Saturday, 22 March 2014 12:55

አለቀ በቃ

Written by  ከዳኛቸው ወርቁ
Rate this item
(2 votes)

..ተረት ተረት.. አሉ ባለቤቷ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ዕድሜ ያለው የሚመስል አንድ ወንድ ልጅ እየተመለከቱ። ቤቱ ሬሳ የወጣበት ይመስል ጭር ብሎ ነበር፡፡
ከባንኮው በስተውስጥ ቆመዋል፤ ባለቤ.. በስተ ውጭ፤ በጎን በኩል፣ ሁለት የሰፍነግ ትራስ ተደራርቦ እተመቻቸበት ሶፋ ላይ አንድ ረዘም ያለ ቀጭን ሰው እግሮቹን በሰፊው አራዝሞ ተቀምጧል። የራሱ ጸጉር ከግምባሩ መካከል አንስቶ እስከ ማጅራቱ ተረተር ድረስ በቀጭኑ ተመልጧል፡፡ በረጅም መቃ ዓይነት ነገር የተሰራ ሲጃራውን፣ ባውራጣቱና በትንሽ ጣቱ መካከል አሾልኮ ፣ በሌባ ጣቱ ጫን እያለ፣ ካለፍ አገደም ወደ አፉ በመውሰድ፣ የጭስ ኩቦቹን እያከታተለ ቡልቅ ቡልቅ ያደርጋል፡፡ ዓይኖቹ በር በሩን ይመለከታሉ፡፡
“ተረት ተረት” አሉ ባለቤቷ ደግመው “የላም በረት” መለሰች አንዲቷ ቆንጆ፤ አንድዬ በብዙው አንድዬ በትንሹ ሲጃራዋን እየመጠጠች፣ እንደሰውዬው የጭስ ኩቦች ለመሥራት ትደክማለች። አልፎ አልፎ ምትን እያላት እንደሳል ያረጋታል፡፡ በሥራው የሠለጠነው ቀጭኑ ሰውዬ የጎድን አየት እያረጋት ሳቅ ይላል፤ እያከታተለ አንድዬ በዝግታ፣ አንዴ በፍጥነት ኩቦቹን በማስወጣት፡፡
..ተረት ተረት.. አሉ ባለቤቷ ለሦስተኛ ጊዜ
..የላም በረት.. አለች መልሳ፤ ኩቦቹን ለመስራት እየተጋለች፤ ቆንጆዋ፡፡
..አንቺ አልተጠራሽም.. አሉ ባለቤቷ ኮስተር ብለው
ትንሹ ልጅ እክፍሉ ውስጥ ከተኮለኮሉት ሶፋዎች መካከል ረጅሙ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ካርታ በመደርደር ይጫወት ነበር፡፡ ቆንጆይቱ ድንገት ብድግ ብላ መጥታ ካርታውን ከልጁ እጅ መንጭቃ ወስዳ የካርታ ጥንቆላ ጀመረች።
..ምነው አስረስ ተረቱን ንገረን እንጂ.. አሉ ባለቤቷ ዋጋ የሚያስከፍል በሚመስል ድምፅ፡፡
“አንድ ቤት ሁለት ውሾች ነበሩ፡፡” ጀመረ አስረስ “ቤቱ ቀዳዳ ነበር” ቀጠለ አስረስ የተነጠቀውን ካርታ እየተመለከተ “በቀዳዳው ወጡ፡፡”
“ታዲያስ” አሉ ባለቤቷ
“አለቀ በቃ” መለሰ አስረስ፡፡ ዓይኖቹ ከካርታው ላይ አልተነቀሉም፡፡
“እሺ ፍቅርስ እንዴት ያረጋል?” ቀጠሉ ባለቤቷ፡፡
“ያስለቅሳል” አለ አስረስ እንባው እንደመጣበት ዓይነት
“ያስለቅሳል? ከየት አመጣኽው ደሞ እንዲህ ያለውን መልስ?” ከባንኮው ወደሶፋው መጥተው ቀና አርገው ዓይኑን ይመለከቱታል፡፡
“ምነው ምን ሆንክ”
“ያስለቅሳል”
“አይ ለቅሶ እዚህ የለም፣ የምን ያስለቅሳል ነው ደሞ” ይቀጥላሉ ባለቤቷ ቆጣ ባለ አንደበት፤ ወዲያው ፊቱን አበስ አበስ በማድረግ “በል እንግዲህ አሁን ንገረኝ፤ ፍቅር ምን ምን ይላል?” በማለት
“ስኳር ስኳርም አይል ........ማር ማርም አይል.......
“ጋብዙኝ” አለች ድንገት እጎኔ ተስጋ፣ ካርታ ቀሚዋ፡፡ ስትጠጋኝ አላየኋትም፡፡
 “ጋብዙኝ” አለችኝ ደግማ
“ቢራ ጠጭ” አልኳት፡፡ “እሺ” አለችና ትንሽ “ጅን” ጠብ ያለበት “ቤርሙጥ” አምጥታ እጎኔ ተመልሳ ተቀመጠች። ባለኩቡ እግሩን አንጠራርቶ ባንኮው ወገብ ላይ ወግቶ በመወጠር ተዝናንቷል።
“ድገሙኝ” አለችኝ፤ ስትጨልጠው አላየኋትም፡፡ ደገመች፡፡ ከሰውዬው ሲጃራ ለምና አመጣችና በመለኮስ ኩቦቹን ለመስራተ ትፍጨረጨር ጀመር እንደገና። ለኔ ለማሳየትም ይሁን ነገሩ አልገባኝም። እኔ ለራሴ የሲጃራ ሽታ ያሰክረኛል፤ አልወድም፡፡ ደጉ ነገር ፈንጠር ብዬ ነበር መስኮት አጠገብ የተቀመጥኩት፡፡ የቀዩ አምፖል ብርሃን ውጋጋን ፊት ላይ በማይንተገትበት በኩል፡፡ የምጠጣውም የጊዮርጊስ ቢራ ነበር፡፡
“ቆንጆ ፎርም አለኝኮ” አለችኝ ቀስ ብላ
“ጥሩ ነው” አልኳት ከጪሱ በመሸሽ.
“ላሳይህ” አለችኝ
“አየሁትኮ” አልኳት
“የለም አላየኽውም” አለችኝ
“አልገባኝም” አልኳት
“ሦስት ዊስኪ ብትገዛልኝ አሳይሃለሁ” አለችኝ፡፡
“ምን? ልብስሽን......” አልኳት ዓይኔ ሳልወድ
ጎርጮ
“አዎ ምናለበት........
“ኧረ ተይ.....”
..ልታይ አይደለም..
..ሁላችንም እያለን?..
“ምንድነው ስድስታችን አይደለንም....” አለች እንደሷ ዓይነት ቆንጆ ጓደኛዋን እየተመለከተች፡፡
“ታዲያ አትፈሪም?”
“ምን ታደርጉኛላችሁ? አትበሉኝ”
“በምን ታውቂያለሽ?”
“አይ ከበላችሁኝም ሕግ አለ”
“አሁን እውነት ካንጀትሽ ነው?”
በቀኝ እግሯ መሬቱን መታ መታ እያደረገች፤ ሐሳቧ ርቆ የሄደ፣ ከንፈሯ ብቻ የሚንቀሳቀስ በሚመስል ሁኔታ፡፡
“አይ ለውስኪው ሰስተህ እንደሁ ተወው.. አለችኝ
“ሰውነትሽን በመጠጣት ለመርሳት ትፈልጊያለሽን?” አልኳት፡፡
“ሳልጠጣ ሰው መሆኔን አውቀዋለሁ መቼ አልኩህ?” ስትል መለሰችልኝ፡፡
“እኔ መቼም ሰው ነሽ እላለሁ” አልኳት
“ሰው ስለሆንኩማ መጠጥ እፈልጋለሁ፡፡”
“የሰው ምልክቱ መጠጥ ነው?”
“አይ ለዊስኪው ሰስተህ እንደሁ ተወው”
“እውን አሁን ያልሽውን ታደርጊያለሽ?”
“ለምን አላደርግም”
“አይ እንዲያው አልመሰለኝም”
መልስ ከመስጠቴ በፊት ብዙ ጊዜ ቆየሁ፡፡
“እንድመልስልህ ከፈለግህ ዊስኪውን ግዛልኝ..
“እንግዲያውስ ጠጪ” አልኳት፡፡ እንዴት እንደሄደች የምታውቀው ራሷ ናት፡፡ አንድ ግማሽ ጠርሙስ ዊስኪና አንድ ብርጭቆ ይዛ መጣች፤ ቀዳች። ባንድ ትንፋሽ ጠጣችው፡፡ ደገመች አሁንም ባንድ ትንፋሽ ጠጣችው፡፡ የነፍስ ስልክም ነፋስ እንደሆነ አላውቅም፤ እውነትም ጠምቷት ኖሯል፡፡
አየት አደረገችኝ፡፡ ..ትዊስት.. የሚባለው የዳንስ ሙዚቃ መሰማት ጀመረ። ከወንበሯ ላይ እያለች እንቅስቃሴዋን ጀመረች፡፡ ሦስተኛ ጊዜ ዊስኪዋን ቀዳች፡፡ ገንዘቤ መሆኑ ተሰማኝ።
“ታዲያስ ተነሻ” አልኳት
የምትንጠራራም መሰለኝ። ሰው የምትጠራም መሰለኝ፡፡ ሽንጭና ዳሌዋን፣ ጣቶቿንና ክንዷን የምታሳየንም መሰለኝ። አንደኛውን ጫማዋን አወለቀች፡፡ ሁለተኛውን ደገመች። ከወገቧ ጎብደድ፡ ከሽንጥና ከዳሌዋ ጎበጥ፣ ከደረትና ከትከሻዋ ቀና ብላ ግራ እጇን አራዝማ፣ በቀኝ እጇ ከግራ ከእጇ መዳፍ ጀምራ፣ ክንዷን ፣ ጡቶቿን እስከ ቀኝ ትከሻዋ ጫፍ ድረስ በቀስታ እየደባበሰች ታሪካዊ አነካሥ አሳየች። ወደፊቷም እንደመንደርደር ብላ አንገቷን ብቻ ዘወር በማድረግ አንድ ባንድ አየችን፡፡ ቀስ እያለችም ወደ እኔ ዞረች፡፡ እጇንም በማሽቆልቆል ከቁርጭምጭሚቷ ጀምራ ባትና ጭኗን እየደባበሰች ወደ ደረቷ አመጣችው፡፡ እግረ መንገዱንም ሰውነቷን ገለጠው። የባት ጡንቻ የላትም፣ ሙላው ሙሉ ነው፡፡ እንደገና አየት አደረገችን፤ ሳቅ አይሉት ሳቅ ሳቀች፤ አስፈራችኝ። ወዲያውም “ልድገም ወይ” አለችኝ ፤ ዓይን ዓይኔን እየተመለከተች፡፡ ባለኩቡ ቀድሞ ድገሚ አላት፡፡ የሚሠራው የጭስ ኩብ ራሱ ላይ ይትጎለጎላል፡፡ እኔ ነገሩም አልገባኝ፣ እሷና እሱ ግን ተግባብተዋል። የምትደግመው፣ ያሳየችውን ትርኢት ሳይሆን ውስኪውን ኖሯል፡፡ አራተኛው ብርጭቆ ስሙ እውነትም ድጋሞሽ ከሆነ ደገመች፤ ትርኢቱ ቀጠለ፡፡
ሶፋ ላይ ነበር የተቀመጥኩት፤ እግሮቼን አዝናንቼ፤ መጣች፡፡ በኋላዋ ወደ እኔ፡፡ እጭኔ ውስጥ ቀስ እያለች ገብታ ቆመች፡፡ ጭንና ጭኔን እየነካካች። ቀስ እያለችም ፊቷን ወደኔ አዞረች፡፡ እኔ አዟዟሯን ስመለከት ዱሮ ሹራቧን አውልቃለች፡፡ የት እንደወረወረችው ግን እግዜር ይወቅ፡፡
ከላይ የለበሰችው ስስ ሸሚዝ ነው። ጉርድ ቀሚሷ በሰፊ ቀበቶ ታስሯል። ደረቷን ሰፋ አድርጋ ቆማ ቁልቁል ተመለከተችኝ፡፡ ከመቅጽበትም በረጃጅም ጣቶቿ፣ ጸጉሬንና አንገቴን ስትዳብሰኝና ቀሚሷ እጫማዬ ላይ ሲወድቅ አንድ ሆነ፡፡ ዓይኔ አብሮ ወደ ሆዴ ገባ፡፡ ቱር ብላ ወደ ወለሉ ስትወጣ እንኳ የሚታየኝ እንደህልም ነበር፡፡ ብንን ያልኩት ብቻ እሜዳ ላይ ሳያት ነው፡፡
ተመስገን ነው! ሆኖም ታዲያ የውስጥ ልብሷን አላወለቀችም፤ ብዙም ሳይቆይ ወደ እኔ ቀስ እያለች ተጠጋች፡፡ እንደ በፊቱ ግን አልተሞኘሁም፤ እግሬን ሰብስቤያለሁ። ምን ያረጋል? እሶፋው ገሌንችና እገራ ጭኔ ላይ ጀርባዋን ሰጥታ ተቀመጠችብኝ። የተወለወለ ነው ጀርባዋ። ጠባሳና ዥንጉርጉርነት አይታይባትም፡፡
“ቁልፉን ከኋላዬ ፍታልኝ” አለችኝ
“የምኑን” አልኳት
“የጡት መያዣዬን”
..እንዴት ነው?..
..አይዞህ ንጹህ ነኝ፤ ምን አስፈራህ? ጡቴን ማየት ጠላህ እንዴ? የወደቀ መስሎህ እንደሁ.. አለችኝ፡፡
..የለም ለሱ እንኳን.....” ብዬ በመመለስ፣ ራሴን ማደፋፈሪያ ነገር ልናገር ስጀምር እንደትሬንታ የሚጮህ፣ የካርታ ድርጅት ታርጋ ያለበት “ቼብሮሌት” ኦቶሞቢል ወደ ነበርንበት ገደማ መጣ። ቆመ፡፡
“ታዲያ ምንድንው ፍታልኛ” አለችኝ። ልፈታ ስፈራ ስቸር ሁለት ፈረንጆችና አንድ ኢትዮጵያዊ እኛ ወዳለንበት ገቡ፡፡ ዱሮ በምታውቅበት ዘዴ ጡቷን ነቅነቅ፤ ደረቷን ሰበቅ ስታደርግ ጡት መያዣዋ ጧ ብሎ ኖሯል፡፡ ውጥርጥር ያለ ጃኬት የለበሰው አንደኛው ፈረንጅ፤ ፊቱ ድንገት ደም ለብሶ ተንደርድሮ መጥቶ ታቅፎ ሲያሽከረክራት ሁኔታው ታየኝ፡፡
የቤቱ ውስጥ ባንዳፍታ ነፍስ ዘራ፡፡ አንዲቷ ዙሪያ ጠረጴዛ መጥረግ፣ አንዲቷ መቀመጫ ማስተካከል፣ አንዲቷ ክንድ መጥለፍ ጀመሩ፡፡ ልጅቷን ጥርቅም አርጎ አቅፏት የነበረው ፈረንጅ ድንገት ለቀቃት፡፡
በቅጽበትም አንድ ስቴካ “ዊንስተን” ሲጃራ ከጃኬቱ ውስጥ አውጥቶ ከፈተና እቤቱ ውስጥ ላለው ሁሉ ማደል ጀመረ፡፡ እየወረወረ። ያመለጠ ንም ብንኖር ከመሬት አንስተንም ቢሆን ሲጃራችንን እየኪሳችን አደረግን፡፡ እኔ እንኳን አላጨስም ነበር፤ ከማን አንሼ፤ አልተግደረደርኩም፡፡
ኩብ ሠሪው ኢትዮጵያዊ የዱሮ ባኮውን ቀደደና ሲጃራውን ተያያዘው፡፡ የሱም ተማሪ ቀደደችና ተያያዘችው፡፡ “እስቴካው” ሲጃራ አላለቀ ኖሮ ድጋሚ ሊሰጠን ሲል፣ ባለቤቷ ከባንኮው ወጥተው ነጠቁት፡፡ “ሌላ ባለ ሱስ ሞልቷል” ብለው። የተረፈውን በሙሉ አውጥቶ ጨመረላቸው፡፡ ኢትዮጵያዊውና አንደኛው ፈረንጅ ተመቻችተው ተቀመጡና መሎቲ ቢራ ተቀዳላቸው፡፡ ጋባዣችንም ፈረንጁ ትንሽ ወዲያ ወዲህ ካለ በኋላ ተቀመጠ፡፡ ግብዣዬን የተቀበለችው ወይዘሮ እግዜር ይስጥልኝ እንኳ ሳትል ዱሮ ሄዳ እሱው ላይ ተጠመጠመች፡፡ እጎኔ የነበረውን ወንበር ወደሪቴ አሽቀንጥሬ እግሬን እላው ላይ ዘረጋሁት። ዘርግቼ የማላውቀው ሰውዬ። ቢራዬንም ጭልጥ አደረግሁና፣ “ውስኪ ብላክ ኤንድ ሁዋይት” አልኩኝ ድምጼን ከፍ አድርጌ፡፡ ውስኪው ተቀዳልኝ፤ ባንድ ትንፋሽ ጭው አረግሁት፡፡ “ድገሚኝ” አልኳት። ስትደግመኝ ሁለተኛው ቅጂ ተቀጣጥሎ ቁርቢል “ድቡል” አልኳት፤ ሳቅ ብላ “ድቡል” ቀዳችልኝ፡፡
“አስረስ” አሉ እመይቴ “ተረት ተረት”
“ባንድ ቤት ሁለት ውሾች ነበሩ፡፡ ቤቷ ቀዳዳ ነበር፡፡ በቀዳዳው ወጡ፡፡”
“ታዲያስ”
“አለቀ በቃ፡፡”
“ጋብዘኝ” ትላለች የኔ ተጋባዥ፤ ታቅፏት የነበረውን ፈረንጅ እያሻሸች፡፡ ሲጃራዬን ከኪሴ መዠረጥሁት “ክብረቲት እባክሽ” አልኳት፡፡
እውጭ ስወጣ፣ አጥሩ ሥር እነበረው ቁሻሻ ውሃ መውረጃ ውስጥ ልገባ ነበር፡፡ ቀና አልኩኝ፤ አለፍ አለፍ እያለ የደመና ኩብ ይትጎለጎላል፡፡ የቤቴን መንገድ ስያያዝ ማካፋት ጀመረ፡፡

Read 4386 times