Monday, 31 March 2014 11:46

“ማራቶን ልዕልቷ” ትመጣለች ወደ ቤቷ!?

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)
  • በ2014 የኢትዮጵያ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች ከ8 በላይ ማራቶኖችን አሸንፈዋል፡፡
  • በዓመቱ ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ የኢትዮጵያ አትሌቶች ብዛት ከኬንያ በእጥፍ ይበልጣል፡፡
  • ቀነኒሳ በፓሪስ፤ ጥሩነሽ በለንደን የመጀመርያ ማራቶናቸውን ይሮጣሉ፡፡
  • የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት ከነገሰ 20 ዓመታት አልፈዋል፡፡
  • በትልልቅ ማራቶኖች  ታዋቂ አትሌት  ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ፤ ሪከርድ በመስበር ካሸነፈ በሽልማት እና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ከሆነ በአማካይ እስከ 750ሺ ዶላር ሊያገኝ ይችላል፡፡

       በመላው ዓለም ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች የሚካሄዱበት ወቅት ከገባ ወር አልፎታል፡፡ በትልልቆቹ የማራቶን ሊግ ውድድሮች እና ሌሎች ማራቶኖች ኢትዮጵያዊያን  ሯጮች በውጤታማነት ነጥብ ለማስመዝገብ፤ በየውድድሩ የሚቀርቡ ማራኪ የገንዘብ ሽልማቶችና ቦነሶችን ለመሰብሰብ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የማራቶን ሯጮች ዘንድሮ ያሳዩት መልካም አጀማመር ‹‹ማራቶን ልዕልቷ››ን ከእነ ክብረወሰኖቿ ወደ ቤቷ ሊመልሷት እንደሚችሉ ተስፋ ፈጥሯል፡፡ 2014 ከገባ ወዲህ ኢትዮጵያዊ የማራቶን ሯጮች በሁለቱም ፆታዎች የውድድር ዘመኑን ፈጣን ሰዓቶች በማስመዝገብ እና በተለያዩ የዓለም ከተሞች በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች በማሸነፍ እና ተከታትለው በመግባት ከፍተኛ የበላይነት አሳይተዋል፡፡ በዓለም የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር ኤአርአርኤስ ድረገፅ የውድድር ዘመኑ የፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ላይ እንደተመለከተው ባለፉት ሶስት ወራት በተደረጉ የማራቶን ውድድሮች በወንዶች ከተመዘገቡ 24 ሰዓቶች 25 ፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ ከ25 ፈጣን ሰዓቶች 16 በኢትዮጵያን አትሌቶች ተመዝግበዋል፡፡ ባለፉት 3 ወራት   በወንዶች ምድብ ፀጋዬ መኮንን በዱባይ፤ በዙ ወርቁ በሂውስተን እንዲሁም ድሬባ ሮቢ በማራኬሽ በተካሄዱ ማራቶኖች አሸንፈዋል፡፡ በሴቶች ምድብ ደግሞ ማሬ ዲባባ በሻይናሜን፤ ሙሉ ሰቦቃ በዱባይ፤አበበች አፈወርቅ በሂውስተን እንዲሁም ድንቅነሽ መካሻ በሙምባይ የማራቶን ውድድሮች ድሎችን ተጎናፅፈዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በሮም ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ያሸነፉት  ሹሜ ሃይሉ እና አየሉ ለማ መሆናቸው፤ በሚቀጥሉት ሳምንታት በሚካሄዱት የፓሪስ፤ የለንደንና የቦስተን ማራቶኖች ኢትዮጵያውያን ከኬንያውያን የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆኑ ያመለክታል፡፡ በ2013 /14 “የዎርልድ ማራቶን ሜጀር ሲሪዬስ” “ማራቶን ሊግ” በስድስት ትልልቅ ማራቶኖች  በሚመዘገብ ውጤት መሰረት 1ኛ ሆኖ መጨረስ በሁለቱም ፆታዎች በነፍስ ወከፍ የ500ሺ  ዶላር ይገኝበታል፡፡ ከሳምንት በኋላ በፓሪስ፤ ከ15 ቀናት በኋላ በለንደን እንዲሁም ከሶስት ሳምንታት በኋላ በቦስተን የሚካሄዱት የማራቶን ሊግ ውድድሮች የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ፉክክር የሚጠበቅባቸው ናቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአትሌቲክስ  የረጅም ርቀት ውድድሮች የምንግዜም ከፍተኛ ውጤት  በማስመዝገብ የሚታወቁት ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለ እና ጥሩነሽ ዲባባ  በማራቶን የመጀመርያ ተሳትፏቸውን በሚቀጥሉት  ሳምንታት ማድረጋቸው ሲያነጋግር ሰንብቷል። የ31 ዓመቱ አትሌት  ቀነኒሳ በቀለ የመጀመርያ ማራቶኑን የዛሬ ሳምንት በፓሪስ ሲሮጥ፤  ከአስራ አምስት ቀናት በኋላ ደግሞ በለንደን ማራቶን   ጥሩነሽ ዲባባ ትሳተፋለች፡፡
በ2013 /14 የማራቶን ሊግ በቀጣይ ሳምንታት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከሚካሄዱ ማራቶኖች የ2013 /14 ማራቶን ሊግ ነጥብ የሚያዝባቸው ትኩረት ይስባሉ፡፡  ከማራቶን ሊግ ስድስት ትልልቅ  ውድድሮች የመጀመርያው የዛሬ ወር የተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ነበር፡፡ በማራቶን ሊግ በስድስት ከተሞች የሚደረጉት ውድድሮች የቶኪዮ፤ የለንደን፤ የቦስተን፤ የበርሊን የቺካጎና የኒውዮርክ ማራቶኖች ናቸው፡፡  ከወር በፊት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ትርፊ ፀጋዬ ማሸነፏ ሲታወስ በወንዶች ደግሞ ኬንያዊው ዲክሰን ቹምባ አሸንፈዋል፡፡ የየ2013 /14 ማራቶን ሊግን በወንዶች ምድብ በ50 ነጥብ የሚመራው የኬንያው ዴኒስ ኪሜቶ ነው፡፡ ቶኪዮ እና በቺካጎ ማራቶኖችን የቦታዎቹን ሪከርዶች በማስመዝገብ ያሸነፈው ዴኒስ ኪሜቶ ከሶስት ሳምንታት በኋላ በቦስተን ማራቶን ከአምናው አሸናፊ ሌሊሳ ዴሲሳ መገናኘታቸው ይጠበቃል፡፡ ሌሊሳ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ40 ነጥብ 3ኛ  ላይ ነው፡፡ አምና የመኻራቶን ሊጉን በአንደኛነት በመጨረስ 500ሺ ዶላር የወሰደው ፀጋዬ ከበደ በ45 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በኋላ አምና ባሸነፈበት የለንደን ማራቶን  በመሳተፍ የሊጉን የመሪነት ደረጃ ለመረከብ ያነጣጥራል፡፡ የማራቶን ሊጉን ደረጃ በሴቶች ምድብ የሚመሩት እኩል 50 ነጥብ ያስመዘገቡት ሁለቱ ኬንያውያን ፕሪሲካ ጂፔቶ እና ሪታ ጄፔቶ ናቸው፡፡ ፕሪስካ በለንደን፤ ሪታ በቦስተን ማራቶኖች ሲወዳደሩ፤ በ40 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ የምትገኘው ሌላዋ ኬንያዊት ኤድና ኪፕላጋት በለንደን ትሮጣለች፡፡
ቀነኒሣ በፓሪስ የመጀመርያ ማራቶን ውድድሩን የዛሬ ሳምንት በፓሪስ የሚሮጠው ቀነኒሣ  በቀለ አሸንፎ አጀማመሩን ለማሳመር ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ ገልጿል፡፡ የማራቶንን 42.195 ኪ.ሜ ርቀት በሩጫ ዘመኑ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሮጥ 2 ከ03፤ ከ2 ከ05 እንዲሁም 2 ከ06 ለመግባት እንደሚያስብ የተናገረ ሲሆን፤ ማናጀሩ ጆስ ሄርማንስ ከ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ በታች መግባት እንደሚችል ምናልባትም የፓሪስ ማራቶንን የቦታ ሪከርድ በመስበር ጥሩ አጀማመር እንደሚኖረው መስክረዋል፡፡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በፓሪስ ማራቶን ከተሳካለት በኋላ ዋና ዓላማው እስከ 2016 እኤአ ብቃቱን በመጠበቅ በ30ኛው ኦሎምፒያድ ብራዚል ሪዮዲጄኔሮ ላይ በመሳተፍ የወርቅ ሜዳልያ ማግኘት መሆኑን ጆስ ሄርማንስ በተጨማሪ ተናግረዋል፡፡ ፓሪስ ማራቶን ዘንድሮ ሽናይደር ኤሌክትሪክስ በተባለው ኩባንያ ስፖንሰርነት  ከሳምንት በኋላ የሚደረገው በታሪኩ ለ38ኛ ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ማራቶን የሚሮጠው ኢትዮጵያዊ አትሌት ቀነኒሳ ብቻ አይደለም፡፡ ሌላኛው አዲስ ኢትዮጵያዊ አትሌት በሃይሉ ከተማ ይባላል፡፡ በማራቶን ምርጥ ሰዓታቸው ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃዎች በታች ያስመዘገቡ የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች ተሳታፊ በሚሆኑበት የፓሪስ ማራቶን ላይ በወንዶች ሌሎች አራት አትሌቶች እንዲሁም በሴቶች ሁለት አትሌቶች ኢትዮጵያን በመወከል ተወዳዳሪ ናቸው፡፡ በወንዶች ምድብ ባስመዘገበው ፈጣን ሰዓት በአንደኛ ደረጃ የሚጠቀሰው አብዱላህ ሻሚ ነው 2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎች ከ42 ሴኮንዶች ፈጣን ሰዓት አለው፡፡ ሌሎቹ 2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ12 ሰኮንዶች ያስመዘገበው አዝመራው በቀለ፤ 2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ35 ሰኮንዶች ያለው  ነጋሪ ተፈራ፤ 2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ35 ሰኮንዶች የሮጠው ልመነህ ጌታቸው እና 2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ41 ሰኮንዶች የተመዘገበለት ገዛሐኝ ግርማ ናቸው፡፡ በሴቶች ምድብ  ደግሞ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃዎች ከ17 ሰኮንዶች ያስመዘገበችው መስከረም አሰፋ እና 2 ሰዓት ከ27 ደቂቃዎች ከ12 ሰኮንዶች የተመዘገበላት ዘምዘም አህመድ ናቸው፡፡
የፓሪስ ማራቶን አብይ ስፖንሰር የሆነው ሽናይደር ኤሌክትሪክስ በኦፊሴላዊ መግለጫው የአትሌት ቀነኒሳ በቀለ ተሳታፊነት የውድድሩን ድምቀት እንደጨመረው ገልፆ፤  አትሌቱ የቦታውን ክብረወሰን የማስመዝገብ ብቃት እንዳለው ገምቷል፡፡ ሌሎች የአትሌቲክስ ዘገባዎች በአንፃሩ አትሌት ቀነኒሳ በፓሪስ የዓለም ሪከርድን ለመስበር ብዙ እድል እንደሌለው ቢያመለክቱም ከማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች አንዱን ሊያስመዘግብ እንደሚችል ጽፈዋል። አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ከ4 ወራት በፊት የመጀመርያ ግማሽ ማራቶን ውድድሩን በእንግሊዝ ኒውካስትል ባደረገበት ወቅት ያስመዘገበው ውጤት በማራቶን ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆን ያረጋገጠበት ነው፡፡ በወቅቱ በግማሽ ማራቶን ውድድሩ ታላላቆቹን አትሌቶች ሞ ፋራህና ኃይሌ ገብረስላሴን አስከትሎ በመግባት  ሲያሸንፍ ያስመዘገበው ሰዓት 1 ሰዓት ከ09 ሰኮንዶች የሆነ ጊዜ በፓሪስ ማራቶን ማሸነፍ እንደሚችል ያመለክታል በሚል ግምቱን የሰነዘረው ደግሞ ሌትስ ራን የተባለው የአትሌቲክስ ዘጋቢ ድረገፅ ነው። አትሌቲክስ ኢልስትሬትድ የተባለ ድረገፅ በበኩሉ በቀነኒሳ የመጀመርያ የማራቶን ተሳትፎ ላይ በሰራው ትንታኔ አትሌቱ ፓሪስ ላይ ስኬታማ ጅማሮ እንደሚኖረው ሲያስረዳ፤ በመጀመርያው ማራቶኑ ቢፈጥን በ2 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ከ05 ሴኮንዶች (አዲስ እና አስደናቂ የዓለም ሪከርድ ሊሆን የሚችል ነው) ከዘገየ ደግሞ ከ2 ሰዓት 06 ደቂቃዎች አካባቢ ሊገባ እንደሚችል ገምቷል፡፡ ከ1500 ሜትር ጀምሮ እስከ ግማሽ ማራቶን ባሉ ውድድሮች የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ አትሌት የሆነው ቀነኒሳ በማራቶን የሚኖረው ስኬት በአትሌቲክስ ታሪክ ከፍተኛው ውጤት ያስመዘገበ አንደኛ አትሌት ያደርገዋል፡፡ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር በያዛቸው ክብረወሰኖች ላለፉት 10 ዓመታት  በበላይነት የቆየው አትሌቱ፤ በሁለቱ ርቀቶች በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ እንዲሁም በአገር አቋራጭ ውድድሮች 19 የወርቅ ሜዳልያዎች ሰብስቧል፡፡ እነዚህን የቀነኒሣ ከፍተኛ ውጤቶች ከዘረዘረ በኋላ በፓሪስ የመጀመርያ ማራቶኑን ሲሮጥ ከዓለም ሪከርድ ይልቅ የቦታውን ክብረወሰን ማሻሻል እንደሚችል የገመተው ደግሞ ራነርስ ዎርልድ የተባለው የአትሌቲክስ ዘጋቢ መፅሄት ነው፡፡ የፓሪስ ማራቶን የቦታ ሪከርድ ከሁለት ዓመት በፊት በኬንያዊው አትሌት ስታንሊ ኪውት በ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃዎች ከ12 ሰኮንዶች የተመዘገበ ነው፡፡ በረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድሮች ስኬታማ ዓመታት የነበራቸው አትሌቶች በማራቶን የመጀመርያ ተሳትፏቸው ሪከርድ የማስመዝገብ አቅም እንደሌላቸው በርካታ መረጃዎች ያስገነዝባሉ፡፡ ብዙዎቹ ምርጥ የረጅም ርቀት አትሌቶች በመጀመሪያ ማራቶናቸው  በፈጣን ሰዓቶች ደረጃ እስከ 20ኛው ባለ እርከን ለመግባት የሚያስችል ስኬት ነበራቸው፡፡ የወቅቱን የዓለም ማራቶን ሪከርድ የያዘው ኬንያዊው አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ በ2003 እኤአ ላይ የመጀመርያ ተሳትፎውን በፓሪስ ማራቶን ሲያደርግ ሶስተኛ በመውጣት ያስመዘገበው ሰዓት 2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ13 ሰኮንዶች ነበር፡፡ ሞሮካዊው ካሊድ ካኑቺ በ1997 እኤአ በቺካጎ ማራቶን 2 ሰዓት ከ07 ደቂቃዎች ከ10 ሴኮንዶች፤ ፖል ቴርጋት በ2001 እኤአ በለንደን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ ሲያገኝ 2 ሰዓት ከ08 ደቂቃዎች ከ15 ሴኮንዶች፤ እንዲሁም ኃይሌ ገብረስላሴ በ2002 እኤአ በለንደን ማራቶን ሶስተኛ ሲወጣ አዲስ የኢትዮጵያ ሪከርድ በማስመዝገብ  ስኬታማ  ጅማሮ ነበራቸው፡፡
ጥሩነሽና ሞ ፋራህ በለንደን ከ2 ሳምንታት በኋላ የሚካሄደው የለንደን ማራቶን በትልልቅ አትሌቶች ስብስብ የምንግዜም ምርጥ ተብሏል፡፡ እንግሊዛዊው ሞ ፋራህ እና ኢትዮጵያዊቷ ጥሩነሽ ዲባባ በማራቶን የመጀመርያ ተሳትፏቸውን ለንደን ላይ ማድረጋቸው ልዩ ትኩረት ፈጥሯል፡፡  ከ650ሺ በላይ የለንደን ነዋሪዎች በከተማዋ ጎዳናዎች ተሰብስበው የሚከታተሉት ማራቶኑ የዓለም ምርጥ ማራቶኖችን ደረጃ በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን በ150 አገራት የቴሌቭዥን ስርጭት ያገኛል፡፡ ከ2 ሳምንታት በኋላ በሚደረገው የለንደን ማራቶን ላይ ክብረወሰን እንዲሰብር የውድድሩ አዘጋጆች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ ለዚህም ይመስላል የዓለም ማራቶን ክብረወሰንን በበርሊን ለሁለት ጊዜያት በመስበር ክብሩን ለ5 ዓመታት ይዞ የነበረው ኃይሌ ገ/ስላሴን ከአሯሯጮቹ አንዱ አድርገውታል፡፡ ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በለንደን ማራቶን ለሶስት ጊዜያት ተሳትፎ ብዙም አልተሳካለትም፡፡ ዘንድሮ በ40 ዓመቱ በአሯሯጭነት ሲሳተፍ እስከ 30 ኪሎሜትር ድንቅ ፍጥነት እንዲያሳይ እምነት ተጥሎበታል፡፡
በለንደን ማራቶን ላይ 5 የዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 3 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች ያሏት ጥሩነሽ ዲባባ የመጀመርያ ማራቶን ውድድሯን ስትካፈል በከባድ ተፎካካሪዎች ተከብባ ነው፡፡ ዋናዋ ተቀናቃኟ ኬንያዊቷ ፕሬሲካ ጄፕቶ ስትሆን በ2013 የኒውዮርክ ማራቶንን በማሸነፍ እና የማራቶን ሊግን በአንደኛነት በመጨረስ 625ሺ ዶላር ያገኘች ምርጥ አትሌት ናት፡፡ ሌሎቹ ተፎካካሪዎቿ በማራቶን ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው። በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ በማራቶን ሻምፒዮን የሆነችውና በ2012 የሮተርዳም ማራቶንን ስታሸንፍ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ56 ሰኮንዶች በመጨረስ የኢትዮጵያን ማራቶን ሪከርድ ያስመዘገበችው ቲኪ ገላና ግንባር ቀደሟ ተጠቃሽ ናት፡፡ ለሁለት ጊዜያት የበርሊንን ማራቶንን እንዲሁም ባለፈው አመት የቶኪዮ እና የሻንጋይ ማራቶኖችን ያሸነፈችው አበሩ ከበደ ሌላዋ ተሳታፊ ናት። በማራቶን 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች ከ30 ሰኮንዶች ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበችው አበሩ ከበደ ዘንድሮ በለንደን ማራቶን የምትሳተፈው ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን በ2011 እኤአ 9ኛ እንዲሁም በ2012 እኤአ 6ኛ ነበረች፡፡ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ደግሞ በ2012 እኤአ የቺካጎ ማራቶንን  አምና ደግሞ የፓሪስ ማራቶንን ያሸነፈችውና 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃዎች ከ06 ሰኮንዶች ፈጣን ሰዓት ያላት ፈይሴ ታደሰ ናት፡፡ በዘንድሮው የለንደን ማራቶን ከሚሳተፉ ሴት አትሌቶች ሶስቱ ፈጣን ሰዓታቸው ከ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃዎች በታች ሲሆን 8 አትሌቶች ደግሞ ከ2 ሰዓት 25 ደቂቃዎች በታች ያስመዘገቡ ናቸው፡፡በለንደን ማራቶን በሴቶች ምድብ እንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ላለፉት 10 ዓመታት ይዛ የቆየችው 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ25 ሰኮንዶች የሆነው ሪከርድ ሊሰብር እንደሚችል አንዳንድ ባለሙያዎች እየገለፁ ናቸው፡፡ ለዚህ እጩ የሆኑት የመጀመርያው ተሳትፏዋን የምታደርገው ጥሩነሽ ዲባባ፤ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኗ ቲኪ ገላና፤ የዓለም ሻምፒዮኗ ኤድና ኪፕላጋት እና አምና አሸናፊ የነበረችው ፕሪስካ ጄፕቶ  ነበሩ።  ይሁንና አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በመጀመርያ የማራቶን ሩጫዋ የዓለም ሪከርድን እንደምታስመዘግብ ብዙም ባይጠበቅም፤ የለንደን ማራቶንን የቦታ ሪከርድ ወይ ደግሞ የኢትዮጵያን አዲስ ሪከርድ ልታስመዘግብ እንደምትችል ግን ግምት ተሰጥቷል።  እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ በ2002 እኤአ ላይ በለንደን ማራቶን የመጀመርያዋን ተሳትፎ አድርጋ ስታሸንፍ ያስመዘገበችው 2 ሰዓት ከ18 ደቂቃዎች ከ55  ሴኮንዶች  ነበር፡፡ የጥሩነሽ ሰዓት በዚሁ አካባቢ እንደሚሆን የተገመተ ነው፡፡  
በለንደን የመጀመርያ ማራቶን ውድድሩን የሚያደርገው ደግሞ ሞፋራህ ብቻ አይደለም፡፡ በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች በ10ሺ ሜትር የተናነቀው ኢትዮጵያዊው ኢብራሂም ጄይላንም ይሮጣል፡፡ ከእነሱ ባሻገር የዘንድሮ ለንደን ማራቶን በታላላቅ አትሌቶች የተጨናነቀ ነው። አምና የዓለም የማራቶንን ሪከርድን በበርሊን የሰበረው ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግ፤ በማራቶን በኦሎምፒክ እና በዓለም ሻምፒዮና የወቅቱ ሻምፒዮን የሆነው ኡጋንዳዊው ስቴፈን ኪፕሪቺች፤ የወቅቱ የማራቶን ሊግ አሸናፊ በመሆን ከ500ሺ ብር በላይ የተሸለመውና በ2013 የለንደን ማራቶንን ያሸነፈው ኢትዮጵያዊው ፀጋዬ ከበደ እና የለንደን ማራቶንን ሪከርድ የያዘው ኬንያዊ ኢማኑዌል ማታይ ተሳታፊ ናቸው፡፡ ሞ ፋራህ ወደ ማራቶን ለመግባት ሲወስን ኃይሌ ገብረስላሴ  እድሜው ገና ነው በሚል ድጋፍ ባይሰጠውም እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ግን ውሳኔው ልክ እንደሆነና በትራኩ እንደተሳካለት ማራቶኑንም ይቆጣጠራል በማለት መስክራለት ነበር፡፡  ሞ ፋራህ ስለመጀመርያው የማራቶን ተሳትፎው ሲናገር‹‹ በትራክ ብዙ ውጤቶች እና ሜዳልያዎችን አግኝቻለሁ፡፡ ስለዚህ ለምን በማራቶን ራሴን አልፈትንም፡፡ ለንደን ላይ ከተሳካልኝ በሌሎች ሁለት እና ሶስት ትልልቅ ማራቶኖች እሮጣለሁ፡፡›› በማለት  ተናግሯል። ከሳምንት በፊት በኒውዮርክ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን የተሳተፈው ሞፋራህ በውድድሩ ዋናው ትኩረቱ ለለንደን ማራቶን አቋሙን መፈተሽ ነበር፡፡ በዚሁ ውድድር ላይ ሞ ፋራህ ሶስተኛ ደረጃ አግኝቶ አጠናቅቋል። ይሁንና የውድድሩን መጨረሻ መስመር አልፎ ሲገባ ተዝለፍሎ በመውደቅ ለሶስት ደቂቃም እራሱን ስቶ ነበር። አንዳንድ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ሁኔታው በለንደን ማራቶን ሲሮጥ የሚጠብቀውን ከባድ ፈተና እንደሚያሳይ በመግለፅ ውጤታማነቱን ተጠራጥረዋል፡፡
የማራቶን ሪከርዶች የኪፕሳንግ 2፡03፡23፤ የራድክሊፍ 2፡15፡25
በዓለም የማራቶን ሪከርድ ታሪክ በወንዶች ምድብ የኢትዮጵያ አትሌቶች በክብረወሰኖቹ መሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ባለፉት 3 ዓመታት ግን ይህ የበላይነት በኬንያውያን እጅ ገብቷል፡፡ በሴቶች ምድብ ግን አንድም ኢትዮጵያዊ አትሌት የዓለም ሪኮርድ አስመዝግባ አታውቅም፡፡ በማራቶን ታሪክ በወንዶች የመጀመርያው የዓለም  ሪከርድ የተመዘገበው እኤአ በ1908 በለንደን ማራቶን በአሜሪካዊው ጆን ሄይስ በ2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ከ18 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ የመጀመርያ ሪከርድ ከተመዘገበ ከ32 ዓመታት በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያዊ አትሌት የተመዘገበው በ1960 እኤአ ላይ በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ባሸነፈው አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ በወቅቱ አበበ ያስመዘገበው የማራቶን ክብረወሰን 2 ሰዓት ከ16 ደቂቃዎች ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ከ4 ዓመታት በኋላ አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ሪከርድን   በ1964 እኤአ ላይ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ያስመዘገበ ሲሆን ጊዜውም 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃዎች ከ11 ሰኮንዶች ፡፡ አበበ በቂላ  በኦሎምፒክ መድረክ ባስመዘገበባቸው  ሁለት የዓለም የማራቶን ሪከርዶች  ለአምስት አመታት ነግሶ ቆይቷል፡፡ ከአበበ ቢቂላ ሪከርዶች 24 ዓመታት  በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድን ሊያዝ የበቃው  ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት በላይነህ ዴንሳሞ ነበር፡፡ በላይነህ እኤአ በ1988 በተካሄደው ሮተርዳም ማራቶን ሲያሸንፍ ርቀቱን የሸፈነበት 2 ሰዓት ከ06 ደቂቃዎች ከ50 ሴኮንዶች የሆነ ጊዜ አዲስ የዓለም ሪከርድ ነበር፡፡ በላይነህ ዴንሳሞ በዚህ ሪከርዱ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 7 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያው አትሌት ከመሆኑም በላይ ክብረወሰኑን ለ10 ዓመታት ይዞ ቆይቷል። ከበላይነህ ዴንሳሞ በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ክብረወሰን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከ19 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሰኮንዶች   በሆነ ጊዜ ባሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት ነበር፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ኃይሌ ይህን ክብረወሰኑን በድጋሚ ሲያሻሽል 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ነበር። ይሄው ሰዓት የኢትዮጵያ ሪከርድ ነው፡፡ በዚሁ ሁለተኛ የማራቶን  ሪከርዱ ኃይሌ ገብረስላሴ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያ አትሌት ሲሆን በክብረወሰኑ ባለቤትነት ለ5 ዓመታት ቆይቷል። በአጠቃላይ በወንዶች የዓለም ማራቶን  ታሪክ ሶስት የኢትዮጵያ አትሌቶች 5 ጊዜ ሪከርዶችን አሻሽለዋል። 3 ደቂቃዎች 49 ሰኮንዶች ከማራቶን የሪከርድ ሰዓት ላይ በመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው፡፡ ኢትዮጵያ በሪከርዱ ባለቤትነት ለ19 ዓመታት የበላይ ሆና እንድትቆይ አድርገዋል፡፡ የዓለም ማራቶን ሪኮርድ በኬንያ ቁጥጥር ስር የገባው  በ2012 እኤአ ላይ በኬንያዊው አትሌት ፓትሪክ ማካው በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ38 ሴኮንዶች በሆነ ጊዜ ተሰብሮ ነበር፡፡ ባለፈው አመት ደግሞ ሌላው ኬንያዊ አትሌት ዊልሰን ኪፕሳንግ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ23 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ተይዞ ይገኛል፡፡
በበርሊን ማራቶን ባለፈው ዓመት የተመዘገበው የዊልሰን ኪፕሳንግ የዓለም ማራቶን ሪከርድ በውድድሩ ታሪክ ለ32ኛ ጊዜ የተመዘገበ ክብረወሰን ነው፡፡ አስቀድሞ በኬንያዊው ፓትሪክ ማኩ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን በ15 ሰኮንዶች ያሻሻለ ነው፡፡ ዊልሰን ኪፕሳንግ ሪከርዱን ሲያስመዘግብ 31 ዓመቱ የነበረ ሲሆን በማራቶን መወዳደር ከጀመረ ከ4 ዓመታት እና ከ7 ውድድሮች ተሳትፎ በኋላ ሊያሳካው ችሏል፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት በትልልቅ ማራቶኖች በምርጥ አትሌቶች የሚመዘገቡ ፈጣን ሰዓቶች የተለየ መሻሻል ቢታይባቸውም አዲስ የዓለም ሪከርድ የሚመዘገብበት እድል የጠበበ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በቦስተን 2፡07፤ በለንደን 2፡06 ፤ በቺካጎ 2፡08 እንዲሁም በበርሊን 2፡05 ነው፡፡ እንደስፖርት ሳይንቲስት ድረገፅ ጥናታዊ ትንታኔ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ከእንግዲህ እስከ 25 ዓመታት ይጠይቃል። አሁን ዊልሰን ኪፕሳንግ የያዘውን ክብረወሰን ለማሻሻል እና ድፍን 2 ከ03 በመግባት ሪከርድ ሰዓት ለማስመዝገብ የሚቻለው በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ነው፡፡ ከ2 ሰዓት 02 እና ከዚያም በታች ለመግባት እስከ 10 ዓመት ይፈጃል፡፡
በሴቶች ምድብ እንግሊዛዊቷ አትሌት ፓውላ ራድክሊፍ ላለፉት 10 ዓመታት ይዛ የቆየችው ክብረወሰን በቅርብ ጊዜ እንደሚሻሻል ተገምቶ አያውቅም፡፡ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ25 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የተመዘገበው የራድክሊፍ ሪከርድ በለንደን ማራቶን የተመዘገበ ነበር፡፡
በሁለቱም ፆታዎች የተመዘገቡ የዓለም የማራቶን ሪከርዶች በየትኛው ውድድር እንደሚሰበር ለመገመት በተሰሩ ጥናቶች ግነባር ቀደም የሆነው የበርሊን ማራቶን ነው፡፡ቺካጎ፤ ሮተርዳም፤ ለንደን  እና ፓስ ማራቶኖች እስከ 5 ያለውን ደረጃ ያገኛሉ፡፡
የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት በማራቶን ውድድሮች የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች ላለፉት 10 እና 15 ዓመታት ተፎካካሪ አጥተዋል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በየትኛውም የዓለም ክፍል በሚደረጉ የማራቶን ውድድሮች እስከ አምስተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ተከታትለው በመግባት ፍፁም የበላይነት እያሳዩ ናቸው። የኤስያ፤ የአውሮፓ እና የአሜሪካ አትሌቶች የበላይነት ካከተመ ከ30 ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ምዕራባውያን እንደ ምስራቅ አፍሪካውያን ለማራቶን ውድድር ፍቅር ስለሌላቸው ውጤታማ አልሆኑም በሚል ቀሽም ማስረጃ ሁኔታውን ለማብራራት የሚሞክሩ አሉ፡፡ እነዚህ አስተያየት ሰጭዎች አሜሪካውያንና አውሮፓውያን ከማራቶን ይልቅ በቅርጫት ኳስ፤ በእግር ኳስ፤ በቤዝቦል እና ሌሎች ስፖርቶች ስኬታማ መሆንን ቅድሚያ በመስጠታቸው በምስራቅ አፍሪካ የሩጫ ገድል ተበልጠዋል በማለት ይከራከራሉ፡፡ አንዳንድ የጥናት ውጤቶች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በማራቶን ውድድሮች ስኬታማ የመሆናቸው ምስጥርን ሲያብራሩ ግን ሁኔታው ለየቅል ነው፡፡ በኢትዮጵያ እና ኬንያ ታዳጊ ወጣቶች በየቀኑ ወደትምህርት ቤት ለመጓዝ አምስት እና 10 ኪሎሜትር የእግር ጉዞ በማድረጋቸውና በከፍተኛ አልቲትዩድ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታዎች በማደጋቸው  ፅናት በሚጠይቁት የማራቶን ውድድሮች ስኬት ማግኘት አይከብዳቸውም በሚል ጥናታዊ ማስረጃዎች ቀርበዋል፡፡ በሌላ በኩል በአትሌቲክስ ስፖርት በሚኖር ውጤታማነት የሚገኘው የሽልማት ገንዘብ እና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅም ድህነትን ለማሸነፍ አማራጭ ሆኖ በመገኘቱ ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ውጤታማነት አብይ ምክንያት ሆኗል በማለት ያስረዳሉ፡፡
የምስራቅ አፍሪካን አትሌቶችን የበላይነት አሃዛዊ መረጃዎችም ያመለክታሉ፡፡ በ2013 እኤአ ላይ በወንዶች ምድብ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃዎች የገቡ 149 አትሌቶች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ አትሌቶች መካከል 80 ያህሉ ኬንያውያን ሲሆኑ 47 ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ስምንት አትሌቶች ደግሞ የኤርትራ እና የኡጋንዳ ዜግነት አላቸው፡፡
በአጠቃላይ በማራቶን ውድድሮች  የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን የበላይነት ሌላው ዓለም ክፍል በቅርበት የሚቀናቀነው አይደለም፡፡ በኦል አትሌቲክስ ድረገፅ የተሰባሰበ አሃዛዊ መረጃ እንደሚያመለከትው ደግሞ በወንዶች ማራቶን ፈጣን ሰዓት ደረጃ እስከ 100ኛ ድረስ ከተመዘገቡት ከምስራቅ አፍሪካ ውጭ የሌሎች አገራት  ውክልና በ9 አትሌቶች ብቻ የተወሰነ ነው፡፡ ከ101 እስከ 200 ባለውም ደረጃ ቢሆን 14 አትሌቶች ብቻ ከጃፓን፤ ከብራዚል፤ ከደቡብ አፍሪካ ፤ ከአሜሪካ እና ከጣሊያን ናቸው፡፡ በአጠቃላይ በዓለም ዙርያ ከሚገኙ 300 ፕሮፌሽናል የማራቶን ወንድ ሯጮች 246 ያህሉ ከምስራቅ አፍሪካ የፈለቁ ናቸው፡፡ ከ50 ዓመት በፊት በተካሄደ የቦስተን ማራቶን ከ1 እስከ 10 ደረጃ ያገኙ አትሌቶች ከአምስት አገራት ቤልጅዬም፤ ፊንላንድ፤ ካናዳ፤ አሜሪካ እና አርጀንቲና የተውጣጡ ነበሩ፡፡ በዚያው ዓመት በተካሄደ ኦሎምፒክ በተመሳሳይ ከ1 እስከ 10 ያለውን ደረጃ ከአምስት አህጉራት የተወከሉ አትሌቶች ያገኙት ነበር፡፡
የማራቶንና ማራኪ ገቢዎች አንድ የማራቶን ሯጭ ለአንድ ውድድር ቢያንስ የ3 ወራት ጥብቅ የልምምድ እና የዝግጅት ጊዜ ያስፈልገዋል፡፡ ምርጥ የሚባሉት የማራቶን ሯጮች በእንደዚህ አይነት የልምምድ ሁኔታዎች በአንድ አመት ሁለት እና ሶስት ማራቶኖችን መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ማራቶኖችን ከሌሎች የአትሌቲክስ ውድድሮች የሚለያቸው በሽልማት መልክ፤ በስፖንሰርሺፕ እና በቦነስ ክፍያዎች ከፍተኛ ገቢ ስለሚገኝባቸው ነው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር የሚካሄዱ የትራክ ውድድሮች በመመናመናቸው  በርካታ አትሌቶች በጎዳና ላይ ሩጫዎች በተለይ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ አብዛኛዎቹ የማራቶን ውድድሮች ለአሸናፊ አትሌቶች ከ50ሺ እስከ 100ሺ ዶላር በመሸለም ይታወቃሉ፡፡ ቀነኒሳ የሚሳተፍበት የፓሪስ ማራቶን ሽልማት በግልፅ ባይታወቅም እስከ 150ሺ ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ የኒውዮርክ ማራቶን 130ሺ ዶላር፤ የበርሊን ማራቶን 150ሺ ዶላር፤ የቦስተን ማራቶን 150ሺ ዶላር፤ የቺካጎ ማራቶን 100ሺ ዶላር፤ የለንደን ማራቶን እስከ 55ሺ ዶላር  በነፍስወከፍ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች ያበረክታሉ፡፡ አንድ የማራቶን ሯጭ በአሸናፊነቱ ከውድድሮቹ አዘጋጅ ከሚያገኛቸው ሽልማት ባሻገር በሚያስመዘግበው ፈጣን ሰዓት እና ሪከርድ  የቦነስ ሽልማች የሚያገኝበትም እድል አለው፡፡ አሁን ለምሳሌ በኒውዮርክ ማራቶን የቦታውን ሪከርድ  ለሚያስመዘግብ 70ሺ ዶላር ቦነስ አለ፡፡   ከ2 ሰዓት ከ5 ደቂቃ በታች ለሚገባ አትሌት በለንደን ማራቶን 100ሺ ዶላር ፤ በኒውዮርክ ማራቶን 50ሺ ዶላር ቦነስ ይሰጣል፡፡ በብዙዎቹ ማራቶኖች የቦታ ሪከርድ ለሚያስመዘግቡ አትሌቶች ከ25 እስከ 100ሺ ዶላር ይሰጣል፡፡  ሌላው የገቢ ምንጭ ትልልቅ አትሌቶችን በውድድሮቻቸው ለማሳተፍ የሚፈልጉ አዘጋጆች ከ100ሺ ዶላር ጀምሮ መክፈላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የለንደን ማራቶን ለአንዳንድ አትሌቶች ተሳትፎ እስከ 200ሺ ዶላር እንደሚሰጥ ይገልፃል፡፡
በሌላ በኩል አትሌቶች ትጥቃቸውን ስፖንሰር ከሚያደርግላቸው ኩባንያም በአንድ ማራቶን ውድድር በመሳተፍ ውጤታማ ሲሆኑ ከ50 እስከ 70 ሺ ዶላር ይበረከትላቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም አንዳንድ እውቅ አትሌቶች የሚያገኙት የመሮጫ ጫማቸውን በሚያቀርብላቸው ኩባንያ የሚያገኙትም ጥቅም አለ፡፡ በአጠቃላይ በትልልቆቹ የዓለማችን ማራቶኖች አንድ ታዋቂ አትሌት ተሳትፎ ጥሩ ሰዓት በማስመዝገብ የሚያሸንፍ ከሆነ በአማካይ እስከ 750ሺ ዶላር ሊያካብት ይችላል፡፡

Read 3746 times Last modified on Monday, 31 March 2014 12:01