Saturday, 10 December 2011 10:18

ሁለተኛው ዙር የአረብ አብዮት ቀጥሏል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(0 votes)

በግብጽ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ እየመራ ይገኛል
እንዳልተጠበቀ አውሎ ነፋስ ድንገት የአረቡን ዓለም ከዳር እስከዳር ያጥለቀለቀው የዲሞክራሲ፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የኢኮኖሚ ጥያቄ አሁንም ጋብ አላለም፡፡ በቱኒዚያ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የተረጋጋ ፖለቲካ በአገሪቷ የሰፈነ ቢሆንም፣ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ገና ምላሽ አላገኙም፡፡ በየመን ደግሞ አሊ አብደላ ሳላ ቃላቸውን በየጊዜው እያጠፉ ስላስቸገሩ በየካቲት ወር ሥልጣን እንደሚለቁ መናገራቸውን ተከትሎ ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ተገደዋል፡፡

በየቀኑ በተለይም ዓርብ (በጁምአ ቀን) ይታይ የነበረው ትዕይንተ ሕዝብ ጋብ ብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የአብደላህ ሳላህ መንግስት መውረድ ብቻውን፣ ከዘመናዊ ከተሞች ይልቅ የጥንታዊ ከተሞች ገጽታ ባላት በሰንዓና በሌሎች የየመን ግዛቶች ለሚኖሩ በድህነት ለቆረቆዙ የመናዊያን አፋጣኝ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም፡፡ በሌላም በኩል በአፍጋኒስታን ሳለ የአሜሪካ ዱላ የበዛበት ዋነኛው የአልቃይዳ ክንፍ፣ ጥቂት ቅሪቶቹን ብቻ ትቶ ጓዙን ጠቅልሎ የከተመው የመን ድንበር ላይ ነው፡፡
እንዲያውም ሕዝባዊ አመጹ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖለት በደቡብ የመን የሚገኙ ጥቂት ከተሞችን በቁጥጥር ስር አድርጓል፡፡ ሕዝባዊ አመጹ ባይነሳባቸው ኖሮ አልቃይዳን እንዳያስፋፋ ገትረው የሚይዙት አብደላህ ሳላህ፤ በስልጣን ቢቆዩ የአሜሪካ ፍላጐቷ ነበር፡፡ ነገር ግን አብደላህ ሳላህ በየካቲት ወር ስልጣናቸውን ይለቃሉ፤ የመንም ብዙ የቤት ስራ ይጠብቃታል፡፡
እንደ ሞሮኮ፣ ኳታር፣ ዮርዳኖስ፣ ሳውዲ አረቢያና ኩዌት በመሳሰሉ አገሮች ተቀስቅሶ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ፣ መንግስቶቻቸው የኑሮ ውድነትን ያለዝባል በሚል የደሞዝ ጭማሪና እህል በቅናሽ በማከፋፈላቸውና ድጐማዎችን በማድረጋቸው አመጹ ብዙም ሳይገፋ ተቋርጧል፡፡ ለስምንት ወራት ያለማቋረጥ የሕዝባዊ አመፅን በማካሄድ ሪኮርድ የያዘችው ሶሪያ ህዝቦች ዋነኛ ፍላጐታቸው በሽር አል - አሳድን ከሥልጣን ማውረድ ነው፡፡ አንዳንዶችም አል-አሳድ የጋዳፊ ዕጣ ቢገጥማቸው የሚጠሉ አይደሉም፡፡ እስካሁን 4000 ሶሪያዋያን በሶሪያ የፀጥታ እና የጦር ኃይሎች መገደላቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በሽር አል - አሳድ፤ አምባገነንነትን ከአባታቸው ከአፌዝ - አል - አሳድ የወረሱት ሲሆን እሳቸውም በውርስ ያገኙትን አምባገነንነት እርሳቸው ከአባታቸው የወረሱትን ለ4000 ሶሪያዊያን ዕልቂት ዋነኛ ተጠያቂ ለሆነው ታናሽ ወንድማቸው እንዳወረሱት ይነገራል፡፡ የበሽር አል አሳድ ታናሽ የአገሪቱ የፀጥታና ጦር ኃይል ዋና አዛዥ ነው፡፡
በሊቢያ ደግሞ ከጋዳፊ አገዛዝ መገርሰስ በኋላ አገሪቱ በሸሪያ ሕግ ትመራ ወይስ አትመራ በሚለው ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙስጠፋ አብዱልጀሊል፤ ሶሪያ በሸሪያ ሕግ እንደምትመራ ጠቁመው አንድ ወንድ ከአንድ በላይ ሴት ማግባት እንደሚችልም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአብዱልጀሊልን ንግግር ተከትሎ በሊቢያ በርካታ ሴቶች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡
በተለይም በትሪፖሊ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ሴቶች ሌላ ሴት ያገባን ወንድ በጭራሽ ለማግባት እንደይፈልጉ በመግለጽ፣ ጠ/ሚኒስትሩን አጥብቀው ነቅፈዋል፡፡
ጋዳፊን ለመጣል ነፍጥ አንግበው የተነሱት ታጣቂዎች በበኩላቸው፤ በሽግግሩ መንግስት እምነት እንደሌላቸው በመጥቀስ ትጥቅ ለመፍታት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል እንዲያም ሆኖ ግን በሊቢያ አንፃራዊ መረጋጋት ሰፍኗል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የአረብ አብዮት ከቱኒዚያ ለጥቃ በሕዝባዊ አመጽ ሙባረክን ያወረደችው ግብጽ፣ ሁለተኛውን ዙር ሕዝባዊ አመጽ ጀምራለች፡፡
በስልጣን ላይ የሚገኘው ወታደራዊ መንግስት ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲቀርቡ የቆዩት ግብፃዊያን፤ ባጠናቀቅነው ወር የተጠናከረ ሕዝባዊ አመጽ አድርገዋል፡፡
በህዳር 18/2011 ዓ.ም በታህሪር አደባባይ የወጡ ተቃዋሚዎች ከፖሊሶች ጋር በፈጠሩት ግጭት 33 ሰዎች ሲሞቱ፣ 1700 ያህሉ ደግሞ ቆስለዋል፡፡ በርካታ ተቃዋሚዎች በፖሊሶች ከሚረጭ አስለቃሽ ጭስ ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል ጭንብል በማጥለቅ ድንጋይ ሲወረውሩም ተስተውሏል፡፡
በየካቲት ወር ሙባረክን ለማውረድ በተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ፣ በአብዛኛው ከፖሊሶች ጋር የጐላ ግጭት ያልተከሰተ ሲሆን፣ አሁን ግን ከባድ የከተማ ውጊያ በካይሮ ተደርጓል፡፡
ሙባረክ ከወረዱ በኋላ ስልጣን የያዘው የወታደራዊ ካውንስል አስተዳደር መሪ የሆኑት የ76 ዓመቱ ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴን ታንታዊ የሙባረክ ቀኝ እጅ ነበሩ፡፡
በሚያዚያ ወር መጀመሪያ ላይ መሀመድ ታንታዊ ከ2012 ዓ.ም በፊት ስልጣን እንደሚለቁ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ በመስከረም ይካሄዳል የተባለው ምርጫ ከተላለፈ በኋላ ግን እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆዩ ተጠቅሷል፡፡ ግብፃዊያን የሙባረክ አስተዳደር አካል እንደሆነ በመግለጽ የሚነቅፉት የመሀመድ ታንታዊ መንግስት፤ ሌላ አምባገነን መንግስት እንደሆነባቸው ይናገራሉ፡፡ የታይም መጽሔት ዘጋቢ አቢጌል ሃውስሎህነር፤ “The Revolution’s Second Act” በሚል ርዕስ ባቀረበችው ጽሑፉ፤ ካይሮ ከተማ በፖሊሶችና በተቃዋሚዎች መካከል በተካሄደ ግጭት የጦርነት አውድማ መስላለች ብላለች፡፡ አብዛኞቹ ሰልፈኞች “ፊልድ ማርሻል መሐመድ ሁሴን ታንታዊ ስልጣን ይልቀቁ” የሚል ጩኸት ያስተጋቡ ነበር፡፡ ሙስጠፋ አቡ ሁሴን የተባለ ወጣት ተቃዋሚ ሲናገር “ዘጠኝ ወር አለፈ፤ ነገር ግን ምንም የተደረገ ነገር የለም፡፡ መሐመድ ታንታዊ እስከ 2013 ዓ.ም በስልጣን እንደሚቆዩ ተገልጿል፡፡ ምናልባትም ራሳቸውን ቀጣዩ የግብጽ ፕሬዚዳንት አድርገው ሾመውም ይሆናል” ብሏል፡፡
ተቃዋሚዎች በህዳር 18/2011 ዓ.ም ያስነሱት ሕዝባዊ አመጽ መልኩን እየቀየረ እና እየተባባሰ ሲመጣ፣ ህዳር 22/2011 ዓ.ም ወታደራዊ ካውንስል ካቢኔውን እንደሚበትን ለተቃዋሚዎች አስታወቀ፡፡ በተጨማሪም እስከ 2013 ሳይሆን በ2012 አጋማሽ ድረስ ወታደራዊው ካውንስል ሥልጣን እንደሚለቅ ገለፀ፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ተቃዋሚዎች በተገባው ቃል መሰረት እንደሚፈፀም ሙሉ በሙሉ እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል በቀጣይ የሚካሄደው ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ስለመሆኑ አብዛኞቹ ግብፃዊያን ጥርጣሬ አላቸው፡፡ በግብጽ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት 10 ሚሊዮን የሚሆኑትን የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችንም ስጋት ላይ ጥሏል፡፡ በአገሪቱ የፖለቲካ የበላይነትን እያገኘ የመጣው የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ (Muslim Brotherhood’s freedom and Justice party) ምናልባት ስልጣን ከያዘ፣ በግብጽ ምንም አይነት የክርስትና እምነት እንዲኖር ስለማይሻ የኮፕት ኦርቶዶክሶች መጨነቃቸው አልቀረም፡፡
International Herald Tribune ጋዜጣ “Vote Galvani Zes Egypt’s Christians” በሚል ርዕስ ባቀረበው ዘገባ፣ የሙባረክ አስተዳደር ሃይማኖታዊ ያልሆነ መንግስት (Secular government) እንደነበረ አስታውሶ አክራሪ ሙስሊሞች የመደራጀት መብት አልነበራቸውም ብሏል፡፡ እንዲያውም አብዛኞቹ የሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ አባላት በሙባረክ ዘመን ታስረው እንደነበርም ይታወቃል፡፡
የሙስሊም ወንድማማቾች መስራች የነበረውና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአልቃይዳ መሪ የሆነው ዶክተር አይመን አልዛዋሃሪ፤ በሙባረክ አስተዳደር ወቅት በግብጽ አክራሪነት ለማስፈን ቢሞክርም መፈናፈኛ በማጣቱ አልቃይዳ ውስጥ ሊቀላቀል ችሏል፡፡
ዛሬ ግን ሃይማኖታዊ አክራሪነትን የሚያወግዘው የሙባረክ አገዛዝ ወርዷል፡፡ ከአክራሪነት ወደ አሸባሪነት የተቀየሩት እነ አይመን አልዛዋሃሪ በግብጽ ለመንቀሳቀስ መብት ባይኖራቸውም ሙስሊም ወንድማማቾች ግን ሰፊ ተቀባይነት አላቸው፡፡
ሙባረክን ለመጣል ሕዝባዊ አመጽ ያደረጉት አብዛኞቹ ወጣቶች የተማሩና ከዘመናዊ ዓለም ጋር ራሳቸውን ያቀራረቡ ቢሆንም የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄያቸው ምላሽ ካገኘ በኋላም ቢሆን፣ በግብጽ እስልምና የበላይነቱን እንዲቀዳጅ የሚፈልጉ ናቸው፡፡
ሙባረክን ለመጣል ሕዝባዊ አመጽ ከተነሣበት ከጥር 25 ጀምሮ እስካሁን ድረስ 100ሺህ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል፡፡ የተቀሩት ደግሞ በየጊዜው በቅዱስ ማርቆስ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመሰባሰብ ፀሎት ያደርጋሉ፡፡ አንድ ሃይማኖትን የሚያቀነቅን መንግስት በግብጽ ከተቋቋመ እጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ይወያያሉ፡፡
በጥር ወር ሊጠናቀቅ ይችላል ተብሎ በሚጠበቀው የፓርላማ ምርጫ ወደ 50 የሚጠጉ ፓርቲዎች ይወዳደራሉ፡፡ ሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲን ጨምሮ አብዛኞቹ የሙስሊም ፓርቲዎች ሲሆኑ፣ ጥቂት ዲሞክራቲክና የክርስትና ፓርቲዎችም አሉ፡፡ ከግብጽ ኮፕቶች እና ሙስሊሞች የተውጣጡ አባላት ያካተተው ሃይማኖታዊ ያልሆነው “The Egyptian Block” የተባለው ፓርቲም ይወዳደራል፡፡ ፓርትቲው የሶስት የተለያዩ ፓርቲዎች ውህደት ሲሆን “Neo-Liberal Free Egyptian” “The Socialist Gathering Party” እና “Egyptian Socialist Democrats” የተባሉት ናቸው፡፡ ይህ ፓርቲ ዲሞክራት ፓርቲ በመሆኑም በርካታ የግብጽ ኮፕቶች ሊመርጡት እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ባለፈው እሁድ በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን ለፀሎት ለተሰበሰቡት ምዕመናን ንግግር ያደረጉት የኮፕት ኦርቶሂክ ቄስ ይስሃቅ ሲናገሩ፣ “እኛ የኮፕት ኦርቶዶክሶች በጣም ጥቂት ቁጥር ያለን ነን፡፡ ቢሆንም ግን የመምረጥ መብታችንን ተጠቅመን እንመርጣለን፡፡ የምንመርጠውም “The Egyptian Bloc” የተባለውንና ሃይማኖታዊ ያልሆነውን ፓርቲ ነው፡፡ ይህ ፓርቲ ሙስሊም ወንድማማቾችንም ሆነ ማንኛውንም የእስልምና ፓርቲን ይቃወማል፡፡ በተጨማሪም በዲሞክራሲና በእኩልነት የሚያምን ፓርቲ ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ 85 ሚሊዮን ከሚጠጋው ሕዝብ ውስጥ 10 ሚሊዮን የሚጠጉት የኮፕት ኦርቶዶክስ መራጮች የመረጡት ፓርቲ ያሸንፋል ማለት ዘበት ነው፡፡ እንዲያውም እስካሁን በተካሄደው ምርጫ ለፓርቲዎች የተሰጠውን 2/3ኛው ወንበር የሙስሊም ወንድማማቾች 36% በማግኘት እየመራ ሲሆን፣ ሳላፊስት የተባለው ሌላው ሙስሊም ፓርቲ ደግሞ 24% አግኝቷል፡፡ በአጠቃላይ 42 መቀመጫዎችን እስካሁን ያገኙ ሲሆን፣ ለግለሰብ በተሰጠው መቀመጫ ደግሞ 52 ወንበሮችን ያገኙ የእስልምና ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው፡፡
በቀጣይ የሚመሰረተው ፓርላማ 508 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ 10 መቀመጫዎችን ፕሬዚዳንቱ የሚመርጠው ይሆናል፡፡ እስካሁን በአጠቃላይ 80% ያገኙት የእስልምና ፓርቲዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በሙባረክ አስተዳደር ወቅት የኮፕት ኦርቶዶክሶች ከ2% ያልበለጠ መቀመጫ የነበራቸው ቢሆንም፣ ነፃነትና የተረጋገ ሕይወት ግን ነበራቸው፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ግን የተቀየረ ይመስላል፡፡ በየጊዜው በሚከፈቱት አዳዲስ የቴሌቪዥን ቻናሎች የሚተላለፉት የእስልምና አስተምህሮ አክራሪነትን የሚያስፋፉ ሆነዋል፡፡ የ27 ዓመቷ የሂሳብ ባለሙያና የኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆነችው ሚና አብዱራህማን ስትናገር፤ “እኔ ሙስሊም ብሆን፣ በቴሌቪዥን የሚተላለፉት የእስልምና ትምህርቶች በክርስቲያኖች ላይ አመጽ እንዳነሣሣ ነው የሚያደርጉኝ” ብላለች፡፡ ሕፃናት ሳይቀሩ ፀረ-ኮፕት ኦርቶዶክስ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያበረታቱ ትምህርቶች ናቸው ብላለች፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በኮፕት ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችና በሙስሊሞች መካከል ግጭቶች መነሣታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በቅርቡም በአስዋን የሚገኘው የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተቃጥሏል፡፡
ከፖለቲካ ቀውስ በበለጠ ሃይማኖታዊ ግጭቶች እየተበራከቱባት የመጣችው ግብጽ፤ በጥር መጨረሻ ከሚጠናቀቀው የፓርላማ ምርጫ በኋላ አገሪቷ ወደ መረጋጋት ወይም ወደ ባሰ ግጭት ልታመራ እንደምትችል ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡ የሆነ ሆኖ አንድ ወር ከሶስት ሳምንት የቀረው ምርጫ ሲጠናቀቅ የሚሆነውን አብረን የምናየው ነው፡፡

 

Read 5210 times Last modified on Saturday, 10 December 2011 10:25