Saturday, 15 March 2014 14:24

“እጅግ በጣም ትልቁ የብረት በር እንኳን የሚከፈተው በትንሽ ቁልፍ መሆኑን አትርሳ” ቻርለስ ዲከንስ

Written by 
Rate this item
(9 votes)

            ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ማታ ላይ፤ አንድ ሰው ወደ አንድ ቡና ቤት፣ አንድ አሣማ ይዞ ይገባል። የቡና ቤቱ የመጠጥ ኃላፊ፤ በጣም ጠንቃቃና የጉጉት-ዐይን ያለው ዓይነት ሰው ነው፡፡ ሰውዬው ይዞት የመጣው አሣማ አንድ እግሩ በእንጨት የተጠገነ ነው፡፡ ይህንን የመጠጥ ኃላፊው አይቷል፡፡
ወደ እንግዳው ሄዶ እንዲህ አለው፡-
“ይህ አሣማ ምን ሆኖ ነው አንድ እግሩ እንጨት የሆነው?”
ሰውዬውም፣
“አንድ ቢራ ከሰጠኸኝ፤ ስለዚህ ልዩ ባህሪ ስላለው አሣማ ታሪክ እነግርሃለሁ!” አለው፡፡
የመጠጥ ኃላፊው፤ “መልካም፡፡ ጥሩ ታሪክ የሚወጣው ስለመሰለኝ፤ እንካ አንድ ቢራና ታሪኩን ትነግረኛለህ” አለና አንድ ቢራ አቀረበለት፡፡
“ስለዚህ ተዓምረኛ አሣማ ልንገርህ” አለና ጀመረ ያ ሰውዬ፡፡ “በጣም ልዩ አሣማ ነው፡፡ አንድ ማታ፤ ከአንድ ዓመት በፊት ገደማ፣ ድንገት ቤቴ በእሳት ተያያዘ፡፡ ይሄኔ ያ አሣማ ከበረቱ በርግዶ ወጣና፣ ወደ ቤቴ መጣ፡፡ ሁለቱን ልጆቼን ተሸክሞ ይዟቸው ወጣ፡፡ እኔና ሚስቴንም ሰላም ወደሆነው ሥፍራ ይዞን ወጣ! ስለዚህ፤ ቤተሰቤንና ህይወቴን አዳነልኝ ማለት ነው!!”     
ያ የመጠጥ ክፍል ኃላፊም፤ በታሪኩ ተገርሞ፣
“በጣም የሚገርም ጉድ ነው፡፡ ግን ለምን አንድ እግሩ እንጨት ሆነ?” አለው ደገመና፡፡  ሰውዬውም፤
“አንድ ቢራ ከጋበዝከኝ የዚህን ተዓምረኛ አሣማ ታሪክ እነግርሃለሁ” ይለዋል፡፡ የመጠጥ ክፍል ኃላፊው ምሥጢሩን ለማወቅ በጣም ጓጓ፡፡ ካረግኸው ጥሩ፤ ብሎ አንድ ቢራ ጨመረለት፡፡
ሰውዬውም፤
“ከእኔ ቤት ጀርባ አንድ ሐይቅ አለ፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን፤ ጀልባ ይዤ ልቀዝፍ ወጥቻለሁ፡፡ ድንገት ማዕበል መጥቶ ጀልባዋ ተገለባበጠች፡፡ እኔ እጀልባዋ ወለል ላይ ተፈጠፈጥኩ፡፡ ከዚያ ወዲያ መዋኘት አልቻልኩም፡፡ ይሄ አሣማ ያንን አውቆ፤ በረቱን በርግዶ ወጥቶ ወደ እኔ ዋኝቶ መጥቶ ወደ ሐይቁ ዳርቻ ወሰደኝ፡፡  መተንፈስ አቅቶኝ አሸዋው ላይ ተንጋለልኩኝ፡፡ ከዚያ ወደ ቤቴ ሄዶ፣ ባለቤቴን ቀስቅሶ ይዟት መጣ፡፡ እሷ ትንፋሽ መግባኝ ነብሴን ዘራሁ፡፡ ይሄ አሣማ ህይወቴን አዳነልኝ” እልሃለሁ አለው፡፡
የመጠጥ ክፍሉ ኃላፊ በጣም ተደንቆ፣ ግን በመጠኑ ትዕግሥት አጥቶ፤ “በጣም አስደናቂ ትንግርት ነው፡፡ ግን የአንድ እግሩ እንጨት መሆን ሚሥጥር ትርጉሙ ምንድን ነው?” አለና ጠየቀው፡፡
“አንድ ሌላ ቢራ ጋብዘኝና እነግርሃለሁ…” አለው፡፡ ባለ መጠጥ ቤቱ ሌላ ቢራ ከፈተለት፡፡
“ስለዚህ ተዓምረኛ አሳማ አሁን ልንገርህ፡፡ ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ አውሎ ንፋስ ተነስቶ እኔ ለመሸሽ ወደ ምድር ቤት ስሮጥ አዳለጠኝና ወደቅሁኝ፡፡ አሳማ ሆይ ከበረቱ በርግዶ ወጥቶ እየጐተተ ምድር ቤት አውርዶኝ ከአውሎ-ነፋሱ ተረፍኩኝ እልሃለሁ”
ባለ መጠጥ ቤቱ ይሄ የመጨረሻው ተዓምር መሆን አለበት ብሎ፤
“ይገርማል ተዓምረኛ አሣማ ነው ባክህ! ከእሣት፣ ከውሃና ከአውሎ ነፋስ አዳነህ! ግን ይሄ የእንጨት እግሩ ከየት መጣ?”
ሰውዬውም በመጨረሻ፤     
“እንዲህ ያለውን ተዓምረኛ አሣማኮ ሁሉንም ባንድ ጊዜ አትበላውም፡፡ ቀስ ቀስ እያልክ፣ ትንሽ ትንሽ ብልቱን እየለየህ፣ ነው መብላት ያለብህ!!” አለው፡፡   
*    *    *
ለአገር ባለውለታ የሆኑን ሰዎች በምንም ዓይነት ውለታቸውን መርሳት አይገባንም፡፡ ሁሉም ዜጋ የየራሱ ድርሻ አለውና ያንን አስተዋፅዖውን አለመርሳት ብልህነት ነው፡፡ የተሻለና የበለጠ ያገለገለን ዜጋ ደግሞ፤ የተሻለ እውቅና መስጠት ይገባናል፡፡ ይህ “ሥራ ለሠሪው እሾህ ላጣሪው” ዓይነት መንገድ ነው፡፡ ስለሆነም፤ የሀገርን የዕድገት መንፈስ የሚያፀና ነው!
አስተሳሰባችን ሙሉ ይሁን፡፡ ለእኛ የሚመች የሚመቸውን ብቻ የፖለቲካ መዘውር ነው ካልን የሚያጎድለን እንጂ የሚያሟላን ፀጋ አልጨበጥንም ማለት ነው፡፡ ጨቋኝና ተጨቋኝ  ባለበት አገር በድሮው አነጋገር Class based society ውስጥ የተበዳዩን ቁጥር ለመቀነስ ፍትሐዊ አስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ “በምድር ላይ የሚራመድ አንድ ‘ባሪያ’ እስካለ ድረስ፤ ሙሉ በሙሉ ነፃ አንወጣም” ይሉናል ፀሐፍት። መልካም አስተዳደር እኛ እንደምንገምተው ቀላል አይደለም፡፡ ባህላዊ ታሳቢ እሴቶችን ሳናመዛዝን፤ የውጪውን አስገብተን እንዳለ ህዝባችን ላይ እንጫን ብንልም ዓላማው ጉዳዩን ከማወሳሰብ አያልፍም፡፡ ለዚህ ነው በሀገራችን መሻሻል የማናየው፡፡ ከመሠረታችን እንደማተባችን የማንበጥሳቸው አልበገር-ባይነት (Resistance) ውስጣችን አለ፡፡ ያንን ለማውጠንጠን ነፃ አስተሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ መንግሥትም የራሱን ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ህዝብም እንደዚሁ ይህ ይሆን ዘንድ መጣጣር አለበት፡፡ የረዥም ጊዜ ግልፅ ውይይት፤ ሀሜትን ያስወገደ ዕውነተኛና ልባዊ ለውጥ ላይ ያተኮረ ረዥም ጉዞ ያስፈልገናል። ችግሩ እንግዲህ፤ መለወጣችንን የሚያይልን ራሱ ያልተለወጠ ሰው ከሆነ ተያይዞ ገደል መግባት ሊሆን ነው፡፡ ለምሳሌ ይሄ የእገሌ፣ ያ የእገሌ ብሄረሰብ፣ ጎሣ፣ መንደር ወዘተ ሰው ነው በሚል ሌላውን አሳንሶ የማስቀመጥ አመለካከት፤ እንደቀንድ-አውጣ ውስጣችን ያደፈጠ የለውጥ እንቅፋት ነው። ለፍቅረኞች ቀን፤ የአበበ ዘንግ ሽያጭ፤ አበባ ልብን ላያመላክት ይችላል! ገቢ አለ፡፡ በገቢው የምንሠራው ምንድነው? ይሄ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ሲነገር ሰምተናል፡፡ ጠጋ ብለን፣ የችግሩ ምንጭ የት ጋ ነው ብለን ግን ለማጤን አልፈቀድንም፡፡ “አንድን ጉድ፣ ሺ ጊዜ ከሰው ከመስማት አንዴ ሄዶ በዐይን አይቶ እርፍ ማለት ይሻላል” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ የታመመ ሰውን ጠይቆ የሚነግረን ሰው፤ ስለበሽተኛው የግሉን ስሜት ብቻ አጋኖ እንደሚነግረን እረስተን፤ እኛም ያንኑ ወሬ ለሌላ ጆሮ እናስተላልፋለን፡፡ ሺ ጊዜ በማጉላትም ጣር-አልጋ ላይ ያለ ሰው አድርገነው ቁጭ እንላለን፡፡ አገራችን ታማለች ካልን ቀርቦ ማየት ነው፡፡ የሚሻለውን መምከር፣ የምትታከምበትን መላ መምታት ነው ያለብን፡፡
የሀገራችን ችግሮች እጅግ በርካታ ለመሆናቸው አዋቂ መጠየቅ አያሻንም፡፡ ተራ በተራ ለመፍታት መጣጣር ነው እንጂ የለም ብሎ መካድ ግን ቢያንስ ራስን ማታለል ነው፡፡ ከራሳችን አበሳ በተጨማሪ፤ በተጋቦት እስከሚመጡት የድምበርተኛ ጎረቤቶቻችን ችግር ድረስ፤ የችግር መተላለፊያ ኮሪዶር ነን ብለናልና፤ ኮሪዶሩ መጠረግ አለመጠረጉን አለማረጋገጥ ለባሰ መዘዝ ይዳርገናል፡፡ “እንኳን አሁንና ብዙ ትጥቅ እያለን
በጦር በጎራዴ፣ ታንክ እናማርካለን”
ማለት በዘመነ-ግሎባላይዜሽን (የለየለት ቅኝ-ገዢነት) እንደማያዋጣ ማንም ሊስተው አይገባም። የሀብት ምንጮቻችንን እንጠብቅ፡፡ የሰው ኃይላችንን፣ ጦራችንን በአግባቡ እንጠብቅ! ለገዛ ጥቅሙ በስተቀር ለእኛ ብሎ እሹሩሩ የሚለን የዓለም ታላቅ አገር የለም፡፡ “አበሻም ይሁን ፈረንጅ ማንም ህዝቡ ላይ ጫና ሊጥል አይገባም” የሚለውን አባባላችንን ማጥበቅ መልካም ነገር ነው! “አነስተኛ ነን ብለን እጃችንን መጠምዘዝ የለብንም፡፡ ችግራችን የብረት በር ሆኖብናል አንበል፡፡ “እጅግ በጣም ትልቁ የብረት በር እንኳን የሚከፈተው በትንሽ ቁልፍ መሆኑን አትርሳ” ይለናል ደራሲ ቻርልስ ዲከንስ፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል ነው ነገሩ!!   

Read 7564 times