Saturday, 19 April 2014 12:21

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ፍለጋ ክሽፈት በዝቶበታል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

       የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር በተከተለው የአሰራር ሂደት 3 ወራት ቢያስቆጥርም ተደጋጋሚ ክሽፈት እየገጠመው መሆኑ የስፖርት ቤተሰቡን አሳሰበ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በመጨረሻ እጩነት ከቀረቡት አራት አሰልጣኞች እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፖርቱጋላዊውን ማርዮ ባሬቶ እንደመረጠ በመገናኛ ብዙሃናት ከተገለፀ በኋላ መረጃው ሃሰተኛ ነው ተብሎ በማግስቱ ማስተባበያ ተሰጠ። ሰሞኑን ደግሞ  ፌደሬሽኑ በመጨረሻ እጩነት ከያዛቸው አሰልጣኞች አንደኛ እጩ የነበሩትን  ጎራን ‹ፕላቪ› ስቴፋኖቪች ለመቅጠር ከጫፍ መድረሱን በመግለፅ ሰርቢያዊው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አዲስ አበባ ገብተው የመጨረሻውን ድርድር እንዲያደርጉ ጋብዞ ስምምነት ላይ አለመደረሱን  በመግለጫው አስታውቋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የማሰልጠን ልምድ ያለው አሰልጣኝ ለመቅጠር ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን የሚገልፀው ፌደሬሽኑ የሁለቱ አሰልጣኞች የቅጥር ሂደት ከከሸፈበት በኋላ አስቀድሞ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተጠባባቂነት ከተያዙት  አሰልጣኞች ጋር በፍጥነት ድርድር እንደሚካሄድ   አስታውቋል። ስለዚህም ትኩረቱ በ3ኛ ደረጃ ወደተቀመጡት ፓርቱጋላዊው ዞራን ፍሊፖቪች እና በአራተኛ ደረጃ ወደ ተያዙት ስዊድናዊው ላርስ ኦሎፍ ማትሰን ሆኗል።    
በአሰልጣኙ  ቅጥር ዙርያ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ አንዳንድ የስራ አስፈፃሚ እና የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በተናጠል በተለያዩ ሚዲያዎች ከሚሰጧቸው ማብራርያዎች ባሻገር ሁሉንም የሚዲያ አካላት በመጥራት ይፋ መግለጫ አለመሰጠቱ  የቅጥር ሂደቱን ግልፅነት የተሳነውና ግራ አጋቢ ሲያደርገው፤  ፌደሬሽኑ በህዝብ ግንኙነቱ አማካኝነት መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃናት በኢ-ሜይል መልእክት ብቻ  ማሰራጨቱ ትክክለኛ እና አሳማኝ መረጃ እንዳይገኝ ምክንያት ሆኗል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚረከበው አዲሱ አሰልጣኝ መቼ ተቀጥሮ በይፋ   ስራውን እንደሚጀምር ፤  በቅጥሩ  ውል ከአዲሱ አሰልጣኝ ምን ውጤት እንደሚጠበቅና በሃላፊነቱ ለምን ያህል ግዜ  እንደሚቆይ፤ ምን ያህል ወርሃዊ ደሞዝ እንደሚከፈልና እንዴት እንደሚከፈል በግልፅ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።
በአንዳንድ ዘገባዎች  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በውጭ አሰልጣኝ ቅጥር በዓመት እስከ 10 ሚሊዮን ብር ሊያስፈልገው እንደሚችል የተገመተ ሲሆን ከሳምንት በፊት ይህን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት  የአሰልጣኙን ወርሀዊ ክፍያ ከፌዴሬሽኑ ውጪ የሚሸከመው ማንም የለም ብለው እንደ አማራጭ ስፖንሰር የሚደርጉንን ድርጅቶች ስላሉ በስፖንሰር አልያም ደግሞ የባለሀብቶች ድጋፍ ልንወጣው እናስባለን  ብለዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲሱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ መታወቃቸው ግድ የሆነ ይመስላል። በ2015 እኤአ ሞሮኮ ለምታስተናግደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሚደረገው የምድብ ማጣርያ ከሳምንት በኋላ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ  በካይሮ በሚካሄድ ስነስርዓት የምድብ ድልድል ማውጣቱ ዋናው ምክንያት ነው።   ብሄራዊ ቡድኑ ያለ አሰልጣኝ ለ3 ወራት መቆየቱ ከዚሁ የምድብ ማጣርያ  በፊት ሊኖር የሚገባውን ዝግጅት እንዳያስተጓጉል ስጋትም ተፈጥሯል።
የመጨረሻዎቹ እጩዎች ከታወቁ በኋላ…
ፌደሬሽኑ ካወጣው የቅጥር ማስታወቂያ በኋላ  27 አሰልጣኞች  ማመልከታቸው የሚታወስ ሲሆን በቴክኒክ እና ብሄራዊ ልማት ኮሚቴ አወዳዳሪነት ከመካከላቸው አምስት የመጨረሻ እጩዎችን በደረጃ ተለይተው ከታወቁበት ካለፉት ሶስት ሳምንታት ወዲህ የስፖርት ቤተሰቡንና መገናኛ ብዙሃናት በሚያደናግሩ ሁኔታዎች ቅጥሩ አነጋጋሪ ሆኗል። በመጨረሻ እጩነት ከቀረቡ 5 አሰልጣኞች አንዱ ሆነው ገና ሳይወዳደሩ ተቀንሰው በሌላ የተተተኩት  ሆላንዳዊውን  ጆ ቦናፍሬ ነበሩ። ከናይጄርያ ብሄራዊ ቡድን ጋር የኦሎምፒክ ሜዳልያ ያገኙት እኝህ አሰልጣኝ ሊቀነሱ የበቁት በእድሜያቸው አንጋፋነት ነው። በምትካቸው ከመጨረሻዎቹ እጩዎች ተርታ  ስዊዲናዊው ላርስ ኦሎፍ ማትሰን ገብተዋል።፡ ከቦናፍሬ በመቀጠል ከመጨረሻ እጩዎች ውጭ የተደረጉት ሌላው አሰልጣኝ ደግሞ   ዲያጎ ጋርዚያቶ ሲሆኑ አስቀድመው ብሄራዊ ቡድኑን በማሰልጠናቸው ለድጋሚ ቅጥር ባለመፈለጋቸው ተቀንሰዋል። ቦናፍሬ እና ጋርዚያቶ በመጨረሻው ሰዓት ከ5ቱ እጩዎች ተርታ ውጭ ከሆኑ በኋላ ሰርቢያዊው ጎራን ስቴፋኖቪች፤ ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቶ፤ ስዊድናዊው ላርስ ኦሎፍ ማትሰን እና ፖርቱጋላዊው  ዞራን ፍሊፖቪች ምርጫውን በማከናወን ላይ በሚገኘው የፌደሬሽኑ የቴክኒክ እና የልማት ኮሚቴ አማካኝነት በየደረጃቸው ለመጨረሻ ድርድር ቀረቡ። ከዚህ በኋላ  ኮሚቴው ባወጣቸው የተለያዩ የመምረጫ መስፈርቶች መሠረት  ከአራቱ አሰልጣኞች ጋር የቀጥታ ግንኙነት በማድረግ በደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ጉዳዮች ዙሪያ ድርድሩን ከተጀመረ ሁለት ሳምንት አለፈ። ከእነዚህ እጩዎች መካከል ሳይጠበቅ በሁለተኛ ደረጃ የነበሩት ፖርቱጋላዊው ማርያኖ ባሬቲ ተመረጡ የሚል ዘገባ ተናፈሰ። ይሁንና ስለእኝህ አሰልጣኝ ከጋና እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከጋዜጠኞች በደረሰ መረጃ ከመጨረሻዎቹ እጩዎች ተርታ ውድቅ መደረጋቸውን ገልፆ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የወጡ መረጃዎችን ያስተባበለው በማግስቱ ነበር። በወቅቱ በሱፕር ስፖርት ዘገባ እንደተገለፀው ግን ማርያኖ ባሬቶ ጋር ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ያልተግባቡት ከክፍያ በተያያዘ እንደሆነ ተጠቅሶ በምርጫው ሌላው ፖርቱጋላዊ ዞራን ፍሊፖቪች እንዲሾሙ ተመክሯል።
የጎራን ቅጥር ለምን ከሸፈ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለመጨረሻው ምርጫ ካሳለፋቸው አራት እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የመጀመሪያ ደረጃ ከተሰጣቸውና በዜግነት ሰርቢያዊ ከሆኑት ሚስተር ጐራን ስቴቫኖቪች ጋር ላለፋት ሁለት ሳምንት በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ድርድሮች ሲያካሂድ ነበር።
በስልክና በሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ቀደም ብሎ ሲካሄድ የቆየውን ድርድር መሠረት  በማድረግም አሰልጣኙ  ወደ አዲስ አበባ መጥተው በአካል የተሟላ ድርድር ለማካሄድ ፈቃደኝነታቸውን በማሳየታቸው ፌዴሬሽኑ ይፋዊ ጥሪ በደብዳቤ አድርጐላቸው ጎራን ጥሪውን በመቀበል ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ገብተው ከፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ጥልቅና ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን የህዝብ ግንኙነቱ መግለጫ ያትታል።
ድርድሩ በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማተኮሩን የጠቀሰው መግለጫው በመጀመሪያው ነጥብ የደሞዝ ድርድር ላይ መቀራረብ ቢቻልም ጎራን ስቴፋኖቪች   ባነሷቸው ሁለት ነጥቦች ዙሪያ ስምምነት ላይ ባለመደረሱ ምክንያት ድርድሩን መቋረጡን አመልክቷል። ፌዴሬሽኑንና ጎራን ስቴፋኖቪችን ያላስማማው አሰልጣኞች ከቤልግሬድና ከግሪክ እንዲመጡላቸው መጠየቃቸውና በተጨማሪ የቤተሰብ ችግር እንዳለባቸው በመጥቀስ ሙሉ ጊዜያቸውን አዲስ አበባ በማድረግ መስራት እንደሚቸገሩ በማመልከት ከአዲስ አበባ ቤልግሬድ እየተመላለስኩ ልስራ ማለታቸው ነው። በተለይ የረዳት አሰልጣኞች ምርጫ በአሰልጣኙ ፍላጐት የሚወሰን ቢሆንም ሁሉንም አሰልጣኞች ከውጭ መምረጥ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር ለማድረግና የአሠራር ለውጥ ለማምጣት ከታሰበው እቅድ ጋር የሚቃረን ነው በሚል አቋሙ ፌዴሬሽኑ የጎራንን ጥያቄ ሳይቀበለው መቅረቱ በመግለጫው ተብራርቷል።  በተያያዘ  ጎራን ስቴፋኖቪች ዋልያዎችን ለማሰልጠን  እስከ 25ሺ ዶላር በወር እንዲከፈላቸው  መስማማታቸውን የገለፀው የሱፕር ስፖርት ዘገባ  ሲሆን በድርድራቸው  ወቅት ከግሪክ እና ከቤልግሬድ ይምጡ ላሏቸው ሁለት ረዳት አሰልጣኞች ለእያንዳንዳቸው 10ሺ ዶላር ክፍያ መጠየቃቸውን ጨምሮ አውስቷል።
ቀሪዎቹ እጩዎች ማትሰንና ፍሊፖቪች
 የመጀመርያ ምርጫ ከነበሩት  ሰርቢያዊው ጎራን ስቴፋኖቪች  በኋላ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በአሰልጣኙ ቅጥር የቀሩት ሁለት እጩዎች የ69 ዓመቱ ፖርቱጋላዊ አሰልጣኝ ዞራን ፍሊፖቪች እና የ59 ዓመቱ ስዊድናዊ አሰልጣኝ ላርስ ኦሎፍ ማትሰን  ናቸው።  ለዋልያዎቹ ሃላፊነት በሶስተኛ ደረጃ እጩ የሆኑት ላርስ ኦሎፍ ማትሰን በስዊድንና በኖርዌይ ያሉ ትልልቅ ክለቦችን በማሰልጠን ከፍተኛ የሙያ ልምድ ያካበቱ ሲሆን የስዊድን ሀ-21 ቡድን በመምራት እና ከዚያም በ2010 እኤአ ላይ ደግሞ በሲሪላንካ ብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝነት በመቀጠር ለ2 ዓመት ሰርተዋል። በሌላ በኩል በእጩነት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፖርቱጋላዊው ዞራን ፍሊፖቪች በአሰልጣኝነት ስራ የጀመሩት በ1988 እ.ኤ.አ  ሲሆን ለ2 ዓመት የፖርቱጋሉ ትልቅ ክለብ ቤነፊካ አሰልጣኝ ሆነው ከመስራታቸው በላይ በ1999 እኤአ በጣሊያኑ ክለብ ሳምፕዶርያም አገልግለዋል። ከዚያም ተጫውተው ወዳሳለፉበት ታዋቂው ክለብ ስታር ቤልግሬድ በመመለስ ለ3 ዓመት በአሰልጣኝነት አገልግለው በ2007 እ.ኤ.አ  የሞንቴኔግሮ ቡድንን በመምራት  ለ2 ዓመት አገልገለው ከዚያ ወዲህ  ስራፈት ሆነው ቆይተዋል። ዞራን ፍሊፖቪች በዜግነታቸው ፖርቱጋላዊ ቢባሉ የሞንቴኔግሮ ዜግነት እንዳላቸው ያመለከቱ መረጃዎችም አሉ።
ሰውነት ዝምታን መርጠዋል፤ ይመለሱ እንዴ?
የእግር ኳስ ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን  ባለፈው 2 ዓመት ከ6 ወር በዋና አሰልጣኝነት የመሩትን ሰውነት ቢሻው  በተሻለ ለመተካትና ለውጥ ለመፍጠር በሚል ካሰናበተ 3 ወራት አልፈዋል። በዋና አሰልጣኝነት ምትክ ሆነው ለመቀጠር ማመልከቻ ያስገቡት 27 አሰልጣኞች በስራ ልምዳቸው አይሻሉም እና የፌደሬሽኑ የቅጥር ሂደት ስኬታማ አይደለም የሚል ምክንያቶችን የሚያቀርቡ የስፖርት ቤተሰቦች በኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች ሰውነት ቢሻው ይመለሱ እያሉ ናቸው።
በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን  ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈ፤ ለ20ኛው ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ለሚደረገው የመጨረሻ ማጣርያ ምእራፍ ለመገባት ከበቁ 10 የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ ለመሆን የበቃ፤ በአፍሪካ አገራት ሻምፒዮንሺፕ ወይም ቻን ውድድር በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈ፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ከዓመቱ ምርጥ ሶስት ብሄራዊ ቡድኖች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። አሰልጣኝ ሰውነት በአሁኑ ጊዜ የእረፍት ጊዜያቸውን ከቤተሰባቸው ጋር እያጣጣሙ ሲሆን በመላው አገሪቱ በመዘዋወር የነበራቸውን ታሪካዊ ተሞክሮ በክብር እንግድነት እያቀረቡ ቆይተዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት ደግሞ በጋና የሚገኝ ራይት ቱ ድሪም የተባለ አካዳሚን ጎብኝተዋል። የጋናውን ክለብ ሃርትስ ኦፍ ኦክ ለማሰልጠን እየተደራደሩ መሆናቸውም በዚያው ሰሞን ተነግሮ ነበር።አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በጋና ቆይታቸው:- “ በእርግጠኝነት የኮትዲቭዋር ብሔራዊ ቡድን በዘንድሮው የአለም ዋንጫ ላይ አፍሪካን የሚያኮራ ውጤት ያስመዘግባል”  የሚል አስተያየት እንደተናገሩም ተዘግቧል።  

Read 2732 times