Monday, 14 April 2014 10:17

የትሮይ ፈረስ

Written by  አሳምነው ባርጋ
Rate this item
(6 votes)

ምን ዓይነት ዕዳ ነው እባካችሁ?!
አንዳንዴ ደሞ ከአብሮነቱ ጊዜ እጅግ በላቀ አኳኋን ትዝታው የሚጣፍጥ ፍቅር አለ፡፡
በሰለጠኑ ጥንዶች ወግ “ይብቃን …. አይደል?” ተባብለን በጨዋ ደንብ በቅርቡ የተለየኋት የዓመታት ፍቅረኛዬ ለካንስ ያኔ አልታወቀኝ ኖሮ እንጂ ካሉት ሁሉ የተሻለች ኖራ መርሳቱ ላይ ትንሽ አወከኝ፡፡
አይ …፣ ልመን - ምናባቱ፡፡ ቆጭቶኛል፡፡
ከዚያ ወዲህ “የሚያክለኝ አጣሁ!” ብዬ ራሴን እዚያ ላይ ኮፈስኩና ሥራ ሥራዬን ብቻ መከታተል ዓላማዬ አደረግሁ፡፡
ነገር ግን በየት በኩል?
የኔ ነጠላ መሆን ለፍቅር ሕይወታቸው ብርቱ አደጋ እንደሆነ የሰጉ ይመስል እኔን የሴት ጓደኛ ለማስያዝ ባልንጀሮቼ ተማማሉብኝ፡፡
ተቀምጬ ደህና ሂሳቤን ከምቀምርበት ዴስክ አንዷን ማቶት ፊት አምጥቶ ያሳየኝና “እ…? እንዴት ናት?” ይለኛል፡፡ “… ምንም አትል፣” እለዋለሁ “አይ ሰው!” እያልኩ በልቤ፡፡ ወየው ጉድ! ለራሱ እንደ ሱፍ አበባ የደመቀች ውብ ልጅ መርጦ ይዞ ሲያበቃ፣ ለኔ ይቺ ጣቷ አጫጭሩን ሙዝ የመሰለ ጦጣ ያጨልኝ ከቶ እንዴት ቢገምተኝ ይሆን?
ደሞ ሌላዋን አመጡ፡፡ “ተውኝ፣ ይቅርብኝ …. አይሆንም!” ብዬ ተቃውሞየን ባስመዘግብም “ምን ቸገረህ ለትንሽ ጊዜ አጥናት፣” ብለው ሐይ ሐይ አሉኝና ጥናቱን ጀመርኩ፡፡ እውነት እውነት ነው የምላችሁ … እንደዚያ ያለ ውድ Feasibility Study ከሰሐራ በስተደቡብ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ልጅቷ አሥራ አምስት ቀን በማይሞላ ጊዜ ውስይ ከቆንጆ ልጅነት አጭር ቀሚስ ወደ ለበሰ ተንቀሳቃሽ Cost Centernet ተቀይራ ትታየኝ ጀመር፡፡
ሸሸሁ፡፡
እንባዬን የተመለከቱ ጓደኞቼ በሐዘኔታ የአጭር ጊዜ ፋታ ሰጡኝ፡፡
ጥቂት ሰነባብተው ተመለሱብኝ፡፡
ያ ሚካኤል ነው ዛሬ በጠዋቱ የመጣው፣ “… ኋላ ምሳ አብረን ነን፣” አለኝ “ሌላ ሰው አያስፈልግም፡፡ የማናግርህ ነገር አለ!”
ቀና አልኩና አየሁት፡፡ የእፎይታ ጊዜዬ እንደተፈፀመ ታውቆኛል፡፡ ቢሆንም ያለ ሙግት እጄን ላለመስጠት ስል “… ልብ አርግ፣ የጋብቻ ሕይወቴን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውይይት አናካሂድም፣” አልኩት ኮስተር ብዬ፡፡
ለጥቂት ሰከንዶች ያህል በተመስጦ በዝምታ አስተዋለኝና ሄደ፡፡
ምሣ ቀርቧል፡፡ እምጵ - አቤት ዓሣ! ከክሣቱና የመጣመሙ የሌሊት ወፍ እንጂ ምኑም ዓሣ አይመስል፡፡ ክክ ወጡም እንደ ግሎብ ተድቦልቡሎ ለእንጀራው መሃል አለ፡፡ የአንዱ አተር ክክ ስፋት ከዲስክ አይተናነስም፡፡
“ብላ እንጂ!” አለኝ ሚካኤል ምግቡን እንደ ጸጉረ-ልውጥ ፍጡር በመገረም ሳጤነው ተመለከተና፡፡ ወጡ የዘንድሮ ለመሆኑ ለጌታ ፀሎቴን እያደረስኩ ጀመርኩት፡፡ እርቦኝ ነበር፡፡
እሱም አተሩን አፉ ውስጥ ለመፈርከስ ያመቸው ዘንድ ፊቱን ቁልቁልና ሽቅብ እያረዘመ ስለ አዲሷ ልጅ ያወጋኝ ጀመረ…
“አበጋዝ..፣” አለኝ ገና ሲጀምር፣ የጉዳዩን ክብደት ለማስረገጥ ሲባል ከወትሮው ወፈር በተደረገ ድምፅ፤፣ “”አበጋዝ-ፍቅር ይዞህ ያውቃል?”
“አዬ፣ የዛሬውስ - ፍልስፍና ቅልቅል ነው!” እያልኩ በልቤ፣ “አዎን” ስል መለስኩለት፡፡
“ፍቅር ስልህ … ‘አልይህ!’ እየተባልክ ሄደህ ልጅቷ ፊት ጧት ማታ የተገተርክበት? ‘አልፈልግህም!’ እየተባልክ ደርዘን ባለ ሁለት ገጽ ደብዳቤ የፃፍክበትን? ሌላዋ ከምትስምህ እሷ ብትገላምጥህ የመረጥክበት … ?”
እያቅማማሁ አቋረጥኩት፣ “እኔ እንጃ!” ግር እያለኝ፣ “እንደሱ እንኳ እኔ እንጃ …፤”
“በትካዜ ብዛት ቀልድ አላስቅህ፣ እህል አልበላልህ …፤”
“አአይ፣” አልኩት አሁን እርግጠኛ ሆኜ፣ “እንደ እሱ አይነቱ እንኳን … አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ እኔ ሆዴን ቢያመኝም እንኳን እህል እንቢ አይለኝም። ጥሩ አድርጎ ይበላልኛል፡፡ ሆሆሆይ! ደግሞ ጨጓራና ፍቅር ምን አገናኛቸው?” እያልኩ ጮክ ብዬ ተገረምኩ፡፡
ሚካኤል በትንሹ እየፈገገ ንግግሩን ቀጠለ፣ “ይኸውልህ አበጋዝ፣ አንድ እንዲህ አሁን እንዳልኩህ የምወዳት ልጅ ነበረችኝ፡፡ የመልንኳና የቁመቷን፣ የአይኗንና የጥርስዋን ካለየሀት በቀር እንኳንስ በእኔ ጎልዳፋ ንግግር በዳቪንቺ የስዕል ችሎታም ሊገለጽ የሚቻል አይደለም…፡፡”
“የሥላሴ ያለህ!” አልኩና አቋረጥኩት፣” “አደራህን…፣ መቸም - ስለ ማርሊን ሞንሮ አይደለም የምታወራው!” አልኩት በተጠቀመው የውበት አገላለጽ በዕውነት ደንግጬ፡፡
“አትቀልድ!” አለኝ ድንገት ዓይኑ እንባ አቅርሮ እያብረቀረቀ፣ “አትቀልድ”
ከዚያጥቂት ፀጥ ብሎ ቆየና “እንዴት እወዳት ነበር መሰለህ!? እንዴት!”
“ታዲያ ምን ሆነች? አገባች? ውጪ ሄደች? ወይስ … ሞተች? መቸም ከዚህ አያልፍም፡፡”
“አለች …፣ እንደውም ከእዚህ ከኛ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ያለው የጉዞ ወኪል ቢሮ ነው የምትሰራው፤”
“እና?”
“እናማ … በአጭሩ ልጅቷ አውሬ ነች፡፡ “እንቢ” የምትልህ አንተን ስለምትወድህ ወይም ስለምትጠላህ አይደለም እንዲሁ ወንድ ስለምትፀየፍ ይመስለኛል፡፡ ቃሉ በ“መፀየፍ” ነው፡፡ በኋላ እንደ ደረስኩበት አባቷ፣ እናቷን ክፉኛ ያሰቃያት ነበር አሉ። ያለ መጠን ቀናተና፣ ጠጪና ተደባዳቢ፡፡ ሲነሳበት ጉማሬና ካራ ይዞ በውድቅት ሉሊት ቀበሌ ግቢ ድረስ ነበር የሚያሯሩጣት - ዕርቃኗን! አሁን ተፋተዋል፡፡ ያልኩህ ልጅ ከእናትዋ ጋር ብቻዋን ነው የምትኖር፤ እና ለዚህ ይመስለኛል አይደለም ወንድ፣ ሴት እንኳን እንደ አውሬ ነው የምትሸሸው፡፡ ከአንድ ሴት ጓደኛዋ በቀር ከሌላ ጋር አትታይም፡፡ ፈፅሞ! የጓደኛዋ መልክ ደግሞ አስቀያሚነቱ ከሷ ቁንጅና በእጥፍ ስለሚልቅ ማንም አይጠጋትም…”
እንደ ምንም ብዬ ጣልቃ ገባሁና አቋረጥኩት፣ “… ይኸውልህ… ሚካኤል፣ ስላሰብክልኝ ከልብ አመሰግንሃለሁ፡፡ ነገር ግን … እኔ የአባቷን ዕዳ ለሷ የምከፍልበት አቅሙም ፍላጎቱም የለኝም፡፡ ምሳችንን አብቅተናል - እንሂድ፡፡” ድምፄ የመጨረሻ ነበር፡፡
“እሺ .. ይሁን፣” አለኝ፡፡ “ግን - አንዴ ብቻ እግሯን እየው፡፡ እግር እንደ ምትወድ አውቃለሁ። አንዴ ብቻ እግሯን እየውና የቀረው .. ያንተ ፈንታ ነው፡፡”
እግር … በእርግጥ እወዳለሁ፡፡ ከሴት ልጅ ውበት ከቶ ምንም ቢሆን ዕድሜ የማያደበዝዛቸው ረዥም ቁመናና ያማረ ቅርፅ ያለው እግር ናቸው፡፡ እና … እኔም በስተርጅና ዘመኔ ለዓይኔ ማረፊያም መፅናኛም ይሆነኝ ዘንድ የማገባት ልጅ እነዚህን ሁለት ነገሮች ታሟላ ዘንድ የግድ ነው፡፡
“እእእ…፣ እስኪ፣” አልኩ፡፡
ሚካኤል ይስቅብኝ ጀመር፡፡
አዲሱን ሐሳቤን የሰሙ ጓደኞቼ “Kamikaze Pilot” በሚል ስም ይጠሩኝ ጀምረዋል፡፡ የዚያችን ሴት - ነብር የሆነች ልጅ ዝና ሁሉም ያውቃሉ፡፡ ለካስ እኔ ለረዥም ጊዜ ትዳር-አከል በሆነ ጥሩ ፍቅር ውስጥ ስለቆየሁ ኖሯል እንጂ ከሁሉም ጓደኞቼ የልጅቷን የግርፊያ ወላፈን ያልቀመሰ አልነበረም፡፡
“ዋ…! አርፈህ ብትቀመጥ ይሻልሀል፡፡ ቀዳድዳ ነው የምትጥልህ!” ይሉኛል ቢሮ ውስጥ ተሰብስበው እየሳቁ፡፡
ሚካኤልን ያልተቀየመ የኔ የቅርብ ወዳጅ አንድም አልተገኘም፡፡ “እንዴት! እንዴት ዓይንህ እያየ ይህንን የዋህ ልጅ ወስደህ ሳማ ላይ ታስተኛዋለህ?!” ይሉታል፡፡
እርጉም እልህ ያዘኝ፡፡
በዚያ ላይ … እግሯ ደሞ! እግሯ… ደግሞ! እግሯ!!!! ሰአሊ ለነ ቅድስት!
ሐቁን ልናገር አይደል? እህል … እንደ ድሮው አልበላ ብሎኛል፡፡
እኔ እንጃ!
ዕቅዴን በጥበብና በማስተዋል አሰናዳሁ፡፡
ማንንም ምስጢረኛ አላረግሁም - ከልቤ በቀር። የልጅቷ አንድና፣ አንድ ደካማ ጎን ያቺ በአሳዛኝ ሁኔታ መልከ ጥፉ የሆነች ባልንጀራዋ ብቻ ነበረች፡፡
ዕቅዴ በሚገባ ተጠንቶ ከተጠናቀቀ በኋላ አጭር ፀሎት አድርሼበት ተንቀሳቀስኩ - “አምላኬ ሆይ! ይቺን ልጅ የዘላለም ዕርስት አድርገህ ስጠኝ….”
ቢሮዋ ስገባ ደንበኛ እያስተናገደች ስለነበር የእንግዳ ማረፊያው ላይ ሄጄ ተቀመጥኩ፡፡
ቢሮው ሰፊ፣ እጅግ ዘመናዊ፣ ንፁህ እና የሚያምር ነው፡፡ በዚያ ላይ የውጪውን የሚፋጅ አየር በምን ውጪ እንዳስቀሩት አላውቅም - ቀዝቃዛ ነበር፡፡ በግማሽ ክብ ቅርጽ ከተሰራ ረዥም ዴስክ ጀርባ ብዙ ሆነው በፀጥታ ይሰራሉ፡፡
ሰውየውን አስተናግዳ እንደ ጨረሰች ሄድኩና ጠረጴዛዋ ጋ ተቀመጥሁ፡፡ አቤት ፊቷ - አለት ማት አይደል እንዴ! ምንም ነገር አይነበብበትም፡፡ “ምን ነበር?” እንኳን አላለችኝም፡፡ ዝም ብላ ጣቶቿን ኮምፒውተሩ መደገፊያ ላይ አሳርፋ ትጠብቀኛለች፡፡
“… አይ … የግል ጉዳይ ላናግርሽ ነበር፣” ከማለቴ
እግዚኦ!
ይህስ - እውነትም የበሽታ ነው፡፡
በአፍታ ድሮም ቀጥ ብሎ የነበረው ከወገቧ ላይ ያለው አካሏ እንደ ኮብራ ዕባብ ሆኖ ቀጥ አለ። ከዚያም ዛር እንደ ያዘው ሁሉ ሰውነቷን አንድ ጊዜ በብርቱ ሰበቃትና ቀይ ፊቷ የበሰለ እንጆሪ መስሎ ተቀጣጠለ፡፡ አስከትላ በጎላ ድምጽ መዓቱን ልታወርድብኝ ስትሽቀዳደም ቶሎ በመጣደፍ “… ጓደኛሽን እንድታማልጅኝ ነበር፣” አልኳት በተሰበረ ድምጽ፣ በታሪክ የመጨረሻው ግሩም በሆነ ትህትና።
የኮብራው ምላስ ስርቅርቅ የሕንድ ዘፈን የሰማ ያክል ከመቅፅበት ወደ ሰገባው ተከተተ…
ዛሬ ቅዳሜ እሷን እየጠበቅሁ ነው፡፡ ሁነኛ ቀጠሮ አለን፡፡
ያን እለት እንዴት ደስ ተሰኝታለች! በዚያ ላይ ገርሟትም አላባራ፡፡ ምክንያቱም - ይኸውና ለውድ አስቀያሚ ጓደኛዋ በመጨረሻ የወንድ ጓደኛ ተገኝቷልና ነው፡፡
መጣች፡፡
እስከ አሁን ዕቅዴ ሁሉ እንደ ታሰበው ያለ እንከን እየተሳካ ቢሆንም አሁን አንድ ግዙፍና አስቸጋሪ መሰናክል ተጋርጦብኛል፡፡
ዓይኔ፡፡
ከንፈርና እግሯ ላይ ሳፈጥ ብትይዘኝ በነዚያ አለንጋ ጣቶቿ ሁለቴ በጥፊ ገርፋ ስታበቃ እንዳታባርረኝ እጅግ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ነበረብኝ፡፡
እኔ ጋ መጥታ ተቀመጠች፡፡ (በህይወቷ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም) ፈገግ ብላ ነበር።
ገና ካሁኑ ሴቱም ወንዱም በቅናት አይን ያየኝ ጀምሯል፡፡
“እንደምን ነሽ?” አልኳት፣ ከማክበር ጋር፡፡
“አለን፣” አለችኝ፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ ነፃ ሁና ነበር የምታዋራኝ፡፡
“ማን ነው ስምሽ?”
“ልያ፣”
ሻይ ቡና ቀርቦልናል፡፡
“ይኸውልሽ ልያ…፣ ጓደኛሽን በጣም እወዳታለሁ፡፡ በቁም ነገር…፣”
ዓይኗን እንባ አቅርሮ አቋረጠችኝ፣ “ፅጌ እኮ እንዴት አይነት ሰው መሰለችህ! ወይኔ እኮ - ውስጧ ሲያምር! እንዴት ዕድለኛ ልጅ እንደሆንክ ብታውቅ!”
“ዝም በይ - ሰባኪ!” አልኳጽ በሆዴ፡፡ የጓደኛዋ አፍንጫ እኮ ዝናብ ያስገባል፡፡ ልፊ ቢላት ነው እንጂ ፅጌን እንደሆነ “የወርቅ እንቁላል ትወልዳለች” ቢሉትም አይሁድ እንኳን አይነካትም፡፡
ሆኖም ግን በፍቅር ፍላፃ እንደተወጋ አፍቃሪ ሁሉ ገጽታዬን ማደካከሜ አልቀረም፡፡
“እሱንማ አውቄኮ ነው፡፡ የአክስቴ ልጅ አብራችሁ ኮሜርስ ትማር ነበርና …፣”
“ማን?” አለችኝ ፊቷ ሁሉ በፈገግታ እየሞቀ፡፡
“አታውቂያትም፣ የምትታወቅ ዓይነት ልጅ አይደለችም፡፡ ጭምት ነገር ነች …”
“ሳባ?”
“እንዴ! እንዴት አወቅሽ?” አልኩ የተደነቀ መስዬ፡፡ እኔ እኮ ከመጽሐፍ ቅዱሷ በስተቀር ሳባ የምትባል ልጅ በሕይወቴ አላውቅም፡፡
“እና … እባክሽን ልያ፣ በራሴ መንገድ ልቀርባት ሞክሬ ሁሌ አንድ ላይ ስለምትሆኑብኝ አልቻልኩም። ከሉሉ በፊት አንድ ነገር ግልጽ እንዲሆንልሽ እፈልጋለሁ፡፡ ከእሷ ጋር እስከ ሕይወቴ መጨረሻ ድረስ አብሬ መሆን የምፈልግ ሰው ነኝ፡፡ በዚያ ላይ ካንቺ ቃል እንደማትወጣ ሳባ ነግራኛለች። ስለዚህ ነገሩ እንደ ማይበላሽ እርግጠኛ ለመሆን ስል ነው አስቀድሜ አንቺ ዘንድ ልመና የመጣሁት። እኔ ምንም ነገር አይደለም የምጠይቀው፡፡ ልታይ!! መጀመሪያ አንቺ ለጥቂት ሳምንታት እይኝ፡፡ ከዚያ አንድ ላይ እዩኝ… እና ወስኑ፡፡” አቤት የድምፄ መለስለስ! የዓይኔ መቅለስለስ!
“እሱ ችግር የለዉም! ግን … በእናትህ እንዳትጎዳት! በእናትህ …፣” አለችኝ ዓይኖቿ ወፍራም እንባ አቅርረው፡፡
“ለማንኛውም፣” አልኳት፣ “… ለማንኛውም አንቺ አይተሽኝ አንድ ውሳኔ ላይ እስክትደርሺ ጉዳዩን በምስጢር ብትይዥው…፣”
አሁን እሷ ነች ጧትና ማታ የምትደውልልኝ፡፡ እጅግ ለምታፈቅራት ጓደኛዋ “ሸበላ” ባል ተገኝቷልና ነው እንዲህ እንቅልፍ ያጣችው፡፡
በየጊዜው እየተገናኘን መጨዋወቱን ተያይዘነዋል፡፡
“ግን …፣ እንዴት እንዲህ ልትወዳት ቻልክ?” ትለኛለች፡፡
“ምን መሰለሽ ልያ፣” እላታለሁ፣ “… ለትዳር ለትዳር እኮ እንደ እሷ ውበታቸው ትንሽ ከተት ያለ ቆንጆዎች ናቸው ጥሩ፣፡፡
በመገረምና በመደነቅ አፍ አፌን ታየኛለች - ‘እንዴት ያለ ብልህ ነው!’ በሚል አኳኋን፡፡
“እንዴ - ‘ቆንጆ ነን’፣ ‘የተማርን ነን!’ የሚሉትማ ፍዳሽን ነው የሚያስቆጥሩሽ፡፡ ትዳር ሳይሆን ከአንቺ ጋ ፉክክር ነው የሚገቡት፡፡ ልጅ ጡት አጥቢ ስትያቸው እንኳ አንተስ ሊሉሽ ምንም አይቀራቸውም! ምኔን አጠባለሁ?”
የሳቀችው … ሳቅ!
አንዳንዴ ደሞ ዕልም ብዬ እጠፋባታለሁ፡፡
ቢሮ ድረስ ፍለጋ የመጣች ዕለት በድንጋጤ አፋቸው በሀይለኛው የተላቀቀ ጓደኞቼ፣ ዛሬ ድረስ በትክክል መልሶ አልገጠመም፡፡
ሀይለኛ ቅናትና ክብር አድሮባቸዋል፡፡
“ለምን ጠፋህ?” አለችኝ እኔን እጅግ ደስ ባሰኘ ቅሬታ፡፡
ውበቷ ትንፋሽ ያሳጥራል፡፡
“ምን እባክሽ፣ ትንሽ ስራ ብጤ በዝቶብኝ ነው፡፡ በዚያ ላይ ፈተናውም ደርሷል…፣”፡፡
“የምን ፈተና?”
“አልነገርኩሽም እንዴ … ዩኒቨርሲቲ እየተማርኩ ነው እኮ…፣” አልኳት አቃልዬ፡፡
“እንዴት - በዲግሪ ተመርቄያለሁ አላልከኝም ነበር?” አለችኝ - ‘አንተ ቀጣፊ፣ ያዝኩህ!’ በሚል ቃና፡፡
“እሱማ … አዎ፣ ጨርሻለሁ፡፡ ግን … ማታ ማታ ድራፍት ከምጠጣ ብዬ እንደ ቀልድ ዩኒቨርሲቲ ጀመርኩና ዘንድሮ እመረቃለሁ፡፡”
ደነገጠች፣ “ወይኔ … ታድለህ! ሁለት ዲግሪ!”
“ምን … ይደረግ ብለሽ ነው፣” ራሴን ዓይን አፋርነትና ትህትና በተመላው አኳኋን አከክ አከክ አደረግሁ፡፡
የማናወራው ነገር አልነበረም፡፡ ቅራቅንቦ ነገር ሁሉ፡፡
“መጀመሪያ ሴት ነው ወንድ መውለድ የምትፈልገው?”
“ሴት፣”
“እንዴ - ለምን?” ትለኛለች፡፡
“ለምን እንደሆነ አላቅም፡፡ ግን ከመጀመሪያ ሴት ልጄ ጋር በጣም የቅርብ ጓደኛ የምንሆን ይመስለኛል። ለምሳሌ ቤት የተሰራው እራት ባያምረን እኔና እሷ ብቻ ተጠቃቅሰን ቀስ ብለን … ውጪ በልተን እንዳልቀመሰ ሰው የምንመለስ…. ምናምን፡፡ ብቻ … እንጃ እንደዚህ እንደዚህ ዓይነት ከሴት ልጄ ጋ ይታየኛል፡፡”
ዓይኗ ቅዝዝ እንደ ማለት ብሎ ታየኝ ጀመር፡፡
“እሺ ግን …፣ አያምስልብህና ፅጌ ‘አልፈልግም’ ብላ ድርቅ ብትል ምን ታረጋለህ?” አለችኝ አንድ ቀን፡፡
“እህ…! ምን አደርጋለሁ! እያዘንኩ፣ እየከፋኝ ይቀራል እንጂ፡፡ እንዴ - እኔ እሷን የመምረጥ መብት ያለኝን ያክል እሷም እኔን ያለመምረጥ መብት አላት እኮ!”
በእንዴት ያለ ከፍተኛ መገረምና አድናቆት እንዳስተዋለችኝ!    
“እሺ … ቆይ፣ ከተጋባችሁ በኋላ ብታናድድህስ?”
“እህ - እሱማ ያለ ነው እኮ!”
“አትቀጠቅጣትም?” ድንገት የእልህ እንባ በዓይኗ ሳይሆን በአፍንጫዋ በኩል መጣ፡፡
“አልገባኝም?!” አልኳት ፍፁም የተደናገርኩ በመምሰል፣ “እንዴት? ዱላ - ዱላ? እጄን አንስቼ?” ክፉኛ ግር እንዳለው ሰው ቅንድቦቼን አርገበገብኩ። “እንዴ ሚስቴ እኮ ናት - ግማሽ አካሌ፡፡ ለዛውም የተሻለው ግማሽ፡፡ እና - እንዴት ነው ራሴን የምመታው?”
አሁን ደሞ እሷን ግር አላት - የእውነት፡፡
“እስኪ … እግዚአብሔር ልክ እንደ ሰለሞን ሁሉ አንድ ነገር ብቻ ለምነኝ ቢልህ ምን ትጠይቀዋለህ?”
“መልካም ሚስት!” አልኳት፡፡
“አይ አንተ ደሞ!” አለችኝ እየሳቀች፣ “አይዞህ የፅጌን ፈተና እንደሁ ታልፋለህ፡፡ አታስብ፡፡ አሁን ጥያቄዬን በትክክል መልስ፣” ትላለች እያሾፈች፡፡
“ሙች እውነቴን እኮ ነው” እላታለሁ “እኔ ሀብት፣ ስልጣን፣ ዕውቀት … ለፍቼ፣ ደክሜ ላገኝ እችላለሁ ስል አስባለሁ፡፡ መልካም ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የምትገኝ ስጦታ ነች። በዚያ ላይ የተባረከች ሚስት ካለችኝ ሁሉ ነገር ይሳካልኛል፡፡ ምክንያቱም - እሷን ደስ ለማሰኘት ሌት ከቀን ነው የምሰራው፡፡ ጨቅጫቃ ነገር ከሆነች ግን የያዝሽው እንኴን ያመልጥሻል…፣
“አዎ፣” አለች በመስማማት ራስዋን እየነቀነቀች፣ … “ከእያንዳንዱ የተሳካለት ወንድ ጀርባ አንድ ሴት አለች ይባል የለ…፣”
“ከብዙ ያልተሳካለት ወንድ ጀርባም አንድ ሴት አለች፣” አልኳት፡፡
እንደ ፈላስፋ ልታየኝ ጀምራለች፡፡
ምሳሌ ሺ ዘመን ይንገስና ልጅትዋስ ወጥመዴ ውስጥ እየገባች ነው…
በቀን አንዴ ሳንገናኝ ከዋልን ቅር ይላት ጀምሯል። በምንም ተዓምር የማልቀይረውን በሳምንት አንድ ግዜ ብቻዬን ወደ ሲኒማ ቤት የመሄድ ልምዴን እንኳን ትቀናቀነኝ ጀመር፡፡ ያቺ ጽጌ የተባለችው ፍጡርማ ጭራሹኑ ከውይይታችን ውስጥ መነሳቷ ቆመ፡፡ ከኔ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ በጨመረ ቁጥር ከጓደኛዋ ጋ የምትገናኝበት እየቀነሰ መጣ፡፡
“ዛሬ አርብ አይደል? አልችልም!” እላት ጀመር፡፡ ቅር ሲላት አቤት ደስ ሲል፡፡
አንድ ቀን “እኔም ሲኒማ መግባት እፈልጋለሁ” አለች፡፡
“እሺ፣” አልኳት፡፡
በጨለማው ውስጥ እንደ ንጹህ ውሃ ጠረን - አልባ የሆነ አንገቷ ስር ተሸጉጫለሁ፡፡
“አንተ ክፉ ..” ትለኛለች፡፡
ከንፈሮቿን በከንፈሮቼ ዳበስኳቸው፡፡
ከንፈሮቿ ከሌሎች ሴቶች ከንፈር ጋር አንዳችም ተዛምዶ አልነበራቸውም - ከማር እንጀራ ጋር እንጂ።
ትንፋሽ እስኪያጥራት ድረስ ነበር የምስማት፡፡ አሁንም “አንተ … ተንኮለኛ…” ማለቷን አላቆመችም፡፡ በእርግጥ ብዙ ትንፋሽ አልሰጣትም፡፡ ግን እንደ ምንም በመሳሙ መሃል ጥቂት ፋታ ባገኘች ቁጥር” አንተ ክፉ፣” ትለኛለች
መቸስ - ምን ይደረግ - ታዲያ፡፡
(“የትሮይኑ ፈረስ እና ሉሎች አጫጭር ታሪኮች” ከሚለው መድበል የተወሰደ)    

Read 4248 times