Saturday, 19 April 2014 11:58

በዕንቁላሉ ጊዜ ያልተቀጣው ሠይፉ ፋንታሁን

Written by  በዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(67 votes)

ኢቢኤስ፣ ሠይፉ ፋንታሁንና ግሩም ኤርሚያስ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል
ሰይፉ በኢቤስን ያን ዕለት ላላያችሁ
የዛሬ ሶስት ሳምንት መሆኑ ነው…ለነገሩ በሠይፉ የኢቢኤስ ትርዒት፣ ዋናው እንግዳ አርቲስት ዓለማየሁ ታደሠ ነበር፡፡ ሠይፉ ከዓለማየሁ ጋር እዚህ ግባም የማይባል ወግ ቢጤ ከጠራረቀ በኋላ የዓለማየሁን የትወና ብቃትና አዲስ የሰራውን ፊልም በተመለከተ ምስክርነት እንዲሰጡ ኮሜዲያን ደረጄ ሃይሌና የፊልም ተዋናይ ግሩም ኤርሚያስ ተራ-በተራ ቀረቡ፡፡ ይህን ጊዜ ዋናው እንግዳ አለማየሁ ታደሰ ተረሳና ትርዒቱ የደረጄና የግሩም ሆነ፡፡ ይሁና….ይኸ ለወትሮውም ቢሆን እንጀራው የሆኑትን የጥበብ ሰዎች ባለማክበር፣ በማንጉዋጠጥና በማሸማቀቅ የሚታወቀው የሰይፉ ፋንታሁን ባህሪ ነውና ምን ያስገርማል?
ይልቁኑ ጉዱ የታየው በግሩም ኤርሚያስ ቃለ-መጠይቅ ወቅት ነው፡፡ ግሩም በዋና ተዋናይነት ተሳትፎበት በቅርቡ ለዕይታ ይበቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በራሱ አንደበት ስለነገረን አንድ ፊልም ማውራት ጀመረ፡፡ ቆየት ብሎ የአንድን የትወና ስታይል ፈጣሪ በማጣቀስ “ከእንግዲህ የምሰራቸውን ፊልሞችና ትወናዎችን መስዬ ሳልሆን ሆኜ መጫወት እፈልጋለሁ” አለ፡፡ ከዚያም ምሳሌ አጣቅሶ እንዲህ ተናገረ፡፡ “ለምሳሌ በአዲሱ ፊልም ላይ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ የሆነ ወጣትን ወክዬ ነው የተጫወትኩት፡፡ ታዲያ ይሄንን ባህሪ ስጫወት ሙሉ በሙሉ ሆኜ ለመጫወት ፍላጎት ስለነበረኝ፣ አደንዛዥ ዕፁን ተጠቅሜ፣ ራሴን ስቼ ደንዝዤ ነበር” ብሎ በጀብድ የተመላ ትርክቱን ነገረን፡፡
በዚህም ቢበቃን መልካም ነበረ…ደፋሩ ሰይፉሻም “እስኪ የፊልሙ ቅንጫቢ ከደረሰ ልቀቁልን” ብሎ አጋፋሪዎቹን አዘዘ፡፡ ወዲያው ግሩም አደንዛዥ ዕፁን ከወሰደ በኋላ የዕውነትም ደንዝዞ፣ ንፍጡ ተዝረክርኮና በላብ ተጠምቆ--- አንድ ጥግ ስር ተቀምጦ “ጦዣለሁ እኮ--” እያለ በመንተባተብ፣ ለሜካፕ ሰሪዎቹና ለካሜራ ባለሙያዎቹ ሲያወራ ፊልሙ ያሳያል፡፡ ይህ ትዕይንት ሲጠናቀቅ በዕለቱ የነበሩት ታዳሚዎች ለጀብደኛው ተዋናይ ግሩም፣ ከዕውቀት ፅድት ብለው ሲያጨበጭቡለት፣ ደፋሩ ሰይፉ ደግሞ ስለአደንዛዥ ዕፅ አስከፊነት ሊመካክረን ወደደ፡፡   
እንግዲህ የተከሰተው ይህ ነው፡፡ አደንዛዥ ዕፆችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የወንጀል ህግ ምን እንደሚል ቃል በቃል የገለበጥኩትን ለአንባቢያን ላካፍል፡፡
የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ 525
ማንኛውም ሰው ልዩ-ፈቃድ ሳይኖረው
ሀ. ዕፆችን ያበቀለ፣ ያመረተ፣ የሰራ፣ የለወጠ፤ ወይም የፈበረከ
ለ. ከላይ በፊደል (ሀ) ከተዘረዘሩት ነገሮች አንዱን ይዞ የተገኘ፣ ወደ አገር ያስገባ፣ ወደ ውጪ አገር የላከ፣ ያከማቸ፣ የደለለ፣ የገዛ፣ ያሰራጨ፣ ያዘዋወረ፣ አሳልፎ የሰጠ ወይም ለሌላ ያስገኘ
ሐ. ከላይ በፊደል (ሀ) ከተዘረዘሩት ነገሮች አንዱን ለማምረት፣ ለማቀነባበር፣ ወይም ለመፈብረክ የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን የሰራ፣ ይዞ የተገኘ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ ወይም ወደ ውጪ አገር የላከ
መ.  ከላይ በፊደል (ሀ) ለተዘረዘሩት ነገሮች መስሪያነት ማቀነባበሪያነት፣ ማምረቻነት፣ መሸጫነት፣ ወይም ባለይዞታ የሆነበትን ቤቱን፣ ግቢውን ወይም ቦታውን የሰጠ ቤቱን ያከራየ ወይም የፈቀደ እንደሆነ ከአምስት ዓመት በማያንስ ፅኑ እስራትና ከአንድ መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
እንግዲህ ከዚህ አንቀፅ ብንነሳ በዋነኛነት ግሩም ከዚያም ገዝተው ያመጡት ዳይሬክተሮች፣ የፊልሙን መቅረጫ ቤት አከራዮች ወዘተ በሙሉ በወንጀል ሊጠየቁ የሚችሉበት ሁኔታ እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ በዚሁ የወንጀለኛ መቅጫ ላይ የሚከተለውም ሰፍሮአል፡፡  
የወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ 640
ፀያፍ ወይም የብልግና ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮችን ለህዝብ መግለፅ
ማንኛውም ሰው  
ሀ. ፀያፍ ወይም ለመልካም ጠባይ ተቃራኒ የሆኑ የሆኑ ፅሁፎችን፣ ምስሎችን፣ ስዕላዊ መግለጫዎችን (ፖስተሮችን) ፊልሞችን ወይም ሌሎች ነገሮችን ያዘጋጀ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ ወይም ወደ ውጪ አገር የላከ፣ የተቀበለ፣ የያዘ፣ ለህዝብ ያሳየ፣ ለሽያጭ ወይም ለኪራይ ያቀረበ፣ ያከፋፈለ፣ ያሰራጨ ወይም በማናቸውም ሌላመንገድ ከቦታ ቦታ ያዘዋወረ ወይም በእነዚህ ነገሮች የነገደ እንደሆነ የተከሰሰባቸው ነገሮች መወረሳቸው ወይም እንዲጠፉ መደረጋቸው ሳይቀር ከስድስት ወር በማያንስ ቀላል እስራትና በመቀጮ ይቀጣል…ይላል፡፡
እንግዲህ እዚህ ላይ ደግሞ እነ ኢቢኤስ፣ እነሰይፉሻ፣እነ የፊልሙ ፕሮዱዩሰሮችና የመሳሰሉት ከተጠያቂነት ላያመልጡ ነው፡፡ ስራውም ከመወረስ ላይድን የሚችልበት መንገድም አለ እንደማለት ነው።
ይህንን በዝርዝር ለመጥቀስ የተገደድኩት ሰይፉና መሰል የቶክ ሾውና የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጆች--- ህዝብን እያዝናናን እናስተምራለን ከማለታቸው በፊት ለጥቂት ሰዓታትም ቢሆን ለንባብ ጊዜ እንዲመድቡ፣ የሚሰሩትንም  የህግ አግባብን በተከተለ መልኩ እንዲያደርጉት ለማሳሰብም ጭምር ነው፡፡
ኢቢኤስ ሃላፊነት እንዳለበት የሚዲያ ተቋም፣ ይህንን ፕሮግራም በዘፈቀደ ካስተላለፈ/ለዓየር ካበቃ በኋላ ደግሞ በከተማዋ የተሰሙትን ትችቶች መሰረት አድርጎ አቶ ሰይፉ በቅዳሜው የሸገር የአየር ሰዓቱ “ታዲያስ አዲስ” በተሰኘው ፕሮግራሙ ላይ ግሩምን በስልክ ጋብዞ ልክ ጀግንነት እንደሰራ ሰው ሲወዳደሱ ስሰማ፣ ብስጭቴን ለመቆጣጠር ተስኖኛል፡፡ ቃል በቃል ባላስታውሰውም አንድ ሶስት የተባባሉትን ሃሳቦች ላካፍላችሁ፡፡
ሰይፉ፤- እኛ ትምህርት እናስተምራለን ብለን ነበር  ያቀረብነው…ግሩሜ ያንን በመስራትህ ትፀፀታለህ?
ግሩም፤- በፍፁም አልፀፀትም፡፡ እኔ እንደውም ከህዝቡ የተለየ አድናቆትና ሽልማት ነበር ስጠብቅ የነበረው፡፡ በዚህ በጣም ስሜቴ ተነክቶአል፡፡
ሰይፉ፤- አንዳንድ ሰዎች “ሆኖ መጫወት” ትንሽ ይከብዳል ይላሉ…ለምሳሌ አፄ ቴዎድሮስን ሆኖ ቢሰራ ጥይቱን የዕውነት ሊጠጣ ነው? እያሉ ነው፣ ምን ትላለህ? (አያችሁ መልሶ ሲያሾፍበት…የእርሱኑ ፕሮግራም ባደመቀ!)
ግሩም፡- ይህንን የሚሉት ፍልስፍናው ስላልገባቸው ነው፡፡ ቢገባቸው እንዲህ አይሉም፡፡ መሆን ሲባል ሁሉም ነገር አይኮንም…ለምሳሌ ሞት፣ እሳት መቃጠል ወዘተ-- ተሆኖ ሊተወን አይችልም
ሰይፉ፤- እና ይቅርታ አትጠይቅም?
ግሩም፤- እኔ ምናልባት ይቅርታ መጠየቅ ካለብኝም ከ18 ዓመት በታች የሆኑትን ህፃናት ነው። እነሱን አስቀይሜ ከሆነ ይቅርታ እጠይቃቸዋለሁ፡፡ በሌላው ግን ለማስተማር ስለሆነ የሰራሁት ልደነቅ እንጂ እንዲህ ስሜቴ ሊነካ አይገባም ወዘተ--
እንዲህ እንዲህ ተባብለው ስልኩ ተዘጋ፡፡ ወዳጆቼ… ይቅርታ መጠየቅ ብቻም ሳይሆን በህግም መጠየቅ አለ እያልን እኮ ነው፡፡ ይህንን እየፃፍኩ አንድ ሁልጊዜ የሚከነክነኝና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆችና የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኜ የተከሰተ አንድ ክስተትን አስታወስኩ፡፡
የአባባ ተስፋዬ ከኢቴቪ መባረር!
 እንደምታስታውሱት ባንድ ወቅት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ፕሮግራም ላይ የኦሮሞ ብሄረሰብን ክብር የሚነካ ቃል በአንዲት ህፃን በተረት መልክ ተነግሮ ብዙ አዳርሶ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት የጣቢያው የበላይ ሃላፊዎች አባባ ተስፋዬንና የእለቱ ፕሮግራም አስፈፃሚ የነበረችውን ባልደረባችንን ከስራ ሲያግዱ፣ በጣቢያው የሁለት ሰዓቱ የዜና እወጃ ላይ፣ መላውን የኦሮሞ ህዝብ በይፋ በጣቢያው ስም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ ይህ የይቅርታ ጥያቄ ተገቢና የሰለጠነ አካሄድም እንደነበረ ተገንዝቤአለሁ፡፡ የህዝብን ክብር የሚነካ፤ የሚያሳቅቅና የሚያሸማቅቅ ተግባር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ሲፈፀም ጣቢያው የመጀመሪያውን ሃላፊነት ወስዶ ይቅርታ መጠየቅ በእርግጥም መሰልጠን ነው፡፡ እንደነ ሰይፉ ዓይነቱ ደፋር ደግሞ በኢቢኤስ ላይ የሰራውን ስህተት በሸገር ሬዲዮ ላይ ይጨማምርበታል፡፡
ሰይፉ በተለያዩ ጊዜያት ባለሙያዎች ላይ ሲያፌዝ፣ ሲያንጉዋጥጣቸው፣ በአራዶቹ አነጋገር ሙድ ሲይዝባቸው አድምጨዋለሁ፡፡ እንደ ሳያት ያለችዋ ጀግና ደግሞ ሰጥ-ለጥ ስታደርገውም አስታውሳለሁ፡፡ በይፋም ይቅርታ አስጠይቃው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም በዕንቁላሉ ጊዜ ተገቢው እርምጃ ያልተወሰደበት ሰይፉ ፋንታሁን፣ ነገ ደግሞ ምን እንደሚያመጣብን ምን ይታወቃል?
እዚህ ላይ አንድ ሸዋፈራሁ ደሳለኝ የሚሰራት ማስታወቂያ ትዝ አለኝ፡፡ ማስታወቂያው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን መልዕክትን ለማስተላለፍ የተዘጋጀ ነው፡፡
በአንድ የሬዴዮ ጣቢያ የተላለፈ ዘገባ፣ የድርጅቴን ስምና ክብር አጉድፏል ብሎ ሸዋፈራሁ በወከላቸው ሽማግሌ ገፀ-ባህሪ አማካኝነት ለብሮድካስቱ ባለስልጣን ክስ ሊያቀርብ ሲንቀሳቀስ ያሳይና እንዲህ ዓይነቱ የመብት ጥሰትና መሰል አግባብ ያልሆኑ ነገሮች ሲተላለፉ አቤት ማለት እንደሚቻል ያስተዋውቃል፡፡
እና እኛም (እኔና እኔን መሰሎች) እንደ ትውልድ ተቆርቋሪ - ኢቢኤስ ቲቪ፣ ሰይፉ ፋንታሁንና ግሩም ኤርሚያስ በጋራ ሆነው ይቅርታ ካልጠየቁን የሸዋፈራሁን ጥቆማ ተግባራዊ የምናደርግበት ቀን ሩቅ ላይሆን ይችላል፡፡
መልካም በዓል!

Read 16536 times