Saturday, 19 April 2014 12:27

ህፃናት ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸው ከሆነ እነዴት ማወቅ ይቻላል?

Written by  አበበ ተሻገር abepsy@yahoo.com
Rate this item
(3 votes)

በመጀመሪያ እነዚህን የሚከተሉትን አጫጭር ወሬዎች ልንገራችሁ፣
የአራተኛ ክፍል ተማሪና  የ10 ዓመት ልጅ ነው- ኳስ ይወዳል አግር ኳስ። ይህን የሚያውቅ የ 18 ዓመት ወጣት የሰፈሩ ልጅ ይህን ህፃን ምርጥ የአውሮፓ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ምስል የያዙ ስቲከሮችን በየጊዜው በመስጠትና በማታለል አስገድዶ ደፈረው። ህፃኑ አባቱ ጋራዥ የሚሰራ በአልኮል መጠጥ እለት አለት የሚደነዝዝ ሰው ሲሆን እናቱ ደግሞ የአእምሮ በሽተኛ በመሆኗ ቤቷ የማትውል ሰው ነች። ድርጊቱ አንዴ ከተጀመረ በኋላ ይህን ህፃን የሚረዳው ቤተሰብ በቅጡ ስለሌለውና ደፋሪውም ይህን ስለሚያውቅ በየጊዜው እያስፈራራ፣ እያስገደደ ቀጠለ። ህፃኑ ት/ቤት ይሄዳል ሆኖም መቀመጫው ላይ በሚሰማው ህመም ምክንያት መቀመጥ ያቅተዋል፤ ረብሻ የመሰላቸው መምህራን  ደግሞ አርፎ እንዲቀመጥ ያስገግዱታል። ትምህርቱን ተወው፣ እየቆየ አይነ ምድሩን መቆጣጠር አቃተው፣ መተኛት አይችልም፣ ቢተኛም በቅዠት ይባንናል፣ ይቀጥላል።
*******
ይችኛዋ የአራት አመት ህፃን ደግሞ ደፋሪዋ አባቷ ነው። ይህም የተፈፀመው በቤታቸው እናት ባለችበት ግን እንቅልፍ በጣላት ሰዓት ነው። መሃላቸው የምትተኛው ህፃን እናት እንቅልፍ ሲወስዳት ሰውየው (ከባህል አንፃር ልገልፃቸው በማልደፍራቸው መንገዶች) የተለያዩ የወሲብ ተግባራትን ይፈፅማል። ጉዳዩ በእናት በኩል ተደርሶበት ሰማንያቸው ተቀደደ።
*******
እናቷና አባቷ በሞት ከተለዩዋት በኋላ አዲስ አበባ የሚገኙ ዘመዶቿ እናስተምርሻለን ባሏት መሰረት ከጎጃም ተነስታ አዲስ አበባ ደረሰች፤ ያኔ እድሜዋ አስር ነው። “አንድ ክፉ ቀን” ትላለች ታሪኩን ስታስታውስ ያለሁባት ዘመዴ የባለቤቷ ወንድም ሊያገባ ለሰርግ ወደ ገጠር ተጠሩ ሆኖም ባለቤቷ የተለያዩ ምክንያቶችን አቅርቦ በወንድሙ ሠርግ ላይ እንደማይገኝ ገለፀ። ሚስቱ ወደ ሰርጉ በሄደችበት በዚያው እለት ምሽት የአስር አመቷን ህፃን አስገድዶ ደፈረ። ህፃኗ በዚህ ምክንያት ከበረገገች በኋላ ወደዛቤት አልተመለሰችም፡
*******
የ14 ዓመቷ ታዳጊ ደግሞ በተደጋጋሚ ራሷን የማጥፋት ሙከራ አድርጋለች። “ራሴን እጠላለሁ፣ በተደጋጋሚ አለቅሳለሁ፣ መተኛት አልችልም።” አባቷ ከሞተ በኋላ የሚኖሩት ከእናቷ ጋር ነው። እናቷ ኑሮአቸውን የሚደጉሙት እንጀራ በመሸጥና ልብስ በማጠብ ነው። ታዳጊዋ አልፎ አልፎ ቤተ ክርስቲያን ትሄዳለች፤ ዘወትር የምትሄደው ደግሞ ከሰዓት በኋላ ባለው ጊዜ ነው። “አንድ ቀን ትላለች በአጋጣሚ ከቤተክርስቲያን ስመለስ መሸ” ሆኖም መንገዷ ላይ የሚያውቃት የሰፈሯ አንድ ጎረምሳ አገኛትና አብረው ወደ ሰፈር መጓዝ ቀጠሉ። ለታዳጊዋ እሱን መንገዷ ላይ ማግኘቷ እረፍት ሰጥቷታል መንገዱን ፈርታ ስለነበር። ሆኖም በቀጣዩ ህይወቷ ላይ ፍርሃት እንዲነግስ ይኸው ጎረምሳ ምክንያት ሆነ። መንገዳቸው ላይ ባለ አንድ ካፌ (ሻይ ቤት ) “ሻይ ቡና እንድንል ጋበዘኝ (ድህነቴ መሰለኝ) እሺ አልኩት ለሁለታችንም ኮካ ኮላና ቦንቦሊኖ አዘዘ። ጠጣሁ በላሁ ሆኖም የጠጣሁት ኮካ ኮላ ረበሸኝ ከዛ በኋላም የሆነውን በውል አላውቅም። ከእንቅልፌ ስነቃ ግን ደም በደም ሆኛለሁ።
*******
“እናቴ ወደ አረብ ሃገር ስትሄድ እኔ የስምንት አመት ልጅ ነበርኩ” ትላለች ሌላዋ ታዳጊ። ቀጣዩ ህይወቷ ከአባቷ ጋር ብቻ ሆነ። ሆኖም አባቷ ልጄም ሚስቴም ነሽ በሚል እለት እለት መረጃውን ወደ ህሊናዋ እንዲሰርፅ አደረገ። በዚህ ሁኔታም ልጁን በተደጋጋሚ ይደፍራታል። በግቢው ውስጥ የሰውየው ወላጆችም ስለሚኖሩ በአንድና በሌላ ሁኔታ በምንም መንገድ የሚያደርገውን ነገር እንዳትናገር ያስፈራራታል፤ ከተናገረች እንደሚገድላትም ይነግራታል። ድርጊቱ በተደጋጋመ ቁጥር ግን ታዳጊዋ ህመሙን መቆጣጠር ያቅታታል፣ ለመጮህ ስትፈልግ አፏን ያፍናታል ማስፈራሪያውን ይቀጥላል። በመጨረሻ ህመሙን መሸከም ያቃታት ህፃን ለአያቷ (ለሰውየው እናት) ተናገረች፤ ከአባቷ ጋር ተፋታች።
*******
እነዚህንና ሌሎች በርካታ ታሪኮች የተፈፀሙት እዚህ አዲስ አበባ ነው። በተለያዩ ድርጅቶች ጥቃት ለደረሰባቸው ህፃናት የስነ ልቦናና የማህበራዊ ድጋፍ ይሰጣል። ታሪኮቹ በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን በማናገርና የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመቃኘት የተገኙ ናቸው (ይህ የሆነው በተለይ “psychological challenges of male and female children” በወንድና ሴቶች ህፃናት ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች የሚያደርሱት ሥነ ልቦናዊ ጫና - በሚል ርዕስ አጭር የቅኝት ጥናት ለማድረግ በሞከርኩበት ወቅት የተገኙ ናቸው።)
አሁን በውል በማላስታውሰው አንድ የሳይኮሎጂ መፅሃፍ ላይ ከልምድና ከቀላል እይታ በመነሳት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የየራሳችንን ግምትና መደምደሚያ እንወስዳለን። ሆኖም ይህ ግምታችን ጥናት ተደርጎ ውጤቱ ሲታይ ከግምታችን በተቃራኒ እናገኘዋለን። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥም ክስተት እንደሆነ ያወሳል። በህፃናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች የማይታወቁ፣ እንግዳና ዝምድና የሌላቸው ሰዎች ሊመስሉን ይችላሉ። ሆኖም ጥናቶች የሚያሳዩት ህፃናትን አስገድደው ከሚደፍሩ ሰዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ የቅርብ ሰዎች ናቸው። አባት፣ ጎረቤት፣ ዘመድ፣ መምህር፣ የት/ቤት ዘበኛ፣ የእንጀራ አባት ወዘተ ናቸው።
ወሲባዊ ጥቃት ፈፃሚዎች ህፃናትን ወደራሳቸው በመሳብና በማታለል፣ በማጫወትና በማስመሰል ጥበብ የተካኑ ናቸው። ህፃናቱን እንዴት ወደሚፈልጉት ጉድጓድ፣ አሳቻ ቦታና መረባቸው ማስገባት እንደሚችሉ ያቃሉ፤  ደግሞም ይሳካላቸዋል። የሚሳካላቸው ህፃናቶቹ ከእነሱ በጣም ያነሱ፣ በአካልም በአእምሮም ያልበሰሉ፣ ሁሉንም ነገር በመልካም ጎኑ ብቻ የሚመለከቱ በመሆናቸውና አንዳንድ መረጃ ያላቸውና ብልህ ህፃናት ሲሆኑ ደግሞ ጉልበት ስለሚጠቀሙ ነው(በነገራችን ላይ ወሲባዊ ጥቃት ስንል የግድ የአካል ተራክቦን ወይንም ወሲባዊ ግንኙነትን ብቻ የሚመለከት አድርጎ የሚወሰድ አይደለም። በተለይ በህፃናት ላይ የሚደርስ ጥቃት አግባብ በሌለው መንገድ ወይም ደፋሪው ከራሱ ጋር ምክር መክሮ፣ አንዳች እኩይ ጥንስስ(motive) አምቆ ወይም ይዞ ህፃናትን ማታለል፣ መደባበስ፣ መራቢያ አካላቸውን በማኛውም መንገድ መንካት፣ ለህፃናቱ ወሲብ ነክ ስእሎቸን ወይም ቪድዮዎችን ማሳየት፣ እርቃንን ማሳየት ወይም እርቃናቸውን በክፋት መመልከት፣ ወሲብ ነክ ቃላትን መወርወርና መገፋፋት እነዚህን ሁሉ የጥቃቱ አካልና ወደሚፈለገው ወሲባዊ ጥቃት የሚወስዱ መረማመጃ ናቸው።)
ህፃናት አንዴ መሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ በአመዛኙ መረጃውን ላያወጡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ከደፋሪው ማስፈራሪያ ጋር በተያያዘ ወይም ወላጆችን በመፍራት ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ምንም ያህል አምቀው ይያዙት እንጂ በባህሪያቸው ላይ ለውጦችን ማሳየታቸውና ከሥነ ልቦና መታወክ ሊያመልጡ አይችሉም። ወሲባዊ ጥቃት በየትኛውም የእድሜ ደረጃ እጅግ ህፃናት በምንላቸው ሁሉ ሊፈፀም ይችላል (ህፃናቶች አያስታውሱም በምንልበት እድሜ ደረጃም ሁሉ ቢፈፀም) አንጎል ክስተቱን ይመዘግባል። የመዘገበውን ደግሞ ጠብቆ ያስቀምጣል። ልጆቹ እያደጉ ሲሄዱ ምን እንደተከሰተ አይወቁ ወይም አያስታውሱት እንጂ የስነ ልቦና ጫናዎቹ ወይም የባህሪ ችግሮቹ ይንፀባረቃሉ (የበሽተኛው ህመም ይታወቃል መንስኤውን ግን መለየት ያስቸግራል) የሰው ማንነት ቅርፅ የሚይዘው በልጅነት ወቅት በሚፈፀሙ ጉዳዮችና ሊኖረን ከሞችለው የአስተዳደግ ዘዬ አንፃር ነው። ስለዚህ በልጅነት የወሲብ ጥቃት የተፈፀመባት ወይም የተፈፀመበት ሰው የሥነ ልቦና እርዳታ ካላገኘ ማንነቱ(ቷ) ላይ አሉታዊ ጫና ይኖረዋል።
ብዙ ጊዜ ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት የእንቅልፍ ማጣት፣ የድብርት፣ የጭንቀት፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ፍርሃት፣ ቁጣ፣ የመማር አቅም (ፍላጎት) መቀነስና ማጣት፣ ስሜቶች ይንፀባረቃሉ። ከወሲብ ጋር ለተገናኙ ነገሮች ባልተለመደ ሁኔታ መመሰጥ ወይም ርዕሰ ጉዳዩን መጥላት፣ ጉዳዩ ሲነሳ መፍራት ክስተቶች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ከጓደኛና ቤተሰብ ራስን ማግለል፣ ሰውነታቸው እንደቆሸሸ ማሰብ (መፀየፍ)፣ መጥላት፣ አንዳች የጎደለ ነገር እንዳለ ማሰብ፣ ከዘወትር ተግባር መቆጠብ፣ መነጫነጭና መቆጣት፣ ድብቅ መሆን፣ ምናልባም ደግሞ ራስን የማጥፋት ሙከራ ማድረግ ሊከሰት ይችላል(እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚሻው ጉዳይ ራሱን ለማጥፋት ሙከራ የሚያደርግ ሰው እርዳታ ካላገኘ ጊዜው ይጠርም ይርዘም ራሱን ሊያጠፋ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።) ወደ ኋለኛው እድሜያቸው ደግሞ ሁሉንም ተቃራኒ ፆታ ያለማመን፣ የወሲብ ፍላጎት ማጣት ወይም መፍራት፣ ድርጊቱ በተደጋጋሚ በተፈፀመባቸው ላይ በራስ የመተማመን ሁኔታ አለመኖር፣ የማልረባ ዋጋ ቢስ ነኝ በሚል ስሜት መዋጥ፣ ለወሲባዊ ግንኙነት የተዛባ አመለካከት የመውሰድ ሁኔታዎች ይታያሉ።
እነዚህ ምልክቶችና የስነ ልቦና ጫናዎች ጥቃት በደረሰባቸው ህፃናት ሁሉ ሁሉም ይታያሉ ማለት አይደለም እንደተፈፀመው የድርጊት ክብደትና ደረጃ ድግግሞሽና እንደፈፃሚው ግለሰብ የስነ ልቦና መታወኩ ሊለያይ ይችላል።
በከተማችን በህፃናት ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች  የሚፈፀሙትን ያህል አይደለም ወደ ጆሮአችን የሚደርሱት። ምክንያቶቹ ግልፅ ናቸው፤ ተከትሎ የሚመጣውን ችግር ከመፍራት ለምሳሌ የደፋሪውን ዛቻ፣ ከሃፍረትና መሳቀቅ ጋር ይያያዛል። ስለዚህ ህፃናቱን ማስተዋልና የባህሪ ለውጦቻቸውን የተገነዘበ ሰው ችግሩን መፈተሽ ተገቢ ይሆናል። እነዚህን ህፃናት ደግሞ ወደ ስነ ልቦና ባለሙያዎች ማድረስ ከተቻለ የመፍትሄዎቹ መንገዶች የተወሳሰቡ አይደሉም። ወሲባዊ ጥቃት በአካልና ጤና ላይ የሚያደርሰው ችግር ምናልባት ወዲያው ወይም በሳምንታት ይታከማል በስነ ልቦና ላይ የሚያደርሰው ችግር ግን ከአካላዊው ጠባሳ የከፋና ከፍ ያለ ስለሆነ ሂደቱ ቀላል ላይሆን ይችላል። ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናት ለስነልቦና ችግር እንደሚዳረጉ ሁሉ ጥቃቱን ያደረሰው ሰው ደግሞ መጀመሪያም ጤናማ አእምሮ የያዘ አይደለም ያም ሆኖ እነዚህም እርዳታ የሚያሻቸው ናቸው። ለንባባችሁ ምቾት ከሰጣችሁ ፀሀፊው ከጋዜጠኝነት ሞያው በተጨማሪ የስነልቦና ባለሞያ በመሆኑ መረጃዎቹ ከታማኝ ምንጭ እንደወጡ መረዳት ይቻላል።
መልካም የትንሳኤ በዓል!!!

Read 6533 times