Monday, 14 April 2014 09:02

ኢቴቪ በ”አኬልዳማ” ጉዳይ ይግባኝ ሊጠይቅ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

ከሁለት አመት በፊት አየር ላይ በዋለው “አኬልዳማ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ምክንያት በአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ክስ ቀርቦበት በፍ/ቤት የተረታው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) በውሳኔው ቅር በመሰኘቱ  ይግባኝ እንደሚጠይቅ፣ የጣቢያው የህግ ክፍል ሃላፊ አቶ ተማም ሁሴን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ የፍትሃብሔር ችሎት፣ በቅርቡ ያስተላለፈውን ውሣኔ በመቃወም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ እንደሚሉ የገለፁት የህግ ክፍል ሃላፊው፤ይግባኙ የሚጠየቀው ጣቢያው ለቀረበበት ክስ የሰጣቸው መልሶች በአግባቡ አልታዩም ከሚል ቅሬታ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
አንድነት ፓርቲ በኢቴቪ ላይ ባቀረበው የክስ ዝርዝር፤ ፓርቲው ህጋዊ ሆኖ ሳለ የግንቦት 7 ተላላኪ እንዲሁም  ለግንቦት 7 ሽፋን የሚሰጥ አድርጐ ማቅረቡ፣ ህጋዊ አባላቱን በሁከት ፈጣሪነት መፈረጁ፣ እንዲሁም ከፓርቲው በራሳቸው ፍቃድ የለቀቁና በዲሲፒሊን የታገዱ ግለሰቦችን የፓርቲው አባላት አድርጐ ማቅረቡ የሚሉ የክስ ጭብጦችን ያስመዘገበ ሲሆን በዚህም ሆን ተብሎ በታቀደና በተቀነባበረ መንገድ የፓርቲውን  መልካም ስምና ዝና አጉድፏል ብሏል፡፡
ኢቴቪ ለቀረበበት ክስ በሰጠው ምላሽ፤ ትክክለኛ እንጂ የሃዘት ዘገባ አለመስራቱን፣ የመንግስትና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን እንደመሆኑ ሁሉንም አዋጆችና ህጐች ባከበረ መልኩ የህዝብን  መረጃ የማግኘት መብት መሠረት አድርጐ፣ የህግ አስከባሪ አካላት ስለወሰዱት እርምጃ በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ፕሮግራሙ እንዲቀርብ መደረጉን ጠቅሶ፤በዚህም ሂደት የየትኛውንም አካል ስም አለማጥፋቱን አመልክቷል፡፡ በዚህ መነሻም ፓርቲው ለጣቢያው የላከውን ማስተባበያ አለመቀበሉን አስታውሷል፡፡
እነዚህ ሁሉ መከራከሪያዎች በአግባቡ ባለመታየታቸው ኢቴቪን ጥፋተኛ እንዳሰኙ የገለፁት የህግ ክፍል ሃላፊው፤ የህግ ስህተት ተሠርቶበታል የሚለውን ከለየን በኋላ የይግባኝ ማመልከቻችንን ለሚመለከተው ፍ/ቤት እናስገባለን ብለዋል፡፡ ፍ/ቤቱ በሰጠው ውሣኔ ላይ ስለሞራል ካሣ አላነሳም ያሉት አቶ ተማም፤  ፓርቲው የወጪ ኪሣራውን መጠየቅ እንደሚችል ትዕዛዝ ማስተላለፉን ጠቅሰው፤ እሱም ቢሆን ኢቴቪ የሚያቀርበው ይግባኝ ውሣኔ ከታየ በኋላ የሚስተናገድ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የአንድነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ባለፈው ሳምንት የፍርድ ውሳኔውን በተመለከተ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤በፍ/ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት ፓርቲው ለደረሰበት የሞራልና የንብረት ኪሣራ ተገቢውን ካሣ እንደሚጠይቁ መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

Read 1746 times