጎርፍ አፈሰስኩት … ‘እሳትን በእንባህ ልታጠፋው አትችልም’ እንደሚባለው የሚበጀውን ተነጋገርን - ለማስወረድ … ሁለቱም ተስማሙ … በሳምንት ጊዜ ውስጥ ሁሉንም አጠናቅቄ እንደማሳውቃቸው ቃል ገባሁላቸው፡፡
ልምድ አለው የተባለው ዲረሰር በሰው በሰው አገኘሁ … በቀጠሮአችን ሁለቱንም ብጠብቃቸው ዝር አላሉም … እንዲያውም ቤቴ መምጣት እርም ብለው ቀሩ … ወደ ሚሰሩበት ምግብ ቤት ሄጄ፣ ዘበኛውን ውዴን እና የሺ እንዲጠራልኝ ስጠይቀው፣ ቤቱን መልቀቃቸውን በደፈናው ነገረኝ … ቀና ስል ጤናዬ በረንዳው ላይ ቆማ ቁልቁል ስታየኝ፣ በርግጌ እብስ አልኩ፡፡
የት ሄዱ? እንደ እንፋሎት አየር ላይ በነኑ-ተነኑ…
የዚያኑ ዕለት ማምሻውን ጤናዬ አይኗን በጨው አጥባ ቤቴ መጣች፡፡ ሰይጣን ቤቱ እንደገባ ቆሌዬ ተገፈፈ…” አለና አረቄውን ሳበ፡፡ ለሻከረው ድምጹ ጥራት ይሆን? … እኔም አፕሬቲቬን ተጎነጨሁ - ለጆሮ ጥራት መሆኑ ነው፡፡
“ጤናዬም እየተንተፋተፈች … የምግብ ቤቱ ባለቤት የእነውዴን ነፍሰጡርነት ተጠራጥረው እንደጠየቋቸው… ሁለቱም ማመናቸውን … አስወርዳለሁ ብለው ሕይወታቸውን እንዳያጡ - ወደ ቤተሰብም ሂደው እንዲወልዱ አሳምነው፣ ሁሉንም አሟልተው እንደሸኟቸው መሰሪዋ ጤናዬ ነገረችኝ …
እነ ውዴ ሀገር ቤት በገቡ በመንፈቁ አንድ ዘመዴ ከአባቴ የተላከ ደብዳቤ ይዞልኝ መጣ። የሰማውንም ጉድ እንደ ዶፍ አወረደው፡፡ የአቶ አርጋው ልጅ ፍቃዱ፤ ሁለት የዋህ ልጃገረዶችን መስተፋቅር አስነክቶ ድንግልናቸውን ገሰሰ፤ አስረገዘ የሚለው ወሬ እንደ ተስቦ በአንዴ መንደሩን ማዳረሱን … በቅርቡ ከአዲስ አበባ የመጣ እማኝም፣ ጤናዬ ከፍቃዱ ቤት በምሽት ስትወጣ በአይኑ በብረቱ ማየቱን - ሦስተኛዋ እርጉዝ በቅርቡ ካልገባች ከምላሴ ፀጉሩ ይነቀል ብሎ ማውራቱን… ሀገር ጉድ አለ፡፡ ፍቃዱ አርጋው ከዚህ መንደር የወጣ ሳይሆን ነፍሱ ከሲኦል የወጣች፣ ደም የጠማኝ ጋኔንነቴ ፀድቆ “ሉሲፈር” የሚል ቅጽል እንደወጣልኝ … ዘከዘከልኝ።
የአባዬን ደብዳቤ አነበብኩት … በተከበረበት ሀገር በውርደት ቅስሙ መሰበሩን - የልጅ እባብን ማሳደጉን … ቢሞት ቀብሩ ላይ እንዳልደርስ … ያኔ ውስጤ ተናደ፤ ከቀምቃሚነቴ ጋር ተዳምሮ ለሞራል ውድቀት፣ ለብኩንነት በቃሁ-ወፈፍ አደረገኝ… ሥራዬም ተበለሻሸ … አመታት እንደ ወንዝ ፈሰሱ - ከብርሌ አጣቢነት የሕይወት ደለል ላይ ጣሉኝ…           

Read 6009 times