Saturday, 22 March 2014 12:28

“የደም ባንክ ደም ሲሰጥ ሽራፊ ሳንቲም አይቀበልም”

Written by 
Rate this item
(3 votes)
  • ምትክ ደም መቅረቱ የደም ደላሎችን ከጨዋታ ውጭ ያደርጋል
  • ከ2500 በላይ ቋሚ በጎ ፈቃደኛ  ደም ለጋሾች አሉን
  • ታዋቂ ሰዎችን መጠቀማችን ለጋሾቻችንን እያበዛልን ነው

ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል ይባላሉ፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የብሔራዊ ደም ባንክ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በተለይ ከሶስት ዓመት ወዲህ ብሄራዊ ደም ባንኩ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ወጥቶ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመዛወር በርካታ የአሰራር ለውጦችን አድርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል ለበሽተኞች ደም ሲሰጥ የሚጠየቀውን ምትክ ደም አስቀርቶ ዜጎች ደም በነፃ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ  የደም እጥረት ቢያጋጥም ምን ሊፈጠር ይችላል የሚሉ ስጋቶች ይስተጋባሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በስጋቶቹ፣ በህገ-ወጥ የደም ደላሎች፣ በበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከዶክተር ዳንኤል ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ  አድርጋለች፡፡

ቀደም ሲል ብሄራዊ ደም ባንኩ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስር ነበር የሚተዳደረው፡፡ አሁን ወደ ጤና ጥበቃ ዞሯል፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ከደም ባንኩ አመሰራረት ብንነሳ በኢትዮጵያ የደም ባንክ የተመሰረተው በ1962 ዓ.ም ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 42 ዓመታት ደም ባንኩ ይተዳደር የነበረው በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ስር ነው። ደም ባንኩ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተዛወረበት ምክንያት ሚኒስቴሩ እያስፋፋ የሄደባቸው የጤና ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣት፣ ደም አቅርቦቱ ከፍላጎት ጋር አለመጣጣም በማስከተሉ፣ ይህንን ለማስተካከልና ካሉት የጤና ተቋማት ጋር አስተሳስሮ ለመምራት በመታሰቡ ነው፡፡  ከ2003 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ነው ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ወደ ክልል ጤና ቢሮዎች አገልግሎቱ እንዲዛወር የተደረገው፡፡
የደም ባንኩ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተዛወረ በኋላ አዳዲስ አሰራሮች እየመጡ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ታካሚ ምትክ ደም እንዲያመጣ የሚገደድበት አሰራር ቀርቶ በነፃ የሚገኝበት አይነት አሰራር እየተከተላችሁ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሊሰጡኝ ይችላሉ?
እንዳልሽው ቀደም ሲል አንድ ታካሚ ደም በሚያስፈልገው ከጊዜ ቤተሰቡ ወይም የቅርብ ሰው ምትክ ደም እንዲሰጥ ይደረግ ነበር፡፡ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በተለይም በአዲስ አበባ ይህ አሰራር ቀርቶ፣ አንድ ሰው ደም በሚፈልግበት ጊዜ የህክምና ባለሙያው ለዚህ ታካሚ ደም ያስፈልጋል ብሎ፣ ወረቀት ይዞ ይቀርባል፤ በቀጥታ ደሙ ይፈቀድለታል። ሁለተኛው አሰራር እና አዲስ የተጀመረው በተለይ በመንግስት ሆስፒታሎች እዚያው ሆስፒታሉ ውስጥ ሚኒ (ትንሽ) ደም ባንክ በማዘጋጀት፣ፍሪጃቸው ውስጥ ለሳምንት የሚበቃቸውን ደም ይወስዱና በሳምንቱ ሲያልቅ መጥተው ይወስዳሉ፡፡ በቀጣይ በግል ሆስፒታሎችም አሰራሩ ይቀጥላል፡፡ ይህ አሰራር በተለይ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ በደንብ እየተሰራበት ነው፡፡ ምክንያቱም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከሚሰበሰበው ደም አርባ በመቶውን ይጠቀማል፡፡ በቀጣይ ወደ የካቲትና ጳውሎስ ሆስፒታሎች የማስፋፋት ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡
ይህን አሰራር የግል ሆስፒታሎች መቼ የሚጀምሩ ይመስልዎታል?
በአሁኑ ሰዓት ለግል ሆስፒታሎች እየወሰዱ ለመስጠት ከባድ ነው፣ ምክንያቱም በአዲስ አበባ ውስጥ ከመቶ በላይ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት በመኖራቸው ሁሉንም ለማዳረስ ይከብዳል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው፣ ከደም ባንኩ ደም የሚወስዱት አዲስ አበባ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ እስከ መቶ ኪሎ ሜትር ያሉና ከዚያም በላይ እንደነደብረብርሃን ያሉት ሁሉ ደም ይወስዳሉ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ለሳምንት የሚበቃቸውን እንዲወስዱ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ እስከ ሻሸመኔ ድረስ ከዋናው (ከአዲስ አበባው) ደም ባንክ ይወስዳሉ፡፡ ዋናው ደም ባንክ ከፍተኛ ጫና አለበት፡፡
የክልል ጤና ቢሮዎች አሰራር ምን ይመስላል? ለምሳሌ የሻሸመኔ  ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ለምን ከክልሉ ደም ባንክ አይወስዱም?
ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ወደ 25 የሚጠጉ ደም ባንኮች ይገኛሉ፡፡ በዚህም በየመቶ ኪሎ ሜትር ራዲየስ የሚገኙ የግልና የመንግስት ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ከአቅራቢያቸው የደም ባንኮች እንዲወስዱ የሚደረግበት አሰራር እየተዘረጋ ነው፡፡ ለምሳሌ የሻሸመኔ ጤና ተቋማት ከአዳማ ወይም ከሀዋሳ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ አሁን ለጊዜው ባለው ሁኔታ ግን ከዋናው እየወሰዱ ነው፡፡ ነገር ግን እንዳልሽው አሰራሩ ተዘርግቶ ሲያልቅ ከየአቅራቢያቸው ደም ባንኮች እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡
አሁን 25 የደም ባንኮች መኖራቸውን ነግረውኛል። አዳዲሶች እንደተከፈቱም ጠቁመዋል። ቀደም ሲል በአገራችን ምን ያህል የደም ባንኮች ነበሩ?
ቀደም ሲል የነበሩት ከ12 አይበልጡም ነበር። ደም ባንኩ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተዛወረ በኋላ በተደረገው እንቅስቃሴ ወደ 25 አድገዋል። እነዚህም አዳዲስ ደም ባንኮች ስራ የጀመሩት ገና በቅርቡ ነው፡፡ በሙሉ አቅማቸው መስራት ሲጀምሩና በደንብ ሲጠናከሩ ቀደም ብለሽ ያነሳሽው በየአካባቢያቸው ደም የሚከፋፍሉበት አሰራር ይቀጥላል፡፡ አሁን ግን አዲስ እንደመሆናቸው የሚችሉትን ያህል እየሰሩ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ያሉት በደንብ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በኦሮሚያ በዚህ ዓመት ስድስት የደም ባንኮችን ከፍተው በደንብ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ አዳማ፣ ነቀምት፣ መቱ፣ ጎባ፣ ወሊሶ በደንብ እየሰሩ ነው፡፡ በጭሮ (አሰበ ተፈሪም) ደም ባንኩን ለመክፈት የሰራተኛ ቅጥርና በቢሮው ላይ የማስተካከያ ስራዎች እየተሰሩ ነው፤ በቅርቡ ይጀምራል፡፡
ቀደም ሲል ሰዎች ምትክ ደም እንዲያመጡ የሚገደዱበት አሰራር ቀርቶ ሰዎች ደም በነፃ እንዲያገኙ መደረጉ ፋይዳው ምንድነው?
ይህ አሰራር እንዲቀር የተደረገበት ዋናው ምክንያት የዓለም የጤና ድርጅት (WHO)ም ሰዎች ደምና የደም ተዋፅኦዎችን በነፃ ማግኘት አለባቸው የሚል ሲሆን ደም መገኘትም ያለበት ከበጎ ፈቃደኞች ነው ይላል፡፡ ምክንያቱም አንድ ሰው ምትክ ደም በሚሰጥበት ጊዜ ግዴታ ነው። እናትህ ታማለችና ደም መስጠት አለብህ ተብሎ ይገደዳል፡፡ ይህ አሰራር በብዙ ምክንያቶች ጥሩ አይሆንም፤ ከምክንያቶቹ አንዱ ይህ ሰው የስነ-ልቦና ዝግጅት ላይኖረው ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በጤናው ላይ ችግር ሊኖርበት ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ለምሳሌ ኤችአይቪ በደማቸው ያለባቸው፣ ከቤተሰብ ደብቀው መድሃኒት የሚወስዱ ይሆኑና ደም ስጡ ሲባሉ ሚስጥሩ እንዳይታወቅ ደም ይሰጣሉ፡፡ ደማቸው ምትክ ሆኖ ሲቀርብ አያገለግልም፡፡ ከቤተሰብ በምትክ የሚገኝ ደም በአብዛኛው ለተለያዩ ችግሮችና በሽታዎች የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ በመረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡ በጎ ፍቃደኞች በየሶስት ወሩ የኤችአይቪ እና የሌሎች የጤና ምርመራዎች የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ስለሆነም የዓለም የጤና ድርጅት በ2020 ዓ.ም ሁሉም አገሮች መቶ በመቶ ደም ከበጎ ፈቃደኞች ብቻ እንዲሰበስቡ በሚል አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ አገራችንም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ነው እየተንቀሳቀሰች ያለችው፡፡ በመሆኑም የፌደራል ጤና ጥበቃም ይህን አቅጣጫ በመከተል መቶ በመቶ ደም ከበጎ ፈቃደኞች ብቻ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡
በጎ ፈቃደኞች የሚፈለገውን ያህል ደም መለገስ ባይችሉና ያለው ክምችት ቢያልቅ ምን ተማምኖ ነው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምትክ ደም እንዲቀር ያደረገው?
ይህንን ጉዳይ በጣም አስበንበት ነው የጀመርነው፤ ዝም ብሎ በስሜት የሚሰራም አይደለም፡፡ በደንብ አቅደንና አስልተነው ነው ወደ ትግበራ የገባነው። ከላይ ላነሳሽው ስጋት መፍትሄው በጎ ፈቃደኞች  እንዲለግሱ ግንዛቤ መፍጠርና ማስተማር ነው፡፡ ጠንክረን እስካስተማርን ድረስ እጥረት ይገጥመናል ብለን አናስብም። ሁለተኛው እጥረት በሚገጥመን ጊዜ ፈጥነው ደም የሚሰጡ ተመዝግበው የተቀመጡ ከ2500 በላይ በጎ ፈቃደኞች አሉን፡፡ እነዚህ በጎ ፈቃደኞች በማንኛውን ሰዓት እጥረት ቢገጥመን ደውለን የምንጠራቸው ቋሚ ደም ለጋሾቻችን ናቸው፡፡ ሆኖም የእነዚህን በቋሚነት ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር በ10 እጥፍ የማሳደግ እንቅስቃሴ እቅድ አለን፡፡ ስለዚህ ህብረተሰቡ ደም መለገስን ባህሉ እንዲያደርግ ከጣርን፣ እነዚህ ከ2500 በላይ ቋሚ ለጋሾቻችን በየሶስት ወሩ የሚሰጡን ደም ካለ፣ የህሙማንን ቤተሰቦች ደም በነፃ ስንሰጣቸው ማወቅ ያለባቸው ያህል ካስተማርናቸው እጥረት ሊገጥመን አይችልም፡፡ ለህሙማን ቤተሰቦች ደም በነፃ ከሰጠን በኋላ በደንብ አስተምረን፣ ወደፊት እነሱም ደም በመለገስ የሰዎችን ክብር ህይወት እንደያተርፉ ነግረን፣አድራሻቸውን ወስደን ነው የምናሰናብታቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች ዛሬ እናታቸው፣ እህታቸው ወይም ወንድማቸው በሌላ ሰው ደም መዳኑን ስለሚያውቁ፣ ነገ የሌላውን ህይወት ለማትረፍ እየመጡ ደም ይሰጣሉ፡፡ ይህን በተጨባጭ እያየነው ነው፡፡ በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የደም እጥረት ያጋጥመናል ብለን አናስብም ግን ብዙ መስራትን ይጠይቀናል፡፡፡
ደም ሻጭ ደላሎች ሰዎችን እያጭበረበሩ በአሰራሩ ላይ እንቅፋት ሆነዋል የሚሉ ቅሬታዎች አሁንም ሆስፒታሎች አካባቢ እየተደመጡ ነው፡፡ ይህን ችግር ታውቁታላችሁ?
በነገራችን ላይ ምትክ ደም አስቀርተን በነፃ መስጠት ስንጀምር አካባቢ፣ ትልቁ ራስ ምታታችን ደም ሻጭ ደላሎች ጉዳይ ነበር፡፡ አንድ ሰው በፊት ምትክ የሚሰጥለት ዘመድ ሳይኖረው ሲቀር “የሚሸጥ ደም አለ” እያሉ ደላሎች ካገናኙት በኋላ “የአጎቴ ልጅ ነው፣ የአክስቴ ልጅ ነው” እያለ ደም ገዝቶ ያመጣ ነበር፡፡ ደም ገዝቶ ያመጣ ነበር ሲባል ሻጩና ገዢው በደላላ ከተገናኙ በኋላ ተደራድረው “ዘመድ ነኝ” በማለት ደም ሰጥቶ ይሄድ ነበር፡፡ በተጠና ጥናትና ባለው መረጃ መሰረት፣ ደም ሻጮቹ ደማቸውን ሸጠው ለጫት፣ ለመጠጥ፣ ለአደንዛዥ ዕፅ መግዣ ነው የሚጠቀሙበት፡፡
እነዚህ ዕጾች ደግሞ ጤናማ ደም እንዳይኖራቸው ያደርጓቸዋል?
በትክክል! ለምሳሌ ከአደንዛዥ እፅ ጋር በተገናኘ ሱስ ያለባቸው ጠጥተው የሚሰክሩ ሰዎች ራሳቸውን ለኤችአይቪ ኤድስና መሰል በሽታዎች ሊያጋልጡ ይችላሉ፡፡ ይህን ደግሞ ራሳችን የምናጠናበት መንገድ አለ፣የታተሙ ጥናቶችም አሉ፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ ደም በገንዘብ የሚሸጡ ሰዎች “Paid donors” ይባላሉ፡፡ በእኛ አገር ደም አይሸጥም አይለወጥም፣ ይህ ወንጀል ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የደም ባንካቸው ገንዘብ እየከፈለ ደም የሚሸጡ አሉ። ይህ በስትራቴጂና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ አገር እንደ ስትራቴጂ የምንከተለው የበጎ ፈቃደኝነት ደም ልገሳን ነው፡፡ አሁን በዓለም ጤና ድርጅት ውስጥ አባል የሆነ አገር ደም መግዛትና መሸጥ ይከለክላል፡፡ ወደ ደም ሻጮች እና አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚዎች ደም ስንመጣ፣ከሚለግሱት ደም 50 በመቶው ጤናማ ባለመሆኑ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፡
ስለዚህ እኛም አገር እነዚህ ደም ሻጮች በቤተሰብ ምትክ ውስጥ ተሸሽገው ሊኖሩ ይችላሉ። ቤተሰብ ነኝ እያሉ ይመጣሉ፡፡ ያኔ ታዲያ ባለሞያዎቻችን ቤተሰብ ነው አይደለም የሚለውን ለማየት መታወቂያ መጠየቅና መሰል ስራዎች አስቸግረዋቸው ነበር። ምትክ ደም መቅረቱ ደም ሻጮችንና ደላሎችን ከጨዋታ ውጭ የሚያደርግ ነው፡፡
ግን እኮ አሁንም ሆስፒታሎች አካባቢ ይህ ማጭበርበር አልቀረም እየተባለ ነው?
እርግጥ አሁንም በተለይ ከገጠር የሚመጡ ወገኖች እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ አውጥተው ደም ይገዛሉ የሚባል ነገር ይሰማል፡፡ ይህ ግን ከደም ባንኩ ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ በፊትም ሆነ አሁን የደም ባንክ ደም ሲሰጥ ሽራፊ ሳንቲም አይቀበልም። ወደፊትም አይቀበልም፡፡ ማንኛውም ዜጋ ደም በነፃ ነው የሚያገኘው፡፡ የሰራተኞች ደሞዝ፣ የደም ከረጢትና የመመርመሪያ መሳሪያዎችን ወጪ መንግስት ነው የሚሸፍነው፡፡ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችም ከማንም ሽራፊ ሳንቲም ሳይፈልጉ በነፃ ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን በመሀል ቢሮክራሲ በመፍጠርና ሲስተሙን በማዛባት ገንዘብ ለማግኘት የሚጥሩ አንዳንድ ግለሰቦች አይኖሩም ማለት አይደለም። ሆስፒታሎች አካባቢ ከደም ጋር የተያያዘ ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ደም ለመስጠት ወይ ምትክ ደም አለበለዚያ ገንዘብ አምጡ እያሉ እንደሚያጭበረብሩ ሰምተን፣ ጉዳዩን እጅ ከፍንጅ ለመያዝ በድብቅ ክትትል አድርገን ነበር፣ እስካሁን ግን ያጋጠመን ነገር የለም፡፡ ይህ በግለሰብ ደረጃ ነው የሚደረገው፡፡ ሆስፒታሎችም አካባቢ የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው ግለሰቦች አይጠፉም። ዋናው ነገር ህብረተሰቡ ደም በነፃ የማግኘት መብት እንዳለው አውቆና ተገንዝቦ፣ “ምትክ አምጣ ገንዘብ፣ ክፈል” የሚሉ አጭበርባሪዎችን ማጋለጥና ለህግ ማቅረብ አለበት፡፡
ደም ባንኩ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተዛወረ በኋላ ያለው የደም ክምችት በምን ያህል ፐርሰንት ጨምሯል?
በዓመት ውስጥ የሚሰበሰበው የደም ክምችት ምን ያህል ነው የሚለውን ብንመለከት፣ ከሶስት አመት ወዲህ፣በፊት ከነበረው እጥፍ በሚባል መልኩ እየተሰበሰበ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ግን በአመት የሚሰበሰበው የደም መጠን ከ40 ሺህ ከረጢት በታች ነበር፡፡ አሁን ወደ ሚኒስቴሩ ከተዛወረ በኋላ ለሁለት አመቱ አፈፃፀም በዓመት ወደ 63ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ሌላው ቀርቶ በ2006 ዓ.ም በስድስት ወር ውስጥ 40 ሺህ ከረጢት ደም ተሰብስቧል፡፡ ይህ መጠን ከሶስት ዓመት በፊት በዓመት የሚሰበሰብ የደም መጠን ነበረ። ስለዚህ በእጥፍ መጨመሩን ያመለክታል፡፡ ይህ ለውጥ በሁለት መንገድ ነው የመጣው፡፡ አንደኛው የሰራነው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ነው። ትምህርቱ በቂ ነው ብለን ደረታችንን ባንነፋም በተቻለ መጠን ህብረተሰቡ ደም ልገሳ ላይ ያለው አመለካከት እንዲሰፋ እያደረግን ነው፡፡ ግን በጣም ይቀረናል፡፡ ሁለተኛው የደም ባንኮችን ቁጥር በእጥፍ ማሳደግ በመቻላችን ለውጥ አምጥቷል፡፡ በፊት  የደም ባንኮች አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ ትልልቅ ከተሞች ብቻ ነበር የሚገኙት፡፡ ለምሳሌ ደሴ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ አዳማና ሌሎች ከተሞች ነበሩ፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደም ባንኩን በስሩ ካደረገ በኋላ በሁሉም የክልል ከተሞች እንዲኖሩ አድርጓል፡፡ በተለይ በማደግ ላይ ያሉት እንደ አፋር፣ ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ ባሉትም ክልሎች የደም ባንክ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ወደፊትም የበለጡ ቅርንጫፎች እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡
በአዲስ አበባ ከ2500 በላይ ቋሚ ደም ለጋሾች እንዳሏችሁ ነግረውኛል፡፡ ከነዚህ በጎ ፍቃደኞች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
በጣም ከፍተኛ ግንኙነት አለን፡፡ አንደኛ በየአመቱ ሰኔ ሰባት ቀን የአለም ደም ለጋሾች ቀን በመሆኑ በዓሉን በደመቀ ሁኔታ እናከብራለን፡፡ ሁለተኛ ከደም ለጋሽ አስተባባሪዎች ጋር በየስድስት ወሩ ውይይት  አለን፡፡ ሶስተኛው መንገድ ዓመት በዓላት በሚኖሩ ጊዜ እየደወልን “እንኳን አደረሳችሁ” እንላለን፡፡ እንደ ቤተሰብ ነው የምናያቸው፣ የምንሳሳላቸው፣ እነሱም በየሶስት ወሩ ለደም ልገሳ ሲመጡ እንገናኛለን፡፡ የጤና ምርመራ፣ የምክር አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ በዚህ በዚህ መልኩ መልኩ የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለስልጣናት ደም እየለገሱ ነው፡፡ ይህ ምን ያህል ረድቷችኋል?
ጥሩ! አንደኛ እነዚህ ትልልቅ ሰዎች በተለይም የፌዴሬሽንና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤቶች አፈ ጉባኤዎች አቶ አባዱላ ገመዳና አቶ ካሳ ተክለብርሃን ደም ሲሰጡ ድርብ ኃላፊነት እየተወጡ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ባለስልጣናት በህዝብ የተመረጡ ናቸው። ስለዚህ የመረጣቸውን ህዝብ ለማስተማር እነሱ በተግባር ማሳየታቸው ህብረተሰቡ ላይ መነሳሳትን ፈጥሯል። አርአያ በመሆን ለሌሎች ለጋሾች ብርታትን ሰጥተዋል፡፡ እነ አትሌት ሀይሌ ገ/ሥላሴ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ እነ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ፣ እነ አርቲስት አብርሀም ወልዴ እና መሰል ታዋቂ ሰዎች መጠቀማችን ለጋሾቻችንን እያበዛልን ነው፡፡
በእቅድ ደረጃ በዚህ ዓመት ይህን ያህል ደም እንሰበስባለን የሚል ግብ አስቀምጣችኋል?
አዎ! ለምሳሌ በ2006 ዓ.ም መጨረሻ 150ሺህ ከረጢት ደም ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል። በየዓመቱ የጤና ተቋማት በጨመሩ ቁጥር የሚፈለገው የደም መጠንም እየጨመረ ይሄዳል። በየክልሉ እና በየወረዳው አዳዲስ ሆስፒታሎች ጤና ተቋማት እየተስፋፉ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ እቅዳችን የደም ባንኩ ተወዳዳሪና ለሁሉም ዜጋ በቂ የሆነ የደም አቅርቦት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ወደፊት የግልም የመንግስትም ጤና ተቋማት ፈቃድ ያላቸው ደረጃቸውን የጠበቁ እስከሆኑ ድረስ ደም እኩል የማግኘት መብት አላቸው፡፡ ላስገነዝብ የምወደውም ከደም ባንክ በነፃ የሚያገኙትን ደም ለህሙማኖቻቸው በነፃ  መስጠት እንዳለባቸው ነው፡፡  
ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ከደም ባንክ የወሰዱትን ደም በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል አለማዋላቸውን የምታረጋግጡበት መንገድ ምንድነው?
አሁን በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራው እዚህ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ስለሚኖረን ግንኙነት ከሆስፒታሎች ጋር ቁጭ ብለን ተወያይተናል፡፡ ከሆስፒታሎች ጋር የምንዋዋለው ምንድነው? እነሱ በየሳምንቱ ለሳምንት የሚበቃ ደም ይወስዳሉ። ከዚያ በኋላ በየወሩ ያላቸውን አፈፃፀም ሪፖርት እንዲያደርጉ ይጠበቃል፡፡ እስካሁን ሪፖርት አላደረጉም፡፡ ወደፊት ግን ምን ያህል ደም ወሰዱ፣ ምን ያህሉ ጥቅም ላይ ዋለ---የሚለውን ሪፖርት እንዲያደርጉ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ መልኩ ነው የምንከታተለው። ይህን ሲስተም ከሁለትና ከሶስት ሳምንት በኋላ ደረጃውን ከሚያሟሉ ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ጋር እንፈራረማለን፡፡ ከዚያም ለሚወስዱት ለእያንዳንዱ ከረጢት ደም ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡  

Read 4070 times