Saturday, 19 April 2014 11:44

የዓውዳመት ገበያ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

   ሰፊ የበአል ሸመታ ከሚከናወንባቸው የአዲስ አበባ የገበያ ስፍራዎች የአቃቂ እና የሳሪስ ገበያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ማክሰኞ እና ቅዳሜ በሚውለው የአቃቂ ገበያ እንዲሁም ረቡዕና ቅዳሜ በሚውለው የሳሪስ ገበያ የበግ ዋጋ ከአነስተኛ እስከ ትልቅ ከ900 እስከ 2200 ብር ሲጠራ፣ በሬ ከ7ሺህ እስከ 12ሺህ ብር፣ ዶሮ ከ85 እስከ 170 ብር፣ እንቁላል አንዱ 2፡50 ብር፣ ቅቤ 1ኛ ደረጃ 160ብር በኪሎ፣ 2ኛ ደረጃ 145ብር፣ ሽንኩርት 15.50 እና 16 ብር በኪሎ ሲሸጡ ሰንብቷል፡፡
በሸመታ ወቅት ስለ ግብይቱ ካነጋገርናቸው ሸማቾች አንዷ ወ/ሮ ቀለሟ ደጉ፤ ለበአል አስፈላጊ የሆኑትን ግብአቶች አስቀድመው መሸመታቸውን ገልፀው፣ የሽንኩርት ዋጋ በቀናት ልዩነት ከ7.50 ወደ 15.50 ብር ከፍ ከማለቱ ውጪ ካለፈው የገና በአል የተለየ የዋጋ ልዩነት በአብዛኞቹ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ አለማስተዋላቸውን ገልፀዋል፡፡ በሳሪስ ገበያ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሌላዋ እማወራ የዘንድሮው በአል ገበያ የተረጋጋ መሆኑን ጠቅሰው የዳቦ ዱቄት ላይ ዋጋ ባይጨመርም በአብዛኞቹ ሱቆች የለም እንደሚባልና እጥረት መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡
በሳሪስ ገበያ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ የሆነው ወጣት በበኩሉ፤ በዘንድሮው የፋሲካ በአል ላይ መንግስት ከውጭ የሚያስገባቸው ባለ 3 እና ባለ 5 ሊትር ዘይት እጥረት መፈጠሩንና አብዛኛው ሸማች በሊትር 42፡50 የሚሸጠውን የኑግ ዘይት ለመሸመት እንደተገደደ ገልጿል፡፡ ወደ ሱቁ ጐራ የሚሉ ደንበኞች ከውጭ የሚገባው ዘይት በቀላሉ እንደማይገኝ እንደሚጠቁሙት የተናገረው ነጋዴው፤ እጥረቱ የተፈጠረው ጅምላ አስመጪዎች ለቸርቻሪዎች በሚፈለገው መጠን እያቀረቡ ባለመሆኑ ነው ባይ ነው፡፡  
የበዓል ገበያ በሾላ
ወደ አዲሱ ገበያ መስመር ሲጓዙ በሚገኘው ሾላ ገበያ በዓሉን ሞቅ ደመቅ ለማድረግ ዶሮ፣ ሽንኩርት፣ ቅቤና በግ ለመግዛት አባወራዎችና እማወራዎች ከወዲህ ወዲያ ይላሉ፡፡ ወ/ሮ ሰላማዊት አበራ፤ ሽንኩርት 16 ብር መግባቱ ሻጩና ሸማቹ ያመጣው ትርምስ እንጂ የሽንኩርት እጥረት ተከስቶ እንዳልሆነ ይናገራሉ “ከዚህ በፊትም በእንቁጣጣሽ ጊዜ ሽንኩርት 20 ብር መግባቱን አስታውሳለሁ፡፡ ሸማቾችም በዓል ሲሆን እናበዛዋለን፡፡ ሻጩም የሸማችን ፊት እያየ ዋጋ ይቆልላል” ሲሉ አማረዋል፡፡ በመሆኑም ደረቅና ጥራት ያለው ሽንኩርት በ16 ብር ሲሸጥ መለስ ያለ ጥራት ያለው በ14 እና በ15 ብር እየተሸጠ ነው፡፡
ሀሙስ ዕለት ነው ያነጋገርነው የዶሮ ነጋዴው አቶ ለሚ፤ በዓሉ እየቀረበ ሲመጣ ቅዳሜ ዶሮ እየተወደደ እንደሚሄድ ይናገራል፡፡ በሾላ ገበያ ባለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ በዓላት ዶሮ በመሸጥ ስራ ላይ መሰማራቱን የሚናገረው አቶ ለሚ፤ ነጋዴው የሸማቹን ፍላጎትና ሽሚያ እያየ ዋጋ እንደሚጨምር በመግለፅ፣ የወ/ሮ ሰላማዊትን ሀሳብ ይጋራል፡፡ “ረቡዕ እለት ጥሩ ስጋ አለው የሚባለውን ትልቅ ዶሮ በ190 ብር እንደሸጠ የሚናገረው አቶ ለሚ፤ ዛሬ (ሐሙስ) ከዚያው ዶሮ ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዶሮዎችን በ240 ብር እየሸጠ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ተዘዋውረን ለማየት እንደሞከርነው ዶሮ ከ110 ብር እስከ 235 ብር ድረስ እየተሸጠ ነበር፡፡
በሾላ ገበያ ለጋ ቅቤ በ180 ብር ሲሸጥ መካከለኛው 160 ብር በሳሉ ደግሞ 145 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ ወርቅነሽ አባተ የተባሉ ቅቤ ነጋዴ፤ ከበዓል በፊትና በኋላ የቅቤ ዋጋ ብዙ ልዩነት እንደሌለው የገለፁ ሲሆን በበዓል ሰሞን በኪሎ ከአምስት ብር በላይ እንዳልጨመረ ተናግረዋል፡፡ ከነጋዴዋ ጋር ስለዋጋ በምንነጋገርበት ጊዜ ጣልቃ የገቡ አንድ እናት፤ በበዓሉ የቅቤ ዋጋ መጨመሩን ገልፀው ከአንድ ወር በፊት ጥሩ የሚባለው ቅቤ በ130 ብር ይሸጥ እንደነበር መስክረዋል፡፡
ከመቼውም በበለጠ በበዓል ሰሞን ገበያ የሚደምቀው ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጀርባ የሚገኘው ሾላ ገበያ ለዘንድሮው ፋሲካ በሰው ተጨናንቋል፡፡ እንቁላል በ2.50 እየተሸጠ ሲሆን የተዘጋጀ በርበሬ በኪሎ 85 ብር፣ በግ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከ850 ብር እስከ 2800 ብር መሆኑን የገለፁልን በግ ነጋዴዎች፤ በዓሉ ቀረብ እያለ ሲመጣ የበግ ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ዘመናዊ ገበያዎች የበዓል አማራጮች ሆነዋል
ድሮ ዓመት በአል ሲመጣ አብዛኛው ሴት ወደ መርካቶ ነበር የሚሮጠው፡፡ አሁን ጊዜው ተለውጧል፡፡ በየአካባቢው በተከፈቱ ሱፐር ማርኬቶች የሚፈልጉትን ስለሚያገኙ መርካቶ መሄድ ትተዋል፡፡ መገናኛ ሸዋ ሃይፐር ማርኬት ዕቃ ስትገዛ ያገኘኋትን ሴት “ከመርካቶና ከዚህ ገበያው የቱ ይሻላል?” አልኳት “ያው ነው፤ እንዲያውም እዚህ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም መርካቶ የምታገኘውን ሁሉ እዚህም ታገኛለህ፡፡ ጥራጥሬው፣ ቅመማ ቅመሙ፣ አትክልቱ፣ ፍራፍሬው፣ ዱቄቱ፣ ዶሮው፣ ሥጋው፣ አይቡ፣ የልጆች ልብስ ብትል፣ ጌጣጌጡ፣ … ኧረ ሁሉም ሞልቶአል፤ በዚህ ላይ መንገዱ ስለተቆፈረ መርካቶ መሄድ ስለማይፈልጉ ትራንስፖርት አስቸጋሪ ነው፡፡ ዋጋውስ? ያልክ እንደሆነ የትራንስፖርቱን፣ ያውራጅ ጫኚውን ስትደምርበት ያው ነው፡፡ በዚህ ላይ ፀሐይዋ! አናት ትበላለች ሳይሆን ልብን ነው የምታጥወለውለው፡፡ ኧረ ምን አገኝ ብዬ ነው የምንከራተተው?...” አለች፡፡
በሸዋ ሃይፐርማርኬት የሀበሻ ዶሮ 84 ብር፣ የፈረንጅ እንደኪሎው ከ136 ብር እስከ 178 ብር፣ በጣም ትልቁ ደግሞ 202 ብር፣ የክትፎ ሥጋ አንድ ኪሎ 126 ብር፣ የወጥ 110 ብር፣ የበግ ሥጋ አንድ ኪሎ 93 ብር፣ አንድ ኪሎ አይብ 60 ብር፣ ትልልቅ ቀይ ሽንኩርት 22 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 45 ብር ይሸጣል፡፡  
ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ ባለው ኦልማርት ያገኘኋትን ሴት፣ “ገበያው እንዴት ነው? ከዚህና ከውጪው የቱ ይሻላል?” አልኳት፡፡ “ያው ነው፤ ብዙ ልዩነት የለውም፡፡ አንዳንድ ዕቃ ጥራቱን ስታይ እዚህ ይሻላል፤ ውጭ ደግ ጥራቱ ቀነስ ያለ በቅናሽ ዋጋ ታገኛለህ” እስቲ ለምሳሌ ምን? አልኳት “ለምሳሌ ቀይ ሽንኩርት ብንወስድ እዚህ 21 ብር ከምናምን ነው፡፡ ትልልቅ ነው ጥራቱም ጥሩ ነው፡፡ ውጭ ከሆነ ከ15 እስከ 16 ብር ታገኛለህ፡፡ ነገር ግን መካከለኛ ወይም አነስ ያለ ነው፡፡…”
ለፋሲካ ዶሮ ገዝታ እንደሆነ ጠየኳት፡፡ እንዳልገዛች ነገረችኝ፡፡ ከየት ለመግዛት እንዳሰበች ስጠይቃት፣ ከሱፐር ማርኬት እንደምትገዛ ነገረችኝ፡፡ ለምን? አልኳት፡፡ “እኔ የኮንዶሚኒየም ነዋሪ ነኝ፡፡ እዚያ ዶሮ ለማረድና ለመገነጣል አይመችም፡፡ ቆሻሻ መድፊያው ያስቸግራል፡፡ ከላይ ታች መመላለሱም ይሰለቻል፡፡ ዋጋውም ያው ነው፤ የታረደውን ከዚሁ እገዛለሁ” በማለት ምርጫዋን ነገረችኝ፡፡
በኦል ማርት ሱፐር ማርኬት የፈረንጅ ዶሮ በኪሎ 133 ብር፣ የሀበሻ ዶሮ የተበለተ ከ133 እስከ 139 ብር፣ ቀይ ሽንኩርት 21.70፣ አንድ ኪሎ የበግ ስጋ 100 ብር፣ የበሬ 138 ብር፣ የጥጃ 110 ብር፣ የጭቅና ሥጋ 210 ብር፣ ቅቤ የተነጠረ 165 ብር (1 ኪሎ ግን አይሞላም)፣ ዕንቁላል 2.65 ይሸጣል፡፡ እዚያው አካባቢ የጎንደር የተጣራ የኑግ ዘይት አንድ ሊትር 44 ብር፤ አምስት ሊትር 235 ብር፡፡
ገርጂ ሰንሻይን ኮንዶሚኒየም ፍሬሽ ኮርነር በተባለ ሱፐርማርኬት የፈረንጅ ዶሮ በኪሎ 115 ብር፣ የተገነጣጠለ ሙሉውን የሀበሻ ደሮ 125 ብር፣ ያልተገነጣጠለ 100 ብር፣ አንድ ዕንቁላል 3 ብር፣ 10 ዕንቁላል 35 ብር፣ አይብ አንድ ኪሎ 60 ብር፣ ሽንኩርት በኪሎ 16 ብር፣ ነጭ ሽንኩርት 48 ብር፣ የተነጠረ ኪሎ ቅቤ 200 ብር፣ ሎሚ በኪሎ 35 ብር፣ ግማሽ ኪሎ 17 ብር፣ ለወጥ የሚሆን ሥጋ 100 ብር፣ የጥብስ 140 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

Read 4469 times